በጌዲዖ ማኀበረሰብ ላይ የተፈፀመው የዘረኝነት ጥቃት እና ፖለቲካዊ የርሃብ ቅጣት

ብስራት ወልደሚካኤል

በዶ/ር አብይ አህመድ እና አቶ ለማ መገርሳ የሥልጣን ዘመን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የዘረኝነት ጥቃት ሰለባ ከደረሰባቸው ወገኖች መካከል የጌዲዖ ማኀበረሰብ ላይ የደረሰው ከፍተኛው ነው። ነገር ግን በተፈናቃይ የጌዲዖ ማኀበረሰብ ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶችና በደሎች አቶ ለማ መገርሳም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብይ አህመድ ጠንቅንቀው ያውቃሉ። ባለፈው ክረምት የተፈፀመው በደል በኦነግ እንደሆነ ብዙ ሸፋፍኖ ለማለፍ ተሞክሮ ነበር። ግን አልነበረም። መጀመሪያ ላይ የተፈፀመው ማፈናቀልና አካላዊ ጥቃት በምሥራቅ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ባሉ የኦህዴድ/ኦዴፓ ከፍተኛ እና የወረዳ አመራሮች ራሳቸውን “ቄሮ” ብለው የሚጠሩ ወጣቶችን በማስተባበር ጭምር እንደተሳተፉ የጥቃቱ ሰለባዎችና ድርጊቱን የተቃወሙ የጉጂ ዞን ሌሎቹ አመራሮች አጋልጠው ከኦሮሚያ ክልል ሪፖርት አድርገው ነበር። ይሄንንም የክልሉ ፕሬዘዳንት አቶ ለማ መገርሳ እና ምክትላቸው ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን ያውቃሉ። ለዚህም ነው አቶ ለማ መገርሳ ተፈናቃዮቹ ያሉበት ጉጂ ዞን በአካል ሄዶ የጎበኘውና ድርጊቱን ኮንኖ ሀዘኑን የገለፀው። ይህም ብቻ አይደለም በድርጊቱ የተሳተፉና መረጃ የተገኘባቸው ናቸው ያየተባሉት ላይ ወዲያውኑ ከሥራ ማገድ እስከ እስር ርምጃ መውሰዳቸውን ያሳወቁት። በወቅቱ የነበረውን የዘረኝነት ቅስቀሳና ማፈናቀሉን የተቃወሙ አመራሮችና የሀገር ሽማግሌዎች ቢኖሩም አደጋውን ከመቀነስ ባለፈ ማስቆም አልቻሉም ነበር። ምክንያቱም ጥቃቱ በመሳሪያ የታገዘ ስለነበር። ድርጊቱ ከዚህ ቀደም ሱማሌ ክልልና ወሰን አካባቢ በአብዲ ኢሌ እና አጋዦቹ በምስኪኑ ኦሮሞ ላይ ከተፈፀመው ጋር ተመሳሳይ ነው። ያንን አውግዘን እና ኮንነን ይሄን መሸፋፈን አይቻልም። ወንጀል የትም በማንም ላይ ይፈፀም ያው ወንጀል ነው።

ድርጊቱ የተፈፀመው በፖለቲካ መሪዎችና የፀጥታ ኃይሉ እንጂ በህዝቡ አለነበረም። ታዲያ በአብዲ ኢሌ የተፈፀመውን ኮንነን እና አውግዘን ስናብቃ ምስኪኑ የጌዲዖ ማኅበረሰብ መፈናቀልን እና የፖለቲካዊ የርሃብ ጥቃት መሸፋፈን ለምን አስፈለገ? የጌዲዖ መፈናል እና ሰብዓዊ ርዳታ ልክ ኦሮሞ በክፉ ሥራው የተጋለጠ ለማስምሰል ሌላ ጥፋት ነው። አንድም የግለሰቦችን ወንጀል ለምስኪኑ ኦሮሞ ማላከክ አሊያም ኦሮሞ ላይ የተፈፀመ ስም ማጥፋት አስመስሎ ማስፈራራት እና ወንጀሉን ለመሸፋፈን የመሞከር ወንጀል። ይሄ ጊዜ ያለፈበት ነው። ልክ የሶማሌ ማኅበረሰብ ኦሮሞ ከአስተዳደር ክልላቸው የኦሮሞ ማኅበረስብ እንዲፈናቀል ለእነ አብዲ ኢሌ ትዕዛዝ እና ድጋፍ እንዳላደረገ ሁሉ በምስኪን የጌዲዖ ማኅበረሰብ ከጉጂ ዞኖች መፈናቀል የኦሮሞ ማኅበረስብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ድጋፍ አድርጓል ብሎ የሚያምን የለም። የአካባቢው የኦህዴድ/ኦዴፓ ፅንፈኞችና ዘረኛ አመራሮች ግን አድርገውታል። ይሄን መካድ አይቻልም። ለዚህም በሁለት ዙር በግፍ የተፈናቀሉ የጌዲዖ ማኀበረሰብን ሰቆቃ በአካል ሄዶ ማየት በቂ ነው። ይሄ ደግሞ ከህግም፥ ከሞራልም ሆነ ከሰብዓዊነት አንፃር መጋለጥና መወገዝ ያለበት ወንጀል ነው። ያውም “ብሔር” ተኮር የዘረኝነት ጥቃት። ያኔ በህወሓት እና አብዲ ኢሌ ፖለቲካዊ ወንጀል የኦሮሞ ማኅበረሰብ ከሶማሌ ክልል በግፍ ሲፈነቀል ከሀገሩ ሊፍናቀል አይገባም ብለን በጋራ እንደተቃወምነው ሁሉ የጌዲዖ ማኀበረሰብ በግፍ መፈናቀልንም ልናወግዝ ይገባል እንጂ ጉዳዩ ተጋለጠ ብሎ በርሃብና ሞት እንዲቀጡ መሸፋፈን ትክክል አይደለም። ይሄ ጭካኔ የተሞላበት ኢ- ሰብዓዊነት ነው።
Gedeo crises
ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በማንነታቸው የተፈናቀሉ የጌዲዮ ማኅበረሰብ በከፊል (ፎቶ፡ የጌዲዮ ዞን ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት)
በተለይ አቶ ለማ መገርሳ ከፌደራል የደኢህዴን አመራሮች መካከል ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እና ከደቡብ ክልል ደግሞ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ እንዲሁም በችግሩ ቅርበት ያለው የጌዲዖ ዞን አመራሮች የጥቃቱ ሰለባዎች የሚገኙበት ጊዜያዊ መጠለያ ቦታ ድረስ በመሄድ አረጋግጠው፤ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲፈታ፥ የተፈፀመባቸው ጥቃትም ወደ አደባባይ እንዳይወጣ ብዙ ሞክረው ነበር። ጉዳዩን አለዝቦ “በጉጂ ኦሮሞ እና በጌዲዖ ማኀበረሰብ ተከስቶ የነበረው ግጭት በሀገር ሽማግሌዎች ርቀሰላም ተፈቷል” በሚል ለዘብ ያለ የዜና ሽፋን ሁሉ ተሰጥቶት ነበር። ያውም ከቪዲዮ ምስል ጋ ተያይዞ። እንደ ጥቃቱ ሰለባዎች ገለፃ ከሆነ ግጭቱ የተቀሰቀስውም ሆነ የተቀነባበረው በጉጂ ኦሮሞ ማኀበረሰብና ብጌዲዖ ማኀበረብ መካከል ሳይሆን በምሥራቅና ምዕራብ ጉጂ ዞን በሥልጣን ላይ ባሉ አካላትና የ“ብሔር” እና ጥላቻ ቅስቀሳ ሲያደርጉ በነበሩና ራሳቸውን “ቄሮ” ብለው በሚጠሩ ወጣቶች እና የማኀበራዊ ሚዲያ “አክቲቪስቶች” ነበር። በተለይ ከአካባቢው ጋር በተያያዘ በማኀበራዊ ሚዲያ ጭምር በኦሮሚኛ “ብሔር” ተኮር የዘረኝነት ጥላቻ ቅስቅሰሳ ይደርግ ሁሉ እንደነበር አስታውሰዋል።

በወቅቱ የጌዲዖ ማኅበረሰብ አባላት የደረሰባቸው የዘረኝነት ጥቃት መካከል፡-

1ኛ. በርካቶች ቤቶቻቸው እየተመረጠ ተቃጥሎባችዋል።
2ኛ. የእርሻ ማሳ ላይ ያለ ቡና እና ሰብሎችን ጨምሮ ንብረቶቻቸው ተዘርፈዋል፥ መሬቶቻቸውም በአካባቢው ባለሥልጣናትና ራሳቸውን “ቄሮ” ብለው በሚጠሩ ወጣቶች የተነጠቁም ይገኙበታል።
3ኛ. እናቶችን ጨምሮ ወጣት ሴቶች ተደፍረዋል።
4ኛ. በዚህ ወቅት ሊታሰብ የማይችል አሰቃቂ ግድያ ተፈፅሞባቸዋል። ከሞት የተረፉትም በዲላ እና ይርጋለም ሆስፒታሎች ሳይቀር ህክምና ርዳታ ያገኙ ነበሩ። በወቅቱም የኦሮሚያና የደቡብ ክልል ባለሥልጣናትም እንደተጎበኙ መረጃው አለ። ለውጡ እንዳይደናቀፍ በሚል ችላ ከተባለ በኋላ ዘግይቶ ጥቃቱ ግን በኦነግ ላይ ብቻ ተሳቦ ተሸፋፍኖ ታልፏል። ይሁን እንጂ የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የደቡብ ክልል ባለሥልጣናት እውነታውን በደንብ ያውቁት ነበር። ከዚያም አቶ ለማ መገርሳ በጥቃቱን የተሳተፉ የምስራቅና ምዕራብ ጉጂ ዞን አመራሮችን ከሥልጣን በማንሳት እንዲታሰሩና በህግ እንዲጠየቁ ማድረጋቸውን በአደባባይ በዕርቀ ሰላሙ ወቅት ተናግረው ነበር። ጥቃቱ የደረሰባቸው ምሥራቅና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ውስጥ በተጨማሪ አጎራባች የደቡብ ክልል ጌዲዖ ዞን ወረዳዎች የነበሩ ምስኪን ገበሬዎችም ጥቃት ደርሶባቸው ተፈናቅለዋል። በተለይ አጎራባች በጌዲዖ ዞን ትምህርት ቤቶች ሁሉ በጥቃቱ ወድመዋል። ከዛም በመንግሥት ግፊት፥ በሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ድርድር አማካኝነት ነሐሴ 30 ቀን 2010 ዓ. ም. ወደ 359 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ተደርጎም ነበር።

ነገር ግን የመንግሥትን እና የሀገር ሽማግሌዎችን ጥሪ ተቀብለው ወደ ቀዬያቸው ሲመለሱ የተዘረፉና ንብረቶቻቸውን እና የተወረሱ መሬቶቻቸውን ተከልክለው ድጋሚ ሌላ ጥቃት ደርሶባቸዋል። በዚህም ወደ 175 ሺህ ያህ የጌዲዖ ማኅበረሰብ አባላት በድጋሚ እንዲፈናቀሉ ተደርጓል። የሁለተኛው መፈናቀል ላይ ከኦህዴድ/ኦዴፓ የአካባቢው አመራሮች በተጨማሪ የኦነግ ታጣቂዎችም እንደተሳተፉ የተገለፀ ሲሆን፤ ድርጊቱን አውግዘው የተቃወሙ የጉጂ የሀገር ሽማግሌዎች በጥቃት አድራሽ የአካባቢው አመራሮች፥ ወጣቶችና ታጣቂዎች ማስፈራሪያና ዛቻ እንደደረሰባቸው ለኦሮሚያ ባለሥልጣናት ጭምር አሳውቀዋል። ይሄን በደል ያጋለጡ እና ለኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ሪፖርት ያደረጉ አካላት አሁንም አሉ። ይሁን እንጂ ተፈናቃዮቹ ከኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናትም ሆነ የሚመለከተው የፌደራል መንግሥት ተገቢውን የሰብዓዊ እና የህግ ከለላ ድጋፍ ካለማግኘታቸው በተጨማሪ ፥ የተዘረፉና የተወረሱባቸው ንብረቶች እና የእርሻ ማሳዎች ሳይመለሱ ለረጅም ጊዜ በታፈነ አነስተኛ ጊዜያዊ የሸራ መጠለያ እንዲቆዩ መደረጉንም ያስታውሳሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ያለሰብዓዊ ድጋፍ በመጠለያ እያሉ የህግ ከለላና ድጋፍ ባለማግኘታቸው በተወስኑ ተመላሾች ላይ በፅንፈኞቹ ተደጋጋሚ የዘረኝነት ጥቃት ሲደርስባቸው በድጋሚ ከጉጂ ዞን ጊዜያዊ መጠለያዎቻቸውም ተፈናቅለው ወደ ጌዲዖ ዞን በተለይም ገደብ፥ ይርጋጭፌ እና ወናጎ ባሉ ወረዳዎች ተሰደው በአብያተ ክርስቲያናት አዳራሽ መኝታ አልባ ወለል ላይ እንዲሁም በሸራ በተወጠረ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ተፋፍገው ይገኛሉ። ከርሃቡ በተጨማሪም ለተለያየ ተላላፊ በሽታም የተጋለጡ ይገኝበታል። በድጋሚ ከተሰደዱትና በከፍተኛ ደረጃ ለርሃብ ከተጋለጡት መካክለ ከ45 ሺህ በላይ የሚሆኑት በጌዲዖ ዞን ገደብ ወረዳ ባሉ ቤተክርስቲያኖችና ትምህርት ቤቶች የተጠለሉ ቢሆንም በድጋሚ ወደ ቀዬያችሁ ካልተመለሳችሁ በሚል በፌደራል፥ በደቡብ እና ኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት ግፊት ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደረግላቸው መደረጉን መረጃዎች ይፋ ከሆኑ ሁለተኛ ሳምንቱን ይዟል። በዚህም በአማካይ በቀን ከ2 እስከ 3 ሰዎች በርሃብ እየሞቱ እነደሆነ፥ ቀሪዎቹ ለከፍተኛ ርሃብ በመጋለጣቸው አስቸኳይ የምግብ፥ የጤና እና መሰል የሰብዓዊ ድጋፍ ካላገኙ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃይ የጌዲዖ ማኀበረሰብ አባላት ለሞት እንደሚጋለጡ የገደብ ወረዳ አመራሮች፥ የአካባቢው የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጉዳዩን አጋልጠዋል።
Gedeo
ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ጉጂ ዞን ከተፈናቀሉና የፖለቲካዊ ርሃብ ቅጣት ሰለባ ከሆኑ እናቶች መካከል አንዷ ናቸው።(ፎቶ፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ድርጊቱን ያጋለጡ የዲላ ዩኒቨርስቲ በጎ ፈቃደኞች እና ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የተወሰደ)

መረጃው የደረሳቸው የዲላ እና ይርጋጨፌ ከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም የተወሰኑ የዲላ ዩኒቨርስቲ ማኅበረሰብ አባላት ፈጥነው በመድረስ የተቻላቸውን ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ጉዳዩን ለቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲደርስና አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ከምስል ጋር ይፋ አድርገዋል። ይሁን እንጂ የደቡብ ክልል፥ የጌዲዖ ዞን፥ የኦሮሚያ ክልል እና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች በተለይም የሰላም ሚኒስቴር እና የፌደራል አደጋ መከላከል ዝግጁነት አመራሮች ጉዳዩን እያወቁ ለማስተባበል ሞከረው የነበረ ቢሆንም፤ በድጋሚ በቪዲዮ ማስረጃ ጭምር ከተጋለጠ በኋላ የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያ ካሚልና የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ልክ ጉዳዩን እንደማያውቅ በመምሰል ተፈናቃይ ተጎጂዎችን በአካል ጎብኝተዋል።

በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እና የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በከፍተኛ ርሃብ የተጋለጡ ከ45 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ያሉበትን ገደብ ወረዳ መካከል ኮቲት ቀበሌን ብቻ ጎብኝተው በመመለስ የገጎጂዎቹን ቁጥር 13 ሺህ ናቸው በሚል ዝቅ ለማድረግና አደጋውንም ለማሳነስ ሞክረዋል። ይሄ የቀዳማዊ አጽ ኃይለሥላሴ ዘመን የትግራይና ወሎ ርሃብ እንዲሁም የደርግ ዘመን የ1977ቱ ርሃብ መደበቅ ጋር ተመሳሳይ ተግባር መሆኑ ነው። የጌዲዖ ርሃብ የሚለው ርሃቡ በተፈጥሮ ድርቅ ምክንያት የተከሰተ ሳይሆን በአመራሮች እና ጽንፍ የያዙ ዘረኞች የተቀናጀ ቅጣት መሆኑ ነው። ርሃቡን ለመሰበቅ ብቻ ሳይሆን ለማስተባበልም በሶስት ቀን ውስጥ ብቻ የተለያየ ይሐሰት ማስተባበያ መረጃ ለማሰራጨት ተሞክሯል። ግን ለምን? ሰው እንዴት በወገኑ ላይ ይህን ያህል ይጨክናል? ይባስ ብሎ ራሳቸው የኦሮሞ “ጠበቃ” ያደረጉ እና ዘረኝነት በተደጋጋሚ ሲያቀነቅኑ የነበሩ አካላት የመፈናቀሉና ርሃቡ መጋለጡ ለምን አስቆጣቸው? ምናልባት የማፈናቀሉና የርሃቡ ቅጣት ላይ ተባባሪ ነበሩ ወይስ በምስኪን ህፃናትና ሞት የሚገኝ ሌላ ትርፍ ፍለጋ? ያሳዝናል።

የጌዲዖ ማኅበረሰብ “ብሔር” ተኮር ዘረኝነት ላይ መሰረት አድርጎ የተፈፀመው መፈናቀል እና የአመራሮች የተቀናጀ የርሃብ ቅጣት በዝምታ መታለፍ የለበትም። ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ምርመራ ተደርጎበት ተሳታፊዎችና ጉዳዩን ለመሸፋፈን የሞከሩ የሚመለከታቸው አካላት በህግ ሊጠየቁ ይገባል። ይሄ በዋናነት የምሥራቅ ጉጂ፥ ምዕራብ ጉጂ እና ጌዲዖ ዞኖች፥ የደቡብ ክልል እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ለማ መገርሳ እና ካቢኔያቸው፥ የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፥ የፌደራል፥ የኦሮሚያ እና የደቡብ ክልል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቋቋሚያ) አመራሮች እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በህግ ሊጠየቁና መልስ ሊሰጡ ይገባል። ምክንያቱን ጉዳዩን በደንብ ያውቁ ነበርና። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በስተቅር የተጠቀሱ አካላት እና አመራሮች ከዚህ ቀደም ችግሩን በአካል ድረስ ሄደው አይተዋልና። ስለዚህ ለተጎጂው የሚደረገውን የሰብዓዊ ድጋፍና ርዳታ ለማጣታልና ከኦሮሞ ህዝብ ጋራ ማያዝ ተገቢ አይደለም። ይሄ የባሰውኑ የለየለት ዘረኝነትና ጥላቻ ነው። ቢያንስ ሰብዓዊነት ተሰምቶን ለተጎጂዎች ቀና ትብብር ማድረግ ቢያቅተን እንኳ ደጋግና ቅን ሰዎች ድጋፍ ሲያደርጉ ከ”ኦሮሞ ብሔር” ስም አስታከን ለምን ተጋለጠ በሚል ግብዝነት ዓይናችን ሊቀላ አይገባም። ስለሆነም ተጎጂዎቹ የጌዴዖ ማኀበረሰብ አባላት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች “ብሔር” ተኮር የዘረኝነት ጥቃት ሰለባ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካዊ ርሃብ ቅጣት ሰላባም ጭምር መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል።

የጌዲዮ ማኀበረስብ የአረንጓዴ ወርቅ “ቡና” የበለፀጉ ታታሪ ገበሬና ነጋዴዎች ናቸው። በድርቅ ምክንያት በርሃብ የሚጎዱ የአካባቢውን ወገን ከመርዳት ባለፈ በርሃብ ምክንያት ለልመና እጅ የሚሰጡም አይደሉም። በዛ ላይ በዓለም ላይ ውድ የሆነውን እና የኢትዮጵያ ቡና (ኮፊ አረቢካ) ልዩ ተፈጥሯዊ ጣዕም የይርጋጨፌ ቡና ብራንድ ብቸኛ አምራችም ናቸው። ጥራት ያለው ተፈጥሯዊ ልዩ የይርጋጭፌ ቡና ወደዓለም አቀፍ ገበያ በመላክምለሀገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት በተጨማሪ የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃም የተካኑና የተመሰገኑ ታታሪዎች ናቸው። ዛሬ ቀን ጎድሎና በዘረኝነት የፖለቲካ ጥቃት ሰለባ ሆነው ለርሃብ ሲጋለጡ ቢያንስ በሰብዓዊነት ልናዝንላችውና ልንደርስላቸው ይገባል እንጂ ለምን ጥቃታችውና ርሃባቸው ተጋለጠ፥ ለምን ተረዱ በሚል ቡራ ከረዩ ማለት ያስገምታል። ቢያንስ እኮ የክፉ ቀን ደራሽ ባለፀጎች እንጂ በሥንፍና ደኽይተው ለርሃብ የተጋለጡ አልነበሩም። የደረሰባቸው “ብሔር” ተኮር ፖለቲካዊ የርሃብ ቅጣት እንጂ። ይሄ በኢትዮጵያ ያልነበረ አዲስ አስቀያሚና ልዩ ታሪክ ነው። ምንም እንኳን ዴሞክራሲያዊና በህዝብ የተመረጠ መሪ ኖሮን ባያውቅም፤ በሀገራችን የነበሩ ርሃቦች በተፈጥሮ የድርቅ አደጋ ተከስተው መሪዎች ለግል ፖለቲካ ስብዕናቸው ሲሉ (አጼ ኃይለሥላሴና መንግሥቱ) ደብቀዋል እንጂ “ብሔር” ተኮር የዘረኝነት ጥቃት ደርሱ ዜጎች ተፈናቅለው ፖለቲካዊ ርሃብ ጥቃት ደርሶ አያውቅም።

የተፈፀመባቸው እኮ የዘረኝነት ጥቃት ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ የርሃብ ቅጣትም ጭምር ነው። በዚህ ልናፍርና ሊሰማን ይገባ ነበር። ጉዳዩ ለታሪክም መመዝገብ አለበት። ህዝብን ማፈናቀልና በርሃብ መቅጣት ወንጀል። ይሄ ወንጀል የተፈፀመው በምስኪኑ ኦሮሞ ህዝብ ድጋፍና ይሁንታ አይደለም፤ በአመራሮቹና በደጋፊዎቻቸው እንጂ። ይሄ ደግሞ በ”ኦሮሞ” ስም ራሳቸውን “የመብት” አራማጅና ወኪል አድርገው የሚቆጥሩ “አክቲቪስቶች” ሚና ቀላል አልነበረም። ለዚህም በተለይ ከ2008 ዓ. ም. ጀምሮ የአቶ ጃዋርን፥ አውስትራሊያ ሜልቦርን የሚገኘው አቶ ፀጋዬ አራርሳ፥ ኖርዌይ ኦስሎ የነበረው አቶ ግርማ ጉተማ፥ ሀገር ውስጥ ያለው አቶ አየለ ደጋጋ ፥ አሜሪካ ያለው ኢታና ሀብቴ እንዲሁም አንዳንድ በ #OMN_TV እና #ONN_OnlineTV ላይ በተለያየ ጊዜ “ብሔር” ተኮር ጥላቻ አዘል ንግግሮች እና ውይይት ላይ ሲሳተፉ የነበሩት ተጠቃሾችን ማኀበራዊ ገፅና ቪዶዮ መመልከት ይቻላል። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ግለሰቦች አሊያም የፖለቲካ ድርጅቶች በ”አሮሞ” ስምና ሰቆቃ ከመነገድ እና ራስን የህዝብ “እንደራሴ” አድርጎ ከማቅረብ ባለፈ ማንም ጥላቻና ዘረኝነት እንዲሰብክም ሆነ ዜጎችን እንዲያፈናቅል ሥልጣን አሊያም ውክል የሰጠው ኦሮሞም ሆነ ሌላ ብሔር የለም።
Gedeo displacement
ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ተፈናቅለው በጌዲዮ ዞን ገደብ ወረዳ መጠለያ ካሉ የጌዲዮ ተጎጂዎች በከፊል (ፎቶ፡ የጉጂ ዞን ኮሚኒኬሽን)
በአጠቃላይ በሀገርም ሆነ በብሔር ወይም በፖለቲካ ፓርቲ ወይም ድርጅት ከአቻዎቹ ጋር ተወዳድሮና አማራጭ ሐሳብ አቅርቦ በህዝብ ተመርጦ የተወከለ ማንም የለም። ለደረሱትም ሆነ እየደረሱ ላሉ ጥፋቶች ተጠያቂዎች የበደሉ ፈፃሚዎችና ተባባሪዎቻቸው እንጂ ህዝብ አይደለም። ምክንያቱም ህዝብ እንደ ህዝብ አይበድልም፤ በህዝብ የተወከለም የለምና። የበደል ውክልናም ሆነ ውርስ የለም። ስለዚህ በየትኛውም ቦታ ከክፉዎች ጋር አትተባበር።

እውነታው ከላይ የተጠቀሰው ሆኖ ሳለ ራሳቸውን የ”ኦሮሞ” ማኅበረሰብ ተወካይ ወኪል አድርገው የሾሙና ራሳቸውን የመብት አራማጅ አድርገው የሚቆጥሩ አካላት ፤ የጌዲዖ ማኀበረሰብ ፖለቲካዊ ርሃብና ጥቃቱ መጋለጥ ለምን አስቆጣቸው? የምስኪኖች ርሃብና ስቃይ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ምን ያገናኘዋል? ርግጥ ነው። የተፈናቀሉትም ሆነ በደል የደረሰባቸው በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ውስጥ ነው። በደሉ የተፈፀመባቸው ደግሞ በኦህዴድ/ኦዴፓ ፥ በዘረኝነት ጥላቻ የተገፋፉ ወጣቶች እና በኋላም በአካባቢው በነበሩ የኦነግ ታጣቂዎች ነው። እዚህ ላይ የደቡብ ክልልና፥ በተለይ ለርካሽ ጊዜያዊ ሥልጣናቸው ሲሉ በግፍ ተፈናቃይ ህዝብ ላይ በተፈፀመው ፖለቲካዊ የርሃብ ቅጣት ላይ የደቡብ ክልልና የጌዲዖ ዞን አመራሮች እንዲሁም የተወሰኑ የፌደራል ባለሥልጣናት እጅ አለበት። በተለይም በርሃብ መቅጣትና መሸፋፈኑ ላይ የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ጉዳዩን በደንብ ያውቁ ነበርና ህግ ካለ ሊጠየቁ ይገባል። ይሄን መካድ አይቻልም።

ሌላው አስቂኝ ነገር መልካም ነገር ሲሆን “እኔ ይህን አድርጌ፥ እገሌ ይህን አድርጎ” ይሉናል፥ ሲወደሱም ምስጋናው እና ውዳሴውን ለግላቸው ጠራርገው ይወስዱና ስንት ዋጋ የከፈለውን እና አስተዋፅዖ ያበረከቱትን ስም ቅርጫት ውስጥ ይጥሉታል። ያው ባለሥልጣን ወይም “አክቲቪስት” ሲበድልና ግፍ ስፈፅም ልክ ኦሮሞን አማክረውና አስፈቅደው ያደረጉ ይመስል፤ በደሉንም ውግዘቱንም ኦሮሞ ላይ የተፈፀመ በማስመስል ለማስፈራራት ይሞክራሉ። ወዴት ወዴት!? ይሄ ግብዝነት ብቻ ሳይሆን ድንቁርናም ነው። የቀድሞው ጭካኙ አቶ ጌታቸው አሰፋ በወንጀል ሲጠየቅ ተመሳሳይ የህወሓት ደናቁርት አቶ ጌታቸውን ከምስኪኑ የትግራይ ህዝብ ጋር አያይዘው “ የትግራይ ህዝብ ላይ የተቃጣ ጥቃት” አስመስለው ካድሬዎቻቸው ህዝቡን አስገድደውና አታለው ሰልፍ አስወጥተው ነበር። ይሄንንም ራሳቸውን ተረኛ ባለሥልጣንባለጊዜ አድርገው የሚያቀርቡልን ድኩማን የኦህዴድኦዴፓ ካድሬዎችን ጭምሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሲኮንኑ ነበር። በዛ እኔም እስማማለሁ። ምክንያቱም አቶ ጌታቸውም ሆነ የህወሓት አመራሮች እንደዛ አረመኔና ጨካኝ እንዲሆኑ የትግራይ ህዝብ ውክልናም ሆነ ድጋፍ አልሰጣቸውምና። ቀድሞንስ የተበደለ ካልሆነ ማን ያውቅና? ህዝቡ ሚኒገረው ልክ እንደዛርው እንደነ ጠቅላይ ሚኒስር ዶ/ር አብይና ካድሬዎቻቸው የምናቧን ኢትዮጵያ አልነበር? የህወሓት አመራሮችን በተለይም የነ መለስ ዜናዊ እና ጌታቸው አሰፋ የፈፀሙትን በደል ከትግራይ ህዝብ እንደለያችሁት ሁሉ በጉጂዎች የተፈፀመውንም በደል ከኦሮሞ ጋር አታገናኙት። በደለኛው ራሱ ይጠየቅ፥ ሥራው ያውጣው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ አቶ ለማ መገርሳም ቢሆኑ ሰዎች እንጂ መላዕክት አይደሉም። አንዳንዱም ፈጣሪ አድርጎ ሊስላቸው ሚዳዳው ሁሉ አለ። ይቅር በለን እንጂ። ትናንት ጅልጣን ላይ የነበሩም ሆነ ዛሬ በህዝብ ማዕበል ተገፍተውና ተደግፈው ወደ ሥልጣን የመጡት እነ አብይ፥ ደመቀ፥ ለማ፥ ገዱ ያው ኢህአዴግ ናቸው፤ እንደየ ድርሻቸው የተለያየ ወንጀልብደል ላይም ተሳትፎ የነበራቸው ናቸው። ይሄን እነሱም ሚክዱት አይመስለኝም። ያው ከነበረው የ27 ዓመታት ሰቆቃ ወደ ለውጥ መግባታችን ጥሩ፥ “የሚታየውን ብሩህ ለውጥ” ማጨለምና እንቅፋት መሆን ጥሩ አይደለም በሚል እንጂ እያንዳንዱ ዶሲው ከቢሮው መደርደሪያ ቢፀዳም ከያንዳንዱ የጥቃት ሰለባ ወገን እና ተባባሪዎቻቸው ህሊና ሊጠፋ አይችልምና ድጋፉንም ቢሆን በልክ እናድርገው። በየትኛውም ቦታና ጊዜ በደልን እንፀየፍ። መልካም ነገሮችን እናበረታታ። ከዛ ውጭ የሚፈፀሙ በደሎችን ደብቁልን እያሉ ከምስኪኑ ህዝብ ጋር ለማገናኘት መጋጋጥ የትም አያደርስም። የህወሓትም ሰዎችም ቢሆኑ ይህንንም ነበር ያደረጉት። ግን አልጠቀማቸውም። እና ያንን የቆሸሸ መንገድ መልሶ መድገም ጭፍኑ እና ላሞኛችሁ” ዓይነት የጅል ጨወታ ስልሆነ ጉድፍና ቆሻሻን ነገር ከ”ብሔር” ጋር ማያያዝ ተውትይቅርባችሁ። በ”ኦሮሞ” ስም ራሳቸውን ባጩ “ልሂቃን” እና “አክቲቪስቶች” በስሙ፥ በአስከሬኑ እና ሰቆቃው እየተነገደ ለነበረው ኦሮሞ ማኅበረሰብ ልክ ለፖለቲካ መቆመሪያ የያ ርካሽ ትውልድ እንዳደረገው ዛሬም የልቅሶና የበታችኘት፥ የማስፈራሪያና ዛቻ ስሜት ቅስቀሳን ፖለቲካ አይመጥነውም።

በሰው በደል የሚደሰት ኦሮሞ፥ አማራ፥ ትግሬ፥ ሶማሌ፥ ጌዲዖ፥ አፋር፥ ሲዳማ፥ አኝዋክ፥ ጋሙ፥ ሀዲያ፥ ጉራጌ፥ ስልጤ፥ ሐረሬ፥ … ወዘተረፈ የለም። ህዝብ እንደህዝብ በደል የለበትም፤በጅምላ አንዱን ወገን ከሌላው በመለየት በደልም አያደርስም። ልክ ውዳሴና ሙገሳውን ለግላችሁ እንደምታደርጉት የፈፀማችሁትን በደልና ልለበደሉ ያላችሁን ተሳትፎም ኃላፊነቱን ለወንጀለኞችና ተባባሪዎች እንተው። የተጎዱ ወገኖቻችንን ግን እንታደግ። ሰብዓዊነት ዜግነትም ሆአ ብሔር የለውም። ብሔር ሰውን አልፈጠረም፤አይፈጥርም። ሰው ነው ብሔርንም፥ ባህልንም የፈጠረው። ስለዚህ ቅድሚያ ሰው እንሁን፤ ለሰብዓዊነት ይሰማን። በዛ ላይ የኦሮሞ ማኀበረሰብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ማኀበረሰብ ነው። ማኅበራዊ ህይወት የሚመቸው፥ ከመንደርና ቀበሌኛ አስተሳሰብ ይልቅ ሰፋ ያለ ቦታና አድማስን የሚያስቀድም፥ ቀናዒ፥ ኃይማኖትና ሥርዓት ያለው ማኅበረሰብ ነው።

በስሙ የምትነግዱ “ሊሄቃን” እና አክቲቪስቶች” ግን በተቃራኒው ጥላቻ፥ ቀበሌኛ፥ መንደርተኛ፥ የበታችነትና ተጠቂነት ስነ ልቦና ላይ ቆሞ የቀረ ጊዜ ያለፈበት ኋላቀር አስተሳሰብ ላይ ናችሁ። በዛ ላይ ትውልዱም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆኖ ከአድማስ ወዲያ አስቦና ሰርቶ፤ ራሱን፥ ቤትሰቡን፥ ማኅበረሰቡን፥ ሀገሩን፥ አህጉሩን እና ዓለምን ሊረዳ የሚችልበት ጉልበቱን፥ አእምሮና ጊዜውና በጥላቻ፥ በተጠቂነት፥ መንደርተኝነትና ቀበሌኛ ስነልቦና ውስጥ አታስቀሩት። የትናንቷ ዓለም ዛሬ የለችም። የዛሬዋ ደግሞ ነገ አትኖርም። ነገ ደግሞ ከዛሬው የበለጠ ብዙ ፈታኝ ውስብስብ የውድድር ዓለም ነው የሚጠብቀን። ከትንሽ ጊዜ በኋላ አይደለም የመንደር “ብሔር” ተኮር ቀበልኛ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ቀርቶ ኢትዮጵያ ራሷ ትንሽዬ መንደር የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ያውም ዓለም በመሰረተ ልማትና በዲጅታል ትክኖሎጂ ከምናስበው ፍጥነት በላይ እየተሳሰረ ባለበት በዚህ ወቅት። እንኳን የስግብግብ መንደርተኛ ፖለቲካ ላይ እኝኝ ብለን ቀርቶ ምሥራቅ አፍሪካ እንኳ አንድ ላይ ብንቀናጅ እየመጣ ያለውን ፈታኝ የውድድር ህይወት መቋቋም አንችልም። ከመቼው ጊዜ በላይ የጠነከረ ህብረት፥ አንድነትና መከባበር ያስፈልጋል። ለአንዱ ሚያስፈልገው መልካም ነገር ሁሉ ለሌላውም ያስፈልገዋል። አንዱ ላይ የንፈፅመው በደልና ጥላቻ ሁሉ ይዋል ይደር እንጂ አፀፋዊ መልስ ይዞ መምጣቱ የማይቀር ነው። በዛ ላይ መቶ ዓመት ለማንኖርባት ጊዜያዊ ዓለም።

በርግጥ አውቃለሁ። በ”ኦሮሞ” ስም የሚነግዱ ኋላቀር እና የዘረኝነት ቅስቃሳና ፖለቲካ የሚያራምዱ በምቾት የሚኖሩበት የሌላ ሀገር ፓስፖርትና መኖሪያ ቤት አንዳንዶቹ በአሜሪካ፥ አውሮፓና አውስትራሊያ አላቸው። እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ብትጎዳ፥ ወይም እንደ ህዝብ ኦሮሞ ቢጎዳ እነሱ ሌላ የምቾት መኖሪያሌላ ሀገር ስላላቸው ሳይነግሩህ በቦሌ ተሳፍረው ነው ሚሄዱት። ከዛ ባንተ አስከረንና ሰቆቃ ገንዘብ ይለቃቅማሉ። አለቀ። አንተ ሰላም ከሆንክና አተመቸንህ ግን ባንተ ስም ገቢ የላቸውም። ከዚህ የተለየ ግብ አላቸው ካልክ በስምህ ምለው ተገዝተው የሚነግዱትን ፍላጎታቸውና ዓላማቸውን እንዲሁም ምክንያታቸውን ጠይቅ። ከዛ ለምን የሌላ ሀገር ፓስፖርት ይዘው እንደሚኖሩ ጠይቅና፤ ከዛ እሱን ትተውካንተ ጋ ያለውን ተካፍለው እንዲኖሩ ጠይቃቸው። ያኔ ምላሽና ተግባራቸውን ተመልከት። በነጋታው ቻዎ እንኳን ሳይሉህ ደጋግ፥ ሥልጡን እና ሰብዓዊነት የሚሰማቸው ሰዎች ወደሰጧቸውና ወደፈቀዱላቸው የምቾት ሀገር ይመጣሉ። የሚያሳዝነኝ ምስኪኑ ወጣት ነው። አጣችም ደኽየችም ያለችው ያቺው ምስኪን አንዲት ኢትዮጵያ ናት። ተከባብሮ በአንድነት በሰላም ኖሮና ሰርቶ ፤ወጣቱ ተረጋግቶ እንዳይኖር በሰቆቃው የጉስቁልናው ህይወቱ ለሚነግዱ መቆመሪያ ማድረጉ ነው። ወዳጄ! ከሞት በኋላ ትንሳኤ ኃይማኖት ላይ እንጂ ምድርና ፖለቲካ ላይ የለም። ከሞትክ ሞትክ ነው፤ አበቃ። ስትሞትና ስትጎዳ ምታጎለው ራስህን እና ቤትሰብህን ሌላ ማንንም አይደለም። በሞትህ የሚጠቀመው ደግሞ፥ የሬሳ ሳጥን ሻጭ፥ የመቃብር ጉድጓድ ቆፋሪና በሞትህና ስቃይ ቆምሮ የሚከብር አረመኔን ብቻ ነው። ስለዚህ ነፃ ሆነህ፥ ሰልጥነህ፥ ጤናማ ደስተኛ ሆነህ ከሁሉም ጋር በፍቅር ኑር።

አንተ ላይ እንዲፈፀም የማትፈልገውን መጥፎ ነገር በሌሎች ላይ አታድርግ፤ ላንተ እንዲሆንል የምትመኘውን መልካም ነገር ሁሉ ያለምንም አድሎ ለሌሎችም አድርግ!! ምክንያቱም ሌላውም ሰው ልክ እንዳንተ መልካም ነገሮች የሚያስፈልጉት ሰው ነውና።

Leave a comment