በኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተገደሉ

(ዳጉ ሚዲያ) ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህርዳር ከተማ በስብሰባ ላይ የነበሩ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ በተፈጸመ ጥቃት የክልሉ ፕሬዘዳንት ዶ/ር አምባቸው መኮንን እና የማኀበራዊ ዘርፍ አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴን ጨምሮ ቁጥራቸው ያልተገለጸ ጠባቂዎቻቸውም ሲገደሉ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሆኑት አቶ ምግባሩ ከበደ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል::

ዶ/ር አምባቸው መኮንን (ፎቶ፡ ከአማራ ቴቪ)

በተመሳሳይም በአዲስ አበባ

አቶ እዘዝ ዋሴ (ፎቶ፡ ከአማራ መገናኛ ብዙኃን)

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዡር ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና በጡረታ ላይ የነበሩት የቀድሞ የስራ ባልደረባቸውና የሰራዊት የሎጀስቲክ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት ሜጀር ጀነራል ገዛዒ አበራ
በጀነራል ሰዓረ መኖሪያ ቤት እያሉ በኢታማዡሩ ጠባቂ መገደላቸውን መንግሥት አረጋግጧል:: ድርጊቱን ያወገዙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) በተለይ የባህር ዳሩን የባለሥልጣናት ግድያ ጥቃት “በአማራ ክልል የተፈጸመ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መሆኑና መክሸፋን” ገልፀዋል::

 

ነገር ግን እስካሁን ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም መንግሥት በበኩሉ “ጥቃቱን የመሩትና ያቀናበሩት የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ኃላፊ ብርጋዴየር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ናቸው::” ቢልም ከገለልተኛ አካልም ሆነ በስም የተጠቀሱት ተጠርጣሪ ብርጋዴየር ጀነራል አሳምነው የተሰጠ ማረጋገጫም የለም:: ከጥቃቶቹ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከመከላከያ ሰራዊት ሹማምንት ግድያ ጋር በተያያዘ የጀነራል ሰዓረ መኮንን ታማኝ የግል ጠባቂያቸውና ሌሎች የመከላከያ ሰራዊት ተጠርጣሪ የጦር መኮንኖች በቁጥጥር ስር ውለዋል::

ጀነራል ሰዓረ መኮንን (ፎቶ፡ ከኢቴቪ)

ከአማራ ክልል አመራሮችና ጠባቂዎቻቸው ግድያ ጋር በተያያዘ የክልሉ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ እና የፖሊስ ኮሚሽኑ ኮምሽነር አበረ አዳሙ ተጠርጥረው በፌደራል ፖሊስ እና በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መዋላቸው የተሰማ ሲሆን በቀዳሚነት ተጠርጥረው ስማቸው የተነሳው ብርጋዴየር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ይህ እስከተጠናቀረበት ድረስ በቁጥጥር ስር እንዳልዋሉና ያሉበትም እንዳልታወቀ ተጠቁሟል::

ሜጀር ጀነራ ገዛዒ አበራ (ፎቶ፡ ከኢቴቪ) 

የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎችም ጥቃቶቹን በመኮንንና በማውገዝ ህዝቡ እንዲረጋጋ እንዲሁም በጋራ አንድነቱን እና ሰላሙን እንዲያስጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል:

Leave a comment