በኢትዮጵያ የለውጥ ተስፋ እና ስጋቶች

ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com

ጥንታዊ እና ቀዳሚ ከነበሩ ሀገሮች መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በተለይ በቅርቡ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በዓለ ሲመት ከተደረገበት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. አካባቢ የተስፋ አድማሶች ጎልተው ይታዩ ነበር። ዛሬም በርካታ ፈተናዎች ተደቅነውባታል። ህዝቡም ዛሬም ቅን መሪና የዴሞክራሲ ሥርዓትን ይናፍቃል። ምንም እንኳ የተፈጥሮ ሃብትን የተቸረች ቢሆንም፤ ዛሬም ድረስ ለዜጎቿ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፥ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ፥ የመብራት አቅርቦት እና አገልግሎት መጓል፥ ጥራቱን የጠበቀ በቂ የትምህርት እና የጤና ሽፋን በበቂ ሁኔታ አለመዳረስ ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው።

በሀገሪቱ ስር የሰደደ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ሌላው የዜጎች ትልቁ ፈተና ነው። በተለይ ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጋር ያልተመጣጠነ የህዝብ ብዛት፥ የወጣቶች ሥራ አጥነት፥ የህግ የበላይነት አለመረጋገጥ እንዳለ ሆኖ፤ ልቅ የሆነው የሙስና ሰንሰለት ሀገሪቱ ከውጭ በዕርዳታ፥ ብድርና ንግድ ከምታገኘው ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ይልቅ በተደራጀ ፖለቲካዊ መዋቅር ተደግፎ ከሀገር የሚሸሸው የዶላር መጠን እና አድሏዊነት የተፀናወተው ሥርዓት አልባው የንግድ ሥርዓት የዜጎችን ሰላምና ህይወት ሲፈታተን ቆይቷል።

PM_Abiy_Ahmed_Ali
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ (ፎቶ፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተወሰደ)

በርግጥ በኮሎኔል መግሥቱ ኃይለማርያም ይመራ ከነበረው የኢሕዴሪ መንግሥታዊ ሥርዓት መገርሰስ በኋላ ግንቦት 1983 ዓ.ም. በምዕራባዊያን እና አረብ ሀገራት ድጋፍ ወደ ሥልጣን የመጣው የቀድሞው የጫካ አማጺ የትግራይ ነፃ አውጭ ድርጅት (ህወሓት) ኢህአዴግ በሚል ካባ በአምሳሉ ከፈጠራቸው የፖለቲካ ድርጅት (ብአዴን/አዴፓ፥ ኦህዴድ/ኦዴፓ እና ደኢህዴግ/ደኢህዴን) ድርጅቶች ጋር ኢህአዴግ በሚል ግንባር ወደ ሥልጣን ሲመጣ ብዙ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ይሁን እንጂ በነበረበት ያለፉት 27 ዓመታት የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ቆይታው ለሀገሪቱም ሆነ ለዜጎችም በበርካታ ጉዳዮች እጅግ ፈተና የበዛበት የግፍ አገዛዝ ነበር። በአገዛዙም በርካታ ዜጎች በግፍ ታስረዋል፥ ተገድለዋል፥ ከሀገር ተሰደዋል። የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰትም ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በርካታ ሰነዶችና ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የህዝቡን ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ የሀገሪቱን ጥቅም በማሳጣትም በሀገሪቱ ታሪክ ከነበሩ አገዛዞች በተለየ በጥቁር መዝገብ እንዲሰፍር ተደርጓል።

ከሶስት ዓመታት ተከታታይ ህዝባዊ አመፅ በኋላ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ ም የሀገሪቱ 15ኛው ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ወደ ሥልጣን የመጡት አብይ አህመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም ከወትሮ የኢህአዴግ አሰልቺ የቃላት ጋጋት እጅጉን የራቀና በዜጎች የተወደደላቸውን ንግግር በተሰማበት ወቅት ሀገሪቱ በብሩህ ተስፋ ተሞልታ ነበር። በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተከታታይ በወሰዷቸው መልካም ርምጃዎች፤ በተለይም የታሰሩ የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪዎችን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፥ መንግሥት በዜጎች ላይ ለፈፀመው ጥፋት በይፋ ይቅርታ መጠየቅ፥ ብረት ያነሱ ተቀናቃኝ አማጺያንን ጨምሮ በውጭ ያሉ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች በሰላም ወደ ሀገር ገብተው ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲያካሂዱ ጥሪና ድጋፍ ማድረግ ተጠቃሽ በጎ ርምጃዎች ናቸው።

ለረጅም ጊዜ “ሞት አልባ” ጦርነት የነበረው የኢትዮጵፃ እና የኤርትራ መፋጠጥ በሰላም እንዲቋጭ ማድረጋቸው እና ብሔራዊ አንድነትና መግባባትን በአደባባይ ከማቀንቀን አልፈው ለተግባራዊነት መንቀሳቀሳቸው ከህዝቡ ባልተለመደ መልኩ በርካታ ድጋፍና አጋርነት አስገኝቶላቸዋል። እንዲሁም ለበርካታ ዓመታት ህዝቡ ያለገዥው ህወሓት/ኢህአዴግ ፍላጎት ውጭ ናቸው የተባሉና ታግተው የነበረው የሳተላይትና የመረጃ መረብ ሚዲያዎች ክፍት እንዲሆኑና ለህቡም አማራጭ ሆነው እንዲያገለግሉ መፍቀዳቸው፤ በተለይ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ እና የፕሬስ ነፃነት አቀንቃኞችና ተሟጋቾች ሳይቀር ይበል የሚያሰኙ በርካታ ውዳሴዎችን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

በሀገር ውስጥ በተለያዩ ከተሞች ጉብኝትና ምክክር ከማድረጋቸው በተጨማሪ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ያደረጉት ምክክርና መቀራረብም ያልተለመደና የተወደሰ አዲስ የለውጥ ክስተት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በህዝባዊ አመፅ ተዳክሞ የነበረውን እና የተራቆተውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሻሻሉ እየወሰዱ ያሉት በጎ ርምጃም ከሚወደስላቸው ተግባራት መካከል አንዱ ነው። በተጨማሪም ላለፉት 27 ዓመታት በፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ለሁለት ተከፍሎ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ አንድነት እንዲመጡ የተደረገው ድጋፍና አስተዋፅዖ ፤ እንዲሁም በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ ሙስሊም መጅልስ ተቋም ላይ በተደረ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት የነበረው መለያየት ወደ አንድነት እንዲመጣ መደረጉ በበጎ የሚወሱ ተግባራት ናቸው። እነኚህ በጎ ተግባራት የህዝቡን አንድነትና ህብረት ከማጠናቀር በተጨማር በሀገሪቱ ሰላም፥ ዕድገትና ብልፅግና ላይ ዜጎች ብሩህ ተስፋን እንዲሰንቁ አስችሏቸዋል።

ነገር-ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያ ሁሉ የነበረው ተስፋና ድጋፍ ግን ከአንድ ዓመታ በላይ መዝለቅ የቻለ አይመስልም። ለአንድ ዓመት ያህል የመብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች ሳይታሰሩ የመቆየታቸው በጎ ተስፋ አሁን አሁን ስጋት እየታየበት ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የለውጥ መሪውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይወክሉታል በሚባለው ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በርካታ ዜጎች የደህንነት ዋስትና ማጣት እየተለመደ መጥቷል። በአማራ ክልል፥ በደቡብ እና ቤኒሻንጉል ክልልም የተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ የፀጥታና ደህንነት ስጋቶች ይስተዋላሉ።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ከሚነሱ ነቀፌታዎች መካከል ይሰሩልኛል ብለው የነበረውን ህግ ወደ ጎን በመተው የራሳቸውን ሰው ከህግ አግባብ ውጭ የሾሟቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካላት ሹመት፥ የሥራ ስምሪት እና የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን እና ሹመት ከብቃትና አካታችነት ይልቅ ከዚህ ቀደም ይወገዝና ተቃውሞ ይቀርብበት የነበረውን የሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ እና የድርጅታቸው ህወሓት አገዛዝን ተመሳሳይ መንገድ እየተከተሉ ነው በሚል በርካታ ደጋፊዎቻቸው ሳይቀር ነቀፌታ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በዋናነት ሶማሊና ኦሮሚያ ክልል አካባቢ ወደ አንድ ሚሊዮን ዜጎች ከመደበኛ መኖሪያቸው የተፈናቀሉ ቢሆንም፤ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የአንድ ዓመት አስተዳደር ጊዜ ውስጥ ግን ወደ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች በኃይል ተፈናቅለዋል፥ በርካቶችም በርስ በርስ ግጭት ተገድለዋል፥ ቆስለዋል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ብቻ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ከአንዴም ሁለት ጊዜ ያለምንም ህጋዊ መሰረትና ምክንያት በጅምላ ሰብስቦ ማሰርና ማንገላታት በቀዳሚነት ይደግፏችው የነበሩ ወጣቶች አዲሱን አስተዳደር በጥርጣሬ እንዲያዩት ምክንያት ሆኗል። በተለያዩ መንግሥታዊ አስተዳድር ጉዳዮች እና አገልግሎት አሰጣጥ ላይም ሁሉንም በእኩል ከማየት ይልቅ ፖለቲካዊ ወገንተኝነትን የተላበሰ አድሏዊነት እየተንፀባረቀ ነው በሚልም የነበረውን ተስፋ በሂደት ወደ ስጋት እየተለወጠ መጥቷል። በተለይም በኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ አቅራቢያ ቡራዩ፥ ለገዳዲና ለገጣፎ ከተሞች፥ ምዕራብ ወለጋ፥ ቄለም ወለጋ፥ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፥ ምሥራቅ ወለጋ፥ ምዕራብ እና ምሥራቅ ጉጂ ዞን፤ በአማራ ክልል፥ ሰሜን ጎንደርና ምዕራብ ጎንደር፤ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን፥ ጉጂ ዞን፥ ቡርጂ ጌዲዮ፥ አማሮ፥ ከፋ ዞን እና ደራሼ አካባቢን መጥቀስ ይቻላል። ይህ ዘገባ በሚጠናከርበት ጊዜም መንግሥት ባመነው መረጃ እንኳ ወደ ሶስት ሚሊዮን ዜጎች ከመደበኛ ኑሯቸውና ቀዬያቸው ተፈናቅለዋል። በርግጥ የተወሰኑት ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ጥረት እየተደረ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ አሁንም ድረስ ዜጎች ተረጋግተው የመኖር ተስፋቸው ላይ ስጋትን ጭሯል።

በኦሮሚያ ክልል ለሰላማዊ ትግል በሚል ስምምነት ወደ ሀገር ውስጥ ጥሪ ተደርጎለት ከኤርትራ አስመራ ወደ ሀገር የገባውና በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ሸኔ የሚባለውና የኦነግ ክንፍ
በአራቱም የወለጋ ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ 19 ያህል የንግድ ባንኮች ዘረፋ መፈፀሙ ቢገለፅም በጉዳዩ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ አዲስ አበባ የሚገኙት የድርጅቱ መሪም ሆኑ ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ዝምታን መምረጣቸው የህግ የበላይነት መላላትና የዜጎች ደህንነት ከዕለት ወደ ዕለት አደጋ ውስጥ መውደቁ ሌላኛው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ድክመት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የሀገሪቱ ፀጥታና ደህንነት ጉዳይ ከወዲሁ ትኩረት ካልተሰጠው፥ ተጠያቂነትና የህግ የበላይነት በሁሉም ዜጎች ላይ በእኩል የማይሰራ ከሆነ ወደ አላስፈላጊ ረብሻና ሥርዓት አልበኝነት እንዳያመራ ስጋት አለ። የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከመጠበቅ አኳያ በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ያለው የእርምትም ይሁን የጥንቃቄ ርምጃ እጅጉን ደካማ ነው።

ሐሳብን ከመግለፅና ከፕሬስ ነፃነት ጋር በተያያዘ ያለው ተስፋ በቅርቡ በአንዳንድ ጋዜጠኞችና ጦማሪዎች ላይ ስጋቶች እንደ አዲስ ተደቅኖባቸዋል። በተለይ የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አቅራቢያ ባሉ የኦሮሚያ ክልል ለገዳዲና ለገጣፎ ከተሞች በመንግሥት አስተዳድር በግልፅ ውሳኔና ርምጃ የተፈናቀሉ ዜጎችን አስመልክቶ ለዘገባ የተጓዙ የ”መረጃ ቲቪ” ዘጋቢ ጋዜጠኛ ፋሲል አረጋይ እና የፎቶ ጋዜጠኛው ሀብታሙ ኦዳ በከተማው ፖሊስ ጣቢያ ፊትለፊት የአካል ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል። ጋዜጠኛ ፋሲልም በደረሰበት ጥቃት አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የህክምና ርዳታ ተደርጎለታል። በቅርቡም የአሃዱ ቴቪ ጣቢያ ከሰንዳፋ ከተማ ጋር በተያያዝ በተላለፍ ዘገባ ጋር በሚል ግንቦት 16 ቀን 2011ዓ.ም. ጋዜጠኛ ታምራት አበራ ከሚሰራበት አሃዱ ቴልቪዥን እና ሬዲዮ ጣቢያ በኦሮሚያ ፖሊስ ተወስዶ መታሰሩና፤ በዕለቱ የታሰረውን ጋዜጠኛ ሊጎበኘው የሄደው የኢትዮ-ኦንላየን ሚዲያ ጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለው መታሰሩ በነፃው ፕሬስ ጫና ጅማሮ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። እንደ ምንጮች ከሆነ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር እየተፈፀሙ ያሉ ብልሹና አድሏዊ አሰራሮችን የሚያጋልጡ የኢንተርኔት መረጃ አምደኛ ጋዜጠኞች፥ ጦማሪዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የጦማሮቻቸው እና የግል የይለፍ ቃል በኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (INSA) ብርበራና የይለፍ ቃል ነጠቃ እየተሞከረ እንደሆነ ይነገራል። እነኚህ ሁሉ የነበሩ የለውጥ ብሩ ተስፋዎች ላይ የስጋት ደመና ጋርደዋል።

ሌላው ከዚህ ቀደም በህወሓት/ኢህአዴግ የመንግሥት አስተዳደር ወቅት የአመራር አካልና የወጣት አደረጃጀት አባላት የነበሩና ተከታዮቻቸው በአዲሱ የአብይ አህመድ ኦዴፓ/ኢህአዴግ አመራር ላይ የተለያየ ጫና ለመፍጠር ሲጥሩ ይስተዋላል። ለአብነትም የቀድሞ የኦህዴድ/ኦዴፓ የታችኛው አንዳንድ አመራር አካላት፥ የህወሃት አመራሮች፥ የቀድሞ ብአዴን/አዴፓ እና የደኢህዴን አመራሮች በየአካባቢያቸው ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጨማሪ በማኀበራዊ ሚዲያ ሳይቀር አንዳንዶቹ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መምጣት በኋላ ከኢህአዴግ አካል የነበሩት አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅት በመፍጠር ጭምር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በአንዳንድ አካባቢዎች ጥርጣሬ፥ ግጭትና ስጋት መፍጠራቸው አልቀረም። በአንፃሩ ከኦነግ ታጣቂ በስተቅር አብዛኛው ከውጭ የመጡትም ሆነ በሀገር ውስጥ ያሉ የገዥው ኢህአዴግ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች ከአዲሱ አስተዳደር ጋር የተሻለ መከባበርና መቀራረብ ይታይባቸዋል። ይሄ ለሰላምና መረጋጋቱ ተስፋ ሰጭ ቢሆንም፤ በአንዳንድ ሚዲያ ላይ የሚታዩ የጋዜጠኝነት የሙያ ስነ ምግባር ጋር የሚቃረኑ የሚዲያ አጠቃቀም ክፍተቶች፥ ተጠያቂነትና ኃላፊነትን ተላብሶ እንዲሰራ ሊረዳ የሚችል ነፃና ገለልተኛ የጋዜጠኞች የሙያ ማኀበር አለመኖርም እንደ አንድ ስጋት የሚታይ ነው።

በተለያ በማኀበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ረገድ በርካታ የማኀበራዊ የግል ገፆች ትክክለኛ ባልሆነ ስም፥ አንዳንዱ ደግሞ በህይወት ባለም ሆነ በሌለ ስመ ጥር ግለሰቦች ስም ገፅ በመክፈት የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት እና የጥላቻ ንግግሮች ሌላው የለውጡ ፈተና ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በተለይ ሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን የሚያሰራጩ ግለሰቦች እየተበራከተ ከሄደ መንግሥና አስተዳደር ላይ ብቻ ሳይሆን የዜጎች ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትና የፕሬስ ነፃነት ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል። ምናልባትም ችግሩ ተባብሱ በዜጎች መካከል ግጭት እና ቅራኔ መፍጠር ሲባባስ መንግሥት የራሱን አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወስድ ሊጋብዝ ይችላል። ይሄ ደግሞ በሌላ በኩል በዜጎች ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትና የፕሬስ ነፃነት ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ሚና ይኖረዋል። ስለዚህ ብሩህ ተስፋን ሰንቆ የነበረው ለውጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥትና በአንዳንዴ ዜጎች መካከል ጥርጣሬና ስጋትን እየታየ ይገኛል።

Leave a comment