ወይዘሪት ንግስት ይርጋ በክሷ ምክንያት በደል እየደረሰባት እንደሆነ ተገለፀ
ጌታቸው ሺፈራው
የ”ሽብር” ክስ የተመሰረተባት ንግስት ይርጋ በክሷ ምክንያት ማረሚያ ቤት ውስጥ በደል እየደረሰባት መሆኑን ጠበቃዋ ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል። ንግስት ይርጋ በቤተሰብ ጥየቃ ገደብ እየተደረገባት መሆኑን ለፍርድ ቤት አቤቱታ ባቀረበችው መሰረት ፍርድ ቤቱ ምንም ገደብ ሳይደረግባት እንድትጠየቅ ቢወስንም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ሳያከብር ቀርቷል።
ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ለምን እንዳላከበረ በችሎት እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ቢልክም ማረሚያ ቤቱ በሁለት ቀጠሮች ቀርቦ አላስረዳም። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ለ3ኛ ጊዜ በሰጠው ትዕዛዝ ዛሬ ህዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም.ሁለት ኃላፊዎች ቀርበዋል።
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የፍትህ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አስቻለው መኮንን የማረሚያ ቤቱን እና የታራሚውን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ንግስት ተለይታ እንደምትጠየቅ፣ እንዲሁም ሁሉን እስረኛ በተመሳሳይ ሰዓት ማስተናገድ ስለማይቻል የንግስት ጥየቃ ሰዓት ከሌሎች እስረኞች የተለየ መሆኑን እና ባስመዘገበችው የቤተሰብ አባላት እየተጠየቀች መሆኑን አስረድተዋል።
ንግስት ይርጋ በበኩሏ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ስትገባ የሚጠይቋትን አስመዝግቢ መባሏንና ከተመዘገቡት ውጭ ያሉና 720 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ሊጠይቋት የሚመጡ ዘመድና ወዳጆቿ አልተመዘገባችሁም እየተባሉ እንደሚመለሱ ለፍርድ ቤቱ ገልፃለች። ጉዳዩን ለፍርድ ቤት በአቤቱታ አቅርባ ገደብ እንዳይደረግባት ብይን ቢሰጥም ማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝን አለማክበሩን አስታውሳለች። ማረሚያ ቤቱ ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንደማያከብር በጠየቀችበት ወቅትም የሴቶች ጥበቃ እና ማረፊያ አስተዳደር ኃላፊ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አለም ጥላሁን “ይህን ትዕዛዝ የሰጠው ዳኛ ማን ነው? ማወቅ እፈልጋለሁ።” እንዳሏትና እኚህ ኃላፊ ችሎት ውስጥ እንደሚገኙ ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች።
ሆኖም ፍርድ ቤቱ ችሎት ውስጥ የነበሩትን ኃለፊ ለምን ይህን እንዳሉ መልስ እንዲሰጡ ሳይጠይቃቸው ቀርቷል። ማረሚያ ቤቱ ለፍርድ ቤቱ በፅሁፍ በሰጠው መልስ ላይ የፈረሙት የሴቶች ጥበቃና ማረፊያ አስተዳደር ጥበቃና ደኅንነት ስራ ዘርፍ ኃላፊ ለተ እግዜር ገ/ መድኅን ናቸው። ሆኖም ትዕዛዙን ለፍርድ ቤት ያደረሱትና በቃል መልስ የሰጡት የለተ እግዜር ኃላፊ ናቸው የተባሉት ዋና ሱፐር አለም ናቸው።
ማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ከሰጡት መልስ በተቃራኒ ገደብ እየተደረገባት መሆኑን ንግስት ለፍርድ ቤቱ ገልፃለች። በሀገራችን ባህል የታመመ እና የታሰረ ሰው ማንም እንደሚጠይቀው ያስታወሰችው ንግስት ይርጋ ጠያቂዎቿ መታወቂያ እስከያዙ እና ጠያቂና እሷን የሚቆጣጠሩ ፖሊሶች እስካሉ ድረስ በማንኛውም ሰው መጠየቅ መብቷ እንደሆነ ገልፃለች።
“ማንኛውም የተከሰሰ ሰው ነፃ ሆኖ የመገመት መብት አለው” ያሉት ጠበቃ ሄኖክ አክሉሉ በበኩላቸው፣ ማረሚያ ቤቱ ንግስት ይርጋን በክሷ ምክንያት በደል እየፈፀመባት እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። የፌደራል ማረሚያ ቤቱ ተወካይ ከገለፁት በተቃራኒ ሌሎች እስረኞች ከ3 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ሲጠየቁ ንግስት ይርጋ ከ6 እስከ 7 ሰዓት ባለው አንድ ሰዓት ብቻ እንደምትጠየቅ ገልፀውም ማረሚያ ቤቱ የሚያደርሰውን አድሎ አስረድተዋል። ካስመዘገብሽው ውጭ አትጠየቂም የሚለው የማረሚያ ቤቱ አሰራርም ህገ መንግስታዊ እንዳልሆነ ገልፀዋል።
የንግስት ይርጋ ሌላኛው ጠበቃ አቶ አለልኝ ምህረቱ ፍርድ ቤቱ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት መልስ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ መልስ ለመስጠት የመጡት የእስረኞችን የዕለት ተዕለት ጉዳይ የማይከታተሉ የፌደራል ማረሚያ ቤት ኃላፊ መሆናቸው ጉዳዩን በደንብ እንደማያውቁት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ባስመዘገበቻቸው ዘመድና ጓደኛ እየተጠየቀች ነው ያለ ሲሆን አቶ አለልኝ በበኩላቸው ህገ መንግስቱ የቅርብ ዘመድ እና ጓደኛ ሲል ወሰን እንደሌለው፣ ከዚህ መለስ ተብሎ ሊገደብ እንደማይገባ አብራርተዋል።
በንግስት አቤቱታ ጉዳይ ቀጠሮ የተሰጠው ማረሚያ ቤቱ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለምን እንዳላከበረ ቀርቦ እንዲያስረዳ ለማዳመጥ የነበር ቢሆንም ዛሬም የሁለቱን ክርክር አዳምጦ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በዚህም መሰረት ንግስት ይርጋ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 21 መሰረት ገደብ ሳይደረግባት እንድትጠየቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ንግስት ይርጋ የማይገባ ጭቅጭቅ ማድረጓን ባይገልፁም ፍርድ ቤቱ ” ተከሳሽም የማይገባ ጭቅጭቅ ውስጥ ላለመግባት ጥንቃቄ ያድርጉ፣ ህጉን ለይተው አውቀው ይጠቀሙ” ብሏዋል። ከችሎት ውጭ ያነጋገርኳቸው የንግስት ጠበቆች ንግስት መሰል ባህሪ አሳይታለች ባልተባለበት ፍርድ ቤቱ ያልተነሳ ነገር ላይ ለተከሳሽ ትዕዛዝ መስጠቱ ተገቢ አይደለም ብለዋል። በሌላ በኩል ንግስት ይርጋ ጥርሷን ታማ መድሃኒት ቢታዘዝላትም መድሃኒቱ በታዘዘላት ሰዓት እየተሰጣት እንዳልሆነ አቤቱታ አቅርባለች።
የማረሚያ ቤቱን መልስ ከመስማት በተጨማሪ እነ ንግስት ይከላከሉ ወይስ አይከላከሉ በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ተቀጥረው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ “መዝገቡ ተመርምሯል።ጊዜ አግኝተን ማጠቃለል አልቻልንም” ብሎ ለህዳር 5/2010ዓ•ም ለብይን ሌላ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ኢትዮጵያ- የአማራ ህዝብ የመብት ጥያቄና ( #AmharaProtests) በመንግስት የተወሰደው የኃይል እርምጃ
በአማራ የተቃውሞ ድምጽ በሚያሰሙ ዜጎች ላይ የሚደርሰው የመብት ጥሰት ግድያ፣ የእስርና ደብዛ መጥፋት መጠኑ ይለያይ እንጂ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ በተለይም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ አሁንም ድረስ በጎንደር፣ በባህር ዳርና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች ዜጎችን በገፍ የማሰሩ እርምጃ ቀጥሏል፡፡
ወጣት ንግስት ይርጋ በጎንደር ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ
በተቃውሞ ሰልፎች የተሳተፉ ወጣቶችን በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በገፍ ማሰሩ ተቃውሞዎች በበረቱባቸው ከተሞች ከፍተኛ ነው ፡፡ ለምሳሌ በጎንደር ከተማ በሚገኙ 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 5ኛ እና 6ኛ ፖሊስ ጣቢያዎች በጠባብ ክፍሎች ውስጥ በአንድ ጣቢያ በአማካይ እስከ 140 ሰዎች እንደሚታሰሩ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ጎንደር ከተማ ውስጥ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ለሁለት ሳምንታት ታስሮ የነበረ ወጣት ደረጀ ጌቱ (ስሙ የተቀየረ) እንደሚናገረው በጣቢያው ውስጥ አብረውት ታስረው የነበሩት አብዛኞቹ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ መሳተፋችሁ በፎቶ ተረጋግጧል በሚል ለእስር ተዳርገው የነበሩ ናቸው፡፡
በተመሳሳይ በባህር ዳር ከተማ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች እንዲሁ በከተማዋ ተደርጎ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት በተሳተፉ ወጣቶች በገፍ እየታሰሩ ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች አንዳንዶቹ በአጭር ጊዜ ሲታሰሩ እና ሲፈቱ ሌሎች ደግሞ በተደጋጋሚ መታርና መፈተታ እንደሚገጥማቸው ማየት ተችሏል፡፡
በእነዚህ ፖሊስ ጣቢያዎች የሚታሰሩትን ማን እንደታሰረና፣ የት እንደታሰረ ቤተሰብና ዘመድ የማወቅ እድል ቢኖረውም ሌሎች የት እንደታሰሩ ሳይታወቅ ለቀናት፣ ለሳምንታትና ለወራትም የሚከርሙ መኖራቸውም ታውቋል፡፡ እነዚህ የእስር ስፍራዎች በይፋ የማይታወቁና በተቃውሞ እንቅስቃሴው እጃቸው በሰፊው አለበት በሚል መንግስት የጠረጠራቸውን “የሚመረምርባቸው” ናቸው፡፡
ከእነዚህ ድብቅ የእስር ቦታዎች መካከል ለምሳሌ ባህር ዳር አባይ ማዶ ከብአዴን ጽ/ቤት ጀርባ የሚገኝ ቀድሞ የመሳሪያ መጋዘን የነበረ ስፍራ ይገኝበታል፡፡ በዚህ ቦታ የሚታጎሩ ወጣቶችን ቤተሰቦቻቸው ለመጠየቅም ሆነ በዚያ ስፍራ ስለመኖር አለመኖራቸው ለማወቅ እንደማይችሉ ታስረው የተፈቱና፣ ታስረው እንደነበርም እንዳይናገሩ ማስፈራሪያ ደርሷቸው የወጡ ይመሰክራሉ፡፡ አበበ አስረስ (ስሙ የተቀየረ) በዚህ ድብቅ የእስር ቦታ ለ17 ቀናት ሲሰቃይ ቆይቶ መለቀቁን ይናገራል፡፡
‹‹ቦታው የሆነ መጋዘን ነገር ነው፤ ሰፊ አዳራሽ ነው፡፡ በዚህ አዳራሽ ውስጥ በጣም ብዙ ሰዎች አብረውኝ ታስረው ነበር፡፡ የእስራችን ምክንያት ብለው የነገሩን ባህር ዳር ነሐሴ 01/2008 ዓ.ም በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ሰልፉን አደራጅታችኋል የሚል ነው፡፡ በእስራችን ጊዜ ቤተሰቦቻችን አንድም ቀን አላገኙንም፡፡ በኋላ ብዙዎችን ወደ ብርሸለቆ ሲወስዷቸው እኔን ድጋሜ ሰልፍ ላይ ካገኘንህ እንገድልሃለን ብለው ዝተውብኝ የሆነ ወረቀት ላይ አስፈርመው ለቀውኛል፡፡ ማታ ላይ ነው በመኪና ከሌሎች ሦስት ልጆች ጋር ጥለውኝ የሄዱት›› ሲል ያስታውሳል አበበ፡፡
አበበ አስረስ ከድብቅ እስር ቤቱ መፈታቱን ተከትሎ ዘመድ ለመጠየቅ በሚል ከአካባቢው ዞር ለማለት አስቦ የቤተሰቦቹን ምክር ተቀብሎ ወደ አዲስ አበባ ዘመድ ጋር ሳምንታትን አሳልፏል፡፡ ‹‹በጣም ከባድ ጊዜ ነበር እስር ላይ ሆኜ ያሳለፍኩት›› የሚለው አበበ፣ ከሳምንታት የአዲስ አበባ ቆይታ በኋላ የገና በዓልን ከቤተሰቦቹ ጋር ለማሳለፍ ወደ ባህር ዳር በተመለሰበት ወቅት፣ ‹‹የት ጠፍተህ ከርመህ እንደመጣህ እናውቃለን!›› በሚል በድጋሜ ለእስር እንደተዳረገ ታውቋል፡፡
በድብቅ እስር ቤቶችም ሆነ በፖሊስ ጣቢያዎች የሚታሰሩ ሰዎች የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም ለማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን፣ በተለይ ድብደባ በብዙዎቹ ላይ በምርመራ ወቅት የሚፈጸም የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ በባህር ዳር ከተማ 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በምርመራ ወቅት ጥፍርን እስከመንቀል የሚደርስ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ድርጊት ይፈጸምባቸዋል፡፡
ብዙዎች በፖሊስ ጣቢያ ለሳምንታት እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ ወደ ብርሸለቆ የወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም ለ‹ተሃድሶ ስልጠኛ› ተግዘዋል፡፡ በማሰልጠኛ ተቋሙ በሚኖራቸው ቆይታም ቢሆን ተመሳሳይ፣ አንዳንዴም የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምባቸዋል፡፡ (በተሃድሶ ማሰልጠኛ ስፍራዎች ስለሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት በቅርቡ ለማሳያነት ይፋ ያደረገውን ሪፖርት መመልከት ይቻላል፡፡)
በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት በዋናነት ቀድሞውንም በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ በሚታገሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ ያነጣጠረ የእስር እርምጃ ሲወስድ ታይቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ‹የጸረ-ሽብር ግብረ-ኃይል› በሽብር ጠርጥሬያቸዋለሁ በሚል 2008 ዓ.ም ሐምሌ ወር መግቢያ ላይ በጎንደር በነበሩ የወልቃይት አማራ ማንነት ጠያቂ የህዝብ ተወካይ (ኮሚቴ) አባላትን ለማሰር በተደረገ እንቅስቃሴ በሁዋላ በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች ህዝባዊ ተቃውሞዎች በተደጋጋሚ መከሰታቸው ይታወሳል፡፡ የህዝባዊ ተቃውሞዎቹም መነሻ ከመስፋፋታቸው በፊት ጎንደር ላይ ብዙ ነዋሪዎች የተሳተፉበት ትልቅ እና ሰላማዊ ሰልፍም ተካሄዷል፡፡
ከጎንደር በማስከተል በሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም የተከናወነው የባህር ዳር ሰልፍ ግን በተለየ መልኩ በአሳዝኝ ሁኔታ የተጠናቀቀ ነበር፡፡ ሰልፉ ሲጀምር ሰላማዊ የነበር ቢሆንም ዘግይቶ የመንግስት ታጣቂዎች በወሰዱት እርምጃ በአንድ ቀን ብቻ ከ50 በላይ የሚገመቱ ንጹሃን መገደላቸው የሚታወስ ነው፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት አማራ ክልል ከሚገኙት በአጠቃላይ 11 ዞኖች በስድስቱ ዞኖች የጎላ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተደርጎባቸዋል፡፡ እነዚህም ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ባህር ዳር ልዩ ዞን፣ አዊ ዞን፣ ምዕራብ ጎጃም እና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች ናቸው፡፡ በስድስቱ ዞኖች የሚገኙ አብዛኞቹ የዞንና የወረዳ ከተሞች (አንዳንድ ቦታዎች ላይ ገጠር ቀበሌዎችንም ጨምሮ) መንግስትን የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎችንና የቤት ውስጥ አድማዎችን አስተናግደዋል፡፡ የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና ከተማና የቱሪስት መናሃሪያዋ ጎንደር ላይ የተጀመረው እንቅስቃሴ፣ ደባርቅ፣ ደብረታቦር፣ መተማ፣ አምባ ጊዮርጊስ፣ ወረታ፣ ስማዳ፣ ጋይንት፣ ባህር ዳር፣ ፍኖተ ሰላም፣ ቡሬ፣ እንጅባራ፣ ዳንግላ፣ ቻግኒ፣ ቲሊሊ፣ ብርሸለቆ፣ ቋሪት፣ ደምበጫ፣ አማኑኤል፣ ደብረ ማርቆስና ሌሎች በርካታ ከተሞችን አዳርሷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት አድማሱን እያሰፋ የሄደውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለመግታት የኃይል እርምጃ መውሰዱን በተግባር ከማሳየቱም በላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የመንግስት ጦር ተቃውሞውን ለመግታት ‹ማንኛውንም እርምጃ እንዲወስድ› ማዘዛቸው የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ ብርሸለቆ የመሰሉ የጦር ማሰልጠኛዎች ውስጥ ሳይቀር በተለያዩ ቦታዎች ታስረዋል፤ በርካቶች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት ባለፉት ወራት በተደረጉት የአማራ ህዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ወቅት ለጊዜው ያሰባሰበው መረጃም ብዙ ዜጎች በመንግስት ኃይሎች እንደተገደሉ ያሳያል፡፡ ከዚህ በታች ያለው ዝርዝር ለጊዜው ተለይተው የታወቁ የሟቾችን ስምና አድራሻ አካትቶ ለማሳያነት የቀረበ ነው፡፡
የተገደሉ ሰዎች ስም አድራሻ
1. ይሻል ከበደ ……………………………ጎንደር
2. ሲሳይ ታከለ ……………………………ጎንደር
3. አበበ ገረመው…………………………ባህር ዳር
4. ተፈሪ ባዬ ………………………………ባህር ዳር
5. እድሜዓለም ዘውዱ ……………………ባህር ዳር
6. አደራጀው ደሳለኝ …………………… ባህር ዳር (ዩኒቨርሲቲ)
7. ይበልጣል…………………………………ደብረ ታቦር
8. ግዛቸው ከተማ …………………………ጎንደር
9. አዳነ አየነው ………………………………ጎንደር
10. ማንደፍሮ አስረስ………………………ባህር ዳር
11. ቁምላቸው ቃሉ …………………………ባህር ዳር
12. አወቀ ጥበቡ ……………………………ፍኖተ ሰላም
13. ሲሳይ ከበደ ……………………………ጎንደር
14. ሰጠኝ …………………………………ጎንደር (የወልቃይት ተወላጅ)
15. እቴነሽ ሽፈራው ……………………ም/ጎጃም፣ ጂጋ
16. እንዳለው መኮነን …………………ጎንድር፣ ጋይንት
17. እሸቴ ……………………………… ባህር ዳር (ቀበሌ 16)
18. ሰለሞን አስቻለ ………………………ባህር ዳር
19. ሙሉቀን ተፈራ ………………………ባህር ዳር
20. አደራጀው ኃይሉ ………………………ባህር ዳር
21. አስማማው በየነ ……………………… ባህር ዳር
22. ታዘበው ጫኔ …………………………ባህር ዳር
23. አስራት ካሳሁን …………………………ባህር ዳር
24. የሺዋስ ወርቁ ……………………………ባህር ዳር
25. ብርሃን አቡሃይ ………………………… ባህር ዳር
26. ሽመልስ ታየ ………………………………ባህር ዳር
27. አዛናው ማሙ …………………………… ባህር ዳር
28. ሲሳይ አማረ ………………………………ባህር ዳር
29. ሞላልኝ አታላይ ………………………… ባህር ዳር
30. መሳፍንት ………………………………………ጎንደር፣ እስቴ
31. እንግዳው ዘሩ ………………………………… ባህር ዳር
32. ዝናው ተሰማ ………………………………… ባህር ዳር
33. ሞገስ ሞላ ………………………………………ባህር ዳር
34. ሞላልኝ ታደሰ …………………………………ባህር ዳር
35. ይታያል ካሴ ………………………………………ባህር ዳር
36. እሸቴ ብርቁ …………………………………… ባህር ዳር
37. ሞገስ………………………………………………ባህር ዳር
38. ገረመው አበባው ………………………………ባህር ዳር
39. ማህሌት…….…………………………………… ባህር ዳር
40. ተስፋየ ብርሃኑ …………………………………ባህር ዳር
41. ፈንታሁን………………………………………… ባህር ዳር
42. ሰጠኝ ካሴ ……………………………………… ባህር ዳር
43. ባበይ ግርማ ………………………………………ባህር ዳር
44. አለበል ዓይናለም ……………………………… ደብረ ማርቆስ
45. አብዮት ዘሪሁን …………………………………ባህር ዳር
46. አበጀ ተዘራ ………………………………………ወረታ
47. ደሞዜ ዘለቀ ……………………………………ወረታ
48. አለበል ሀይማኖት ………………………………ባህር ዳር
49. እስቲበል አስረስ …………………………………አዴት
50. ዓይናዲስ ለዓለም ……………………………… ደብረወርቅ
51. ሽመልስ ወንድሙ ……………………………… ቡሬ
52. ታደሰ ዘመኑ ………………………………………አዴት
53. ሀብታሙ ታምራት ……………………………ባህር ዳር
54. ይበልጣል እውነቱ …………………………ባህር ዳር፣ ጭስ አባይ
55. ይህነው ሽመልስ ………………………………ደብረታቦር
56. በለጠ ካሴ ………………………………………ደብረታቦር
57. አዳነ እንየው ……………………………………ጎንደር፣ ቀበሌ 16
58. አለማየሁ ይበልጣል ……………………………ዳንግላ
59. ያየህ በላቸው …………………………………… ዳንግላ
60. በረከት አለማየሁ …………………………………ዳንግላ
61. ተመስገን ……………………………………………ዳንግላ
62. ቅዱስ ሀብታሙ ………………………………… ባህር ዳር
63. ፍስሃ ጥላሁን ………………………………………ባህር ዳር
64. ሰለሞን ጥበቡ …………………………………… ቻግኒ
65. እስቲበል አስረስ …………………………………አዴት
66. ዘሪሁን ገደብዬ …………………………………ጎንደር
67. ሲሳይ ባብል ………………………………………ጎንደር
68. ባየሁ ጎንደር ………………………………………ጎንደር
69. በለጡ መሃመድ …………………………………አዘዞ፣ ጎንደር
70. እንጀራ ባዬ ………………………………………አዘዞ፣ ጎንደር
71. ወንድም ……………………………………………ጎንደር
72. ግርማቸው ከተማ ………………………… ላይ አርማጭሆ
73. ሊሻን ከበደ ………………………………………አይባ
74. መሌ አይምባ …………………………………… አይባ
75. አዛነው ደሴ ………………………………………አርማጭሆ
76. አራገው መለስ ……………………………………አርማጭሆ
77. ሰጠኝ አድማሱ ……………………………………ደልጊ
78. ታረቀኝ ተሾመ ……………………………………ደልጊ
79. ሄኖክ አታሎ ………………………………………ደልጊ
80. ደሴ ደረሰ …………………………………………ሻውራ
81. ግርማቸው ሞገስ …………………………………ሻውራ
82. ወርቁ ጠቁሳ ………………………………………ሻውራ
83. ማማዬ አንጋው …………………………………ዳንሻ
84. ፈንታ አህመድ ……………………………………ዳንሻ
85. ክንፌ ቸኮል ………………………………………በአከር
86. ሲሳይ ታከለ ……………………………………… አርማጭሆ
87. ማዕረግ ብርሃን …………………………………ደብረታቦር
88. መምህር ተስፋየ ብርሃን ……………… ደብረታቦር ቀበሌ 01
89. ይበልጣል ደሴ ………………………… ደብረታቦር ቀበሌ 01
90. አራጋው መለሰ …………………………… አርማጭሆ
91. አዳነ አያሌው ………………………… አርማጭሆ
92. አያናው ደሴ ………………………… አርማጭሆ
93. ትርፌ አጣናው ……………………… አርማጭሆ
94. መምህር ብርሃኑ አየለ …………… ሰሜን ሸዋ፣ ማጀቴ
95. አብራራው አለማየሁ ………………ደቡብ ጎንደር፣ ስማዳ
96. ተመስገን ሲሳይ …………………… ደቡብ ጎንደር፣ ስማዳ
97. ጋሻው ሲራጅ ……………………… ደቡብ ጎንደር፣ ስማዳ
98. ፈንታ ሞገስ ……………………… ደቡብ ጎንደር፣ ስማዳ
99. ታደለ ያየህ ……………………………ምዕራብ ጎጃም፣ ቡሬ
(*ማስታወሻ፡- መንግስት ህዝባዊ ተቃውሞዎች በበረቱባቸው አካባቢዎች የኢንተርኔትና የስልክ ግንኙነቶችን በሙሉና በከፊል መዝጋቱ በእነዚህ አካባቢዎች ስለተከሰቱ ጉዳዮች መረጃ የማግኘት ስራውን አዳጋች በማድረጉ ይህ ዝርዝር ሁሉንም የመብት ጥሰት የደረሰባቸው ዜጎችን ያሳያል ተብሎ አይጠበቅም፡፡)
*ሌላው ከአማራ ህዝባዊ ተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ለእስር ተዳርገው የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው
1. ንግስት ይርጋ………የመብት ተሟጋች፣ አድራሻ ሳንጃ ሰሜን ጎንደር…. ቃሊቲ እስር ቤት ታስራ ትገኛለች
2. አለምነው ዋሴ የመኢአድ አባል አድራሻ ጎንደር ቂሊንጦ በእስር ላይ ያለ
3. ቴዎድሮስ ተላይ……….አድራሻ ጎንደር
4. አወቀ አባተ……………….የመኢአድ አባል
5. በላይነህ አለምነህ…የሰማያዊ ፓርቲ አባል፣ አድራሻ ባህር ዳር
6. ያሬድ ግርማ…………………. የመኢአድ አባል
7. አታላይ ዛፌ…የወልቃይት አማራ ማንነት መብት ኮሚቴ አባል
*ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት
7. ማሩ ዳኛው
8. ቢሆን
9. መልካሙ ታደለ
10. ሲሳይ ታፈረ
11. ወርቁ ጥላሁን
12. ድንቁ
13. ስማቸው ማዘንጊያ
14. እያዩ መጣ
15. ድርሳን ብርሃኔ
16. አንዳርጌ አባይ
17. ዮናስ ሰለሞን
18. መሃመድ ኑርየ
19. መምህር መሃመድ አሊ
20. መንግስቴ ብርሃኔ
21. ጌታነህ ደምሴ
22. ታደለ እንዳልፈራ
23. መምህር ለወየሁ ጌቱ
24. እሸቴ ደረሰ
25. ጌጤ ላሽተው
26. ሰይዒድ እንድሪስ
27. አህመድ በዛብህ
28. ጀማል ኡመር
29. አብደላ መሃመድ
30. አዲሱ ጌታነህ
31. ዘሪሁን እሸቱ
32. ጀማል ይመር
33. አበበ ጥላሁን
34. ተሻገር ወልደሚካኤል
35. እያሱ ሁሴን
36. በላቸው አወቀ
37. ዘውዱ ነጋ
38. ወልደመስቀል ማማየ
*የህዝቡን የመብት ጥያቄ (ህዝባዊ ተቃውሞ) ደግፋችኋል በሚል ከታሰሩት መካከል፡-
39. ገድፍ ጌታነህ……ሰሜን ጎንደር በለሳ ወረዳ
40. ሊቀሊቃውንት እዝራ (ቤተ-ክርስቲያንን ሽፋን አድርገው የህዝቡን ተቃውሞ ይደግፋሉ በሚል የታሰሩ)
41. ቀለመወርቅ ዓለሙ (በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የጎንደር ሀገረ ስብከት ጳጳስ ኃላፊ)
42. ሂሪያኮስ አበበ…..ጎንደር ከተማ
43. ዶክተር ጋሹ ክንዱ
(ዶክተር ጋሹ ክንዱ የቡሬ ዳሞት ሆስፒታል ሜዲካል ዳሬክተር ናቸው፡፡ ታህሳስ 27 ቀን 2009 ዓ.ም ለገና በዓል ወደ ቤተሰቦቻቸው ባመሩበት ጊዜ ባህር ዳር ከተማ ለእስር ተዳርገው ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እንዲዛወሩ ተደርገው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
ምንጭ፦ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ፕሮጀክት (ኢሰመፕ) የተዘጋጀ