በጅጅጋና አካባቢው በተፈጠረው ብጥብጥና ሁከት አብዲ መሀመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ)ን ጨምሮ 47 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሰረተባቸው።
የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዘዳንት (ፎቶ፤ ናሆም ተስፋዬ_ሪፖርተር)
በ1ኛ ክስ ከ1-26 ያሉ ተከሳሾችን ሚመለከት ሲሆን ለጊዜው ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን በቀጥታ ወይም በመላ አሳባቸውና አድራጎታቸው የወንጀሉ ድርጊትና የሚሰጠውን ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን ድርጊቱን የራሳቸው በማድረግ በህብረትና በማደም በሶማሌ ክልል ከሰኔ ወር 2010 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ቀናቶች በክልሉ ውስጥ አንዱ ወገን በሌላው ነዋሪ ላይ ጥቃት በመፈፀም እና አለመረጋጋት በመፍጠር ተሳትፈዋል በሚል በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል። ተጠርጣሪዎቹ በአካባቢው በተለምዶ ሀበሻ በሚል በሚጠሯቸው የክልሉ ነዋሪዎችና በሶማሌ ማኅበረሰብ መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር ተንቀሳቅሰዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ተከሳሾቹ በግጭቱ ውስጥ የሚሳተፉ ሄጎ በሚል ስያሜ ወጣቶችን በማደራጀት፤ የተደራጀውን የሄጎ ቡድን በገንዘብ እና በተለያዩ ቁሳቁሶች በመደገፍ፣መሳሪያ በማስታጠቅ፣ ግጭቱ የሚመራበትና መልዕክት የሚተላለፍበት ሄጎ ዋሄገን (Heego waaheegan) የሚል በፌስቡክ ገጽ በመክፈትና በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ሰዎችን ለግጭት ሊያነሳሳ የሚችሉ ይዘት ያላቸው መልእክቶችን በማሳተም እንዲሁም በክልሉ ውስጥ የጥቃቱ ዒላማ የተደረጉ ነዋሪዎችን መግደል ፣ንብረታቸውንም መዝረፍ እና ማውደም፣ባንኮችን እና ኢንሹራንሶችን መዝረፍ ፣ቤተክርስቲያኖችን እና ነዳጅ ማደያዎችን ማቃጠል አለብን በማለት በየቦታው ተንቀሳቅሰው ትእዛዝ በመስጠት በክልሉ ውስጥ ግጭት እንዲነሳ በማድረግ፥ የሰው ህይወት እንዲጠፋ ፣ በመንግስት እና በእምነት ተቋማት እንዲሁም በግለሰብ ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ፣ ሴቶች እንዲደፈሩና እና በርካታ የከተማው ነዋሪ እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸው በክሱ ላይ ተገልጿል፡፡
በ2ኛ ክስ ደግሞ ከ27-47 ያሉ ተከሳሾች በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በጠተቀሰው ቀን በክልሉ ውስጥ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ የጦር መሳሪያ እንዲያነሳ ለማድረግ በማሰብ በሶማሌ ብሔር ተወላጆች እና በሶማሌ ክልል የሚኖሩ ከሶማሌ ብሔር ተወላጅ ውጭ በተለምዶ በአካባቢው አጠራር ሀበሻ በሚል በሚጠሯቸው የክልሉ ነዋሪዎች መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር በማሰብ ሄጎ በሚል ስያሜ ወጣቶችን በማደራጀት ፣መሳሪያ በማስታጠቅ ሰዎችን ለአመፅ ሊያነሳሱ የሚችሉ መልእክቶችን በመቅረጽ እና የሄጎ አደረጃጀት ውስጥ አባል እና አመራር በመሆን ከሐምሌ 28 ቀን 2010 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ውስጥ የተለያዩ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ መሳሪያዎችን በመያዝ በግጭቱ በመሳተፍ የሰው ህይወት እንዲጠፋ ፣ በመንግስት እና በእምነት ተቋማት እንዲሁም በግለሰብ ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ፣ሴቶች እንዲደፈሩና እና በርካታ የከተማው ነዋሪ እንዲፈናቀል አድርገዋል፡፡
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎትም ተጠርጣሪዎች አቃቤ ህግ የመሰረተባቸውን ክስ በእጃቸው አንዲደርሳቸው መደረጉም ተጠቁሟል። ፍርድ ቤቱም ተከሳሾቹ በጉዳዩ ላይ ከጠበቆቻቸው ጋር ተነጋግረው መልስ ይዘው እንዲቀርቡ ጥር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ተጠርጣሪዎቹም አዲስ አበባ በሚገኘው ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የደህንነት ችግር እንዳይገጥማቸው ለፍርድ ቤቱ ያመለከቱ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም ወደፊት ከጠበቆቻቸው ጋር በመነጋገር በሚቀርቡ አቤቱታዎች ተመስርቶ ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት ሶማሌ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ጥቃቶች በመንግሥት አመራር አካላት ትዕዛዝና እውቅና ይፈፀሙ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል። መረጃው የፍደራሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ነው።