Daily Archives: November 26th, 2015

የዞን 9 ብሎገሮች የ2015 የዓመቱን የፕሬስ ነፃነት ሽልማት ተቀበሉ

በአሜሪካ ኒዮርክ ከተማ ዋና ቢሮውን ያደረገው ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (Committee to Protect Journalists) በዘንድሮው የ2015 የዓመቱ የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ላበረከቱት አስተዋፅዖ ኢትዮጵያውያኑ ዞን 9 ብሎገሮች ሽልማት ተቀበሉ፡፡ በስፍራው ማክሰኞ ህዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በተከናወነው ምሽት የዞን 9 አባላት መካከል እንዳልካቸው ኃይለሚካኤል እና ሶሊያና ሽመልስ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡

CPJ Zone 9

ሀገር ቤት የሚገኙት ቀሪዎቹ የዞን 9 አባለት ከአንድ ዓመት እስር ቆይታ በኋላ ቢለቀቁም ከሀገር እንዳይወጡ የጉዞ እገዳ የተጣለባቸውና የጉዞ ሰነድ የተነጠቁም እንዳሉ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ለፕሬስ ነፃነት በሀገሪቱ ውስጥ ላበረከቱት አስተዋፅዕ ሲፒጄን ጨምሮ መቀመጫውን በፈረንሳይ ፓሪስ ያደረገው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የዓለም አቀፍ ተሸላሚ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በዕለቱ በእንግድነት የተገኘችው በቅርቡ የተፈረደባትን እስር አጠናቃ ከእስር የወጣችው ርዕዮት ዓለሙ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላታል፡፡ በያዝነው ዓመት የሲፒጄ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ከኢትዮጵያውያኑ ዞን 9 በተጨማሪ ሶሪያዊ እና ማሌዥያዊ ጋዜጠኛ እና አክቲቪስቶችም ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በተመሳሳይ ከ አምስት ዓመት በፊት የቀድሞው የአውራምባ ታየምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ዳዊት ከበደ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ ሲፒጄ ዓለም አቀፍ የሃዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲሆን፤በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት በፕሬስ ነፃነት እና በጋዜጠኞች ላይ የሚወስደውን አፈና አጥብቆ በመኮነን ይታወቃል፡፡

የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከአስመራ የትግል ሜዳ ወደ አውሮፓ መዲና ቤልጀም ብራሰልስ መጠራት

ብስራት ወልደሚካኤል

ፕሮፌሰሩ ለረቡዕ ህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. (December 2, 2015) ከአስመራ ወደ ቤልጄየም ብራሰልስ የተጠሩት በሀገራችን ኢትዮጵያ ድርቅን ተከትሎ በተከሰተው ፖለቲካዊ የፖሊሲ ውድቀት ወለድ ርሃብ ጉዳይ ላይ ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ንግግር፣ ምክክር እና ውይይት ለማድረግ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የኢህአዴግ የ11 በመቶ የቁጥር ኢኮኒሚ ዕድገት ጋጋታ ገደል የከተተውና በምግብ ራሳችንን ችለናል መዝሙር ከአዳራሹ ነፋስ እንደወሰደው የሚያሳብቀው ከ15 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በርሃብ አለነጋ ከመገረፍ አልፎ አስቸኳይ የምግብ ርዳት እንደሚያስፈልገው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅቶች እና የተባበሩት መንግሥታት ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሄንን እውነታ ለመደበቅ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ለማስተባበልና በርሃቡ ወደተጎ ዜጎች አካባቢ ሚዲያ ድርሽ እንዳይል እና እንዳይዘገብ በውስጥ መመሪያ መተላለፉንም ከሰማን ሰነበትን፡፡

dr-berhanu-Nega

ይሄ ሁሉ የራስን የጥፋት ገመና ለመሸፈን ሲባል ህዝብ ርሃቡ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ አይደለም ሲባል ለሀገሬው ዜጋ በቋንቋው ሲነገር፤ ለዓለም አቀፍ ለጋሽ ሀገሮች ደግሞ በእንግሊዘኛ በሀገሪቱ ከፍተኛ የርሃብ አደጋ መከሰቱን እና በሀገሪቱ የእርዳታ ማስተባበሪያ የጠገኘው እህል ከአንድ ወር እንደማያልፍ በመግለፅ ተማፅኖውን ማሰማቱን ቀጥሏል፡፡ ይህንን ስንሰማ የኢህአዴግ መንግሥት አስተዳደር ኃላፊነቱ ለነጮች ነው ወይስ ለኢትዮጵያውያን የሚል ጥያቄ ቢያጭርም ከተለመድ የተለየ ነገር ግን የለም፡፡ ለዓመታት የተለመደ የመረጃ (ዳታ) ጋገራ መግለጫና ፕሮፖጋንዳ በተጨማሪ በግልፅ መረጃ ለማፈን ከፍተኛ በጀት መድቦ መንቀሳቀስ ከጀመረ እነሆ ከ10 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ልዕለ ኃያሏ አሜሪካም ብትሆን ከስርዓቱ ያላትን የፀጥታ ጉዳይ ትብብር (ወታደሮችን ለአላስፈላጊ እልቂት ማገዳ ካላት ስምምነት) አኳይ እንደ ጥሩ አጋር ብትቆጥርም የስርዓቱን አምባገነንነት፣ ዘረኛ አገዛዝ፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት አለመኖር፣ የፍትህ እጦት፣ ሙስና እና ተጠያቂነት የሌለው አሰራር የሚከተለው ስርዓት እንደሆነ ልትሸሽገው አልቻለችም፡፡

EU

ይሁን እንጂ የአውሮፓ ህብረት የተለመደ ሰብዓዊ እርዳታውን በስሱም ቢሆን መለገሱን ባያቆምም የምንጊዜም የስርዓቱ ቀኝ እጅ የሆኑት እንግሊዝ፣ ጣሊያን እና አየርላንድ እንደድሮ ለስርዓቱ ሰዎች ፊት መስጠቱን የቀነሱ ይመስላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን በሚመለከት በአውሮፓ ህብረት አሊያም በአውሮፓ ኢኮኖሚ ቅንጅት የጋራ አባል ሀገሮች በኩል ውሳኔ እንዲያልፍ እየተደረገ መሆኑን እየታዘብን ነው፡፡ ወቅታዊውን ርሃብ ለማስታገስና ለተጎዱ ወገኖች የሚደረው ሰብዓዊ እርዳታ እንኳ እንደቀድሞ በቀጥታ ለመንግሥት ከመስጠት ይልቅ በእርዳታ መልክ የተሰጠው ገንዘብ በሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች በኩል በቀጥታ ለተጎጂዎች እንዲደርስ የሚያስችል አሰራር እየተከተሉ እንደሆነ የስርዓቱ አጋር አሜሪካ እና በቅርቡም ስውድን የወሰደችው እርምጃ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ስርዓቱ በተለያዩ ለጋሽ ሀገሮች እንኳ እምነት እንደታጣበት እና የተለመደው የመረጃ ጋገራ ሪፖርትና ጋጋታ ፋይዳቢስ መሆኑን የተገነዘቡ ይመስላል፡፡

እነሆ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያውን ርሃብ በተመለከተ ህዝባዊ ዓመኔታና ቅቡልነት ባይኖረው ኃላፊነት ያለበት መንግሥት እያለ ስርዓቱን ለመገርሰስ ከሚታገሉት መካከል ተዓማኒና ትክክለኛ መረጃና ትንታኔ ይሰጣሉ ተብለው ከታመኑት መካከል በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አማካኝነት ከአስመራ የትግል ሜዳ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተጋብዘዋል፡፡ በርግጥ ፕሮፌሰሩ ካላቸው የፖለቲካ ስብዕና በተጨማሪ በሙያቸው ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ባለሙያና ተመራማሪ እንደመሆናቸው መጠን በስፍራው መጋበዛቸው የህብረቱ ትክክለኛ ምርጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ የስርዓቱን ሰዎች የበለጠ ምክንያታዊ መሸሸጊያ የሚያሳጣ ወቅታዊ የመረጃ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የሚገርመው በኢትዮጵያ ስም ስርዓቱን ወክሎ በቤልጀየም ከፍተኛ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እያሉ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ መረጃና ትንታኔ እንዲሰጡ ከበረሃ የትግል ሜዳ የፕሮፌሰሩ መጋበዝ ለስርዓቱ ትልቅ ራስምታት ነው፡፡ ምክንያቱም ፕሮፌሰሩን እና የሚመሩትን የፖለቲካ ድርጅትና አባላት በሽብርተኝነት ለማስፈረጅ ለዓመታት በተለመደ የመረጃ ጋገራ ቢሞከርም በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ተቀባይነት አላገኘምና፡፡

በተለይ በመረጃ እና ሐሳቡን ለመግለፅ ለታፈነው የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ አጋጣሚ ሲሆን፤ ለፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ለሚመሩት ድርጅት እንደ አንድእመረታ ሊታይ ይችላል፡፡ እንደ አንዳንድ የስርዓቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጥቆማ ከሆነ መንግሥት ርሃቡን ከሀገሬው ሰው በመደበቅ ለጋሽ ሀገራት በተማፅኞ በማጨናነቅ ዕርዳታቸውን በጥሬ ገንዘብ ወይም ዶላር እንዲሆን እየሰራ እንዳለ እና ለዚህም ያቀረበው ምክንያት ገንዘቡ ከተሰጠኝ ከሀገር ውስጥ ነጋዴዎች እህሉን ራሴ ገዝቼ በማከፋፈል ጊዜና ጉልበት መቆጠብ እችላለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡ ይህ ለተጎጂዎች ታስቦ ሳይሆን መንግሥት በሀገሪቱ ከደረሰበት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ አጋጣሚውንም እንደ ጥሩ ዕድል ሊጠቀምበት እንዳሰበና እስካሁንም እንዳልተሳካለት ለስርዓቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተጠቁሟል፡፡

በአሁን ወቅት ከአስከፊው ርሃብ በተጨማሪ በሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመከሰቱ የተለያዩ አስመጪዎች እና ኢንዱስትሪዎች ለአብነትም ቴክኖ ሞባይል የስልክ መገጣጠሚያን የመሳሰሉት ስራ ማቆማቸውም መነገር ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በዚህ ሁሉ የስርዓቱ አጣብቂኝ ውስጥ ፕሮፌሰሩ የበለጠ ተዓማኒነትና ተቀባይነት አግኝነተው በአውሮፓ ህብረት መጋበዛቸው በቀጣይ ምን ሊያሳየን ይሆን የሚለውን ወደፊት አብረን የምናየው ነው ሚሆነው፡፡

አዲሱ ማስተር ፕላን አሁንም ተቃውሞ ቀስቅሷል

አዲስ አበባን ከሌሎች አጎራባች ከተሞች በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር በሚል በመንግሥት ይፋ ባደረገው አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ከትናንት ጀምሮ በድጋሚ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡

AA new masterplan protesting

በተለይ በምዕራብ ሸዋ አምቦ፣ ጊኒጪ እና ምዕራብ ወለጋ ተቃውሞው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በተቃውሞው ከተሰለፉት መካከል በመንግሥት በተወሰደ ርምጃ በምዕራብ ሸዋ ድሬ ኢንጪኒ አካባቢ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንዳሉም መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በዋናነት ተቃውሞን የቀሰቀሰው አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን ያከተተ በመሆኑ እና የዞኑን እና የክልሉን ጥቅም እንዲሁም ገበሬዎችን ያለምንም በቂ ካሳና ቦታ በማፈናቀል ለጎዳና ህይወት ይዳርጋል የሚሉ ሐሳቦች እንደሚገኙበት የተጠቆሙ ሲሆን፤ ይህንን ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ ኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅት አባል ከሆነው ከኦህዴድ አመራር አባላት ከመፅደቁ ውጭ ወደ ህዝብ ያልወረደና ለምክክርም እንዳልቀረበ ታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት የዚህ ማስተር ፕላን ተቋውሞው በ2006 ዓ.ም. በመንግሥት በተወሰደ እርምጃ በርካታ ተማሪዎች እና የተቃውሞ ታዳሚዎች ግድያ ከቆመ በኋላ ድጋሚ ማገርሸቱ ተሰምቷል፡፡

 

AA masterplan protesting

በአንዳንድ ከተሞች የመኪና መንገዶች የተዘጉ ሲሆን፤ በተቃውሞው የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችም መካተታቸው ታውቋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ምንም የተሰጠ ማብራሪያም ሆነ አስተያየት የለም፡፡

የሳውዲ ባለሃብት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ቅሬታ ማሰማት ጀመሩ

ነብዩ ሲራክ

* “በኢትዮጵያ በደልና ዘረፋ ተፈጸመብን !” ባለሃብቱ!
* ” ቅሬታ ውንጀላው መሰረት ቢስ ነው ” የኢትዮጵያ ዲፕሎማት

ታዋቂው የሳውዲ ጋዜጣ አረብ ኒውስ ‪#‎Arabnews‬ የኢትዮጵያ መንግስት አንዳንድ ባለ ኃላፊዎች መሬታቸውን እየተቀሙ በደልና ዘረፋ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ሞሀመድ አልሸህሪ የተባሉ ሳውዲ ባለ ሃብት አስታውቀዋል። እኒሁ ባለሃብቶችን መርተው ወደ አፍሪካና ወደ ኢትዮጵያ ከአመታት በፊት የዘለቁት ባለ ሃብት Investor በኢንቨስትመንት ፈቃድ ወደ ኢትዮጵያ ያስገቧቸው ንብረቶችን ለመውረስ በእርሳቸውና በጓደኞቻቸው ላይ የወንጀል ክስ አንደተመሰረተባቸው ማስታወቃቸውን አረብ ኒውስ ዘግቧል ። ቅሬታ አቅራቢው ሳውዲ ባለሃብት ሞሃመድ አልሸህሪ ለአረብ ኒውስ ጋዜጣ እንዳስታወቁት ሙስናው የከፋ እየሆነ መምጣቱን በመጠቆም ሳውዲ ባለሃብቶች በማመሳሰል ( Forgery) ወንጀል ሳይቀር ተወንጅለው ለስራ ያስገቧቸውን እቃዎች መመለስ እንዳልቻሉ አስረድተዋል።

Ethio farmer

ከስድስት አመት በፊት ጀምሮ በእርሻ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሳውዲ ባለሃብቶች በመንግስት የተገባላቸው ቃል በተግባር ባለመፈጸሙ 50 % እጅ ያህሉ ከኢትዮጵያ ለቀው መውጣታቸውን እኒሁ ቅሬታ አቅራቢ ሳውዲ ባለ ሃብት ተናግረዋል ። ” በደረሰባቸው በደል ተማረው ሀገሪቱን ለቀዋል !” ስላሏቸው ባለሃብቶች ሲያስረዱም የቻሉት ሸጠው መውጣታቸውን አልደበቁም። መሸጥ ያልቻሉትና ያልቻሉት እቃቸውን ትተው የወጡት ግን ተመልሰው እቃቸውን ቢጠይቁ ” በማናውቀው ወንጀል እንያዛለን !” በሚል ስጋት ባለ ሃብቶች ኢትዮጵያ ላይ ወረታቸውን በትነው መቅረታቸውን ሞሃመድ አልሸህሪ ለአረብ ኒውስ አስታውቀዋል ።
ከዚህ ቀደም ተሰምቶ የማይታወቀውን የሳውዲ ባለ ሃብቶች ቅሬታና ብሶት ለታዋቂው የሳውዲ ጋዜጣ ለአረብ ኒውስ በአደባባይ ያጋለጡት ባለሃብቱ ሞሃመድ አልሻህሪ ቅሬታቸውን ለሁለቱም ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቢያቀርቡም እስካሁን ምነም አይነት ምልሽ እንዳላገኙ ጠቁመዋል !
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዜናውን ማስፈንጠሪያ Link በፊስ ቡክ የፊት ገጼ ላይ እንደለጠፍኩ ” እንዴት ይህን ያልተጨበጠ አደገኛ መረጃ ሊንክ Link ይዘህ ትለጥፋለህ? ” በማለት የጅዳ ቆንስል ዲፕሎማት ቆንስል ሸሪፍ በስልክ ቅሬታቸውን ግልጸውልኛል ። ለሚሊዮኖች በአለም ዙሪያ የተሰራጨውን መረጃ ማስተላለፌን በአግራሞት የተመለከቱትና በጅዳ ቆንስል የኢኮኖሚ ኋላፊ አቶ ሸሪፍ ኼሪ በዜናው ዙሪያ ዘርዘር ባለ መልኩ አነጋግረውኛል ። እኔም ያቀረብኩት መረጃ ከአረብ ኒውስ ማግኘቴን ደግሜ በማስረዳት ማሰተባበያ ማቅረብ እንጅ የወጣውን መረጃ አታሰራጩ ፣ አለያም አትለጥፉ ማለት እንደ ሚከብድ አሳውቄቸዋለሁ !
ቆንስል ሸሪፍ በመጨረሻም ” አረብ ኒውስ ጋዜ ለ ያወጣው መረጃ የተዛባ በመሆኑ አስፈላጊው ሁሉ እርምጃ ይወሰዳል ” በማለት “ፍጹም መሰረተ ቢስ ነው ! ” ላሉትን የተሰራጨ መረጃ ምላሽ ለመስጠት በሪያድ የኢትዮጵያ ኢንባሲ በኩል አስፈላጊ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸውልኛል !
ቸር ያሰማን !

%d bloggers like this: