አቃቤ ህግ ለ‹‹ሽብር›› ተከሻሾች በነፃ የቆሙ ጠበቆችን ማስፈራራቱ ተገለፀ
‹‹አቃቤ ህግ ጠበቆችን በማስፈራራትና በመክሰስ ከፍርድ ስርዓቱ ለማራቅ እየጣረ ነው›› ጠበቆች
በጌታቸው ሺፈራው
አቃቤ ህግ የቂሊንጦ እስር ቤትን በማቃጠል፣ ንብረት ማውደምና የሰው ህይወት መጥፋት ተጠያቂ ናችሁ ተብለው ክስ የተመሰረተባቸው እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ ስር ከተከሰሱ 38 ግለሰቦች መካከል የነፃ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ጠበቆች ሊከሰሱና የጥብቅና ፈቃዳቸው ሊነጠቅ እንደሚችል አስፈራርቷል፡፡ ጠበቆቹ ፍርድ ቤቱን በማስፈቀድና በማሳወቅ በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ ለተከሰሱት ግለሰቦች በነፃ ከመቆም በተጨማሪ ለበርካታ ተከሳሾች የቆሙትን አቶ ወንድሙ ኢብሳን በማገዝም እየተከራከሩ ቆይተዋል፡፡
ይሁንና ዛሬ ነሀሴ 4/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት አቃቤ ህግ ለተከሳሾች በነፃ የሚቆሙት ጠበቆች ከተከሳሾች ጋር የፈፀሙት ውል እስከሌለ ድረስ ተከሳሾችን ወክለው እንዳይቆሙ፣ የሚቆሙ ከሆነም ሊከሰሱና ፈቃዳቸውን ሊነጠቁ እንደሚችሉ ማስፈራሪያ አዘል አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጠበቆቹ አቃቤ ህግ ያቀረበውን አቤቱታ ተቀብለው ለተከሳሾቹ የጥብቅና አገልግሎት መስጠት እንዲያቆሙ ወይንም ለጥያቄው መልስ እንዲሰጡበት ምርጫ ባቀረበው መሰረት ጠበቆቹ መልስ በመሰጠት ተከሳሾቹን ወክለው እንዲቆሙ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ጠበቆቹ በአንድ ወንጀል የተከሰሰ ሰው የጥብቅና አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳለው፣ እንዲሁም በአመት ቢያንስ 40 ሰዓት በነፃ የማገልግል ግዴታ እንዳለባቸው ገልፀው በነፃ የሚሰጥ አገልግሎትም ውል ሊፈፀምበትና ለፍርድ ቤትም ሊቀርብ እንደማይችል አሳውቀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንድ ጠበቃ ሊጠየቅ የሚችለው የሙያ ፈቃዱን እንጅ በነፃ በቆመበት ጉዳይ ውል መጠየቅ እንደማይገባ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ክሱ አንድ በመሆኑና አንድ ምስክር በርካታ ተከሳሾች ላይና ተፈፀመ የሚባለው ጉዳይ ላይ እየመሰከረ ባለበት ሁኔታ ጠበቆች ደንበኛቸው ባይሆንም ሌላ ደንበኛ ላይ የተመሰከረውን ጉዳይ ላይም በመከራከር ክሱን ውድቅ ማድረግ ስላለባቸው ሌሎች ተከሳሾች በማገዝ መከራከር እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ ጠበቆቹ አቶ ወንድሙ ሌላ ችሎት ለሚቀርቡ ደንበኞቻቸው ሲቆሙ፣ እንዲሁም ጠበቃ የሌላቸውን ሲወክሉ ፍርድ ቤቱ አውቆና ፈቅዶ መሆኑን በመግለፅ አቃቤ ህግ ያቀረበውን አቤቱታና ማስፈራሪያ ላይ ጠንካራ ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡
አቃቤ ህግ ያቀረበው አቤቱታና ማስፈራሪያ የህግም የሞራል ድጋፍ የለውም ያሉት ጠበቆቹ ‹‹አቃቤ ህግ ጠበቆችን በማስፈራራትና በመክሰስ ከፍርድ ስርዓቱ ለማራቅ እየጣረ ነው›› ብለዋል፡፡ የእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የምስክር ሂደት ጠንካራና የአቃቤ ህግን ክስ የሚያስተባብል ክርክር እየተደረገበት ያለ በመሆኑ እና አቃቤ ህግ ደግሞ ጠበቆችን በማራቅ ክሱ እራሱ በፈለገው መንገድ እንዲሄድለት በመፈለጉ አቤቱታና ማስፈራሪያውን እንዳቀረበ ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ ጠበቃ ገልፀዋል፡፡
አቃቤ ህግ አቤቱታና ማስፈራሪያውን ካቀረበ እና ጠበቆችም ምላሽ ከሰጡ በኋላ የፍርድ ቤቱን ብይን ሳይጠይቅ ‹‹በህጉ መሰረት አቤቱታችን አቀረብን እንጅ አላስፈራራንም›› ብሏል፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ጉዳዩን መርምሮ ለመበየን ጊዜ የሚወስድ መሆኑንና ችሎት ላይ መበየን እንደማይቻል ገልፆ፣ በገንዘብ ጠበቃ ማቆም ላልቻሉ ተከሳሾች በነፃ የሚቆሙና አቶ ወንድሙ ኢብሳን የሚያግዙ ጠበቆች ውል ሳይኖራቸው ሊቆሙ ይገባል አይገባም የሚለውን ለመበየን በአዳር ቀጠሮ ይዟል፡፡
የመኢአድ አመራር የነበሩት አቶ ማሙሸት አማረ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰሱ
በታምሩ ጽጌ

አቶ ማሙሸት አማረ
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አመራር የነበሩትና ከሁለት ዓመታት ወዲህ ለሌሎች አመራሮች ጋር በተፈጠረ ልዩነት ከአባልነት የራቁት አቶ ማሙሸት አማረ፣ የሽብርተኝነት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
አቶ ማሙሸት የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (4)ን ተላልፈው የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማሴር መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ አቶ ማሙሸት በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም. መልምለው ያደራጇቸውንና በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠና ሲወስዱ የነበሩ የሽብር ቡድን ታጣቂዎችን አስተባብረው፣ በአማራ ክልል በተመረጡ ቦታዎች የሽብር ድርጊቱን እንዲፈጽሙ ማዘጋጀታቸውን በክሱ ገልጿል፡፡ አቶ ማሙሸት ኃላፊነት ወስደው እንቅስቃሴውን ከኢትዮጵያ ውጪ ሆነው ለመምራት ኬንያ ለመሄድ ሞያሌ ከተማ እንደገቡ፣ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው የክስ ዝርዝር ላይ ገልጿል፡፡
ተከሳሹ በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ሽመልስ ለገሰ በተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን አባል አማካይነት እንደተመለመሉ የሚገልጸው ዓቃቤ ሕግ፣ ተልዕኮ በመቀበል ከቡድኑ በሚላክላቸው ገንዘብ የጦር መሣሪያ በመግዛትና ማሠልጠኛ በማመቻቸት በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተነስቶ የነበረውን ሁከት እንዲቀጥል ሲያደርጉ እንደነበር ገልጿል፡፡
በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በምርጫ ሳይሆን በትጥቅ ትግል ከሥልጣን ማስወገድ እንዲቻል፣ በውጭና በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጥምረት በመፍጠር የሽብር ተግባር መፈጸም እንዳለባቸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመቀበል መስማማታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ አባላት በመመልመልና በማደራጀት ለሥልጠና ወደ ኤርትራ እንዲልኩም ተልዕኮ እንደተሰጣቸው አክሏል፡፡
ተከሻሹ በ2007 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ለቡድኑ አባላትን መልምለውና ወታደራዊ ቤዝና ማሠልጠኛ ወዳላት ኤርትራ በሁመራ በኩል መላካቸውን፣ በታኅሳስ ወር 2008 ዓ.ም. ከተለያዩ አካባቢዎች 11 የሽብር ቡድን አባላትን ቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሰብስበው መንግሥትን ከሥልጣን ማስወገድ የሚቻለው በሕዝባዊ አመፅ መሆኑን፣ አመጽ ለመፈጸም ደግሞ የጦር መሣሪያ ስለሚያፈልግ እያንዳንዱ አባል ሌላ አባላት በመመልመል፣ በማደራጀትና በማስፋፋት የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል አንዱን ብሔር በሌላኛው ብሔር ላይ እንዲነሳ ማድረግ እንዳለባቸው ተልዕኮ መስጠታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡
ተከሳሹ በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. ሰሜን ሸዋ ውስጥ ለሽብር ቡድኑ ወታደራዊ ቤዝ የሚሆን ቦታ በመምረጥ፣ ከደብረ ብርሃንና አዲስ አበባ የተመለመሉ ዘጠኝ አባላትን ወደ ማሠልጠኛ በመላክ ሥልጠና ማስጀመራቸውንም ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡
በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. አቶ ማሙሸት ዘመነ ምሕረቱ ከተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ቡድን አመራርና ለገሰ ወልደሀና ከተባለ የቡድኑ አባል ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመሰብሰብ፣ በጎንደር ተቀስቅሶ የነበረውን ሁከት እንዲስፋፋና እንዲቀጥል ሰሜን ሸዋ ጫካ ውስጥ በመግባት፣ በአካባቢው የሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችና የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጥቃት እንዲደርስ ተልዕኮ መስጠታቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
በአጠቃላይ አቶ ማሙሸት የሽብርተኛነት አዋጅ ቁጥር 652/2001ን በመተላለፍ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም የማቀድ፣ የመዘጋጀት፣ የማሴርና የማነሳሳት ሙከራ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ክስ ቀረቦባቸዋል፡፡ ተከሳሹ ዋስትና ተከልክለው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሲሆኑ፣ በግላቸው ጠበቃ ማቆም አለማቆማቸውን ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ምላሽ እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፦ ሪፖርተር
የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የቀረበበት የዶ/ር መረራ አቤቱታ ለመጪው ዓመት ተቀጠረ
በታምሩ ጽጌ

ዶ/ር መረራ ጉዲና
የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን በመጥቀስ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን መከልከሉን የተቃወሙት መረራ ጉዲና (ዶ/ር)፣ ጉዳያቸው የሕገ መንግሥት ትርጉም ስለሚያስፈልገው የአጣሪ ጉባዔውን ውሳኔ እንዲጠይቁ ተነገራቸው፡፡ ውሳኔውን የሚሰሙት በሚቀጥለው ዓመት ነው፡፡
ሦስት የተለያዩ የወንጀል ክሶች የተመሠረቱባቸው ዶ/ር መረራ በክሶቹ የተጠቀሱባቸው የሕግ አንቀጾች የምስክሮችና የማስረጃ ዝርዝሮች እንዳይደርሳቸው የማይከለክሉ መሆኑን በመግለጽ፣ ከሳሽ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/01 አንቀጽ 32ን በመጥቀስ እንዳይሰጣቸው መከልከሉን ተቃውመው ነበር፡፡
ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1)ሀ፣ ለ፣ 38(1)፣ 27(1)፣ 238(1) እና (2)ን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 12(1)፣ 2(1) የወንጀል ሕግ 486(ለ) ማለትም በጋራ በመተባበር፣ ወንጀል ለማድረግ በማደም፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ወንጀል ለማድረግ በመስማማት፣ የሐሰት ወሬ በማውራትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የመጣስ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ሳለ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 32 በመጥቀስ የምስክሮች ዝርዝር እንዳይሰጣቸው መከልከሉ ተገቢ ያልሆነና ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቀረበለትን የመቃወሚያ አቤቱታ የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም?›› በማለት ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አጣሪ ጉባዔ የላከው ቢሆንም፣ ውሳኔው ሊደርስ ባለመቻሉ ለቀጣይ ዓመት ጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የምስክሮች ዝርዝር ‹‹ለተከሳሽ ሊሰጥ ይገባል ወይስ አይገባም?›› የሚሉ ጥያቄዎች የተነሱት በዶ/ር መረራ ክስ ብቻ አለመሆኑን የጠቆመው ፍርድ ቤቱ፣ በርካታ የክስ መዝገቦች ላይ ጉዳዩ በመነሳቱ ቀደም ብሎ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም የሚለውን ምክር ቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሷል፡፡ ምክር ቤቱ ግን ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ መላኩን ከመግለጽ ውጪ ያለው ነገር ስለሌለ ውሳኔውን መጠበቅ የግድ እንደሚል አስረድቷል፡፡
የዶ/ር መረራ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ዶ/ር መረራ ከታሰሩ ዘጠኝ ወራት ሞልተዋቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ደግሞ የዓመቱን ሥራ ሊያጠናቅቅ የቀረው ከ15 ቀናት አይበልጥም፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በራሱ የመተርጎም ሥልጣን ስላለው ተርጉሞ ወይም የምክር ቤቱ ውሳኔ የሚፈጥንበት ሁኔታ ካለ ተባብሯቸው፣ ወደሚቀጥለው ዓመት ከመተላለፉ በፊት ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ዶ/ር መረራ በክርክር መቃወሚያቸው ምክንያት ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ለትርጉም መላኩን አስታውሶ፣ የመቃወሚያ ሐሳባቸውን ለማንሳት ፈልገው ከሆነ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡ የዶ/ር መረራ ጠበቆች ተመካክረው ምላሽ ሲሰጡ መቃወሚያ ያቀረቡት ሕጉ በሚፈቅድላቸው መሆኑን በመጠቆምና ፍርድ ቤቱም ትዕዛዝ እንደሰጠበት ተናግረው፣ መቃወሚያቸውን እንደማያነሱ ገልጸዋል፡፡
በመቀጠልም ዶ/ር መረራ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንኳን ሳይሰጡ እየተጉላሉ መሆኑን ገልጸው፣ ጉዳዩ በአጭር ቀናት ውስጥ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ መቃወሚያችሁን አንሱ የሚል ጥያቄ አለማቅረቡን ገልጾ፣ እሳቸው በራሳቸው ተነሳሽነት መቃወሚያቸውን እያነሱ ስለመሆናቸው ለማወቅ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ዶ/ር መረራም ሆኑ ሌላ ተከሳሽ እንዲመላለስና እንዲጉላላ ፍላጎት እንደሌለው በመንገር፣ መዝገቦችን የሚያስተናግደው ክስ በተመሠረተበት ጊዜ (ዕድሜ) ቅደም ተከተል ከመሆኑ አንፃር የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ መጠበቁ ለተከሳሹም ሆነ ለፍርድ ቤቱ ጥቅም ስላለው፣ ለጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. መሸጋገሩ የግድ መሆኑን በማስረዳት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የዶ/ር መረራ ጠበቃ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም፣ የጥብቅና ፈቃድና ውክልና እያላቸው ማረሚያ ቤት ደንበኛቸውን እንዳይጎበኙና እንዳያነጋግሩ እንደከለከላቸው ላቀረቡት ጥያቄ፣ ማረሚያ ቤቱ እንዲያገናኛቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ዘገባው ይሪፖርተር ነው።
ፖሊስ በወልቃይት ኮሚቴዎች ላይ አንድ ምስክር ለማቅረብ የበጀት እጥረት ገጥሞኛል አለ
በጌታቸው ሺፈራው
• ‹‹ደንበኞቻችን እየተንገላቱ ነው›› ጠበቆች

በእስር ላይ የሚገኙ የወልቃይት ኮሚቴ አባላት በከፊል
የፌደራል ፖሊስ በሽብር ተከሰው ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ የሚገኙት የወልቃይት ኮሚቴ አባላት ላይ በተደጋጋሚ ያልቀረበውን አንድ ምስክር አስሮ እንዲያቀርብ በፍርድ ቤት ታዞ የነበር ቢሆንም ምስክሩ የሚኖረው ትግራይ ክልል በመሆኑ እና በጀት ስላልተለቀቀልኝ ምስክሩን አስሮ የሚያመጣ አባል መላክ አልቻልኩም ሲል ዛሬ ሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት መልሱን በደብዳቤ ገልፆአል።
አቃቤ ህግም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ አጋጠመኝ የሚለውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ምስክሩን ይዞ እንዲያቀር ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆአል። በሌላ በኩል የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኞቻቸው እስር ቤት ከመሆናቸውም ባሻገር ፖሊስ ያቀረበው ምክንያት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ምስክሩ ታልፎ ለብይን እንዲቀጠርላቸው ጠይቀዋል። አቃቤ ህግ ለመመስከር የሚመጡትን ምስክሮች አልፈልጋቸውም ብሎ እያሰናበተ፣ የማይገኝና የሌለ ምስክር አመጣለሁ በማለት ደንበኞቻቸውን እያንገላታ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተውታል።
‹‹ትግራይ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። በአከባቢው የክልሉ ፖሊስ አለ። ፖሊስ ምስክሩን ማቅረብ ቢፈልገግ በቀላሉ ማቅረብ ይችላል ነበር።›› ሲሉ ፖሊስ ሆን ብሎ በደንበኞቻቸው ላይ በደል እየፈፀመ እንደሆነ ገልፀዋል። አቃቤ ህግና ፖሊስ ቀጠሮ በማራዘም ደንበኞቻቸው ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈፀሙ ነው ያሉት ጠበቆቹ ‹‹የታሰረው ሰው ነው። ሰውን እስር ቤት አስቀምጠው ምስክሩን ለማቅረብ በጀት የለንም ማለት የተከሳሾችን ሰብአዊ መብት መጣስ ነው። የቀረበው ምክንያትም አሳማኝ ባለመሆኑ ምስክሩ ይታለፍ›› የሚል አቤቱታ አቅርበዋል።
ይሁንና ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የሰጠውን ምክንያት ታሳቢ አድርጌያለሁ በሚል የመጨረሻ ቀጠሮ ሰጥቶአል። እነ መብራቱ ለአራተኛ ጊዜ ለምስክር ተቀጥረው ምስክሩ ከመቅረቱም በተጨማሪ የዛሬው ቀጠሮ ለመጨረሻ እንዲሆን እና ፖሊስ ምስክሩን አስሮ ማምጣት ካልቻለ ምስክሩ ታልፎ መዝገቡ ተመርምሮ ብይን ለመስጠት ሊቀጠር ይገባ እንደነበር ገልፀዋል። ፖሊስ በበጀት ምክንያት ማቅረብ አልቻልኩም ያለውን ቀሪ አንድ ምስክር ለመስማት ለነሐሴ 11 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
በሽብር የተከሰሰው ወጣት ህክምና ተከልክሎ እንደሞተ ተገለፀ
በጌታቸው ሺፈራው
• ‹‹አውቀው ነው የገደሉት፡፡ እኛንም ይገድሉናል!›› 1ኛ ተከሳሽ መልካሙ ክንፈ
• ‹‹ይህን የሚያደርገው መንግስት ከሆነ ቁርጡን አውቀነው እንሞታለን!›› 4ተኛ ተከሳሽ ይማም መሃመድ

አቶ አየለ በየነ
በእነ መልካሙ ክንፈ የክስ መዝገብ በሽብር ተከሶ ቂሊንጦ እስር ቤት ታስሮ የነበረው ወጣት አየለ በየነ ነገሰ ህክምና እንዳያገኝ ተከልክሎ እንደሞተ ተገለፀ፡፡ ወጣት አየለ በየነ ህክምና ተከልክሎ ለሞት እንደተዳረገ በአባሪነት የተከሱት ዛሬ ሀምሌ 18/2009 ዓ.ም ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4 ወንጀል ችሎት ገልፀዋል፡፡
ተከሳሾቹ የፀረ ሽብር አዋጁ ከሚፈቅደው አራት ወር በተጨማሪ 5 ወር በአጠቃላይ 9 ወራትን ማዕከላዊ ታስረው እንደቆዩ የተገለፀ ሲሆን ሟች ለረዥም ጊዜ ታሞ ህክምና ቢጠይቅም ህክምና ሳይገኝ ቀርቷል ተብሏል፡፡ ህመሙ ከጠናበት በኋላም ከ10 ቀን በላይ ምግብ መብላት ባለመቻሉ ለእስር ቤቱ አስተዳደሮች በቀን ከሶስት ጊዜ ባላይ ህክምና እንዲያገኝ ጥያቄ ቢያቀርቡም መልስ ሳያገኙ መቅረታቸውንና በመጨረሻ ከእስር ቤቱ ውጭ እንዲታከም ቢታዘዝለትም በተቋሙ ቶሎ ህክምና ማግኘት ባለመቻሉ ህይወቱ ማለፉን ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል፡፡
ቀሪዎቹ ተከሳሾችም ህክምና ሊያገኙ ባለመቻላቸው ለህይወታቸው እንደሚሰጉ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታቸው አሰምተዋል፡፡ 1ኛ ተከሳሽ መልካሙ ክንፈ ታሞ በየወሩ ህክምና እየወሰደ የነበር ቢሆንም መርማሪዎች የፈለጉትን መረጃ ስላልስጠ ህክምና መከልከሉንና የሟች እጣፈንታ ሊደርስበት እንደሚችል ስጋቱን ለፍርድ ቤት ገልፆአል፡፡ ‹‹አውቀው ነው የገደሉት፡፡ እኛንም ይገድሉናል፡፡›› ያለው 1ኛ ተከሳሽ ንፁህ በመሆናቸውና መረጃ ስላልተገኘባቸው ህጉ ከሚፈቅደው ውጭ ለ9 ወራት ማዕከላዊ መቆየታቸው ይህም ለንፁህነታቸው ማስረጃ እንደሆነ ገልፆአል፡፡ ማች ንፁህ በመሆኑም ክሱ እንዳይቋረጥ፣ ምስክሮችም ተሰምተው የፍርዱን ሂደት ማወቅ እንደሚፈልጉ ገልጾአል፡፡
ሌሎች ተከሳሾም ተመሳሳይ ችግር እንደገጠማቸው የተገለፀ ሲሆን 4ኛ ተከሳሽ ይማም መሃመድ ‹‹ይህን የሚያደርገው መንግስት ከሆነ ቁርጡን አውቀነው እንሞታለን›› ሲል ገልፆአል፡፡ ‹‹አየለን ሞተ ማለት አልችልም፡፡ ተቀጠፈ ነው የምለው፡፡ የሞተው ዘመድ አጥቶ አይደለም፡፡ ጓደኛና ቤተሰብ አጥቶ አይደለም፡፡ የሞተው ህክምና የሚሰጠው አጥቶ ነው›› ሲልም አክሏል፡፡
ባለፉት ቀጠሮዎች ሟችን ፍርድ ቤት ሳያቀርብ የቀረውን ቂሊንጦ እስር ቤት ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን የማያቀርብበትን ምክንያት እንዲገልፅ ወይንም ተከሳሹን እንዲያቀርብ በጻፈለት ትዕዛዝ መሰረት ሀምሌ 17/2009 ዓ.ም ተከሳሽ መሞቱን ቢገልጽም በምን ምክንያት እንደሞተ እንዳልገለፀ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ቂሊንጦ ሟች በምን እንደሞተና ለሞቱ ማረጋገጫ ባልላከበት ሁኔታ ግለሰቡ መሞቱን እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል እስር ቤቱ ለሀምሌ 26/2009 ዓ.ም ተከሳሹ ስለመሞቱ የሚያሳይ ማረጋገጫና የሞተበትን ምክንያት እንዲያመጣ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
አየለ በየነ በመዝገቡ ስር 2ኛ ተከሳሽ የነበር ሲሆን ከኦነግ መሪ ዳውድ ኢብሳ ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና ሀገር ውስጥ ያሉ መረጃዎችን ሪፖርት አድርጓል የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር፡፡ የሟች ታናሽ ወንድም ቦንሳ በየነም በዚሁ ክስ መዝገብ ስር ክስ ተመስርቶበታል፡፡ በመዝገቡ ስር፡-
1.መልካሙ ክንፉ ተፈሪ
2. አየለ በየነ ነገሰ
3. ቦንሳ በየነ ነገሰ
4. ይማም መሃመድ ኬሮ
5. ለሜሳ ግዛቸው አባተ
6. ኩመራ ጥላሁን ዴሬሳ
7. መያድ አያና አቶምሳ
8. ሙሉና ዳርጌ ሩዳ የተከሰሱ ሲሆን ተመሳሳይ ችግር እየደረሰባቸው እንደሆነ ተገልፆአል፡፡