Tag Archives: Bahir Dar

የሰኔ 15 ቀን ጥቃት ሰለባ አመራሮች የቀብር ስነ ሥርዓት ተፈፀም

(ዳጉሚዲያ) ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህርዳር እና አዲስ አበባ በተፈፀሙ ጥቃቶች ሰለባ የሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች መካከል የአማራ ክልል ፕሬዘዳንት ዶ/ር አምባቸው መኮንን፥ የክልሉ አደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ እንዲሁም በአዲሴ አበባ የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዡር ሹም የነበሩት ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና ከአንድ ዓመት በፊት በጡረታ የተሰናበቱት ሜጀር ጀነራል ገዛዒ አበራ በዕለቱ ተገድለዋል። በዕለቱ በአማራ ክልል በደረሰው ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩት የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የነበሩት አቶ ምግባሩ ከበደ የህክምና ዕርዳታ ቢደረግላቸውም ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ በጥቃቱ መንግሥት ጠርጥሬያቸዋለሁ ያላቸው የክልሉ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ብርጋዴየር ጀነራል አሳምነው ጽጌ በፌደራል ፖሊስና መከላከያ በተወሰደባቸው ወታደራዊ ጥቃት ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. መገደላቸውን መንግሥት አስታውቋል።

Amhara regiona victim leaders
ዶ/ር አምባቸው መኮንን፥ ብጀነራል አሳምነው ጽጌ፥ አቶ ምግባሩ ከበደ እና አቶ እዘዝ ዋሴ (ፎቶ፡ ከማኀበራዊ ሚዲያ)

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት በአዲስ አበባ በጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጀነራል ገዛዒ አበራ ግድያ ግድያ ተጠርጣሪው የጀነራል ሰዓረ መኮንን የግል ጠባቂ የአስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ነው ሲል ይፋ አድርጓል። ይሁን እንጂ ተፈፀሙ ለተባሉ ጥቃቶች መንግሥት “መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው” በሚል ለዓለም ይፋ ቢያደርግም የጥቃት አድራሾችን፥ ጥቃቱን እና ምክንያቱን በተመለከተ ርስ በርሱ የተጣረሰ የአንድ ወገን መረጃ ብቻ በመሆኑ ይህ እስከተጠናቀረበት ድረስ ሁኔታውን በተመለከተ ከጥቃቱ ተርፈናል ከሚል አራት የአማራ ክልል አመራሮች በስተቀር ከተጠርጣሪዎችም ሆነ ከገለልተኛ አካል የተሰጠ ምላሽም ሆነ ማረጋገጫ የለም። ጥቃቱን ተከትሎ ከከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ግድያ በተጨማሪ ቁጥራቸው ያልተገለፀ ሌሎችም በርካታ ዜጎች መገደላቸውንም የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰማኽኝ አስረስ ለሮይተርስ ገልፀዋል።

በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈ አመራሮች ዶ/ር አምባቸው መኮንን፥ አቶ ምግባሩ ከበደ እና አቶ እዘዝ ዋሴ ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ ም በባህርዳር ከተማ አባይ ማዶ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው የተፈፀመ ሲሆን፤ የብርጋዴየር ጀነራል አሳምነው ጽጌ በትውልድ ከተማቸው በላሊበላ አብያተ ቤተክርሥቲያናት በቤተ ጊዮርጊስ የቀብር ስፍራ ተፈፅሟል። በተመሳሳይም ጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀን የጀነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጀነራ ገዛዒ አበራ የቀብር ሥነሥርዓት በመቀሌ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።
General Seare and M.General Gezae
ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜ/ጀነራል ገዛዒ አበራ (ፎቶ፡ ከማኅበራዊ ሚዲያ)

የአመራሮችን ግድያ እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ቢያሳውቅም፤ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ የወታደራዊ የኃይል ርምጃ የተገደሉ በርካታ ዜጎች ቢኖሩም መንግሥት እስካሁን ቁጥራቸውንም ሆነ ማንነታቸውን አልገለፀም። መንግሥት ቀደም ሲል ጥቃቱን “መፈንቅለ መንግሥት ነው፥ የአዲስ አበባው ከባህርዳሩ ጥቃት ጋር የተያያዘ ነው” በሚል በጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ኃላፊዎች እና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ የተገለፀ ቢሆንም፤ ዛሬ ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ ም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ቢልለኔ በበኩላቸው “የአዲስ አበባው ከባህር ዳሩ ጥቃት ጋር ስለመያያዙ ገና ይጣራል።” ሲሉ ገልፀዋል። በተለይ የባህርዳሩን እና የአዲስ አበባውን የባላሥልጣናት ግድያ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ቃል አቀባይ ኃላፊዎች እና ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ የሰጡት መግለጫዎች ርስ-በርስ የሚጣረሱ በመሆናቸው፤ መንግሥት እየሰጠ ያለው መረጃ ተዓማኒነት ላይ በርካቶች ጥርጣሬ እንዳላቸው እየገለፁ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበኩሉ በመተከል ዞን ሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ ም ከ 30 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን ይፋ አድርገዋል።

መንግሥት ባህርዳሩን እና የአዲስ አበባውን ጥቃት ተከትሎ በርካታ ዜጎችን እያሰረ ሲሆን፤ ከነዚህ መካከል የአማራ ክልል የፀጥታ ዘርፍ አመራሮች፥ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮች እና አባላት፥ በጋዜጠኛ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ የሚመራው የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) አመራር አባላት፥ ጋዜጠኞች እና የፀጥታ ዘርፍ አባላት እና ሰኣላማዊ ጄጎች በጅምላ መታሰራቸው ታውቋል። እስካሁን ባለው መረጃ ከ300 በላይ ዜጎች በጅምላ እንደታሰሩ መረጃዎች ቢጠቁሙም፤ ሌሎች ምንጮች ደግሞ የእስካሁኑ የጅምላ እስር በሺህዎች የሚቆጠር እንደሚሆን ይገምታሉ። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ሰዎች በማኀበራዊ ሚዲያ ላይ መንግሥት የአማራ ማኅበረሰብ ልሂቃን ላይ ያነጣጠረ የጅምላ እስር እየተፈፀመ ነው ሲሉ የኮነኑት ሲሆን መንግሥትም በግፍ በጅምላ ያሰራቸውን ዜጎች እንዲፈታ፥ ያለውን እውነታም ለህዝብ ግልፅ እንዲያደርግ ተጠይቋል።

በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም የተቀሰቀሰው እሳት በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተሰማ

  • ቃጠሎው ለአትክልት ልማት ከተደረገ ምንጣሮ ጋራ የተያያዘ መኾኑ ተጠቁሟል
ጣና ሐይቅ ዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም የሚገኝበት ደሴት

ጣና ሐይቅ ዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም የሚገኝበት ደሴት

በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ደን ውስጥ ዛሬ፣ ጥር 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ከረፋዱ 4፡30 ላይ የተቀሰቀሰው እሳት በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለጸ፡፡

ቃጠሎው በቁጥጥር ሥር የዋለው ከቤተ ክርስቲያኑ በግምት ከመቶ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ በደረሰበት ኹኔታ ነው ብለዋል – እሳቱን በማጥፋት የተራዱ የዐይን እማኞች፡፡

የዳጋ እስጢፋኖስን ጨምሮ ከሌሎች የደሴቱ ገዳማት የመጡ መነኰሳት፣ የአቅራቢያው ነዋሪዎች፣ ከባሕር ዳር ከተማ በጀልባ ተጓጉዘው የደረሱ ምእመናን፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሓላፊዎች፣ የባሕር ዳር ዙሪያ ፖሊስና ልዩ ኃይል በጋራ ቃጠሎውን በማጥፋት ከፍተኛ የጋራ ርብርብ ማድረጋቸው ተገልጧል፡፡

የቃጠሎው ትክክለኛ መንሥኤ እስከ አኹን በይፋ ባይረጋገጥም፣ መሬቱን ለጌሾ ልማት ዝግጁ ለማድረግ በአንድ የገዳሙ መነኰስ የተለኰሰው እሳት በአቅራቢያው በብዛት በሚገኙት የሐረግ ተክሎችና ሸምበቆዎች መቀጣጠሉ እንደኾነ ማኅበረ መነኰሳቱን ያነጋገሩ የዐይን እማኞች ገልጸዋል፡፡

በገዳሙ ከሚገኙት ታላላቅ አገር በቀል ዛፎች ይልቅ በብዛት ተቃጥለው የሚታዩትም የሐረግና የሸምበቆ ተክሎቹ ናቸው – ‹‹አንድ አባት ጌሾ የሚያለሙበት አካባቢ ሐረግ ነበር፤ እርሱን ለማቃጠል ሲለኩሱት እሳቱ አሸንፎ ወጣ፤ ለማጥፋትም ከመነኰሳቱ አቅም በላይ ኾነ፡፡››

ጣና ሐይቅ ደሴት ላይ የሚገኘው ዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም

ጣና ሐይቅ ደሴት ላይ የሚገኘው ዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም

በአኹኑ ወቅት በስፍራው ከሚታየው ጢስና የተዳፈነ እሳት ጨርሶ መጥፋቱን ለማረጋገጥ ከሚደረግ እንቅስቃሴ በቀር የእሳት ቃጠሎው ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ከዓይን እማኞች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በጣና ሐይቅ ውስጥ ከደቅ ደሴት በስተምሥራቅ የሚገኘው የዳጋ እስጢፋኖስ የደሴት ገዳም የተመሠረተው በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ  ሲኾን መሥራቹም የዐፄ ይኩኖ አምላክ ወንድም አቡነ ሂሩተ አምላክ ናቸው፤ የተገደመውም በዐፄ ይኩኖ አምላክ እንደኾነ የገዳሙ አበው ይተርካሉ፡፡

በበርካታ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት ማእከልነቱ የሚታወቀው ዳጋ እስጢፋኖስ÷ የመሥራቹ የአቡነ ኂሩተ አምላክ መቋሚያ፣ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የተሣለች የእመቤታችን ምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕል፣ ብዛት ያላቸው የወርቅ፣ የብርና የነሐስ መስቀሎች ጨምሮ የዐፄ ዳዊት፣ የዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ፣ የዐፄ ሱስንዮስ፣ የዐፄ ፋሲልና ሌሎች ነገሥታት አዕፅምት፤ ዘውዶች፣ አልባሳት፣ ሰይፍና ጎራዴ የመሳሰሉ የነገሥታቱ የክብርና የወግ ዕቃዎች ተጠብቀው ይገኙበታል፡፡

የማኅበረ መነኰሳቱ ዋነኛ መተዳደርያ በተለያየ መንገድ ከሕዝብ የሚገኘው ድጋፍ ቢኾንም ቡና፣ ጌሾ፣ ሙዝና ፓፓዬ የመሳሰሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማምረትም የገዳሙን አገልግሎት ይደጉማሉ ሲል የ ”ሐራ ዘተዋህዶ” ዘገባ አመልክቷል፡፡

%d bloggers like this: