Tag Archives: Oromia Regional state_Ethiopia

በኦሮሚያ ክልል ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በነበረው ተቃውሞ ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች ይፋ አደረገ

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች የሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ ከህዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከ400 በላይ የሚሆኑ ሰልፈኞችን የገደሉ ሲሆን ከአስር ሺህ በላይ የሚቆጠሩትን ደግሞ ማሰራቸውን አስታውቋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ “የኢትዮጵያ መንግስት የተፈጸሙ ግድያዎችን፣ እስራቶችንና ሌሎች የመብት ጥሰቶች በአስቸኳይ ተአማኒነት ያለውና ገለልተኛ የሆነ ማጣሪያ እንዲካሄድ ድጋፍ ማድረግ አለበት።” ሲል ባለ 61 ገፅ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

HRW logo

ድርጅቱ ሰኔ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው ባለ 61 ገጽ ሪፖርት “ጭካኔ የተሞላበት አፈና’ – የግድያ እና የእስራት ምላሽ፤ ለኢትዮጵያ የኦሮሞ ተቃውሞ” የሚል ነበር፡፡ መንግሥትም በነበረው ተቃውሞ ያልተመጣጠነ ርምጃ መውሰዱን በመግለፅ ድርጊቱን አውግዟል፡፡ ሪፖርቱ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ እንዲሁም ሀሳባቸውን በነጻነት በሚገልጹ ዜጎች ላይ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን፣ ከ125 በላይ የሚሆኑ የተቃውሞ ሰልፎች ተሳታፊዎችን፣ ጉዳዩን በአንክሮ ሲከታተሉ የቆዩ ግለሰቦችን፣ በተለያዩ ጊዜያት የመብት ጥሰት የተካሄደባቸውና ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ያካተተ ቃለ መጠይቅ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡

በመንግሥት የተቋቋም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮምሽን ይህንን የኦሮሚያ ክልል ተቋውሞ ተከትሎ በተወሰደ ርምጃ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 173 ብቻ መሆናቸውን እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተወሰደው ርምጃም “ተገቢና ተመጣጣኝ” ነው ሲሉ ኮሚሽነሩ ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ሰኔ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. “ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” እና ለጋዜጠኞች ገልፀዋል፡፡ ኮሚሽነሩ ተገቢና ተመጣጣኝ ያሉት ርምጃ የተወሰደው በመከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ እና በኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል መሆኑንም ለጋዜጠኞች ጠቁመዋል፡፡

Oromo Protest_Ethiopia

መንግሥታዊ ያልሆነው ሀገር በቀል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ፤ በኦሮሚያ ክልል በነበረው ተቃውሞ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተወሰደው ርምጃ ተገቢና ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ቀደም ሲል ይፋ ባደረገው ዝርዝር ሪፖርት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በነበረውን ተቃውሞ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ፤ ሀገር በቀል የሆነው የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ባለፈው መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በ140ኛው የተቋሙ ሪፖርት “የኦሮሚያ ክልል በ18 ዞኖች እና በ342 ወረዳዎች የተከፋፈለ ሲሆን ሰመጉ ከ9 ዞኖች ውስጥ በ33 ወረዳዎች ብቻ ባደረገው የመስክ ምርመራ ባገኘው ውጤት መሰረት 103 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 57 ሰዎች በጥይት የመቁሰል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡” ብሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተገደሉትና ከቆሰሉት በተጨማሪ በ22 ሰዎች ላይ ማሰቃየት እና ድብደባ መፈፀሙን፣ 84 ሰዎች መታሰራቸውን እንዲሁም 12 ሰዎች የደረሱበት ወይም ያሉበት አለመታወቁንም በመግለፅ ሪፖርቱን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

ሙሉውን የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት እዚህ https://www.hrw.org/news/2016/06/15/ethiopia-protest-crackdown-killed-hundreds  ያገኙታል፡፡

በኦሮሚያ ለግጭት ምክንያት የነበረው የከተሞች አዋጅ ሦስት አንቀጾች ተሰረዙ

በውድነህ ዘነበ

Fekadu Tesema,Oromia PR

በኦሮሚያ ክልል ሕዝባዊ ጥያቄ የተነሳበት የከተሞች አዋጅ ሦስት አንቀጾች ተሰረዙ፡፡ እነዚህ አወዛጋቢ የተባሉ አንቀጾች ከተሰረዙ በኋላ ባለፈው ሳምንት የተሰበሰበው ጨፌ ኦሮሚያ አዋጁን አፅድቋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ተነስቶ ለነበረው ረብሻ የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላንና የኦሮሚያ ከተሞች አዋጅ ምክንያት እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የማስተር ፕላኑን ተግባራዊነት ማቆሙን በወቅቱ በይፋ የገለጸ ሲሆን፣ ለውዝግቡ መባባስ ምክንያት የነበሩ የኦሮሚያ ከተሞች አዋጅ ሦስት አንቀጾች እንዲሰረዙ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የተሰረዙት ሦስት አንቀጾች ከተሞችን መቀላቀል፣ የተቀላቀሉ ከተሞች ስያሜና ራዲዮ ፖሊ (የክልሉን ትልልቅ ከተሞች በተመለከተ) የሚያትቱ ናቸው፡፡ የኦሮሚያ ከተሞች አዋጅ አንድ የክልሉ ከተማ በዙሪያው ካሉት አነስተኛ ከተሞችን (ሳተላይት) በመያዝ እንደ አዲስ ይደራጃል ይላል፡፡
ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የሆነው የኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ ያሉ ከተሞችን ከአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) ጋር ለመቀላቀል ነው የሚሉ ግምቶችን ከተለያዩ ወገኖች በመስጠቱ ነው ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል የክልሉ ከተሞች ሲቀላቀሉ አንድ ስም የግድ ይመርጣሉ፡፡ ይህ ሁኔታ የክልሉን ታሪክና ባህል ያጠፋል፣ ልዩ ዞኑን ከአዲስ አበባ ጋር ለመቀላቀል ያለመ ነው የሚል ትንታኔ አሁንም በመስጠቱ ለችግሩ መንስዔ ነው ተብሏል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የራዲዮ ፖሊ ትንታኔ ነው፡፡ የአገሪቱ መዲና አዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥት ከተማ ነች፡፡ የክልል ከተሞች ባህር ዳር፣ መቐለ፣ ሐዋሳ፣ ጅማ፣ አዳማና የመሳሰሉት ከተሞች በራዲዮ ፖሊ ምድብ ይገኛሉ፡፡
የፌዴራል መንግሥት ባወጣው የከተሞች ፖሊሲ ራዲዮ ፖሊ ከተሞች ከፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ታቅዷል፡፡

የኦሮሚያ ክልል በከተሞች አዋጅ ላይ ስለ ከተሞቹ የገለጸ ሲሆን፣ ለዚህ ጉዳይ ከተለያዩ ወገኖች የተሰጠው ምላሽ ግን የኦሮሚያ ከተሞች በፌዴራል ሥር ሊገቡ ነው የሚል ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ጉዳዮች በኦሮሚያ ተከስቶ ለነበረው ደም አፋሳሽ ግጭት መንስዔ እንደነበሩ ተገልጿል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊና የካቢኔ አባል አቶ ፈቃዱ ተሰማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሕዝብ ጥያቄ በማንሳቱና የኦሮሚያ መንግሥት ሕዝብ የማይስማማበትን አንቀጾቹን ከአዋጁ ውስጥ ፍቆታል፡፡

አቶ ፈቃዱ ‹‹እነዚህ አንቀጾች ጉዳት ኖሯቸው ሳይሆን ፅንፈኞች በአሉታዊ መንገድ ጉዳዩን እጅግ ያስተጋቡት በመሆኑና እኛ ደግሞ በተገቢው መንገድ ግልጽነት ስላልፈጠርን የተፈጠረው ብዥታ ከፍተኛ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እነዚህ ጉዳዮች የሕዝቡን ጥቅም የሚጎዱ ሆነው አይደለም፤›› በማለት ክልሉ ሐሳቡ የሕዝብ እስከሆነ ድረስ የሕዝብን ጥያቄ እንደሚቀበለው አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡

እነዚህ አንቀጾች ከመሰረዛቸው በተጨማሪ በሌሎች ሁለት ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ መደረጉን አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡ ፀድቆ በነበረው የከተሞች አዋጅ የክልሉ ከተሞች የሚሰበስቡትን ፋይናንስ ለራሳቸው ይጠቀማሉ የሚል አንቀጽ ነበር፡፡ ነገር ግን ገቢ የማመንጨት አቅም የሌላቸውን ከተሞች ስለሚጎዳ፣ በማዕከል ደረጃ በጀት ቢከፋፈል የተሻለ መሆኑ ስለታመነበት ማሻሻያ ተደርጓል፡፡

ቀደም ሲል በክልሉ ከተሞች በላይኛው የአስተዳደር እርከንና በቀበሌ መካከል ራሱን የቻለ የመንግሥት መዋቅር አልነበረም፡፡ ቀደም ብሎ ፀድቆ በነበረው አዋጅ የወረዳ መዋቅር እንዲከፈት ተደንግጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ከወረዳ ይልቅ ክፍለ ከተማ የተሻለ መዋቅር ነው ተብሎ ማሻሻያ መደረጉን አቶ ፈቃዱ ገልጸው፣ ትልልቅ ከተሞች የክፍለ ከተማ መዋቅር እንዲመሠርቱ በአዲሱ አዋጅ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡

ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሁለት የስራ ሀላፊዎችን ከሃላፊነታቸው አነሳ

OPDO

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከየካቲት 25 ጀምሮ ለአምስት ቀናት በአዳማ ከተማ ባካሄደው ጉባኤ ሁለት የስራ ሀላፊዎችን ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ በማድረግ እና የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የስራ ሃላፊዎቹ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገው በአመራር ችግር መሆኑን አስታውቋል።

በዚህም 1ኛ የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሞቴ የስራ አስፈጻሚ አባል እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል እንዲሁም የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ዳባ ደበሌ ሲሆኑ፥ በታየባቸው የአመራር ችግር ምክንያት ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መወሰኑን እና ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባልነት ተነስተው ነገር ግን የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው እንዲቀጥሉ ወስኗል።

2ኛ የኦህዴድ እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል እና የኦሮሚያ ክልል የእርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ጀማነ ሲሆኑ፥ እስከ ቀጣዩ የድርጀቱ ጉባኤ ድርስ ከማንኛውም የድርጅት እንቅስቃሴ መታገዳቸውን ድርጅቱ ማስታወቁን ፋና ቢሲ ዘግቧል፡፡
ምንጭ፡ http://www.fanabc.com/index.php/news/item/1428

አዲሱ ማስተር ፕላን አሁንም ተቃውሞ ቀስቅሷል

አዲስ አበባን ከሌሎች አጎራባች ከተሞች በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር በሚል በመንግሥት ይፋ ባደረገው አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ከትናንት ጀምሮ በድጋሚ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡

AA new masterplan protesting

በተለይ በምዕራብ ሸዋ አምቦ፣ ጊኒጪ እና ምዕራብ ወለጋ ተቃውሞው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በተቃውሞው ከተሰለፉት መካከል በመንግሥት በተወሰደ ርምጃ በምዕራብ ሸዋ ድሬ ኢንጪኒ አካባቢ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንዳሉም መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በዋናነት ተቃውሞን የቀሰቀሰው አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን ያከተተ በመሆኑ እና የዞኑን እና የክልሉን ጥቅም እንዲሁም ገበሬዎችን ያለምንም በቂ ካሳና ቦታ በማፈናቀል ለጎዳና ህይወት ይዳርጋል የሚሉ ሐሳቦች እንደሚገኙበት የተጠቆሙ ሲሆን፤ ይህንን ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ ኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅት አባል ከሆነው ከኦህዴድ አመራር አባላት ከመፅደቁ ውጭ ወደ ህዝብ ያልወረደና ለምክክርም እንዳልቀረበ ታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት የዚህ ማስተር ፕላን ተቋውሞው በ2006 ዓ.ም. በመንግሥት በተወሰደ እርምጃ በርካታ ተማሪዎች እና የተቃውሞ ታዳሚዎች ግድያ ከቆመ በኋላ ድጋሚ ማገርሸቱ ተሰምቷል፡፡

 

AA masterplan protesting

በአንዳንድ ከተሞች የመኪና መንገዶች የተዘጉ ሲሆን፤ በተቃውሞው የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችም መካተታቸው ታውቋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ምንም የተሰጠ ማብራሪያም ሆነ አስተያየት የለም፡፡

አዳማ የኤድስ ተጠቂዎች ማደርያን ወደ መቅዲ ባርና ሬስቶራንት ቀየረች?!

የትነበርክ ታደለ
ይህ የምስራች እንዳይመስላችሁ! እጅግ ዘግናኝ አሳፋሪና አሳዛኝ የሀገራችን እውነታ ነው። ከአመታት በፊት ሀገር በኤች አይቪ የደረሰባትን የጭለማ ድባብ አንረሳውም! እርግጥ አሁንም ገና ከሀዘኑ ሙሉ በሙሉ አልተላቀቅንም። በዝያ የጭለማ ዘመን፣ መፍትሄ ከሀገር ውስጥም ከውጭም ሲፈለግ፣ ወጣቱ በየቦታው ሲረግፍ፣ ቤተሰብ ሲበተን አዳማ ውስጥ አንድ ሰው ተገኘ።

መስፍን ፈይሳ (የመስፍነ ፈይሳ ኢኒሼቲቭ በጎ አድራጎት መስራች)

መስፍን ፈይሳ (የመስፍነ ፈይሳ ኢኒሼቲቭ በጎ አድራጎት መስራች)

ይህ ሰው መስፍን ፈይሳ ይባላል። መስፍን ራሱም የቫይረሱ ተጠቂ መሆኑን ይፋ አውጥቶ በመናገር የሱ ቢጤ ወገኖቹን ለመርዳት ቆርጦ ተነሳ። እሱ እንደሚናገረው ማዳበርያ ከረጢት አንገቱ ላይ አስሮ በየደጃፉ እየዞረ ምግብ እየለመነ የሰበሰባቸውን ወገኖቹን መመገብ ያዘ።

እየቆየ ጥረቱ ፍሬ አፍርቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጠውና ከ5000 ሰዎች በላይ የተረዱበት “መስፍን ፈይሳ ኢኒሼቲቭ በጎ አድራጎት” ተቋቋመ።

ይህ ተቋም አሁን “መቅዲ ባርና ሬስሮራንት ተብሎ ወጣቶች ቀንና ለሊት የሚጨፍሩበት፣ በሺሻ ጢስ የሚታጠኑበትና ህልማቸውን የሚነጠቁበት ቦታ ሆኗል።

ከሰአታት በፊት ግለሰቡ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ በለቀቀው ቪዲዮ እንዳስታወቀው በጉልበት ከሀገር እንድወጣ ካደረጉኝ በኋላ ተቋሙን አፈራርሰው አራት ሚሊየን የሚገመት ንብረት ዘርፈው ጉዳተኞቹን በትነው ህንጻውን ከኤች አይቪ መከላከያነት ወደ ማሳራጫነት አዙረውታል ብሏል።

እጅግ የሚደንቀው ደግሞ ይህ ተቋም (አሁን መቅዲ ባር) የሚገኘው ከአዳማ ዩኒቨርስቲ አጠገብ መሆኑ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ አለማቀፍ ሚዲያዎች እንደሚዘግቡት ሀገራችን ውስጥ ዝሙት በርካሽ የሚሸጥባቸው ስፍራዎች ዩኒቨርስቲዎች ባሉበት አካባቢ ነው።

በተለይ ደግሞ አዳማ ናዝሬት በዚህ ግምባር ቀደም ተጠቃሿ ናት። አንድ የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው አዳማ 230.000 ነዋሪዎች ያላት ስትሆን ከዚህም ውስጥ ካሉት ሴቶች 5000 ዝሙት አዳሪዎች ናቸው። ይህም ማለት ከመቶ አምስት ፐርሰንቱ በዚሁ ስራ የሚተዳደሩ ናቸው። ልብ በሉ ይህ ቁጥር የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን አይጨምርም።

እንግዲህ ይህንን አይነት ጉድ የተሸከመች ከተማ እንዴት ባለ አስተዳደር እጅ ብትወድቅ ነው የህዝብን ሁለንተናዊ ጤንነት ከመጠበቅ ሀላፊነቱ እየሸሸ በግለሰብ የተቋቋመ ተቋም ለማፈረስ የተደፈረው?

እጅግ በጣም የሚገርመው ደግሞ ይህ ተቋም ሲጀመር የመሰረት ድንጋይ የጣሉት በአሁን ሰአት የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት ኦቦ ሙክታር ከድር መሆናቸው ነው። (አቡነ ጳውሎስም በቦታው ነበሩ)

Mesfin Feyisa Initiative adama-nazereth

እና ምነው? ኦቦ ሙክታር አዳማ ውስጥ ምን እየተካሄደ ማወቅ አይችሉም ማለት ነው? ለአንድ ትልቅ አላማ ራሳቸው በቦታው ድረስ ሄደው መሰረት የጣሉለት ተቋም እጅግ በሚያሳፍርና በሚያዋርድ ሁኔታ ተሽቆልቁሎ ሲጠፋ ምንም አልሰሙም ማለት ነው? አዳማ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ነች! ይህንን ሳይስሙና ሳያዩ ወለጋ ጫፍ ወይም አርሲ ቦረና ስላለው እንዴት ሊሰሙ ይችላሉ? ነው ወይስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሳቸው ይሁንታ አለበት? እውነት ለመናገር መልስ ሊሰጡበት የሚገባ ጥያቄ ነው።

የአዳማ ህዝብስ ቢሆን በራሱ ጉዳይ ላይ ከሱ የተሻለ ማን ሊጠይቅለት ይችላል? ግለሰቡ እንደተናገሩት ወደዚህ ባርና ሬስቶራንት ልጆቻችሁ እየሄዱ እያያችሁ ዝም ብትሉ በልጆቻችሁ ህይወት ላይ ፈርዳችኋል።

መንግስትም ቢሆን እነ መቄዶኒያን የመሳሰሉ ወገንን ከጎዳና የሚሰበስቡ ተቋማት ነገ በተመሳሳይ መንገድ እንደማይፈርሱና ወደ ሺሻ ቤትነት እንደማይቀየሩ ምን ማስተማመኛ ይሰጠናል? ትውልድ እየጠፋ ነው! ህግ እየተጣሰ ነው! የምንፈልገውን እያጣን የማንፈልገው እየተጫነብን በዚህ ላይ ለጩሀታችን ዝምታ እየተመለሰልን ነው! ነገ አጣብቂኙ ለሀገር ነውና መቅዲ ባር በአስቸኳይ ወገኖቻችን ወደ ሚረዱበት ተቋምነት ይመለስልን! ወገን በጭፈራ ቤት አይታከምም!

%d bloggers like this: