Daily Archives: December 10th, 2017

ፍርድ ቤቱ ጫልቱ ታከለን በገንዘብ ቀጣ

በጌታቸው ሺፈራው

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በእስር ላይ የምትገኘው ጫልቱ ታከለን በገንዘብ ቀጥቷል። በእነ ደቻሳ ሞሲሳ የክስ መዝገብ 4 ተከሳሽ ጫልቱ ታከለ “እናንተ ኢህአዴግ ናችሁ፣ ከኢህአዴግ ፍርድ ቤት ምንም አልጠብቅም” ብላ ተናግራለች በሚል በችሎት መድፈር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባታል።
Chaltu Takele
ፎቶ፡- ጫልቱ ታከለ

ህዳር 28 ቀን 2010 ዓም እነ ደቻሳ ሞሲሳ ተከላከሉ የሚል ብይን በተሰጠባቸው ወቅት 3ኛ ተከሳሽ የሆነችው ጫልቱ በሰነድ ማስረጃነት የቀረበባት የደህንነት ሪፖርት ወደ ኤርትራ ስለመሄድ የጠቀሰው ነገር ሳይኖር ብይን ላይ ወደ ኤርትራ ልትሄድ እንደነበር ተጠቅሶ ተከላከይ መባሏ እንዳሳዘናት ገልፃለች።
ጫልቱ ታከለ በወቅቱ “ከኢህአዴግ ፍርድ ቤት ምንም አንጠብቅም። ወደፊትም ፍትህ እንደማናገኝ ነው የምናስበው።” ብላ በመናገሯ በችሎት መድፈር ጥፋተኛ ተብላ በአዳር ዛሬ ህዳር 29 ቀን 2010ዓ.ም. የ500 ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባታል።

ጫልቱ ታከለ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ክስ ተፈርዶባት ፍርዷን ጨርሳ እንደወጣች ተገልጿል።

አባ ገብረ-ኢየሱስ ዘዋልድባ፤ ተደብድበውና አካላቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ ጭለማ እንደሚገኙ ተጠቆመ

በጌታቸው ሺፈራው

#የፌደራልከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ውሎ
” #አባገ/እየሱስ ዘ _ዋልድባ ተደብድበው፣ ተሰባብረው እኔ ጋር ጨለማ ቤት ነው ታስረው ያሉት” አስቻለው ደሴ
#እስረኞች ለህይወታቸው እንደሚሰጉ ገልፀዋል
#የዐቃቤሕግ ምስክር ስሙን እየቀያየረ በተለያዩ መዝገቦች እየመሰከረ ነው ተብሏል
#የአማራክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ዛሬም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣኑን አጥቷል የሚል ብይን ተሰጥቶበታል

Aba gebre-eyesus Z-waldeba
ፎቶ:- አባ ገብረ-ኢየሱስ ዘ-ዋልድባ

~የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬም (ህዳር 28/2010) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣኑን አጥቷል የሚል ብይን ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ብይን የሰጠው በእነ አስቻለው ደሴ መዝገብ የተከሰሱ 4 ግለሰቦች ወንጀል ፈፅማችኋል የተባልነው በአማራ ክልል በመሆኑ ጉዳያችንን ሊያየው የሚገባው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው ብለው ላቅቡት የክስ መቃወሚያ ነው።

ብይኑን በአብላጫ ድምፅ የሰጠው ፍርድ ቤቱ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ እንዲሁም ሶማሊ፣ አፋር፣ ሀረሪ(?)፣ ደቡብና ቤንሻንጉል ክልሎች የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችየፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ስራ ደርበውና ወክለው እንዲሰሩ ስልጣን ስለተሰጣቸው የአማራ ክልልን ጨምሮ ሌሎች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣንን አጥተዋል ተብሏል።

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ለቀረቡለት የክስ መቃወሚያዎች ከአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሶማሊ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉልና ሀረሪ(?) ክልሎች ውጭ ያሉ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣንን አጥተዋል ብሎ በተደጋጋሚ ብይን ሰጥቷል።

~ብይኑ የተሰጠው በአብላጫ ድምፅ ሲሆን የመሃል ዳኛው ዮሃንስ ጌስያብ ለሌሎች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣን በሕግ መሰጠቱ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህን ስልጣን እንዲያጣ አያደርገውም በሚል የልዩነት ሀሳባቸውን አስመዝግበዋል። መሃል ዳኛው ለብይኑ መንስኤ በሆነው ምክንያት ልዩነት ቢያስመዘግቡም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ”ሽብር” ጉዳይን የማየት “ተፈጥሯዊ መብት” አለው በሚል በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩ ሊታይ አይገባም በማለት በብይኑ ውጤት ከሌሎች ዳኞች ላይ ተስማምተዋል።

~ በእነ አስቻለው ደሴ ክስ መዝገብ አንደኛ ተከሳሽ እና ህዳር 14/2010 ሱሪውን አውልቆ በምርመራ ወቅት ብልቱ መኮላሸቱን ያሳየው አስቻለው ደሴ አሁንም ህይወቱ አደጋ ውስጥ መሆኑን ተናግሯል። አስቻለው ደሴ ምንም አይነት ጥፋት ሳያጠፋ ጨለማ ቤት ታስሮ እንደሚገኝና አሁን የታሰረበት ሁኔታ ለህይወቱ አስጊ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል። አባ ገ/ እየሱስ ኪዳነ ማርያም ጨለማ ቤት መታሰራቸውን ገልፆአል። ” አባ ገ/እየሱስ ዘ ዋልድባ ተደብድበው፣ ተሰባብረው እኔ ጋር ጨለማ ቤት ነው ያስረው ያሉት” ሲል አባ ገ/እየሱስ ስለታሰሩበት ሁኔታ ገልፆአል።

~ ከክፍለ ሀገር የመጡ ቤተሰቦቹ ፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ በፖሊስ መያዛቸውን ገልፆ፣ ለምን እንደተያዙና የት እንደሚገኙ እንዲጣራ በጠየቀው መሰረት ቤተሰቦቹን የያዘችው ፖሊስ የአስቻለው ቤተሰቦች እጃቸውን አጣምረው ለተከሳሹ ሰላምታ ሲሰጡ በማየቷ እንደያዘቻቸውና መክራ እንደለቀቀቻቸው ገልፃለች። አስቻለው ደሴ “ካላየኋቸው አላምንም” በማለቱ ፍርድ ቤቱ “ዘመነኛውን የተቃውሞ ምልክት አሳይተው መለስኳቸው ብላለች። ከዚህ ግቢ ውስጥ እንዲህ አይነት ነገር አይደረግም” ብሏል።

~በአስቻለው የክስ መዝገብ 4ኛ ተከሳሽ ማዕከላዊ በደረሰበት ድብደባ ምክንያት አንድ ጉድን፣ ኩላሊት እና ልቡ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ገልፆአል። በዚህም ምክንያት በአንድ ጉኑ ብቻ ለመተኛት መገደዱን፣ በቂ ህክምናም እያገኘ እንዳልሆነ ገልፆ “በቅርቡ ህይወቴ ያልፋል ብየ እሰጋለሁ” ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። ማዕከላዊ የደበደቡት ቸርነት እና ተስፋዬ የተባሉ መርማሪዎችም እንዲጠየቁ አቤቱታ አቅርቧል።

~በእነ አብዱ አደም ክስ መዝገብ የተከሰሱ 7 ግለሰቦች አንድ የአቃቤ ህግ ምስክር ለመስማት በሚል 6 ጊዜ እንደተቀጠረባቸው በመግለፅ ምስክርነቱ እንዲታለፍ ጠይቀዋል። አድራሻው ሻሸመኔ ነው የተባለውን ምስክር ለመስማት በተደጋጋሚ እንደተቀጠረባቸው የገለፁት ተከሳሾቹ ምስክርነቱ ታልፎ እንዲበየንላቸው ጠይቀዋል።
~ 1ኛ ተከሳሽ :_
” ከታሰርን አንድ አመት ከአራት ወር ሆኖናል። እኔ ተማሪ ነኝ። ከትምህርት ቤት ነው የተያዝኩት። አባቴ የ70 አመት አዛውንት ናቸው። በሌላ መዝገብ ተከሰው ቂሊንጦ ታስረው ነበር። የተለያየ ዞን ታስረን ነበር። ለቤተሰብ ጥየቃ ስለማይመች በደብዳቤ ጠይቄ ከእኔ ጋር ታስረው ነበር። ነገር ግን ካቦ(የእስረኞች ኃላፊ) ይቀየር ብለው ስለጠየቁ ትናንት ማታ ወዳልታወቀ ቦታ ተወስደዋል። የት እንደሄዱ አላውቅም። ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እፈልጋለሁ።”

~እነ አበራ ለሚ ክስ መዝገብ ስር የተከሰሱ የመከላከያ ምስክር አሰምተዋል። ለ3ኛ ተከሳሽ ሆራ ከበደ የመከላከያ ምስክርነቱን የሰጠው ቡልቲ ተሰማ በእነ አበራ ለሚ መዝገብ ያሉ ተከሳሾች ላይ የመሰከረው ግለሰብ ስም እየቀየረ በተለያዩ መዝገቦች ክስ የቀረበባቸው እስረኞች ላይ እንደሚመሰክር አስረድቷል። ምስክሩ ሀምሌ 13/2009 ዓም በእነ አበራ ለሚ ክስ መዝገብ ሀብታሙ ፈይሳ፣ እንዲሁም ነሃሴ 6/2009 ደግሞ ጋድጌዳ ግርማ ብሎ በራሱ በአቶ ቡልቲ ላይ እንደመሰከረ ተገልፆአል።

~እነ መልካሙ ክንፉ ክሳቸው እንዲሻሻል በጠየቁት መሰረት ሁለት ጊዜ ተሻሻለ ተብሎ ሳይሻሻል መቅረቱን ገልፀዋል። በዛሬው እለት ለ3ኛ ጊዜ የተሻሻለ ነው የተባለ ክስ ተነቦላቸዋል። ፍርድ ቤቱ የአንደኛ ተከሳሽ መልካሙ ክንፉ ክስ መሻሻሉን ገልፆአል። ሆኖም ክሱ ከተነበበ በኋላ ተከሳሾች ይሻሻል የተባለው የ1ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች መሆኑን አስታውሰው የተነበበላቸው የመጀመርያው ክስ እንጅ የተሻሻለ ነገር እንደሌለው ገልፀዋል። ባለፈው ቀጠሮ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ክሱን አሻሽሎ በቶሎ ካላመጣ ተከሳሾቹን በነፃ አሰናብታለሁ እንዳለ አስታውሰው ቃሉን እንዲጠብቅ ገልፀዋል።

~ፍርድ ቤቱ የሟች አየለ በየነ ክስ እንዲቋረጥ በመወሰን ለአቃቤ ህጉ ትዕዛዝ ባስተላለፈበት ወቅት አቃቤ ህጉ አቶ መኩሪያ አለሙ “ተከሳሽ መሞቱን ሳላረጋግጥ ክሱን ማቋረጥ አልችልም” ብለዋል። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠቱን በማስታወስ፣ የአስከሬን ምርመራ ማስረጃም መዝገቡ ጋር መያያዙን ገልፆአል። አቃቤ ሕጉ ይህን መረጃ ካገኘ ክሱን እንደሚያቋርጥ ገልፆአል። ፍ/ ቤቱ መዝገቡን አይቶ ክሱ ተሻሽሏል አልተሻሻለም የሚለውን አይቶ ለመበየን ለታህሳስ 10/2010 ዓም ቀጠሮ ይዟል።

~ በማስተር ፕላኑ ምክንያት የተነሳውን የህዝብ ተቃውሞ አስተባብሯል፣ የኦነግ አባላትን አደራጅቶ አመፅ መርቷል የሚል የ”ሽብር” ክስ የተመሰረተበት ጃራ ሃዋዝ 5 አመት ተፈርዶበታል።

የፖለቲካ እስረኞች በኢትዮጵያ እየተፈፀመባቸው ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን አስመልክቶ የድረሱልን ጥሪ አቀረቡ

በመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ ላይ ያሉ 38ቱ ተከሳሾች አቤቱታ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ያቀረበውን ሪፖርት አያይዘን ለዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ጀኔባ ለመክሰስ የተገደድን ስለሆነ ስለ ሰዎች መብትና ነፃነት የሚያስብ፣ የሚቆረቆር ግለሰብም ሆነ ተቋም ፣ የማንኛውም ሀገር ዜጋ ኢሰብአዊ ድርጊት የፈፀሙብን አካላትን በህግ እንድንፋረዳቸው እንድትረዱን፣ ለዓለም ህዝብ እንድታደርሱልን ጥሪ እናቀርባለን!
Masresha Setie
ፎቶ፡- ማስረሻ ሰጤ

~ጥፍራችን በፒንሳ ተነቅሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ አይደገምም ተብሎ ሀውልት የተሰራለት የቶርች ገረፋ ተፈፅሞብናል። ንብረታችንን ዘርፈውናል። ህክምና ተከልክለናል። ለነርቭ፣ ስነ ልቦና እና ለተለያዩ በሽታዎችና ቀውስ ተዳርገናል። ይህንን የደረሰብንን በደል ለፍርድ ቤት በመናገራችን ለ3 ወራት ጨለማ ቤት ከተውን ቤተሰቦቻችን እንዳናገኝ ተከልክለን ሕገ መንግስታዊ መብታችን ተጥሷል።

~አማራና ጉራጌ ግንቦት ሰባት፣ ኦሮሞን ኦነግ፣ ሙስሊሞችን አልሻባብ በማለት መብታችን ተረግጧል። በእኛ በተከሳሾች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙብን አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን ምርመራ እንዲያካሂድ ግልባጭ የተላከለት ቢሆንም እስካሁን ድረስ ቀርቦ ያናገረን አካል የለም። ይህም በመሆኑ የሰዎችን መብት ለማስጠበቅ ኃላፊነት ላለበት ዓለም አቀፈ የሰብአዊ መብት ኮምሽን ለማመልከት ተገደናል።

እኛ 38ቱ ተከሳሾች ቀድሞ ተከሰን በነበርንበት ክስ የዋስትና መብተችንን ተከልክለን እንደማንኛውም እስረኛ ክሳችንን በቀጠሮ እየተከታተልን ሳለን ነሃሴ 28/ 2008 ዓ•ም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ ምክንያት “ሊያመልጡ ሞክረዋል!” በሚል ሰበብ፣ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የመብት ጥያቄ የሚጠይቁ ወንድሞቻችን (ጓደኞቻችንን) እኛ ፊት በጥይት ገድለው እሳት ውስጥ ጨምረው አቃጥለዋቸዋል።

እንዲህ ያለ አረመኔያዊ ድርጊት ከፈፀሙ በኋላ ገና ለገና ይህንን እውነት ያጋልጡብናል ብለው በመስጋት እኛን ወደ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት በመውሰድ ለ3ወራት ከቤተሰቦቻችን ጋር እንዳንገናኝ በማፈን፣ ለምርመራ በሚል ሰበብ በዋና ኢንስፔክተር አለማየሁ በሚመራው ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ አይደገምም ተብሎ ሰማዕታት ሙዝዬም ውስጥ ሀውልት የተሰራለት የ”ቶርች” ገረፋ ተፈፅሞብናል።

በካቴና ታስረን፣ ተሰቅለን ተገርፈናል። ጥፍራችን በፒንሳ ተነቅሏል። በኤሌክትሪክ ሾክ ተደርገናል። በሚስማር ውስጥ እግራችንና ጀርባችን ተበሳስቷል። ጭንቅላታችንን በሰደፍ ፈንክተውናል። የተወሰንን ታራሚዎች ተለይተን ብልታችን ላይ ሁለት ሊትር ሀይላንድ ውሃ ተንጠልጥሎብናል። ሌሎችም ተዘርዝረው የማያልቁ ብዙ በደሎች ተፈፅመውብናል።

ይህ የደረሰብን ኢ_ሰብአዊ ድርጊት ታህሳስ 14/2009 ዓ•ም ለፍርድ ቤት በማሳየትና በማስረዳት ፎቶ መነሳት አለብን ብንልም ፍርድ ቤቱ ጥያቄያችን ሊቀበለን አልቻለም። ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ስንመለስ ደግሞ “ፍርድ ቤት ሄዳችሁ ብትለፈልፉ ምንም አታመጡም!” በማለት እስከ መጋቢት 12/2009 ዓ•ም ድረሰ ለ3 ወራት ጨለማ ቤት ውስጥ ከተው የቤተሰብ ግንኙነት ከልክለውን በፀሀይ ብርሃን እጦት መልካችን ቢጫ እስኪሆንና አይናችን ብርሃን ማየት እስኪያቅተው ድረስ ተቆልፎብን ተሰቃይተናል።

እንደዚህ አይነት ግፍ የተፈፀመብን በወቅቱ የነበሩ በጣት የሚቆጠሩ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎችን ከተጠያቂነት ለማዳን በጣም ደካማ አስተሳሰብ ያላቸው የመንግስት ኃላፊዎች እኛን የፖለቲካ መልስ ለማድረግ የወሰኑት ውሳኔ ነው። ህሊናቸውን ሸጠው በእኛ በንፁሃን ላይ እንዲህ አይነት ስቃይ የፈፀሙብን፣ ያስፈፀሙብን እንዲሁም ሀሳት የተቀነባበረ ክሰ የከሰሱን።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ወደ ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስደን የተፈፀመብንን ኢ_ሰብአዊ ድርጊት የኮምሽኑ መርማሪዎች ከ10 ወራት ቆይታ በኋላም ቢሆን በአይናቸው ያዩትን እውነት በዝርዝር በሪፖርት ለፍርድ ቤት አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱም ሰብአዊ መብት ኮምሽን ሪፖርት ላይ ብይን ለመስጠት ለህዳር 29/ 2010 ዓ•ም ቀጠሮ ይዟል።

#የኢትዮጵያሰብአዊመብትኮምሽን ስላቀረበው ሪፖርት ያለን አስተያየት:_
1) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን (ኢሰመኮ) የተፈፀመብንን ኢ_ሰብአዊ ድርጊት ሙሉ ለሙሉ አላካተተም።

2)የኢሰመኮ ኢ _ሰብአዊ ድርጊት የፈፀሙብን አካላት በሕግ እንዲጠየቁ በማለት ቁርጥ ያለ ሪፖርት ማቅረብ ሲገባው እና የኮምሽን መስርያ ቤቱ ጉዳዩን ተከታትሎ በዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያደረሱ አካላት በሕግ ማስቀጣት ሲገባው ምክረ ሀሳብ በማለት የተለሳለሰ የፍራቻ የሚመስል ሪፖርት በማቅረቡ ቅር ተሰኝተናል። መስርያ ቤቱ እውነቱን እያወቀ እንዲህ ያለ ሪፖርት በማቅረቡ ምን ያህል የደህንነት ቢሮ ተፅዕኖ እንዳለበት እና በራስ መተማመን የጎደለው መስርያ ቤት መሆኑን የሚያሳይ ነው።

3) ኢሰመኮ በእኛ ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት የፈፀሙ አካላትን እንዲመረምር ወይም እንዲያጣራ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽንና ለህክምና ቡድን አባላት በመፃፉ ቅር ተሰኝተናል። ምክንያቱም ኢ_ሰብአዊ ድርጊት ከፈፀሙብን አንዱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን ነው። ውሻ ነከሰን ብለን ለጅብ እንድንናገር መደረግ የለበትም።

4) ኢሰመኮ በዚህ መልክም (በጥቂቱም) ቢሆን የተፈፀመብንን ግፍ በሪፖርት በማቅረቡ ምስጋና እናቀርባለን። ምክንያቱም ምን ያህል ተገደን ለፖሊስ ቃል እንደሰጠንና ለዶክመንተሪ ፊልማቸው በቪዲዮ እንደተቀረፅን የሚያሳይ ነው። በፍርድ ቤቱም በ27(2) ቃላችን ውድቅ እንዲደረግ የሚጠቅመን የሰነድ ማድረጃ በመሆኑ ነው።

#የህዝብተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደራል ማረሚ ያ ቤቶች ላይ ያለን አስተያየት:-
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ነን፣ ለምርመራ ነው የመጣነው ብለው በግልና በጋራ አናግረው መርምረው ምንም አይነት መፍትሄ አልሰጡንም። ምንም አይነት ሪፖርትም አላቅረቡም። በዚህም በጣም ቅር ተሰኝተናል። እንዲህ ነው እንጅ የህዝብ ተወካይ መሆን፤
1) የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እውነቱን እያወቀ፣ እኛ እንድንከሰስ በማቀነባበር፣ በህግ ጥላ ስር እያለን ወደ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስደን ያ ሁሉ ኢሰብአዊ ድርጊት እንዲፈፀምብን ማድረጉ፣
~ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ያሉ እስረኞችን በማስፈራራትና በማባበል ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በመውሰድ በእኛ ላይ እንዲመሰክሩብን በማድረጉ፣
~መርማሪዎች ነን ከሚሉ አካላት ጋር በመተባበር እኛን በመደብደብና በማስደብደብ ጨለማ ቤት አስገብቶ፣ ቤተሰብ ግንኙነት ከልክሎ በማሰቃየት በተፈፀመብን ኢሰብአዊ ድርጊት ቅር ተሰኝተናል።

2) በዚህ ኢትዮጵያዊነት በጎደለው በዘራችንና በሀይማኖታችን ተመርጠን፣ በሀሰት ተከሰን ለአመታት እንዲህ ያለ ስቃይ እንድንሰቃይ መደረጋችን ታሪክ የማይሽረው ጠባሳ በልባችን ላይ ጥላችሁብናል። የሞቱት ጓደኞቻችን! ገዳይ እናንተ! በሀሰት ተከሰን የምንሰቃየው እኛ! ፈጣሪን አትፈሩም? ግፍ አይደለም? ነገ በልጆቻችሁ አይደርስም? ከትግራይ ተወላጆች ውጭ ሌላው ዘር ጠላት ነው? ያሳዝናል!

3) በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከትግሬ ውጭ ሌላ አመራር የለም። አንድም የተማረ ወይም የበሰለ አስተዳደር የለም። ተናዳጅ፣ ተቆጭ፣ መሃይሞች ብቻ ናቸው። አብዛኛዎቹ ታጋይ የነበሩና በዘረኝነት ያበዱ ከትግሬ ውጭ ሌላው ዘር ሰው የማይመስላቸው ያልሰለጡ ናቸው። ይህ ደግሞ ለጭካኔና አረሜኔያዊ ተግባር ለመፈፀም አግዟቸዋል። ለዚህ ነው ፍርድ ቤት ሄደን ስንናገር የምንደበደበው። ጨለማ ቤት የምንገባው ማገናዘብ በማይችሉ አመራሮች ስለምንመራ ነው።

ቂሊንጦ ማረፊያ የሆኑት ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አሰፋ ኪዳነ ቃጠሎው ሲደርስ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ነበርኩ ብለው ተጠርጣሪዎች በቆይታቸው ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ሰብአዊ መብት ኮምሽን መርማሪዎች የደረሰብንን ጉዳት እያወቀ! በምን አይነት ሰዎች እጅ ተይዘን እንዳለን ማሳያ ነው።

#በ19ኛወንጀልችሎት ዳኞች ላይ ያለን ቅሬታ

ከነሃሴ 1 እስከ 12/2009 ዓ•ም በተከታታይ ቀናት ዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን እንዲያሰማ ቀጠሮ የተያዘ ቢሆንም ሌሎች መዝገቦችን በተደራቢ በመስራት በጠዋቱ ፕሮግራም ላይ ዳኞች ከ4 ሰዓት በፊት ባለመግባት ጉዳያችን ተጓትቶብናል።

ይህ ሳያንስ ቀሪ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት በሚል ነሃዴ 12/2009 ዓም፣ ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 3 /2010 ዓም ድረስ የግማሽ አመት ቀጠሮ ተቀጥሮብናል። በዚህም ቅር ተሰኝተናል። “የዘገየ ፍትህ እንደተከለከለ ይቆጠራል” የሚለውን መርህ የጣሰ ተግባር ነው።

2) በፍርድ ቤቱ ውስጥ ለሟች ቤተሰቦች፣ ለእኛ ቤተሰቦችና የእኛን ጉዳይ መከታታል እና መታዘብ ለሚፈልጉ የትኛውም ወገኖች በችሎት ውስጥ በቂ የመቀመጫ ወንበር አለመኖር፣ የችሎት መጥበብ፣ በምስክር አሰጣጥ ወቅት ዳኞች ገለልተኛ አለመሆን ቅር አሰኝቶናል።

#ለኢትዮጵያሕዝብና #ለዓለምአቀፍ ማህበረሰብ የምናቀርበው የድረሱልን ጥሪ!
1) ይህ ክስ ባለቤት አለው። ክሱ ለባለቤቶቹ ይሰጥ! ክሱ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎችና ፖሊሶች ነው።
2) ኢትዮጵያ ውስጥ እውነት መንግስትና ሕግ ካለ በእኛ ላይ የቀረበው ክስ ሊቋረጥ ይገባዋል። የምናውቀው ብዙ ሚስጥር አለን። ከፍተኛ የመንግስት አካላት መጥተው ሊነጋግሩን ይገባል።
3) የብሔራዊ ደህንነት ስብሰባ ላይ በቴሌቪዝን ያየነው ዋና ኢንስፔክተር አለማየሁ ኃይሉ የተባለው የማዕከላዊ መርማሪ ፖሊስ የሚመራው ቡድን ለፈፀመብንና ላስፈፀመብን ኢሰብአዊ ድርጊት በህግ ይጠየቅልን።

4) ኢሰመኮ ያቀረበውን ሪፖርት አያይዘን ለዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ጀኔባ ለመክሰስ የተገደድን ስለሆነ ስለ ሰዎች መብትና ነፃነት የሚያስብ፣ የሚቆረቆር ግለሰብም ሆነ ተቋም ፣ የማንኛውም ሀገር ዜጋ ኢሰብአዊ ድርጊት የፈፀሙብን አካላትን በህግ እንድንፋረዳቸው እንድትረዱን፣ ለዓለም ህዝብ እንድታደርሱልን ጥሪ እናቀርባለን!

5) ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 3/2010ዓ•ም ድረስ ዐቃቤ ሕግ የሚያሰማቸውን የሀሰት ምስክሮችና የሀሰት ሁኔታ እንድትታዘቡልን ጥሪ እናቀርባለን።

6) በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ ምክንያት ከእኛ ከ38ቱ ተከሳሾች ውጭ 121 ተጠርጣሪዎች በዚሁ ወንጀል ከ20 እስከ 25 ተከፋፍለው በሌላ መዝገብ መከሰሳቸው ይተወቃል። ከእነሱ ውስጥ አርማዬ ዋቄ በማረሚያ ቤት ፖሊሶች ተደብድቦ የተገደለ በመሆኑ ጉዳዩ በሕግ ተይዞ እየተመረመረ ይገኛል። ሌሎቻችን ሰውነታችን በድብደባ በልዞ፣ ዝለን፣ ከነገ ዛሬ ገደሉን እያለን ስጋት ላይ ስለሆንን ይህ ግፍ እንዲቆም እንጠይቃለን።

#ለዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ኮምሽን
#ጀኔባ

እኛ 38ቱ ተከሳሾች ቀድሞ ተጠርጥረን በታሰርንበት ክስ የዋስትና መብታችን ተከልክለን ክሳችን በመከታተል ላይ እያለን ነሃሴ 28/2008 ዓ•ም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በደረሰበት የእሳት ቃጠሎ ሊያመልጡ ሞክረዋል በሚል ምክንያት በእስር ቤት ውስጥ የመብት ጥያቄ ይጠይቁ የነበሩ በርካታ ወንድሞቻችን ተነጥለው በማረሚያ ቤተ ፖሊሶች በጥይት እኛ ፊት ተገድለውብናል። ይህ ሳያንሳቸው ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን እኛ ለምርመራ በሚል ሰበብ ወደ ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስደን በዘራችን ብቻ ተመርጠን የአማራ፣ የኦሮሞና የጉራጌ ተወላጆች ብቻ ከፍተኛ የሆነ ኢሰብአዊ ድርጊት ተፈፅሞብናል።

ጥፍራችን በፒንሳ ተነቅሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ አይደገምም ተብሎ ሀውልት የየሰራለት የቶርች ገረፋ ተፈፅሞብናል። ንብረታችንን ዘርፈውናል። ህክምና ተከልክለናል። ለነርቭ፣ ስነ ልቦና እና ለተለያዩ በሽታዎችና ቀውስ ተዳርገናል። ይህንን የደረሰብንን በደል ለፍርድ ቤት በመናገራችን ለ3 ወራት ጨለማ ቤት ከተውን ቤተሰቦቻችን እንዳናገኝ ተከልክለን ሕገ መንግስታዊ መብታችን ተጥሷል።

አማራና ጉራጌ ግንቦት ሰባት፣ ኦሮሞን ኦነግ፣ ሙስሊሞችን አልሻባብ በማለት መብታችን ተረግጧል። ይህን ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ጥቅምት 20/2010 መርምሬ አረጋግጫለሁ ባለው ሪፖርት ላይ በመጠኑም ቢሆን ተፈፀመብንን ኢ ሰብአዊ ድርጊት አቅርቧል። በእኛ በተከሳሾች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙብን አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን ምርመራ እንዲያካሂድ ግልባጭ የተላከለት ቢሆንም እስካሁን ድረስ ቀርቦ ያናገረን አካል የለም። ይህም በመሆኑ የሰዎችን መብት ለማስጠበቅ ኃላፊነት ላለበት ዓለም አቀፈ የሰብአዊ መብት ኮምሽን ለማመልከት ተገደናል።

1)አሁንም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከፍተኛ የሆነ ድብደባ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰብን ስለሆነ፣ አሁንም ህይወታችን አደጋ ላይ ነው። በዚሁ በቃጠሎ ምክንያት በሌላ መዝገብ ከተከሰሱ ወንድሞቻችን ውስጥ አርማዬ ዋቄ የተባለ ተከሳሽ በማረሚያ ቤት ፖሊስ ተደብድቦ ተገድሎ ቤተሰቦቹ በክስ ላይ ይገኛሉ
2) ከነሃሴ 1 እስከ 12/2009 ዓ•ም ድረስ ዐቃቤ ሕግ በሀሰት ያሰለጠናቸውን ምሰረክሮች ያሰማ ሲሆን ቀሪ ምስክሮችን ለማሰማት በሚል ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 3/2010ዓ•ም በተከታታይ ቀናት ተቀጥረናል። እስካሁንም ፍርድ ቤት ቀርበው የመሰከሩ ምስክሮች በተፅዕኖ ስር ሆነው ዐቃቤ ሕግ ባሰለጠናቸው መሰረት የመሰከሩ ናቸው። ቀሪ ምስክሮችም እንደ ቀድሞ ምስክሮች የታሰሩና በተፅዕኖ ስር ሆነው የሚመሰክሩ ናቸው። አንዳንድ በዋስት እና በነፃ የተፈቱ ምስክሮችን በዐቃቤ ሕግና ፖሊስ “እኛ በምንላችሁ መሰረት ነው የምትመሰክሩት” እየተባሉ ፣”ይህን ካደረጋችሁ ከቀድሞ ክሳችሁ ነፃ ትባላላችሁ” እያሉ በመደለል እንዲሁም፣ የተለያየ ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው እንደሆነ አረጋግጠናል። ይህንን በተፅዕኖና ምስክሮችን በማስገደድ የሚደረግ አመሰካከር እንድትታዘቡልን ጥሪ እናቀርባለን።

3) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ባቀረበው ሪፖርት መሰረት በእኛ በተከሳሾች ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት የፈፀሙብን አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ግፊት እንድታደርጉልን እንጠይቃለን። ነገር ግን ኢሰብአዊ ድርጊት ከፈፀሙብን አንዱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን በመሆኑ በሌላ ገለልተኛ ወገን ምርመራው እንዲካሄድ እንጠይቃለን።

4) ኢትዮጵያ ውስጥ የምትገኙ ኤምባሲዎች ይህንን በሀገራችን እየተፈፀመብን ያለውን ኢሰብአዊ ድርጊት እንድትቃወሙልንና አሁንም ህይወታችን አደጋ ላይ በመሆኑ የድረሱልን ጥሪ እናቀርባለን።
5) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ምርመራ አረጋግጫለሁ ብሎ ባቀረበው ሪፖርት ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ሲገባው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን የወንጀል ምርመራ ክፍልና የህክምና ባለሙያዎች አስፈላጊ ምርመራ በማድረግ ውጤቱን ለሚመለከተው አካል አስተላልፈው የተደረሰበትን ድምዳሜ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን እንዲያቀርቡ ምክረ ሀሰብ ቀርቧል በማለት ያቀረበው ሪፖርት ላይ በጣም ቅር ተሰኝተናል።

ምክንያቱም በሕግ ሊጠየቁ የሚገባቸው አካላት በሕግ ሊጠየቁ ይገበል ማለት ሲገባው፣ ጉዳዩን ተከታትሎ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ሲገባው በጣም ተለሳልሶ የፍራቻ የሚመስል መደምደሚያ ሪፖርት በማቅረቡ ቅር ተሰኝተናል።

#ግልባጭ:_
#ለአፍሪካ ህብረት
#ለአሜሪካ፣ ለብሪታኒያ፣ ስውይድን፣ ካናዳ፣ ኖርዎይ ኤምባሲዎች
#ለማህበራዊ ሚዲያ፣ ለራዲዮ ጣቢያዎች፣ ኢቢሲና ሌሎች ሚዲያዎች ይድረስልን
#ወደእንግሊዝኛና አረብኝ ተተርጉሙ ለዓለም ህዝብ ይድረስልን

%d bloggers like this: