የሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ንብረት እያወዛገበ ነው

1ሚ. ብር አበድሬአቸዋለሁ የሚል ድርጅት ክስ ሊመሰርት ነው የአዋሣው ቤታቸው ተሸጦ ስም መዛወሩ እያነጋገረ ነው

Afewerk

እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ንብረት እያወዛገበ ነው፡፡ አርቲስቱ በሕይወት ሳሉ አንድ ሚሊዮን ብር አበድሬአቸዋለሁ የሚል ድርጅት ለክስ ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱን ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ሎሬት አፈወርቅ በህይወት ሳሉ የስዕል ሥራዎቻቸውን፣ ቪላ አልፋንና ሙሉ ንብረታቸውን ለመንግስት ማውረሳቸውን ተከትሎ፣ መንግስት ንብረቱን ለመረከብ እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የእኚሁን ታላቅ አርቲስት ንብረት ለማጣራትና ለመመዝገብም ከፍርድ ቤት፣ ከታዋቂ ሰዎችና ከሙያ ባልደረቦች የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ ምዝገባና ቆጠራ ቢጀመርም ፍፃሜ ሣያገኝ ተቋርጧል፡፡ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ በህይወት ሣሉ የአክሲዮን ባለ መብት ለመሆን አንድ ሚሊዮን ብር ወስደዋል በሚል የአርቲስቱን ስዕሎች ይሸጥ በነበረ አንድ የማስታወቂያ ድርጅት ክስ ሊመሰረት መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ጉዳዩ በፍርድ ቤት እልባት እንዲያገኝ ለኮልፌ ምድብ ችሎት ተመርቶ እየታየ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ ለጊዜው የንብረት ምዝገባና ቆጠራው መቋረጡን ገልፀዋል፡፡ በአዋሣ ከተማ የሚገኘውና በሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ስም የተመዘገበው ቤት በቀድሞ ባለቤታቸው አማካኝነት መሸጡን የጠቆሙት ምንጮች፤ የቤቱ ስም የተዛወረበት አሠራር ሕጋዊነት አነጋጋሪ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡ በሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ስም በለንደንና በስኮትላንድ ባንኮች ያለ ገንዘብ እንዲመለስ ጥረት እየተደረገ ሲሆን በተለያዩ አገራት ያሉ ስዕሎችና ንብረቶችን ለማስመለስም እየተሞከረ ነው ተብሏል፡፡ የአርቲስቱ ንብረት ካለባቸው አገራት መካከልም ንብረቱንና ገንዘባቸውን ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑና በመመለስ ሂደት ላይ የሚገኙ እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡

የሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ቪላ አልፋ፤ በኮሚቴዎቹ ሲከፈት በሺዎች የሚቆጠር ፓውንድ በካዝናቸው ውስጥ መገኘቱንና ይህም በንብረት ዝርዝር ላይ ተመዝግቦ መያዙን ምንጮች ገልፀዋል፡፡ በፍርድ ቤት ጉዳይ የተቋረጠው የሎሬት አፈወርቅ ንብረት ቆጠራና ርክክብ መዘግየት በንብረቱ ላይ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል የጠቆሙት ምንጮች፤ እጅግ ውድ ዋጋ ያላቸው

ስዕሎቻቸውና የአርቲስቱ የመኖሪያ ቤትና የስዕል ስቱዲዮ የሆነው ቪላ አልፋም የመበላሸት አደጋ አንዣቦበታል ብለዋል፡፡ የሎሬት አፈወርቅ ተክሌ የቀብር ሥፍራ ምንም አይነት የማስታወሻ ሐውልት ሣይሰራበት መቅረቱን የጠቀሱት ምንጮች፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የቀብራቸው ሥፍራ ሊጠፋ ይችላል የሚል ሥጋት መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡

Written by መታሰቢያ ካሣዬ- http://www.addisadmassnews.com/

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: