የፍርድ ቤት ችሎት ትዝብት
ማህሌት ፋንታሁን
የጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ትዝብት። ብዙ መዝገቦች በቀጠሯቸው መሰረት ሳይሰሩ ተለዋጭ ቀጠሮዎች እየተሰጠባቸው ነው። የሚሰጠው ምክንያት ‘ለችሎቱ አዲስ ዳኞች በመሆናችን’ የሚል ነው። ተከሳሾችም በጉዳያቸው አላግባብ መራዘም እና በማረሚያ ቤት በሚደርስባቸው በደል ተማረው አቤቱታቸውን እያሰሙ ነው።
የዛሬዎቹን አቤቱታዎች በስሱ እነሆ!
� አቤቱታ አንድ። በእነ ክንዱ ዱቤ መዝገብ 2ኛ ተከሳሽ ዘመነ ጌቴ ፤ “ማእከላዊ እያለሁ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ግፍ እና በደል ደርሶብኛል። በድቅድቅ ጨለማ ለ6ወር ተቀምጫለሁ። በድብደባ ብዛት የግራ አይኔ ማየት አይችልም። ዘሬን እንዳልተካ የዘር ፍሬዬን መተውኛል። አማራነታችን እየተጠቀሰ ይሰድቡናል። እኛ ስንወለድ አማራ ሆነን ወይም ኦሮሞ ሆነን መወለድ ፈልገን አይደለም። የተፈጥሮ ነገር ሆኖ ነው። አማራ አህያ ነው። አማራ ጅብ ነው። አህያውን በጅቡ እናስበላዋለን ይሉናል። በማእከላዊ የነበረው ስቃይም ተከትሎኝ ቂሊንጦ መጥቷል። የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች እየጠሩ ይደበድቡኛል። ምንም አይነት የመኖር ህልውና የለንም።” ዘመነ ጌቴ ይህን እያለ ዳኞቹ እንዲያበቃ/እንዲያቆም ሲነግሩት አብዛኞቹ እስረኞች ‘ይናገር! የሆነውን ነው ሚያወራው’ በማለት መናገሩን እንዲቀጥል ጠይቀዋል። ዘመነ ጌቴ ይህን ብሎ አቤቱታውን አጠቃሏል። “ስቃዬን እየተናገርኩ ነው። ስነልቦናዊ እና አካላዊ ጉዳት ደርሶብኛል፤ እየደረሰብኝም ነው። ፍርድ ቤቱ መፍትሄ ይሰጥልኝ ዘንድ ነው የምናገረው።”
�አቤቱታ ሁለት። በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል መዝገብ አባ ገ/እየሱስ ፤ “ማእከላዊ የደረሰብንን ግፍ ከዚ ቀደም ተናግረናል። ቂሊንጦ ከገባሁ በኋላ ችግር እየተከሰተብኝ ነው። ከወንድሞቼ ጋር እንዳልገናኝ እና አብሬ እንዳልበላ ይከለክሉኛል። ኦፊሰር ካሱ የሚባለው የዞን 3 ሃላፊ ነው የሚከለክለኝ። እኔ አዲስ አበባ ዘመድ ስላለኝ በሰሃን ተቋጥራ የምትመጣልኝን ምግብ ከሌሎች ጋር ተካፍዬ እንዳልበላ ተደርጌአለሁ። ማውራትም መጫወትም አልቻልኩም። ተፅእኖ እየተደረገብኝ ነው። ይሄን ክረምት የከረምኩት ክራሞት እ/ር የቁጠረው።”
�አቤቱታ ሶስት። 5ኛ ተከሳሽ አባ ” እሳቸው[አባ ገ/እየሱስ] የተናገሩት በደልና ግፍ በኔ ላይም ደርሷል። እኔ ወገን የለኝም። በልጅነቴ ነው ወገኔን ትቼ ገዳም የገባሁት። በገዳሙ[ዋልድባ] የነበሩትን አፅመ ቅዱሳን አፈራርሰው ዛፎቹን ቆርጠው ክሰል እያወጡበት ነው። ይህን ተቃውመን ብንናገር አሸባሪ ተባልን።” አባ ይህን ሲናገሩ ዳኞቹ በፊት ስለተከሰተ ነገር ሳይሆን በማረሚያ ቤት ስለሚደርስባቸው በደል ብቻ መናገር ገልፀውላቸዋል። ሆኖም አባ “ስለበፊቱም ስለአሁኑም መናገር እችላለሁ” ብለው የነበረ ቢሆንም ዳኛው ስነስረአቱ እንደማይፈቅድላቸው ከገለፁላቸው በኋላ አባ በማረሚያ ቤቱ ስለሚደርስባቸው በደል ማሰማት ቀጥለዋል። ” በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 3ቴ እና 4ቴ ቢሮ እየጠሩ ያንገራግሩናል (ያስፈራሩናል ፤ ይዝቱብናል)። ፀሎት እንድንፀልይ አይፈቀድልንም። መንግስት ነው እንዴ ይቺን ሃገር የሚጠብቃት?! እ/ር ነው የሚጠብቃት! አበበ የሚባል ፖሊስ እና ካሱ የሚባል ኦፊሰር ‘አመፅ እያነሳሳችሁ ነው ጨለማ ቤት እናስገባችኋለን’ እያሉ ያስፈራሩናል። ከ2004 ጀምሮ እየተሰቃየን ነው። ገዳም እንዳንቀመጥ ተከለከልን። እናንተስ ለምንድነው እውነት ማትፈርዱልን? ለምን ፀሎት እንዳንፀልይ ተከለከልን?”
�አቤቱታ አራት። በእነ ተሰኢድ ኑርሁሴን ኑሩ ” የታሰርኩት አማራ ስለሆንኩ ነው። ጎንደሬ ስለሆንኩ ነው። ማእከላዊ ጥፍሬን ነቅለውኛል። ማእከላዊ የዘር ፍሬ ሚኮላሽበት የሶት ልጅ ጡት አስረው የሚጎትቱበት የስቃይ ቦታ ነው። እዚህ ያለነው ሁላችንም በማእከላዊ ስቃይ አሳልፈናል። በአደባባይ መናገር የቻልነው እና የደፈርነው ብቻ እንናገር ብለን ነው። እኔ የኪነጥበብ ሰው ነኝ። የዜማ እና የግጥም ደራሲ ነኝ። ያሰሩኝ ‘ላባ’ የተሰኘ ባለ መቶ ገፅ የግጥም መድብሌን ለማሳተም እየሄድኩ ሳለ ነው። እና የግጥም መድብሉ አልተመለሰልኝም። የጣሱት የሰብአዊ መብት እንኳን ሊመለስልኝ የሚቻል አይደለም። የግጥም መድብሌን ይመልሱልኝ። ከክሱ ጋር ግንኙነት የለውም። በማስረጃነትም አልተያያዘም። እያዝናና የሚያስተምር የስነፅሁፍ ስራ ነው። በተጨማሪም ፀሎት እንዳላደርግ ተከልክያለው። እኔ ሙስሊም ነኝ። እንዳልሰግድ ይከለክሉኛል። ክርስቲያኖችም እንዳይፀልዩ ተከልክለዋል። ከዚህ የመጣችሁ ቤተሰቦች ይህን በደላችንን ለሚዲያዎች ሁሉ ንገሩልን። ” ዳኞች የሰይድን አቤቱታ ከሰሙ በኋላ በማእከላዊ መርማሪዎች ተወሰደብኝ ያለውን የግጥም መድብል በተመለከተ ለማጣራት ከማእከላዊ የመጣ ፖሊስ መምጣቱን ጠይቀው ሲቪል የለበሱ እና ከአቃቤ ህግ ጎን ቁጭ ብለው ከነበሩ 3ት የማእከላዊ ፖሊሶች አንዱ በመቆም ከማእከላዊ መምጣቱን ለዳኞቹ መልስ ሰጥቷል። ፖሊሱ ስለጉዳዩ ሲጠየቅ የሚያቀው ነገር እንደሌለ የገለፀ ሲሆን ዳኞች በቀጣይ ቀጠሮ አጣርቶ ምላሽ ይዞ እንዲመጣ ካዘዙት በኋላ ስሙን ሲጠይቁት በችሎት ስሙን ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ዳኞች ከመታወቂያው ላይ ስሙን እንዲገለብጡም መታወቂያውን በማውጣትም በችሎት አስተባባሪ በኩል ለዳኞቹ ልኳል።
�አቤቱታ አምስት። በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል መዝገብ 28ኛ ተከሳሽ አራጋው፤ ” በማእከላዊ ድብደባ ያደረሱብን መርማሪዎች እዚሁ ቁጭ ብለዋል። ግፍና በደል ያደረሱብን እነሱ ናቸው። ያልሆነ ነገር ፤ ያላልነውን ፤ ያላደረግነውን ፅፈው በግዳጅ ያስፈረሙን እነሱ ናቸው። መርማሪው ስሙን ሲጠየቅ በግልፅ ያልተናገረበት ምክንያት ይታወቃል። የሰራውን ስለሚያውቅ ነው። ህግ ካለ በህግ እንዳኝ። እነዚህ [ወደ ማእከላዊ መርማሪ ፖሊሶች እየጠቆመ] መርማሪዎች ናቸው፤ ደብዳቢዎች ናቸው እንደገና እዚህ መጥተው ደግሞ ይከታተሉናል። ምስክርም የሚሆኑት እነሱ ናቸው። ብዙ ነገር ሆነው ነው የሚሰሩት። ” ዳኞች የአራጋውን አቤቱታ ሰምተው ከማእከላዊ የሚመጡ ፖሊሶች እንደማንኛውም ሰው መጥተው ችለቱን መከታተል እንደሚችሉ እና የመከልከል ስልጣን እንደሌላቸው ተናግረዋል።
�አቤቱታ ስድስት። በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል መዝገብ ተከሳሽ ሙላቱ ተሰማ ፤ ” ማእከላዊ በነበርኩ ጊዜ አሁን ልገልፀው በማልችለው አካሌ ላይ ድብደባ ደርሶብኛል። ከተፈቀደልኝ ልብሴን አውልቄ አሳያለሁ። እኔ የአንድነት የፍትህ እና ዲሞክራሲ ፓርቲ አባል ነኝ እንጂ አሸባሪ አይደለሁም። ካሸባሪም ጋር የምገናኝ አይደለሁም። ቂሊንጦ ጠባብ ክፍል ውስጥ አርባ እና ሃምሳ ሆነን ነው የምንኖረው። በ90ሳሜ ፍራሽ ላይ ለሁለት ነው ምንተኛው የሚቀርብልን ምግብ ተመጣጣኝ አይደለም። ቤተሰቡ ቅርብ ያለ የሚቋጥርለትን ይበላል። እኛ ሚጠይቀን የሌለ በቂ ምግብ አናገኝም። የክልላችን ፍርድ ቤት ስልጣን ስላለው ክሳችን ወደ ክልላችን ይዙርልን።”
�አቤቱታ ሰባት። በነተሻገር ወ/ሚካኤል መዝገብ ተከሳሽ ተስፋሁን ማኔ ፤ ” ማእከላዊ እያለሁ መርማሪው ተምረሃል ወይ ብሎ ጠየቀኝ። አዎ ስለው ፤ ስንት ጊዜ ወደቅክ አለኝ። አልወደቅኩም ስለው፤ አማራ ደደብ አይደለ እንዴ እንዴት አልወደቅክም? አለኝ። በቂሊንጦም ግንባታ እያስፋፉ ነው። ለግንባታው የሚሆን ድንጋይ በግዳጅ እንድሸከም እየተደረኩ ነው። ጀርባዬ ተላልጧል። ጉዳያችን በክልላችን ይታይልን።”
ለይቅርታ ያመለከተችው ‘ዘማሪት’ ምርትነሽ ጥላሁን: በምልአተ ጉባኤው ፊት ቀርባ አስረዳች፤ በይቅርታ ተቀበላት፤ በቡራኬ አሰናበታት
• በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስተባባሪነት የሚዲያ መግለጫ ትሰጣለች፤
• ለሌሎችም መመለስ ጥረት እንድታድርግ ብፁዓን አባቶች አሳሰቧት፤
• “ቤተ ክርስቲያን የይቅርታ ቤት ናት፤ጥፋታቸውን አምነው ከመጡ እንቀበላቸዋለን፤” /ብፁዓን አባቶች/
†††
ፎቶ፡ ዘማሪት ምርትነሽ ጥላሁን እና የኢ.ኦ.ተ.ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ
የቅዱስ ሲኖዶስን የምሕረት ጥሪ በመቀበል፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮና ሥርዓት ከሚገዳደረው የእነበጋሻው ደሳለኝ ሕገ ወጥ ቡድን፤ ራሷን ለይታ፣ ይፋዊ የይቅርታ ጥያቄ ያቀረበችው ‘ዘማሪት’ ምርትነሽ ጥላሁን፣ የምልአተ ጉባኤውን ይቅርታ አገኘች፡፡
የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን በተመለከተ፣ ለጥፋተኞችና ለበደለኞች እንደጥፋታቸው መጠን ምሕረት የመስጠት፣ ይቅርታ የማድረግና አስፈላጊ ከኾነም በቀኖና የመቅጣት ሥልጣን ያለው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በዛሬ፣ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የቀትር በኋላ ውሎው፣ የ‘ዘማሪት’ ምርትነሽን ማመልከቻ ተቀብሎ ይቅርታ አድርጎላታል፡፡
የይቅርታ ማመልከቻዋ፣ በምልአተ ጉባኤው ፊት በንባብ ሲሰማ፣ ከሕገ ወጥ ቡድኑ ጋራ በአባሪነት ትንቀሳቀስ እንደነበር የጠቀሰችው ‘ዘማሪት’ ምርትነሽ፣ ጥፋት መፈጸሟን አምና ይቅርታ እንዲደረግላት ጠይቃለች፡፡
“ከእነርሱ ጋራ የነበርኩ ቢኾንም፣ የዓላማቸው ተከታይ አይደለሁም፤” ያለችው ‘ዘማሪት’ ምርትነሽ፣ ሕገ ወጡ ቡድኑ ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ እንቅስቃሴ በማድረጉ ለመለየት መወሰኗን ገልጻለች፡፡ “እነርሱ ወደ ሌላ እምነት ቢሔዱም የእኔ እምነቴ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነው፤ ወዳሳደገችኝ ቤተ ክርስቲያኔ ተመልሻለሁ፤ አስተምህሮዋንና ሥርዓቷን ጠብቄ እኖራለሁ፤” በማለት ውሳኔዋን ለምልአተ ጉባኤው አረጋግጣለች፡፡
በይፋ ለመመለስ መወሰኗን አድንቀው ምክር የሰጡ ብፁዓን አባቶች፣ “ተቀብለንሻል” ብለዋታል፡፡ እንደ እርሷ፣ ጥፋታቸውን አምነው የሚመለሱ ሌሎችም ካሉ፣ የይቅርታ ቤት የኾነችው ቤተ ክርስቲያን እጆቿን ዘርግታ እንደምትቀበላቸው አስታውቀዋል፤ የበኩሏን ጥረት እንድታደርግም አበረታተዋታል፡፡
በመጨረሻም፣ ቡራኬ እንድትቀበል የታዘዘችው ምርትነሽ ጥላሁን፣ ከርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ፊት ወድቃ መስቀል ከተሳለመች በኋላ በይቅርታና ቡራኬ መሰናበቷ ተገልጿል፡፡
በቅርቡም፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤቱ አስተባባሪነት፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ቴሌቪዥንና ጋዜጣ ጨምሮ ለብዙኃን መገናኛዎች መግለጫ እንደምትሰጥ ተጠቁሟል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው፣ የምርትነሽ ጥላሁንን የይቅርታ ጥያቄ ተቀብሎ ምሕረት ያደረገላትና በቡራኬ ያሰናበታት፣ የተሐድሶ ኑፋቄ ተላላኪ በጋሻው ደሳለኝን አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን በለየበት ማግሥት መኾኑ ትኩረት ያሰጠዋል፡፡
ከሕገ ወጥ ቡድኑ ተለይታና የምሕረት ጥሪውን ተቀብላ ለመመለስ ለወሰነችው ምርትነሽ ጥላሁን፣ በዛሬው ዕለት የተደረገላት ሲኖዶሳዊ ይቅርታና አቀባበል፣ ብዙዎች፣ ራሳቸውን ከኑፋቄው ተጽዕኖ ቶሎ በማላቀቅ፣ ዛሬ ነገ ሳይሉ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ የሚያበረታታ አብነታዊ እንደ ኾነ አያጠያይቅም፡፡
ምንጭ፦ ሐራ ተዋሕዶ