የነ አቶ አንዱዓለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ክስ ውሳኔ በድጋሚ ተቀጠረ
በእነ አንዱዓለም አራጌ የክስ መዝገብ ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቁት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ እንዲሁም እውቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም፣አቶ ዮሐንስ ተረፈ፣አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ እና አቶ ምትኩ ዳምጤ ውሳኔ ለዛሬ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ተቀጥሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ 6 ኪሎ የሚገኘው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኙን የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም ውሳኔውን ሳይሰጥ ለአምስተኛ ጊዜ ለሚያዚያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ተቀጠረ፡፡
ፍርድ ቤቱም ውሳኔውን ሊሰጥ ያልቻለበትን ምክንያት ሲገልፅ የክሱን ሂደት ገና መርምሬ አልጨረስኩም በሚል ተጨማሪ ቀነ ቀጠሮ መስጠቱን አስታውቋል፡፡ በወቅቱ የፍርድ ቤቱ ዳኞች ሽመክት አሰፋ፣ በላቸው አንሺሶ እና ዳኜ መላኩ ተሰይመው ሲሆን ከከሳሽ በኩል አቃቤ ህግ ብርሃኑ ወንድማገኝ እንዲሁም ከተከላካይ ጠበቆች አቶ አበበ ጉታ፣ አቶ ደርበው ተመስገን እና አቶ ሳሙኤል አሰፋ ተገኝተዋል፡፡ ተከሳሾችም በሰዓቱ የቀረቡ ቢሆንም የነበረው በበርካታ ያልተለመደ የጦር መሳሪያ አጀብ አዲስ ያልተለመደ ክስተት ቢሆንም በተለይ የአቶ አንዱዓለም አራጌ በከፍተኛ ደረጃ መጎሳቆል የችሎት ታዳሚዎችን ሐዘን ውስጥ ከቶ ተከሳሾቹ የውሳኔ ፍርዱ ሳይሰጥ ከቀኑ 6፡30 ሰዓት ወደ የመጡበት እስር ቤት ተመልሰዋል፡፡