Tag Archives: Arena Tigray Party Ethiopia

በተከሳሽ የፓርቲ አመራሮችና በአቃቂ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መካከል ያለው አቤቱታ ምላሽ አላገኘም

∙በቃል የቀረበው አቤቱታ ከድምጽ ክምችት ክፍል ጠፍቷል ተብሏል

politician prisoners

በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች እና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ ያሉ የሽብር ተከሳሾች በቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር መካከል ያለው አቤቱታ እስካሁን እልባት ሊያገኝ አልቻለም፡፡

ዛሬ ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቅአገኘሁን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች ማረሚያ ቤቱ የመብት ጥሰት እየፈጸመባቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አቤት ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዛሬ ዕለት በጉዳዩ ላይ የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪ ችሎት ቀርበው መልስ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ቀጠሮ ወቅት አቤቱታው በቃል ተሰምቶ በመቅረጸ ድምጽ ተቀድቶ እንደገና በጽሑፍ ተገልብጦ ከመልስ ጋር እንዲቀርብ ታዝዞ የነበር ቢሆንም ድምጹ ከፍርድ በቱ ድምጽ ክምችት ክፍል ሊገኝ ስላልቻለ በወረቀት ተገልብጦ መልስ እንዲሰጥበት ለማረሚያ ቤቱ አለመድረሱ ተገልጹዋል፡፡

በዚህ የተነሳም ፍርድ ቤቱ ለጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ችሎት ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ለማስቻል፣ በቀጣዩቹ ቀናት ውስጥ አቤቱታው እንደገና በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ እንዲቀርብ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ኦኬሎ አኳይ

 አቶ ኦኬሎ አኳይ

በተመሳሳይ በቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦኬሎ አኳይ የክስ መዝገብ በተከሰሱ ሰዎች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የሰጡት ምስክርነት ከድምጽ ክምችት ክፍል ስለጠፋ እንደገና በሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ድጋሜ ምስክሮቹ እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ኢህአዴግ በክልል የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ማሰርና መደብደቡን ቀጥሏል

የታሰሩ አመራሮች የአንድነት፣መኢአድ፣ ሰማያዊ እና አረና ፓር  እና የሲቪክ ተቋም አመራር ይገኙበታል፡፡  እነኚህም ከአንድነት  ከሰሜን ጎንደር  ምዕራብ አርማጭሆ አቶ አንጋው ተገኝ፣ አቶ አባይ ዘውዱ፣ አቶ እንግዳው ዋኘው እንዲሁም ከመተማ አቶ በላይነህ ሲሳይ እና አቶ አለባቸው ማሞ ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም.፤ ከበመቀሌ የአንድነት አባል የሆነው አቶ ሺሻይ አዘናው ደግሞ ጥቅምት 26 2007 ዓም ተይዘው እስካሁን ባልታወቀ ስፍራ በመንግስት ፀጥታ ኃይሎች ታፍነው መሰወራቸው ተጠቁሟል፡፡

prisonበተመሳሳይ ወቅት ሌሎች የአንድነት አመራሮች ከወረታ አቶ አለበል ዘለቀ፣ከምዕራብ ጎጃም ደጋ ዳሞት ወረዳ አቶ ጥላሁን አበበ በመንግስት ፀጥታ ይሎች ታፍነው ወዳልታወቀ ቦታ መታሰራቸው ፓርቲው አስታውቋል፡፡ ሌላው የአንድነት ፓርቲ የወላይታ ዞን አመራሮች አቶ ማሞ ጎሙ፣ አቶ ወኖ መናሳ እና አቶ አልታዬ አቦታ በመንግስት የደህንነት ኃይሎች ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸውና የህክምና ዕርዳታም እየተደረገላቸው እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ አንድነታ ፓርቲ ድርጊቱን በመቃወምና በማውገዝ ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. መግለጫ ማውጣቱ ታውቋል፡፡

ከመኢአድ  የቀድሞው የፓርቲው ዋና ፀሐፊነ አመራር ተስፋዬ ታሪኩ ከጎጃም ደጀን በፀጥታ ኃይሎች ታፍነው መወሰዳቸው እንዲሁም ከሰማያዊ  ፓርቲ ደግሞ  የሰሜን ጎንደር የዞን አመራር የሆኑት አቶ አግባው ሰጠኝ ጎንደር ከተማ ውስጥ ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በተመሳሳይ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ታፍነው ወዳልታወቀ ስፍራ እንደሰወሯቸው ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል፡፡ በተያያዘ ዜና ከአረና ትግራይ ፓርቲ ደግሞ በትግራይ ክልል የሚገኙ አመራሮቹና አባሎቹ ቀሺ ብርሃኑ ቀባዕ፣ኣቶ ኣያሌው ጣዕምያለው፣,አቶ ሓለፎም ገብረዝጊ እና ቀሺ ገብረእግኣብሄር ካሳዬ ጥቅምት 26 ቀን 2007 ዓ.ም.በተመሳሳይ በፀጥታ ኃይሎች ታፍነው መወሰዳቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡ የኢህአዴግ መንግስት መጪውን ምርጫ 2007 ዓ.ም. ከወዲሁ ታሳቢ በማድረግ ከላይ የተጠቀሱ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ወጣት አመራሮችን ማሰር፣ መሰወርና መደብደቡን አጠናክሮ መቀጠሉ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመግባባት፣ አንድነትና ሰላም (ሰላም) ማህበር የተሰኘው የሲቪክ ተቋም ስራ አስኪያጅ አቶ ፋንታሁን ብርሃኑ ጥቅምት 23 ቀን 2007 ዓ.ም.መታሰራቸው ተጠቁሟል፡፡ አቶ ፋንታሁን ማኀበራቸው በህግ የተፈቀደለትንና የቆመለትን ዓላማ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ተይዘው መታሰራቸውን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በተለይ የፓርቲዎቹ ወጣት አመራሮች ላይ በተከታታይ እየደረሰ ያለውን እስርና ድብደባ  ምክንያት በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡ  የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ጥረት ቢደረግም አልተሳካም፡፡ በተለይ ከሚያዚያ 2006 ኣ.ም. ጀምሮ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት  ጋዜጠኞችን፣ ብሎገሮችን እና ወጣት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በጅምላ ማሰሩን አጠናክሮ መቀጠሉን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

በእስር ላይ የሚገኙት 10 ወጣቶች የሽብርተኝነት ክስ ተመሰረተባቸው

  • አብርሃ ደስታ ከሁለት ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አለው የሚል ክስ ተመስርቶበታል
  • ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ታዟል

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ በተሰየመው ችሎት 10 ተከሳሾች በፌደራል አቃቢ ህግ በይፋ ክስ ተመሰረተባቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከ100 ገጽ በላይ የክስ ቻርጅ የተነበበላቸው ሲሆን ከክስ ቻርጁ ጋር ከ300 ገጽ በላይ የምርመራ ሰነድ ቀርቦባቸዋል፡፡

የክሱ መዝገብ የተከፈተው ዘላለም ወርቃገኘሁ በተባለውና ‹‹የግንቦት 7 አመራር ነው፡፡›› ተብሎ ክስ በተመሰረተበት ግለሰብ ሲሆን በዚህ የክስ መዝገብ የተካተቱትም፡-

1ኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ
2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው
3ኛ ተከሳሽ ዳንኤል ሺበሺ
4ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታ

5ኛ ተከሳሽ የሽዋስ አሰፋ
6ኛ ተከሳሽ ዮናታን ወልዴ
7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን
8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ
9ኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ደጉ
10ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ተፈሪ ናቸው

ለሁሉም ተከሳሾች ከዛሬ በፊት ክስ እንዳልደረሳቸውና ዛሬ ፍርድ ቤት ውስጥ እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡ በችሎቱ 6ኛ ተከሳሽ ከሆነው ዮናታን ወልዴ በስተቀር ሁሉም ያለ ጠበቃ የቀረቡ ሲሆን ጠበቃዎቹ ያልቀረቡበት ምክንያትም ጠበቆቹ ደምበኞቻቸው የሚቀርቡበት ቦታና ጊዜ ስላልተነገራቸው እንዲሁም ቀደም ብለው እንዳይገናኙ በመደረጋቸው መሆኑን አቶ ኃብታሙ አያሌው ችሎቱ ላይ ተናግሯል፡፡

politician prisonersከሳሹ የፌደራል አቃቢ ህግ በ1996 የወጣው የወንጀል ህግ እና የጸረ ሽብር ህግ ጠቅሶ ክስ ያቀረበ ሲሆን ክሶቹ በሁለት ዋና ዋና ጭብጦች ቀርበዋል፡፡ የመጀመሪያው ጭብጥ ‹‹ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር በጋራ በመስራት›› የሚል ሲሆን ‹‹ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ፣ የመንግስትን መሰረተ ልማት በማፈራረስ፣ ህዝብን ለአመጸ በማነሳሳት መንግስትን መለወጥ አላማው አድርጎ ከሚሰራውና ራሱን ግንቦት 7 ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር አባል በመሆንና በወንጀል ድርጊቶች በመሳተፍ›› በሚል ቀርቧል፡፡

ሁለተኛው የክስ ጭብጥ ‹‹የሽብር ቡድን አመራር በመሆን›› የሚል ሲሆን በተለይም የአንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ‹‹የሽብር ቡድኑ አመራር በመሆንና አባል በመመልመል›› በሚል የክስ ጭብጥ ቀርቦበታልል፡፡

ከ2-5ኛ የክስ መዝገብ የሚገኙት ማለትም ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሽ፣ አብርሃ ደስታና የሸዋስ አሰፋ ‹‹ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲን ከለላ በማድረግ ግንቦት 7 የተባለውን የሽብር ቡድን አላማ ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ፋሲል የኔ ዓለምና ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር በስልክ በመነጋገርና በማህበራዊ ድህረ ገጸ የተለያዩ መልዕክቶችን ተለዋውጠዋል›› የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ አብርሃ ደስታ ከግንቦት 7 በተጨማሪ ‹‹ደምኢት የተባለ ቡድን አባል ነው፡፡›› የሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡

በስተመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ሁለት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ አንደኛው ረቡዕ ጥቅምት 26/2007 ዓ.ም 3 ሰዓት ተከሳሾቹ ዋስትና ይሰጣቸው አይሰጣቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቱ ከተከሳሾቹ ጠበቆች ጋር ተማክሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሏል፡፡ በሁለተኛነት ተጠርጣሪዎቹ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ቀደም ሲል ለአራት ወራት ወደቆዩበት ማዕከላዊ እስር ቤት እንዳይመለሱ ፍርድ ቤቱን ስለጠየቁ ፍርድ ቤቱ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት (3ኛ) እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ ትናንት ጥቅምት 20/2007 ዓ.ም አራዳ ምድብ ችሎት ይቀርባሉ ተብሎ የነበር ቢሆንም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ በተመሳሳይ ዛሬ ጥቅምት 21/2007 ዓ.ም ጠዋት ወደ ልደታ ፍርድ ቤት ተወስደው የነበረ ቢሆንም እንደገና ወደማዕከላዊ ተመልሰው ከሰዓት እንዲቀርቡ ተደርገዋል፡፡

ምንጭ፡- ነገረ-ኢትዮጵያ

 

ወጣቶቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በድብቅ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደረገ

ከአራት ወራት በፊት በሽብር ስም በአዲስ አበባ የፌደራሉ ወንጀል ምርመራ “ማዕከላዊ” የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አቶ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፤ የሰማያዊ እና የአረና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አቶ የሺዋስ አሰፋና አቶ አብርሃ ደስታ ዛሬ ጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት በድብቅ ልደታ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጋቸውንና ነገ ጠዋት በድጋሚ ልደታ ፍርድ እንደሚቀርቡ የፍኖተ ነፃነት ዘገባ ያስረዳል፡፡politician prisoners

የህሊና እስረኞቹ እንደተለመደው አራዳ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ በሚል የትግል አጋሮችቸው እና ደጋፊዎቻቸውና ጋዜጠኞች ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ እስከ 11፡30 በቀጠሮው ስፍራ ቢጠብቁም፤ ፖሊስ በድብቅ ልደታ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማድረጉ ተሰምቷል፡፡ ታሳሪዎቹ ልደታ ፍርድ ቤት እንደሚገኙ መረጃ የደረሳቸው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በስፍራው ሲደርሱ አቶ  ሀብታሙ አያሌው፣አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣አቶ የሺዋስ አሰፋና አቶ አብርሃ ደስታ በመኪና ውስጥ ሆነው ወደ ማዕከላዊ ሲወሰዱ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ብሎም የልደታው ፍርድ ቤት “ጉዳዩን የሚያይ ዳኛ የለም” በማለት ለነገ ጠዋት ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ መሰጠቱም ተጠቁሟል፡፡

ምንጭ፡- ፍኖተ ነፃነት

 

የፖለቲካ አመራሮቹ ችሎት ያለ ተከላካይ ጠበቃ ሲታይ፤ቀጣይ ቀጠሯቸው ግልፅ አይደለም

ዛሬ መስከረም 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ፒያሳ አራዳ በሚገኘው የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የፖለቲካ  ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ በዝግ ችከሎት ያለ ተከላካይ ጠበቃ ቀጠሮ መስጠቱ ተጠቆመ፡፡ የፖለቲካ አመራሮቹ አቶ ሀብታሙ አያሌው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ የአንድነት ፓርቲ ምክትል የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ አቶ አብርሃ ደስታ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህርና የአረና ፓርቲ ምክትል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዲሁም አቶ የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ከተከላካይ ጠበቆቻቸው ጋር ሳይገናኙ ከቀጠሮ ሰዓታቸው አርፍደው ከቀኑ 10 እና 11 ሰዓት ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

detained politiciansበነበረው የፍርድ ቤት ችሎት ተከላካይ ጠበቃ ደንበኞቻቸውን ህጉ በሚፈቅደው መሰረት በማዕከላዊ ሄደው መጎብኘትና መነጋገር ቢፈልጉም፤ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል “ማዕከላዊ” ፖሊስ ስላልተፈቀደላቸው ፍርድ ቤት መገኘቱ ለፕሮፖጋንዳ ካልሆነ ከህግ አግባብ ትርጉም ስለሌለው እንደማይገኙ አስቀድመው ማሳወቃቸው ተጠቁሟል፡፡ በችሎትም ቤተሰብ፣ ጋዜጠኛ፣ ዲፕሎማቶች እና ወዳጅ ዘመድ እንዳይከታተል መከልከሉም ታውቋል፡፡ የእስረኞቹ ቀጣይ ቀጠሮ መቼ እንደሆነ እስካሁን ከፍርድ ቤቱ ማግኘት ባይቻልም፤ እንደ ነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ ከሆነ የማዕከላዊ ምርመራ ኃላፊ አቶ ተክላይ ሹመት ተጠርጣሪዎቹ የተቀጠሩት ለጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲሉ፤ ሌላ ፖሊስ ደግሞ ለጥቅምት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው የሚል ጥቆማ መስጠታቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስረኞቹ እስካሁን በነበረው ምርመራ ፖሊስ ምንም ዓይነት ለወንጀል ክስ የሚያበቃ መረጃ ባለማግኘቱ፤ ወደ ኃይል እርምጃ በመሄድ ፖሊስ የሚፈልገውን ቃል እስረኞቹ ያልፈፀሙትን አስገድዶ የእምነት ቃል እንዳስፈረማቸው የማዕከላዊ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ ይሄም ለህዝቡና ለመገናኛ ብዙኃን እንዳይገለፅና ፍርድ ቤትም በቅሬታ መልክ እንዳይቀርብ ስለተፈለገ ነው ተከላካይ ጠበቆቹ እንዳይጎበኙ የተከለከሉት ሲሉ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡  በዚህም የዛሬው ችሎት ያለጠበቃ ጭምር በዝግ ችሎት መካሄዱ የተጠቆመ ሲሆን፤ የቀጠሯቸው ቀንም ከላይ ከተጠቀሰው ውጭ እስካሁን ትክክለኛውን ከፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ እንዳልተቻለ መረጃዎእ አመልክተዋል፡፡ ችሎቱን ለመታደም ወደ ስፍራው ያቀኑ ሰዎችም ፍርድ ቤቱ ግቢ ሲገቡ ከወትሮ በተለየ በፖሊሶች ከፍተኛ ፍተሻ፣ እንግልትና ወከባ እንደተፈፀመባቸው  የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡

%d bloggers like this: