Tag Archives: PM Abiy Ahmed

የተራራቁት የለውጥ ዕይታዎች

Ethiopian politics ECA August 2019

ነአምን አሸናፊ

ሐሙስ ነሐሴ 16 እና ዓርብ ነሐሴ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የስብሰባ ማዕከል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው የፖለቲካና የአካዳሚክ ልሂቃን በአገሪቱ ጅመር የለውጥ ሒደት፣ ዕድሎች፣ ፈተናዎችና ሥጋቶች ላይ የሁለት ቀናት ውይይት አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ለሁለት ቀናት በቆየው ውይይት መድረክ ላይ በለውጡ ዙሪያ የተለያየ ሐሳቦች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ በተለይ በሁለተኛ ቀን ውሎ ሦስት ፖለቲከኞችን በአንድ መድረክ ያገናኘው ውይይት የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡ በሁለተኛው ቀን ውይይት ሐሳባቸውን ያጋሩት ተወያዮች በለውጡ ላይ ያላቸውን አተያይ ያስረዱ ሲሆን፣ የግለሰቦቹ ምልከታ በራሱ በለውጡ ላይ አንድ ወጥና ተመሳሳይ አቋም፣ እንዲሁም አረዳድ ላይ አለመደረሱን አመላካች ነበሩ፡፡ በምሥሉ ላይ ከግራ ወደቀኝ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ጌታቸው ረዳና አቶ ልደቱ አያሌው ከአወያያቸው ወ/ሮ ፀዳለ ለማ ጋር ይታያሉ፡፡

ለውጡን አስመልክቶ ያሉ አተያዮች

ሐሙስ ነሐሴ 16 እና ዓርብ ነሐሴ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ተሳታፊ የሆኑ ፖለቲከኞችና በፖለቲካ ሒደቱ ላይ የተለያዩ ምርምሮችን ያካሄዱና ጽሑፎችን ማቅረብ የቻሉ ምሁራን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ቅጥር ግቢ ውስጥ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የተከሰተውን ለውጥ አስመልክቶ ለመወያየትና አሁን ያለበትን ደረጃና ፈተናዎች ለመተንተን ለስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡

ይህን የውይይት ኮንፈረንስ ያዘጋጁት ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ፣ የምክክር የጥናትና ትብብር ማዕከል፣ አማኒ አፍሪካ፣ ቤርጎፍ ፋውንዴሸን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ማዕከል ሲሆኑ፣ የሁለት ቀናቱን የውይይት መድረክ በንግግር የከፈቱት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ነበሩ፡፡

ከ1960ዎቹ የፖለቲካ ተዋንያን አንስቶ እስከ ቅርብ ጊዜ እስከ ተመሠረቱት ፓርቲ አባላትና አመራሮች በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ አንጋፋ ምሁራን እንዲሁ ‹‹የኢትዮጵያ የለውጥ ሒደት ወቅታዊ ቁመናው፣ መፃኢ ዕድሎቹ፣ ፈተናዎቹና ሥጋቶቹ›› በሚል ርዕስ ለተዘጋጀው መድረክ የልምዳቸውን ለማካፈል ተሰይመዋል፡፡

ከእነዚህ የአገር ውስጥ ምሁራንና ፖለቲከኞች በተጨማሪም፣ የዓለም አቀፍ የለውጥ ተሞክሮዎችን ለማውሳትና ልምዳቸውን ለማካፈል የውይይቱ አካል ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት በቱኒዚያ ሕዝባዊ አመፅ ማግሥት በተቋቋመው ሕዝባዊ የውይይት ምክር ቤት አባል የነበሩ፣ የየመን ሕዝባዊ የውይይት ምክር ቤት አባል የነበሩ ሁለት ተወካዮች በለውጥ ሒደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን እንዴት መፍታት እንደሚቻልና እንደሚገባ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሽግግር አስተዳደር ጋር በተያያዘ በርካታ ምርምሮችን ያደረጉት ማይክል ሉንድ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ምንም እንኳን በመጀመርያው ቀን የውይይቱ ውሎ ለውይይቱ ከተሰጠው ርዕስ አንፃር የለውጡን ፈተናዎች፣ ተግዳሮቶችና መልካም ዕድሎችን አስመልክቶ በዝርዝር የቀረበ የውይይት ሐሳብ ባይኖርም፣ በታዋቂው የታሪክ ምሁር ገብሩ ታረቀ (ፕሮፌሰር) አወያይነት፣ እንዲሁም በሌላው ታዋቂው የታሪክ ምሁር ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) እና የቀድሞው የመኢሶን መሥራችና መሪ በነበሩት በአቶ አንዳርጋቸው አሰግድ መነሻ ሐሳብ አቅራቢነት ኢትዮጵያ ያመከነቻቸውን የለውጥ ዕድሎች አስመልክቶ ገለጻና ውይይት ተደርጓል፡፡

የመጀመርያ ዕለት ውሎ በእነዚህ አጠቃላይ ሐሳቦችና ጉዳዮች ሲወያዩና ውይይቱን ሲያዳምጡ የነበሩ ተሳታፊዎች፣ በሁለተኛው ቀን ግን አሁን አገሪቱ ካለችበት የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር አንገብጋቢ የሆኑ ጉዳዮች የተዳሰሱበት የሦስት ፖለቲከኞችን ውይይት በተመስጦ አዳምጠዋል፡፡ ከማዳመጥ ባለፈም የምሣ ሰዓትን እስከ መግፋት የደረሰ ጥያቄና መልስ፣ ውይይትና ሙግት አካሂደዋል፡፡

በሁለተኛው ቀን የከፍተኛ ፖለቲከኞችና ምሁራን ውይይት በለውጡ ወቅታዊ ቁመና፣ ፈተናዎቹና ዕድሎቹ ዙሪያ ያላቸውን አተያይ እንዲያቀርቡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እና የዝሕባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባና ታዋቂውን ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌውን በመድረኩ ሰይሟል፡፡

እነዚህ ሦስት ፖለቲከኞች ከሚወክሉት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አንፃር፣ ለውጡን አስመልክቶ ሊለዋወጡ የሚችሉት ሐሳብ ከመጀመርያው ቀልብን የሳበ ነበር፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በአገሪቱ እየተካሄደ ባለው ለውጥ ምንነት ዙሪያ ሦስቱም ሐሳብ ሰንዛሪዎች የተለያየ አረዳድ እንዳላቸው የገለጹ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ግን ሒደቱ በጀመረበት ፍጥነት ካለመጓዙም በላይ ሊቀለበስ እንደሚችል ሥጋታቸውን አጋርተዋል፡፡ ሆኖም ሦስቱም ተናጋሪዎች አሠራሮችን ዳግም ለማየት ከተሞከረ ሒደቱን ከመቀልበስ አደጋ መታደግም እንደሚቻል አውስተዋል፡፡

ለውጡን ለመተርጎም በመሞከር ንግግራቸውን የጀመሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ለውጥ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ላይ በሒደቱ ተዋናይ የሆኑት ቡድኖች ወጥ ትርጓሜ እንደሌላቸው አውስተዋል፡፡ ለዚህም በምዕራባውያን ስለለውጡ የሚሰጠው ትርጓሜና በኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች ዘንድ የሚሰጠው ትርጓሜ ለየቅል መሆኑን በማውሳት ነው፡፡

‹‹የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት በሚሉ በጣም አጓጊ ቃላት የሚታጀብ ቢሆንም፣ በዋነኛነት የምዕራባውያን የለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ተቋማትን ወደ ግል ይዞታ ብቻ ሳይሆን ወደ ምዕራባውያን የግል ይዞታ ከማዞር አንፃር ብቻ ነው የሚያዩት፤›› በማለት፣ የምዕራባውያንን አረዳድ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ደግሞ፣ ‹‹በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች የራሳቸው ውስንነት ቢኖራቸውም ለውጥ ሲሉ የፖለቲካ ምኅዳር መስፋትን፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጠናከርን፣ በግለሰብና በቡድን ነፃነትና መብቶች መካከል ያለውን ሚዛን መጠበቅ፣ አገራዊ ማንነትና ብሔራዊ ማንነትን ማመጣጠን የሚሉ በርካታ ነገሮችን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፤›› በማለት፣ በአገራዊውና በውጭው ኃይሎች መካከል ያለውን የጉዳዩን አረዳድ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር እነዚህ ውስንነት ያሉበትን ጽንሰ ሐሳብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደተፈታና ስምምነት እንደተደረሰበት አድርጎ ማቅረቡ በራሱ ችግር አለበት በማለት፣ በጉዳዩ ላይ የጠራ አቋም መያዝ አስፈላጊነት ላይ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አቶ ጌታቸው የለውጡ ባለቤትነት ጥያቄ ያስከተላቸው ውዥንብሮች በራሱ የለውጡ ተግዳሮት እንደሆነ በመግለጽ፣ በዋነኛነት ግን ለውጡ የኢሕአዴግ ነው በማለት በተለያዩ መድረኮች በተደጋጋሚ የሚገልጹትን አቋማቸውን በዚህ መድረክም አራምደውታል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም፣ ‹‹አመራሩ በጋራ አንድ ላይ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ ሲያበቃ በተወሰኑ የአመራር አካላት ግን ለውጡ የእኔ ነው ወደሚል ሁኔታ ተሂዷል፡፡ ስለዚህ ለውጡ የማን ነው የሚለው ጥያቄ ችግር ያለበት ነው፡፡ እዚህ መግለጽ ካለብን ለውጡ የሕዝብ ጥያቄ ያመጣው፣ ግን ደግሞ ኢሕአዴግ በሕዝብ ግፊትም ቢሆን ተገዶ ይህን ካላደረግኩ በስተቀር አገር ይፈርሳል ብሎ አምኖ የተቀበለው ነው፤›› ተብሎ መወሰድ እንዳለበት ሞግተዋል፡፡

ለውጡ የሕዝቡ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው የለውጡ ችግሮች ያሏቸውን ሐሳቦችም አያይዘው አቅርበዋል፡፡ ከነዚህ ችግሮች መካከል ለውጡ ኢሕአዴግን እንደ ፓርቲ ማግለሉ፣ የአመራሩ እውነታን መሸሽ፣ በየሥፍራው የታጠቁ ኃይሎች መበራከት፣ እንዲሁም ድሮም ጠንካራ ያልነበሩት ተቋማት ከለውጡ ወዲህ ይበልጥ መልፈስፈሳቸውን እንደ ችግር በመጥቀስ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳም፣ ‹‹አሁን ባለንበት ሁኔታ ለውጡ ፈተና ውስጥ የገባ ነው የሚል እምነት አለኝ፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ ለውጥ መደረግ አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ከአሁን በፊት የሠራቸው ጥፋቶች መቀጠል አለባቸው የሚል ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው የለም፡፡ ነገር ግን መልካም ነገሮችን አስቀጥሎ ለአገር ህልውና ቀጣይነት በሚያግዝ መንገድ ለውጥ መደረግ አለበት ብሎ መሥራት አንድ ነገር ነው፡፡ ኢሕአዴግን ወደ ጎን አድርገህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ስምና ዝና ላይ የተመሠረተ ለውጥ ለማድረግ መንቀሳቀስ፣ አማራጭ የፖለቲካ አስተሳሰብ ባስቀመጥክበትና በቅጡ የተተረጎመ ጽንሰ ሐሳብ እየመራህ ባለህበት ሁኔታ አሁን በምናየው ደረጃ ለውጡን ማስቀጠል ሳይሆን፣ አገር ትርምስ ውስጥ የሚከት ነገር ውስጥ ነው የሚከተን፤›› ብለዋል፡፡

እነዚህን ሥጋቶች ለማስወገድና ቅቡልነት ያለው መንግሥት እንዲመሠረት ደግሞ የመጪው ዓመት ምርጫ መካሄድ አለበት በማለት አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን፣ ‹‹የኢትዮጵያን ሕዝብ አምነን ቢቻል በወቅቱ ካልሆነ እንዲያውም አስቸኳይ (Snap) ምርጫ ማድረግ አለብን፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

ብዙ የማያግባቡ የታሪክ ሰበዞች እንዳሉ በመጥቀስ ንግግራቸውን የጀመሩት አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው ደግሞ፣ ‹‹ምንም እንኳን የማያግባቡን በርካታ የታሪክ ክስተቶች ቢኖሩም ቢያንስ ግን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያለማወቃችን፣ ራሳችን በመረጥነው መንግሥት ተዳድረን አለማወቃችንና የመሳሰሉት ነገሮች የሚያግባቡን የታሪክ ሰበዞቻችን ይመስሉኛል፤›› በማለት፣ አሁንም አገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን ሁኔታ ከታሪካዊ ዳራው ጋር እያያያዙ አብራርተዋል፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት ግፍ ያልተፈጸመበት የአገሪቱ ክልል የለም ያሉት አቶ በቀለ፣ የግፉ ደረጃ ግን ከሥፍራ ሥፍራ እንደሚለያይ በመጥቀስ በተለይ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ከመሬት ጋር በተያያዘ ጥያቄና አመፅ በመላው ኦሮሚያ በመቀስቀሱ፣ እንዲሁም ይህንና መሰል ጥያቄዎች በአማራ ወጣቶች ዘንድ መፈጠራቸውና በገዥው ፓርቲ ውስጥም ለውጥ ያስፈልጋል የሚሉ አመራሮች መፈጠራቸው፣ አሁን ላለው አጠቃላይ አገራዊ ለውጥ አስተዋጽኦ ማድረጉን አትተዋል፡፡

በገዥው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረው የአሠላለፍ ለውጥ በርካታ ትሩፋቶች ማስከተሉን በዝርዝር ገልጸው፣ የእስረኞች መፈታትን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ቃል መገባቱን፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ መቆሙን ማወጅ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ መደረጉን እንደ ምሳሌ ጠቃቅሰዋል፡፡

ይህን ጊዜ የጫጉላ ሽርሽር ጊዜ በማለት በመጥቀስ በተለይ ከውጭ አገር የገቡ ፓርቲዎች ያራመዷቸው አንዳንድ አቋሞች መፈጠር ሲጀምሩ፣ የለውጥ እንቅስቃሴው እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አገሪቱ አሁን ቅርቃር ውስጥ መግባቷን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

‹‹አገሪቱ አሁን በሁለት ጽንፎች መካከል ተወጥራ የምትገኝ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በፊት ያልተሞከረውን ሁሉን ነገር አጥፍተንና አውድመን እንደ አዲስ ከመጀመር አባዜ ወጥተናል ብለን ተስፋ ባደረግንበት ወቅት፣ አሁን ደግሞ ወደዚያ ሊመልሱን የሚችሉ አዝማሚያዎች እየታዩ ነው፡፡ አንደኛው የሌላውን ሐሳብ ለመቀበል ፈጽሞ ያለ መፈለግና የእኔ ብቻ ነው ትክክል የማለት፣ ቁጭ ብሎ ለመደራደርና ለመነጋገር ያለ መፈለግ አዝማሚያዎች እጅግ በጣም እየገነገኑ መጥተዋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

እነዚህ ሁኔታዎችም ለውጡን እየመሩ ላሉ ኃይሎች ከባድ ችግር መፍጠራቸውን በመጥቀስ፣ ‹‹ለውጡ ማዝገም ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላ እየተንሸራተተ ያለበት ሁኔታ ነው የሚታየኝ፤›› ብለዋል፡፡

ለውጡ ወደ ኋላ ስለመጓዙ ያቀረቡት መከራከሪያና ምክንያት ደግሞ ከዚህ ቀደም የተቃውሞ ምንጭ የነበረው የመሬት ዘረፋ ተስፋፍቶ እየተከናወነ መሆኑ፣ የሕዝብ መፈናቀል፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎችን ማሰር መቀጠሉን፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶች መታፈን መጀመራቸው፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብቶች መገደብ የሚሉትን ነው፡፡ ‹‹ስለዚህ ወደ ቀደመው ሥርዓት እየተመለስን መሆናችን በግልጽ እየታየ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

‹‹ስለሆነም ያሉንን ተቋማት ወደ ማደራጀት እንጂ አዲስ ተቋም ለመገንባት መሯሯጥ የለብንም፤›› ብለው፣ እነዚህን የመሳሰሉ ሥራዎች ምርጫውን በጊዜው በማካሄድ የሚመረጠው መንግሥት በሒደት ሊሠራው ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡

በአገሪቱ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል የተከሰተውን ለውጥ በተመለከተ ያለፉት 27 ዓመታት የአገሪቱ የፖለቲካ ትግል መዘንጋት እንደሌለበት በመግለጽ ሐሳባቸውን መስጠት የጀመሩ አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፣ ‹‹የማስታወስ ችግር ስላለብን ነው እንጂ ለውጡ ላለፉት ሰባት ዓመታት የተደረገ ትግል ውጤት ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹አንዱና ትልቁ የለውጡ ጉድለት ውለታ ቢስ መሆኑ ነው፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን በዋነኛነት በአገሪቱ የተከሰተው ለውጥ የአገሪቱን መሠረታዊ የፖለቲካ ቅራኔ መፍታት አለበት የሚል አቋም እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ የአገሪቱ መሠረታዊ የፖለቲካ ቅራኔ የሚመነጨው ከሕገ መንግሥቱ እንደሆነ ገልጸው፣ ሕገ መንግሥቱ አገሪቱን ያፈራርሳታል በሚል፣ የለም ሕገ መንግሥቱ በፓርቲ ማዕከላዊነት ተጠለፈ እንጂ የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ የሚመልስ ነው በሚል እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

‹‹እነዚህ ጥያቄዎች እስካለፈው አንድ ዓመት ተኩል ድረስ መሠረታዊ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ አንድ ለውጥ መመዘን ያለበት እነዚህን መሠረታዊ ቅራኔዎች ለማስታረቅ በሚሄደው ርቀት ነው፤›› በማለት፣ ለውጡን በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ መመልከት ተገቢ መሆኑንና መመዘን ያለበትም በዚህ መሥፈርት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን በአገሪቱ ካለፉት አንድ ዓመት ተኩል ጀምሮ እየተተገበረ ያለውን ለውጥ ጠንካራ ጎኖች አውስተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል በአንፃራዊነትም ቢሆን ትግሉ የሰላማዊ ትግል ውጤት መሆኑ፣ በመጣበት ወቅት ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኝቱ፣ ገዥው ፓርቲ እስከ መጨረሻው ድረስ ከመጋፈጥ ይልቅ ሽንፈቱን መቀበሉና ይቅርታ መጠየቁ፣ እንዲሁም የለውጡ መሪዎች ሆነው ብቅ ያሉት ወጣቶች መሆናቸው የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡

ነገር ግን እነዚህን ጠንካራ ጎኖች ወይም ትሩፋቶች የያዘው ይህ ለውጥ፣ አሁን ግን የመቀልበስ አደጋ ተጋርጦበታል በማለት እሳቸውም እንደ ቀዳሚ ተናጋሪዎች ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ምንም እንኳን ይህ ለውጥ የረፈደበት ቢሆንም የመሸበት አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም አዲስ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት አለብን፤›› ሲሉ፣ አዲሱ የለውጥ እንቅስቃሴ ደግሞ ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ሊጀመር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የለውጥ ሒደቱን የሚመራ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ድርሻ ደግሞ የሁሉም የኢትዮጵያ ኃይሎች እንደሆነ በመጥቀስ፣ ‹‹ይህን ለማድረግ ግን ቀጣዩ ምርጫ መራዘም አለበት፤›› በማለት ሞግተዋል፡፡

‹‹ይህን ሳናደርግ ወደ ምርጫ ብንገባ ምናልባት በኢትዮጵያ ታሪክ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ያደረገችው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ያደረገችው ምርጫ እንዳይሆን እሠጋለሁ፤›› በማለት ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

ባለፉት አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የተካሄደውን ለውጥ አስመልክቶ በአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ ጽንሰ ሐሳቡን ከመረዳት ጀምሮ እስከ ውጤቱ ድረስ፣ የተለያዩና ጽንፍ የያዙ አተያዮች የተስተናገዱበት ይህ መድረክ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማስተናገድ ተጠናቋል::

Ethiopian Reporter

የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ቤቶችን የማፍረስ ዕርምጃና የተፈናቃዮች ጩኸት

ሻሂዳ ሁሴን

በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ከማስተር ፕላን ውጪ ተገንብተዋል የተባሉ ከ12,000 በላይ ቤቶች እንዲፈርሱ መወሰኑና ቤቶቹም መፍረስ መጀመራቸው ውዝግብ አስነስቷል፡፡ እስካሁን በከተማው በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ማለትም ቀበሌ 03 የካ ዳሌና ቀበሌ 01 አባ ኪሮስ በመባል በሚታወቁ ሥፍራዎች ከ930 በላይ የሚሆኑ ቤቶች መፍረሳቸው ተነግሯል፡፡ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የተሰጣቸው የማስጠንቀቂያ ጊዜ አጭር መሆኑን፣ እየፈረሱ ያሉትም የተመረጡ ቤቶች ናቸው ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ ካርታ ለማግኘት ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ቤቶች እየፈረሱ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ገልጸዋል፡፡ ድርጊቱንም የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ እንዲያስቆሙ ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው፣ ሕገወጥ ግንባታዎችን የማፍረስ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

Legetafo_social crises 2019 በገለጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር እንዲፈርሱ ከተወሰነባቸው ከ12,300 በላይ ቤቶች ውስጥ አንዱ

ሪፖርተር በሥፍራው ተገኝቶ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ሜዳ ላይ መበተናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ በቀበሌ 03 የመፍረስ ዕጣ ከገጠማቸው ቤቶች የአንዱ ይህንን ይመስላል፡፡

ሦስት ክፍሎች ያለው ቤት ግድግዳው በከፊል ፈርሷል፡፡ ጣራውም ሙሉ ለሙሉ ተነስቷል፡፡ በርና መስኮትም የለውም፡፡ ሊወድቅ ቋፍ ላይ የደረሰውን የጭቃ ግድግዳ ተደግፎ ከቆመው መሰላል ውጪ ምንም አይታይም፡፡ ከወንዝ ዳርቻ የተሠራው ቤት ወደ ፍርስራሽነት የተቀየረው ዕድሜ ተጭኖት ወይም የቦምብ ፍንጣሪ መትቶት አይደለም፡፡ ሕገወጥ ግንባታ ነው ተብሎ በአፍራሽ ግብረ ኃይል በትዕዛዝ የፈረሰው ረቡዕ ረፋዱ ላይ ነበር፡፡

‹‹ጠላ ሸጬ ነው ቤቱን የሠራሁት፤›› የሚሉት ወይዘሮ ግን ቤቱ ከፈረሰ ሰዓታት ያለፉት ቢሆንም አልተፅናኑም፣ ከድንጋጤያቸውም አልተላቀቁም፡፡ ‹‹ሕገወጥ›› የተባለው ቤታቸው እንደሚፈርስና ንብረታቸውን እንዲያወጡ የሚገልጽ ደብዳቤ የደረሳቸው ቅዳሜ የካቲት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሰዓቱ ደብዳቤውን የተቀበለችው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የምትማር ልጃቸው በድንጋጤ መታመሟን፣ እስካሁንም እንዳልተሻላትና ወደ ትምህርት ገበታዋ እንዳልተመለሰች ሲናገሩ እያነቡ ነው፡፡ ‹‹ለነገሩ ደንዳና ነኝ፤›› የሚሉት ወይዘሮዋ ቢሆኑም፣ አፍራሽ ግብረ ኃይሉ ግድግዳውን በላያቸው መናድ ሲጀምር ራሳቸውን ስተው እንደ ነበር ይናገራሉ፡፡ መናገርና መስማት አትችልም የሚሏት ትንሽ ልጃቸው ቤታቸውን እያፈረሱ የነበሩትን ሰዎች ልብስ እየጎተተች ስትለምናቸው እንደበር የሰሙትም፣ ከወደቁበት ሲነሱ ሰዎች ነግረዋቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹ቤቱን ለቃችሁ ውጡ› የሚለው ደብዳቤ ሲደርሳቸው፣ ‹‹እውነት አልመሰለኝም ነበር፤›› ብለዋል፡፡ የተሰጣቸው የአራት ቀናት ቀነ ቀጠሮም አጭር ነበርና መፍትሔ ለማፈላለግም ሆነ ንብረታቸውን ለማውጣት በቂ ስላልነበረ፣ ከማስፈራሪያነት ያለፈ ሚና ይኖረዋል ብለው እንዳላሰቡ ተናግረዋል፡፡ ረቡዕ የካቲት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ረፋዱ ላይ አፍራሽ ግብረ ኃይሉ ግድግዳቸውን መናድ ሲጀምር ግን እያነቡ ከመለመን ባለፈ ንብረታቸውን ለማውጣት እንኳን ፋታ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

“ነገሮች ከአዕምሮዬ በላይ ራሴን ስቼ ወደቅኩ፤” ብለው፣ ወደ ራሳቸው ሲመለሱ ጠላ ሸጠው የገነቡት ቤት ወደ ፍርስራሽነት ተቀይሮ እንዳገኙት ተናግረዋል፡፡ የቀረላቸው ነገር ቢኖር በቆርቆሮ በር የሚዘጋው ትንሹ ኩሽናቸው ነው፡፡ በማንኛውም ሰዓት ሊያፈርሱት ይችላሉ ብለው በሚሠጉበት ኩሽናቸው ውስጥ አዳራቸውን ማድረጋቸውን፣ ከፍርስራሹ ውስጥ የወጣ ንብረታቸውን ደግሞ ቤታቸው እንደሚፈርስ ቀነ ቀጠሮ በተሰጣቸው ጎረቤቶቻቸው ቤት በታትነው ማስቀመጣቸውን አስረድተዋል፡፡

ባለትዳርና የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮዋ ያለ ወትሯቸው ሜዳ ለሜዳ ይዞራሉ፡፡ አፉን ከፍቶ የቀረ ቤታቸው የሚያርፉበት ባይሆንም ቤት እንዳለው ሰው ወደ ፍርስራሹ ያመራሉ፡፡ ‹‹ከእነ ልጆቼ ሜዳ ላይ ቀርቻለሁ፤›› አሉ ትንሽ ልጃቸውን አዝለው ወደ ተቆለለው ፍርስራሽ ላይ እየወጡ፡፡ በመንደሩ ተመሳሳይ ችግር የደረሰባቸው ብዙዎች ስለሆኑ እየዞሩ ሌሎችንም ያፅናናሉ፡፡

እንደ ወይዘሮዋ ሁሉ መውደቂያ ባያጡም ጎረቤታቸው ወ/ሮ መቅደስ ተሰማ ግን እውነታውን መቀበል ተስኗቸዋል፡፡ ‹‹ሊፈርስ ነው የሚባል ነገር ከሰማሁ ቀን ጀምሮ እንዳለቀስኩ ነው፡፡ ደብዳቤው ቅዳሜ ዕለት በእጃችን ሲገባ ያልሄድንበት ቦታ የለም፡፡ ነገር ግን ማንም የደረሰልን አካል የለም፡፡ የቀን ጨለማ ነው የሆነብን፡፡ ይኼንን ቤት ለመሥራት የለፋሁትን እኔ ነኝ የማውቀው፤›› አሉ ወደ ተከመረው ፍርስራሽ በእጃቸው እያመለከቱ፡፡

በአካባቢው ይኖሩ ከነበሩ ከአንድ ግለሰብ የገዙትን ቤት አድሰውና ባለው ትርፍ ቦታም ቤት ገንብተው ኑሮ ለመጀመር ነገሮች ቀላል አልነበሩም ይላሉ፡፡ በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥረው እንደሚሠሩና በወር የሚያገኙትም 3,000 ብር እንደማይሞላ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ያለው ሰው እኮ እዚህ አይኖርም፡፡ አማራጭ የሌለን ድሆች ነን እዚህ ገዝተን የምንገባው፤›› በማለት ዕንባቸውን አዘሩ፡፡

የፈረሰባቸውን መኖሪያ ቤት ለመሥራት ለዓመታት እንደተቸገሩ ይናገራሉ፡፡ ቆርቆሮ ለመምታት፣ ግድግዳ ለማቆም በወር ከሚያገኙት ላይ እየቆጠቡ ዕቁብ መጣል እንደነበረባቸው ያስታውሳሉ፡፡ የዋናው ቤት ግንባታው ባያልቅም ቀስ በቀስ ያልቃል በማለት ከአራት ዓመታት በፊት ገብተው መኖር እንደጀመሩም ያስረዳሉ፡፡ በአንዱ ዕቁብ በር፣ በሌላው ኮርኒስ እያሠሩ መደበኛ ቤት ለመሆን አንድ መስኮትና የፍሳሽ ማስወገጃ ሲቀረው፣ ሕገወጥ ግንባታ ተብሎ ረቡዕ ዕለት መፍረሱን ተናግረዋል፡፡ የቀራቸው ለተከራይ የሰጡት ሰርቪስ ቤት ቢሆንም፣ የቱ እንደሚፈርስና የቱ እንደሚቀር ስለማይታወቅ መጨረሻቸውን አላወቁም፡፡ “የዋናውን ቤት የተወሰነ ክፍል አፍርሰው ይኼ ቀርቶልሻል እጠሪው ካሉ በኋላ ነው ተመልሰው የቀረውን ሆ ብለው ያፈረሱት፡፡ አሁን ጭንቀት ሊገድለኝ ነው፡፡ የማይወለድ ልጅ ማማጥ ሆኖብኛል፤” አሉ እንደገና እያነቡ፡፡

አራት ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት እንዳለባቸው፣ ከዘራቸውን ተደግፈው የሚቆዝሙ ወላጅ አባታቸውን የማስተዳደር ኃላፊነትም የእሳቸው መሆኑን መኖሪያ ቤታቸው በላያቸው የፈረሰባቸው ወ/ሮ መቅደስ ይናገራሉ፡፡ አንገት ማስገቢያ ጎጆ ለመቀለስ ባወጡት ወጪና ልፋት ውጤቱን ሳያዩ ስለፈረሰባቸው ሐዘን እንደሰበራቸው አክለዋል፡፡ ቤቱን ለመሥራት ከፍለው ያልጨረሱት የዕቁብ ዕዳም ዕረፍት ነስቷቸዋል፡፡ በሁኔታው ተስፋ ቆርጠው አፍራሾቹን ቆመው ሲመለከቱ እንደነበር፣ ንብረታቸውን ያወጡላቸውም ዕድርተኞቻቸው እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ አለኝ የሚሏቸው የቤት ዕቃዎች ወደ አንድ ጎን ተከምረው አቧራ ይጠጣሉ፡፡ 276 የሚል የቤት ቁጥር የሠፈረበትን ቆርቆሮ የያዘ የብረት በር ከአንዱ ጥግ ተሸጉጧል፡፡ ወይዘሮ መቅደስ የቤት ቁጥር ከተሰጣቸው ዓመታት እንደተቆጠሩ ይናገራሉ፡፡

በራፋቸው ላይ ከተተከለው የኤሌክትሪክ ፖልም የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኛሉ፡፡ ከዓመታት በፊት አንድ ክፍል ቤት ያለውን ግቢ የገዙት በግል ውል ነበር ይላሉ፡፡ ‹‹ማዘጋጃ ቤት በሊዝ ለባለሀብት ይሸጣል እንጂ ለምን ለእኔ ይሸጥልኛል? ባለሀብት ደግሞ እንዲህ ዓይነት ቦታ ላይ ምን ይሠራል?›› ሲሉ ለኑሮ የማይመቹ ቦታዎች ላይ ተገፍቶ የሚወጣው አማራጭ ያጣ እንደ እሳቸው ያለ ደሃ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ቦታው ላይ ሲኖሩ ካርታ ባያገኙም ሕጋዊ መሆናቸውን የሚያመላክቱ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ እንደነበሩ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የአከራይ ተከራይ ግብር ለመክፈል የሚመለከተው አካል ከቀናት በፊት አነጋግሮን ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይኼንን እየተነጋገርን ባለንበት ሰዓት ደብዳቤው እንደ ዱብ ዕዳ ዓርብ ወጪ ተደርጎ ቅዳሜ እጃችን ላይ ገባ፡፡ በአራት ቀናት ውስጥ ምን ማድረግ እንችላለን?›› ብለው ሌላው ቢቀር እንዲወጡ የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ነገሮችን ያላገናዘበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቀረልኝ የሚሉት ተከራዮች ይኖሩበት የነበረው ቤትም እንደማይፈርስ ማረጋገጫ የለም ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ከቀናት በፊት በእጃቸው የገባው በኦሮሚፋ የተጻፈው ደብዳቤ የቱ እንደሚፈርስና የቱ እንደሚቀርላቸው አይገልጽም፡፡

አካባቢውን በአንድ ጊዜ ወደ ፍርስራሽነት የቀየረው ዘመቻ በርካቶችን ሐዘን ላይ ጥሏል፡፡ ለገጣፎ የሚገኘው የካ ዳሌ 03 ቀበሌ ልጅ አዋቂ ሳይል ሁሉም በአንድነት የሚያነባበት መንደር ሆኖ ነበር ያረፈደው፡፡ እንደ ነገሩ ተበታትነው ከሚታዩ የቤት ዕቃዎች፣ የቆርቆሮና የፍርስራሽ ክምር ባሻገር የሚገቡበትን ያጡ በትካዜ የተዋጡ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ማረፊያ እንዳጡ ሁሉ በየመንገዱና በየጥጋጥጉ እንደቆሙ ይተክዛሉ፡፡ የደረሰባቸውን የሰሙ ዘመድ አዝማዶች ከያሉበት እየሄዱ እከሌን ዓይታችኋል እያሉ የዘመዶቻቸውን አድራሻ ሲፈልጉ ታይተዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ‹ቤት ለእምቦሳ› ብለው የመረቁላቸው ቤቶች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋልና ሜዳ ላይ ቆመው ያወራሉ፡፡ ምርር ብለው የሚያለቅሱ ዘመዶቻቸውን ያፅናናሉ፡፡ ሰብሰብ ሲሉ ‹የአንተም ቤት ፈረሰ?› እየተባባሉ የቁም ቅዠት የሆነባቸው ክስተት በሌላው ላይ ደርሶ እንደሆነ ይጠያየቃሉ፡፡ ‹የእኔ ቤት እዚያ ጋ ነበር› እያሉ ነው የፈረሰባቸውን ለሰዎች የሚያሳዩት፡፡ የፈረሰባቸውን ሲያፅናኑ የቆዩ ደግሞ ተራው የእነሱ ሆኖ ቤታቸው ሲፈርስ እያዩ እንደ አዲስ ይደነግጣሉ፣ ያለቅሳሉ፡፡

“100 የሚደርሱ ሰዎች ሆ ብለው መጥተው አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ብለው ግድግዳ ገፍተው ሲንዱ ማየት ግራ ያጋባል፡፡ ከማልቀስ ውጪ ምንም ማድረግ አይቻልም፤” ይላሉ ወይዘሮ መቅደስ፡፡ የሚፈርሰውን ቤት መታደግ ባይቻልም ጥረው ግረው ያፈሩት ንብረት በፍርስራሽ እንዳይዋጥ ጎረቤት ተሯሩጦ ለማትረፍ ይረባረባል፡፡

ቄስ ኪሮስ ዓለምነህን ሪፖርተር ያገኛቸው ከፈረሰው ቤታቸው ውስጥ የወጣ ንብረታቸውን በጎረቤቶቻቸው ዕገዛ ወደ አንድ በኩል ሲቆልሉ ነበር፡፡ ቄሱ በሆነው ነገር ከመደንገጣቸው የተነሳ ግራ መጋባት ይታይባቸዋል፡፡ ጎረቤቶቻቸው ግቢያቸውን ሞልተው የተበተነውን ንብረታቸው ዝናብ እንዳይመታው ቆርቆሮ ይመቱላቸዋል፡፡

እናቶች በየጥጋጥጉ እንደተቀመጡ ያለቅሳሉ፡፡ ከአርሶ አደር ላይ በ250 ሺሕ ብር የገዙትን ቤት አፍርሰው በሚፈልጉት ዲዛይን ለማሠራት ብዙ ገንዘብ ማፍሰሳቸውን፣ ቤቱን የሠሩትም በ2003 ዓ.ም. እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ቦታውን ገዝቶ ቤት ለመሥራት ከዘመድ አዝማድ ብዙ ገንዘብ መበደራቸውንና እስካሁንም ያልተከፈለ 80 ሺሕ ብር የሚሆን ውዝፍ ዕዳ እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡

ቄስ ኪሮስ በአካባቢው ሕጋዊ ነዋሪ መሆናቸውን የሚያሳይ የቀበሌ መታወቂያ አላቸው፡፡ ለመንገድ፣ ለውኃና ለኤሌክትሪክ የከፈሉበት ደረሰኝም አላቸው፡፡ በሌሎች ማኅበራዊ ግዴታዎች ክፍያ የፈጸሙባቸው ሕጋዊ ደረሰኞች ይዘዋል፡፡ የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ውልም በእጃቸው ይዘዋል፡፡

‹‹ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ዕዳ ላይ ነው ያለሁት፡፡ ቤቱን ለመገንባት ከ500 ሺሕ ብር ከላይ አውጥቻለሁ፤›› በማለት፣ ዕዳቸውን ከፍለው በወጉ መኖር ሳይችሉ የቤታቸው መፍረስ የተደበላለቀ ስሜት እንዳሳደረባቸው ይናገራሉ፡፡ ቤቱን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ የሚያሳስበው ደብዳቤ የተጻፈውና እጃቸው ላይ የደረሰው በአጭር ጊዜ ነው በማለት፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ጊዜው እጅግ አጭር እንደሆነና ነገሩን ለመረዳትም ፋታ ሳይሰጣቸው ሕይወታቸው እንዳልነበረ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ሌላው ቢቀር ቀልባቸውን ሰብስበው ንብረታቸውን በመልክ መልኩ ለማሰናዳት እንኳ አልሆነላቸውም፡፡ ሕጋዊ ነዋሪ መሆናቸውን የሚመሰክሩ ሰነዶችን ቅጂ እንደያዙ ፍርስራሽ የዋጠው ቅጥር ግቢ ውስጥ ቆመዋል፡፡ ዕዳ ገብተው የሠሩት ቤት ፈራርሶ ማየታቸው በቤታቸው እንግድነት እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡

ከጎናቸው ሆኖ የሚያፅናናቸው የ29 ዓመቱ አቶ ቀናው በላይ ደግሞ 150 ካሬ ላይ ያረፈው ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ፈርሶበት ሜዳ ላይ መቅረቱን ይናገራል፡፡ ደሳሳ ቤት የነበረውን ቦታ በ2004 ዓ.ም. ገዝቶ ከ300 ሺሕ ብር በላይ አውጥቶ የብሎኬት ቤት እንደሠራ፣ ባለትዳርና የልጅ አባት መሆኑን፣ በቴክኒክና ሙያ ከሰባት ዓመታት በፊት በዲፕሎማ ቢመረቅም፣ በተማረበት ሙያ ሥራ ማግኘት አለመቻሉን ያስረዳል፡፡

ቤተሰቡን የሚያስተዳድረውም ፑል ቤት ተቀጥሮ እየሠራ በሚከፈለው 1,500 ብር ቢሆንም፣ የራሱ የሚለው ቤት ስለነበረው ግን ብዙም እንደማይቸግረው፣ ዓለም የተደፋበት የመሰለው ሕገወጥ ነህ ተብሎ ቤቱ ሲፈርስበት መሆኑን ገልጿል፡፡ ‹‹ቤቴ የፈረሰው ማክሰኞ ነው፡፡ ‹‹አሁን ያለሁት አንድ ወዳጄ ዘንድ ተጠግቼ ነው፡፡ መንግሥት አካባቢውን ለማልማት ፈልጎ ከሆነ ደስ ይለናል፣ ግን እኛ የት ሄደን እንውደቅ?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ ‹‹ከአሁን በኋላ የሚጠብቀኝ የጎዳና ሕይወት ነው፡፡ ሚስቴንም ወደ ቤተሰቦቿ እልካለሁ፡፡ ከቻሉ ሁላችንንም ወደ ትውልድ ቀዬአችን የምንመለስበትን ገንዘብ ይስጡን፤›› ይላል፡፡

ቴሌቪዥን፣ ፍሪጅ፣ ቁም ሳጥን ሳይወጣ የፈረሰባቸው፣ ፅዋ እንኳ ሳይወጣ በላያቸው የፈረሰባቸው፣ እንዲሁም ሁኔታው በፈጠረባቸው ድንጋጤ ከታመሙና ራሳቸውን ስተው ከወደቁ ባሻገር የከፋ ነገር የገጠማቸውም መኖራቸው ይሰማል፡፡

ጎረቤቶቿ ዓረብ አገር ሠርታ ባጠራቀመችው ገንዘብ ከጎናቸው ቤት ገዝታ እንደምትኖር፣ ቤቱ ላይዋ ሲፈርስ ግን ተስፋ ቆርጣ ራሷን ማጥፋቷንና አፍራሽ ግብረ ኃይሉ በአምቡላንስ እንደወሰዳት የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ አስከሬኗ የትና በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳለም አይታወቅም ብለዋል፡፡ ዘመድ ይኑራት፣ አይኑራት የደረሰባትን ይስሙ፣ አይስሙ የሚያውቅ የለም ብለው ወደ ፍርስራሽነት የተቀየረው ቤቷና እሷ በአንድ አፍታ ታሪክ ሆነው መቅረታቸውን ይናገራሉ፡፡

ዱብ ዕዳ የሆነ ክስተት እንደ አቶ ጌታቸው ህያሴ ያሉ በአካባቢው ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች እንኳ አላለፈም፡፡ አቶ ጌታቸው ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በአካባቢው እንደሚኖሩ ይናገራሉ፡፡፡ ዓምና ደግሞ የቀበሌውን ሊቀመንበር አስፈቅደው በዘመናዊ መንገድ ከብቶች ማርባት ጀምረዋል፡፡ በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር የካ ዳሌ 03 ቀበሌ አሉ የተባሉና ጠንካራ የልማት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ ‹‹ይኼ ሁሉ ነገር ሲሠራ አብረውን ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ያውቃሉ፡፡ ገና ሲጀመር ማስቆም ይችሉ ነበር፤›› ይላሉ፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ከብቶቹን ለማርባት ከ500 ሺሕ ብር በላይ ወጪ አድርገው ወደ ሥራ ሲገቡ የከለከላቸው አልነበረም፡፡ በዘመናዊ መንገድ የገነቡት የከብቶች በረት እንዲፈርስ ሲደረግ ግን ብዙ ነገር ማጣታቸውን ይናገራሉ፡፡

አቶ ጌታቸው የአካባቢው ወጣቶች የልማት ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ ነዋሪዎች ገንዘብ እያዋጡ መንገድና የተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮች እንዲሟሉ እያስተባበሩ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሠሩ መቆየታቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ነዋሪዎች ለተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች አሥር፣ አሥር ሺሕ ብር እንዲከፍሉ ተደርጎ አካባቢው መልማቱን፣ ቤታቸው ሕገወጥ ተብሎ ከፈረሰባቸው ነዋሪዎች መካከል ሪፖርተር ያነጋገራቸው አብዛኞቹ ገንዘብ አዋጥተው አካባቢውን ማልማታቸው ይነገራል፡፡ ‹‹ኮሚቴአችን በልማት አንደኛ ተብሎ የተሰጠን የምስክር ወረቀት ቤት አለኝ፤›› የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ከማዘጋጃ ቤቱ ጋር ተባብረው አካባቢውን ሲያለሙ የነበሩ ነዋሪዎች ሳይቀሩ ሕገወጥ መባላቸው ግር አሰኝቶኛል፤›› ይላሉ፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች ይህንን ያህል ገንዘብ አውጥተው ቤት ሲገነቡና አካባቢውን ሲያለሙ ዝም ተብሎ አሁን እንዲፈርስ መደረጉ ብዙዎችን አስቆጥቷል፡፡ ግንባታውን ከጅምሩ ማስቆም ሲቻል ገንዘብ እየተቀበሉ ፈቃድ የሚሰጡ የአመራር አካላት መኖር፣ ሌሎችም እንዲገነቡ ያደፋፍር እንደነበር ነዋሪዎቹ እየተናገሩ ነው፡፡ አብዛኞቹ ቤቶች ሲገነቡ አሥር ሺሕ ብርና ከዚያ በላይ ለቀበሌው አስተዳደር አካላት ይከፈል ነበር ተብሏል፡፡

ሕጋዊ ነዋሪ እንደሆኑ የሚያሳይ የቤት ቁጥር፣ የነዋሪነት መታወቂያ፣ የኤሌክትሪክና የውኃ አገልግሎት ካገኙ በኋላ ሕገወጥ ተብለው መፈናቀላቸው ሌላ አስተዳደራዊ ችግር ቢኖር ነው ያሉም አሉ፡፡፡ በቀናት ውስጥ ቤታቸውን እንዲለቁ የሚያዘው ደብዳቤ እንደደረሳቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በኩል ድምፃቸውን ያሰሙም፣ ‹ማስፈራሪያ እየደረሰን ነው፡፡ የምንንቀሳቀሰውም ተደብቀን ነው፡፡ አብረውን ችግሩን በተመለከተ በሚዲያ የተናገሩ ሁለት ሰዎችም ተይዘዋል› ብለዋል፡፡ ቤቶቹን ሲያፈርሱም ‹እስቲ ሚዲያዎች ይድረሱላችሁ፣ እናያለን› መባላቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ቤቶቹን ሲያፈርሱ ከነበሩት መካከል በሦስቱ ላይ ግድግዳ ተደርምሶ ጉዳት እንደ ደረሰባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ አንደኛው ተጎጂ ሕይወቱ ወዲያው እንዳለፈ ቢናገሩም፣ የከተማው የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ የሞተ እንደሌለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ቤቶቹን የማፍረስ ኃላፊነት የተሰጠው በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ከንቲባ የሚመራው ገብረ ኃይል፣ አስለቃሽ ጭስና መሣሪያ በታጠቁ የፀጥታ አካላት ታጅቦ እንደነበር ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ ሐቢባ ሲራጅ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ፣ ቤቶቹ እንዲፈርሱ የተወሰነው ከተማዋን በማስተር ፕላን የምትመራ ለማድረግ፣ እንዲሁም ምቹና ፅዱ ቦታ ለመፍጠር ነው ብለዋል፡፡ ይፈርሳሉ የተባሉ ከ12,000 በላይ የሚሆኑ ቤቶችም የከተማውን ማስተር ፕላን በመጣስ፣ ለአረንጓዴ ልማት የተተውና የተከለከሉ የወንዞች ዳርቻዎች ላይ የተገነቡ በመሆናቸውም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በሕግ ከተፈቀደላቸው ቦታ ውጪ ተጨማሪ ቦታ አጥረው የያዙ ባለሀብቶችም የዚሁ አካል ናቸው ብለዋል፡፡

ዓርብ የካቲት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬታሪ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ኦዴፓ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የገጠርና ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋና ሌሎች የክልሉ ሹማምንት በለገጣፎና አካባቢው ጉብኝት አድርገው ነበሩ፡፡ ከንቲባዋ ወ/ሮ ሐቢባ በሰጡት ገለጻ መሠረት፣ ከ12,300 በላይ ካርታ የሌላቸው ቤቶች በከተማዋ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየፈረሱ ያሉ ቤቶች በመንግሥት ይዞታ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸው፣ የማፍረስ ዕርምጃ ከመወሰዱ ሁለት ወራት በፊት ደብዳቤ ለባለ ይዞታዎቹ ደርሷል ብለዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ከመመሥረቱ ሦስት ዓመት በፊት ግብር የከፈሉበት ደረሰኝ ማቅረብ አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ውኃና መብራት ማስገባት ዋስትና አይሆንም፤›› ያሉት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማው የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ነፃነት ከበደ በበኩላቸው፣ ቤቶቹን የማፍረስ ዘመቻው በማስተር ፕላኑ መሠረት ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ግንባታ የተከናወነባቸው አንዳንዶቹ ቦታዎች መንግሥት ለልማት የሚፈልጋቸውና ካሳ የከፈለባቸው እንደሆኑም አስረድተዋል፡፡ ከአርሶ አደሩ እየገዙ የሠፈሩም አሉ ብለዋል፡፡ አለ ለሚባለው ችግር ተጠያቂው ከዚህ በፊት የነበረው የአስተዳደር አካል እንደሆነ፣ ከእነዚህም ውስጥ በሕግ እየተጠየቁ ያሉ ሰዎች መኖራቸውንና አሁንም ተጠያቂ የሚደረጉ ሌሎች መኖራቸውን፣ ከአርሶ አደሮችም የሚጠየቁ እንደሚኖሩ አስረድተዋል፡፡

ቤት የፈረሰባቸው ነዋሪዎችን የፌዴራል ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባለሙያዎች ዓርብ የካቲት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በቦታው ተገኝተው እንዳነጋገሯቸው ታውቋል፡፡ ዘገባው የሪፖርተር ነው።

ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ

ካሊድ ኢብራሂም
nafkothager@gmail.com

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአፍሪካ ቀንድ በርካታ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበት የቀይ ባህር እና የሰሜን ምዕራብ ህንድ ውቅያኖስ አካባቢ የሚገኝ ዋነኛ ዓለም አቀፍ የባህር ንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት አካባቢ ነው። ቀጠናው በቅርብ ርቀት የአረብ ሀገራት የሚገኙ ሲሆን፤ አካባቢው ከትናንሽ ሀገር በቀል የፖለቲካ ሽኩቻ እስከ ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ሽኩቻና ፉክክር የሚካሄድበት ሰላም አልባ የግጭት ቀጠና ነው። በቀጠናው ኤርትራ፥ ጅቡቲ፥ ሱዳን፥ ደቡብ ሱዳን፥ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ይገኛሉ።

ቀጠናው ባለው የተፈጥሮ ሃብት አይታማም። ውድ ከሆኑ ማዕድናት፥ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ፥ በርካታ ወንዞች፥ የቁም እንሰሳት፥ ስራ ፈት የሆኑ ለንግድ ምቹ የሆኑ የባህር በሮች እና በተፈጥሮ ቱሪዝም የበለፀገ አካባቢ ነው። የአየር ፀባዩ የተለያየ ቢሆን ለነዋሪውም ይሆን ከሌላ አካባቢ መጥቶ መዋዕለ ነዋይ አፍስሶ መኖሪያውን እዚህ ማድረግ ለሚፈልግ የተመቸ ነው። ነገር ግን በቀና እና የሰለጠኑ መሪዎችና የፖለቲካ ልሂቃን እጦት በኢኮኖሚ፥ በመሰረተ ልማትም ይሁን በቴክኖሎጂ እጅግ ኋላቀር አካባቢ ነው። ቀውስ የማያጣው የአፍሪካ ቀንድ።

የአፍሪካ ቀንድ በአሁን ወቅት በርካታ ህዝብ የሚኖርበት ሲሆን፤ በተለይም ኢትዮጵያ 105 ሚሊዮን፥ ኤርትራ 5 ሚሊዮን፥ ጅቡቲ 1 ሚሊዮን፥ ሱዳን 40 ሚሊዮን፥ ደቡብ ሱዳን 12 ሚሊዮን 500 ሺህ እና ሶማሊያ 14 ሚሊዮን 500 ሺህ በድምሩ 178 ሚሊዮን አካባቢ ህዝብ ይኖራል። ቀጠናው ርስ በርስ በሚሻኮቱ እና ሐሳብን በጦር መሳሪያ ባሉ አማጺያን እና እብምባገነን መሪዎች ዋሻ ሲሆን፤ ከአቅራቢያው አረብ ሀገራት እስከ ምዕራባውያን ፍላጎቶች የሚርመሰመሱበትም ነው። በተለይ ፍትህ፥ ዴሞክራሲ፥ እኩልነት፥ የፕሬስ ነፃነት፥ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ እና የሰብዓዊ መብት በግልፅ የሚጨፈለቁበት የአምባገነን ጣዖታት መሪዎች ልዩ ግዛት ነው ማለት ይቻላል።

በተለይ በፖለቲካው መድረክ በጦር መሳሪያ ወደ ስልጣን ከመጡት ውጭ የብዙሃን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ የማይስተናገድበት ሲሆን፤ ሐሳብን በነፃነት መግለፅና የፕሬስ ነፃነት ተግባራት በሽብር የሚያስቀጡ ከባድ ወንጀሎች ነው። በአንፃሩ ገዥዎች በይፋ የሚፈፅሙት የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ረገጣ፥ ሙስና እና በስልጣን መባለግ እንደልማትም የሚቆጠርበት ልዩ ቀጠና ነው።

የአካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ከመንደር የጎበዝ አለቃ እስከ ማዕከላዊ መንግሥት ሹማምንት የሚፈፅሙት ርግጫ ከሞት የተረፉት ሀገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ። ለአምባገነኖቹ ገዥዎች ግን ይህም የልማት አካል ተደርጎ ይወሰዳል። ዜጎቻቸውን ከቀዬአቸው እና ሀገራቸው የበረሃና የባህር ሲሳይ ከሆኑት የተረፉት ብሰቆቃ ውስጥ ላለው ወገናቸው የሚመፀውቱት ገንዘብ በምንዛሪ መልክ ለክፉ መሪዎች ኪስ ማደለቢያ እና ጥይት መግዣ ከመዋል አይድንም።

የቀጠናው የገንዘብ ሀብት ኃላፊነት በማይሰማቸው ጨካኝ መሪዎች አማካኝነት ከደሃው ህዝብ ጉሮሮ ተነጥቆ የገዥዎች ቤተሰቦችና ወዳጆቻቸው ከሚንደላቀቁበት የተረፈው ብር በሀብታም ሀገራት ባንኮች ወስዶ መሰወርና ማከማቸት የተለመደ ተግባር ነው። ምክንያቱም ተጠያቂነትና ግልፅነት እንዲሁም የህግ የበላይነት የለምና። በተለይ ርሷን እንደ ነፃ ሀገር ከምትታየውና በዓለም አቀፉ ማኅበረስብ የሶማሊያ ፌደራል ግዛት አካል ተደርጋ ከምትቆጠረው ሶማሌ ላንድ በስተቀር ሁሉም ገዥዎች ወደ ስልጣን የያዙት በጦር መሳሪያ አመፅ የቀድሞ ገዥዎችን ገልብጠው ነው አሊያም በውጭ ኃይሎች ድጋፍ ነው። ለዚህም ይመስላል ራሳቸው ከዴሞክራሲ ጋር የየዕለት ተግባራቸው ተራርቆ ስሙን ሲደጋግሙ የሚውሉት። ለዜጎቻቸውም የተስፋ ዳቦን ከመመገብ በተጨማሪ የዕለት ጉርስ የሚቀመስ በሚናፍቅ ዜጎቻቸው ስም ሳይቀር እየለመኑ ልማት በሚዲያ የሚሰራጭ ተስፋ የሚመግቡም አሉ። ግን ምን ዋጋ አለው። ሁሉን ነገር መደበቅና ዋሽቶ ማሳመን አይቻል ነገር።

በኢትዮጵያ ዶ/ር አብይ አህመድ መጋቢት 2010 ዓ ም የጠቅላይ ሚኒስተርነትን መንበር ከያዙ በኋላ ከወትሮ በተለየ መልኩ ብሩህ ተስፋ ይታይባታል። ለዓመታት ያለበደላቸው በሰቆቃ ስር የነበሩ አብዛኛው የፖለቲካ እስረኞች ከስር ነፃ እንዲወጡ ተደርጓል። ዋነኛ የአፈና እና የመጨቆኛ ተቋማትና ዋነኛ ተዋናይ ግለሰቦች ከቦታቸው እንዲነሱ ተደርጓል። በጎ የሆኑ የተለያዩ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፤ እየተደረጉም ነው። ለዚህም ይመስላል ለአስርት ዓመታት ሰላምና ዴሞክራሲን ይናፍቅ የነበረ ህዝብ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የድጋፍ ሰልፉን ችሮታል። ይሁን እንጂ አስታዋሽ ያጡ እና ሚዲያ ያላወቃቸው የፖለቲካ እስረኞች አሁንም በትግራይና እና በተለያዩ አካባቢ ወህኒ ቤቶች አሉ። ሌሎች ማሻሻያዎች ይጠበቃሉ። ነገር ግን የአርካ ቀንድን በሚመለከት የዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ከሀገር ውስጥ ባልተናንሰ መልኩ በቀጠናው ብሩህ ተስፋ ይታያል። በህዝብ ቁጥር አምስቱ የቀጠናው ሀገሮች ተደምረው ኢትዮጵያን አያህሉም። ስለሆነም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ በቀጠናው ላይ ያለው ሚና ምን ያህል እንደሆነ በቀላሉ ማየት ይቻላል።

Horn of African Map
የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ካርታ (ፎቶ ዊኪፔዲያ)

ዶ/ር አብይ ሥልጣን በያዙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከደቡብ ሱዳን በስተቀር ሁሉንም የቀጠናውን እና የአካቢውን ሀገሮች በመጎብኘትና ያረበበውን ሌላ የግጭትና የስጋት ፖለቲካ ለማረጋጋት ሞክረዋል። በተለይ ላለፉት 21 ዓመታት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን የጦርነትና የግጭት ስጋት ወደ ሰላም መቀየራቸው ለቀጠናው ትልቅ ተስፋ ነው። በጎረቤት ደቡብ ሱዳን ውስጥ ያለውንም የርስ በርስ ግጭትና ስጋት ለማረጋጋትና ለማርገብ የወሰዱት ርምጃም የሚበረታታ ነው። በተለይ ተፋላሚዎቹ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሰላም ከመጡ ለዶ/ር አብይም እንደ ሀገር ለኢትዮጵያም ትልቅ ድል ነው።

ነገር ግን በጠቅላይ ሚንስትር አብይ እና በፕሬዘዳንት ኢሳይያስ መካከል እንዲሁም በሌሎች የጎረቤት ሀገሮችም ይሁን በቀጠናው መካከል የሚደረጉ ስምምነት እጅግ በጣም ጥንቃቄና ብስለትን ይጠይቃሉ። ምክንያቱም ቀጠናው ከባለቤቶቹ ሀገራት በተጨማሪ ለዘመናት ለውጭ ጣልቃ ገብ ፖለቲካ ክፍት የነበረ በመሆኑ እና በነበሩ ግጭቶች በፖለቲካውም ይሁን በኢኮኖሚው ተጠቃሚ የነበሩ ሶስተኛ ሀገራት ስላሉ በአንድ ግለሰብ ወይም ሀገር ቅንነትና ተነሳሽነት ብቻ ዘላቂ ሰላም ማምጣት አይቻልም። ለጋራ ሰላም የጋራ ተነሳሽነትና የጋራ ተጠቃሚነት ትልቅ ድርሻ አለው።

ላለፉት ጊዜያት ከልክ ባለፈ ራስ ወዳድ በሆኑ ገዥዎች ፍላጎትና ጥቅም ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረው በኢትዮጵያና በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት መካከል የነበረው ግንኙነትም ከጥርጣሬ ይልቅ ወደ አጋርነት የመሄድ አዝማሚያ ይታይበታል። ይህ የሚበረታታና ጥሩ ጅምር ነው። ይሁን እንጂ የነ አቶ መለስ ዜናዊ ርካሽ የግል ጥቅምንና ፍላጎትን ብቻ ማዕከል አድርጎ የነበረው የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሉዓላዊና ህልውና ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በሌሎች ሀገሮች መልካም ፈቃድ ያውም 1 ሚሊዮን አካባቢ ህዝብ ባላት ጅቡቲ ላይ ሳይቀር ጥገኛ እንዲሆን ተደርጓል። ይህም ሀገሪቱንም ህዝቡን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል። ችግሮቹ ተጠንተው፥ ተለይተውና መፍትሄ ተበጅቶላቸው እርምት ካልተወሰደ ችግሮቹ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይችል ይሆናል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ በሚያስገርም አሀዝ እየጨመረ ሲሆን፤ የገበያ ፍላጎቱም የዛን ያህል ይጨምራል። ለዚህም ተመጣጣኝ አቅርቦት የሚያስፈልግ ሲሆን፤ ከሀገር ውስጥ ምርት በተጨማሪ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በፍጥነት ለማዳረስና የሀገር ውስጥ ምርትን በነፃነት በውጭ ላሉ ተጠቃሚዎች ለማድረስ መሰረተ ልማት ቁልፍ ድርሻ አለው። በተለይ ነፃ የባህር በር። ምክንያቱም ነፃ የባህር በር ከአንዲት ሀገር ያውም ከባህር 60 ኪሎ ሜትር ቤቻ የምትርቅ ወደብ አልባ ሆና የምትቀጥል ሀገር ከሉዓላዊነቷ በተጨማሪ ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ፈተና ይጋርዳል። ለምሳሌ ፈጣን የንግድ እንቅስቃሴ፥ ፍትሃዊ የንግድ ቁጥጥር ስርዓትና ተጠቃሚነት፥ የሸማቹ ደህንነት እና የአቅርቦት ተጠያቂነትና ግልፅነት ላይ ትልቅ ጫና አለው። ይሄ የተለያዩ አዋጭና ዘላቂ አማራጮችን አይቶ መፍትሄ ካልተወሰደ አሁን ያለው ግን ደግሞ ትኩረት ያልተሰጠው ችግር ከህዝብ ቁጥርና ፍላጎት ጋር እየተባባሰ የሚሄድ በመሆኑ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጥሞና ማሰብ አለባቸው።

ስለሆነም ኢትዮጵያ የራሷን ብሔራዊና ታሪካዊ መብትና ጥቅሟን እስካላስጠበቀች ድረስ አሁን ያለው ሰላም መልካም ቢሆንም ዘላቂ የመሆን ዕድሉ ግን አጠራጣሪ ነው። ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ያለህዝብ ፍላጎትና ፈቃድ ታሪካዊ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ እጅግ አንገብጋቢና ፈታኝ ሲሆን፤ በዶ/ር አብይ አስተዳደር ወደ ፊት ምን እንደታሰበ እስካሁን ግልፅ የሆነ ነገር ባለመኖሩ፤ ነገስ የሚል ጥያቄን ያጭራል። ሌላው መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ቢኖር በሀገራቱ መካከል ያለውን ሰላም ወደ ዘላቂ ደረጃ የማሸጋገር ዕድሉ በመሪዎች መልካም ፈቃድ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በእያንዳንዱ ሀገር ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎትም ጭምር በመሆኑ አሁን ያለውን ሰላም ምሉዕ አያደርገውም።

በርግጥ የአብይ አንድ ጥሩ ጅምር አለ። እሱም ቀጠናውን በኢኮኖሚና በመሰረተ ልማት ማስተሳሰር። ይህ ለጋራ ተጠቃሚነት እጅግ በጣም ጥሩ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የነበረውን የርስ በርስ ጥርጣሬ አጥፍቶ ያለውን ሰላም ወደተሻለ ምዕራፍ ሊያሸጋግረው ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ በኢኮኖሚው መስክ ሁሉም የቀጠናው ሀገራት በሌሎች ሀገሮች መልካም ፈቃድ ልግስና እና ብድር ጥገኛ በመሆናቸው በቅድሚያ ለፖለቲካው ነፃነት የኢኮኖሚ ደረጃዎቻቸውን በፈጣን ሁኔታ ማሻሻልና መቀየር አለባቸው።

አንዲት ሉዓላዊ ሀገር በርካታ ብድሮችንም ይሁን ርዳታዎችን ከአንድ የተወሰኑ ሀገራት ወይም ተቋማት ወይም የፖለቲካ አጋር ላይ ጥገኛ ከመሆን መላቀቅና አማራጮችን መጠቀም በራስ አስቦ ለመወስን ጉልበት ይሆናል። አለበለዚያ ኢኮኖሚው፥ የሀገር ውስጥ በጀት እና ትብብሩ በሶስተኛው ወገን ላይ ጥገኛ በሆነበት ሁኔታ በራስ ፈቃድ ብቻ ሰላምን አስፍኖ ዘላቂ ማድረግ እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ ነው። ይሄ ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀሪዎቹ የቀጠናው ሀገራት ይሰራል። ምክንያቱም ብቻህን ደሴት ሆነህ እስካልኖርክ ድረስ፥ የኢኮኖሚ ነፃነት እስካላረጋገጥክ ድረስ የቱንም ያህል ቅን እና መልካም ሆነህ የፖለቲካ ነፃነት ለማረጋገጥ ብትሞከር ጊዜያዊ ካልሆነ በቀር ከጎረቤት ሀገሮች የሚኖረውን ግንኙነት በሌላ ሶስተኛ ወገን መፈተኑ የማይቀር ነው።

ኢትዮጵያ ያላትን ታሪካዊ ዳራ፥ የህዝብ ብዛት፥ የገበያ ፍላጎትና የፖለቲካ ሚናዋን ታሳቢ በማድረግ ቀጠናዋን በተለያየ አቅጣጫ መመልከትና መመርመር ይጠበቅባታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይም አንዱና ዋነኛ የአስተዳደራቸው ፈተና ሊሆን የሚችለውም በቀጠናው ያለው የገዥዎች ስግብግብነት እና አምባገነንነት በተጨማሪ የሶስተኛ ወገን ጥቅምና ፍላጎት በቀጠናው ፖለቲካና ማኀበራዊ መስተጋብር ያለውን ሚና መለይት፥ መፍትሄውንም በብዙ አቅጣጫ መቃኘት፤ ለሚወስዷቸው ርምጃዎችም ጥንቃቄ በማድረግ ነገ ሊያስከትል የሚችለውንም ነገር ታሳቢ ማድረግ አለባቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ በሀገር ውስጥ እየወሰዷቸው ካሉ በጎ ርምጃዎችና ማሻሻያዎች በተጨማሪ በቀጠናው ላይ የወሰዱት ፈጣን ርምጃ ይበል የሚያሰኝ ነው። የሚመሩትን ሀገርና ህዝብ እንዲሁም ታሪክ በሚመጥን መልኩ የወሰዷቸው ርምጃዎች ጥሩዎች ናቸው። ነገር ግን ከኤርትራ የተደረጉ ስምምነቶች ምንም እንኳ በግልፅ የታወቁ ነገሮች ባይኖሩም በኢኮኖሚውና በፀጥታ መስክ ያለውን ግንኙነት ከወዲሁ ፈር ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል። ለምሳሌ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለሁለት አስርት ዓመታት የነበረው ውጥረት ከረገበ በኋላ ከርስ በርስ ማኅበራዊ ግንኙነት በተጨማሪ በቅርቡ የርስ በርስ ንግድ ልውውጥ ተጀምሯል። በጎ ጅምር ነው። ነገር ግን በሁላቱ ሀገራት መካከል ያለው የገንዘብ አጠቃቀምና የምንዛሪ ተመን በግልፅ መታወቅና መነገር አለበት።

የወደብ አገልግሎትን በሚመለከት ከጅቡቲ ጋር እንደነበረው ፤ ለዜጎች ኑሮና የውጭ ምርት አቅርቦት ዋጋ መናር አንዱ ምክንያት እንደሆነው ልክ እንደ ጅቡቲ ወደብ ኪራይ ነው ወይስ በጋራ ማልማት አሊያም በሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያን ከዛሬ 27 ዓመታት በፊት እንደነበረው ሀገሪቱን የባህር በር ባለቤት ባደረገ መልኩ? በኪራይ ከሆነስ ለምን ያህል ጊዜ በምን ያህል ዋጋ? የወደብ መሰረተ ልማትና አገልግሎት ዘረፍ አጠቃቀም ጉዳይስ በምን ዓይነት ስምምነት ተካቷል? በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታ በተለይም መደበኛ የየብስ መንገድ፥ የባቡር ትራንስፖርትና ሀዲድ ግንባታ፥ መብራት፥ ሎጅስቲክ፥ የፀጥታ ጉዳይ (በተለይ ወታደራዊ እንቅስቃሴ፥ የባህርና የአየር ኃይል) ለኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴና ለአካባቢው የፀጥታ ደህንነት አጠባበቅ ጉዳይ፥ ሌላ ሁለተኛ ወይም ሶስተኛ አካል የወደብ አገልግሎት አልሚና ተጠቃሚ ቢመጣ የኢትዮጵያ የሚኖራት ሚና እና የምትስተናገድበት አግባብ ፥… የመሳሰሉ ጉዳዮች በግልፅ ስምምነት ላይ ተደርሶ ለተጠቃሚው ህዝብ ይፋ መደረግ አለበት።

በሁለት ተራ ግለሰቦች አለመግባባት ወይም የጥቅም ሽኩቻ ግጭት ሀገራቱን ሊያቃቅር እንዳይችል መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች ከወዲሁ መታየት አለባቸው። የሚደረጉ ስምምነቶች ምንም እንኳ ዶ/ር አብይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎትን ለሌላ አካል አሳልፎ በመስጠት ይደራደራሉ ተብሎ ባይታሰብም በፖለቲካ በተለይ በዲፕሎማሲው የአንድ መሪ ወይም ግለሰብ ቅንነት ብቻውን ሰላምን ማስፈን ጉልበት ቢኖረውም በሀገራት መካከል ቅንነትና በየዋህነት የሚደረጉ ስምምነቶች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል። ምክንያቱም በፖለቲካም ይሁን በተፈጥሮ አስገዳጅ ሁኔታ የመሪዎች መለዋወጥ አሊያም ከነፍስ ወከፍ ገቢ ጋር ያልተመጣጠነ የህዝብ ብዛትና ፍላጎት ባልተጠበቀ ጊዜ ሁነቶችን የመለወጥ ባህርይ ስላላቸው ቢቻል የሚፈፀሙ ስምምነቶች ዘላቂ ሰላም የሚያስገኙ ቢሆኑ መልካም፤ የውል ስምምነቶች ግን ከአስር ዓመት ባይዘሉ ይመከራል። ምክንያቱም በሁለት ሀገሮች መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች ዓለም አቀፍ ሰነድ ሆነው የሚቆዩ በመሆናቸው፥የአካባቢና የሀገር ውስጥ ፖለቲካና ነባራዊ ሁኔታ ሲቀያየር አማራጭ እይታዎች ሊለያዩ ስለሚችሉ አሳሪ መሆን የለባቸውም።

ሌላው ኢህአዴግ ለመቀበል ከወሰነውና አቶ መለስና ስዩም መስፍን በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ፈርመው ካረጋገጡት የአልጀርስ ስምምነት ተፈፃሚ ከማድረግ በስተቀር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይም ሆነ በአስተዳደራቸው ስር ያሉ አካላት የቀድሞ ስምምነቶችና ውሎች ካሉ ተገቢው ምክክር፥ ምርመራና ጥንቃቄ ሳይደረግበት ማፅደቅም ሆነ መስማማት የለባቸውም። ይህ ለሁለቱ ሀገራት ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ሰላምም የራሱ ድርሻ ይኖረዋል።

ከቀጠናው አዋሳኝ አረብ ሀገራት ጋር እየታዩ ያሉ ጥሩ የሚመስሉ መግባባቶች ይበረታታሉ። ይሁን እንጂ ከሌሎች ሀገሮች በተለየ መልኩ ከአረብ ሀገራት ጋር የሚደረግ ወዳጅነትና አጋርነት በጥንቃቄ መታየት አለበት። ምክንያቱም ሁሉም ነዳጅ አምራጅ የቀጠናው አረብ ሀገራት በኢኢኮኖሚ ነፃ ቢመስሉም በፖለቲካውና በፀጥታ ጉዳይ ሌላ ሁለተኛ ወገን ላይ ጥገና የሆኑ ስለሆነ ከእነሱ ፍላጎት ውጭም ሊሆን በሚችል መልኩ በየጊዜው ያልተጠበቁ ተለዋዋጭ ባህርዮች ይታያሉ።

በተለይ የአረብ ሀገራት ዴሞኬርሲ አልባ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የሀገራቸው ኢኮኖሚም በገዥዎችና ቤተሰቦቻቸው እጅ የተከማቸ፥ የፀጥታ ጉዳዮቻቸውም ምንም እንኳ ጠንካራ ቢሆንም ከብሔራዊ ይልቅ በገዥዎች ፍላጎትና ተክለ ቁመና ላይ የተገነባ በመሆኑ እነሱ ያለ እንቅስቃሴ የአፍሪካ ቀንድ ጋር ቀጥተኛ ትስስር ይኖረዋል። ምክንያቱም በባህል እንዲሁም በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ከአረብ ሀገራት ጋር የሚጋሩት ነገር ስላለ እዛ የሚፈጠረው ችግር ከራሳቸው አልፎ የአጋር ሀገሮችንም ሰላም የማናጋት አቅም አለው። ለምሳሌ አሜሪካ 66 % የኃይል አቅርቦት በተለይም ነዳጅ፥ የተፈጥሮ ጋዝና የድንጋይ ከሰል የአሪካ ቀንድ አጎራባች የሆኑ የአረብ ሀገራት ላይ ጥገኛ ስትሆን፤ እነሱም ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ፥ የምግብ አቅርቦት ንግድ፥ የጦር መሳሪያ ፥ መሰረተ ልማት ቴክኖሎጂ አገልግሎትና አቅርቦት በዋነኝነት አሜሪካና ሸሪኮቿ ላይ ጥገኞች ናቸው። ርስ በርስ ያላቸው ወዳጅነትም ቢሆን አንዱ ያኩረፈ ቀን ቀጠናውን ማመስ የተለመደ ተግባራቸው ነው። ለምሳሌ የአሁኗን የመንን እንዲሁም ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማየት ይቻላል። ስለዚህ አንዱ አጋር ጋር የአደጋ ወይም ችግር ዝናብ ቢያካፋ በኢኮኖሚ የደከሙ ሌሎች ሶስተኛ አጋር ሀገሮችን የሚገጥማቸው የችግር ካፊያ ሳይሆን ጎርፍ ነው። ስለዚህ ከበጎ ርምጃው ጎን ለጎን ጥንቃቄዎችም በደንብ መታየት አለባቸው።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የምታደርጋቸው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችና ርምጃዎች በቀጠናው ላይ ትልቅ ተፅኖ አለው። ሰላሟና ደህንነቷ ከራሷ በተጨማሪ ቀጠናው ላይ የሚኖራት ሚና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ስለሆነም የቀጠናውን ህዝብ ብዛት 59 በመቶ ያህል የያዘች ሀገር መሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይና አስተዳደራቸው እየወሰዱት ያሉት ርምጃና ስምምነቶች ቀጠናውንም ታሳቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታል። እየወሰዷቸው ካሉ በጎ ርምጃዎች በተጨማሪ በቀጠናውም ሆነ በሌላው ዓለም አቀፍ የፖለቲካው መድረክ ኢትዮጵያ የነበራትን ተሰሚነትና ቦታ እንድትይዝ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ መረጋጋት፥ የህግ የበላይነትና የፀጥታ ጉዳይ ሳይዘነጋ ማለት ነው።

በተለይ በአንድ ሀገር ሁለት መንግሥት አሉ ብለው የሚፎክሩትን፥ የመንጋ ፍርድ ሰጪና ትጥቃቸውን አንግበው ሰላማዊ ዜጎች መሃል እየተንቀሳቀሱ የሚያውኩ “ተፎካካሪ” የፖለቲካ ኃይሎች ከወዲሁ በቃችሁ ተብለው እንዲታረሙ መደረግ አለበት። በአንድ ሀገር ሁለት እና ከዚያ በላይ ማዕከላዊ መንግሥት የጦር ሰራዊት የለም ሊኖርም አይችልም። ትንንሽ ተብለው በቸልታ አሊያም በየዋህነት የሚታለፉ ነገሮች በሌላው ወገን እንደ ጅልነትና አላዋቂነት ተቆጥሮ ለሀገርም ለህዝብም ጥቁር ጠባሳ የሚጥል አደጋ እንዳያስከትል ለቀጠናው ሰላም ኢትዮጵያ ቤቷን ማፅዳት ግድ ይላታል። በመጨረሿም ለማንኛውም የሀገር ውስጥ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴም የጦር መሳሪያና የሁለተኛ አካል ወይም ሀገር የፋይናንስ ድጋፍ፥ ዝውውርና ጣልቃ ገብነት ከእንግዲህ እንዳይኖር የፀጥታው ዘርፍ ከመንደር ባለፈ ሀገሪቷንና ቀጠናውን በበቂ ሁኔታ የተረዳ ፥ በቴክኖሎጂ የታገዘና ከነበረው ኋላቀር የገዥዎችን ፍላጎትና ጥቅም ታሳቢ ያደረገ መዋቅር በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ብሔራዊ መልክ የያዘ የፀጥታ ኃይል መገንባትና ማሰማራትም ቅድሚያ ሊሰጡ ከሚገቡ አብይ ጉዳዮች አንዱ ተደርጎ ቢወሰድ ለሚታሰበው ሰላም ጉልህ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።

%d bloggers like this: