እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱና ንግስት ይርጋ ክሳቸው ተቋርጦ ፤ እነ ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ እና አሳምነው ጽጌ በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑ ተገለፀ
(ዳጉ ሚዲያ) ከወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ህዝባዊ ተቃውሞ በእስር ላይ ከነበሩት ሰዎች መካከል ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፥ አቶ ጌታቸው አደመ፥ አቶ አታላይ ዛፌ፥አቶ ተሻገር ወልደሚካኤል እና ንግስት ይርጋ ጨምሮ የ 101 እስረኞቸ ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እና ወ/ት ንግስት ይርጋ
ክሳቸው እንዲቋረጥ ከተወሰነላቸው እስረኞች መካከል 56 በግንቦት ሰባት፥ 41 እንዲሁም ከኦነግ ጋር ተባብራችኋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው ነበሩ።
ብ/ጄነራል ተፈራ ማሞ እና ብ/ጄነራል አሳምነው ጽጌ
በተያያዘ ዜና፤ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የሚል ክስን ጨምሮ በተለያየ ጉዳይ ተከሰው የተፈረደባቸውና በይቅርታ ከእስር እንዲለቀቁ ከተወሰነላቸው መካከል ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞና ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌን እንደሚገኙብት ተጠቁሟል።
የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ የፍርድ ቤት ውሎ
ጌታቸው ሺፈራው
ፍርድ ቤቱ ኮ/ል ደመቀ ያቀረቡትን መቃወሚያ በመቀበል የብሔራዊ ደኅንነት እና መረጃ አገልግሎት ያቀረበው ሪፖርት አልተረጋገጠም ብሏል! በመሆኑም ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ባቀረቡት መቃወሚያ መሰረት የቀረበባቸው ማስረጃ ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ የድምፅ ቅጅ እንዲመጣ ታዟል። ከሌሎች ግለሰቦች ጋር ተደዋውለውባቸዋል የተባሉት የስልክ ቁጥሮችም እንዲጠቀሱና እንዲረጋገጡ ተበይኗል።
ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓም ጎንደር ከተማ ላይ ከሚያስችለው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለብይን ተቀጥረው እንደነበር ይታወሳል። የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ላይ ባቀረበው የ”ሽብር” ክስ የሰው ምስክሮችን ማሰማቱን እንዲሁም፣ የሰነድ ማስረጃዎችን አጠናቅቄ አቅርቤያለሁ በማለት ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ የቀረበባቸውን ክስ ይከላከሉ ወይም መከላከል አይገባቸውም የሚል ብይን እንዲሰጥ ጠይቆ ነበር። በመሆኑም የአቃቤ ህግ ማስረጃዎችን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት27/2010 ዓም ቀጠሮ ይዞ ነበር።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በማስረጃነት ያቀረበው የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት ያዘጋጀውና ከስልክ ምልልስ ተገኘ የተባለ ሪፖርት “ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም የተለያዩ የስልክ ቁጥሮችን በመጠቀም ለነ መብራቱ ጌታሁን፣ አታላይ ዛፌ እና ለሌሎች ግለሰቦች ስልክ በመደወል ስለ “ወንጀሉ” ሲነጋገሩ ቆይተዋል” የሚል ሰፋ ያለ ይዘት ያለው ማስረጃ እንደነበር ተገልፆአል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን ተከላከል ወይንም መከላከል አይገባህም በሚል ብይን ከመስጠቱ በፊት የሰነድ ማስረጃዎቹ በሕጋዊ መንገድ ያልተገኙ ናቸው በማለት ሰፋ ያለ መቃወሚያ አቅርበዋል። ካቀረቧቸው መቃወሚያዎች መካከል ዋናው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከስልክ ምልልስ ያገኘሁት ነው ብሎ ያዘጋጀው ሪፖርት ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ያደረጉት የስልክ ንግግር እንዳልሆነ በሰፊው አትቷል። መቃወሚያው የስልክ ንግግር ቀጥተኛ ማስረጃው ድምፅ በመሆኑ ይህ ማስረጃ ከስልክ ንግግር ወደ ፅሑፍ መለወጡ ከተረጋገጠ ወደ ፅሑፍ የተለወጠው የድምፅ ቅጅ ሊቀርብ ይገባው ነበር የሚል ነበር።
በሌላ በኩልም ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ በስልክ አግኝተዋቸዋል የተባሉ ግለሰቦች ስልክ ቁጥር አለመጠቀሱ ሪፖርቱ ከስልክ ምልልስ የተገኘ መሆኑን ስለማያረጋግጥ የሰነድ ማስረጃው ውድቅ እንዲደረግልን በማለት መቃወሚያዎችን አቅርበው የነበር ሲሆን ፍርድ ቤቱ መቃወሚያዎቹን ተቀብሏቸዋል።
ፍርድ ቤቱ ወደ ዋናው ክርክር ገብቶ ብይን ከመስጠቱ በፊት መቃወሚያ የቀረበባቸው የሰነድ ማስረጃዎች ትክክለኛ መሆናቸው ካልተረጋገጠ በፍሬ ጉዳይ ላይ ብይን መስጠት እንደማይችል መግለፁን ጠበቃ አለልኝ ምህረቱ ገልፀዋል። የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አለልኝ ምህረቱ እንደገለፁት ፍርድ ቤቱ ማስረጃዎቹ ያልተረጋገጡ ስለመሆናቸው ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶችን አስቀምጧል። እነዚህም:_
1) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሪፖርቱን አገኘሁት ያለው ከስልክ ምልልስ ነው ከተባለ፣ በተከሳሽና በሌሎቹ ግለሰቦች መካከል ተደረገ የተባለው የስልክ ምልልስ በትክክል ሊኖር ስለሚችል ወደፅሑፍ መቀየሩን ወይም የተቀነሰ እና የተጨመረበት ነገርም ካለ ይህን ማጣራት አስፈላጊ በመሆኑ፣
2)ከኮለኔል ደመቀ ዘውዱ ጋር ስለ “ሽብር ወንጀል” ተነጋገሩ የተባሉ ግለሰቦች ስልክ ቁጥሮች በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሪፖርት ላይ ስላልተጠቀሱ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ በስልክ አነጋግረዋቸዋል የተባሉት ግለሰቦች የስልክ ቁጥሮች እና ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ተገናኙባቸው ተብለው በሪፖርቱ የተጠቀሱ ስልክ ቁጥሮች የእርሳቸው ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ያስፈልጋል የሚሉ ናቸው።
ፍርድ ቤቱ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ሪፖርትን በማጣራት የሰነድ ማስረጃ ላይ በቀረበው መቃወሚያ ላይ ውሳኔ መስጠት እንዲያስችለውም ሁለት ትዕዛዞችን አስተላልፏል። ትዕዛዞቹም:_
1ኛ) የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ለዐቃቤ ሕግ ማስረጃነት በሪፖርት ያቀረበው ከስልክ ምልልስ ተገኘ የተባለ ሪፖርት ያዘጋጀበትን የስልክ ምልልስ የድምፅ ቅጅ እንዲያቀርብ እና፣
2ኛ) ከኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ጋር በስልክ ተገናኙ የተባሉት ግለሰቦች ስልክ ቁጥሮች፣ እንዲሁም እነዚህ ስልክ ቁጥሮች ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ደወሉባቸው ከተባሉት ስልክ ቁጥሮች ጋር ግንኙነት የነበራቸው መሆንን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ዐቃበ ህግ እነዚህን ማስረጃዎች እንዲያቀርብም ለህዳር 19/2010 ዓም ቀጠሮ ተይዟል።
ፍርድ ቤቶች በ”ሽብር ወንጀል” ላይ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ከስልክ ምልልስ ያገኘሁት ነው ብሎ የሚፅፈው ሪፖርትን ለማረጋገጥ የድምፅ ቅጅ በማስመጣት ከማረጋገጥ ይልቅ ሪፖርቱን በቀጥታ እየተቀበሉ ይገኛሉ። በኮ/ል ደመቀ ላይ የቀረበው የደኅንነት ሪፖርቱ ላይ መቃወሚያ ካቀረቡት መካከል አንዱ የሆኑት ጠበቃ አለልኝ በኮ/ል ደመቀ ተቃውሞ ላይ የተሰጠውን ትዕዛዝ ሌሎች መሰል ክሱችን የሚያስችሉ ችሎቶችም ቢጠቀሙበት “ዳኞች ተገዥነታቸው ለህሊናቸውና ለሕጉ ብቻ ነው !” የሚለውን መርህ ማስከበር ይቻል ነበር ብለዋል።
በጎንደር ህዝባዊ ተቃውሞ እና ውጥረቱ ቀጥሏል
(አዲስ ሚዲያ) በጎንደር ከተማ የወልቃይት የማንነት ጥያቄን የሚመሩ የኮሜቴ አባላትን ለማሰር በተወስደ እርምጃ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከፍተኛ ግጭት አስከተለ። ግጭቱ የተከሰተው ትናንት ሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ሌሊት ጀምሮ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
የመንግሥት ደህነት እና የፀጥታ ኃይሎች የወልቃይት ማንነት ጥያቄ የሚመሩ ኮሜቴ አባላት መካከል አቶ አታላይ ዘርፌ፣ አቶ ጌታቸው አደመ፣ አቶ መብራቱ ጌታሁንና አቶ አለነ ሻማ በቁጥጥር ስር ያደረገ ሲሆን፣ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ በህግ የምትፈልጉኝ ከሆነ ሲነጋ መምጣት ትችላላችሁ በማለታቸው በተፈጠረው አለመግባባትና ግጭት በግድ እጅ እንዲሰጡ በኃይል በመንቀሳቀሳቸው ኮሎኔሉ እርምጃ መውሰዳቸው ተሰምቷል። ለምንግሥት የፀታ ኃይል እጃቸውን እንዲሰጡ በኃይል የተጠየቁት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፤ ቤታቸው በፀጥታ ኃይል መከበቡን ተሰምቷል፡፡ በተፈጠረው አለመግባባት ሰላማዊ ሰዎች በመንግሥት በመገደላቸው በህዝቡ በተወሰደ የአፀፋ እርምጃ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችም መገደላቸውን የኢሳት ዘገባ አመልክቷል፡፡
መንግሥት ማክሰኞ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጎንደርና ወልቃይት አካባቢን በተመለከተ ማምሻውን በሰጠው መግለጫ በተፈጠረው አለመግባባት 3 የልዩ ሃይል ፖሊሶች ሲገደሉ፣ 5 መቁሰላቸውን አስታውቋል። ይሁን እንጂ መንግሥት ለግጭቱ መንስኤ የወልቃይት ማንነት መብት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል መሆኑን ከመግለፅ በመቆጠብ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን እና ለማዋል የፈለጋቸውን የወለወቃይት ማንነት መብት አስተባባሪ ኮሚቴ አባላትን ከኤርትራ መንግሥት ጋር በማያያዘ ሲወነጅል ተሰምቷል፡፡
በያዝነው 2008 ዓ.ም. ቀደም ሲል የወልቃይት ማንነት መብት ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴ አባላት መካከል አቶ ሲሳይ ሊላይ የሚባሉ የኮሚቴ አባል በትግራይ ክልል ልዩ ኃይል ታግተው ከተሰወሩ በኋላ በአካባቢው ውጥረት መንገሡን ተከትሎ ወህኒ ቤት በማሰር ለፍርድ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡ የእስርና ፍርድ ጉዳያቸውም በሰቲት ሁመራ መቀጠሉ ታውቋል፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ፤ በጎንደር የመንግሥት የኃይል ርምጃን በመቃወም ህዝቡ ንብረትነቱ የህወሓት/ኢህአዴግ የሆነውን ሰላም የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ፣ በተጨማሪ ሌላ መለስተኛ የፀጥታ ኃይሉ ተሽከርካሪ እና በጎንደር ከሚገኙ የህወሓት የንግድ ኩባንያ መደብሮች መካከል የተወሰኑት ላይ የማቃጠል ርምጃ መወሰዱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በተቃውሞው ከጎንደር አዲስ አበባ ያሉ መንገዶችም በድንጋይ ተዘግተው ታይተዋል፡፡