Daily Archives: October 1st, 2015

የታክሲዎች ፖለቲካ

ጌታቸው ሺፈራው

ታክሲ ውስጥ በብዛት ከሚፃፉት ጥቅሶችም በላይ አንዳንዴ ታክሲ ውስጥ ካሉት ሰዎች ጣል የሚደረጉት የምሬት አሊያም ሌሎች የፖለቲካ ወጎች የማህበረሰቡን አመለካከት በግልፅ ያሳያሉ፡፡ መጀመሪያ ከጎናቸው ያለውን ሰው የሚጠራጠሩት ተሳፋሪዎች ሁኔታውን አይተው ብሶታቸውን ያወራሉ፡፡ አንዳንዶቹ ወሬ የሚያስጀምር ሳያስፈልጋቸው በከተማው የሚታዘቡትን በግልፅ ይቃወማሉ፡፡ ስርዓቱን የሚደግፉ፣ የሚያስመስሉም እንደሚገኙበት ሁሉ፡፡

tavxi politics

ዛሬ ያጋጠመኝ ግን ትንታኔ ነው፡፡ በቀልድም ቢሆን ደንበኛ የፖለቲካ ትንታኔ፡፡ ህዝቡ ፖለቲካን በደንብ እንደሚከታተልና እንደሚረዳ የሚያሳይ ትንታኔ ነው፡፡ በየ ሰዓቱ የሚነገረውን ፕሮፖጋንዳ ህዝብ ገልብጦ እንደሚያነበው የሚያሳይ አጋጣሚ፡፡

ከአራት ኪሎ ወደ ስድስት ኪሎ ከዛም ወደ ፈረንሳይ እየሄድን ነው፡፡ የፈረንሳይ ህዝብ ‹‹በወንበር›› የሚጫነው ከአራት ኪሎ እስከ ስድስት ኪሎ ብቻ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ከሰው ላይ ሰው ይደራረብበታል፡፡ ሰው እንደ ሽንኩርት ነው የሚጭኑት፡፡ ታክሲው እስከ አፍ ጢሙ ሞልቶ ‹‹ሁለት ሰው የቀረው›› እያለ የሚጠራን አንድ የታክሲ ረዳት ለቀልድ ‹‹ለምን ከላይ አትጭንም?›› ብዬው ‹‹ቢፈቀድ እንዴት አሪፍ ነበር መሰለህ! ጥሩ ሀሳብ ነበር›› ብሎኛል፡፡ ሰውን እንደበግ አስሮ ጭኖ ብር ከሀምሳ ሊያስከፍል!

አብዛኛዎቹ ረዳቶች በግድ ነው አጠጋግተው የሚጭኑት፡፡ ካልሆነ አልጠጋም ያለውን ‹‹ውረድ!›› ለማለትም ይዳዳቸዋል፡፡ ዛሬ የመጣንበት ታክሲ ረዳት ግን ተጫዋች ነው፡፡ ያስቃል እንጅ አያስገድድም፡፡ ‹‹ተጠጉ›› ሲልም እያባበለና በቀልድ ነው፡፡ ስድስት ኪሎ ስንደርስ ተሰብስቦ ታክሲ የሚጠብቀውን ሰው ‹‹ፈረንሳይ ፈረንሳይ!›› ብሎ የታክሲውን መዳረሻ ካሳወቀው በኋላ ‹‹ይኸው ቤታችሁ ነው ግቡ፡፡ ለሁላችሁም ይበቃል፡፡ ዋናው ፍቅር ነው!›› እያለ ጎረምሳ የ70 አመት ሽማግሌ፣ ነፍሰ ጥሩ ሴትና ህፃናት ጋር ሲጋፋ ፈንጠር ብሎ ይታዘባል፡፡ ምን አልባት ሊያሳዝነውም፣ ሊያስደስተውም ይችላል፡፡ ለምዶት ምንም ላይመስለው ይችላል፡፡ አብዛኛው ሰው ተገፍትሮም፣ ቦታ አይኖርም ብሎ ተስፋ ቆርጦም ተመልሷል፡፡ ቦታ ይኖራል ብለው ታክሲው በር ላይ ቆመው የቆዩት ሰዎች ቦታ እንደሌለ አውቀው ወደ ኋላ ሲመለሱ እሱ ወደ ታክሲው በር ተጠጋ፡፡ መቀመጫ አጥተው መተላለፊያው ላይ አጎንብሰው የቆሙ መንገደኞች አሉ፡፡ ታክሲዋ ወስጥ በግምት ከ19- 20 ያህል ሰዎች ተጠጋግተው ተቀምጠዋል፡፡ እድል የቀናቸውም አአንዳሚው ወንበር ላይም ተደርድረዋል፡፡ ያን ያህል ተጋፍቶ ወንበር ማግኘት ደስታ የሚፈጥርባቸው አሉ፡፡ በግፊያው ወቅት በነበረው ትይንት የሚስቀም፣ የሚናደደም አለ፡፡ እንዲህም ሆኖ ሶስት ያህል ሰዎችጠባቧ መተላለፊያ ላይ በሰው ተጣብቀው ‹‹ቆመው›› ቦታ እየፈለጉ ነው፡፡
የታክሲው ሚኒስቴር ዴኤታ (ረዳቱ) ቦታ እንደሌለ ቢያውቅም ‹‹ተጠጉላቸው፡፡ ተጠጉላቸው እንጅ!›› እያለ ያባብላል፡፡ ሁለቱ ወንበሮች ሶስት ሶስት ሰው ይዘዋል፡፡ አግዳሚው ወንበርም ሞልቷል፡፡ ሶስቱ ሰዎች አሁንም አልወረዱም፡፡ የታክሲ ሚንስቴር ዴኤታም ‹‹ኧረ ተጠጉ!›› ቢል የሚሰማው አላገኘም፡፡ ቦታ የለማ! እሱ እራሱኮ ቦታ ስለሌለ አልገባም፡፡ አንዱ ወረደ፡፡ ሁለቱ ተስፋ አልቆረጡም፡፡ ረዳቱን ታስፋ አድርገው እንጅ ቦታ እንደሌለስ አይተዋል፡፡

አሁን ረዳቱ ቢያንስ ለመቆሚያ ቦታ አግኝቷል፡፡ ከበሩ ትንሽ ወደ ታክሲው ገብቶ ‹‹ቤታችሁ ነው፡፡ ቆማችሁም ቢሆን ትሄዳላችሁ፡፡›› ይላቸዋል ሁለቱን መንገደኞች፡፡ ግን ማባበሉንም አላቆመም፡፡ ‹‹ተጠጉላቸው! ወገን ተጠጉላቸው! እነሱም እንደኛው መሄድ ይፈልጋሉ፡፡ የሀገራችን ሰዎች ናቸውኮ፡፡ አቅፈንም ቢሆን እንወስዳቸዋለን፡፡ ቻይና እንኳን በታክሲያችን ይሄድ የለ፡፡ ያው በሳምንት የሚፈራርስ መንገድ ቢሰራም ….›› እሱ የተናገረውን ሁሉ ለመያዝ ከባድ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እሱ በላይ በላይ ስለሚናገር ከማዳመጥ በሳቅ ነው ያሳለፍነው፡፡ አሁን ቦታ እንደሌለ እሱም አውቋል፡፡ ግን ቀልዱን ቀጥሏል፡፡ እየሳኩም ቢሆን አንዱ ቀልዱ ግን ትንተና ሆነብኝ፡፡ ሳቄን አስቆመኝ፡፡ አስገረመኝ!

Taxi-Politics Ethiopia

ሰው መጠጋት ተስኖታል፡፡ የት ይሄዳል? እየቀለደ የሚጭነው ልጅ ግን በዛው ፖለቲካም ያወራል፡፡ ሰው አልጠጋለት ሲል ‹‹ተጠጉላቸው! ተጠጉላቸው እንጅ! ያው ከዚህ ሀገር መጠጋጋት እንጅ መተካካት የሚባል ነገር የለም፡፡ ተጠጉላቸው….›› ብሎ ሰውን ከታክሲዋ ጣራ በላይ አሳቀው፡፡ ግሩም ትንታኔ ነው፡፡ ‹‹ምሁራን›› በ10ና በ20 ገፅ ‹‹ጥናታዊ ፅሁፍ›› ሲገልፁት ያልሰማሁት ትንታኔ፡፡

እውነቱን ነው፡፡ መጠጋጋት እንጅ መተካካት የሚባል ነገር ብዙም አይታይም፡፡ እኔን የገረመኝ የእሱ ቀልድና ትንታኔ ብቻ አይደለም፡፡ የሰው ሳቅ ጭምር እንጅ፡፡ የታፈነው ህዝብ የሚቀልድለት ወይንም የሚናገርለት ሲያገኝ ፍርስ እስኪል ይስቃል፡፡ የሚፈራራው፣ የሚጠራጠረው መንገደኛ አይን ገላጭ ሲያገኝ ከጎኑ ምን እንዳለም ጭምር ይረሳዋል፡፡ በሬዲዮና በቴሊቪዥን ስለ መተካካት ብዙ ቢወራም ከልቡ አልገባም፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ በውል የሚያውቀው መጠጋጋትን እንጅ መተካካት የሚባል ነገር እንደሌለ ነው፡፡ ታክሲም ውስጥ በፖለቲካውም!

ጋዜጠኛ ግሩም ተክለኃይማኖት ተፈታ

በየመን ሁቲ አማጽያን እጅ ለእስር ተዳርጎ የነበረው ጋዜጠኛ ግሩም ተክለኃይማኖት ከእስር ተፈትቶ ከቤተሰቡ ጋር ተቀላቅሏል። ጋዜጠኛ ግሩም ተክለኃይማኖት የታሰረበት ምክንያት ይደግፈው በነበረ አንድ ስደተኛ ኢትዮጵያዊ ጥቆማ ሲሆን ” በስደተኛው ስም እርዳታ ይሰበስባል ፣ ስለየመን የተለያዩ መረጃዎችም ወደ ውጭ ያቀብላል ” የሚል ክስ ተመስርቶበት ነበር ።

ጋዜጠኛ ግሩም ተ/ኃይማኖት ከልጁ ጋር

ጋዜጠኛ ግሩም ተ/ኃይማኖት ከልጁ ጋር

ጉዳዩን ያጣራው ፖሊስ በቀረበው ክስ ዙሪያ ጭብጥ መረጃ ማስረጃ በማጣቱ ግሩም በነጻ ተለቋል ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የከሳሽ ምስክር ሆነው የቀረቡት አብዛኛው ምስክሮች ” እውነትን በጥቅም አንለውጥም ” በሚል ከሳሽን በመክዳት ወደ ህሊናቸው መመላሳቸው ታውቋል ።

%d bloggers like this: