Tag Archives: Dr.Merera Gudina

ዶ/ር መረራ ጊዱናን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ተፈቱ

በአውሮፓ ቤልጅየም በተደረገላቸው ግብዣ መሰረት በኢትዮጵያ ጉዳይ ውይይት አድርገው ሲአመለሱ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ታስረው የነበሩት ዶ።ር መረራ ጉዲና ከእስር ተለቀዋል። ዶ/ር መረራ የኦፌኮ /መድረክ ሊቀመንበር ሲሆኑ፤ በአቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንዳለ ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጎ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ ም ከእስር ተለቀዋል።
Dr. Merera _Ambo .jpg
ዶ/ር መረራ ጉዲና ከእስር ሲለቀቁ በአምቦ የተደረገላቸው ህዝባዊ አቀባበል ላይ

ዶ/ር መረራ ከእስር ሲለቀቁ በርካታ ቤተሰቦቻቸው፥ የትግል አጋሮቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ደማቅ አቀባበል ያደርጉላቸው ሲሆን፤ በተለይም በቡራዩ መኖሪያ ቤታቸው፥ እና በትውልድ አካባቢያቸው አምቦ በርካታ ህዝብ በተገኘበት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

Dr. Merera _Ambo 1
ዶ/ር መረራ ጉዲና ከእስር ሲለቀቁ በአምቦ የተደረገላቸው ህዝባዊ አቀባበል ላይ

ከዶ/ር መረራ ፥ የወለጋ ዩኒቨርስቲ መምህር ሩፋኤል ዲሳሳን ጨምሮ በደቡብ ክልል ኮንሶ እና ጌዲዮ ዞን የታሰሩ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች መለቀቃችው ታውቋል።

ቀደም ሲል መንግሥት በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል እየተደረገ ያለውን ህዝባዊ አመፅና ጫና ተከትሎ የፖለቲካ እስረኞችን እንደሚፈታ ቃል መግባቱ ይታወሳል።

በዶ/ር መረራ ላይ ሁለት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ተሰሙ

ጌታቸው ሺፈራው

የፌደራል አቃቤ ህግ በኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ ዛሬ ጥቅምት 24/2010 ዓም ሁለት ምስክሮች አሰምቷል። ሁለቱም ምስክሮች ታህሳስ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ዶ/ር መረራ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ከኮምፒውተር የወጣን ፅሁፍ የእራሴ ነው ብለው ሲፈርሙ ተገኝተን ታዝበናል ያሉ የደረጃ ምስክሮች ናቸው። ስማቸው ደራራ እና ጌታቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤት ያስመዘገቡት ምስክሮች በአንድ ቀን የታዘቡ እና የሚተዋወቁ ጓደኛሞች እንደሆኑ ገልፀዋል።

Dr.Merera Gudina
ዶ/ር መረራ ጉዲና

ደራራ (አንደኛ ምስክር) ወደ ማዕከላዊ የሄደበትን ምክንያት ሲጠየቅ ቶሎሳ የሚባል ዘመዱን ሊጠይቅ መሄዱን፣ ብቻዬን ከምሄድ በሚል ሁለተኛ ምስክር (ጌታቸው) አብሮት እንዲሄድ ጠይቆት ከሚሰሩበት መስርያቤት አስፈቅደው አብረው እንደሄዱ እና ፖሊስ ታዛቢ እንዲሆኑት ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ጠይቋቸው እንደተስማሙ ገልፆአል።

በሌላ በኩል ሁለተኛ ምስክር (ጌታቸው) አንደኛ ምስክር (ደራራ) ጋር አንድ ክፍለ ከተማ እንጅ አንድ መስርያ ቤት እንደማይሰሩ፣ ብቻውን በመስርያ ቤት ትዕዛዝ ለመርማሪዎች ሰነድ ለመስጠት እንደሄደ፣ ስራውን ጨርሶ ከመርማሪው ቢሮ ሲወጣ ኮማንደር አሰፋ በተባለ የምርመራ ክፍል ሀላፊ እማኝ እንዲሆን መጠየቁን፣ እሱ ስራዉን ጨርሶ ከወጣ እና እማኝ ለመሆን ፈቃደኛ ከሆነ በኋላ ደራራን እንዳገኘው እንዲሁም አንደኛ ምስክር (ደራራ) ወደ ማዕከላዊ የመጣበትን ጉዳይ የነገረው እማኝ ከሆነ በኋላ እንደሆነ አንደኛ ምስክር ከመሰከረው የተለየ ቃሉን ለፍርድ ቤቱ ሰጥቷል።

በተጨማሪም አንደኛ ምስክር በወቅቱ ዶ/ር መረራ ሹራብ ለብሰው ነበር ሲል ሁለተኛ ምስክር ጅንስ ሱሪና ጅንስ ሸሚዝ ለብሰው ነበር ብሏል። አንደኛ ምስክር (ደራራ) ዶ/ር መረራ በኮማንደር አሰፋ ብቻ ታጅበው ምስክሮቹ ወደነበሩበት ምርመራ ቢሮ እንደገቡ ሲመሰክር፣ ሁለተኛ ምስክር (ጌታቸው) ከኮማንደር አሰፋ በተጨማሪ ሁለት ፖሊሶች ነበሩ ብሏል።

አንደኛ ምስክር ዶ/ር መረራ ወደ ምርመራ ቢሮ እስኪመጡ በግምት ለአንድ ሰዓት ያህል መጠበቃቸውን ሲገልፅ፣ ሁለተኛ ምስክር ( ጌታቸው) በግምት ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ያህል ብቻ እንደጠበቁ ገልፆአል። አንደኛ ምስክር የዶ/ር መረራ ነው ከተባለ ኮምፒውተር ፕሪንት ተደርገው የወጡ ፅሁፎችን በከፊል እንዳነበበ ሲመሰክር ሁለተኛ ምስክር የፅሁፎችን ይዘት ብቻ ሳይሆን ርዕሶችንም አለማንበባቸውን፣ ዶ/ር መረራ አንብበው ሲፈርሙ ታዝበው መፈረማቸውን ገልፀዋል።

በዶ/ር መረራ ላይ ይቀርባሉ ተብለው የነበሩት ሌሎች ሁለት ምስክሮችን ፖሊስ በአድራሻቸው ፈልጎ እንዳላገኛቸው የገለፀ ሲሆን ሁለቱን ቀሪ ምስክሮች ለመስማት ለህዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የቀረበበት የዶ/ር መረራ አቤቱታ ለመጪው ዓመት ተቀጠረ

በታምሩ ጽጌ

Dr.Merera Gudina

ዶ/ር መረራ ጉዲና

የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን በመጥቀስ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን መከልከሉን የተቃወሙት መረራ ጉዲና (ዶ/ር)፣ ጉዳያቸው የሕገ መንግሥት ትርጉም ስለሚያስፈልገው የአጣሪ ጉባዔውን ውሳኔ እንዲጠይቁ ተነገራቸው፡፡ ውሳኔውን የሚሰሙት በሚቀጥለው ዓመት ነው፡፡

ሦስት የተለያዩ የወንጀል ክሶች የተመሠረቱባቸው ዶ/ር መረራ በክሶቹ የተጠቀሱባቸው የሕግ አንቀጾች የምስክሮችና የማስረጃ ዝርዝሮች እንዳይደርሳቸው የማይከለክሉ መሆኑን በመግለጽ፣ ከሳሽ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/01 አንቀጽ 32ን በመጥቀስ እንዳይሰጣቸው መከልከሉን ተቃውመው ነበር፡፡

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1)ሀ፣ ለ፣ 38(1)፣ 27(1)፣ 238(1) እና (2)ን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 12(1)፣ 2(1) የወንጀል ሕግ 486(ለ) ማለትም በጋራ በመተባበር፣ ወንጀል ለማድረግ በማደም፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ወንጀል ለማድረግ በመስማማት፣ የሐሰት ወሬ በማውራትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የመጣስ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ሳለ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 32 በመጥቀስ የምስክሮች ዝርዝር እንዳይሰጣቸው መከልከሉ ተገቢ ያልሆነና ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቀረበለትን የመቃወሚያ አቤቱታ የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም?›› በማለት ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አጣሪ ጉባዔ የላከው ቢሆንም፣ ውሳኔው ሊደርስ ባለመቻሉ ለቀጣይ ዓመት ጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የምስክሮች ዝርዝር ‹‹ለተከሳሽ ሊሰጥ ይገባል ወይስ አይገባም?›› የሚሉ ጥያቄዎች የተነሱት በዶ/ር መረራ ክስ ብቻ አለመሆኑን የጠቆመው ፍርድ ቤቱ፣ በርካታ የክስ መዝገቦች ላይ ጉዳዩ በመነሳቱ ቀደም ብሎ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም የሚለውን ምክር ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሷል፡፡ ምክር ቤቱ ግን ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ መላኩን ከመግለጽ ውጪ ያለው ነገር ስለሌለ ውሳኔውን መጠበቅ የግድ እንደሚል አስረድቷል፡፡

የዶ/ር መረራ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ዶ/ር መረራ ከታሰሩ ዘጠኝ ወራት ሞልተዋቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ደግሞ የዓመቱን ሥራ ሊያጠናቅቅ የቀረው ከ15 ቀናት አይበልጥም፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በራሱ የመተርጎም ሥልጣን ስላለው ተርጉሞ ወይም የምክር ቤቱ ውሳኔ የሚፈጥንበት ሁኔታ ካለ ተባብሯቸው፣ ወደሚቀጥለው ዓመት ከመተላለፉ በፊት ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ዶ/ር መረራ በክርክር መቃወሚያቸው ምክንያት ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ለትርጉም መላኩን አስታውሶ፣ የመቃወሚያ ሐሳባቸውን ለማንሳት ፈልገው ከሆነ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡ የዶ/ር መረራ ጠበቆች ተመካክረው ምላሽ ሲሰጡ መቃወሚያ ያቀረቡት ሕጉ በሚፈቅድላቸው መሆኑን በመጠቆምና ፍርድ ቤቱም ትዕዛዝ እንደሰጠበት ተናግረው፣ መቃወሚያቸውን እንደማያነሱ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም ዶ/ር መረራ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንኳን ሳይሰጡ እየተጉላሉ መሆኑን ገልጸው፣ ጉዳዩ በአጭር ቀናት ውስጥ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ መቃወሚያችሁን አንሱ የሚል ጥያቄ አለማቅረቡን ገልጾ፣ እሳቸው በራሳቸው ተነሳሽነት መቃወሚያቸውን እያነሱ ስለመሆናቸው ለማወቅ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዶ/ር መረራም ሆኑ ሌላ ተከሳሽ እንዲመላለስና እንዲጉላላ ፍላጎት እንደሌለው በመንገር፣ መዝገቦችን የሚያስተናግደው ክስ በተመሠረተበት ጊዜ (ዕድሜ) ቅደም ተከተል ከመሆኑ አንፃር የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ መጠበቁ ለተከሳሹም ሆነ ለፍርድ ቤቱ ጥቅም ስላለው፣ ለጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. መሸጋገሩ የግድ መሆኑን በማስረዳት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የዶ/ር መረራ ጠበቃ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም፣ የጥብቅና ፈቃድና ውክልና እያላቸው ማረሚያ ቤት ደንበኛቸውን እንዳይጎበኙና እንዳያነጋግሩ እንደከለከላቸው ላቀረቡት ጥያቄ፣ ማረሚያ ቤቱ እንዲያገናኛቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ዘገባው ይሪፖርተር ነው።

የዶ/ር መረራ ጉዳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትርጉም እንዲሰጥበት ትእዛዝ ተሰጠ

የእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና መዝገብ ለዛሬ የተቀጠረው ከዚህ ቀደም በቀረበው መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ነበር። በመሆኑም ዛሬ – ሰኔ 30/2009 – ዶ/ር መረራ ጉዲና በተመሰረተባቸው 3ት ክሶች ላይ ያቀረቧቸው መቃወሚያዎች ላይ 19ኛው ወንጀል ችሎት ከፊል ብይን ሰጥቶበታል። ችሎቱ፣ ዶ/ሩ ያቀረቡትን ክሱ እንዳይንጓተት ከሌሎቹ በሌሉበት ከተከሰሱት ሶስት ተከሳሾች ይነጠልልኝ የሚለውን መቃወሚያ ጨምሮ ሌሎቹን መቃወሚያዎች በሙሉ ውድቅ ሲያደርግ አንዱን ግን ለትርጉም ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ለትርጉም መላኩን ተናግሯል።

dr-merera-gudina-aau

ዶ/ር መረራ ጉዲና

በእነዶ/ር መረራ መዝገብ የተከፈተው ክስ ላይ አቃቤ ህግ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን በመጥቀስ፣ የምስክሮች ሥም ሳይጠቀስ የቀረ ሲሆን፣ ይህ በሥራ ላይ ያለው የሥነ ስርዓት ሕግ ተከሳሾች የሚቀርብባቸውን ማስረጃ እና ምስክር የማወቅ መብት አላቸው ከሚለው ጋር የሚጋጭ በመሆኑ እንዲተረጎም ወደፌዴሬሽን ምክር ቤት ተልኳል። የተከሳሹ ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሳ በበኩላቸው “እኛ የጠየቅነው፣ ደንበኛችን ባልተከሰሱበት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ የምስክር ጥበቃው አንቀፅ ሊጠቀስባቸው አይገባም ብለን እንጂ ትርጉም ያስፈልጋል ብለን አይደለም” ብለው ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ዶ/ር መረራም መልእክት አለኝ በማለት የሚከተለውን ለዳኞች ተናግረዋል፣ “የተመሰረተብኝ ፖለቲካዊ ክስ ነው። መንግስት ይዞ የተነሳው ተቃዋሚዎችን በራሱ የተበላሸ አስተዳደር ጥፋት ጉዳይ መወንጀል ስለሆነ እንጂ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ በጠየቀበት ጉዳይ ነው የተከሰስኩት። የተከሰስኩት፣ ለኦሮሞ ሕዝብ መብት በመታገሌ ነው። የተከሰስኩት ለኢትዮጵያ ሕዝብ መብት በመታገሌ ነው። የተከሰስኩት ለእኩልነት እና ሁላችንንም እኩል ለሚመለከት ስርዓት በመታገሌ ነው። የተከሰስኩት ሀቀኛ የፍትህ ስርዓትና የፌዴራል ስርዓት እንዲኖር በመታገሌ ነው። ዳኞች እስካሁን ካላነበባችሁ፣ የአቤ ጉበኛን አልወለድም እና የበአሉ ግርማን ኦሮማይ አንብቡ። ሊወድቅ እየደረሰ መንግስት የሚሰራውን ሥራ የሚያስረዱ መፅሃፍት ናቸው።”

ዳኞች መዝገቡን ለሐምሌ 25/ 2009 የተቀጠሩ ሲሆን፤ በሚቀጥለው ቀጠሮ ችሎቱ የምስክሮች ዝርዝር መገለፅ አለበት በሚል ክሱ እንዲሻሻል ወይም የለበትም በሚል የቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለማድመጥ ቀጠሮ ይይዛል ተብሎ ይጠበቃል።

EHRP

ዶ/ር መረራ ጉዲና ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ ተደረገባቸው

(አዲስ ሚዲያ) ባለፈው የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ. ም. በነበረው ቀጠሮ ዶ/ር መረራ ጉዲና በጠበቃቸው አማካኝነት የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጥያቄ አቅርበው ነበር። በዚህም ምክንያት የካቲት 30 ቀን 2009 ዓ. ም. አቃቤ ህግ ባቀረበው የዋስትና ጥያቄ ላይ ያለውን ተቃውሞ አቅርቦ፤ ለመጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ. ም. ተይዞ የነበረው ቀጠሮ በዋስትናው ጉዳይ ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር።

Dr.Merera Gudina

ዶ/ር መረራ ጉዲና

ዳኞች በሁለቱም ወገን የቀረበውን ክርክር መመርመራቸውን ገልፀዋል፥ የዋስትና መብት በህገ መንግስቱ የተደነገገ ቢሆንም ፍፁም መብት ሳይሆን በህግ አግባብ ሊገደብ የሚችል እንደሆነ ጠቅሰው ዶ/ር መረራ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ከዚህ አግባብ መታየት ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዳኞች በማስከተልም የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ-ስርዐት አንቀፅ 63 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ “ማንኛውም የተያዘ ሰው የተከሰሰበት ወንጀል የሞት ቅጣትን ወይም አስራ አምስት አመት ወይም በላይ የሆነ ፅኑ እስራት የማያስቀጣ ከሆነ እና ወንጀል የተፈፀመበት ሰው በደረሰበት ጉዳት የማይሞት የሆነ እንደ ሆነ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ወረቀት አስፈርሞ መልቀቅ ይችላል፡፡” እንደሚል ጠቅሰው፤ ዶ/ር መረራ ላይ የቀረበባቸው የመጀመሪያ ክስ (ወንጀለኛ መቅጫ አንቀፅ 32፣ 38 እና 238) የሚያስቀጣው የእድሜ ልክ እስራት ወይም የሞት ቅጣት በመሆኑ የዋስትና መብት እንደማይፈቀድላቸው ገልፀው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ አዘዋል።

ዶ/ር መረራም የዋስትና መብት እንዳልተፈቀደላቸው ከሰሙ በኋላ

“1ኛ.ከእነ ጄኔራል መንግስቱ ንዋይና ጄኔራል ታደሰ ብሩ ዘመን ጀምሮ ከአንድ ትውልድ በላይ ገዳዮችን፣ ሟቾች፣ አሳሪዎችና ታሳሪዎች በበዙበት የሃገራችን የፓለቲካ አላማ ውስጥ በመቆየት አንድ ከሆዱ በላይ ለሃገሩ የሚያስብ ምሁር ማድረግ እንዳለበት ሁሉ ከአርባ አምስት ዓመታት በላይ ለሃገሬ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ መታገሌ እየታወቀ ወደ ጎን መገፋቱ ፤
2ኛ. ለሁላችንም የምትሆንና በእኩልነት የምታስተናግደን፣ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ነፃ የፍትህ ስርአት በሃገራችን እንዲሰፍን ላለፉት 25 አመታት በመታገሌ፤ መከሰሴ አንሶ የሃገሪቱ ፓርላማ አባል ጭምር የነበርኩ ሰው ለተራ ወንጀለኛ የሚፈቅድ የዋስ መብት በመከልከሌ የተሰማኝ ጥልቅ ሃዘን ለራሴ ብቻ ሳይሆን እኛም ሆነ ልጆቻችን በሰላም ይኖሩበታል ለምንለው መከረኛ ሃገራችን አላልፍለት ብሎ ሲታመስ ለሚኖረው መከረኛ ህዝባችን ጭምር መሆኑን እንዲታወቅልኝ ነው።” ሲሉ ተናግረዋል።

በመጨረሻም በክሱ ላይ የሚቀርብ መቃወሚያ ለመቀበል ለሚያዚያ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል። የተቀሩት ተከሳሾችን በተመለከተ በጋዜጣ እንዲወጣ የታዘዘው የጥሪ ማስታወቂያን ለማየት ለመጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ. ም. የተያዘው ቀጠሮ እንደተጠበቀ መሆኑን በመግለፅ በዕለቱም ዶ/ር መረራ መቅረብ እንዳለባቸው ፍርድ ቤቱ ሲናገር ተደምጧል።

%d bloggers like this: