Daily Archives: December 21st, 2017

በውዝግብ የተጠናቀቀው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የችሎት ውሎ

በጌታቸው ሺፈራው

~ተከሳሾቹ ጆሯቸውን በእጃቸው ደፍነው፣ ጀርባቸውን ለዳኞ ሰጥተው ችሎቱን “አንሰማም! አናይም!” ብለዋል
~ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ነኝ ብሎ የቀረበውን ግለሰብ ዐቃቤ ሕጉ ክዶታል።ዐቃቤ ሕጉ በሀሰት እንድመሰክር ተገድጃለሁ ያለውን ግለሰብ የእኔ ሳይሆን የጠበቃ ምስክር ነው ብሎታል።
~ጨለማ ቤት የታሰሩት መነኩሴ በቀጠሯቸው አልቀረቡም
~ እነ ተሻገር ወ/ሚካኤል ለሁለተኛ ጊዜ በዳኛው ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል። ብይኑ በማረሚያ ቤት ይደርሳቸዋል ተብሏል። ታዳሚ ወደ ችሎት እንዳይገባ ተከልክሏል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ውሎ በውዝግብ ተጠናቅቋል። በጠዋቱ የፍርድ ቤቱ የስራ ሰዓት ተከሳሾች ችሎቱን አንሰማም፣ አናይም ብለው ተቃውሞ አሰምተዋል። ከሰዓት በነበረው የችሎቱ ሰዓት የቀረቡት እነ ተሻገር ወልደሚካኤል ባሰሙት ተቃውሞ ችሎቱ ብይን ማንበብ ባለመቻሉ ብይኑን ባሉበት ለማድረስ ተገዷል። ፍርድ ቤቱ ለእነ ተሻገር በችሎት ቀጠሮ እንዳልሰጠ ታውቋል።

ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት እነ ጎይቶም ርስቃይ ጆሯቸውን በእጃቸው በመድፈን እና ፊታቸውን በማዞር ችሎቱን አንሰማም አናይም ብለው ተቃውሟቸውን ገልፀዋል።
እነ ጎይቶም ዛሬ ታህሳስ 11/2010 ዓም ቀጠሮ የተያዘላቸው በክሱ ላይ ያቀረቡትን መቃወሚያ ብይን ለመስማት ሲሆን ተከሳሾቹ ብይኑ ከመነበቡ በፊት ዳኛ ዘርዓይ ወ/ሰንበት ከችሎት እንዲነሱ አቤቱታ አቅርበው፣ ብይኑ ዳኛው ከተነሱ በኋላ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

ይሁንና ፍርድ ቤቱ ብይኑን ማንበብ በመቀጠሉ ተከሳሾቹ ጆሯቸውን በእጃቸው በመድፈን አንሰማም ብለዋል። በተጨማሪም ፊታቸውን በማዞር ጀርባቸውን ለችሎቱ ሰጥተው ብይኑ ተነቧል። ብይኑን ያነበቡት ተከሳሾቹ ከችሎት እንዲነሱ አቤቱታ እናቀርብባቸዋለን ያሏቸው ዳኛ ዘርዓይ ወ/ሰንበት ናቸው።
~ከሰዓት በነበረው የፍርድ ቤቱ የስራ ሰዓት ፍርድ ቤት የቀረቡት በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል የክስ መዝገብ ስር የተከሰሱ 35 እስረኞች ለ2ኛ ጊዜ በዳኛ ዘርዓይ ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል። ተከሳሾቹ ባለፈው ቀጠሮ ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ሊዳኙን አይገባም የሚል ተቃውሞ በማሰማታቸው ችሎት ደፍራችኋል በሚል እንደተፈረደባቸው በመግለፅ በክሱ ላይ ያቀረቡት መቃወሚያ ብይን ከመነበቡ በፊት ዳኛው ሊነሱ እንደሚገባ መግለፃቸው ታውቋል።

ይሁንና ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹ የዳኛ ይነሳልን አቤቱታ በፅሁፍ ያልደረሰው መሆኑን ገልፆ ብይኑን ለማንበብ በመሞከሩ ተቃውሞ ገጥሞታል። የተከሳሾቹ መዝገብ የያዙትና ብይኑንም ለማንበብ የሞከሩት ከችሎት እንዲነሱ ተቃውሞ የቀረበባቸው ዳኛ ዘርዓይ መሆናቸው ተገልፆአል። ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን ስም ሲጠራ ተከሳሾቹ “አቤት” ባለማለታቸው እንዳልቀረቡ (እንደሌሉ) ተደርጎ ተመዝግቧል።

1ኛ ተከሳሽ ተሻገር ወ/ሚካኤል ዳኛ ዘርዓይ ሊዳኘን አይገባም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አቶ ተሻገር ” እኔ ወልቃይቴ ነኝ። አማራ ነኝ። እኛን በፌስቡክ ሲዘልፍ የነበረ፣ ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ ነው እያለ ሊዳኘን አይገባም። እኛ ትናንትም፣ ዛሬም ነገም አማራ ነን። ዳኛ ዘርዓይ ሊዳኘን አይገባም። ዳኛ ዘርዓይ ሊዳኝ ከፈለገ ከፖለቲካው ገለልተኛ ሆኖ ሌላ ቦታ ሄዶ ይዳኝ” የሚል ይዘት ያለው አስተያየት ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል ቂሊንጦ እስር ቤት ያለው ጨለማ ቤት ውስጥ የሚገኙት አባ ገብረስላሴ ወልደሐይማኖት በዛሬው ቀጠሮ አልቀረቡም። ወደ ችሎቱ መግባት የተከለከለ ሲሆን ፖሊሶችን እንድንገባ ስንጠይቅ ዳኞቹ ታዳሚ እንዳያስገቡ ትዕዛዝ እንደሰጧቸው ገልፀውልናል። ቀድመው ወደ ችሎት ገብተው የነበሩ የተከሳሾች ቤተሰቦች ከችሎት እንዲወጡ ተደርጓል። እነ ተሻገር ሲናገሩ ችሎቱ በር አካባቢ ሆነን ስናዳምጥ ፖሊሶች ከችሎት እንድንርቅ አድርገዋል። ከችሎት እንድንርቅ ያደረጉት በዳኞች ትዕዛዝ እንደሆነም ገልፀውልናል።

~ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዐቃቤ ሕግ ራሱ የቆጠረውን ምስክር የእኔ አይደለም ብሏል። በእነ ክንዱ መሃመድ የክስ መዝገብ ላይ በዐቃቤ ሕግ 1ኛ ምስክር ሆኖ የተቆጠረውን አቶ ሸዋንግዛው የሽጥላ ዐቃቤ ሕግ “የእኔ ምስክር አይደለም” ሲል ክዷል። ምስክሩ በጠዋቱ የችሎት ሰዓት በችሎት ቀርቦ በተከሳሾች ላይ በሀሰት እንዲመሰክር መገደዱን ገልፆአል። በወቅቱ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ሓፍታሙ ቸኮለ ምስክሩን እንደማያውቀው ገልፆ የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ 1ኛ የዐቃቤ ምስክር መሆኑን በማረጋገጡ ዐቃቤ ሕጉም እንደገና 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር መሆኑን አምኖ ነበር።
አቶ ሸዋንግዛው የሽጥላ ከሰዓት ምስክርነቱን እንዲሰጥ ቀጠሮ በተያዘው መሰረት ከሰዓት ሲቀርብ፣ ዐቃቤ ሕጉ “የተከሳሾች ጠበቃ ምስክር እንጅ የእኔ ምስክር አይደለም” ብሎ ክዷል።

የተከሳሾች ጠበቃ አዲሱ ጌታነህ በበኩሉ ምስክሩ ዐቃቤ ሕግ በማስረጃ ዝርዝር ላይ ያስቀመጠው፣ ጠዋትም ማንነቱን ለፍርድ ቤቱ የገለፀ፣ ዐቃቤ ሕግ በጠራው መሰረት በቀጠሮው የቀረበ እና በመታወቂያውም መለየት የሚቻል መሆኑን በመግለፅ የዐቃቤ ሕግ ምስክር መሆኑን አስረድቷል።

ዐቃቤ ሕግ ዛሬ የቀረበው ሳይሆን ሌላና በምስክርነት ቆጥሬዋለሁ የሚለው ሸዋንግዛው ቀርቦ እንዲመሰክር ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ ብሏል። ፍርድ ቤቱ 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር መሆኑን ገልፆ በቀጠሮ መሰረት የቀረበውን አቶ ሸዋንግዛው በጠዋቱ ችሎት ከተናገረው፣ ከዐቃቤ ሕግና ከተከሳሾች ጠበቃ የራሱን ግምት እንደሚወስድ በመግለፅ 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር እንዲቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

%d bloggers like this: