የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ቤቶችን የማፍረስ ዕርምጃና የተፈናቃዮች ጩኸት

ሻሂዳ ሁሴን

በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ከማስተር ፕላን ውጪ ተገንብተዋል የተባሉ ከ12,000 በላይ ቤቶች እንዲፈርሱ መወሰኑና ቤቶቹም መፍረስ መጀመራቸው ውዝግብ አስነስቷል፡፡ እስካሁን በከተማው በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ማለትም ቀበሌ 03 የካ ዳሌና ቀበሌ 01 አባ ኪሮስ በመባል በሚታወቁ ሥፍራዎች ከ930 በላይ የሚሆኑ ቤቶች መፍረሳቸው ተነግሯል፡፡ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የተሰጣቸው የማስጠንቀቂያ ጊዜ አጭር መሆኑን፣ እየፈረሱ ያሉትም የተመረጡ ቤቶች ናቸው ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ ካርታ ለማግኘት ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ቤቶች እየፈረሱ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ገልጸዋል፡፡ ድርጊቱንም የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ እንዲያስቆሙ ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው፣ ሕገወጥ ግንባታዎችን የማፍረስ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

Legetafo_social crises 2019 በገለጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር እንዲፈርሱ ከተወሰነባቸው ከ12,300 በላይ ቤቶች ውስጥ አንዱ

ሪፖርተር በሥፍራው ተገኝቶ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ሜዳ ላይ መበተናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ በቀበሌ 03 የመፍረስ ዕጣ ከገጠማቸው ቤቶች የአንዱ ይህንን ይመስላል፡፡

ሦስት ክፍሎች ያለው ቤት ግድግዳው በከፊል ፈርሷል፡፡ ጣራውም ሙሉ ለሙሉ ተነስቷል፡፡ በርና መስኮትም የለውም፡፡ ሊወድቅ ቋፍ ላይ የደረሰውን የጭቃ ግድግዳ ተደግፎ ከቆመው መሰላል ውጪ ምንም አይታይም፡፡ ከወንዝ ዳርቻ የተሠራው ቤት ወደ ፍርስራሽነት የተቀየረው ዕድሜ ተጭኖት ወይም የቦምብ ፍንጣሪ መትቶት አይደለም፡፡ ሕገወጥ ግንባታ ነው ተብሎ በአፍራሽ ግብረ ኃይል በትዕዛዝ የፈረሰው ረቡዕ ረፋዱ ላይ ነበር፡፡

‹‹ጠላ ሸጬ ነው ቤቱን የሠራሁት፤›› የሚሉት ወይዘሮ ግን ቤቱ ከፈረሰ ሰዓታት ያለፉት ቢሆንም አልተፅናኑም፣ ከድንጋጤያቸውም አልተላቀቁም፡፡ ‹‹ሕገወጥ›› የተባለው ቤታቸው እንደሚፈርስና ንብረታቸውን እንዲያወጡ የሚገልጽ ደብዳቤ የደረሳቸው ቅዳሜ የካቲት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሰዓቱ ደብዳቤውን የተቀበለችው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የምትማር ልጃቸው በድንጋጤ መታመሟን፣ እስካሁንም እንዳልተሻላትና ወደ ትምህርት ገበታዋ እንዳልተመለሰች ሲናገሩ እያነቡ ነው፡፡ ‹‹ለነገሩ ደንዳና ነኝ፤›› የሚሉት ወይዘሮዋ ቢሆኑም፣ አፍራሽ ግብረ ኃይሉ ግድግዳውን በላያቸው መናድ ሲጀምር ራሳቸውን ስተው እንደ ነበር ይናገራሉ፡፡ መናገርና መስማት አትችልም የሚሏት ትንሽ ልጃቸው ቤታቸውን እያፈረሱ የነበሩትን ሰዎች ልብስ እየጎተተች ስትለምናቸው እንደበር የሰሙትም፣ ከወደቁበት ሲነሱ ሰዎች ነግረዋቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹ቤቱን ለቃችሁ ውጡ› የሚለው ደብዳቤ ሲደርሳቸው፣ ‹‹እውነት አልመሰለኝም ነበር፤›› ብለዋል፡፡ የተሰጣቸው የአራት ቀናት ቀነ ቀጠሮም አጭር ነበርና መፍትሔ ለማፈላለግም ሆነ ንብረታቸውን ለማውጣት በቂ ስላልነበረ፣ ከማስፈራሪያነት ያለፈ ሚና ይኖረዋል ብለው እንዳላሰቡ ተናግረዋል፡፡ ረቡዕ የካቲት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ረፋዱ ላይ አፍራሽ ግብረ ኃይሉ ግድግዳቸውን መናድ ሲጀምር ግን እያነቡ ከመለመን ባለፈ ንብረታቸውን ለማውጣት እንኳን ፋታ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

“ነገሮች ከአዕምሮዬ በላይ ራሴን ስቼ ወደቅኩ፤” ብለው፣ ወደ ራሳቸው ሲመለሱ ጠላ ሸጠው የገነቡት ቤት ወደ ፍርስራሽነት ተቀይሮ እንዳገኙት ተናግረዋል፡፡ የቀረላቸው ነገር ቢኖር በቆርቆሮ በር የሚዘጋው ትንሹ ኩሽናቸው ነው፡፡ በማንኛውም ሰዓት ሊያፈርሱት ይችላሉ ብለው በሚሠጉበት ኩሽናቸው ውስጥ አዳራቸውን ማድረጋቸውን፣ ከፍርስራሹ ውስጥ የወጣ ንብረታቸውን ደግሞ ቤታቸው እንደሚፈርስ ቀነ ቀጠሮ በተሰጣቸው ጎረቤቶቻቸው ቤት በታትነው ማስቀመጣቸውን አስረድተዋል፡፡

ባለትዳርና የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮዋ ያለ ወትሯቸው ሜዳ ለሜዳ ይዞራሉ፡፡ አፉን ከፍቶ የቀረ ቤታቸው የሚያርፉበት ባይሆንም ቤት እንዳለው ሰው ወደ ፍርስራሹ ያመራሉ፡፡ ‹‹ከእነ ልጆቼ ሜዳ ላይ ቀርቻለሁ፤›› አሉ ትንሽ ልጃቸውን አዝለው ወደ ተቆለለው ፍርስራሽ ላይ እየወጡ፡፡ በመንደሩ ተመሳሳይ ችግር የደረሰባቸው ብዙዎች ስለሆኑ እየዞሩ ሌሎችንም ያፅናናሉ፡፡

እንደ ወይዘሮዋ ሁሉ መውደቂያ ባያጡም ጎረቤታቸው ወ/ሮ መቅደስ ተሰማ ግን እውነታውን መቀበል ተስኗቸዋል፡፡ ‹‹ሊፈርስ ነው የሚባል ነገር ከሰማሁ ቀን ጀምሮ እንዳለቀስኩ ነው፡፡ ደብዳቤው ቅዳሜ ዕለት በእጃችን ሲገባ ያልሄድንበት ቦታ የለም፡፡ ነገር ግን ማንም የደረሰልን አካል የለም፡፡ የቀን ጨለማ ነው የሆነብን፡፡ ይኼንን ቤት ለመሥራት የለፋሁትን እኔ ነኝ የማውቀው፤›› አሉ ወደ ተከመረው ፍርስራሽ በእጃቸው እያመለከቱ፡፡

በአካባቢው ይኖሩ ከነበሩ ከአንድ ግለሰብ የገዙትን ቤት አድሰውና ባለው ትርፍ ቦታም ቤት ገንብተው ኑሮ ለመጀመር ነገሮች ቀላል አልነበሩም ይላሉ፡፡ በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥረው እንደሚሠሩና በወር የሚያገኙትም 3,000 ብር እንደማይሞላ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ያለው ሰው እኮ እዚህ አይኖርም፡፡ አማራጭ የሌለን ድሆች ነን እዚህ ገዝተን የምንገባው፤›› በማለት ዕንባቸውን አዘሩ፡፡

የፈረሰባቸውን መኖሪያ ቤት ለመሥራት ለዓመታት እንደተቸገሩ ይናገራሉ፡፡ ቆርቆሮ ለመምታት፣ ግድግዳ ለማቆም በወር ከሚያገኙት ላይ እየቆጠቡ ዕቁብ መጣል እንደነበረባቸው ያስታውሳሉ፡፡ የዋናው ቤት ግንባታው ባያልቅም ቀስ በቀስ ያልቃል በማለት ከአራት ዓመታት በፊት ገብተው መኖር እንደጀመሩም ያስረዳሉ፡፡ በአንዱ ዕቁብ በር፣ በሌላው ኮርኒስ እያሠሩ መደበኛ ቤት ለመሆን አንድ መስኮትና የፍሳሽ ማስወገጃ ሲቀረው፣ ሕገወጥ ግንባታ ተብሎ ረቡዕ ዕለት መፍረሱን ተናግረዋል፡፡ የቀራቸው ለተከራይ የሰጡት ሰርቪስ ቤት ቢሆንም፣ የቱ እንደሚፈርስና የቱ እንደሚቀር ስለማይታወቅ መጨረሻቸውን አላወቁም፡፡ “የዋናውን ቤት የተወሰነ ክፍል አፍርሰው ይኼ ቀርቶልሻል እጠሪው ካሉ በኋላ ነው ተመልሰው የቀረውን ሆ ብለው ያፈረሱት፡፡ አሁን ጭንቀት ሊገድለኝ ነው፡፡ የማይወለድ ልጅ ማማጥ ሆኖብኛል፤” አሉ እንደገና እያነቡ፡፡

አራት ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት እንዳለባቸው፣ ከዘራቸውን ተደግፈው የሚቆዝሙ ወላጅ አባታቸውን የማስተዳደር ኃላፊነትም የእሳቸው መሆኑን መኖሪያ ቤታቸው በላያቸው የፈረሰባቸው ወ/ሮ መቅደስ ይናገራሉ፡፡ አንገት ማስገቢያ ጎጆ ለመቀለስ ባወጡት ወጪና ልፋት ውጤቱን ሳያዩ ስለፈረሰባቸው ሐዘን እንደሰበራቸው አክለዋል፡፡ ቤቱን ለመሥራት ከፍለው ያልጨረሱት የዕቁብ ዕዳም ዕረፍት ነስቷቸዋል፡፡ በሁኔታው ተስፋ ቆርጠው አፍራሾቹን ቆመው ሲመለከቱ እንደነበር፣ ንብረታቸውን ያወጡላቸውም ዕድርተኞቻቸው እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ አለኝ የሚሏቸው የቤት ዕቃዎች ወደ አንድ ጎን ተከምረው አቧራ ይጠጣሉ፡፡ 276 የሚል የቤት ቁጥር የሠፈረበትን ቆርቆሮ የያዘ የብረት በር ከአንዱ ጥግ ተሸጉጧል፡፡ ወይዘሮ መቅደስ የቤት ቁጥር ከተሰጣቸው ዓመታት እንደተቆጠሩ ይናገራሉ፡፡

በራፋቸው ላይ ከተተከለው የኤሌክትሪክ ፖልም የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኛሉ፡፡ ከዓመታት በፊት አንድ ክፍል ቤት ያለውን ግቢ የገዙት በግል ውል ነበር ይላሉ፡፡ ‹‹ማዘጋጃ ቤት በሊዝ ለባለሀብት ይሸጣል እንጂ ለምን ለእኔ ይሸጥልኛል? ባለሀብት ደግሞ እንዲህ ዓይነት ቦታ ላይ ምን ይሠራል?›› ሲሉ ለኑሮ የማይመቹ ቦታዎች ላይ ተገፍቶ የሚወጣው አማራጭ ያጣ እንደ እሳቸው ያለ ደሃ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ቦታው ላይ ሲኖሩ ካርታ ባያገኙም ሕጋዊ መሆናቸውን የሚያመላክቱ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ እንደነበሩ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የአከራይ ተከራይ ግብር ለመክፈል የሚመለከተው አካል ከቀናት በፊት አነጋግሮን ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይኼንን እየተነጋገርን ባለንበት ሰዓት ደብዳቤው እንደ ዱብ ዕዳ ዓርብ ወጪ ተደርጎ ቅዳሜ እጃችን ላይ ገባ፡፡ በአራት ቀናት ውስጥ ምን ማድረግ እንችላለን?›› ብለው ሌላው ቢቀር እንዲወጡ የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ነገሮችን ያላገናዘበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቀረልኝ የሚሉት ተከራዮች ይኖሩበት የነበረው ቤትም እንደማይፈርስ ማረጋገጫ የለም ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ከቀናት በፊት በእጃቸው የገባው በኦሮሚፋ የተጻፈው ደብዳቤ የቱ እንደሚፈርስና የቱ እንደሚቀርላቸው አይገልጽም፡፡

አካባቢውን በአንድ ጊዜ ወደ ፍርስራሽነት የቀየረው ዘመቻ በርካቶችን ሐዘን ላይ ጥሏል፡፡ ለገጣፎ የሚገኘው የካ ዳሌ 03 ቀበሌ ልጅ አዋቂ ሳይል ሁሉም በአንድነት የሚያነባበት መንደር ሆኖ ነበር ያረፈደው፡፡ እንደ ነገሩ ተበታትነው ከሚታዩ የቤት ዕቃዎች፣ የቆርቆሮና የፍርስራሽ ክምር ባሻገር የሚገቡበትን ያጡ በትካዜ የተዋጡ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ማረፊያ እንዳጡ ሁሉ በየመንገዱና በየጥጋጥጉ እንደቆሙ ይተክዛሉ፡፡ የደረሰባቸውን የሰሙ ዘመድ አዝማዶች ከያሉበት እየሄዱ እከሌን ዓይታችኋል እያሉ የዘመዶቻቸውን አድራሻ ሲፈልጉ ታይተዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ‹ቤት ለእምቦሳ› ብለው የመረቁላቸው ቤቶች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋልና ሜዳ ላይ ቆመው ያወራሉ፡፡ ምርር ብለው የሚያለቅሱ ዘመዶቻቸውን ያፅናናሉ፡፡ ሰብሰብ ሲሉ ‹የአንተም ቤት ፈረሰ?› እየተባባሉ የቁም ቅዠት የሆነባቸው ክስተት በሌላው ላይ ደርሶ እንደሆነ ይጠያየቃሉ፡፡ ‹የእኔ ቤት እዚያ ጋ ነበር› እያሉ ነው የፈረሰባቸውን ለሰዎች የሚያሳዩት፡፡ የፈረሰባቸውን ሲያፅናኑ የቆዩ ደግሞ ተራው የእነሱ ሆኖ ቤታቸው ሲፈርስ እያዩ እንደ አዲስ ይደነግጣሉ፣ ያለቅሳሉ፡፡

“100 የሚደርሱ ሰዎች ሆ ብለው መጥተው አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ብለው ግድግዳ ገፍተው ሲንዱ ማየት ግራ ያጋባል፡፡ ከማልቀስ ውጪ ምንም ማድረግ አይቻልም፤” ይላሉ ወይዘሮ መቅደስ፡፡ የሚፈርሰውን ቤት መታደግ ባይቻልም ጥረው ግረው ያፈሩት ንብረት በፍርስራሽ እንዳይዋጥ ጎረቤት ተሯሩጦ ለማትረፍ ይረባረባል፡፡

ቄስ ኪሮስ ዓለምነህን ሪፖርተር ያገኛቸው ከፈረሰው ቤታቸው ውስጥ የወጣ ንብረታቸውን በጎረቤቶቻቸው ዕገዛ ወደ አንድ በኩል ሲቆልሉ ነበር፡፡ ቄሱ በሆነው ነገር ከመደንገጣቸው የተነሳ ግራ መጋባት ይታይባቸዋል፡፡ ጎረቤቶቻቸው ግቢያቸውን ሞልተው የተበተነውን ንብረታቸው ዝናብ እንዳይመታው ቆርቆሮ ይመቱላቸዋል፡፡

እናቶች በየጥጋጥጉ እንደተቀመጡ ያለቅሳሉ፡፡ ከአርሶ አደር ላይ በ250 ሺሕ ብር የገዙትን ቤት አፍርሰው በሚፈልጉት ዲዛይን ለማሠራት ብዙ ገንዘብ ማፍሰሳቸውን፣ ቤቱን የሠሩትም በ2003 ዓ.ም. እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ቦታውን ገዝቶ ቤት ለመሥራት ከዘመድ አዝማድ ብዙ ገንዘብ መበደራቸውንና እስካሁንም ያልተከፈለ 80 ሺሕ ብር የሚሆን ውዝፍ ዕዳ እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡

ቄስ ኪሮስ በአካባቢው ሕጋዊ ነዋሪ መሆናቸውን የሚያሳይ የቀበሌ መታወቂያ አላቸው፡፡ ለመንገድ፣ ለውኃና ለኤሌክትሪክ የከፈሉበት ደረሰኝም አላቸው፡፡ በሌሎች ማኅበራዊ ግዴታዎች ክፍያ የፈጸሙባቸው ሕጋዊ ደረሰኞች ይዘዋል፡፡ የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ውልም በእጃቸው ይዘዋል፡፡

‹‹ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ዕዳ ላይ ነው ያለሁት፡፡ ቤቱን ለመገንባት ከ500 ሺሕ ብር ከላይ አውጥቻለሁ፤›› በማለት፣ ዕዳቸውን ከፍለው በወጉ መኖር ሳይችሉ የቤታቸው መፍረስ የተደበላለቀ ስሜት እንዳሳደረባቸው ይናገራሉ፡፡ ቤቱን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ የሚያሳስበው ደብዳቤ የተጻፈውና እጃቸው ላይ የደረሰው በአጭር ጊዜ ነው በማለት፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ጊዜው እጅግ አጭር እንደሆነና ነገሩን ለመረዳትም ፋታ ሳይሰጣቸው ሕይወታቸው እንዳልነበረ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ሌላው ቢቀር ቀልባቸውን ሰብስበው ንብረታቸውን በመልክ መልኩ ለማሰናዳት እንኳ አልሆነላቸውም፡፡ ሕጋዊ ነዋሪ መሆናቸውን የሚመሰክሩ ሰነዶችን ቅጂ እንደያዙ ፍርስራሽ የዋጠው ቅጥር ግቢ ውስጥ ቆመዋል፡፡ ዕዳ ገብተው የሠሩት ቤት ፈራርሶ ማየታቸው በቤታቸው እንግድነት እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡

ከጎናቸው ሆኖ የሚያፅናናቸው የ29 ዓመቱ አቶ ቀናው በላይ ደግሞ 150 ካሬ ላይ ያረፈው ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ፈርሶበት ሜዳ ላይ መቅረቱን ይናገራል፡፡ ደሳሳ ቤት የነበረውን ቦታ በ2004 ዓ.ም. ገዝቶ ከ300 ሺሕ ብር በላይ አውጥቶ የብሎኬት ቤት እንደሠራ፣ ባለትዳርና የልጅ አባት መሆኑን፣ በቴክኒክና ሙያ ከሰባት ዓመታት በፊት በዲፕሎማ ቢመረቅም፣ በተማረበት ሙያ ሥራ ማግኘት አለመቻሉን ያስረዳል፡፡

ቤተሰቡን የሚያስተዳድረውም ፑል ቤት ተቀጥሮ እየሠራ በሚከፈለው 1,500 ብር ቢሆንም፣ የራሱ የሚለው ቤት ስለነበረው ግን ብዙም እንደማይቸግረው፣ ዓለም የተደፋበት የመሰለው ሕገወጥ ነህ ተብሎ ቤቱ ሲፈርስበት መሆኑን ገልጿል፡፡ ‹‹ቤቴ የፈረሰው ማክሰኞ ነው፡፡ ‹‹አሁን ያለሁት አንድ ወዳጄ ዘንድ ተጠግቼ ነው፡፡ መንግሥት አካባቢውን ለማልማት ፈልጎ ከሆነ ደስ ይለናል፣ ግን እኛ የት ሄደን እንውደቅ?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ ‹‹ከአሁን በኋላ የሚጠብቀኝ የጎዳና ሕይወት ነው፡፡ ሚስቴንም ወደ ቤተሰቦቿ እልካለሁ፡፡ ከቻሉ ሁላችንንም ወደ ትውልድ ቀዬአችን የምንመለስበትን ገንዘብ ይስጡን፤›› ይላል፡፡

ቴሌቪዥን፣ ፍሪጅ፣ ቁም ሳጥን ሳይወጣ የፈረሰባቸው፣ ፅዋ እንኳ ሳይወጣ በላያቸው የፈረሰባቸው፣ እንዲሁም ሁኔታው በፈጠረባቸው ድንጋጤ ከታመሙና ራሳቸውን ስተው ከወደቁ ባሻገር የከፋ ነገር የገጠማቸውም መኖራቸው ይሰማል፡፡

ጎረቤቶቿ ዓረብ አገር ሠርታ ባጠራቀመችው ገንዘብ ከጎናቸው ቤት ገዝታ እንደምትኖር፣ ቤቱ ላይዋ ሲፈርስ ግን ተስፋ ቆርጣ ራሷን ማጥፋቷንና አፍራሽ ግብረ ኃይሉ በአምቡላንስ እንደወሰዳት የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ አስከሬኗ የትና በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳለም አይታወቅም ብለዋል፡፡ ዘመድ ይኑራት፣ አይኑራት የደረሰባትን ይስሙ፣ አይስሙ የሚያውቅ የለም ብለው ወደ ፍርስራሽነት የተቀየረው ቤቷና እሷ በአንድ አፍታ ታሪክ ሆነው መቅረታቸውን ይናገራሉ፡፡

ዱብ ዕዳ የሆነ ክስተት እንደ አቶ ጌታቸው ህያሴ ያሉ በአካባቢው ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች እንኳ አላለፈም፡፡ አቶ ጌታቸው ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በአካባቢው እንደሚኖሩ ይናገራሉ፡፡፡ ዓምና ደግሞ የቀበሌውን ሊቀመንበር አስፈቅደው በዘመናዊ መንገድ ከብቶች ማርባት ጀምረዋል፡፡ በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር የካ ዳሌ 03 ቀበሌ አሉ የተባሉና ጠንካራ የልማት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ ‹‹ይኼ ሁሉ ነገር ሲሠራ አብረውን ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ያውቃሉ፡፡ ገና ሲጀመር ማስቆም ይችሉ ነበር፤›› ይላሉ፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ከብቶቹን ለማርባት ከ500 ሺሕ ብር በላይ ወጪ አድርገው ወደ ሥራ ሲገቡ የከለከላቸው አልነበረም፡፡ በዘመናዊ መንገድ የገነቡት የከብቶች በረት እንዲፈርስ ሲደረግ ግን ብዙ ነገር ማጣታቸውን ይናገራሉ፡፡

አቶ ጌታቸው የአካባቢው ወጣቶች የልማት ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ ነዋሪዎች ገንዘብ እያዋጡ መንገድና የተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮች እንዲሟሉ እያስተባበሩ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሠሩ መቆየታቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ነዋሪዎች ለተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች አሥር፣ አሥር ሺሕ ብር እንዲከፍሉ ተደርጎ አካባቢው መልማቱን፣ ቤታቸው ሕገወጥ ተብሎ ከፈረሰባቸው ነዋሪዎች መካከል ሪፖርተር ያነጋገራቸው አብዛኞቹ ገንዘብ አዋጥተው አካባቢውን ማልማታቸው ይነገራል፡፡ ‹‹ኮሚቴአችን በልማት አንደኛ ተብሎ የተሰጠን የምስክር ወረቀት ቤት አለኝ፤›› የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ከማዘጋጃ ቤቱ ጋር ተባብረው አካባቢውን ሲያለሙ የነበሩ ነዋሪዎች ሳይቀሩ ሕገወጥ መባላቸው ግር አሰኝቶኛል፤›› ይላሉ፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች ይህንን ያህል ገንዘብ አውጥተው ቤት ሲገነቡና አካባቢውን ሲያለሙ ዝም ተብሎ አሁን እንዲፈርስ መደረጉ ብዙዎችን አስቆጥቷል፡፡ ግንባታውን ከጅምሩ ማስቆም ሲቻል ገንዘብ እየተቀበሉ ፈቃድ የሚሰጡ የአመራር አካላት መኖር፣ ሌሎችም እንዲገነቡ ያደፋፍር እንደነበር ነዋሪዎቹ እየተናገሩ ነው፡፡ አብዛኞቹ ቤቶች ሲገነቡ አሥር ሺሕ ብርና ከዚያ በላይ ለቀበሌው አስተዳደር አካላት ይከፈል ነበር ተብሏል፡፡

ሕጋዊ ነዋሪ እንደሆኑ የሚያሳይ የቤት ቁጥር፣ የነዋሪነት መታወቂያ፣ የኤሌክትሪክና የውኃ አገልግሎት ካገኙ በኋላ ሕገወጥ ተብለው መፈናቀላቸው ሌላ አስተዳደራዊ ችግር ቢኖር ነው ያሉም አሉ፡፡፡ በቀናት ውስጥ ቤታቸውን እንዲለቁ የሚያዘው ደብዳቤ እንደደረሳቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በኩል ድምፃቸውን ያሰሙም፣ ‹ማስፈራሪያ እየደረሰን ነው፡፡ የምንንቀሳቀሰውም ተደብቀን ነው፡፡ አብረውን ችግሩን በተመለከተ በሚዲያ የተናገሩ ሁለት ሰዎችም ተይዘዋል› ብለዋል፡፡ ቤቶቹን ሲያፈርሱም ‹እስቲ ሚዲያዎች ይድረሱላችሁ፣ እናያለን› መባላቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ቤቶቹን ሲያፈርሱ ከነበሩት መካከል በሦስቱ ላይ ግድግዳ ተደርምሶ ጉዳት እንደ ደረሰባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ አንደኛው ተጎጂ ሕይወቱ ወዲያው እንዳለፈ ቢናገሩም፣ የከተማው የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ የሞተ እንደሌለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ቤቶቹን የማፍረስ ኃላፊነት የተሰጠው በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ከንቲባ የሚመራው ገብረ ኃይል፣ አስለቃሽ ጭስና መሣሪያ በታጠቁ የፀጥታ አካላት ታጅቦ እንደነበር ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ ሐቢባ ሲራጅ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ፣ ቤቶቹ እንዲፈርሱ የተወሰነው ከተማዋን በማስተር ፕላን የምትመራ ለማድረግ፣ እንዲሁም ምቹና ፅዱ ቦታ ለመፍጠር ነው ብለዋል፡፡ ይፈርሳሉ የተባሉ ከ12,000 በላይ የሚሆኑ ቤቶችም የከተማውን ማስተር ፕላን በመጣስ፣ ለአረንጓዴ ልማት የተተውና የተከለከሉ የወንዞች ዳርቻዎች ላይ የተገነቡ በመሆናቸውም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በሕግ ከተፈቀደላቸው ቦታ ውጪ ተጨማሪ ቦታ አጥረው የያዙ ባለሀብቶችም የዚሁ አካል ናቸው ብለዋል፡፡

ዓርብ የካቲት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬታሪ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ኦዴፓ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የገጠርና ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋና ሌሎች የክልሉ ሹማምንት በለገጣፎና አካባቢው ጉብኝት አድርገው ነበሩ፡፡ ከንቲባዋ ወ/ሮ ሐቢባ በሰጡት ገለጻ መሠረት፣ ከ12,300 በላይ ካርታ የሌላቸው ቤቶች በከተማዋ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየፈረሱ ያሉ ቤቶች በመንግሥት ይዞታ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸው፣ የማፍረስ ዕርምጃ ከመወሰዱ ሁለት ወራት በፊት ደብዳቤ ለባለ ይዞታዎቹ ደርሷል ብለዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ከመመሥረቱ ሦስት ዓመት በፊት ግብር የከፈሉበት ደረሰኝ ማቅረብ አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ውኃና መብራት ማስገባት ዋስትና አይሆንም፤›› ያሉት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማው የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ነፃነት ከበደ በበኩላቸው፣ ቤቶቹን የማፍረስ ዘመቻው በማስተር ፕላኑ መሠረት ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ግንባታ የተከናወነባቸው አንዳንዶቹ ቦታዎች መንግሥት ለልማት የሚፈልጋቸውና ካሳ የከፈለባቸው እንደሆኑም አስረድተዋል፡፡ ከአርሶ አደሩ እየገዙ የሠፈሩም አሉ ብለዋል፡፡ አለ ለሚባለው ችግር ተጠያቂው ከዚህ በፊት የነበረው የአስተዳደር አካል እንደሆነ፣ ከእነዚህም ውስጥ በሕግ እየተጠየቁ ያሉ ሰዎች መኖራቸውንና አሁንም ተጠያቂ የሚደረጉ ሌሎች መኖራቸውን፣ ከአርሶ አደሮችም የሚጠየቁ እንደሚኖሩ አስረድተዋል፡፡

ቤት የፈረሰባቸው ነዋሪዎችን የፌዴራል ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባለሙያዎች ዓርብ የካቲት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በቦታው ተገኝተው እንዳነጋገሯቸው ታውቋል፡፡ ዘገባው የሪፖርተር ነው።

Leave a comment