አነጋጋሪዉ የክልል ፍርድ ቤቶች ስልጣን በፌደራል ጉዳዮች ላይ!
በቃሉ ፈረደ
“የአማራ ክልል ዳኞች እና ዓቃቢያነ ህጎች ድምፅ” ገፅ ላይ የተወሰደ ጠቃሚ ትንታኔ
አሁን አሁን የክልል ፍርድ ቤቶች በፌደራል ጉዳይ ላይ ያላቸዉን የዉክልና ስልጣን አስመልከቶ አዲስ የክርክር ምዕራፍ እየተነሳ ይመስላል፡፡ እስካሁን ይህ ጉዳይ አነጋጋሪ ሳይሆን ቢቆይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትበሚታዩ ጉዳዮች በተለይም ከሽብረተኝነት ክስ ጋር በተገናኘ ጉዳዩ ተደገጋግሞ እየተነሳ ይገኛል፡፡ ከተነሱ ጉዳዮች ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ፤
ወንጀል ችሎት ከተወሰኑት ዉስጥ፡-
1ኛ. የወልቃይት ሕዝብ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት ድርጊቱን ፈፀምን የተባለዉ በአማራ ክልል ዉስጥ ስለሆነ በክልሉ በሚገኙ ፍርድ ቤት ጉዳያችን ሊታይ ይገባል በማለት መቃወሚያ አቅርበዉ መቃወሚያቸዉ ዉድቅ
ተደርጓል፡፡
– –
2ኛ. የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ጨምሮ 22 ተከሳሾች የተከሰስንበት ወንጀል ተፈፀመ የተባለዉ በኦሮሚያ ክልል በመሆኑ ጉዳያችን ሊታይ የሚገባዉ በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነዉ በማለት የፍርድ ቤቱ ስልጣን ላይ መቃወሚያ አንስተዉ ነበር፡፡ ችሎቱም ሃምሌ 19-2008 ዓ.ም በሰጠዉ ብይን የፀረ-ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 31 የሽብር ክሶችን የማየት ስልጣን የፌደራል ፍርድ ቤት መሆኑን በመጥቀስ መቃወሚያቸዉን ዉድቅ
አድርጎታል፡፡
– –
3ኛ. በተመሳሳይ በእነ ብርሃኑ ሙሉ እና ነጋ የኔዉ መዝገብ ክስ የቀረበባቸዉ ተከሳሾች ወንጀሉን ፈፀምን የተባለዉ በአማራ ክልል በመሆኑ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 99 እና 100 መሰረት ክሱ ሊታይ የሚገባዉ ድርጊቱ ተፈጸመበት በተባለ ቦታ ሊሆን ይገባል የሚል መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ፍርድ ቤቶች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ህጉ ስልጣን የተሰጣቸዉ አገሪቱ በአሃዳዊ ሥርዓት ሥር በነበረችበት ጊዜ ስለሆነ አሁን ላለዉ ፌደራላዊ ሥርዓት ተፈጻሚነት የለዉም፤ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 78 በፌደራል ጉዳይ ለክልል ፍርድ ቤቶች ተሰጥቶ የነበረዉ የዉክልና ስልጣን የሚቆየዉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል ፍርድ ቤቶችን በክልሎች እስኪያቋቁም በመሆኑና በአዋጅ ቁጥር 322/95 መሰረት በአፋር፣ደቡብ ሕዝቦች፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉልና ጋምቤላ ክልሎች ስለተቋቋሙ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የዉክልና ስልጣኑን ስላጣ የተከሳሾች መቃወሚያ ተቀባይነት የለዉም በማለት ጥቅምት 23-2010 ዓ.ም በዋለዉ ችሎት በአብላጫ ወስኗል፡፡
– –
እነዚህ እና ሌሎች ተመሳሳይ ዉሳኔዎች በሕግ ባለሙያዎች መካከል አወያይ መሆን ጀምረዋል፡፡ ጉዳዩን ከቀረበበት አዉድ መመልከቱ አስፈላጊ ቢሆንም ሕጉና መርሁ ምን እንደሚል ከስሩ በመመልከት እኛም የድርሻችን እንበል፡፡
–
#የክልል ፍርድ ቤቶች በፌደራል ጉዳይ ያለቸዉ ስልጣን የሕግ ማዕቀፍ
– –
ፍርድ ቤቶች በሕግ ያላቸዉ የመዳኘት ስልጣን አንድም ከሕገ መንግስት ወይም ሕግ አዉጭዉ በሚያወጣቸዉ ሕጎች ሊወሰን ይችላል፡፡ በአገራችን የፌደራሉ ሆነ የክልሉ ፍርድ ቤቶች በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 78(2) እዉቅና ተሰጥቷቸዉ የተቋቋሙ ናቸዉ፡፡ የክልል ፍርድ ቤቶችም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስካልተቋቋመ ድረስ የፌደራል ጉዳዮች ስልጣን በግልፅ እንደተሰጣቸዉ በግልፅ ተቀምጧል፡፡
– – –
#የፌደራል ፍርድ ቤቶች በክልሎች ለምን ይቋቋማሉ?
– –
የፌደራል ሥርዓት የሚከተሉ አብዛኞቹ አገሮች የፌደራልና የክልል ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም የሁለትዮሽ የፍርድ ቤት አወቃቀር ስርዓት ይከተላሉ፡፡ በክልሎችም የፌደራልን ጉዳይ የሚመለከቱ ፍርድ ቤቶች የሚሰረቱበትን ስርዓት አብረዉ ይዘረጋሉ፡፡ ጥያቄዉ የሚሆነዉ በክልሎች ለምን የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋም አስፈለገ የሚለዉ ነዉ፡፡
በመስኩ ያጠኑ ልሒቃኖች የፌደራሉን ፍርድ ቤት በክልል እንዲያቋቋም የሚያደርገዉ ትልቁ ገፊ ምክንያት ስጋት ነዉ ይላሉ፡፡ ትልቁ ስጋትም ክልሎች የፌደራሉን ጉዳይ ወይም ፖሊሲ እንደራሳቸዉ አድርገዉ ላያስፈጽሙት ይችላሉ የሚለዉ እንደሆነ ይገልጹና፤ ይሄ ጥርጣሬ ደግሞ የክልል ፍርድ ቤቶች አቅም ላይ ሙሉ እምነት ካለመኖርም ይመነጫል ይላሉ፡፡ በተጨማሪም የፌደራሉን ህግ ከክልል ክልል በተለያዬ ሁኔታ ሊተረጎም ስለሚችል ወጥነት ያለዉ የሕግ አተረጓጎም እንዳይኖር ሊያደርግ ስለሚችል የፌደራል ፍርድ ቤቶች በክልል መቋቋማቸዉ አጠያያቂ እንዳልሆነ ይገልፃሉ፡፡
– –
የፌደራል ፍርድ ቤቱን ከማደረጃት ዉክልና መስጠት ተመራጭ የሆነዉም በክልሎች የፌደራል ፍርድ ቤት ለማቋቋም ከወጪ እና ከሰዉ ሃይል አንጻርም አስቸጋሪ ስለሚያደርገዉ እንደሆነ በጉዳዩ ላይ ጥናት ደረጉ አካሎች ይገልፃሉ፡፡ለሁሉም ክልሎች የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይቋቋም ቢባል ተቋሙ ከሚፈልገዉ የሰዉ ሃይል ጀምሮ ሰፊ እና የረጅም ጊዜ ስራ የሚጠይቅ በመሆኑ በዉክልና እያሰሩ ስርዓቱን በሂደት መገንባት የሕግ አዉጭዉ
ገፊ ምክንያት እንደሚሆን መገንዘብ ይቻላል፡፡
– –
#የክልል ፍርድ ቤቶች ያላቸዉ የዉክልና ስልጣን አይነኬነት!
– –
የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 78(2) አማርኛዉ ድንጋጌ በግልፅ እንዳስቀመጠዉ የፌደራል ፍርድ ቤቶች በክልል እስካልተቋቋሙ ድረስ በፌደራል ጉዳይ የክልል ፍርድ ቤቶች ስልጣን እንዳላቸዉ ነዉ፡፡ የክልል ፍርድ ቤቶች በፌደራል ጉዳይ ያላቸዉን ስልጣን የሚያጡት በክልሉ ፌደራል ፍርድ ቤት ሲቋቋም ብቻ ነዉ፡፡ በዚህ ድንጋጌ መርሁ የፌደራል ጉዳይ በክልል ፍርድ ቤቶች በዉክልና እንደሚታይ ሲሆን በልዩ ሁኔታ አስፈላጊ ሆኖ እስካልተገኘ ድረስ የክልል ፍርድ ቤቶች የፀና ስልጣን የሚኖራቸዉ ይሆናል፡፡ አሁን በቅርብ እየታዬ ባለዉ ሁኔታ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የክልል ፍርድ ቤቶች በፌደራል ጉዳይ በሕገ መንግስቱ የተሰጣቸዉን የመዳኘት ስልጣን እየተቀበሉት አይመስልም፡፡
– –
ለክልል ፍርድ ቤቶች ዉክልናዉን የሰጠዉ ሕገ መንግስት እንጅ የፌደራሉ ፍርድ ቤት አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት የፌደራሉ ፍርድ ቤት የእኔን ጉዳይ ለማየት የተወከልክና በፈለግሁት ጊዜ ጉዳዬን ማየት እችላለሁ ለማለት የሕግ መሰረት የለዉም፡፡ ምክንያቱም ይህ ዉክልና ተራ ከዉል የሚመጣ ዉክልና ሳይሆን ከሕግ የሚመነጭ ዉክልና ነዉ፡፡ በሕግ የተሰጠ ዉክልና ደግሞ ሊነሳ የሚገባዉ አንድም ሕጉን በማሻሻል አልያም በሕጉ የተቀመጠዉ ሁኔታ ሲሟላ ነዉ፡፡ ክልሎች በፌደራል ጉዳይ ያላቸዉን ስልጣንም በፌደራል ፍርድ ቤቶች ስልጣን ሊነጠቁ አይችሉም፡፡ ስልጣናቸዉ ሊወሰድባቸዉ የሚችለዉ ወይ የዉክልና ስልጣን የሰጣቸዉን የሕገ መንግስት ድንጋጌ በማሻሻል ወይም በሕገ መንግስት የተቀመጠዉን ሁኔታ የፌደራል ፍርድ ቤቶች በክልሎች ሲቋቋሙ ብቻ ነዉ፡፡
እስካሁን ባለዉ ሁኔታም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማደረጃ አዋጅ ቁጥር 322/1995 መሰረት ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተቋቋመላቸዉ አፋር፣ ቤንሻንጉል፣ጋምቤላ፣ሶማሌ እና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ብቻ ናቸዉ፡፡ በሌሎቹ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባልተቋቋመባቸዉ የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ሐረሪና ትግራይ ክልል የፌደራል ጉዳዮች የክልል የፍርድ ቤቶች እስካሁን የፀና ስልጣን እንዳላቸዉ ነዉ፡፡ በአምስቱ ክልሎች የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መቋቋምም ከሕግ መርህ ሆነ ከምክንያታዊ መመዘኛ አንጻር ሌሎች ክልሎች ያላቸዉን ስልጣን ሊያሳጣ የሚችል አይደለም፡፡
– –
#የወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርኣት ህጉ ተፈጻሚነት ወሰን፡-
– –
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሕገ መንግስቱ የተሰጠዉን የዉክልና ስልጣኑ ተነስቷል በማለት ሲወስን የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 99 እና 100 አሁን ባለዉ የፌደራል ስርዓት የፍርድ ቤቶችን ስልጣን ለመወሰን ስልጣን እንደሌለዉ ጠቅሷል፡፡ ይህ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓትህ ሕግ አገሪቱ አሃዳዊ የመንግስት ሥርዓት ስርትዳደር በነበረበት ወቅት የወጣ ሕግ ቢሆንም አሁንም ሁሉም የወንጀል ክርክሮች የሚመሩበት ስነ-ስርዓት ሕግ ሆኖ ቀጥሏል፡፡የወንጀል ክስ የሚታይበትን ፍርድ ቤት የሚወስነዉ የሕግ ክፍልም አሁን ባለዉ ሁኔታ እየተሰራበት ያለ ሲሆን ካለዉ የፌደራል ሥርዓት ጋርም የሚጋጭ ነገር የለዉም፡፡
ወንጀል በተፈፀመበት ቦታ ክስ መታየቱም ከየትኛዉም ሕግ ጋር የሚጋጭ አይደለም፡፡ ክልሎች የፌደራልን ጉዳይ እየተመለከቱ የሚገኙት በሕገ-መንግስት ድንጋጌ ተሰጣቸዉ ስልጣን እንጅ በዚህ የስነ-ስርዓት ሕግ አይደለም፡፡ ክልሎች በፌደራል ጉዳዮች ላይ ያልተሻረ እስካሁን የፀና የማየት መብት እስካላቸዉ ድረስ የስነ-ስርዓት ሕጉ ስጋት አይሆንም፡፡
– – –
በአንድ ጉዳይ በስረ-ነገር ደረጃ እኩል ስልጣን ያለቸዉ የፌደራልና የክልል ፍርድ ቤቶች ከየትኛዉ ፍርድ ቤት ክርክሩ ይቅረብ የሚለዉን የሚመልሰዉ ስለ ግዛት ክልል የተቀመጠዉ የስነ-ስርዓት ሕጉ በመሆኑ ካልተሻረ በስተቀር ተፈፃሚ ከመሆን የሚገድበዉ ነገር አይኖርም፡፡ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጎንደር ክላስተር ምድብ ችሎት እየታዬ የሚገኘዉ የኮሎኔል ደመቀ ጉዳይ ለዚህ ማሳያ ነዉ፡፡ ኮሎኔል ደመቀ በግልጽ ክስ የቀረበበት የፀረ-ሽብርተኛ አዋጅ ቁጥር 652/2001 ተላልፏል በሚል ሲሆን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክሱን እየተመለከተ ያለዉ የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 99 እና 100 መሰረት በማድረግ ነዉ፡፡ ይህ የስነ-ስርዓት ሕግ ድንጋጌም ለኮሎኔል ደመቀ ጉዳይ ሲሆን ተፈፃሚ የሚሆን ለሌሎች ተከሳሾች ሲሆን ደግሞ የሚታለፍ አይደለም፡፡
– – –
#የፀረ -ሽብርተኛ አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 31 እና ሕገ- መንግስቱ
አንቀጽ 78(2)
– – –
የፌደራል ፍርድ ቤቶች የግዛት ክልል ስልጣን ተቃዉሞ ሲቀርብላቸዉ አብዛኛዉን ጊዜ መቃወሚያዉን ዉድቅ የሚያደርጉት የፀረ-ሽብርተኛ አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 31 በመጥቀስ ነዉ፡፡ በዚህ ድንጋጌ የሽብርተኝነት ወንጀል የፌደራል ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስልጣን እንደሆነ ይናገራል፡፡ በአዋጁ የሽብርተኛነት ጉዳይ የፌደራል ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስልጣን ስለመሆኑ ቢገልፅም በግልፅ የሽብርተኝነት ጉዳይ በክልሉ ባሉ አቻ ፍርድ ቤቶች በዉክልና ሊታይ እንደማይችል ያስቀመጠዉ ገድብ የለም፡፡ ይህ የፀረ-ሽብር አዋጅ ሲተረጎም ሆነ ስለፍርድ ቤት ስልጣን የሚገልጸዉ ድንጋጌ ሊተረጎም እና ሊፈፀምም የሚገባዉ ከሕገ መንግስቱ አንቀፅ 78(2) ጋር በማጣመር ነዉ፡፡ በዚሕ የሕገ መንግስት ድንጋጌም የክልል ፍርድ ቤቶች የፌደራል ፍርድ ቤት ባለ,ልተቋቋመበት ሁኔታ ስልጣን ያላቸዉ ስለመሆኑ ስለሚገልጽ በተመሳሳይ የሽብርተኝነት ወንጀሎችንም ለማየት ስልጣን አላቸዉ፡፡ ፀረ-ሽብርተኛ አዋጁንም በመጥቀስ የሽብረተኝነት ወንጀሎች የሚታዩት በፌደራል ፍርድ ቤቶች ብቻ ነዉ ለማለት አይቻልም፡፡
– –
#በፌደራል ጉዳይ በክልልና ፌደራል ፍርድ ቤቶች መካከል የሚፈጠር የስልጣን ግጭት!
– –
የፌደራል ጉዳዮች ሕግን፣ተከራካሪ ወገንን እና ቦታን መሰረት አድርገዉ ሊመሰረቱ እንደሚችል በፌደራል ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 3 ተገልፀዋል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች አንድም ፌደራል ክፍተኛ ፍርድ ቤቱ በተደራጄበት ቦታ (አዲስ አበባ፣ድሬደዋ እንዲሁም የፈደራል ፍርድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተደራጄባቸዉ አምስት ክልልሎች) እንዲሁም በሌላ ሁኔታ የፌደራል ፍርድ ቤት ባልተደራጀባቸዉ ግን በዉክልና ጉዳዩን መመልከት በሚችሉ ክልል ፍርድ ቤቶች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጉዳዩ የፌደራል ጉዳይ በመሆኑ ስልጣን ሲኖራቸዉ የዉክልና ስልጣን ያላቸዉ የክልል ፍርድ ቤቶችም ደግሞ ከሕገ-መንግስት የመነጨ ጉዳዩን የመዳኘት ሰልጣን አላቸዉ፡፡ ሁለቱም ፍርድ ቤቶች እኩል በጉዳዩ ላይ ከሕግ የመነጨ ስልጣን ያለቸዉ ከሆነ በስረ-ነገር ስልጣን (material jurisdiction) ደረጃ ተመሳሳይ ወይም እኩል
ስልጣን አላቸዉ ማለት ነዉ፡፡
– –
በአንድ ጉዳይ ላይ በስረ-ነገር ስልጣን ደረጃ እኩል ወይም ተመሳሳይ ስልጣን ያላቸዉ ፍርድ ቤቶች ካሉ ደግሞ ጉዳዩ ሊፈታ የሚችለዉ ወይም ክርክሩ ሊታይ የሚገባዉ የግዛት ክልል ስልጣን (Local jurisdiction) መሰረት ባደረገ መልኩ ነዉ፡፡ የግዛት ክልል ስልጣን የሚባለዉ በወንጀል ጉዳይ ወንጀሉ በተፈፀመበት ወይም የወንጀሉ ዉጤት በተገለጸበት ስፍራ ለመሆኑ እና ጉዳዩ ሊታይ የሚገባዉም በዚህ ስፍራ በሚገኝ ፍርድ ቤት ለመሆኑ ከወ/መ/ስ/ስ/ህ/ ቁጥር 99 እና ከታዮቹ ድንጋጌ መረዳት የሚቻል ነዉ፡፡ በዚሁ በስነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር 107 መሰረት ክሱን የሚያቀርበዉ ዓቃቤ ሕግ ነገሩ የሚታይበትን ፍርድ ቤት ሊመራ እንደሚችል ቢያስቀምጥም የከሳሹ ምርጫ ተቃወሞ ሊቀርብለት አይገባም ማለት አይቻልም፡፡ ተከሳሹ ክስ የቀረበበት ሁኔታ መብቴን ይጎዳል ካለ መቃወሚያ ከማቅረብ የሚያግደዉ ነገር አይኖርም፡፡
– –
#የግዛት ክልል ስልጣን አለመከበር የሚያስከትለዉ ስጋት!
– –
የግዛት ክልል ስልጣን ተቃዉሞ የሚቀርበዉ ጉዳዩ የቀረበለት ፍርድ ቤት በስረ- ነገር ደረጃ ስልጣን ኖሮት በግዛት ክልል ስልጣን ደረጃ ግን ድርጊቱ ከተፈፀመበት ወይም ዉጤቱ ከታወቀበት ቦታ ዉጪ ከሚገኝ ፍርድ ቤት መታየት ሲጀምር ነዉ፡፡ ሕጉ ድርጊቱ ተፈፀመ ወይም ዉጤቱ ታወቀ በተባለበት ቦታ ክስ እንዲቀርብ ሲያስቀምጥ በዋናነት መሰረት ያደረገዉ በጉዳዩ ላይ አፋጣኝ እና ፍትሐዊ ዉሳኔ ከመስጠት አንፃር ነዉ፡፡ የአንድ ክርክር አፋጣኝነት የሚገለፀዉም ክርክሩን በአጭር ጊዜ ከማጠናቀቅ አንፃር ሲሆን ፍትሐዊነቱ የሚገለጸዉ ደግሞ ሁለቱም ወገኖች የመደመጥ፣ማስረጃ የማቅረብ መብታቸዉ በእኩልነት
በመጠበቅ እና የተከሳሾችን ሰብዓዊ መብቶች በማስከበር ነዉ፡፡
– –
#ከተከሳሽ መብት አንፃር፡-
– –
የፍርድ ቤቶች የግዛት ስልጣን ካልተከበረ የተከሳሾች መብት ስጋት ዉስጥ ይወድቃል፡፡በወንጀል ክርክር ሂደት አንድ ክርክር ፍትሐዊ የሚባለዉ ከዉጤቱ ሳይሆን ገና ከሂደቱ ጀምሮ በመሆኑ ተከሳሹ በክርክር ሂደት ከአቆያየቱ ጀምሮ የመደመጥ መብቱን ባስከበረ መልኩ ጠብቆ ከተጓዘ ነዉ፡፡ ፍርድ ቤቶችም በግዛት ስልጣን ላይ ተቃዉሞ ሲነሳ ከተከሳሽ መብት አንፃርም ጉዳዩን ሊያዩት ይገባል፡፡ የወንጀል ክስ የቀረበበት አንድ ተከሳሽ ድርጊቱ ተፈፀመ በተባለበት አካባቢ ነዋሪ ከሆነ እና ክርክሩን በማረፊያ ቤት ሆኖ የሚከታተል ከሆነ በዚያዉ አካባቢ መሆኑ በቅርብ በቤተሰብና በወዳጅ የመጎብኘት ሕገ መንግስታዊ መብቱ ይጠብቅለታል፡፡ በተጨማሪም መከላከያ ማስረጃዉን ለማቅረብ እና እዉነቱን ለማስረዳት ምቹ እና ቀላል ሁኔታም ይፈጠርለታል፡፡
አንድ ሰዉ ከቀዬዉ በራቀ ቁጥር ከቦታዉ ርቀት አንፃር የመረጃ ልዉዉጡ ቀልጣፋና ቀላል ስለማይሆን በተከሰሰበት ጉዳይ ማስረጃ ከማሰባሰብ ጀምሮ የሚኖረዉ ሚና ዝቅተኛ ስለሚሆን ተጎጅ ይሆናል፡፡ አንድ ሰዉ ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግስታዊ መብቱን ሊጠቀምበት የሚችለዉ ምቹ ሁኔታ ሲፈጥረለት ነዉ፡፡ ምቹ ሁኔታ በሌለበት ሁኔታ ከቦታዉ ርቆ ታስሮ እንዲሁም ከሳሹ አካል ካለዉ የመደራረደር አቅም ግዝፈት አንፃርም ግምት ዉስጥ ሳይገባ የግዛት ክልል ስልጣንን መወሰን ፍትሐዊ አይሆንም፡፡
በተደጋጋሚ እንደታዬዉ በተለይም ከሽብር ጉዳይ ጋር በተገናኘ ከአማራ ክልል የሚመጡ ተከሳሾች ድርጊቱ ተፈፀመ ከተባለበት ቦታ እና ከሚኖሩበት አካባቢ ርቀዉ ጉዳያቸዉ ስለሚታይ መከላከያ ማስረጃ ማቅረብ ሳይችሉ በመቅረታቸዉ ጥፋተኛ የተባሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ከሚኖሩበት አካባቢም በመራቃቸዉ ለቅጣት ማቅለያ ማስረጃ ሊሆን የሚችላቸዉን ማስረጃ ባለማቅረባቸዉ ፍትሐዊነት እንዲጓደል ሆኗል፡፡
– –
#የፌደራል ስርዓቱን እና የክልሎች ሕልዉና ፡-
– –
የግዛት ክልል ስልጣን መቃወሚያ ሲወሰን የተከሳሾችን መብትና ፍላጎት ብቻ ሳይሆን አገሪቱ የቆመችበትን የፌደራል ስርዓት በጠበቀ መልኩ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በሕገ መንግስቱ እያንዳንዱ ክልል በህግ የተሰጠዉን ስልጣን ከሕግ ዉጪ ማንኛዉም የፌደራል መንግስት ሆነ የመንግስት አካል ሊጥስበት እንደማይገባ የሕግ ድጋፍ አለዉ፡፡ የክልል ፍርድ ቤቶችም በግልፅ በሕግ የተሰጣቸዉን ስልጣን ሊነጠቁ የሚገባ አይደለም፡፡ የግዛት ክልል ስልጣን እያለዉ ስልጣኑን ተጠቅሞ እንዳያይ የሚያደርግ አሰራር ካለ በተዘዋዋሪ የክልሎችን ራስ ገዝነት እና ስልጣን መንጠቅ ወይም ስልጣናቸዉን ማምከን ይሆናል፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የግዛት ክልል ስልጣን ተቃዉሞ ሲነሳባቸዉ ክልሎች ያላቸዉን ስልጣን ስራ ላይ እንዲያዉሉ ጉዳዩ ድርጊቱ ተፈፀመ በተባለበት አቻ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ መደረግ ይኖርበቸዋል እንጅ ከሕገ-መንግስት ለክልል ፍርድ ቤቶች የተሰጠዉን መብት በአንድ ብይን ሊነጥቁ አይገባም፡፡ የክልል ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግስቱ የተሰጣቸዉን የዳኝነት ስልጣን እንዳይጠቀሙ የሚደረግ ከሆነም የፌደራል ሥርዓቱ በራሱ አደጋ ዉስጥ ይወድቃል፡፡
– –
#ከገለልተኛነት እና ያለተፅዕኖ ከመዳኘት መርህ አንፃር፡-
– –
ፍርድ ቤቶች በቅድሚያ ሊያተርፉት የሚገባ የሕዝብ አመኔታ ሊሆን ይገባል። እንደዜጋ በፍርድ ቤቶች ተዳኝቼ ፍትሕ አገኛለሁ የሚል የሕበረተሰብ ክፍል መፍጠር ካልተቻለ የፍትሕ ስርዓቱ በራሱ ለዜጎች ስጋት ይሆናል፡፡ ፍርድ ቤቶችም ከፍትሕ ተቋምነት የአንድ ቡድን ፍላጎት ማስፈፀሚያ መሳሪያ ይሆናሉ፡፡ ለዚህም ነዉ ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸዉ ዉሳኔዎች ገለልተኝነታቸዉን ባስጠበቀ ሊሆን የሚገባዉ፡፡
– –
ክልሎች የፌደራል ጉዳይን እንደራሳቸዉ አድርገዉ ላያስፈጽሙ ይችላሉ የሚለዉ ስጋት የፌደራልን ጉዳይ በክልል የሚመለከት የፌደራል ፍርድ ቤት ለማቋቋም ገፊ ምክንያት እንደሆነ አይተናል፡፡ የፌደራል መንግስቱም ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም በክልሎች እንዲታዩበት የማይፈልገዉም ለዚህ ይመስላል፡፡ በተደጋጋሚ እንደታዘብነዉ ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር በተየያዙ የሚታዩ ጉዳዮች ክልሎች የዉክልና ስልጣናቸዉን ተጠቅመዉ እንዲመለከቱ ከማድረግ ይልቅ ጉዳዮችን ከክልል ፍርድ ቤቶች ስር የማራቅ ስራ ተለምዷል፡፡ ይህ የተለምዶ አሰራር የተከሳሹን መብት በፅኑ የሚጎዳ እና የክልሎችን ሕጋዊ ስልጣን የሚወስድ ከመሆኑ በተጨማሪ የገለልተኛነት ጥያቄ እንዲነሳ የሚያደርግ ነዉ፤እያስነሳም ነዉ፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቶችም ከጉዳዩ የተለዬ ጥቅም እንዳላቸዉ በሚያስመስል መልኩ በግልጽ የተሰጠዉን የክልሎች የግዛት ስልጣን አለማክበር ደረጃም ደርሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተከሳሾች በፌደራል ፍርድ ቤቱ ላይ ያላቸዉን እምነት እንዲሸረሽረዉም አድርጓል፡፡
– –
በተለዬ መልኩ የሽብርተኛ ወንጀል ተከሳሾች የፌደራሉ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ እየደረሰባቸዉ ስላለዉ የመብት ጥሰት፣ቶርቸር እና ያለመደመጥ መብታቸዉን እያስከበረዉ እንዳልሆነ ከመግለጽ እና በችሎትም ዳኞችንም ሃይለ ቃል እስከ መናገር ፍትሕ እናገኛለንም ብለዉ ከማያምኑበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ በተደጋጋሚም እነዚህ ተከሳሾች ከምንንኖርበት እና ድርጊቱ ተፈጸመ ከተባለበት ክልል በሚገኝ ፍርድ ቤት ጉዳያችን ሊታይ ይገባል በማለት የፍርድ ቤት የግዛት ስልጣን ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ ናቸዉ፡፡ አሁን ግን የፍርድ ቤቶችን የግዛት ክልል ስልጣን ጉዳይ ወደ ገለልተኛ እና ያለተፅዕኖ ከመዳኘት መብት ጋር ተገናኝቶ ከፍ ብሎ እተነሳ ነዉ፡፡ ጉዳዩም የግዛት ስልጣን ብቻ ሳይሆን ክሱን ወደ ሌላ ፍርድ ቤት የማዛወር (change of venue) መልክ እንዲይዝም እያደረገዉ ይመስላል፡፡ የዚህም መነሻ የክልል ፍርድ ቤቶች ስልጣን በፌደራል ፍርድ ቤቶች መነጠቅ ያመጠዉ መዘዝ ነዉ፡፡
– –
#እንደመዉጫ!
የፌደራል ፍርድ ቤቶች በአዋጅ ያልተቋቋመባቸዉ ክልሎች በግልጽ ከሕግ የመነጨ የፌደራል ጉዳይን የማየት ስልጣን አላቸዉ፡፡ ስልጣናቸዉንም የሚያጡት በክልሉ የፌደራል ፍርድ ቤት በአዋጅ ከተቋቋመ ወይም ስልጣን የሰጣቸዉ የሕገ መንግስት ድንጋጌ ከተሻሻለ ብቻ ነዉ፡፡ የፍርድ ቤቶች የግዛት
ስልጣን ጥያቄ ዉጤቱ ትክክለኛ ፍትሕ እንዳይሰጥ ከማድረግ አልፎ የክልሎችን ስልጣን በመጋፋት ለፌደራል ስርዓቱ አደጋ የሚሆን እና ገለልተኛ ያልሆነ የፍትሕ ስርዓት እንዳይኖር የሚያደረግ ነዉ፡፡ ለዚህም የፌደራል ፍርድ ቤቶች የክልል ፍርድ ቤቶች እኩል የስረ-ነገር ስልጣን ያላቸዉንና በግዛት ክልል ደረጃ ክልሎች ቀዳሚ ስልጣን ያላቸዉን ጉዳይ ሊመለከቱ አይገባም፡፡ ክልሎች በሕግ የተሰጣቸዉ ስልጣን ፀንቶ ባለበት ሁኔታ ከስልጣናቸዉ ማግለል አንድምታዉ ለአንድ ወገን መሳሪያ ከመሆን ያለፈ ዓላማ አለዉ ለማለት የሚቻል ስላልሆነ እና ተከሳሾችም በቅርብ ማስረጃ አቅርበዉ የተፋጠነ እና ፍትሐዊ የሆነ ዉሳኔ እንዳያገኙ ምክንያት ስለሚሆን ጉዳዩ መፍትሔ የሚያሻዉ ነዉ፡፡ ፍርድ ቤቶች ሕግና መርህን ካለማክበር ተመልሰዉ ቀልብ ካልገዙ የቁልቁለቱን መንገድ ፈጣን ያደረግዋል ፤ ከዛሬ ነገ ይሻል ይሆናል የምንለዉ የፍትሕ ሥርዓትም አይኖርም፡፡
የፍርድ ቤት ችሎት ትዝብት
ጌታቸው ሺፈራው
“በዚህ ፍትህ በሌለበት ሀገር እንደኛ መሆን መታደል ነው። ዳኛ መሆን ከባድ ነው።……ቢገባችሁ የምንታገለው ለእናንተም ነው!” ቴዎድሮስ አስፋው
“መሳርያ ይዛችሁ የመጣችሁት ስርዓት ለማስከበር ነው። ” መሃል ዳኛው ለማረሚያ ቤቱ ፖሊስ አዛዥ
“የዘገየ ፍትህ እንደተከለከለ ይቆጠራል ያላችሁን ራሳችሁ ናችሁ” ፍሬው ተክሌ
ፎቶው (ከግራ ወደ ቀኝ) የኤርሚያስ ፀጋዬ፣ የፍሬው ተክሌ፣ የዳንኤል ተስፋዬ እና የቴዎድሮስ አስፋው ነው።)
ህዳር 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ትንሳኤ በሪሶ የክስ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው 9 ተከሳሾች ይከላከሉ አይከላከሉ የሚል ብይን ለመስማት ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር። ተከሳሾቹ በተደጋጋሚ ለብይን የተቀጠሩ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ዳኛ ባለመሟላቱ ብይኑ እንዳልተሰራ በመግለፅ ለታህሳስ 6/2010 ዓም የአንድ ወር ቀጠሮ ሰጥቷል።
ከተከሳሾቹ መካከል ያለ ጠበቃ የሚከራከሩት ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬ፣ ፍሬው ተክሌና ቴዎድሮስ አስፋው ፍርድ ቤቱ ስለሰጠው ቀጠሮ እና በማረሚያ ቤቱ ስለሚፈፀም የሕግ ጥሰት አስተያየት ለመስጠት እጃቸውን ቢያወጡም ፍርድ ቤቱ አልተቀበላቸውም።
ፍርድ ቤቱ ” ከአቅማችን በላይ ነው” ብሎ እንዳይናገሩ ሲከለክል ቴዎድሮስ አስፋው ” የታሰርነው የመናገር መብታችን ለማስከበር ስንታገል ነው። አሁንም ፍርድ ቤቱ የመናገር መብታችን ሲከለክል ዝም አንልም” ብሏል። ቴዎድሮስ ይህን ሲናገር መሃል ዳኛው “ምን ልታመጣ?” ብለዋል።
ቴዎድሮስ አስፋው ” በዚህ ፍትህ በሌለበት ሀገር እንደኛ (ተከሳሽ) መሆን መታደል ነው። ዳኛ መሆን ከባድ ነው። የታሰርነው የመናገር መብታችን ለማስከበር ነው። ወደፊትም እንታገላለን። ቢገባችሁ የምንታገለው ለእናንተም ነው!” ብሏል።
ከቴዎድሮስ አስፋው በተጨማሪ ፍሬው ተክሌም ቂሊንጦ እስር ቤት ለፍርድ ቤት ለማቅረብ በፅሁፍ ያቀረበውን አቤቱታ ይዞ እንዳይመጣ እንደከለከለው ገልፆ በቀጠሮውና እስር ቤት በሚፈፅመው በደል ላይ አስተያየት መከልከላቸው አግባብ እንዳልሆነ ገልፆአል። ፍሬው ተክሌ አክሎም “የዘገየ ፍትህ እንደተከለከለ ይቆጠራል ያላችሁን ራሳችሁ ናችሁ” ብሏል።
ቴዎድሮስ አስፋው፣ ፍሬው ተክሌ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬና ዳንኤል ተስፋዬ በችሎት ቅሬታቸውን ባቀረቡበት ወቅት ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ከችሎት እንዲያስወጣቸው ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ በፖሊስ ከችሎት እንዲወጡ ተደርገዋል። አራቱ ወጣቶች በፖሊስ ከችሎት እንዲወጡ ሲደረጉም ቅሬታቸውን ሲናገሩ ተደምጠዋል። መሃል ዳኛው የማረሚያ ቤት ፖሊስ አዛዡን አስጠርተው ” እኛ አልተመቸንም ስንል እንደፈለጉ መጮህ የለባቸውም። መሳርያ ይዛችሁ የመጣችሁት ስርዓት ለማስከበር ነው። ” ብለዋል።
ችሎት እየተከታተሉ የነበሩት የተከሳሽ ቤተሰቦችም ቅሬታቸውን የገለፁ ሲሆን የፍሬው ተክሌ እናት “እግዚያብሄር ይፍረድ!” ብለው ከችሎት ሲወጡ በችሎት ተጠርተው ማስጠንቀቆያ ተሰጥቷቸዋል።
በእነ ትንሳኤ በሪሶ የክስ መዝገብ ስር የተከሰሱት
1. ትንሳኤ በሪሶ
2. ዳንኤል ተስፋዬ
3. ግሩም አስቀናው
4. ቴዎድሮስ አስፋው
5. ፍሬው ተክሌ
6. ኤርሚያስ ፀጋዬ
7. አሰጋ አሰፋ
8. ጌታቸው ይርጋ
9. ሽቴ ሙሉ እና ክሳቸው የተቋረጠላቸው ሀይሌ ማሞ ናቸው፡፡
ወይዘሪት ንግስት ይርጋ በክሷ ምክንያት በደል እየደረሰባት እንደሆነ ተገለፀ
ጌታቸው ሺፈራው
የ”ሽብር” ክስ የተመሰረተባት ንግስት ይርጋ በክሷ ምክንያት ማረሚያ ቤት ውስጥ በደል እየደረሰባት መሆኑን ጠበቃዋ ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል። ንግስት ይርጋ በቤተሰብ ጥየቃ ገደብ እየተደረገባት መሆኑን ለፍርድ ቤት አቤቱታ ባቀረበችው መሰረት ፍርድ ቤቱ ምንም ገደብ ሳይደረግባት እንድትጠየቅ ቢወስንም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ሳያከብር ቀርቷል።
ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ለምን እንዳላከበረ በችሎት እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ቢልክም ማረሚያ ቤቱ በሁለት ቀጠሮች ቀርቦ አላስረዳም። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ለ3ኛ ጊዜ በሰጠው ትዕዛዝ ዛሬ ህዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም.ሁለት ኃላፊዎች ቀርበዋል።
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የፍትህ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አስቻለው መኮንን የማረሚያ ቤቱን እና የታራሚውን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ንግስት ተለይታ እንደምትጠየቅ፣ እንዲሁም ሁሉን እስረኛ በተመሳሳይ ሰዓት ማስተናገድ ስለማይቻል የንግስት ጥየቃ ሰዓት ከሌሎች እስረኞች የተለየ መሆኑን እና ባስመዘገበችው የቤተሰብ አባላት እየተጠየቀች መሆኑን አስረድተዋል።
ንግስት ይርጋ በበኩሏ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ስትገባ የሚጠይቋትን አስመዝግቢ መባሏንና ከተመዘገቡት ውጭ ያሉና 720 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ሊጠይቋት የሚመጡ ዘመድና ወዳጆቿ አልተመዘገባችሁም እየተባሉ እንደሚመለሱ ለፍርድ ቤቱ ገልፃለች። ጉዳዩን ለፍርድ ቤት በአቤቱታ አቅርባ ገደብ እንዳይደረግባት ብይን ቢሰጥም ማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝን አለማክበሩን አስታውሳለች። ማረሚያ ቤቱ ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንደማያከብር በጠየቀችበት ወቅትም የሴቶች ጥበቃ እና ማረፊያ አስተዳደር ኃላፊ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አለም ጥላሁን “ይህን ትዕዛዝ የሰጠው ዳኛ ማን ነው? ማወቅ እፈልጋለሁ።” እንዳሏትና እኚህ ኃላፊ ችሎት ውስጥ እንደሚገኙ ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች።
ሆኖም ፍርድ ቤቱ ችሎት ውስጥ የነበሩትን ኃለፊ ለምን ይህን እንዳሉ መልስ እንዲሰጡ ሳይጠይቃቸው ቀርቷል። ማረሚያ ቤቱ ለፍርድ ቤቱ በፅሁፍ በሰጠው መልስ ላይ የፈረሙት የሴቶች ጥበቃና ማረፊያ አስተዳደር ጥበቃና ደኅንነት ስራ ዘርፍ ኃላፊ ለተ እግዜር ገ/ መድኅን ናቸው። ሆኖም ትዕዛዙን ለፍርድ ቤት ያደረሱትና በቃል መልስ የሰጡት የለተ እግዜር ኃላፊ ናቸው የተባሉት ዋና ሱፐር አለም ናቸው።
ማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ከሰጡት መልስ በተቃራኒ ገደብ እየተደረገባት መሆኑን ንግስት ለፍርድ ቤቱ ገልፃለች። በሀገራችን ባህል የታመመ እና የታሰረ ሰው ማንም እንደሚጠይቀው ያስታወሰችው ንግስት ይርጋ ጠያቂዎቿ መታወቂያ እስከያዙ እና ጠያቂና እሷን የሚቆጣጠሩ ፖሊሶች እስካሉ ድረስ በማንኛውም ሰው መጠየቅ መብቷ እንደሆነ ገልፃለች።
“ማንኛውም የተከሰሰ ሰው ነፃ ሆኖ የመገመት መብት አለው” ያሉት ጠበቃ ሄኖክ አክሉሉ በበኩላቸው፣ ማረሚያ ቤቱ ንግስት ይርጋን በክሷ ምክንያት በደል እየፈፀመባት እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። የፌደራል ማረሚያ ቤቱ ተወካይ ከገለፁት በተቃራኒ ሌሎች እስረኞች ከ3 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ሲጠየቁ ንግስት ይርጋ ከ6 እስከ 7 ሰዓት ባለው አንድ ሰዓት ብቻ እንደምትጠየቅ ገልፀውም ማረሚያ ቤቱ የሚያደርሰውን አድሎ አስረድተዋል። ካስመዘገብሽው ውጭ አትጠየቂም የሚለው የማረሚያ ቤቱ አሰራርም ህገ መንግስታዊ እንዳልሆነ ገልፀዋል።
የንግስት ይርጋ ሌላኛው ጠበቃ አቶ አለልኝ ምህረቱ ፍርድ ቤቱ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት መልስ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ መልስ ለመስጠት የመጡት የእስረኞችን የዕለት ተዕለት ጉዳይ የማይከታተሉ የፌደራል ማረሚያ ቤት ኃላፊ መሆናቸው ጉዳዩን በደንብ እንደማያውቁት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ባስመዘገበቻቸው ዘመድና ጓደኛ እየተጠየቀች ነው ያለ ሲሆን አቶ አለልኝ በበኩላቸው ህገ መንግስቱ የቅርብ ዘመድ እና ጓደኛ ሲል ወሰን እንደሌለው፣ ከዚህ መለስ ተብሎ ሊገደብ እንደማይገባ አብራርተዋል።
በንግስት አቤቱታ ጉዳይ ቀጠሮ የተሰጠው ማረሚያ ቤቱ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለምን እንዳላከበረ ቀርቦ እንዲያስረዳ ለማዳመጥ የነበር ቢሆንም ዛሬም የሁለቱን ክርክር አዳምጦ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በዚህም መሰረት ንግስት ይርጋ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 21 መሰረት ገደብ ሳይደረግባት እንድትጠየቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ንግስት ይርጋ የማይገባ ጭቅጭቅ ማድረጓን ባይገልፁም ፍርድ ቤቱ ” ተከሳሽም የማይገባ ጭቅጭቅ ውስጥ ላለመግባት ጥንቃቄ ያድርጉ፣ ህጉን ለይተው አውቀው ይጠቀሙ” ብሏዋል። ከችሎት ውጭ ያነጋገርኳቸው የንግስት ጠበቆች ንግስት መሰል ባህሪ አሳይታለች ባልተባለበት ፍርድ ቤቱ ያልተነሳ ነገር ላይ ለተከሳሽ ትዕዛዝ መስጠቱ ተገቢ አይደለም ብለዋል። በሌላ በኩል ንግስት ይርጋ ጥርሷን ታማ መድሃኒት ቢታዘዝላትም መድሃኒቱ በታዘዘላት ሰዓት እየተሰጣት እንዳልሆነ አቤቱታ አቅርባለች።
የማረሚያ ቤቱን መልስ ከመስማት በተጨማሪ እነ ንግስት ይከላከሉ ወይስ አይከላከሉ በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ተቀጥረው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ “መዝገቡ ተመርምሯል።ጊዜ አግኝተን ማጠቃለል አልቻልንም” ብሎ ለህዳር 5/2010ዓ•ም ለብይን ሌላ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ የፍርድ ቤት ውሎ
ጌታቸው ሺፈራው
ፍርድ ቤቱ ኮ/ል ደመቀ ያቀረቡትን መቃወሚያ በመቀበል የብሔራዊ ደኅንነት እና መረጃ አገልግሎት ያቀረበው ሪፖርት አልተረጋገጠም ብሏል! በመሆኑም ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ባቀረቡት መቃወሚያ መሰረት የቀረበባቸው ማስረጃ ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ የድምፅ ቅጅ እንዲመጣ ታዟል። ከሌሎች ግለሰቦች ጋር ተደዋውለውባቸዋል የተባሉት የስልክ ቁጥሮችም እንዲጠቀሱና እንዲረጋገጡ ተበይኗል።
ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓም ጎንደር ከተማ ላይ ከሚያስችለው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለብይን ተቀጥረው እንደነበር ይታወሳል። የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ላይ ባቀረበው የ”ሽብር” ክስ የሰው ምስክሮችን ማሰማቱን እንዲሁም፣ የሰነድ ማስረጃዎችን አጠናቅቄ አቅርቤያለሁ በማለት ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ የቀረበባቸውን ክስ ይከላከሉ ወይም መከላከል አይገባቸውም የሚል ብይን እንዲሰጥ ጠይቆ ነበር። በመሆኑም የአቃቤ ህግ ማስረጃዎችን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት27/2010 ዓም ቀጠሮ ይዞ ነበር።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በማስረጃነት ያቀረበው የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት ያዘጋጀውና ከስልክ ምልልስ ተገኘ የተባለ ሪፖርት “ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም የተለያዩ የስልክ ቁጥሮችን በመጠቀም ለነ መብራቱ ጌታሁን፣ አታላይ ዛፌ እና ለሌሎች ግለሰቦች ስልክ በመደወል ስለ “ወንጀሉ” ሲነጋገሩ ቆይተዋል” የሚል ሰፋ ያለ ይዘት ያለው ማስረጃ እንደነበር ተገልፆአል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን ተከላከል ወይንም መከላከል አይገባህም በሚል ብይን ከመስጠቱ በፊት የሰነድ ማስረጃዎቹ በሕጋዊ መንገድ ያልተገኙ ናቸው በማለት ሰፋ ያለ መቃወሚያ አቅርበዋል። ካቀረቧቸው መቃወሚያዎች መካከል ዋናው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከስልክ ምልልስ ያገኘሁት ነው ብሎ ያዘጋጀው ሪፖርት ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ያደረጉት የስልክ ንግግር እንዳልሆነ በሰፊው አትቷል። መቃወሚያው የስልክ ንግግር ቀጥተኛ ማስረጃው ድምፅ በመሆኑ ይህ ማስረጃ ከስልክ ንግግር ወደ ፅሑፍ መለወጡ ከተረጋገጠ ወደ ፅሑፍ የተለወጠው የድምፅ ቅጅ ሊቀርብ ይገባው ነበር የሚል ነበር።
በሌላ በኩልም ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ በስልክ አግኝተዋቸዋል የተባሉ ግለሰቦች ስልክ ቁጥር አለመጠቀሱ ሪፖርቱ ከስልክ ምልልስ የተገኘ መሆኑን ስለማያረጋግጥ የሰነድ ማስረጃው ውድቅ እንዲደረግልን በማለት መቃወሚያዎችን አቅርበው የነበር ሲሆን ፍርድ ቤቱ መቃወሚያዎቹን ተቀብሏቸዋል።
ፍርድ ቤቱ ወደ ዋናው ክርክር ገብቶ ብይን ከመስጠቱ በፊት መቃወሚያ የቀረበባቸው የሰነድ ማስረጃዎች ትክክለኛ መሆናቸው ካልተረጋገጠ በፍሬ ጉዳይ ላይ ብይን መስጠት እንደማይችል መግለፁን ጠበቃ አለልኝ ምህረቱ ገልፀዋል። የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አለልኝ ምህረቱ እንደገለፁት ፍርድ ቤቱ ማስረጃዎቹ ያልተረጋገጡ ስለመሆናቸው ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶችን አስቀምጧል። እነዚህም:_
1) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሪፖርቱን አገኘሁት ያለው ከስልክ ምልልስ ነው ከተባለ፣ በተከሳሽና በሌሎቹ ግለሰቦች መካከል ተደረገ የተባለው የስልክ ምልልስ በትክክል ሊኖር ስለሚችል ወደፅሑፍ መቀየሩን ወይም የተቀነሰ እና የተጨመረበት ነገርም ካለ ይህን ማጣራት አስፈላጊ በመሆኑ፣
2)ከኮለኔል ደመቀ ዘውዱ ጋር ስለ “ሽብር ወንጀል” ተነጋገሩ የተባሉ ግለሰቦች ስልክ ቁጥሮች በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሪፖርት ላይ ስላልተጠቀሱ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ በስልክ አነጋግረዋቸዋል የተባሉት ግለሰቦች የስልክ ቁጥሮች እና ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ተገናኙባቸው ተብለው በሪፖርቱ የተጠቀሱ ስልክ ቁጥሮች የእርሳቸው ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ያስፈልጋል የሚሉ ናቸው።
ፍርድ ቤቱ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ሪፖርትን በማጣራት የሰነድ ማስረጃ ላይ በቀረበው መቃወሚያ ላይ ውሳኔ መስጠት እንዲያስችለውም ሁለት ትዕዛዞችን አስተላልፏል። ትዕዛዞቹም:_
1ኛ) የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ለዐቃቤ ሕግ ማስረጃነት በሪፖርት ያቀረበው ከስልክ ምልልስ ተገኘ የተባለ ሪፖርት ያዘጋጀበትን የስልክ ምልልስ የድምፅ ቅጅ እንዲያቀርብ እና፣
2ኛ) ከኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጋር በስልክ ተገናኙ የተባሉት ግለሰቦች ስልክ ቁጥሮች፣ እንዲሁም እነዚህ ስልክ ቁጥሮች ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ደወሉባቸው ከተባሉት ስልክ ቁጥሮች ጋር ግንኙነት የነበራቸው መሆንን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ዐቃበ ህግ እነዚህን ማስረጃዎች እንዲያቀርብም ለህዳር 19/2010 ዓም ቀጠሮ ተይዟል።
ፍርድ ቤቶች በ”ሽብር ወንጀል” ላይ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ከስልክ ምልልስ ያገኘሁት ነው ብሎ የሚፅፈው ሪፖርትን ለማረጋገጥ የድምፅ ቅጅ በማስመጣት ከማረጋገጥ ይልቅ ሪፖርቱን በቀጥታ እየተቀበሉ ይገኛሉ። በኮ/ል ደመቀ ላይ የቀረበው የደኅንነት ሪፖርቱ ላይ መቃወሚያ ካቀረቡት መካከል አንዱ የሆኑት ጠበቃ አለልኝ በኮ/ል ደመቀ ተቃውሞ ላይ የተሰጠውን ትዕዛዝ ሌሎች መሰል ክሱችን የሚያስችሉ ችሎቶችም ቢጠቀሙበት “ዳኞች ተገዥነታቸው ለህሊናቸውና ለሕጉ ብቻ ነው !” የሚለውን መርህ ማስከበር ይቻል ነበር ብለዋል።
በዶ/ር መረራ ላይ ሁለት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ተሰሙ
ጌታቸው ሺፈራው
የፌደራል አቃቤ ህግ በኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ ዛሬ ጥቅምት 24/2010 ዓም ሁለት ምስክሮች አሰምቷል። ሁለቱም ምስክሮች ታህሳስ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ዶ/ር መረራ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ከኮምፒውተር የወጣን ፅሁፍ የእራሴ ነው ብለው ሲፈርሙ ተገኝተን ታዝበናል ያሉ የደረጃ ምስክሮች ናቸው። ስማቸው ደራራ እና ጌታቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤት ያስመዘገቡት ምስክሮች በአንድ ቀን የታዘቡ እና የሚተዋወቁ ጓደኛሞች እንደሆኑ ገልፀዋል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና
ደራራ (አንደኛ ምስክር) ወደ ማዕከላዊ የሄደበትን ምክንያት ሲጠየቅ ቶሎሳ የሚባል ዘመዱን ሊጠይቅ መሄዱን፣ ብቻዬን ከምሄድ በሚል ሁለተኛ ምስክር (ጌታቸው) አብሮት እንዲሄድ ጠይቆት ከሚሰሩበት መስርያቤት አስፈቅደው አብረው እንደሄዱ እና ፖሊስ ታዛቢ እንዲሆኑት ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ጠይቋቸው እንደተስማሙ ገልፆአል።
በሌላ በኩል ሁለተኛ ምስክር (ጌታቸው) አንደኛ ምስክር (ደራራ) ጋር አንድ ክፍለ ከተማ እንጅ አንድ መስርያ ቤት እንደማይሰሩ፣ ብቻውን በመስርያ ቤት ትዕዛዝ ለመርማሪዎች ሰነድ ለመስጠት እንደሄደ፣ ስራውን ጨርሶ ከመርማሪው ቢሮ ሲወጣ ኮማንደር አሰፋ በተባለ የምርመራ ክፍል ሀላፊ እማኝ እንዲሆን መጠየቁን፣ እሱ ስራዉን ጨርሶ ከወጣ እና እማኝ ለመሆን ፈቃደኛ ከሆነ በኋላ ደራራን እንዳገኘው እንዲሁም አንደኛ ምስክር (ደራራ) ወደ ማዕከላዊ የመጣበትን ጉዳይ የነገረው እማኝ ከሆነ በኋላ እንደሆነ አንደኛ ምስክር ከመሰከረው የተለየ ቃሉን ለፍርድ ቤቱ ሰጥቷል።
በተጨማሪም አንደኛ ምስክር በወቅቱ ዶ/ር መረራ ሹራብ ለብሰው ነበር ሲል ሁለተኛ ምስክር ጅንስ ሱሪና ጅንስ ሸሚዝ ለብሰው ነበር ብሏል። አንደኛ ምስክር (ደራራ) ዶ/ር መረራ በኮማንደር አሰፋ ብቻ ታጅበው ምስክሮቹ ወደነበሩበት ምርመራ ቢሮ እንደገቡ ሲመሰክር፣ ሁለተኛ ምስክር (ጌታቸው) ከኮማንደር አሰፋ በተጨማሪ ሁለት ፖሊሶች ነበሩ ብሏል።
አንደኛ ምስክር ዶ/ር መረራ ወደ ምርመራ ቢሮ እስኪመጡ በግምት ለአንድ ሰዓት ያህል መጠበቃቸውን ሲገልፅ፣ ሁለተኛ ምስክር ( ጌታቸው) በግምት ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ያህል ብቻ እንደጠበቁ ገልፆአል። አንደኛ ምስክር የዶ/ር መረራ ነው ከተባለ ኮምፒውተር ፕሪንት ተደርገው የወጡ ፅሁፎችን በከፊል እንዳነበበ ሲመሰክር ሁለተኛ ምስክር የፅሁፎችን ይዘት ብቻ ሳይሆን ርዕሶችንም አለማንበባቸውን፣ ዶ/ር መረራ አንብበው ሲፈርሙ ታዝበው መፈረማቸውን ገልፀዋል።
በዶ/ር መረራ ላይ ይቀርባሉ ተብለው የነበሩት ሌሎች ሁለት ምስክሮችን ፖሊስ በአድራሻቸው ፈልጎ እንዳላገኛቸው የገለፀ ሲሆን ሁለቱን ቀሪ ምስክሮች ለመስማት ለህዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።