ለይቅርታ ያመለከተችው ‘ዘማሪት’ ምርትነሽ ጥላሁን: በምልአተ ጉባኤው ፊት ቀርባ አስረዳች፤ በይቅርታ ተቀበላት፤ በቡራኬ አሰናበታት

• በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስተባባሪነት የሚዲያ መግለጫ ትሰጣለች፤
• ለሌሎችም መመለስ ጥረት እንድታድርግ ብፁዓን አባቶች አሳሰቧት፤
• “ቤተ ክርስቲያን የይቅርታ ቤት ናት፤ጥፋታቸውን አምነው ከመጡ እንቀበላቸዋለን፤” /ብፁዓን አባቶች/
†††
Singer Mirtenesh Tilahun & EOTC Holy Synod
ፎቶ፡ ዘማሪት ምርትነሽ ጥላሁን እና የኢ.ኦ.ተ.ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ

የቅዱስ ሲኖዶስን የምሕረት ጥሪ በመቀበል፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮና ሥርዓት ከሚገዳደረው የእነበጋሻው ደሳለኝ ሕገ ወጥ ቡድን፤ ራሷን ለይታ፣ ይፋዊ የይቅርታ ጥያቄ ያቀረበችው ‘ዘማሪት’ ምርትነሽ ጥላሁን፣ የምልአተ ጉባኤውን ይቅርታ አገኘች፡፡

የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን በተመለከተ፣ ለጥፋተኞችና ለበደለኞች እንደጥፋታቸው መጠን ምሕረት የመስጠት፣ ይቅርታ የማድረግና አስፈላጊ ከኾነም በቀኖና የመቅጣት ሥልጣን ያለው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በዛሬ፣ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የቀትር በኋላ ውሎው፣ የ‘ዘማሪት’ ምርትነሽን ማመልከቻ ተቀብሎ ይቅርታ አድርጎላታል፡፡

የይቅርታ ማመልከቻዋ፣ በምልአተ ጉባኤው ፊት በንባብ ሲሰማ፣ ከሕገ ወጥ ቡድኑ ጋራ በአባሪነት ትንቀሳቀስ እንደነበር የጠቀሰችው ‘ዘማሪት’ ምርትነሽ፣ ጥፋት መፈጸሟን አምና ይቅርታ እንዲደረግላት ጠይቃለች፡፡

“ከእነርሱ ጋራ የነበርኩ ቢኾንም፣ የዓላማቸው ተከታይ አይደለሁም፤” ያለችው ‘ዘማሪት’ ምርትነሽ፣ ሕገ ወጡ ቡድኑ ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ እንቅስቃሴ በማድረጉ ለመለየት መወሰኗን ገልጻለች፡፡ “እነርሱ ወደ ሌላ እምነት ቢሔዱም የእኔ እምነቴ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነው፤ ወዳሳደገችኝ ቤተ ክርስቲያኔ ተመልሻለሁ፤ አስተምህሮዋንና ሥርዓቷን ጠብቄ እኖራለሁ፤” በማለት ውሳኔዋን ለምልአተ ጉባኤው አረጋግጣለች፡፡
በይፋ ለመመለስ መወሰኗን አድንቀው ምክር የሰጡ ብፁዓን አባቶች፣ “ተቀብለንሻል” ብለዋታል፡፡ እንደ እርሷ፣ ጥፋታቸውን አምነው የሚመለሱ ሌሎችም ካሉ፣ የይቅርታ ቤት የኾነችው ቤተ ክርስቲያን እጆቿን ዘርግታ እንደምትቀበላቸው አስታውቀዋል፤ የበኩሏን ጥረት እንድታደርግም አበረታተዋታል፡፡

በመጨረሻም፣ ቡራኬ እንድትቀበል የታዘዘችው ምርትነሽ ጥላሁን፣ ከርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ፊት ወድቃ መስቀል ከተሳለመች በኋላ በይቅርታና ቡራኬ መሰናበቷ ተገልጿል፡፡
በቅርቡም፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤቱ አስተባባሪነት፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ቴሌቪዥንና ጋዜጣ ጨምሮ ለብዙኃን መገናኛዎች መግለጫ እንደምትሰጥ ተጠቁሟል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው፣ የምርትነሽ ጥላሁንን የይቅርታ ጥያቄ ተቀብሎ ምሕረት ያደረገላትና በቡራኬ ያሰናበታት፣ የተሐድሶ ኑፋቄ ተላላኪ በጋሻው ደሳለኝን አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን በለየበት ማግሥት መኾኑ ትኩረት ያሰጠዋል፡፡

ከሕገ ወጥ ቡድኑ ተለይታና የምሕረት ጥሪውን ተቀብላ ለመመለስ ለወሰነችው ምርትነሽ ጥላሁን፣ በዛሬው ዕለት የተደረገላት ሲኖዶሳዊ ይቅርታና አቀባበል፣ ብዙዎች፣ ራሳቸውን ከኑፋቄው ተጽዕኖ ቶሎ በማላቀቅ፣ ዛሬ ነገ ሳይሉ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ የሚያበረታታ አብነታዊ እንደ ኾነ አያጠያይቅም፡፡

ምንጭ፦ ሐራ ተዋሕዶ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: