Tag Archives: Ethiopian human rights commission

በኦሮሚያ ክልል ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በነበረው ተቃውሞ ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች ይፋ አደረገ

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች የሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ ከህዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከ400 በላይ የሚሆኑ ሰልፈኞችን የገደሉ ሲሆን ከአስር ሺህ በላይ የሚቆጠሩትን ደግሞ ማሰራቸውን አስታውቋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ “የኢትዮጵያ መንግስት የተፈጸሙ ግድያዎችን፣ እስራቶችንና ሌሎች የመብት ጥሰቶች በአስቸኳይ ተአማኒነት ያለውና ገለልተኛ የሆነ ማጣሪያ እንዲካሄድ ድጋፍ ማድረግ አለበት።” ሲል ባለ 61 ገፅ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

HRW logo

ድርጅቱ ሰኔ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው ባለ 61 ገጽ ሪፖርት “ጭካኔ የተሞላበት አፈና’ – የግድያ እና የእስራት ምላሽ፤ ለኢትዮጵያ የኦሮሞ ተቃውሞ” የሚል ነበር፡፡ መንግሥትም በነበረው ተቃውሞ ያልተመጣጠነ ርምጃ መውሰዱን በመግለፅ ድርጊቱን አውግዟል፡፡ ሪፖርቱ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ እንዲሁም ሀሳባቸውን በነጻነት በሚገልጹ ዜጎች ላይ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን፣ ከ125 በላይ የሚሆኑ የተቃውሞ ሰልፎች ተሳታፊዎችን፣ ጉዳዩን በአንክሮ ሲከታተሉ የቆዩ ግለሰቦችን፣ በተለያዩ ጊዜያት የመብት ጥሰት የተካሄደባቸውና ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ያካተተ ቃለ መጠይቅ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡

በመንግሥት የተቋቋም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮምሽን ይህንን የኦሮሚያ ክልል ተቋውሞ ተከትሎ በተወሰደ ርምጃ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 173 ብቻ መሆናቸውን እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተወሰደው ርምጃም “ተገቢና ተመጣጣኝ” ነው ሲሉ ኮሚሽነሩ ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ሰኔ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. “ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” እና ለጋዜጠኞች ገልፀዋል፡፡ ኮሚሽነሩ ተገቢና ተመጣጣኝ ያሉት ርምጃ የተወሰደው በመከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ እና በኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል መሆኑንም ለጋዜጠኞች ጠቁመዋል፡፡

Oromo Protest_Ethiopia

መንግሥታዊ ያልሆነው ሀገር በቀል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ፤ በኦሮሚያ ክልል በነበረው ተቃውሞ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተወሰደው ርምጃ ተገቢና ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ቀደም ሲል ይፋ ባደረገው ዝርዝር ሪፖርት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በነበረውን ተቃውሞ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ፤ ሀገር በቀል የሆነው የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ባለፈው መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በ140ኛው የተቋሙ ሪፖርት “የኦሮሚያ ክልል በ18 ዞኖች እና በ342 ወረዳዎች የተከፋፈለ ሲሆን ሰመጉ ከ9 ዞኖች ውስጥ በ33 ወረዳዎች ብቻ ባደረገው የመስክ ምርመራ ባገኘው ውጤት መሰረት 103 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 57 ሰዎች በጥይት የመቁሰል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡” ብሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተገደሉትና ከቆሰሉት በተጨማሪ በ22 ሰዎች ላይ ማሰቃየት እና ድብደባ መፈፀሙን፣ 84 ሰዎች መታሰራቸውን እንዲሁም 12 ሰዎች የደረሱበት ወይም ያሉበት አለመታወቁንም በመግለፅ ሪፖርቱን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

ሙሉውን የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት እዚህ https://www.hrw.org/news/2016/06/15/ethiopia-protest-crackdown-killed-hundreds  ያገኙታል፡፡

የፖለቲካ አመራሮቹ ችሎት ያለ ተከላካይ ጠበቃ ሲታይ፤ቀጣይ ቀጠሯቸው ግልፅ አይደለም

ዛሬ መስከረም 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ፒያሳ አራዳ በሚገኘው የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የፖለቲካ  ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ በዝግ ችከሎት ያለ ተከላካይ ጠበቃ ቀጠሮ መስጠቱ ተጠቆመ፡፡ የፖለቲካ አመራሮቹ አቶ ሀብታሙ አያሌው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ የአንድነት ፓርቲ ምክትል የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ አቶ አብርሃ ደስታ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህርና የአረና ፓርቲ ምክትል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዲሁም አቶ የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ከተከላካይ ጠበቆቻቸው ጋር ሳይገናኙ ከቀጠሮ ሰዓታቸው አርፍደው ከቀኑ 10 እና 11 ሰዓት ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

detained politiciansበነበረው የፍርድ ቤት ችሎት ተከላካይ ጠበቃ ደንበኞቻቸውን ህጉ በሚፈቅደው መሰረት በማዕከላዊ ሄደው መጎብኘትና መነጋገር ቢፈልጉም፤ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል “ማዕከላዊ” ፖሊስ ስላልተፈቀደላቸው ፍርድ ቤት መገኘቱ ለፕሮፖጋንዳ ካልሆነ ከህግ አግባብ ትርጉም ስለሌለው እንደማይገኙ አስቀድመው ማሳወቃቸው ተጠቁሟል፡፡ በችሎትም ቤተሰብ፣ ጋዜጠኛ፣ ዲፕሎማቶች እና ወዳጅ ዘመድ እንዳይከታተል መከልከሉም ታውቋል፡፡ የእስረኞቹ ቀጣይ ቀጠሮ መቼ እንደሆነ እስካሁን ከፍርድ ቤቱ ማግኘት ባይቻልም፤ እንደ ነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ ከሆነ የማዕከላዊ ምርመራ ኃላፊ አቶ ተክላይ ሹመት ተጠርጣሪዎቹ የተቀጠሩት ለጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲሉ፤ ሌላ ፖሊስ ደግሞ ለጥቅምት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው የሚል ጥቆማ መስጠታቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስረኞቹ እስካሁን በነበረው ምርመራ ፖሊስ ምንም ዓይነት ለወንጀል ክስ የሚያበቃ መረጃ ባለማግኘቱ፤ ወደ ኃይል እርምጃ በመሄድ ፖሊስ የሚፈልገውን ቃል እስረኞቹ ያልፈፀሙትን አስገድዶ የእምነት ቃል እንዳስፈረማቸው የማዕከላዊ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ ይሄም ለህዝቡና ለመገናኛ ብዙኃን እንዳይገለፅና ፍርድ ቤትም በቅሬታ መልክ እንዳይቀርብ ስለተፈለገ ነው ተከላካይ ጠበቆቹ እንዳይጎበኙ የተከለከሉት ሲሉ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡  በዚህም የዛሬው ችሎት ያለጠበቃ ጭምር በዝግ ችሎት መካሄዱ የተጠቆመ ሲሆን፤ የቀጠሯቸው ቀንም ከላይ ከተጠቀሰው ውጭ እስካሁን ትክክለኛውን ከፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ እንዳልተቻለ መረጃዎእ አመልክተዋል፡፡ ችሎቱን ለመታደም ወደ ስፍራው ያቀኑ ሰዎችም ፍርድ ቤቱ ግቢ ሲገቡ ከወትሮ በተለየ በፖሊሶች ከፍተኛ ፍተሻ፣ እንግልትና ወከባ እንደተፈፀመባቸው  የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ባለፈው ውድቅ ያደረገውን ጉዳይ ዛሬ ያለምንም ይግባኝ ማፅደቁ ተሰማ

ዛሬ ግንቦት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. የነበረው የፍርድ ቤት ውሎ አዲስ ክስተትን ይዞ ብቅ ማለቱ ተሰምቷል፡፡ ባለፈው ሚያዚያ 2006 ዓ.ም.ተጠርጥረው ከታሰሩ 3 ጋዜጠኞች እና 6 ብሎገሮች መካከል ዛሬ እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ የነበራቸው በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላ እና ማህሌት ፋንታሁን ቀደም ሲል የማዕከላዊ ፖሊስ ጉዳዩን ወደ ፀረ-ሽብርተኝነት የክስ ጉዳይ ለመውሰድ የጠየቀው በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፤ ዛሬ በሌላ ተቀያሪ ወንድ ዳኛ እዛው ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ባለፈው በነበረው ቀጠሮ ውድቅ የተደረገው በፀረ-ሽብርተኝነት ክስ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎ የነበፍቃዱ ፣ አቤል እና ማህሌት ሂደት ለሰኔ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
FF
በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ያቀረብንላቸው ተከላካይ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን፤ ከህግ አኳያ ፖሊስ ጉዳዩን ወደ ፀረ-ሽብርተኝነት ጠይቆ ውድቅ ተደርጎበታል፣ ስለዚህ በነበረው ውሳኔ ፖሊስ ቅር ከተሰኘ ይግባኝ ማለት እንጂ በተመሳሳይ ችሎት እና ጉዳይ ላይ በፍርድ ቤቱ ውድቅ የተደረገ ጉዳይ እንደገና ቀርቦ የፖሊስ ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ እና ተጨማሪ የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ በሚል መፈቀዱ ከህግ አግባብ ውጭ ነው፤ ይሄንንም ለፍርድ ቤቱ ብናቀርብም ተቀባይነት አላገኘም፤ ስለዚህ የህግ አካሄድ (procedure) ስህተት ታይቶበታል ሲሉ የነበረውን ሂደት ተናግረዋል፡፡ ይህን የክስ ሂደት ፖሊስ ጉዳዩን ወደ ፀረ-ሽብርተኝነት ለመውሰድ ውድቅ ያደረገችው ዳኛ ሴት እንደነበረች አይዘነጋም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የነገረ-ኢትዮጵያ ጋዜጠኛ በላይ ማናየ ፖሊስ ፍርድ ቤት ያቀረባቸውን እስረኞች ሲያወጣ፤ ለተወሰነ ጊዜ በጠበቂ የፀጥታ ኃይሎች ለጊዜው ታግቶ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ፤ ለነገ ማዕከላዊ እንዲቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ተለቋል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ የተደረገው የጋዜጠኛው እገታ ምክንያት እስካሁን አልታወቀም፡፡

%d bloggers like this: