ፍርድ ቤት በባለስልጣናቱ ምስክርነት ጉዳይ ብይን መስጠት አልቻለም
ጌታቸው ሺፈራው
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ምስክርነት ጉዳይ ላይ ዛሬ ብይን እሰጣለሁ ባለው መሰረት ብይን መስጠት አልቻለም።
ታህሳስ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጊዜ ጥበት ምክንያት ፍርድ ቤት ቀርበው መመስከር እንደማይችሉ በጠቅላይ ሚንስትሩ ፅህፈት ቤት በኩል ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ ተገልፆአል። በዚሁ ቀን አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተከሳሾች መከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱት የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት መቅረብ ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ በቀጠሮው መጨረሻ፣ ዛሬ ታህሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ብይን እሰጣለሁ ብሎ የነበር ቢሆንም ብይን ሳይሰጥ ቀርቷል። ታህሳስ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተከሳሾች አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ታስረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ለችሎት ያመለከቱ ሲሆን ለኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ትዕዛዝ ስላልደረሳቸው በቀሪዎቹ ሁለት ቀናት ይቀርባሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
ትናንት ታህሳስ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተከሳሾች ጠበቃ አብዱልጀባር ሁሴን በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱትን የኦሮምያ ባለስልጣናት በአካል አግኝተው ባነጋገሯቸው መሰረት ባለስልጣናቱ ለዛሬ ታህሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ሊመሰክሩ እንደሚችሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተው ነበር። ይሁንና ዛሬ ታህሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት በስብሰባ ምክንያት ቀርበው መመስከር እንዳልቻሉና ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲመሰክሩ ከኦህዴድ ማህከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት በተፃፈ ደብዳቤ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
ሆኖም ፍርድ ቤቱ በቀጠሮው የመጨረሻ ታህሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ታስረው እንዲቀርቡ የተነሳው አቤቱታ ላይ ብይን ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ በዚህ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል። ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በተጨማሪ በስብሰባ ምክንያት ለዛሬ ቀርበው መመስከር ባለመቻላቸው ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው በደብዳቤ የጠየቁት የእነ ለማ መገርሳ አቀራረብ ጉዳይ ላይም ታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ብይን እሰጣለሁ ብሏል።
የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን ባለስልጣናቱ ተለዋጭ ቀጠሮ በጠየቁበት ሁኔታ በእነሱ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ መያዙ ግልፅ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በባለስልጣናቱ የመከላከያ ምስክርነት አቀራረብ ላይ ብይን ለመስጠት ብቻ የተያዘ ቀጠሮ ሲሆን ለተከሳሾቹ ከየካቲት 5 እስከ የካቲት 9 ተከታታይ ቀጠሮ ተይዟል።
በውዝግብ የተጠናቀቀው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የችሎት ውሎ
በጌታቸው ሺፈራው
~ተከሳሾቹ ጆሯቸውን በእጃቸው ደፍነው፣ ጀርባቸውን ለዳኞ ሰጥተው ችሎቱን “አንሰማም! አናይም!” ብለዋል
~ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ነኝ ብሎ የቀረበውን ግለሰብ ዐቃቤ ሕጉ ክዶታል።ዐቃቤ ሕጉ በሀሰት እንድመሰክር ተገድጃለሁ ያለውን ግለሰብ የእኔ ሳይሆን የጠበቃ ምስክር ነው ብሎታል።
~ጨለማ ቤት የታሰሩት መነኩሴ በቀጠሯቸው አልቀረቡም
~ እነ ተሻገር ወ/ሚካኤል ለሁለተኛ ጊዜ በዳኛው ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል። ብይኑ በማረሚያ ቤት ይደርሳቸዋል ተብሏል። ታዳሚ ወደ ችሎት እንዳይገባ ተከልክሏል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ውሎ በውዝግብ ተጠናቅቋል። በጠዋቱ የፍርድ ቤቱ የስራ ሰዓት ተከሳሾች ችሎቱን አንሰማም፣ አናይም ብለው ተቃውሞ አሰምተዋል። ከሰዓት በነበረው የችሎቱ ሰዓት የቀረቡት እነ ተሻገር ወልደሚካኤል ባሰሙት ተቃውሞ ችሎቱ ብይን ማንበብ ባለመቻሉ ብይኑን ባሉበት ለማድረስ ተገዷል። ፍርድ ቤቱ ለእነ ተሻገር በችሎት ቀጠሮ እንዳልሰጠ ታውቋል።
ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት እነ ጎይቶም ርስቃይ ጆሯቸውን በእጃቸው በመድፈን እና ፊታቸውን በማዞር ችሎቱን አንሰማም አናይም ብለው ተቃውሟቸውን ገልፀዋል።
እነ ጎይቶም ዛሬ ታህሳስ 11/2010 ዓም ቀጠሮ የተያዘላቸው በክሱ ላይ ያቀረቡትን መቃወሚያ ብይን ለመስማት ሲሆን ተከሳሾቹ ብይኑ ከመነበቡ በፊት ዳኛ ዘርዓይ ወ/ሰንበት ከችሎት እንዲነሱ አቤቱታ አቅርበው፣ ብይኑ ዳኛው ከተነሱ በኋላ እንዲሰራ ጠይቀዋል።
ይሁንና ፍርድ ቤቱ ብይኑን ማንበብ በመቀጠሉ ተከሳሾቹ ጆሯቸውን በእጃቸው በመድፈን አንሰማም ብለዋል። በተጨማሪም ፊታቸውን በማዞር ጀርባቸውን ለችሎቱ ሰጥተው ብይኑ ተነቧል። ብይኑን ያነበቡት ተከሳሾቹ ከችሎት እንዲነሱ አቤቱታ እናቀርብባቸዋለን ያሏቸው ዳኛ ዘርዓይ ወ/ሰንበት ናቸው።
~ከሰዓት በነበረው የፍርድ ቤቱ የስራ ሰዓት ፍርድ ቤት የቀረቡት በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል የክስ መዝገብ ስር የተከሰሱ 35 እስረኞች ለ2ኛ ጊዜ በዳኛ ዘርዓይ ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል። ተከሳሾቹ ባለፈው ቀጠሮ ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ሊዳኙን አይገባም የሚል ተቃውሞ በማሰማታቸው ችሎት ደፍራችኋል በሚል እንደተፈረደባቸው በመግለፅ በክሱ ላይ ያቀረቡት መቃወሚያ ብይን ከመነበቡ በፊት ዳኛው ሊነሱ እንደሚገባ መግለፃቸው ታውቋል።
ይሁንና ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹ የዳኛ ይነሳልን አቤቱታ በፅሁፍ ያልደረሰው መሆኑን ገልፆ ብይኑን ለማንበብ በመሞከሩ ተቃውሞ ገጥሞታል። የተከሳሾቹ መዝገብ የያዙትና ብይኑንም ለማንበብ የሞከሩት ከችሎት እንዲነሱ ተቃውሞ የቀረበባቸው ዳኛ ዘርዓይ መሆናቸው ተገልፆአል። ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን ስም ሲጠራ ተከሳሾቹ “አቤት” ባለማለታቸው እንዳልቀረቡ (እንደሌሉ) ተደርጎ ተመዝግቧል።
1ኛ ተከሳሽ ተሻገር ወ/ሚካኤል ዳኛ ዘርዓይ ሊዳኘን አይገባም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አቶ ተሻገር ” እኔ ወልቃይቴ ነኝ። አማራ ነኝ። እኛን በፌስቡክ ሲዘልፍ የነበረ፣ ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ ነው እያለ ሊዳኘን አይገባም። እኛ ትናንትም፣ ዛሬም ነገም አማራ ነን። ዳኛ ዘርዓይ ሊዳኘን አይገባም። ዳኛ ዘርዓይ ሊዳኝ ከፈለገ ከፖለቲካው ገለልተኛ ሆኖ ሌላ ቦታ ሄዶ ይዳኝ” የሚል ይዘት ያለው አስተያየት ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል ቂሊንጦ እስር ቤት ያለው ጨለማ ቤት ውስጥ የሚገኙት አባ ገብረስላሴ ወልደሐይማኖት በዛሬው ቀጠሮ አልቀረቡም። ወደ ችሎቱ መግባት የተከለከለ ሲሆን ፖሊሶችን እንድንገባ ስንጠይቅ ዳኞቹ ታዳሚ እንዳያስገቡ ትዕዛዝ እንደሰጧቸው ገልፀውልናል። ቀድመው ወደ ችሎት ገብተው የነበሩ የተከሳሾች ቤተሰቦች ከችሎት እንዲወጡ ተደርጓል። እነ ተሻገር ሲናገሩ ችሎቱ በር አካባቢ ሆነን ስናዳምጥ ፖሊሶች ከችሎት እንድንርቅ አድርገዋል። ከችሎት እንድንርቅ ያደረጉት በዳኞች ትዕዛዝ እንደሆነም ገልፀውልናል።
~ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዐቃቤ ሕግ ራሱ የቆጠረውን ምስክር የእኔ አይደለም ብሏል። በእነ ክንዱ መሃመድ የክስ መዝገብ ላይ በዐቃቤ ሕግ 1ኛ ምስክር ሆኖ የተቆጠረውን አቶ ሸዋንግዛው የሽጥላ ዐቃቤ ሕግ “የእኔ ምስክር አይደለም” ሲል ክዷል። ምስክሩ በጠዋቱ የችሎት ሰዓት በችሎት ቀርቦ በተከሳሾች ላይ በሀሰት እንዲመሰክር መገደዱን ገልፆአል። በወቅቱ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ሓፍታሙ ቸኮለ ምስክሩን እንደማያውቀው ገልፆ የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ 1ኛ የዐቃቤ ምስክር መሆኑን በማረጋገጡ ዐቃቤ ሕጉም እንደገና 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር መሆኑን አምኖ ነበር።
አቶ ሸዋንግዛው የሽጥላ ከሰዓት ምስክርነቱን እንዲሰጥ ቀጠሮ በተያዘው መሰረት ከሰዓት ሲቀርብ፣ ዐቃቤ ሕጉ “የተከሳሾች ጠበቃ ምስክር እንጅ የእኔ ምስክር አይደለም” ብሎ ክዷል።
የተከሳሾች ጠበቃ አዲሱ ጌታነህ በበኩሉ ምስክሩ ዐቃቤ ሕግ በማስረጃ ዝርዝር ላይ ያስቀመጠው፣ ጠዋትም ማንነቱን ለፍርድ ቤቱ የገለፀ፣ ዐቃቤ ሕግ በጠራው መሰረት በቀጠሮው የቀረበ እና በመታወቂያውም መለየት የሚቻል መሆኑን በመግለፅ የዐቃቤ ሕግ ምስክር መሆኑን አስረድቷል።
ዐቃቤ ሕግ ዛሬ የቀረበው ሳይሆን ሌላና በምስክርነት ቆጥሬዋለሁ የሚለው ሸዋንግዛው ቀርቦ እንዲመሰክር ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ ብሏል። ፍርድ ቤቱ 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር መሆኑን ገልፆ በቀጠሮ መሰረት የቀረበውን አቶ ሸዋንግዛው በጠዋቱ ችሎት ከተናገረው፣ ከዐቃቤ ሕግና ከተከሳሾች ጠበቃ የራሱን ግምት እንደሚወስድ በመግለፅ 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር እንዲቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።
በቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ ክስ በቀረበባቸው እስረኞች ላይ የተፈፀመ በደል
ጌታቸው ሺፈራው
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ያሬድ ሁሴን ኢብራሂም የክስ መዝገብ ክስ የቀረበባቸው 25 ተከሳሾች በአዲስ አበባ ቀጠሮ ማረፊያ ቤት( ቂሊንጦ) ቃጠሎ ሰበብ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስደው የደረሰባቸው የሰብአዊ መብት ጥሰትን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽ አጣርቶ እንዲያቀርብ በማዘዙ ኮምሽኑ ምርመራውን ለፍርድ ቤት ልኳል።
ተከሳሾቹ ያቀረቡት አቤቱታ:_
የቀጠሮ ማረፊያ ቤት ላይ በተፈጠረው ቃጠሎ ምክንያት በቃጠሎው እጃችሁ አለበት ተብለን ነሃሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለይተን ወደ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስደን ኢሰብአዊ ድርጊት ተፈፅሞብናል። በሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ያልፈፀምነውን ድርጊት እመኑ እየተባልን ለሰው ልጅ በማይመጥን፣ ኢሰብአዊ የሆነ ድርጊት ተፈፅሞብናል። ለአንድ ወር ያህል በካቴና ከአልጋ ጋር ታስረናል። ተገልብጠን ተገርፈናል። የውስጥ እግራችን ተገርፈናል። አንጠልጥለው በማሰር ውሃ እየደፉብን፣ በኤሌክትሪክ ሾክ እየተደረግን ተመርምረናል። በእምነትና ማንነታችን ጥቃት ደርሶብናል። በደረሰብን ድብደባና ስቃይ ብዛት ያልፈፀምነውን ድርጊት ፈፅመናል ብለን ለማመን ተገደናል።
ወደ ቀጠሮ ማረፊያ ቤት (ቂሊንጦ) ከተመለስን በኋላ ቢሆን በደረሰብን ድብደባ ብዛት ላጋጠመን ጉዳት ህክምና አላገኘንም። በቃጠሎው ወቅት አልባሳትን ጨምሮ ንብረቶቻችን በማረሚያ ቤቱ የተወረስን ሲሆን እንዲመለሱልን ስንጠይቅ ተቃጥለዋል የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል።
በምርመራ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው ተከሳሾች:_
1) ፀጋዬ ዘውዱ:_ቀኝ እግር ከጉልበቱ በታች ጠባሳ፣ ግራ እግር ላይ የግርፋት የሚመስል ጠባሰ፣ ጀርባ ላይ ጠባሳ ፣ የአውራ ጣት ጥፍር መነቀል፣ የካቴና የታሰረበት ምልክት
2) ያሬድ ሁሴን:_ ግራ እግር ላይ ጠባሳ፣ቀኝ እጅ ላይ ጠባሳ፣ የካቴና እስር ምልክቶች፣
3) ኃይለ መስቀል ፀጋዬ:_ ሁለት እጆቹ ላይ ጠባሳ
4) ሁሴን አህመድ:_ የግራ እጅ ጠባሳ
5)ሰለሞን ጫኔ:_የቀኝ እጅ የመሃል ጣት ስብራት፣ የቀኝ እግር ደም ስር መዛባት
6)ስማቸው አርጋው:_ የግራ እጅ የመጀመርያ ጣት ስብራት፣ ሁለት እጆቹ ላይ ጠባሳ፣ ሁለት እግር ታፋዎች ላይ የግርፋት ጠባሳ ምልክቶች
7)ዋሲሁን አየለ:_ በካቴና የመታሰር ምልክቶች
8) ሀቢብ ከድር:_ሁለት እጅ ላይ የጠባሳ ምልክቶች፣ ቀኝና ግራ ክንድ ላይ የጠባሳ ምልክቶች፣
9) ግሩም አስቀናው:_ ሁለት እጆቹ ላይ በካቴና የታሰረበት ጠባሳ ምልክቶች፣ ከቀኝ ታፋ በላይ ትልቅ ጠባሳ
10) ሻሾ አድማሱ:_ ወገቡ ላይ ትልቅ ጠባሳ
11)ማናዬ መንገሻ:_ የአውራ ጣት ጥፍር መነቀል
12) ቢንያም አሰፋ:_ የቀኝና ግራ እጅ ላይ በካቴና መጥበቅ ምክንያት የጠባሳ ምልክቶች
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ከላይ የተጠቀሱት እስረኞች ወደ እስር ቤት ሲገቡ የተጠቀሱት ጉዳቶችና ምልክቶች እንዳልነበረባቸው አረጋግጧል። የኮምሽኑ ምርመራው የተካሄደው ድብደባው ከተፈፀመ 10 ወር በኋላ ቢሆንም የግርፋት ምልክቶች በግልፅ እንደሚታዩ በሪፖርቱ ላይ ተገልፆአል። በመሆኑም ተከሳሾች ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስደው በአቤቱታው ላይ የተጠቀሰው ለሰው ልጅ የማይመጥንና ኢ ሰብአዊ የሆነ ድርጊት እንደተፈፀመባቸው ተረጋግጧል።
ይሁንና አቤቱታ ያቀረቡት 25 ተከሳሾች ሆነው ኮምሽኑ የጠቀሰው የ12 ተከሳሾችን በደል ብቻ ነው። በሌሎች መዝገቦችም ተመሳሳይ አቤቱታ ቀርቦ ኮምሽኑ ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን በእስረኞች ላይ የተፈፀመውን በደል በሚገባ በሪፖርቱ አላጠቃለለም ተብሏል።
በደል የተፈፀመባቸው እስረኞች ካለመጠቀሳቸውም በተጨማሪ በሪፖርቱ የተጠቃለሉ እስረኞች የደረሰባቸው በደል በሚገባ አልተጠቀሰም ተብሏል። በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ የተከሰሱ 38 ተከሳሾች ሸዋሮቢት ተወስደው በደል በተፈፀመባቸው 175 እስረኞች ላይ ከተፈፀመው በደል መካከል ኮምሽኑ 6 በመቶውን ብቻ በሪፖርቱ ማጠቃለሉን ተከሳሾቹ በችሎት ተናግረዋል። ኮምሽኑ የተፈፀመውን በደል በሚገባ በሪፖርቱ ባለማጠቃለሉና ገለልተኛ አይደለም በሚል ሌላ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ የተፈፀመባቸውን አስከፊ በደል እንዲያጣራ እስረኞቹ አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤት እያቀረቡ ነው።
ኮምሽኑ በእስረኞች ላይ በደል ፈፀሙ የተባሉ አካላትን ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እንዲያጣራ በምክረ ሀሳብ ያስቀመጠ ሲሆን እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ኃላፊዎች ድብደባ እንደፈፀሙባቸውና እንዳስፈፀሙባቸው የኃላፊዎችን ስም ጭምር በመጥቀስ ገልፀዋል። በመሆኑም በደል የፈፀመው አካል ጉዳዩን እንዲያጣራ መታዘዙ የደረሰብን በደል ተሸፋፍኖ እንዲቀር ስለተፈለገ ነው የሚል ቅሬታ አቅርበዋል። ከተከሳሾቹ ባሻገር ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ያቀረባቸውና ያዘጋጃቸው ምስክሮች በምርመራ ወቅት በደረሰባቸው ድብደባ ምክንያት ተገደው ለምስክርነት እንደቀረቡና ተገደው ምስክር በሆኑት ላይ የተፈፀመው በደልም እንዲጣራ ተከሳሾች ለፍርድ ቤት አመልክተዋል።
ፍርድ ቤቱ ጫልቱ ታከለን በገንዘብ ቀጣ
በጌታቸው ሺፈራው
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በእስር ላይ የምትገኘው ጫልቱ ታከለን በገንዘብ ቀጥቷል። በእነ ደቻሳ ሞሲሳ የክስ መዝገብ 4 ተከሳሽ ጫልቱ ታከለ “እናንተ ኢህአዴግ ናችሁ፣ ከኢህአዴግ ፍርድ ቤት ምንም አልጠብቅም” ብላ ተናግራለች በሚል በችሎት መድፈር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባታል።
ፎቶ፡- ጫልቱ ታከለ
ህዳር 28 ቀን 2010 ዓም እነ ደቻሳ ሞሲሳ ተከላከሉ የሚል ብይን በተሰጠባቸው ወቅት 3ኛ ተከሳሽ የሆነችው ጫልቱ በሰነድ ማስረጃነት የቀረበባት የደህንነት ሪፖርት ወደ ኤርትራ ስለመሄድ የጠቀሰው ነገር ሳይኖር ብይን ላይ ወደ ኤርትራ ልትሄድ እንደነበር ተጠቅሶ ተከላከይ መባሏ እንዳሳዘናት ገልፃለች።
ጫልቱ ታከለ በወቅቱ “ከኢህአዴግ ፍርድ ቤት ምንም አንጠብቅም። ወደፊትም ፍትህ እንደማናገኝ ነው የምናስበው።” ብላ በመናገሯ በችሎት መድፈር ጥፋተኛ ተብላ በአዳር ዛሬ ህዳር 29 ቀን 2010ዓ.ም. የ500 ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባታል።
ጫልቱ ታከለ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ክስ ተፈርዶባት ፍርዷን ጨርሳ እንደወጣች ተገልጿል።
አባ ገብረ-ኢየሱስ ዘዋልድባ፤ ተደብድበውና አካላቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ ጭለማ እንደሚገኙ ተጠቆመ
በጌታቸው ሺፈራው
#የፌደራልከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ውሎ
” #አባገ/እየሱስ ዘ _ዋልድባ ተደብድበው፣ ተሰባብረው እኔ ጋር ጨለማ ቤት ነው ታስረው ያሉት” አስቻለው ደሴ
#እስረኞች ለህይወታቸው እንደሚሰጉ ገልፀዋል
#የዐቃቤሕግ ምስክር ስሙን እየቀያየረ በተለያዩ መዝገቦች እየመሰከረ ነው ተብሏል
#የአማራክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ዛሬም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣኑን አጥቷል የሚል ብይን ተሰጥቶበታል
ፎቶ:- አባ ገብረ-ኢየሱስ ዘ-ዋልድባ
~የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬም (ህዳር 28/2010) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣኑን አጥቷል የሚል ብይን ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ብይን የሰጠው በእነ አስቻለው ደሴ መዝገብ የተከሰሱ 4 ግለሰቦች ወንጀል ፈፅማችኋል የተባልነው በአማራ ክልል በመሆኑ ጉዳያችንን ሊያየው የሚገባው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው ብለው ላቅቡት የክስ መቃወሚያ ነው።
ብይኑን በአብላጫ ድምፅ የሰጠው ፍርድ ቤቱ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ እንዲሁም ሶማሊ፣ አፋር፣ ሀረሪ(?)፣ ደቡብና ቤንሻንጉል ክልሎች የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችየፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ስራ ደርበውና ወክለው እንዲሰሩ ስልጣን ስለተሰጣቸው የአማራ ክልልን ጨምሮ ሌሎች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣንን አጥተዋል ተብሏል።
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ለቀረቡለት የክስ መቃወሚያዎች ከአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሶማሊ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉልና ሀረሪ(?) ክልሎች ውጭ ያሉ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣንን አጥተዋል ብሎ በተደጋጋሚ ብይን ሰጥቷል።
~ብይኑ የተሰጠው በአብላጫ ድምፅ ሲሆን የመሃል ዳኛው ዮሃንስ ጌስያብ ለሌሎች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣን በሕግ መሰጠቱ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህን ስልጣን እንዲያጣ አያደርገውም በሚል የልዩነት ሀሳባቸውን አስመዝግበዋል። መሃል ዳኛው ለብይኑ መንስኤ በሆነው ምክንያት ልዩነት ቢያስመዘግቡም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ”ሽብር” ጉዳይን የማየት “ተፈጥሯዊ መብት” አለው በሚል በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩ ሊታይ አይገባም በማለት በብይኑ ውጤት ከሌሎች ዳኞች ላይ ተስማምተዋል።
~ በእነ አስቻለው ደሴ ክስ መዝገብ አንደኛ ተከሳሽ እና ህዳር 14/2010 ሱሪውን አውልቆ በምርመራ ወቅት ብልቱ መኮላሸቱን ያሳየው አስቻለው ደሴ አሁንም ህይወቱ አደጋ ውስጥ መሆኑን ተናግሯል። አስቻለው ደሴ ምንም አይነት ጥፋት ሳያጠፋ ጨለማ ቤት ታስሮ እንደሚገኝና አሁን የታሰረበት ሁኔታ ለህይወቱ አስጊ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል። አባ ገ/ እየሱስ ኪዳነ ማርያም ጨለማ ቤት መታሰራቸውን ገልፆአል። ” አባ ገ/እየሱስ ዘ ዋልድባ ተደብድበው፣ ተሰባብረው እኔ ጋር ጨለማ ቤት ነው ያስረው ያሉት” ሲል አባ ገ/እየሱስ ስለታሰሩበት ሁኔታ ገልፆአል።
~ ከክፍለ ሀገር የመጡ ቤተሰቦቹ ፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ በፖሊስ መያዛቸውን ገልፆ፣ ለምን እንደተያዙና የት እንደሚገኙ እንዲጣራ በጠየቀው መሰረት ቤተሰቦቹን የያዘችው ፖሊስ የአስቻለው ቤተሰቦች እጃቸውን አጣምረው ለተከሳሹ ሰላምታ ሲሰጡ በማየቷ እንደያዘቻቸውና መክራ እንደለቀቀቻቸው ገልፃለች። አስቻለው ደሴ “ካላየኋቸው አላምንም” በማለቱ ፍርድ ቤቱ “ዘመነኛውን የተቃውሞ ምልክት አሳይተው መለስኳቸው ብላለች። ከዚህ ግቢ ውስጥ እንዲህ አይነት ነገር አይደረግም” ብሏል።
~በአስቻለው የክስ መዝገብ 4ኛ ተከሳሽ ማዕከላዊ በደረሰበት ድብደባ ምክንያት አንድ ጉድን፣ ኩላሊት እና ልቡ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ገልፆአል። በዚህም ምክንያት በአንድ ጉኑ ብቻ ለመተኛት መገደዱን፣ በቂ ህክምናም እያገኘ እንዳልሆነ ገልፆ “በቅርቡ ህይወቴ ያልፋል ብየ እሰጋለሁ” ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። ማዕከላዊ የደበደቡት ቸርነት እና ተስፋዬ የተባሉ መርማሪዎችም እንዲጠየቁ አቤቱታ አቅርቧል።
~በእነ አብዱ አደም ክስ መዝገብ የተከሰሱ 7 ግለሰቦች አንድ የአቃቤ ህግ ምስክር ለመስማት በሚል 6 ጊዜ እንደተቀጠረባቸው በመግለፅ ምስክርነቱ እንዲታለፍ ጠይቀዋል። አድራሻው ሻሸመኔ ነው የተባለውን ምስክር ለመስማት በተደጋጋሚ እንደተቀጠረባቸው የገለፁት ተከሳሾቹ ምስክርነቱ ታልፎ እንዲበየንላቸው ጠይቀዋል።
~ 1ኛ ተከሳሽ :_
” ከታሰርን አንድ አመት ከአራት ወር ሆኖናል። እኔ ተማሪ ነኝ። ከትምህርት ቤት ነው የተያዝኩት። አባቴ የ70 አመት አዛውንት ናቸው። በሌላ መዝገብ ተከሰው ቂሊንጦ ታስረው ነበር። የተለያየ ዞን ታስረን ነበር። ለቤተሰብ ጥየቃ ስለማይመች በደብዳቤ ጠይቄ ከእኔ ጋር ታስረው ነበር። ነገር ግን ካቦ(የእስረኞች ኃላፊ) ይቀየር ብለው ስለጠየቁ ትናንት ማታ ወዳልታወቀ ቦታ ተወስደዋል። የት እንደሄዱ አላውቅም። ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እፈልጋለሁ።”
~እነ አበራ ለሚ ክስ መዝገብ ስር የተከሰሱ የመከላከያ ምስክር አሰምተዋል። ለ3ኛ ተከሳሽ ሆራ ከበደ የመከላከያ ምስክርነቱን የሰጠው ቡልቲ ተሰማ በእነ አበራ ለሚ መዝገብ ያሉ ተከሳሾች ላይ የመሰከረው ግለሰብ ስም እየቀየረ በተለያዩ መዝገቦች ክስ የቀረበባቸው እስረኞች ላይ እንደሚመሰክር አስረድቷል። ምስክሩ ሀምሌ 13/2009 ዓም በእነ አበራ ለሚ ክስ መዝገብ ሀብታሙ ፈይሳ፣ እንዲሁም ነሃሴ 6/2009 ደግሞ ጋድጌዳ ግርማ ብሎ በራሱ በአቶ ቡልቲ ላይ እንደመሰከረ ተገልፆአል።
~እነ መልካሙ ክንፉ ክሳቸው እንዲሻሻል በጠየቁት መሰረት ሁለት ጊዜ ተሻሻለ ተብሎ ሳይሻሻል መቅረቱን ገልፀዋል። በዛሬው እለት ለ3ኛ ጊዜ የተሻሻለ ነው የተባለ ክስ ተነቦላቸዋል። ፍርድ ቤቱ የአንደኛ ተከሳሽ መልካሙ ክንፉ ክስ መሻሻሉን ገልፆአል። ሆኖም ክሱ ከተነበበ በኋላ ተከሳሾች ይሻሻል የተባለው የ1ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች መሆኑን አስታውሰው የተነበበላቸው የመጀመርያው ክስ እንጅ የተሻሻለ ነገር እንደሌለው ገልፀዋል። ባለፈው ቀጠሮ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ክሱን አሻሽሎ በቶሎ ካላመጣ ተከሳሾቹን በነፃ አሰናብታለሁ እንዳለ አስታውሰው ቃሉን እንዲጠብቅ ገልፀዋል።
~ፍርድ ቤቱ የሟች አየለ በየነ ክስ እንዲቋረጥ በመወሰን ለአቃቤ ህጉ ትዕዛዝ ባስተላለፈበት ወቅት አቃቤ ህጉ አቶ መኩሪያ አለሙ “ተከሳሽ መሞቱን ሳላረጋግጥ ክሱን ማቋረጥ አልችልም” ብለዋል። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠቱን በማስታወስ፣ የአስከሬን ምርመራ ማስረጃም መዝገቡ ጋር መያያዙን ገልፆአል። አቃቤ ሕጉ ይህን መረጃ ካገኘ ክሱን እንደሚያቋርጥ ገልፆአል። ፍ/ ቤቱ መዝገቡን አይቶ ክሱ ተሻሽሏል አልተሻሻለም የሚለውን አይቶ ለመበየን ለታህሳስ 10/2010 ዓም ቀጠሮ ይዟል።
~ በማስተር ፕላኑ ምክንያት የተነሳውን የህዝብ ተቃውሞ አስተባብሯል፣ የኦነግ አባላትን አደራጅቶ አመፅ መርቷል የሚል የ”ሽብር” ክስ የተመሰረተበት ጃራ ሃዋዝ 5 አመት ተፈርዶበታል።