Tag Archives: General Seáre Mekonnen

የሰኔ 15 ቀን ጥቃት ሰለባ አመራሮች የቀብር ስነ ሥርዓት ተፈፀም

(ዳጉሚዲያ) ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህርዳር እና አዲስ አበባ በተፈፀሙ ጥቃቶች ሰለባ የሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች መካከል የአማራ ክልል ፕሬዘዳንት ዶ/ር አምባቸው መኮንን፥ የክልሉ አደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ እንዲሁም በአዲሴ አበባ የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዡር ሹም የነበሩት ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና ከአንድ ዓመት በፊት በጡረታ የተሰናበቱት ሜጀር ጀነራል ገዛዒ አበራ በዕለቱ ተገድለዋል። በዕለቱ በአማራ ክልል በደረሰው ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩት የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የነበሩት አቶ ምግባሩ ከበደ የህክምና ዕርዳታ ቢደረግላቸውም ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ በጥቃቱ መንግሥት ጠርጥሬያቸዋለሁ ያላቸው የክልሉ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ብርጋዴየር ጀነራል አሳምነው ጽጌ በፌደራል ፖሊስና መከላከያ በተወሰደባቸው ወታደራዊ ጥቃት ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. መገደላቸውን መንግሥት አስታውቋል።

Amhara regiona victim leaders
ዶ/ር አምባቸው መኮንን፥ ብጀነራል አሳምነው ጽጌ፥ አቶ ምግባሩ ከበደ እና አቶ እዘዝ ዋሴ (ፎቶ፡ ከማኀበራዊ ሚዲያ)

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት በአዲስ አበባ በጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጀነራል ገዛዒ አበራ ግድያ ግድያ ተጠርጣሪው የጀነራል ሰዓረ መኮንን የግል ጠባቂ የአስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ነው ሲል ይፋ አድርጓል። ይሁን እንጂ ተፈፀሙ ለተባሉ ጥቃቶች መንግሥት “መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው” በሚል ለዓለም ይፋ ቢያደርግም የጥቃት አድራሾችን፥ ጥቃቱን እና ምክንያቱን በተመለከተ ርስ በርሱ የተጣረሰ የአንድ ወገን መረጃ ብቻ በመሆኑ ይህ እስከተጠናቀረበት ድረስ ሁኔታውን በተመለከተ ከጥቃቱ ተርፈናል ከሚል አራት የአማራ ክልል አመራሮች በስተቀር ከተጠርጣሪዎችም ሆነ ከገለልተኛ አካል የተሰጠ ምላሽም ሆነ ማረጋገጫ የለም። ጥቃቱን ተከትሎ ከከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ግድያ በተጨማሪ ቁጥራቸው ያልተገለፀ ሌሎችም በርካታ ዜጎች መገደላቸውንም የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰማኽኝ አስረስ ለሮይተርስ ገልፀዋል።

በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈ አመራሮች ዶ/ር አምባቸው መኮንን፥ አቶ ምግባሩ ከበደ እና አቶ እዘዝ ዋሴ ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ ም በባህርዳር ከተማ አባይ ማዶ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው የተፈፀመ ሲሆን፤ የብርጋዴየር ጀነራል አሳምነው ጽጌ በትውልድ ከተማቸው በላሊበላ አብያተ ቤተክርሥቲያናት በቤተ ጊዮርጊስ የቀብር ስፍራ ተፈፅሟል። በተመሳሳይም ጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀን የጀነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጀነራ ገዛዒ አበራ የቀብር ሥነሥርዓት በመቀሌ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።
General Seare and M.General Gezae
ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜ/ጀነራል ገዛዒ አበራ (ፎቶ፡ ከማኅበራዊ ሚዲያ)

የአመራሮችን ግድያ እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ቢያሳውቅም፤ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ የወታደራዊ የኃይል ርምጃ የተገደሉ በርካታ ዜጎች ቢኖሩም መንግሥት እስካሁን ቁጥራቸውንም ሆነ ማንነታቸውን አልገለፀም። መንግሥት ቀደም ሲል ጥቃቱን “መፈንቅለ መንግሥት ነው፥ የአዲስ አበባው ከባህርዳሩ ጥቃት ጋር የተያያዘ ነው” በሚል በጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ኃላፊዎች እና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ የተገለፀ ቢሆንም፤ ዛሬ ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ ም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ቢልለኔ በበኩላቸው “የአዲስ አበባው ከባህር ዳሩ ጥቃት ጋር ስለመያያዙ ገና ይጣራል።” ሲሉ ገልፀዋል። በተለይ የባህርዳሩን እና የአዲስ አበባውን የባላሥልጣናት ግድያ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ቃል አቀባይ ኃላፊዎች እና ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ የሰጡት መግለጫዎች ርስ-በርስ የሚጣረሱ በመሆናቸው፤ መንግሥት እየሰጠ ያለው መረጃ ተዓማኒነት ላይ በርካቶች ጥርጣሬ እንዳላቸው እየገለፁ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበኩሉ በመተከል ዞን ሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ ም ከ 30 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን ይፋ አድርገዋል።

መንግሥት ባህርዳሩን እና የአዲስ አበባውን ጥቃት ተከትሎ በርካታ ዜጎችን እያሰረ ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል የአማራ ክልል የፀጥታ ዘርፍ አመራሮች፥ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮች እና አባላት፥ በጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ የሚመራው የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) አመራር አባላት፥ ጋዜጠኞች እና የፀጥታ ዘርፍ አባላት እና ሰኣላማዊ ጄጎች በጅምላ መታሰራቸው ታውቋል። እስካሁን ባለው መረጃ ከ300 በላይ ዜጎች በጅምላ እንደታሰሩ መረጃዎች ቢጠቁሙም፤ ሌሎች ምንጮች ደግሞ የእስካሁኑ የጅምላ እስር በሺህዎች የሚቆጠር እንደሚሆን ይገምታሉ። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ሰዎች በማኀበራዊ ሚዲያ ላይ መንግሥት የአማራ ማኅበረሰብ ልሂቃን ላይ ያነጣጠረ የጅምላ እስር እየተፈፀመ ነው ሲሉ የኮነኑት ሲሆን መንግሥትም በግፍ በጅምላ ያሰራቸውን ዜጎች እንዲፈታ፥ ያለውን እውነታም ለህዝብ ግልፅ እንዲያደርግ ተጠይቋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተገደሉ

(ዳጉ ሚዲያ) ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህርዳር ከተማ በስብሰባ ላይ የነበሩ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ በተፈጸመ ጥቃት የክልሉ ፕሬዘዳንት ዶ/ር አምባቸው መኮንን እና የማኀበራዊ ዘርፍ አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴን ጨምሮ ቁጥራቸው ያልተገለጸ ጠባቂዎቻቸውም ሲገደሉ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሆኑት አቶ ምግባሩ ከበደ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል::

ዶ/ር አምባቸው መኮንን (ፎቶ፡ ከአማራ ቴቪ)

በተመሳሳይም በአዲስ አበባ

አቶ እዘዝ ዋሴ (ፎቶ፡ ከአማራ መገናኛ ብዙኃን)

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዡር ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና በጡረታ ላይ የነበሩት የቀድሞ የስራ ባልደረባቸውና የሰራዊት የሎጀስቲክ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት ሜጀር ጀነራል ገዛዒ አበራ
በጀነራል ሰዓረ መኖሪያ ቤት እያሉ በኢታማዡሩ ጠባቂ መገደላቸውን መንግሥት አረጋግጧል:: ድርጊቱን ያወገዙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) በተለይ የባህር ዳሩን የባለሥልጣናት ግድያ ጥቃት “በአማራ ክልል የተፈጸመ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መሆኑና መክሸፋን” ገልፀዋል::

 

ነገር ግን እስካሁን ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም መንግሥት በበኩሉ “ጥቃቱን የመሩትና ያቀናበሩት የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ኃላፊ ብርጋዴየር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ናቸው::” ቢልም ከገለልተኛ አካልም ሆነ በስም የተጠቀሱት ተጠርጣሪ ብርጋዴየር ጀነራል አሳምነው የተሰጠ ማረጋገጫም የለም:: ከጥቃቶቹ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከመከላከያ ሰራዊት ሹማምንት ግድያ ጋር በተያያዘ የጀነራል ሰዓረ መኮንን ታማኝ የግል ጠባቂያቸውና ሌሎች የመከላከያ ሰራዊት ተጠርጣሪ የጦር መኮንኖች በቁጥጥር ስር ውለዋል::

ጀነራል ሰዓረ መኮንን (ፎቶ፡ ከኢቴቪ)

ከአማራ ክልል አመራሮችና ጠባቂዎቻቸው ግድያ ጋር በተያያዘ የክልሉ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ እና የፖሊስ ኮሚሽኑ ኮምሽነር አበረ አዳሙ ተጠርጥረው በፌደራል ፖሊስ እና በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መዋላቸው የተሰማ ሲሆን በቀዳሚነት ተጠርጥረው ስማቸው የተነሳው ብርጋዴየር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ይህ እስከተጠናቀረበት ድረስ በቁጥጥር ስር እንዳልዋሉና ያሉበትም እንዳልታወቀ ተጠቁሟል::

ሜጀር ጀነራ ገዛዒ አበራ (ፎቶ፡ ከኢቴቪ) 

የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎችም ጥቃቶቹን በመኮንንና በማውገዝ ህዝቡ እንዲረጋጋ እንዲሁም በጋራ አንድነቱን እና ሰላሙን እንዲያስጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል:

%d bloggers like this: