በሳውዲ በተከሰው አደጋ ከ13 በላይ ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ተገለፀ
ነብዩ ሲራክ
(ከሳውዲ ዓረቢያ)
መስከረም 13 ቀን 2008 ዓ.ም. የሐጅ ሥነ ሥርዓት ተከትሎ ሰይጣንን በድንጋይ በሚመታበት ክንዋኔ ምሳሌ፤በጀማራት ድልድይ በሚወስደው መንገድ በሀጅ ተጓዦች መካከል በመጨረሻው ሰዓት በተፈጠረ ግፊያና መጨናነቅ በተከሰተ አደጋ የሟ ቾች ቁጥር ወደ 1,100 ከፍ ያለ ሲሆን የቆሰሉት ቁጥርም ከፍተኛ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከደረሰው አደጋ ውስጥ እስካሁን ከ13 በላይ ኢትዮጵያውያን ሲሞቱ ከ26 በላይ መቁሰላቸውን እና ከ204 በላይ መጥፋታቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ለሒጅ ፀሎት ስነስርዓት የተጓዙ ኢትዮጵያውያንም 8 ሺህ ያህል እንደነበሩ ተጠቁሟል፡፡
ባለፈው ጳጉሜ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በመካ ሳውዲ ዓረቢያ በደረሰው የክሬን መውደቅ አደጋ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ ለሐጂና ፀሎት ስነስርዓት ወደስፍራው ባቀኑ ሀጃጆች ላይ ከህይወት መጥፋት እስከ አካል ማጉደል አደጋ ማድረሱ አይዘነጋም፡፡ በተለይ የመስከረም 13 ቱን አደጋ በተመለከተ ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡
ኢትዮጵያ…
* ኢትዮጵያ 13 በላይ ሞተውባታል ፣ 26 ቆስለውባታል
ከ204 በላይ ጠፍተውባታል ፣ ፍለጋው ቀጥሏል
* ጅዳ ከተላለፉት ቁስለኞች ኢትዮጵያዊ የለም
* ጅዳ ማህጀር የተላለፈው ሬሳ ማንነት ገና አልተጣራም
* ከማህጀሩ ሬሳ የአፍሪካውያን አለበት ተብሏል
* ኢትዮጵያውያን መካ ላይ ለፍለጋው በግል ተደራጅተዋል
* ማፈላለጉን በሁሉም ሆስፒታሎች መከዎን ገዷቸዋል
* ቤተሰብ ወይም የኢንባሲ ውክልና አምጡ ተብለዋል
* በመካው ክሬን የተጎዳች ኢትዮጵያዊት ሀጃጅ ተገኘች
* ኢትዮጵያቷ ሀጃጅ እስከዛሬ አልታወቀችም ነበር
* ልክ የዛሬ ሳምንት መሞቷ ተጠቁሟል
ህንድና ፖኪስታን …
* በማፈላልጉ የሳውዲ መንግስት አፋጣኝ እርዳታ ተጠየቀ
* የህንድን ፖኪስታን ቆንስሎች መግለጫ ሰጥተዋል
* ህንድ 46 ሞቶባታል 62 ቆስለዋል 82 ጠፍተውባታል
* ፖኪስታን 46 ሞተውባታል ፣ 8 ቆስለዋል 42 ጠፍተውባታል
የጠፉትን ፍለጋና ጭንቅ ድካሙ
ተቀማጭነታቸውን ሳውዲ ያደረጉ ፣ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ፣ በሀጅ ጸሎት ከአደጋው የተረፉ ሀጃጆችና ቤተሰቦቻቸው በሚና ጀማራት አደጋ የጠፉና የሞቱትን ሰዎች ለማፈላለግ ሌት ከቀን ወደ ሚና ፣ ጀማራትና መካ በመመላለስ አድካሚ የጭንቅ ሳምንት መግፋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው። የጠፉ ሃጅ ቤተሰቦች በግሩኘና በተናጠል ቢያፈላልጉም በርካታዎች እንዳልተሳካላቸው ይናገራሉ ። በአደጋው የሞቱ ኢትዮጵያውያን ቁጠር ገና ከአደጋ ቀን አንስቶ ከአምስት በላይ መሆኑ ግልጽ እያለ በኢትዮጵያ ኢንባሲ ፣ ቆንስልና የሀጅ ኮሚቴ የሚደረገው ፍለጋ የተቀናጀ ባለመሆኑ ዝርዝር መረጃው ቀርቶ የሞቱና የቆሰሉትን ዙሪያ ትክክለኛ መረጃ አልቀረበም ነበር ። ከብዙ ጉትጎታ በኋላም ትክክለኛውን መረጃ ለህዝብ ለማድረስ በርካታ ቀናት ወስዷል።
አሁንም በኢትዮጵያ ተወካዮች በኩል ቀናት የወሰደው የሞቱና የቆሰሉትን የማሳወቅ መረጃ ቅበላ ከቀናት በፊት ይፋ ቢደረግም አሁንም ቁጥሩ እየጨመረ ከመጣው የሟቾቸ ብዛት አንጻር የመረጃ ክምችቱን የማሻሻል ስራ እየተሰራ አይደለም በሚል ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ የመካና ጅዳ ነዋሪዎች ገልጸውልኛል፡፡
ኢትዮጵያን ወጣቶች በመካ ሚናው ፍለጋ
የሀጅ ኮሚቴ አካሄድ አዝጋሚ መሆን ያሳሰባቸው በመካ ዙሪያ የሚገኙ ወጣቶች ራሳቸውን በማደራጀት መካ ላይ በሚገኙ በ13 ሆስፒታሎች በአደጋው የተጎዱትን ለማግኘት ፍለጋ ጀምረዋል ። በትናንሽ ሆስፒታሎች ችግር ባይገጣማቸውም መሊክ ፈይሰል ፣ ሄራ ፣ ጀበለር ኑርና መሊክ አብደላ በተባሉ ትላልቅ ሆስፒታሎች እንዳይገቡ ተከልክለዋል ። ያም ቢሆን በቀሩት አንዳንድ ሆስፒታሎች ማፈላለጉን በተወሰነ መልኩ በማሳለጥ 15 ያህል ቁስለኞችን ማግኘታቸውን ጠቁመውኛል። መሊክ ፈይሰል ፣ ሄራ ፣ ጀበለር ኑርና መሊክ አብደላ በተባሉ ትላልቅ ሆስፒታል ሃላፊዎች “የቤተሰብ ወይም የኢንባሲ ውክልና አምጡ !” በማለት አንደከለከሏቸው ወጣቶች አጫውተ ኛል። ይህንን ችግር እንዳጋጠኛቸው ያጋጠማቸውን ለሀጅ ኮሚቴ በመጠቆም ተቀራርበው ለመስራት መሞከራቸው የገለጹልኝ የአፈላላጊ ቡድኑ አባላት አብሮ የመስራት ሙከራውም አለመሳካቱን ገልጸውልኛል! “ከጅዳ ለመጡ ኮሚቴ ነን ” ላሉን ሰዎች በሀጅ ኮሚቴ ወይም በጅዳ ቆንስሉ በኩል ውክልናውን ወይም መታወቂያ ቢሰጠን ብለን ጠይቀን ነበር ያሉኝ አንድ ወጣት በበኩላቸው ” መጣዎቂያ ይሰጣቹሃል!” የሚል ቃል ቢገባላቸውም እስካሁን ከኮሚቴውም ሆነ ከሌላ ወገን መልስ ባለ መሰጠቱ ጥረታቸው መሰናክል እንደገጠመው ገልጸውልኛል፡፡
በአንጻሩ የተመሳሳይ ችግር ያለባቸው የአንዳንድ ሀገራት የመንግስት ተወካዮችና ዲፕሎማቶች እንኳንስ ነዋሪው ተደራጅቶ መጥቶ ነዋሪዉን ለበጎ ስራና በማቀናጀትና በማቀዳጀት በሽዎች የሚቆጠሩ ልዩ የጠፉ ሃጃጆችን አፈላላ ግብረ ሃይል አቋቁመው በመካ ፣ ሚናና ጀናራት ማሰማራታቸው ይጠቀሳል ። የነዋሪውንና የሀጃጆችን ጭንቀት በመረዳትም የቆሰሉትንና የሞቱትን ፎቶ መረጃዎች ከሳውዲ መንግስት በመውሰድ ለዜጎቻቸው አቅርበዋል።
የመካ ወጣቶች በፍለጋው እንደ “አሳ ጎርጓሪ …”
አበው ” አሳ ጎርጓሪ…” የእኒሁ በመካ ዙሪያ ያሉ ወጣቶች በሚና ጀማራት የተጎዱ ሰዎችን ሲያፈላልጉ በመካው ክሬን ተጎድታ የሞተች ኢትዮጵያቷ ሀጃጅ ማግኘታቸው ታውቋል። እስከ ዛሬ የሀጅ ኮሚቴም ሆን የጅዳ ቆንስል ምንም መረጃ ስለሌላቸው ማንም ሳይደርስባት መሞታን ገልጸውልኛል። ይህችው ኢትዮጵያዊት ሃጃጅ በጉዳቱ በከባድ ቆስላ በህክምና ስትረዳ ከቆየች በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት በተከበረው የኢድ አል አድሃ እለት ህይዎቷ ማለፉን ከዶክተሮች እንደተገለጸላቸው ሬሳውን አየሁ ያለ ጎልማሳ አስረድቶኛል። እኔም ጉዳዩን በተዘዋዋሪ መንገድ ለማጣራት ባደረግኩት ሙከራ የተባለችው እህት ሬሳ በሆስፒታሉ የሬሳ ክፍል እንደሚገኝ ማረጋገጥ ችያለሁ! በዚህች ሟች ሀጃጅ ዙሪያ የደረሰኝ መረጃ ለሃጅ ኮሚቴና ለጅዳ ቆንስል በተመሳሳይ ሁኔታ መቅረቡን አረጋግጫለሁ፡፡
ሀጃጆችን ፍለጋ በጅዳ ሆስፒታሎች
አደጋው ከደረሰ በኋላ ባሉት ቀናት የተጎጅዎች ቁጥር ከፍ እያለ በመምጣጡ ወደ 200 የሚጠጉ ቁስለኞች ወደ ጅዳ መተላለፋቸው ይታወሳል ። ይህንኑ ተከትሎ የጅዳ ቆንስል በሳምንቱ መጀመሪያ ዲፕሎማቶችን ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በቡድን በማሰማራት ፍለጋ ጀምረው ነበር ። በዚሁ ፍለጋ ከተጋበዙት መካከል የሴቶች ማህበርና የጅዳ ኮሚኒቲ የሚገኙበት ሲሆን የሴቶች ማህበር አባላት ሲሳተፉ የጅዳ ኮሚኒቲ ግን በፍለጋው አልተሳተፈም ። ለሁለት ቀናት በተደረገው ፍለጋ አንድም ኡትዮጵያዊ አልተገኘም።
የተደረገው ፍለጋ ጅዳ ማህጀር የሚገኘውን የሬሳ ማቆያ ያካተተ ቢሆንም ወደ ማቆያው የተላለፈው ሬሳ ማንነት ገና ባለመጣራቱ መረጃ ማግኘት እንዳልተቻለ የጅዳ ቆንሰል ባወጣው መረጃ ጠቁሟል ። እስከ ዛሬ ረፋድ በዚሁ ሬሳ ማቆያ ተጨማሪ ሬሳዎች መግባታቸው ሲረጋገት ወደ ማህጀሩ ማቆያ አፍሪካውያን ሬሳ እንደሚኖርበት ተገምታል።
ሞተው መለየት ያልቻሉትን የማጣራቱ ስራ
በሳምንት የአደጋው አድሜ በዋናነት አሳሳቢ የሆነው ቁርጡ የታወቀው የሞቱትና የቆሰሉት ዜጎች አልሆነም። ሞተው ፎቷቸውና ቆሰለውም ከሆነ ዝርዝራቸው ያልተገኙት ጉዳይ ብዙ ዜጎችን በመንፈስ እያስጨነቀና እያንገላታ ይገኛል። መዳረሻቸው ” ጠፋ” ከሚባሉት መካከል በደረሰው አደጋ ፊታቸው መለየት ያስቸገረ ይገኙበታል የሚል ጥርጣሬ ቢኖርም የሟቾችን ሬሳ ለመለየት የተለያዩ እርንጃዎች ቀርበዋል። ሀጃጆች በገቡበት አሻራ ለመለየት እየተወሰደ ያለው ማጣራት ረዠም ጊዜ መውሰዱ ተቃውሞ እየቀረበበት መሆኑ ይጠቀሳል ። የሳውዲ መንግስት የየጤና ጥበቃና የፖስፖርት ክፍል ኃላፊዎች ስለመለየቱ ስራ ሲናገሩ በሶስት መንገድ እንደሚከወን ያስረዳሉ ። እስካሁን መለየት ያልተቻለውን ሬሳ ለመለየት የቀረቡት ዘዴዎችም 1ኛ / በገቡበት አሻራ 2ኛ / በገቡበት ፎቶ መለየት እና 3ኛው / የስጋ ዘመድ ቤተሰቦቻቸው እየቀረቡ DNA በመስጠት መለየቱ እንደሚከወን ይናገራሉ ! አሻራቸው የተነሱ ሬሳዎች ውጤት በከነገ ጀምሮ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም የተረጋገጠ መረጃ እስካሁን አላገኘሁም፡፡
የሟቾች ቁጥር ማሻቀብ
የሚና አረፋት አደጋ ከተከሰተ ሰባተኛ ቀኑን የደፈነ ቢሆንም በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ዜጎች መዳረሻ እስካሁን ሊታወቅ አልቻለም ። ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በማህበራዊ መገናኛ መረቦች እስከ ታዋቂ መገናኛ ብዙሀን የዜና አውታሮች የጠፉና ያልተገኙት ዜጎች ጉዳይ አሳሳቢ እንደሂነ ቀጥሏል! ምንም እንኳን የሳውዲ መንግስት የሚቱትን ቁጥር ከ 769 ፈቀቅ ባያደርገውም ሞተየ ተብለው ፎቷቸው የተለጠፉት ቁጥር ከ1500 በላይ እየሆነ መጥቷል። የመንግስት ሃላፊዎች መሞታቸው ተረጋግጦ ፎቷቸው የሚለጠፉት ቁጥር እያደር አሳሳቢ ሆኗል። ለምን ቁጥሩ አደገ ተብለው ሲጠየቁ ” በፎቶው የተካተቱት ሀጅ ከተጀመረ ወዲህ በልብ ድካምና በተለያዩ አደጋዎች የሞቱት ከአደጋው ጊዜ ሰለባዎችን ጭምር ነው “ቢሉም የቁጥሩ በአፋጣኝ ማፈግ ብዙዎቹን አሳስቧል።
የህንድና ፖኪስታን ተሞክሮ
የሳውዲ መንግስት የጠፉትን በማፈላለግ ሂደቱን እንዲያፋጥንና የዜጎቻቸው እጣ ፈንታ እንዲያሳውቅ አጥብቀው እየጎተጎቱን ካሉት ሃገራት ዲፕሎማቶች መካከል ህንድና ፖኪስታን የሳውዲ መንግስት አስቸኳይ ጥሪና ተማጽኗቸውን በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡
የፓኪስታን አምባሳደር መብዙር አለ ሀቅ እና ቆንስል ጀኔራል አፍታብ አህመድ በተገኙበት ሳውዲ የሀጅና ኡምራ ሚኒስትር በድር ሀጃር ጋር ምክክር ያደረጉት የፖኪስታን የሀይማኖት ጉዳዮች ተወካይ ሳድር መሀመድ በጠፉት ፣ በቆሰሉትና በሞቱት ፖኪስታን ሃጃጆች ዙሪያ መንግስታቸ ው አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው የሚኒስትሩን አሳስበዋል ። በአደጋው 46 የሞቱባት ፣ 8 የቆሰለባት እና 42 የጠፉባት ፖኪስታን የሀይማኖት ጉዳይ ተወካይ ሳድር መሀመድ ከሳውዲ ሃጅ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት በሚና ጀማራት አደጋ የቆሰሉት ፣ ሞተው ማንነታቸው ተጣርቶ ባልተነገረ ዜጎቻቸው ዙሪያ ጉዳይ ፖኪስታናውያን ን በእጅጉ ማሳሰቡን ገልጸው አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚሹ ለሃላፊው በአጽንኦ አስታውቀዋል። በተለይም መዳረሻቸው የጠፉ ዜጎቻቸው ጉዳይ የሚወዷቸው ቤተሰቦች የጠፉባቸው ቤተሰቦችን በጣም ያጨናነቀ መሆኑን ጠቁመው የሳውዲ መንግስት ምለሽ እንዲሰጣቸው ተማጽኗቸውን አቅርበዋል፡፡
በአደጋው 46 በሞት ያጣችው 62 የቆስለባትና 82 የጠፉባት ህንድ ዲፕሎማቶች በበኩላቸው የሀጃጅ ዜጎቻቸው ጉዳይ ዜጎቹና መንግስትን እንቅልፍ እንደነሳቸው አሳስበዋል ። በጅዳ የሚገኘው የህንድ በቆንስል መስሪያ ቤቷ የጉዳዩን አሳሳቢነት ለሳውዲ መንግስት ለመሳሰብ ትናንት ሮብ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን በዋናነት የሰጡት የህንድ ሀጅ ኮሚቴ ዋና ኃላፊ መሀቡባ ሙፍቲ የመሩት ሲሆን ስጋራቸውንና የጠፉ ቤተሰብ አባላት ጉዳይ መጣራት መጓተት መንግስታቸውን እንዳሳሰበው በመጠቆም አስቸኳይ መፍትሔ ይፈለግ ዘንድ የሳውዲን መንግስት አሳስበዋል፡፡