ለመከላከያ ምስክርነት የተጠሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ “ሊቀርቡ ባለመቻላቸው” ምስክርነታቸው ውድቅ ተደረገ
*አብርሃ ደስታ 4 ወራት፣ የሺዋስና ዳንኤል 2 ወራት እስር ይቀራቸዋል
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ አንደኛ ተከሳሽ አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ በቀረበበት የሽብር ክስ ላይ ከግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ተጻጽፈሃል የሚል ማስረጃ በአቃቤ ህግ እንደቀረበበት በመግለጽ ይህን እንዲከላከሉለት አቶ አንዳርጋቸውን ለምስክርነት ቢጠራቸውም በተደጋጋሚ ቀጠሮ ሊቀርቡ ባለመቻላቸው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ምስክሩ በተከሳሽ በኩል እንደተተው ይቆጠራል በሚል በይኗል፡፡
ፍርድ ቤቱ ዛሬ የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም ብይኑን ሲያሰማ እንደገለጸው ተከሳሽ አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ ምስክሩን በተመለከተ በተደጋጋሚ እንዲቀርቡለት ጠይቆ እንዳልቀረቡለት በመግለጽ ‹‹ምስክሩ የማይቀርቡልኝ ከሆነ ከምስክሩ ጋር በተያያዘ የቀረበብኝ ክስ ፍሬ ነገር ከክሱ ወጥቶ ብይን ይሰጠኝ›› የሚል አቤቱታ አቅርቧል፡፡
አቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሹ ምስክሩን አቅርቦ የማሰማት ግዴታ እንዳለበት በመጥቀስ ተከሳሹ የጠየቀው የፍሬ ነገር ይውጣልኝ አቤቱታ የህግ አግባብን የተከተለ ስላልሆነ ምስክሩን እንደተዋቸው ተቆጥሮ ብይን እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
ችሎቱ በበኩሉ ለምስክሩ የተጻፈው የመጥሪያ ትዕዛዝ ደርሷቸው እንደቀሩ ማረጋገጫ ስለሌለ በተከሳሽ የቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት እንደሌለው በማስረዳት ምስክሩ እንደተተው ቆጥሮ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በመዝገቡ ላይ በተካተቱት አምስት ተከሳሾች ላይ የፍርድ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 29 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ ቀጠሮ በፊት የክርክር ማቆሚያ ካላቸው ግራቀኙም በጽህፈት ቤት በኩል በጽሁፍ ማቅረብ እንደሚችሉ ፍርድ ቤቱ ገልጹዋል፡፡
በሌላ በኩል ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በዚሁ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ከተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ነጻ ናቸው በሚል የተበየነላቸው እነ አብርሃ ደስታ በዚሁ ችሎት፣ ‹‹ችሎት ደፍራችኋል›› በሚል የተላለፈባቸው ቅጣት ከመቼ ጀምሮ እንደሚታሰብ ግልጽ አድርጓል፡፡
በዚህም አመት ከአራት ወር የተፈረደበት አቶ አብርሃ ደስታ እና እያንዳንዳቸው አንድ አመት ከሁለት ወር የተፈረደባቸው አቶ የሺዋስ አሰፋ እና አቶ ዳንኤል ሺበሺ ከመጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በሚታሰብ እስር መቀጣታቸውን ገልጹዋል፡፡ በመሆኑም አብርሃ አራት ወራት፣ እና እነ የሺዋስ ሁለት ወራት እስር ይቀራቸዋል ማለት ነው፡፡
እነ አብርሃ ደስታ አቃቤ ህግ በጠየቀባቸው ይግባኝ ላይ ብይን ለማግኘት ለመጋቢት 30 ቀን 2008 ዓ.ም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀጠሮ እንዳላቸው ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡ ነገረ ኢትዮጵያ
እነ ሀብታሙ አያሌው በጠቅላይ ፍርድ ቤት የቃል ክርክር አደረጉ
ኢዩኤል ፍስሃ ዳምጤ
“እኔ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል እንደመሆኔ መጠን የኢህአዴግን ጭቆና ማጋለጥ ግዴታዬም መብቴም ጭምር ነው! ይህን ካላደረጉ ምኑን ተቃዋሚ ሆንኩ?” አብርሃ ደስታ
“እኔ አሸባሪ አይደለሁም! የታሰርኩት በኢህአዴግ የፖለቲካ ሴራ ነው! እኔ የፖለቲካ እስረኛ ነኝ!” ዳንኤል ሺበሺ
በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ በነፃ የተሰናበቱት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አቶ የሺዋስ አሰፋና በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ውስጥ ከአመራሮቹ ጋር የተከሰሰው አቶ አብርሃም ሰለሞን በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዛሬ ታህሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም በመቅረብ የቃል ክርክር አድርገዋል፡፡
በችሎቱ የተሰየሙት ግራ ዳኛ መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ታህሳስ 8 ቀን 2008 ዓ.ም ተከሳሾቹ የፍርድ ቤቱ ሰብሳቢ ዳኛ የሆኑት አቶ ዳኜ መላኩ ከሰብሳቢነታቸው እንዲነሱ ባቀረቡት የፅሁፍ አቤቱታ ላይ መልስ ለመስጠት፤ የተከሳሾቹንና የአቃቤ ሕግን የቃል ክርክር ለማድመጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ተከሳሾቹ “ሰብሳቢው ዳኛ ይነሱልን!” ብለው ያቀረቡት ጥያቄ ፍ/ቤቱ ስላላመነበት ውድቅ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
አቃቤ ሕግ በችሎቱ ባቀረበው የይግባኝ አቤቱታው ተከሳሾቹ ከግንቦት ሰባት አመራር አባላት ጋር በተለያየ ጊዜ መገናኘታቸውን፤ ይህንንም የሚያስረዳ ማስረጃ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ማቅረባቸውን ነገር ግን የስር ፍርድ ቤቱ እነዚህን ማስረጃዎች ሳይመዝን “በደፈናው ውሳኔ ስለሰጠ” ይግባኝ መጠየቃቸውንና የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሲሰጥ ከጭብጥ መውጣቱን ገልጿል፡፡ “ፍርድ ቤቱ ከፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀፅ 23 መሰረት የቀረበውን የሰነድ ማስረጃዎች በመመልከት የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን በመሻር ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ይወስንልን ዘንድ እንጠይቃለን” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
1ኛ ተከሳሽ አቶ ሀብታሙ አያሌውና 5ኛ ተከሳሽ አቶ አብርሃም ሰለሞን በጠበቃቸው አምሃ መኮንን በኩል የመከራከሪያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ አቶ አምሃ መኮንን የስር ፍርድ ቤቱ ደምበኞቻቸውን በነፃ ሲያሰናብታቸው የቀረቡትን ማስረጃዎች መዝኖ መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ አቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ያቀረባቸው ነገሮች እንደመረጃ እንጂ እንደማስረጃ ሊያዙ እንደማይገባ የተከሳሾቹ የቀድሞ ጠበቃ በስር ፍርድ ቤት ክርክር አድርገው የስር ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 2 ቀን 2007 ዓ.ም “በማስረጃ ሊያዙ ይገባል!›› ብሎ ብይን ማስተላለፉን አቶ አምሃ አውስተዋል፡፡
ጠበቃው ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ በኩል የሚቀርቡ ማስረጃዎችም ፍርድ ቤት ሊመረምራቸው እንደሚገባ ሲያስረዱ፡- “የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ በኩል የሚቀርቡ መረጃዎችን ፍርድ ቤቱ ሙሉ ለሙሉ የሚቀበል ከሆነ የፍርድ ቤቱ ሚና ምን ሊሆን ነው? ፍርድ ቤቱ ከተቋሙ በኩል የሚቀርቡለትን መረጃዎች ሙሉ ለሙሉ የሚቀበል ከሆነም ፈራጁ ፍርድ ቤት ሳይሆን ብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ነው” በማለት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ደምበኛቸው አቶ ሀብታሙ አያሌውም በክሱ ላይ ‹‹ዘመነ ካሴ›› ከተባለው የግንቦት ሰባት አባል ጋር በመነጋገር አብረው ለመስራት ተስማሙ ተብሎ ቢገለፅም ይህን የሚያስረዳ ማስረጃ አለመቅረቡን ገልፀዋል፡፡ ደምበኛቸው ከግለሰቡ ጋር ባደረጉት የስልክ ልውውጥ አንድም ቦታ ላይ አብረው ለመስራት መስማማታቸውን እንዳልገለፁ ጠበቃው ጠቁመዋል፡፡ በክሱ ላይ የአንድነት ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ የሆነው አቶ ሀብታሙ አያሌው ከዘመነ ካሴ ጋር ግንኙነት አደረጉ ተብሎ የተገለፀው ከእውነታ የራቀ መሆኑን ጠበቃው ገልፀዋል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ አቶ ሀብታሙ አይደለም የአንድነት ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሊሆኑ ቀርተው፤ የፓርቲው አባል እንዳልነበሩም አቶ አምሃ አስረድተዋል፡፡ አቶ ሀብታሙ በበኩላቸው በክሱ ላይ ተከሳሽ በዚህ የሞባይል ቁጥር ግንኙነት አድርጓል ተብሎ አለመገለፁን የስልክ ልውውጡም ምን እንደሆነ የሚያስረዳ አንዳች ነገር አለመቅረቡን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
አቶ አምሃ ደምበኛቸው በሆነው 5ኛ ተከሳሽ አቶ አብርሃም ሰለሞን ላይ ምንም አይነት የሰነድ ማስረጃ አለመቅረቡን የግንቦት ሰባት አባል ነው ሲባልም፤ በግንቦት ሰባት መዋቅር ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ አለመቅረቡን ደምበኛው በምንም አይነት የሽብርተኝነት ተግባር ላይ እንደተሰማራ የሚገልፅ ምንም አይነት ማስረጃ አለመቅረቡን ገልፀዋል፡፡ አቶ አብርሃም ሰለሞን በበኩሉ ያለአንዳች ማስረጃ መታሰሩን ሲያስረዳ፡- “ከታሰርኩ በኋላ ነው ማስረጃ ሲፈለገብኝ የነበረው፤ ከታሰርኩ በኋላም ቤቴ እንኳ አልተፈተሸም፡፡ መንግስት አሰረኝ ብዬ አላምንም ያሰረኝ አንድ ግለሰብ ነው” ሲል ተደምጧል፡፡
2ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ 3ኛ ተከሳሽ አቶ አብርሃ ደስታና 4ኛ ተከሳሽ የሺዋስ አሰፋ ያለጠበቃ በመቆም በግል ክርክራቸውን ያካሄዱ ሲሆን፤ ሶስቱም ተከሳሾች የአቃቤ ሕግ የይግባኝ ማመልከቻ ላይ እነሱን የሚመለከት ቅሬታ አለመቅረቡን ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ሺበሺ “እኔ አሸባሪ አይደለሁም! የታሰርኩት በኢህአዴግ የፖለቲካ ሴራ ነው! እኔ የፖለቲካ እስረኛ ነኝ!” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ የቃል ክርክር ለማድረግ ያዘጋጁት ወረቀትም በማረሚያ ቤቱ እንደተቀደደባቸው ለፍርድ ቤቱ አሳይተዋል፡፡ ወረቀቱ ማህተም የተደረገበት ቦታ ተቀዶ መውጣቱን በችሎቱ ለነበሩ ታዳሚያን በግልፅ ታይቷል፡፡
3ኛ ተከሳሽ አቶ አብርሃ ደስታም ከታሰሩ በኋላ ማስረጃ ሲፈልግባቸው እንደነበርና በብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ የሚቀርብ መረጃ በፍርድ ቤት ሳይመዘን ሙሉ ለመሉ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ ተቋሙ ከሳሽም፣ መስካሪም፣ ዳኛም ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንድ ደግሞ ፍርድ ቤት መምጣትም አያስፈልግም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በክሱ ላይ ለኢሳት ቴሌቪዥን ቃለምልልሰ ሰጠ ተብሎ የቀረበው ክስ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ሲያስረዱ፡- “እኔ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል እንደመሆኔ መጠን የኢህአዴግን ጭቆና ማጋለጥ ግዴታዬም መብቴም ጭምር ነው! ይህን ካላደረጉ ምኑን ተቃዋሚ ሆንኩ?” በማለት ለፍ/ቤቱ የገለፁ ሲሆን፤ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ ሃሳባቸውን ሲገልፁ የነበሩትም የኢህአዴግን ጭቆናን ማጋለጥ መብታቸው በመሆኑ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
4ኛ ተከሳሽ አቶ የሺዋስ አሰፋ በእሳቸው ላይ የቀረበ አንድም የሰው ምስክር እንደሌለ ገልፀው፤ ማዕከላዊ በነበሩበት ወቅትም በምርመራ ላይ አንድም ቀን ስለግንቦት ሰባት ተጠይቀው እንደማያውቁ ምርመራ ላይ ሲጠየቁ የነበሩትም ስለ ሰማያዊ ፓርቲ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አቶ የሺዋስ የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆናቸው ብቻ አያሌ መከራዎችን እየተጋፈጡ እንደሚገኙ ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ያለፉትን 6 ወራት በማንም አለመጎብኘታቸውን ለፍ/ቤቱ ገልፀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የቃል ክርክሩ በፅሁፍ ተገልብጦ ከቀጣይ ቀጠሮ በፊት ከመዝገቡ ጋር ተያይዞ እንዲቀርብ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ 1ኛ ተከሳሽ አቶ ሀብታሙ አያሌው የሚገኙበት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተከሳሹ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ታህሳስ 19 ቀን 2008 ዓ.ም መልስ እንዲሰጥ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ የማረሚያ ቤት ተወካዩ በተጠቀሰው ቀን አቶ ሀብታሙን ይዞ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡
የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር መዝኖ ውሳኔ ለመስጠት ለታህሣሥ 29 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ እነ ሀብታሙ አያሌው ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከተመሰረተባቸው የሽብርተኝነት ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ማስተላለፉ አይዘነጋም፡፡
ሰበር ዜና፤ በእስር ላይ የነበሩት የቀድሞ የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲ አመራሮች እና አንድ ሌላ ተከሳሽ በነፃ እንዲሰናበቱ ተወሰነ
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፤ ዛሬ ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በዘለዓለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ በፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ከአንድ ዓመት ከአንድ ወር አካባቢ ታስረው ከነበሩት መካከል አራት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አንድ መምህር በነፃ እንዲሰናበቱ ወሰነ፡፡
ከተመሰረተባቸው ክስ በነፃ እንዲሰናበቱ የተወሰነላቸው የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ አመራሮች አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋና የቤተል ትምህርት ቤት መምህርና የሀገር አቀፍ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሀገር አቀፍ አሸናፊ የነበረው መምህር አብርሃም ሰለሞን በነፃ የተሰናበቱት፣ የቀረበባቸው የሽብርተኝነት ክስ ከጥርጣሬ ባለፈ ተሳትፎአቸውን ማረጋገጥ ባለመቻሉ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አስታውቋል፡፡
በውሳኔው መሠረት አቶ ሀብታሙ የሚጠየቁበት ወይም ሌላ የሚፈለጉበት ጉዳይ ከሌለ በዛሬው ዕለት እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺና አቶ የሺዋስ አሰፋ ከዚህ ቀደም ችሎት በመድፈር የተፈረደባቸውን ቅጣት እንዳጠናቀቁ እንዲፈቱ ሲል መወሰኑ ታውቋል፡፡
በዚሁ ክስ መዝገብ በተመሳሳይ ተከሰው ከነበሩት 10ሩ መካከል ከላይ የተጠቀሱት 5ቱ እንዲፈቱ ሲወሰን፤ ቀሪዎቹ 5ቱ እንዲከላከሉ እንተበየነባቸው ተጠቁሟል፡፡
በአሁን ወቅት በርካታ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች እና የኃይማኖት ነፃነት ጠያቂዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን፤ ባለፈው ሶስት ጋዜጠኞች፤ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ እና ኤዶም ካሳዬ እንዲሁም የዞን 9 ብሎገሮች መካከል ሁለቱ ዘለዓለም ክብረት እና ማህሌት ፋንታሁን ከተመሰረተባቸው ክስ በነፃ ሲሰናበቱ፤ የተፈረደባቸውን ፍርድ ከጨረሱት መካከል ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እና የኦፌኮ/መድረክ አመራር አቶ በቀለ ገርባ ከእስር መፈታታቸው አይዘነጋም፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ‘ሰጡ’
“ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው አሸባሪ ህወሓት/ኢህአዴግ ነው” አብርሃ ደስታ
“የጦር ችሎት በሚመስል ችሎት እየተንገላታን ነው” የሺዋስ አሰፋ
በዘለዓለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገቡ የተካተቱ ተከሳሾች በተከሰሱበት ድርጊት ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ፡፡
የሰማያዊ፣ የአንድነት እና የዓረና ትግራይ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ 10 ተከሳሾች መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህ መሰረት ከአንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ጀምሮ፣ “በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም?” የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ ለእያንዳንዳቸው የቀረበላቸው ሲሆን ብዙዎቹ ተከሳሾች ምላሻቸውን በቀጥታ ለመስጠት አለመፈለጋቸውን አሳይተዋል፡፡
1ኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ለቀረበለት ጥያቄ፣ “በአቃቤ ህግ እና በፖሊስ ተቀነባብሮ የቀረበብኝን ክስ በተመለከተ ለክሱ እውቅና ላለመስጠት ምንም አልልም፡፡ በክሱ ላይ አስተያየት በመስጠት ለጸረ-ሽብር አዋጁ እውቅና መስጠት አልፈልግም” የሚል መልስ በመስጠቱ ፍርድ ቤቱ ክሱን ክዶ ቃል እንደሰጠ አድርጎ መዝግቦታል፡፡
2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው በበኩሉ “በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት እንዳልፈጸምኩ እንኳን እኔ ከሳሾቼም በደንብ ያውቃሉ፡፡ ከሳሾቼ እኔ ድርጊቱን የመፈፀም ፍላጎቱም ሀሳቡም እንደሌለኝ ያውቃሉ” ብሏል፡፡
3ኛ ተከሳሽ ዳንኤል ሺበሽ ደግሞ፣ “እኔ ስለ ሽብር የሰማሁት ከአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢላደን እና መለስ ዜናዊ ነው፡፡ እኔ አሸባሪ አይደለሁም፤ ሀሳቡም ሆነ ፍላጎቱም የለኝም፡፡ ባህሌና እምነቴም አይፈቅድልኝም” ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
4ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታ “አሸባሪ ማለት የፖለቲካም ሆነ ሌላ ዓላማውን ሰላማዊ ዜጎችን በማሸበር ለማስፈፀም የሚሰራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው አሸባሪ ድርጅት ህወሓት/ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ ደግሞ የዚህ አሸባሪ ድርጅት ተቃዋሚ ነኝ” ብሏል፡፡
5ኛ ተከሳሽ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ፣ “በመጀመሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ስለሆነ የምናገረው እንዳታቋርጡኝ አደራ እላለሁ፡፡ ክሱ ቅንብር ነው፡፡ ዳኞችም ህጉ የሰጣቸው ነጻነት አይታይባቸውም፡፡ ይህ 19ኛ ወንጀል ችሎት የጦር ችሎት ነው የሚመስለኝ፡፡ ስለሆነም የጦር ችሎት በሚመስል ችሎት እየተንገላታን ነው” ሲል ተናግሯል፡፡ የሺዋስ በዳኞች በተደጋጋሚ ንግግሩ እንዲቅረጥ ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም ክሱን ክዶ ቃል ሰጥቷል በሚል ተመዝገቦለታል፡፡
6ኛ ተከሳሽ ዮናታን ወልዴ፣ “የተዘጋጀብኝን ክስ ያለፍቃዴ እንድተውን እየተገደድኩ ነው” ብሏል፡፡
7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን ደግሞ፣ “የተቀነባበረ ክስ ላይ ምንም ማለት አይቻልም” ብሏል፡፡
8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ፣ “ነፃ ሰው ነኝ፡፡”
9ኛ ተከሳሽ ባህሩ ደጉ “ባህሉንና ፈጣሪውን ከሚያከብር ማህበረሰብ ወጥቼ አሸባሪ ልሆን አልችልም” ሲል አስረድቷል፡፡
10ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ተፈሪ ደግሞ፣ “ድርጊቱን አልፈጸምኩም” ብሏል፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሾች ክሱ ላይ የተጠቀሰውን ድርጊት ክደው ቃል በመስጠታቸው አቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያሰማ ለግንቦት 13፣ 14፣ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ለተከታታይ 3 ቀናት ምስክር እንዲሰማ ቀጠሮ መሰጠቱን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክታል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ቅጣት ተላለፈባቸው
᎐ተጨማሪ ቅጣትም ይጠብቃቸዋል፡፡
• “እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው” አብርሃ ደስታ
• “ችሎቱ ላይ ያጨበጨብነው በማፌዝ ሳይሆን በምሬት ነው” የሺዋስ አሰፋ
• “ፍትህ ተጠምተናል፣ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!” ዳንኤል ሺበሽ
በዘለዓለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ከስምንት ወራት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነት እንዲሁም የዓረና ትግራይ ፓርቲዎች አመራሮች ‹ችሎት በመድፈር ወንጀል› ጥፋተኛ በመባላቸው ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት በሦስቱ አመራሮች ላይ እያንዳንዳቸው በሰባት ወራት እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡
የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም ተከሳሾች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸውና ንብረትም እንደተወሰደባቸው በመግለጽ አቅርበውት ለነበረው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ሙሉ ለሙሉ በመቀበል አቤቱታቸውን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ 5ኛ ተከሳሽ አቶ የሺዋስ አሰፋ በማጨብጨቡና 3ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታና 4ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሽ ሳይፈቀድላቸው ‹‹ጥሩ ፍርድ፣ ጥሩ ብይን›› በማለት አቶ የሺዋስን በመደገፍ ችሎት ደፍረዋል ተብለው ጥፋተኛ መሰኘታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ ለዛሬ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ተሰይሞ በአብርሃ ደስታ፣ በየሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽ ላይ የ7 ወራት እስራት በይኖባቸዋል፡፡ ሦስቱም ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ድጋሜ ችሎት ውስጥ አጨብጭበዋል፡፡ በዚህም ድጋሜ ጥፋተኛ ተብለዋል፤ ከሁለት ቀናት በኋላም የቅጣት ውሳኔ ይወሰንባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሦስቱ ተከሳሾች ‹‹እድል ስጡን እንናገር፣ አቤቱታም አለን ተቀበሉን›› ቢሉም ፍርድ ቤቱ ሊሰማቸው አልፈለገም፡፡
በተለይ ዳንኤል ሺበሺ ‹‹ሌላ አቤቱታ አለኝ፣ ፍርድ ቤቱ ያዳምጠኝ›› ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ አሁንም ችሎቱ ላይ እያፌዛችሁ ነው በሚል ጥፋተኛ ሲላቸው ሦስቱም አመራሮች ፍርድ ቤቱን ማስፈቀድ ሳያስፈልጋቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው፡፡ ‹Already› የተደፈረ ችሎት ነው›› ሲል አብርሃ ደስታ ተናግሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ዳኞቹ ጣልቃ በመግባት፣ ‹‹የምትናገረው ነገር እንደገና ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሚወስድህ ጉዳይ ነው፤ ምርመራ ይደረግበታል›› ሲሉ አብርሃ በበኩሉ ‹‹አሁንስ ቢሆን የምናገረውን ፖሊስ እየሰማ አይደለምን?›› ሲል መልሷል፡፡ አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ ‹‹ከስምንት ወር በላይ ታፍነናል፡፡ በህግ አይደለም የተያዝነው፡፡ ደግሞ ማጨብጨባችን በችሎቱ ከማፌዝ ሳይሆን ከምሬት በመነጨ ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ መብታችን ተጥሷል፡፡ እኔ ለምሳሌ የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆኔ ነው የታሰርኩት፡፡›› ብሏል፡፡
አቶ ዳንኤል ሺበሽ ድግሞ ‹‹አሁንም ችሎት ደፍራችኋል ካላችሁ ቅጣቱን ጨምሩብንና ሸኙን፡፡ በእርግጥ ዳኞች ላይ ያለውን ጫና እንረዳለን፡፡›› ሲል ችሎት ውስጥ ተናግሯል፡፡
በዚህ ሁኔታ በተከሳሾችና በችሎቱ መካከል ያለው አለመግባባት ሲጨምር ዳኞቹ መጋቢት 3/2007 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የቅጣት ውሳኔ እንደሚሰጥ በመጥቀስ ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት በፖሊስ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ከችሎት እየወጡ እያሉም አቶ ዳንኤል ሺበሽ ‹‹ፍትህ ተጠምተናል፤ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!›› እያለ ችሎቱን ለቅቆ ወጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት መውጣታቸውን ተከትሎ፣ከዚህ ቀደም በማረሚያ ቤቱ ላይ በቀረበው አቤቱታ ዳኞች በሰጡት አስተያየት ላይ አቤቱታ አቅርቦ እንደነበር በማስታወስ አቤቱታው እንዲመዘገብለት የጠየቀው አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ‹‹በበኩሌ ያሉኝን መረጃዎች እያቀረብኩ ስነ-ስርዓቱን አክብሬ ክርክሩን አቀጥላለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ- ኢትዮጵያ