ዶክተር መረራ ጉዲና እና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ክስ ተመሰረተባቸው
(አዲስ ሚዲያ) ከ3 ወር በፊት በአውሮፓ ፓርላማ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተጋብዘው ንግግር ያደረጉት ዶ/ር መረራ ጉዲና ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተይዘው ለ 3 ወራት በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ከታሰሩ በኃላ የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ።ም በገዥው መንግሥት ጠቅላይ አቃቤ ህግ አማካኝነት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሰረተባቸው።
ዶክተር መረራ ጉዲና እና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የነበሩት እና የኦፌኮ ሊቀመንበር እንዲሁም የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር መረራ ክስ የተመሰረተባቸው፥ በአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ንግግር ለማድረግ ተጋብዘው ሲመለሱ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር እና ሊቀመንበር ከሆኑት ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ታይተዋል በሚል እንደነበር ይታወቃል።
በዶ/ር መረራ ስም የተከፈተው በዚሁ የክስ መዝገብ ፥ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሁለተኛ ተከሳሽ ፣ አቶ ጃዋር መሃመድ ሶስተኛ ተከሳሽ በመሆን በልይሉበት ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ሶስቱም ተከሳሾች የተከሰሱት በወንጀለኛ መቅጫ ህጉን የተለያዩ አንቀጾች በመተላለፍ ሲሆን አራተኛ እና አምስተኛ ተከሳሽ የሆኑት የኢትዮጵያ ሳተላይ ቴሌቪዥን ( ኢሳት) እና ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ( ኢኤም ኤን) ሲሆኑ፥ ተቋማቱ የፀረ ሽብር ህጉን በመተላለፍ ተከሰዋል፡፡
ዶ/ር መረራ ሌላ ተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መተላፍ በሚል ክስ ተመስቶባቸዋል፡፡ የክሱ ጭብጥም ተከሳሾች በዋና አድራጊነት ሽብር ተግባር መፈጸማቸውን እና ለኦሮሚያ እና አማራ ክልል አመጾች ማነሳሳት እና ንብረት መውደም ተጠያቂ መሆናቸው በክሱ ላይ ተጠቅሷል።
የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ክሱን ለማየት ለየካቲት 24 ቀን 2009 ዓ ም ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በተለይ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከዚህ በፊት በሌሉበት በነ ጄነራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሲሆን፥ በነ አቶ አንዱዓለም አራጌ የክስ መዝገብ ደግሞ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው ሲሆን፥ የአሁኑ ከነ ዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር የተመሰረተባቸው ክስ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።
መንግሥት ከህዳር 2008 ዓ ም ጀምሮ በተለይ በኦሮሚያ ፥ በአማራ ክልል እና በደቡብ ክልል ኮንሶ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ህዝባዊ አመፅን ተከትሎ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በመንግሥት ወታደራዊ ኃይል ሲገደሉ፥ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሲታሰሩ ከ15 ሺህ ያላነሱ በተለያየ ጊዜ ከእስር መልቀቁን መንግሥስት ቢያስታውቅም አሁንም ድረስ ህዝባዊ አመፁን ተከትሎ የታሰሩና ሰብዓዊ መብቶቻቸው እየተጣሰ ያሉ ዜጎች መንግሥስት ከእስር ልቅቄያቸዋለሁ ክሚለው ቁጥር እንደሚልቅ ይግመታል።
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አማካኝነት ለህዝባዊ አምፁ ተጠያቂ ራሱ መንግሥት እና አመራሮች እንደሆኑ ቢይሳውቁም፥ ለግድያ፥ እስርና እንግልት የተዳረጉት ግን ሰላማዊ ዜጎች መሆናቸውን የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መግለፃቸው ይታወሳል።
የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከአስመራ የትግል ሜዳ ወደ አውሮፓ መዲና ቤልጀም ብራሰልስ መጠራት
ብስራት ወልደሚካኤል
ፕሮፌሰሩ ለረቡዕ ህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. (December 2, 2015) ከአስመራ ወደ ቤልጄየም ብራሰልስ የተጠሩት በሀገራችን ኢትዮጵያ ድርቅን ተከትሎ በተከሰተው ፖለቲካዊ የፖሊሲ ውድቀት ወለድ ርሃብ ጉዳይ ላይ ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ንግግር፣ ምክክር እና ውይይት ለማድረግ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የኢህአዴግ የ11 በመቶ የቁጥር ኢኮኒሚ ዕድገት ጋጋታ ገደል የከተተውና በምግብ ራሳችንን ችለናል መዝሙር ከአዳራሹ ነፋስ እንደወሰደው የሚያሳብቀው ከ15 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በርሃብ አለነጋ ከመገረፍ አልፎ አስቸኳይ የምግብ ርዳት እንደሚያስፈልገው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅቶች እና የተባበሩት መንግሥታት ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሄንን እውነታ ለመደበቅ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ለማስተባበልና በርሃቡ ወደተጎ ዜጎች አካባቢ ሚዲያ ድርሽ እንዳይል እና እንዳይዘገብ በውስጥ መመሪያ መተላለፉንም ከሰማን ሰነበትን፡፡
ይሄ ሁሉ የራስን የጥፋት ገመና ለመሸፈን ሲባል ህዝብ ርሃቡ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ አይደለም ሲባል ለሀገሬው ዜጋ በቋንቋው ሲነገር፤ ለዓለም አቀፍ ለጋሽ ሀገሮች ደግሞ በእንግሊዘኛ በሀገሪቱ ከፍተኛ የርሃብ አደጋ መከሰቱን እና በሀገሪቱ የእርዳታ ማስተባበሪያ የጠገኘው እህል ከአንድ ወር እንደማያልፍ በመግለፅ ተማፅኖውን ማሰማቱን ቀጥሏል፡፡ ይህንን ስንሰማ የኢህአዴግ መንግሥት አስተዳደር ኃላፊነቱ ለነጮች ነው ወይስ ለኢትዮጵያውያን የሚል ጥያቄ ቢያጭርም ከተለመድ የተለየ ነገር ግን የለም፡፡ ለዓመታት የተለመደ የመረጃ (ዳታ) ጋገራ መግለጫና ፕሮፖጋንዳ በተጨማሪ በግልፅ መረጃ ለማፈን ከፍተኛ በጀት መድቦ መንቀሳቀስ ከጀመረ እነሆ ከ10 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ልዕለ ኃያሏ አሜሪካም ብትሆን ከስርዓቱ ያላትን የፀጥታ ጉዳይ ትብብር (ወታደሮችን ለአላስፈላጊ እልቂት ማገዳ ካላት ስምምነት) አኳይ እንደ ጥሩ አጋር ብትቆጥርም የስርዓቱን አምባገነንነት፣ ዘረኛ አገዛዝ፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት አለመኖር፣ የፍትህ እጦት፣ ሙስና እና ተጠያቂነት የሌለው አሰራር የሚከተለው ስርዓት እንደሆነ ልትሸሽገው አልቻለችም፡፡
ይሁን እንጂ የአውሮፓ ህብረት የተለመደ ሰብዓዊ እርዳታውን በስሱም ቢሆን መለገሱን ባያቆምም የምንጊዜም የስርዓቱ ቀኝ እጅ የሆኑት እንግሊዝ፣ ጣሊያን እና አየርላንድ እንደድሮ ለስርዓቱ ሰዎች ፊት መስጠቱን የቀነሱ ይመስላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን በሚመለከት በአውሮፓ ህብረት አሊያም በአውሮፓ ኢኮኖሚ ቅንጅት የጋራ አባል ሀገሮች በኩል ውሳኔ እንዲያልፍ እየተደረገ መሆኑን እየታዘብን ነው፡፡ ወቅታዊውን ርሃብ ለማስታገስና ለተጎዱ ወገኖች የሚደረው ሰብዓዊ እርዳታ እንኳ እንደቀድሞ በቀጥታ ለመንግሥት ከመስጠት ይልቅ በእርዳታ መልክ የተሰጠው ገንዘብ በሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች በኩል በቀጥታ ለተጎጂዎች እንዲደርስ የሚያስችል አሰራር እየተከተሉ እንደሆነ የስርዓቱ አጋር አሜሪካ እና በቅርቡም ስውድን የወሰደችው እርምጃ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ስርዓቱ በተለያዩ ለጋሽ ሀገሮች እንኳ እምነት እንደታጣበት እና የተለመደው የመረጃ ጋገራ ሪፖርትና ጋጋታ ፋይዳቢስ መሆኑን የተገነዘቡ ይመስላል፡፡
እነሆ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያውን ርሃብ በተመለከተ ህዝባዊ ዓመኔታና ቅቡልነት ባይኖረው ኃላፊነት ያለበት መንግሥት እያለ ስርዓቱን ለመገርሰስ ከሚታገሉት መካከል ተዓማኒና ትክክለኛ መረጃና ትንታኔ ይሰጣሉ ተብለው ከታመኑት መካከል በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አማካኝነት ከአስመራ የትግል ሜዳ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተጋብዘዋል፡፡ በርግጥ ፕሮፌሰሩ ካላቸው የፖለቲካ ስብዕና በተጨማሪ በሙያቸው ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ባለሙያና ተመራማሪ እንደመሆናቸው መጠን በስፍራው መጋበዛቸው የህብረቱ ትክክለኛ ምርጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ የስርዓቱን ሰዎች የበለጠ ምክንያታዊ መሸሸጊያ የሚያሳጣ ወቅታዊ የመረጃ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የሚገርመው በኢትዮጵያ ስም ስርዓቱን ወክሎ በቤልጀየም ከፍተኛ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እያሉ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ መረጃና ትንታኔ እንዲሰጡ ከበረሃ የትግል ሜዳ የፕሮፌሰሩ መጋበዝ ለስርዓቱ ትልቅ ራስምታት ነው፡፡ ምክንያቱም ፕሮፌሰሩን እና የሚመሩትን የፖለቲካ ድርጅትና አባላት በሽብርተኝነት ለማስፈረጅ ለዓመታት በተለመደ የመረጃ ጋገራ ቢሞከርም በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ተቀባይነት አላገኘምና፡፡
በተለይ በመረጃ እና ሐሳቡን ለመግለፅ ለታፈነው የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ አጋጣሚ ሲሆን፤ ለፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ለሚመሩት ድርጅት እንደ አንድእመረታ ሊታይ ይችላል፡፡ እንደ አንዳንድ የስርዓቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጥቆማ ከሆነ መንግሥት ርሃቡን ከሀገሬው ሰው በመደበቅ ለጋሽ ሀገራት በተማፅኞ በማጨናነቅ ዕርዳታቸውን በጥሬ ገንዘብ ወይም ዶላር እንዲሆን እየሰራ እንዳለ እና ለዚህም ያቀረበው ምክንያት ገንዘቡ ከተሰጠኝ ከሀገር ውስጥ ነጋዴዎች እህሉን ራሴ ገዝቼ በማከፋፈል ጊዜና ጉልበት መቆጠብ እችላለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡ ይህ ለተጎጂዎች ታስቦ ሳይሆን መንግሥት በሀገሪቱ ከደረሰበት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ አጋጣሚውንም እንደ ጥሩ ዕድል ሊጠቀምበት እንዳሰበና እስካሁንም እንዳልተሳካለት ለስርዓቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተጠቁሟል፡፡
በአሁን ወቅት ከአስከፊው ርሃብ በተጨማሪ በሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመከሰቱ የተለያዩ አስመጪዎች እና ኢንዱስትሪዎች ለአብነትም ቴክኖ ሞባይል የስልክ መገጣጠሚያን የመሳሰሉት ስራ ማቆማቸውም መነገር ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በዚህ ሁሉ የስርዓቱ አጣብቂኝ ውስጥ ፕሮፌሰሩ የበለጠ ተዓማኒነትና ተቀባይነት አግኝነተው በአውሮፓ ህብረት መጋበዛቸው በቀጣይ ምን ሊያሳየን ይሆን የሚለውን ወደፊት አብረን የምናየው ነው ሚሆነው፡፡