Monthly Archives: November, 2015

የዞን 9 ብሎገሮች የ2015 የዓመቱን የፕሬስ ነፃነት ሽልማት ተቀበሉ

በአሜሪካ ኒዮርክ ከተማ ዋና ቢሮውን ያደረገው ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (Committee to Protect Journalists) በዘንድሮው የ2015 የዓመቱ የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ላበረከቱት አስተዋፅዖ ኢትዮጵያውያኑ ዞን 9 ብሎገሮች ሽልማት ተቀበሉ፡፡ በስፍራው ማክሰኞ ህዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በተከናወነው ምሽት የዞን 9 አባላት መካከል እንዳልካቸው ኃይለሚካኤል እና ሶሊያና ሽመልስ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡

CPJ Zone 9

ሀገር ቤት የሚገኙት ቀሪዎቹ የዞን 9 አባለት ከአንድ ዓመት እስር ቆይታ በኋላ ቢለቀቁም ከሀገር እንዳይወጡ የጉዞ እገዳ የተጣለባቸውና የጉዞ ሰነድ የተነጠቁም እንዳሉ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ለፕሬስ ነፃነት በሀገሪቱ ውስጥ ላበረከቱት አስተዋፅዕ ሲፒጄን ጨምሮ መቀመጫውን በፈረንሳይ ፓሪስ ያደረገው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የዓለም አቀፍ ተሸላሚ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በዕለቱ በእንግድነት የተገኘችው በቅርቡ የተፈረደባትን እስር አጠናቃ ከእስር የወጣችው ርዕዮት ዓለሙ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላታል፡፡ በያዝነው ዓመት የሲፒጄ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ከኢትዮጵያውያኑ ዞን 9 በተጨማሪ ሶሪያዊ እና ማሌዥያዊ ጋዜጠኛ እና አክቲቪስቶችም ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በተመሳሳይ ከ አምስት ዓመት በፊት የቀድሞው የአውራምባ ታየምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ዳዊት ከበደ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ ሲፒጄ ዓለም አቀፍ የሃዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲሆን፤በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት በፕሬስ ነፃነት እና በጋዜጠኞች ላይ የሚወስደውን አፈና አጥብቆ በመኮነን ይታወቃል፡፡

የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከአስመራ የትግል ሜዳ ወደ አውሮፓ መዲና ቤልጀም ብራሰልስ መጠራት

ብስራት ወልደሚካኤል

ፕሮፌሰሩ ለረቡዕ ህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. (December 2, 2015) ከአስመራ ወደ ቤልጄየም ብራሰልስ የተጠሩት በሀገራችን ኢትዮጵያ ድርቅን ተከትሎ በተከሰተው ፖለቲካዊ የፖሊሲ ውድቀት ወለድ ርሃብ ጉዳይ ላይ ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ንግግር፣ ምክክር እና ውይይት ለማድረግ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የኢህአዴግ የ11 በመቶ የቁጥር ኢኮኒሚ ዕድገት ጋጋታ ገደል የከተተውና በምግብ ራሳችንን ችለናል መዝሙር ከአዳራሹ ነፋስ እንደወሰደው የሚያሳብቀው ከ15 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በርሃብ አለነጋ ከመገረፍ አልፎ አስቸኳይ የምግብ ርዳት እንደሚያስፈልገው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅቶች እና የተባበሩት መንግሥታት ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሄንን እውነታ ለመደበቅ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ለማስተባበልና በርሃቡ ወደተጎ ዜጎች አካባቢ ሚዲያ ድርሽ እንዳይል እና እንዳይዘገብ በውስጥ መመሪያ መተላለፉንም ከሰማን ሰነበትን፡፡

dr-berhanu-Nega

ይሄ ሁሉ የራስን የጥፋት ገመና ለመሸፈን ሲባል ህዝብ ርሃቡ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ አይደለም ሲባል ለሀገሬው ዜጋ በቋንቋው ሲነገር፤ ለዓለም አቀፍ ለጋሽ ሀገሮች ደግሞ በእንግሊዘኛ በሀገሪቱ ከፍተኛ የርሃብ አደጋ መከሰቱን እና በሀገሪቱ የእርዳታ ማስተባበሪያ የጠገኘው እህል ከአንድ ወር እንደማያልፍ በመግለፅ ተማፅኖውን ማሰማቱን ቀጥሏል፡፡ ይህንን ስንሰማ የኢህአዴግ መንግሥት አስተዳደር ኃላፊነቱ ለነጮች ነው ወይስ ለኢትዮጵያውያን የሚል ጥያቄ ቢያጭርም ከተለመድ የተለየ ነገር ግን የለም፡፡ ለዓመታት የተለመደ የመረጃ (ዳታ) ጋገራ መግለጫና ፕሮፖጋንዳ በተጨማሪ በግልፅ መረጃ ለማፈን ከፍተኛ በጀት መድቦ መንቀሳቀስ ከጀመረ እነሆ ከ10 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ልዕለ ኃያሏ አሜሪካም ብትሆን ከስርዓቱ ያላትን የፀጥታ ጉዳይ ትብብር (ወታደሮችን ለአላስፈላጊ እልቂት ማገዳ ካላት ስምምነት) አኳይ እንደ ጥሩ አጋር ብትቆጥርም የስርዓቱን አምባገነንነት፣ ዘረኛ አገዛዝ፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት አለመኖር፣ የፍትህ እጦት፣ ሙስና እና ተጠያቂነት የሌለው አሰራር የሚከተለው ስርዓት እንደሆነ ልትሸሽገው አልቻለችም፡፡

EU

ይሁን እንጂ የአውሮፓ ህብረት የተለመደ ሰብዓዊ እርዳታውን በስሱም ቢሆን መለገሱን ባያቆምም የምንጊዜም የስርዓቱ ቀኝ እጅ የሆኑት እንግሊዝ፣ ጣሊያን እና አየርላንድ እንደድሮ ለስርዓቱ ሰዎች ፊት መስጠቱን የቀነሱ ይመስላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን በሚመለከት በአውሮፓ ህብረት አሊያም በአውሮፓ ኢኮኖሚ ቅንጅት የጋራ አባል ሀገሮች በኩል ውሳኔ እንዲያልፍ እየተደረገ መሆኑን እየታዘብን ነው፡፡ ወቅታዊውን ርሃብ ለማስታገስና ለተጎዱ ወገኖች የሚደረው ሰብዓዊ እርዳታ እንኳ እንደቀድሞ በቀጥታ ለመንግሥት ከመስጠት ይልቅ በእርዳታ መልክ የተሰጠው ገንዘብ በሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች በኩል በቀጥታ ለተጎጂዎች እንዲደርስ የሚያስችል አሰራር እየተከተሉ እንደሆነ የስርዓቱ አጋር አሜሪካ እና በቅርቡም ስውድን የወሰደችው እርምጃ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ስርዓቱ በተለያዩ ለጋሽ ሀገሮች እንኳ እምነት እንደታጣበት እና የተለመደው የመረጃ ጋገራ ሪፖርትና ጋጋታ ፋይዳቢስ መሆኑን የተገነዘቡ ይመስላል፡፡

እነሆ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያውን ርሃብ በተመለከተ ህዝባዊ ዓመኔታና ቅቡልነት ባይኖረው ኃላፊነት ያለበት መንግሥት እያለ ስርዓቱን ለመገርሰስ ከሚታገሉት መካከል ተዓማኒና ትክክለኛ መረጃና ትንታኔ ይሰጣሉ ተብለው ከታመኑት መካከል በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አማካኝነት ከአስመራ የትግል ሜዳ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተጋብዘዋል፡፡ በርግጥ ፕሮፌሰሩ ካላቸው የፖለቲካ ስብዕና በተጨማሪ በሙያቸው ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ባለሙያና ተመራማሪ እንደመሆናቸው መጠን በስፍራው መጋበዛቸው የህብረቱ ትክክለኛ ምርጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ የስርዓቱን ሰዎች የበለጠ ምክንያታዊ መሸሸጊያ የሚያሳጣ ወቅታዊ የመረጃ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የሚገርመው በኢትዮጵያ ስም ስርዓቱን ወክሎ በቤልጀየም ከፍተኛ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እያሉ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ መረጃና ትንታኔ እንዲሰጡ ከበረሃ የትግል ሜዳ የፕሮፌሰሩ መጋበዝ ለስርዓቱ ትልቅ ራስምታት ነው፡፡ ምክንያቱም ፕሮፌሰሩን እና የሚመሩትን የፖለቲካ ድርጅትና አባላት በሽብርተኝነት ለማስፈረጅ ለዓመታት በተለመደ የመረጃ ጋገራ ቢሞከርም በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ተቀባይነት አላገኘምና፡፡

በተለይ በመረጃ እና ሐሳቡን ለመግለፅ ለታፈነው የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ አጋጣሚ ሲሆን፤ ለፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ለሚመሩት ድርጅት እንደ አንድእመረታ ሊታይ ይችላል፡፡ እንደ አንዳንድ የስርዓቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጥቆማ ከሆነ መንግሥት ርሃቡን ከሀገሬው ሰው በመደበቅ ለጋሽ ሀገራት በተማፅኞ በማጨናነቅ ዕርዳታቸውን በጥሬ ገንዘብ ወይም ዶላር እንዲሆን እየሰራ እንዳለ እና ለዚህም ያቀረበው ምክንያት ገንዘቡ ከተሰጠኝ ከሀገር ውስጥ ነጋዴዎች እህሉን ራሴ ገዝቼ በማከፋፈል ጊዜና ጉልበት መቆጠብ እችላለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡ ይህ ለተጎጂዎች ታስቦ ሳይሆን መንግሥት በሀገሪቱ ከደረሰበት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ አጋጣሚውንም እንደ ጥሩ ዕድል ሊጠቀምበት እንዳሰበና እስካሁንም እንዳልተሳካለት ለስርዓቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተጠቁሟል፡፡

በአሁን ወቅት ከአስከፊው ርሃብ በተጨማሪ በሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመከሰቱ የተለያዩ አስመጪዎች እና ኢንዱስትሪዎች ለአብነትም ቴክኖ ሞባይል የስልክ መገጣጠሚያን የመሳሰሉት ስራ ማቆማቸውም መነገር ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በዚህ ሁሉ የስርዓቱ አጣብቂኝ ውስጥ ፕሮፌሰሩ የበለጠ ተዓማኒነትና ተቀባይነት አግኝነተው በአውሮፓ ህብረት መጋበዛቸው በቀጣይ ምን ሊያሳየን ይሆን የሚለውን ወደፊት አብረን የምናየው ነው ሚሆነው፡፡

አዲሱ ማስተር ፕላን አሁንም ተቃውሞ ቀስቅሷል

አዲስ አበባን ከሌሎች አጎራባች ከተሞች በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር በሚል በመንግሥት ይፋ ባደረገው አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ከትናንት ጀምሮ በድጋሚ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡

AA new masterplan protesting

በተለይ በምዕራብ ሸዋ አምቦ፣ ጊኒጪ እና ምዕራብ ወለጋ ተቃውሞው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በተቃውሞው ከተሰለፉት መካከል በመንግሥት በተወሰደ ርምጃ በምዕራብ ሸዋ ድሬ ኢንጪኒ አካባቢ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንዳሉም መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በዋናነት ተቃውሞን የቀሰቀሰው አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን ያከተተ በመሆኑ እና የዞኑን እና የክልሉን ጥቅም እንዲሁም ገበሬዎችን ያለምንም በቂ ካሳና ቦታ በማፈናቀል ለጎዳና ህይወት ይዳርጋል የሚሉ ሐሳቦች እንደሚገኙበት የተጠቆሙ ሲሆን፤ ይህንን ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ ኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅት አባል ከሆነው ከኦህዴድ አመራር አባላት ከመፅደቁ ውጭ ወደ ህዝብ ያልወረደና ለምክክርም እንዳልቀረበ ታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት የዚህ ማስተር ፕላን ተቋውሞው በ2006 ዓ.ም. በመንግሥት በተወሰደ እርምጃ በርካታ ተማሪዎች እና የተቃውሞ ታዳሚዎች ግድያ ከቆመ በኋላ ድጋሚ ማገርሸቱ ተሰምቷል፡፡

 

AA masterplan protesting

በአንዳንድ ከተሞች የመኪና መንገዶች የተዘጉ ሲሆን፤ በተቃውሞው የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችም መካተታቸው ታውቋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ምንም የተሰጠ ማብራሪያም ሆነ አስተያየት የለም፡፡

የሳውዲ ባለሃብት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ቅሬታ ማሰማት ጀመሩ

ነብዩ ሲራክ

* “በኢትዮጵያ በደልና ዘረፋ ተፈጸመብን !” ባለሃብቱ!
* ” ቅሬታ ውንጀላው መሰረት ቢስ ነው ” የኢትዮጵያ ዲፕሎማት

ታዋቂው የሳውዲ ጋዜጣ አረብ ኒውስ ‪#‎Arabnews‬ የኢትዮጵያ መንግስት አንዳንድ ባለ ኃላፊዎች መሬታቸውን እየተቀሙ በደልና ዘረፋ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ሞሀመድ አልሸህሪ የተባሉ ሳውዲ ባለ ሃብት አስታውቀዋል። እኒሁ ባለሃብቶችን መርተው ወደ አፍሪካና ወደ ኢትዮጵያ ከአመታት በፊት የዘለቁት ባለ ሃብት Investor በኢንቨስትመንት ፈቃድ ወደ ኢትዮጵያ ያስገቧቸው ንብረቶችን ለመውረስ በእርሳቸውና በጓደኞቻቸው ላይ የወንጀል ክስ አንደተመሰረተባቸው ማስታወቃቸውን አረብ ኒውስ ዘግቧል ። ቅሬታ አቅራቢው ሳውዲ ባለሃብት ሞሃመድ አልሸህሪ ለአረብ ኒውስ ጋዜጣ እንዳስታወቁት ሙስናው የከፋ እየሆነ መምጣቱን በመጠቆም ሳውዲ ባለሃብቶች በማመሳሰል ( Forgery) ወንጀል ሳይቀር ተወንጅለው ለስራ ያስገቧቸውን እቃዎች መመለስ እንዳልቻሉ አስረድተዋል።

Ethio farmer

ከስድስት አመት በፊት ጀምሮ በእርሻ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሳውዲ ባለሃብቶች በመንግስት የተገባላቸው ቃል በተግባር ባለመፈጸሙ 50 % እጅ ያህሉ ከኢትዮጵያ ለቀው መውጣታቸውን እኒሁ ቅሬታ አቅራቢ ሳውዲ ባለ ሃብት ተናግረዋል ። ” በደረሰባቸው በደል ተማረው ሀገሪቱን ለቀዋል !” ስላሏቸው ባለሃብቶች ሲያስረዱም የቻሉት ሸጠው መውጣታቸውን አልደበቁም። መሸጥ ያልቻሉትና ያልቻሉት እቃቸውን ትተው የወጡት ግን ተመልሰው እቃቸውን ቢጠይቁ ” በማናውቀው ወንጀል እንያዛለን !” በሚል ስጋት ባለ ሃብቶች ኢትዮጵያ ላይ ወረታቸውን በትነው መቅረታቸውን ሞሃመድ አልሸህሪ ለአረብ ኒውስ አስታውቀዋል ።
ከዚህ ቀደም ተሰምቶ የማይታወቀውን የሳውዲ ባለ ሃብቶች ቅሬታና ብሶት ለታዋቂው የሳውዲ ጋዜጣ ለአረብ ኒውስ በአደባባይ ያጋለጡት ባለሃብቱ ሞሃመድ አልሻህሪ ቅሬታቸውን ለሁለቱም ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቢያቀርቡም እስካሁን ምነም አይነት ምልሽ እንዳላገኙ ጠቁመዋል !
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዜናውን ማስፈንጠሪያ Link በፊስ ቡክ የፊት ገጼ ላይ እንደለጠፍኩ ” እንዴት ይህን ያልተጨበጠ አደገኛ መረጃ ሊንክ Link ይዘህ ትለጥፋለህ? ” በማለት የጅዳ ቆንስል ዲፕሎማት ቆንስል ሸሪፍ በስልክ ቅሬታቸውን ግልጸውልኛል ። ለሚሊዮኖች በአለም ዙሪያ የተሰራጨውን መረጃ ማስተላለፌን በአግራሞት የተመለከቱትና በጅዳ ቆንስል የኢኮኖሚ ኋላፊ አቶ ሸሪፍ ኼሪ በዜናው ዙሪያ ዘርዘር ባለ መልኩ አነጋግረውኛል ። እኔም ያቀረብኩት መረጃ ከአረብ ኒውስ ማግኘቴን ደግሜ በማስረዳት ማሰተባበያ ማቅረብ እንጅ የወጣውን መረጃ አታሰራጩ ፣ አለያም አትለጥፉ ማለት እንደ ሚከብድ አሳውቄቸዋለሁ !
ቆንስል ሸሪፍ በመጨረሻም ” አረብ ኒውስ ጋዜ ለ ያወጣው መረጃ የተዛባ በመሆኑ አስፈላጊው ሁሉ እርምጃ ይወሰዳል ” በማለት “ፍጹም መሰረተ ቢስ ነው ! ” ላሉትን የተሰራጨ መረጃ ምላሽ ለመስጠት በሪያድ የኢትዮጵያ ኢንባሲ በኩል አስፈላጊ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸውልኛል !
ቸር ያሰማን !

የትግል ሜዳ ውሎ ትውስታ እና ቅኝት

ኤፍሬም ማዴቦ
( ከኤርትራ አርበኞች መንደር)

ኤፍሬም ማዴቦ

ኤፍሬም ማዴቦ

መብራቱን አጥፍቼዉ አልጋዬ ላይ የወጣሁት በግዜ ነዉ። አለወትሮዬ እንቅልፍ የሚባል ነገር በአይኔ አልዞር ብሎኝ ከጨለማዉ ጋር ፊት ለፊት ተፋጥጠናል። የነፋስ ሸዉታ እንኳን የማይሰማበት ደረቅ ሌሊት ነዉ። ጨላማዉ አይን ይበሳል። እቤቱ ዉስጥ ያለዉ ሰዉ ሁሉ ተኝቷል። ቀኑን በሠላም ላዋለኝ አምላክ ምስጋና ሰጥቼ ሌሊቱንም አደራ ብዬዉ ፀሎቴን ጨረስኩ። ያ ምቀኛ እንቅልፍ ግን አሁንም እንደከዳኝ ነዉ። ትንሿ አልጋዬ ላይ ግራ ቀኝ እያልኩ ተገለባበጥኩ። እንቅልፍ ተጎትቶ የሚመጣ ይመስል አሁንም አሁንም ላይ ታች እያልኩ አልጋዉ ላይ እራሴን ጎተትኩት . . . እንኳን እንቅልፍ ሊወስደኝ ጭራሽ አይኖቼ መርገብገባቸዉን ያቆሙ ይመስል ቀጥ ብለዉ ቀሩ። ከተጋደምኩበት ብድግ ብዬ መብራቱን አበራሁና ለመንገድ ከያዝኳቸዉ ሁለት መጻህፍት አንዱን አዉጥቼ ማንበብ ጀመርኩ። እኔ ላንብበዉ ወይ መጽሀፉ ያንብበኝ አላዉቅም ።

ጧት ስነሳ ግን “The Architecture of Democracy” የሚል መጽሐፍ ደረቴ ላይ ተለጥፎ ነበር። ሰዐቴን ሳየዉ ከሌሊቱ ስምንት ሰዐት ተኩል ይላል። ከአልጋዬ ላይ ዘልዬ ወረድኩና ሰዉነቴን ታጥቤ ልብሴን ከለበስኩ በኋላ መኪናዉ ዉስጥ ገብቼ “I’m ready” አልኩ። የመኪናችን መብራት ጨለማዉን እየገላለጠዉ የአስመራ ከረንን መንገድ ተያያዝነዉ። መኪናዉ ዉስጥ ከገባሁ በኋላ እንደገና አፌን የከፈትኩት ባሬንቱ ደርሰን ቁርስ ሳዝ ነዉ። ባሬንቱ በግዜ መድረሳችን ደስ ቢለኝም የቀረን መንገድ ርዝመት ታየኝና ቁርስ መብላቴን ትቼ . . . በሰዐት ይህን ያክል ብንጓዝ እያልኩ ዋናዉ ጉዳያችን ቦታ የምንደርስበትን ሰዐት ማስላት ጀመርኩ። የስሌቱ ዉጤት ከሦስት ሰዐት ሲበልጥብኝ ተናደድኩ። ቀሪዉ መንገድ ገና ሳልጀምረዉ ሰለቸኝ። በተፈጥሮዬ መንገድና መኃላ ሲረዝም አልወድም። Patriotic Ginbot7 fighters.

ተሰነይ ስንደርስ መኪናዉ ዉስጥ የነበረዉ ሰዉ ሁሉ ቡና ካልጠጣሁ አለ። መኪናችንን አቁመን በቁማችን ቡናችንን ፉት አድርገን መንገዳችንን ተያያዝነዉ። እሁድ ጥቅምት 7 ቀን 2008 ዓም አርበኞች ግንቦት ሰባትን የፈጠሩት ሁለት ድርጅቶች ከተዋሃዱ በኋላ ለሁለተኛ ግዜ የሰለጠኑ ታጋይ አርበኞች የሚመረቁበት ቀን ነበር። ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነቱን የምርቃት ዜና የምሰማዉ በኢሳት ሬዲዮና ቴሌቭዥን ብቻ ስለነበር እቦታዉ ደርሼ የምረቃዉን ስነስርዐት ለማየት የነበረኝ ጉጉት እጅግ በጣም ከፍተኛ ነበር። የምሳ ሰዐት ከመድረሱ በፊት በቀኝ በኩል ዋናዉን መንገድ ለቅቀን ዉስጥ ዉስጡን ወደ ምርቃቱ ቦታ የሚወስደዉን ኮረኮንች መንገድ ተያያዝነዉ።
ግቢዉ ዉስጥ ያለዉ ጥድፊያና ግርግር አንድ ትልቅ ዝግጅት መኖሩን በግልጽ ይናገራል። የተለያየ ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱና መሳሪያ የተሸከሙ አርበኞች ግቢዉን ሞልተዉታል። ያነገቱትን ጠመንጃ ስመለከት ቆራጥነታቸዉ ታየኝ። በቀጭኑ ተጎንጉኖ ማጅራታቸዉ ላይ የወደቀዉን ፀጉራቸዉን ሳይ ቴዎድሮስና ዮሐንስ ትዝ አሉኝ። ፈገግታ በፈገግታ የሆነዉን ፊታቸዉን ስመለከት ደግሞ የእናት አገሬ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ደጃፍ ላይ መሆኑ ታየኝና የኔም ፊት እንደነሱ በፈገግታ ተሞላ። ተራ በተራ እየመጡ “ጋሼ አፍሬም” እንደኳን ደህና መጣህ ብለዉ ሲጠመጠሙብኝ በአንዱ ትከሻዬ ፍቅራቸዉ በሌላዉ ጀግንነታቸዉ ዘልቆ ሰዉነቴ ዉስጥ ገባ።ጥንካሬያቸዉ በጅማቴ ፍቅራቸዉ በደም ስሬ ዘለቀ። እኔነቴ ሲታደስና በአገሬ ላይ ያለኝ ተስፋ ሲለመልም ተሰማኝና ደስ አለኝ።

አዎ ደስ አለኝ . . . እየመጣ የሚሄድ ግዜያዊ ደስታ ሳይሆን የዉስጥ አካላቴን የዳሰሰ ዘላቂ የመንፈስ ደስታ ተሰማኝ። በጣም ደስ የሚልና በአሁኖቹ ቋንቋ “የሚመች” ቀን ነበር። የዕለቱን ዝግጅት ለማየት መቸኮሌን ያወቁት እግሮቼ የምረቃዉ በዐል ወደሚከበርበት ዳስ- ፍትህ፤ ነጻነትና እኩልነት የናፈቀዉ ልቤ ደግሞ ወደ ወደፊቷ ኢትዮጵያ ይዘዉኝ ጭልጥ አሉ፡ . . . ለካስ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ሩቅ አይደለችም።

“ማነዉ ሚለየዉ . . .ሚለየዉ፤ ይህም ትዉልድ ፍም እሳት ነዉ” የሚለዉን የጃሉድ ዘፈን በርቀት ሲሰማ በቀኑና በዘፈኑ መግጠም ተገረምኩ። “እዉነትም ይህ ትዉልድ ፍም እሳት ነዉ” እያልኩ በለሆሳስ ለራሴ እየነገርኩት ዳሱ ዉስጥ ገብቼ ቁጭ አልኩ። እርግጠኛ ነኝ ይህንን ጽሁፍ የሚያነብ ሰዉ ዳሱ ዉስጥ የነበረዉን ፍጹም ኢትዮጵያዊ የሆነ የጀግንነት፤ የቆራጥነት፤ የእልህና የመተማመን ልዩ ስሜት መረዳት የሚችለዉ እኔ በዚህ ባልተባ ብዕሬ ስገልጸዉ ሳይሆን እንዳዉ በደፈናዉ ዳሱ እራሱ ኢትዮጵያዊ ነበር ብዬ ባልፈዉ ነዉ።
አገራችን ኢትዮጵያ ከራሱ ምቾትና የተደላደለ ኑሮ ይልቅ የወገኖቹ መብትና ነጻነት የሚያንገበግበዉና እራሱን ለፍትህ፤ ለአንድነትና ለነጻነት ለመሰዋት ዝግጁ የሆነ የየዘመኑ ምርጥ ትዉልድ አላት። ይህንን የኛን ዘመን ምርጥ ትዉልድ ነዉ አርቲስት ጃሉድ “ይህም ትዉልድ ፍም እሳት ነዉ” ብሎ በጣፋጭ ዜማዉ ያወደሰዉ። እኔ ጥርጥርም የለኝ ይህ ትዉልድ አንድና ሁለት ብቻ ሳይሆን ለቁጥር የሚታክቱ ብዙ ፍም እሳቶች አሉት። ችግሩ የእሳት ነገር አዚህ ቤት ነደዳ እዚያም ቤት ነደደ ስራዉ ማቃጠል ነዉና አንዱን እሳት ከሌላዉ እሳት መለየት አስቸጋሪ ነዉ። እኔም ችግሬ እዚህ ላይ ነዉ። ፊት ለፊቴ ላይ ቁጭ ብለዉ ስለማያቸዉ ፍም እሳቶች (ጀግኖች) ላወራችሁ እየፈለኩ ምርጫዉ አዋጅ ሆነብኝ. . . የራሱ ጉዳይ ብዬ አንዱን ጀግና መረጥኩ። ይህንን ዛሬ የምተርክላችሁን ጀግና ስመርጥ ግን እንዳዉ በደፈና አልነበረም። ጉዳይ አለኝ . . . . ጉዳዩ አንዲህ ነዉ።

በዕለቱ በተመራቂ አርበኞች ተዘጋጅተዉ ከቀሩቡት የተለያዩ የኪነት ስራዎች ዉስጥ አንዱ የድራማ ዝግጅት ነበር። ሦስት የተለያዩ ድራማዎች መታየታቸዉ ትዝ ይለኛል። ዳሱ ዉስጥ የተሰበሰበዉን በብዙ መቶዎች የሚቆጠር ሰዉ ስሜት የኮረኮረዉና የእያንዳንዱን ሰዉ የልብ ትርታ ሰቅዞ የያዘዉ ግን በእዉነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተከወነዉ የመጨረሻዉ ድራማ ነበር። ድራማዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ ሰሜን ኢትዮጵያ ዉስጥ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት ናችሁ እየተባለ በየቀኑ በህወሃት የደህንነት ሠራተኞች እጃቸዉ እየታሰረ በየወንዙና በየፈፋዉ በግፍ እየተገደሉ ስለሚጣሉ ኢትዮጵያዉያን የሚተርክ ድራማ ነበር።

ድራማዉ “ኮሜዲ” የሚባል ክፍል የለዉም። ተጀምሮ እስኪያልቅ “ትራጄዲ” ብቻ ነዉ። ያሳዝናል፤ ያስቆጣል፤ ያስቆጫል፤ያንገበግባል፤ አንጀት ያቆስላል፤ ልብ ያነድዳል . . . ወይ ነዶ ያሰኛል ። እኔማ እንኳን ትራጄዲ አይቼ በተፈጥሮዬ ሆደ ቡቡ ነኝና በደል ስመለከት ማዘን ልማዴ ሆኖ አምባዬ መፍሰስ የጀመረዉ ገና ድራማዉ ሲጀምር ነበር። በተለይ አናታቸዉ እየተደበደበ የሚቀበሩበትን ጉድጓድ በግድ እንዲቆፍሩ የተደረጉትን ሁለት ወጣት ወገኖቼን ሳይ ሆዴ ባባ፤ አንጀቴም ቆሰለ። ልቤ ዉሰጥ የነደደዉ እሳት ትንታጉ እየተንቦገቦገ ወጥቶ የዉጭ ሰዉነቴን ጭምር ለበለበዉ። ለወትሮዉ ነገር ማመዛዘን የሚቀድመዉ አዕምሮዬ በቀል በቀል አሰኘዉ።

Arbognoch ginbot 7

የነደደዉ ልቤም ለበቀል አደባ። ጉድጓዱ ተቆፍሮ ካለቀ በኋላ የደህንነት ሠራተኛዉ AK ጠመንጃዉን አንደኛዉ ወጣት አገጭ ላይ ቀስሮ በአፈሙዙ አንገቱን ቀና እንዲያደርግ እያስገደደዉ . . . “አየኸዉ የምትገባበትን ጉድጓድ” እያለ ወጣቱ ወገኔ ላይ ሲሳልቅበት ሰማሁና በሀይወቴ ለመጀመሪያ ግዜ ኢትዮጵያዊነቴን ጠላሁት። አጠገቡ የቆመዉና በቁሙ ሞቱን የሚጠባበቀዉ ሌላዉ ወጣት ወገኔ ደግሞ . . . ግደለኝ . . . ግደለኝ. . . ግደለኝ እንጂ! . . . ምን ትጠብቃለህ እያለ የጓደኛዉን ሞት በአይኑ ከሚያይ የራሱን ሞት የሚለምነዉን ቆራጥ ኢትዮጵያዊ ድምጽ ስሰማ ደግሞ 360 ዲግሪ ተገለበጥኩና ከደቂቃዎች በፊት የጠላሁትን ኢትዮጵያዊነት መልሼ ወድድ አደረኩት። የወያኔዉ ጨካኝ ነብሰ ገዳይ ፉከራና ቆራጡ ኢትዮጵያዊ ያደረጉት የቃላት ምልልስ እምባዬን ጎትቶ አመጣዉና ፊቴ እምባ በእምባ ሆነ። ያ ከግማሽ ሰዐት በፊት ሲጨፈርበትና ሲደነስበት የነበረዉ ዳስ ሰዉ የሌለበት ባዶ ቤት ይመስል ጭጭ አለ። እኔ ኤፍሬም ሰዉ አልገድልም፤ በእኔ እጅ የሰዉ ህይወት ይጠፋል ብዬ አስቤም አልሜም አላዉቅም። ያንን የህወሃት ቅጥረኛ በዚያች ሰዐት ባገኘዉ ኖሮ ግን ለመበቀል ሳይሆን ለሰዉ ልጅ ህይወት ክብር ስል እገድለዉ ነበር።

ድራማዉ እንዳለቀ ወደ ዉጭ ወጣሁና ድቅድቅ ጨለማ ዉስጥ ብቻዬን ቁጭ አልኩ። ሀሳብ. . . የትናንት ሀሳብ፤ የዛሬ ሃሳብ፤ የነገ ሀሳብ፤ የከረመ ሀሳብና ሁሉም ሀሳብ አንድ ላይ ተሰባስበዉ ወረሩኝ። ግራ ሲገባኝና መላቅጡ ሲጠፋኝ ግዜ ትንፋሼን ዋጥ አደረኩና አንቺ እማማ ብዬ አገሬን ተጣራሁ . . . አሁንም አሁንም ደግሜ ተጣራሁ። ህመሟ ብርቱ ነበርና አልሰማችኝም። አይዞሽ ይህ ቀን ያልፍና አንቺም ከህመምሽ እኔም ከማያባራዉ የሀሳብ በሽታ ድነን አዲስ ታሪክ እንጽፋለን ብዬ ከአገሬ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁና ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ዳሱ ዉስጥ ከነበሩት አርበኞች ጋር ተቀላቀልኩ። እለቱን ሲያስጨፍረን የዋለዉ አደራ ባንድ “ነይ ደኑን ጥሰሺ” የሚለዉን ቆየት ያለ የመሀሙድ አህመድ ዘፈን ሲጫወት ልጅነቴ ትዝ አለኝና ከፍም እሳቶች ጋር መደነስ ጀመርኩ።

ጭልጋን ይዞ፤ጋይንትን ይዞ፤ የጎበዞቹን ጎራ ጃናሞራን ይዞ፤ ደምቢያን ይዞ፤ ወልቃይት ጠገዴን ይዞ፤ ላይ አርማጭሆንና ታች አርማጭሆን ይዞ ወዘተ . . .ድፍን ጎንደር የጀግኖች አገር ነዉ። አዎ! ወልቃይት ጠገዴ ከጀግናም የጀግና አገር ነዉ።ወልቃይት ጠገዴ ጎንደሬ አይደለህም ተብሎ ከተነገረዉ ከሃያ አራት አመታት በኋላ ዛሬም ህልዉናዉን ለወያኔ ፋሺስቶች አላስረክብም ብሎ ጎንደሬነቱን ለማረጋገጥ ሽንጡን ገትሮ የሚዋጋ የጀግኖች አገር ነዉ። ጎንደር የአፄ ቴዎድሮስ፤ የእቴጌ ምንትዋብ፤ የፊትአዉራሪ ገብርዬ፤ የአየለ አባ ጓዴና የጄኔራል ነጋ ተገኝ አገር ናት። ጎንደር ኢትዮጵያ ከሌለች እኛ የለንም ብለዉ ሙሉ ህይወታቸዉን ለትግል የሰጡ እነ ታማኝ በየነንና እነ አርቲስት ሻምበል በላይነህን ያበቀለች አገር ናት። ወላድ በድባብ ትሂድ. . . የጎንደር ማህፀን ዛሬም አልነጠፈም።

ዛሬ ይዤላችሁ የመጣሁት ጀግና ተወልዶ ያደገዉ አማራ ክልል ጭልጋ ወረዳ ልዩ ስሟ ጫኮ በምትባል ቦታ ነዉ። የገበሬ ልጅ ነዉ፤ እሱም ምኞቱ ገበሬ መሆን ነዉ። የሚኖረዉ መተማ ከተማ ዉስጥ ነዉ። ስሙ መሠረት ሙሌ ይባላል። ፈገግታ የማይለየዉ ፊቱ የዋህነቱንና ገራገርነቱን አፍ አዉጥቶ ይናገራል። ሲናገር ረጋ ብሎ ነዉ። አተኩሮ ላየዉ ሰዉ አይነ አፋር ይመስላል፤ የቁርጥ ቀን ሲመጣ ግን እንደ መሠረት ሙሌ ደፋር ሰዉ የለም። አይኑ እፊቱ ላይ ቆሞ ከሚያናግረዉ ሰዉ አይን ጋር ሲጋጭ አንገቱን ይሰብራል። እቺ የሰዉ አይን የመሸሽ በሽታ ደግሞ አበሾች ስንባል የሁላችንም በሽታ ናት። ጠይም ፊቱ ላይ እንደ ችቦ የተተከሉት የመሠረት ሙሌ አይኖች የሰዉን ዉስጥ ዘልቀዉ የሚያዩ ይመስላሉ። ሰዉነቱ ደንዳና ቁመቱ መካከለኛ ነዉ። ልቡ ግን ትልቅ ነዉ። አዎ መሠረት ሙሌ ልቡ ትልቅ ነዉ።

ዕለቱ ሰኞ ነዉ – ሰኞ ሚያዝያ 26 ቀን 2007 ዓም። የህወሃት የደህንነት ሰዎች አንድ ኮሎኔልና ሌሎች አራት ሰዎች ተገድለዋል በሚል ድፍን መተማን እያመሷት ነዉ። እያንዳንዱ የመተማ ነዋሪ በግድያዉ የተሳተፈ ይመስል በአጠገባቸዉ ያለፈዉን ሁሉ ወንድ፤ ሴት፤ ወጣትና ሽማግሌ ሳይለዩ ሁሉንም እያስቆሙ አጥንት ዉስጥ ዘልቆ የሚገባ ስድብ ይሰድባሉ፤ ይደበድባሉ ያስራሉ። በሠላም አዉለኝ ብሎ በጧት የተነሳዉ መሠረት ሙሌ የእህል ወፍጮዉን አስነስቶ የዕለት ስራዉን ለመጀመር ጉድ ጉድ ማለት ጀምሯል። ሴቶች እህላቸዉን ያስመዝናሉ። ሸክም የተራገፈለት አህያ ያናፋል። ነጋዴዉ፤ ደላላዉ፤ ገበሬዉና ሸማቹ ዋጋ ቀንስ ዋጋ ጨምር እያሉ ይንጫጫሉ። መተማ መደበኛ ስራዋ ላይ ናት።

“ቁም . . . እጅ ወደ ላይ . . . እንዳትነቃነቅ” የሚል ድምጽ የደራዉን የመተማ ገበያ በአንድ ግዜ ጭጭ አሰኘዉ። መሳሪያ ያነገቡ ፖሊሶችና ሲቪል የለበሱ የደህንነት ሰራተኞች ከመኪና እየዘለሉ ወርደዉ መሠረትን የፊጥኝ አስረዉ መኪናዉ ላይ ወረወሩት። ምነዉ? ምን አጠፋሁ . . . ዬት ነዉ የምትወስዱኝ? አለ መሠረት በሁኔታዉ እጅግ በጣም ተደናግጦ። አንድ አጠገቡ የነበረዉ የህወሃት ነብሰ ገዳይ . . . ዝም በል ብሎ በጥፊ አጮለዉና ለአርበኞች ግንቦት 7 የመለመልካቸዉን ሰዎች አድራሻና ስም ዝርዝር ካላመጣህ ዕድሜህ ከአንድ ጀምበር አያልፍም አለዉ።

መኪናዉ ዉስጥ ከተቀመጡት ሁለት ሰዎች አንደኛዉ አንሂድ ብሎ በእጁ ምልክት ሲያሳይ መሬት ላይ የነበሩት ፖሊሶች እየዘለሉ መኪናዉ ላይ ወጡና መሠረትንና ሌሎች ሦስት እስረኞችን የያዘችዉ ቶዮታ ሂሉክስ መኪና ፍጥነት እየጨመረች የመተማ ሁመራን መንገድ ተያያዘቸዉ። በሚቀጥለዉ ቀን ጧት ሲነጋጋ ሁመራ ደረሱና አራቱ እስረኞች እጃቸዉ እንደታሰረ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ ተደረገ። ከምሽቱ ሦስት ሰዐት ሲሆን መሠረትና ጓደኞቹ እጅ ለእጅ እንደተሳሰሩ ጉዞ ወደ ተከዜ ወንዝ ሆነ። የዚህች ከንቱ አለም የመጨረሻ ጉዟቸዉ ነበር።

ዶማና አካፋ ያዙ እንጂ . . . ደግሞም ፈጠን በሉ ግዜ የለንም. . . አለ የነብሰ ገዳዮቹ አለቃ። ከሁመራ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ተከዜ ወንዝ የሚያደርገዉ ጉዞ በህይወቱ የመጨረሻዉ ጉዞ እንደሆነ የተረዳዉ መሠረት . . . አንተዬ ልትገድሉን ነዉ እንዴ ብሎ ጠየቀ። ፊት ለፊቱ የነበረዉ ፖሊስ ከተቀመጠበት ዘልሎ ተነሳና . . .ዝም በል . . . አንተ የሴት ልጅ . . . ምን አስቸኮለህ ይልቅ የተጠየከዉን ጥያቄ መልስ አለዉና የያዘዉን የእጅ መከርቸሚያ ካቴና ፊቱ ላይ ወረወረበት። ካቴናዉ ሳይሆን ከዚያ ባለጌ አፍ የወጡት ቃላት ጅማቶቹ ድረስ ዘልቀዉ ገብተዉ መንፈሱን ጎዱትና መሠረት ለመጀመሪያ ግዜ ተስፋ ቆረጦ . . . ምንም የምሰጥህ መልስ የለኝም አለና አንገቱን ደፋ።

. . . አንቺ ወላዲት አምላክ ምነዉ . . . ምን አደረኩሽ ብሎ ቀና ሲል እሱንና ሦስት ጓደኞቹን ለመዋጥ አፋቸዉን ከፍተዉ የሚጠባበቁትን አራት ጉድጓዶች ተመለከተ። አይኔ እያየ እዚህ ወስጥ አልገባም ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ ተከታታይ የጥይት ድምጽ ሰማ። ዞር ሲል ፖሊሶች አብረዉት ከታሰሩት ሦስት እስረኞች ዉስጥ አንዱን በእግራቸዉ እየገፉ የተቆፈረዉ ጉድጓድ ዉስጥ ሲጨምሩት አየ። ደቂቃዎች የቀሩት የሱ የራሱ ህይወት ሳይሆን በህወሃት ነብሰ ገዳዮች በግፍ የተገደለዉ የጓደኛዉ ህይወት አንገበገበዉ። አዘነ – በአይኑም በሆደም አነባ። “አይኔ እያየ እዚህ ወስጥ አልገባም” ብሎ የተናገረዉ የራሱ ድምጽ ጆሮዉ ላይ አቃጨለበት። መሠረት ሞት ፈርቶ አያዉቅም፤ ግን ህይወቱ የህይወትን ክቡርነት በማይረዱ ባለጌዎች እጅ እንድታልፍ አልፈለገም። ያ የንጹሃን ኢትዮጵያዉያንን ሰዉነት ማፍረስ የለመደዉ የህወሃት ጠመንጃ ወደሱ ከመዞሩ በፊት አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ ብሎ ወሰነ። እጁ ከጓደኛዉ ጋር የታሰረበትን ገመድ በጥርሱ በጣጠሰዉና ከቀለሁ እንደተላቀቀ ጥይት ተወርዉሮ እግሬ አዉጭኝ ብሎ ጫካ ዉስጥ ዘልሎ ገባ። የህወሃት ነብሰ ገዳዮች የጥይት ናዳ ለቀቁበት፤ እሱ ግን ጫካ ጫካዉን ይዞ ወደማያዉቀዉ ቦታ ሩጫዉን ተያያዘዉ።

መሠረት- ቆራጥነቱና የልቡ ትልቅነት ጉልበት እየሆኑት ነዉ እንጂ ያ የሚጠላዉ የህወሃት ጥይት አካሉን በሳስቶ ወንፊት አድርጎታል። ሰዉነቱ ቁስል በቁስል ሆኗል። ከራሱ ሰዉነት እንደ ጎርፍ የሚፈስሰዉ ደም ጠልፎ የሚጥለዉ እስኪመስለዉ ድረስ አካሉ ደምቷል። ሩጫዉን ግን አላቆመም። ደም እንዳይፈሰዉ ጥይት የበሳዉን ቦታ ሁሉ በሁለት እጆቹ ሸፈነ። እንደኛዉ ቁስል ጋብ ሲልለት እጁን ከሱ ላይ እያነሳ ሌላዉን ቁስል ሸፈነ። ደሙ መፍሰሱን ግን አላቆመም። መሠረትም ሩጫዉን አላቆመም። መሠረት ሙሌ ህይወቱን ለማዳን ወደ ፊት የህወሃት ነብሰ ገዳዮች ደግሞ ወንጀላቸዉን ለመደበቅ ወደኋላ በተለያየ አቅጣጫ ሩጫቸዉን ተያያዙት። ሁለቱም አግሬ አዉጭኝ አሉ።

መሠረት ሞትን እየሸሸ መሆኑን ነዉ እንጂ ከሞት ለመራቁ ምንም ዋስትና አልነበረዉም። ደግሞም መሮጡን ብቻ ነዉ እንጂ ወዴት እንደሚሮጥ አያዉቅም ነበር። ከኋላዉ የሚከተለዉ ማንም ሰዉ እንደሌለ ቢረዳም ከፊት ለፊቱ ህይወቱን የሚታደግለት ሰዉ እስኪያገኝ ድረስ ሩጫዉን ቀጠለ። ጧት ጎህ ከመቅደዱ በፊት “ጠጠዉ በል” የሚል ድምጽ ሲሰማ ያ ሁሉ ሩጫዉ መልሶ ሞት ዉስጥ የከተተዉ መሰለዉና ደነገጠ። ሩጫዉን እንዳይቀጥል ቁም ያሉት ሰዎች ከበዉታል። እሺ ብሎ እንዳይቆም ሞትን አልቀበልም ያለዉ ልቡ አሁንም እንደደነደነ ነዉ። ትንፋሹን ሰበሰበና. . . ማናችሁ እናንተ ብሎ ያቆሙትን ሰዎች ጥያቄ ጠይቆ መልሱን ሳይሰማ ተዝልፍለፎ መሬቱ ላይ በግንባሩ ተደፋ።

የኤርትራ ድንበር ጠባቂ ወታደሮች መሠረትን አንድ ወር ሙሉ በህክምና ሲንከባከቡት ቆዩና እሱ እራሱ በጠየቃቸዉ መሠረት ሃሬና ወስደዉ ለአርበኞች ግንቦት 7 አስረከቡት። መሠረት ሙሌ ጥቅምት 7 ቀን ከተመረቁት አርበኞች ዉስጥ አንዱ ነዉ። ለዚህ ጀግና ያቀረብኩለት የመጨረሻ ጥያቄ . . . ሊገድሉህ የነበሩትን የህወሃት ሰዎች አሁን ብታገኛቸዉ ምን ታደርጋቸዋለህ የሚል ጥያቄ ነበር። ነጻ አወጣቸዋለኋ! አለኝና ጭፈራዉ ዉስጥ ዘልሎ ገባ። አርግጠኛ ነኝ መሠረት ሙሌ አንድ ቀን ሁላችንንም ሸገር ላይ ያስጨፍረናል። ቸር ይግጠመን።

ኤፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር
ebini23@yahoo.com
ምንጭ፡ ከፌስ ቡክ ማኀበራዊ ገፆች

%d bloggers like this: