አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከኦነግ ጋር ተያይዞ የሽብር ክስ ተመሰረተበት
የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና በምርጫ 2007 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ወረዳ 17 የፓርላማ እጩ ተወዳዳሪ የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 የወጣውን አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን ተላልፏል በሚል ክስ ተመስርቶበታል፡፡

ሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ክሱ በዳኞች ቢሮ በንባብ የተሰማበት አቶ ዮናታን ተስፋዬ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሽፋን በማድረግ ከህዳር 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተከሳሹ በሚጠቀምበት ድረ-ገፅ በተለይም ፌስቡክ አማካኝነት በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን “አመፅና ብጥብጥ” ለማስቀጠል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ን ዓላማ ተቀብሎ ተንቀሳቅሷል ሲል አቃቤ ህግ ክስ መስርቶበታል፡፡ የክስ ፋይሉ ሌላ ተከሳሽ ውጭ ለአቶ ዮናታን ብቻ የቀረበበት የማስረጃ ዝርዝር በማኀበራዊ ሚዲያ የለጠፋቸው ፅሑፎች ናቸው፡፡
በዚህም ተከሳሹ የቡድን (ኦነግ) ዓላማን ለማሳካት አመፅና ብጥብጥ እንዲቀጥልና ሌሎችን ለማነሳሳት አስቦ በሚጠቀምበት ድረ-ገፅ (ፌስቡክ) ቀስቃሽ ፅሑፎችን በመፃፍ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም ማቀድ፣ ማዘጋጀት፣ ማሴር እና ማነሳሳት ወንጀል ክስ በአቃቤ ህግ እንደቀረበበት ታውቋል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ በተለያዩ ቀናት በግል የፌስቡክ ገጹ ላይ ያስነበባቸው ፅሑፎች ክሱ ላይ ተካተው በማስረጃነት ቀርቦበታል፡፡
ታህሣሥ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ለጭቆና መሳሪያነት የሚያገለግሉ ማናቸውንም ቁሳቁሶች ማቃጠልና ማውደም እንዲሁም መንገድ መዝጋትን በተመለከተ፣ ታህሣሥ 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ኢህአዴግ ችግር ማዳፈን እንጂ ችግር መፍታት አይችልም በሚል የፃፈው፣ ታህሣሥ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲጀመር ምንም ዓይነት መሪ ዕቅድ (ማስተር ፕላን) የለም በሚል የፃፈው፣ ታህሣሥ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. የተቃውሞ ትግሉ ቀጥሏል በሚል የፃፈው፣ ህዳር 28 ቀን 2008 ዓ.ም. እነሆ 7 መልዕክት ብሎ በፃፈው እና በሌሎችም ፅሑፎች አማካኝነት ቅስቀሳ አድርጓል ሲል አቃቤ ህግ ክስ አቅርቦበታል፡፡
ዮናታን ተስፋዬ በነጠላ መዝገብ ብቻውን ክስ የተመሰረተበት ሲሆን፤ በዕለቱ ክሱ በንባብ በተሰማበት ወቅት ዳኛ አልተሟላም በሚል ምክንያት በዳኞች ቢሮ መታየቱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የክሱን ሂደት ዬናታን ቤተሰቦችም፣ ወዳጆችና ጋዜጠኞች በችሎት መታደም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ አቶ ዮናታንም የክስ መቃወሚያውን ይዞ ለፊታችን ግንቦት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲቀርብ ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡
ምንጭ፡- EHRP.
ነባር የኢሕአዴግ አመራሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለመከላከያ ምስክርነት ተቆጠሩ
ምሁራንና ፖለቲከኞችም ተካተዋል
በታምሩ ጽጌ

ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ሲሄዱ ማይካድራ በተባለ ቦታ ላይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተለገጸውና በሽብር ድርጊት ወንጀል የተከሰሱ አራት ተጠርጣሪዎች፣ አቶ በረከት ስምኦን፣ አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ አቶ ስብሀት ነጋ (አቦይ ስብሃት)፣ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ ጄነራል ሳሞራ የኑስንና ሌሎችንም ነባር ታጋዮችንና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ 141 ሰዎች በመከላከያ ምስክርነት ቆጠሩ፡፡
መከላከያ ምስክሮቹን የቆጠሩት ተጠርጣሪዎች የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት የነበሩት አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ወ/ሪት እየሩሳሌም ተስፋውና አቶ ፍቅረማርያም አስማማው ናቸው፡፡ በክሱ ከላይ የተጠቀሱትን ተጠርጣሪዎች ወደ ኤርትራ ድንበር እንዲሻገሩ በመምራት የተጠረጠረው አቶ ደሴ ካህሳይም ተካቷል፡፡
ተከሳሾቹ ከዓመት በፊት የካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ የተመሠረተባቸው፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) ወንጀል ሆኖ የተደነገገውን ለሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ መሳተፍን ተላልፈዋል በሚል ነው፡፡
ተከሳሾቹ ከላይ የተጠቀሱትን የሕግ ድንጋጌዎች በመተላለፍ፣ የሰው ሕይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም፣ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ፖለቲካዊ ሥልጣን ለመያዝ እየተንቀሳቀሰ ካለው የግንቦት ሰባት ድርጅት ጋር አብሮ ለመሥራት መዘጋጀታቸውም ተጠቅሷል፡፡ ከአዲስ አበባ ተነስተው በባህር ዳር፣ በጎንደርና በሁመራ አድርገው ወደ ኤርትራ ለመሻገር ሲንቀሳቀሱ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች የመረመረው ፍርድ ቤቱ፣ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ታኅሳስ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ብይን ሰጥቶ ነበር፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤቱ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን (141) በዝርዝር ጽፈው አቅርበዋል፡፡ ከምስክሮቻቸው መካከል ለአቶ በረከት ስምዖን፣ ለአቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ ለአቶ አዲሱ ለገሰ፣ ለወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ፣ ለአቶ ተፈራ ዋልዋ፣ ለአቶ ስብሀት ነጋ (አቦይ ስብሀት)፣ ለወ/ሮ ፍሬ ሕይወት አያሌው፣ ለዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ ለጄኔራል ሳሞራ የኑስና ለአቶ ቴዎድሮስ ሐጐስ እነሱ መጥሪያ ለማድረስ እንደማይችሉ (ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመሆናቸው) በፍርድ ቤቱ በኩል እንዲደርሳቸው እንዲደረግ አመልክተዋል፡፡
ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፣ ለዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ለአቶ አስገደ ገብረ ሥላሴ፣ ለአቶ ገብሩ አሥራት፣ ለወ/ሮ አረጋሽ አዳነ፣ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ (ቃሊቲ)፣ ለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ (ቃሊቲ)፣ ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (ዝዋይ)፣ ለአምስት ጦማሪያን፣ ለጠበቃ ተማም አባቡልጉ፣ ለኢንጂነር ይልቃል ጌትነት (ሰማያዊ ፓርቲ) ጨምሮ በድምሩ 141 የመከላከያ ምስክሮችን በመቁጠር ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል፡፡ ረቡዕ ሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡
ምንጭ፡-ሪፖርተር ጋዜጣ
እነ ኦኬሎ አኳይ እስከ 9 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ
የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት እነ ኦኬሎ አኳይ እስከ ዘጠኝ ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ቀጣ፡፡ ተከሳሾችም ሆኑ የፌደራል አቃቤህግ የቅጣት አስተያየታቸውን ሚያዚያ 17 ቀን 2008ዓ.ም ለፍርድቤቱ ያመለከቱ ሲሆን ፍረድቤቱ የግራ ቀኙን አይቶ ዛሬ ሚያዚያ 19 ቀን 2008 የእስራት ፍርድ ስጥቷል፡፡

አቃቤህግ ተከሳሾች የተሸሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ስራ ላይ ውሎ በነበረበት ግዜም ጭምር ወንጀል መፈፀማቸውን ቀጥለውበት የነበረ መሆኑን ገልፆ ፍርድቤቱ ቅጣት ሲያስተላልፍ በተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ እንዲያደርግ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም ፍርድቤቱ የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በአመዛኙ የተሸሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ከመውጣቱ በፊት በመሆኑ እና በድርጊቱም የተጎዳ ሰውም ሆነ ንብረት ስለሌለ የአቃቤውን ጥያቄ አልተቀበለም፡፡
ተከሳሾች ሲያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ በሰው ህይወት፣ንብረት እና አጠቃላይ በሀገር ደህንነት ላይ ሊያስከትል ከሚችለው ችግር አንፃር በመመዘን የተከሳሾቹን የወንጀል አፈፃፀም በከባድ በማለት ፍርድቤቱ መድቦ እንዲቀጡ አቃቤህግ የጠየቀውን ውድቅ ያደረገው ፍርድቤቱ ተከሳሾች የወንጀል ተግባሩን የፈፀሙት ቡድን መስርተው በስምምነት በመሆኑ እንደማክበጃ የወ/ህ/ቁ 84/1/መ/ እንዲያዝለት አቃቤህግ ያመለከተውን ተቀብሎታል፡፡
ተከሳሾች በበኩላቸው ከዚህ በፊት በምንም አይነት ወንጀል ተከሰው የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዳልተላለፈባቸው፣ሁሉም ተከሳሾች የቤተሰብ አስተዳዳሪ ሰለመሆናቸው ታሳቢ ተደርጎ ቅጣት እንዲቀልላቸው ያመለከቱተን ፍርድቤቱ የተቀበለ ሲሆን አንደኛ ተከሳሽ በጋምቤላ ክልል ከ1978 እስከ 1992 ለ13 ዓመታት በጤና ቢሮ የተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች እስከ ክልሉ ፕሬዝዳንትነት የክልሉን ህዝብና የፌደራሉን መንግስት ያገለገሉ መሆኑን ጠቅሰው እንደ ቅጣት ማቅለያ እንዲያዝላቸው ያመለከቱትን ግን ፍርድቤቱ አልተቀበለውም፡፡
በዚህም አንደኛ ተከሳሽ ኦኬሎ አኳይ የጋምቤላ ህዘቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) አባል በመሆን እና የጋምቤላ ክልልን ከፌደሬሽኑ ለመገንጠል በቡድን ሆኖ የአመራር ሚናን በኃላፊነት በመምራታቸው በዘጠኝ አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድቤቱ ወሰኗል፡፡
ሁለተኛ ተከሳሽ ዴቪድ ኡጁሉ የጋምቤላ ህዘቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) አባል እና የውጪ ጉዳይ ኃላፊ በመሆን የጋምቤላ ክልልን ከፌደሬሽኑ ለመገንጠል ቡድኑን በአመራር በማገልገላቸው በተመሳሳይ በዘጠኝ አመት ፅኑ እስራት ቀጥቷል፡፡
ከሶስተኛ እስከ ሰባተኛ ያሉ ተከሳሾች (ኡቻን ኦፔይ፣ ኡማን ኝክየው፣ ኡጁሉ ቻም፣ አታካ ኡዋር እና ኡባንግ ኡመድ ) በጋምቤላ ህዘቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) አባል በመሆን የተለያዩ ተሳትፎዎችን በማድረጋቸው ሁሉም ተከሳሾች በሰባት አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድቤቱ ወሰኗል፡፡
በሰኔ ወር 2006ዓ.ም በፌደራል አቃቤህግ ክስ የተመሰረተባቸው እነ ኦኬሎ አኳይ ለሁለት አመት ከማንኛውም ህዝባዊ መብቶቻቸው እንዲታገዱ ፍርድቤቱ አዟል፡፡
ምንጭ፡-http://ehrp.org
አቃቤህግ እነ ኦኬሎ አኳይ በከባድ ወንጀል ክስ እንዲቀጡ ጠየቀ
በሰኔ 2006ዓ.ም በፌደራል አቃቤህግ የሽብር ክሰ ተመስርቶባቸው ክሳቸው በከፍተኛው ፍርድቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት እየታየላቸው የሚገኙት እነ ኦኬሎ አኳይ(ሰባት ሰዎች) መጋቢት 28 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት ጥፋተኛ ስለመሆናቸው ፍርድቤቱ ውሳኔ ካስተላለፍ በኃላ ከሁለቱም ተከራካሪዎች የቅጣት አስተያየት ለመስማት ለዛሬ ሚያዚያ 17 ቀጠሮ ስጥቶ ነበር፡፡

ተከሳሾችም ሆኑ አቃቤህግ የቅጣት አስተያየታቸውን ለፍርድቤቱ ያቀረቡ ሲሆን አቃቤህግ ተከሳሾች የተሸሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ስራ ላይ ውሎ በነበረበት ግዜም ጭምር ወንጀል መፈፀማቸውን ቀጥለውበት የነበረ መሆኑን ገልፆ ፍርድቤቱ ቅጣት ሲያስተላልፍ በተሻሻለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
ከአንደኛ አስከ ሶስተኛ ያሉ ተከሳሾች የወ/ህ/ቁ 27/1/፣ 32/1/ሀ፣ 38 እና 241 በመተላለፍ ወንጀል ለመፈፀም በተቋቋመ ቡድን አመራር፣ አባል፣የደህንነት ዘርፍ እንዲሁም የውጭ ግንኙነት ሃላፊ በመሆን፣ ገንዘብ በማሰባሰብ እና አባላትን በመመልመል ፣ የቡድኑ አባላት ወታደራዊ ስልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ መሳሪያ በመግዛት፣የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለማግኘት ከኤርትራ መንግስት ጋር እና ከኦነግ እና ግንቦት ሰባት ከተባሉ ቡድኖች ጋር በመደራደር በከፍተኛ አመራርነት ሲንቀሳቀስሱ የነበረ መሆኑን አቃቤህግ ጠቅሶ ተከሳሾች ሲያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ በሰው ህይወት፣ንብረት እና አጠቃላይ በሀገር ደህንነት ላይ ሊያስከትል ከሚችለው ችግር አንፃር በመመዘን ፍርድቤቱ የተከሳሾቹን የወንጀል አፈፃፀም በከባድ በማለት እንዲመድብ ጠይቋል፡፡
የቡድኑን አላማ አውቀው፣ በቡድኑ ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ ጥቃት ለመፈፀም በዝግጅት ላይ ነበሩ ያላቸውን ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ ያሉ ተከሳሾች የወንጀል አፈፃፀማቸው በመካከለኛ ይመደብልኝ ሲል የጠየቀው አቃቤህግ ሁሉም ተከሳሾች የወንጀል ተግባሩን የፈፀሙት ቡድን መስርተው በስምምነት በመሆኑ እንደማክበጃ የወ/ህ/ቁ 84/1/መ/ እንዲያዝለት አመልክቷል፡፡
ተከሳሾች በበኩላቸው በጠበቃቸው አማካኝነት ጥፍተኛ የተባሉት ከ2006 ዓ.ም በፊት ፈፅማቹኃል በተባለው ድርጊት መሆኑ ከቀረበባቸው ክስም ሆነ ፍርድቤቱ በሰጠው ውሳኔ እንድሚታወቅ አስረድተው፣ ለጥፋተኝንት ውሳኔው መሰረት የሆኑት ድርጊቶች ተፈፀሙ በተባለበት ጊዜ በስራ ላይ በነበረው እና በ2002 ዓ.ም በወጣው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ፍርድቤቱ እንዲወስንላቸው ጠይቀዋል፡፡
የወንጀል ህጉ አንቀፅ241 ስር በተደነገገው እና ተከሳሾች ጥፋተኛ በተባሉበት የወንጀል ድርጊት በየትኛውም አካል ላይ ስለመድረሱ የተረጋገጠ የገንዘብም ሆነ የአካል ወይም የህይወት አደጋ የለም ያሉት ተከሳሾቹ ፈፀሙ በተባሉት ወንጀል የደረሰ ጉዳት ባለመኖሩ የወንጀሉ አፈፃፀም ቀላል በሚል ሊያዝ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል፡፡ ተከሳሾች የቅጣት ማቅለያዎንም ፍርድቤቱ እንዲቀበላቸው ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ በፊት በምንም አይነት ወንጀል ተከሰው የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዳልተላለፈባቸው፣ሁሉም ተከሳሾች የቤተሰብ አስተዳዳሪ ሰለመሆናቸው እንዲሆም አንደኛ ተከሳሽ በጋምቤላ ክልል ከ1978 እስከ 1992 ለ13 ዓመታት በጤና ቢሮ የተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች እስከ ክልሉ ፕሬዝዳንትነት የክልሉን ህዝብና የፌደራሉን መንግስት ያገለገሉ በመሆኑ እንደ ቅጣት ማቅለያ እንዲያዝላቸው አመልክተዋል፡፡
ፍርድቤቱ የቅጣት አስተያየቶቹን ተመልክቶ የቅጣት ፍርድ ለመስጠት ለረቡዕ ሚያዚያ 19 ቀን 2008 ቀጠሮ ስጥቷል፡፡
ምንጭ፡-ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ፕሮጀክት (EHRP)
በጋምቤላ ክልል በድጋሚ በ21 ዜጎች ላይ ግድያ ተፈጸመ
ባለፈው ሳምንት ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ በጋምቤላ ክልል የደረሰው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የፈጠረው ሐዘን ሳይሽር፣ በድጋሚ ሌላ አሰቃቂ ግድያ በ21 ዜጎች ላይ ተፈጸመ፡፡

ሐሙስ ሚያዝያ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በጋምቤላ ክልል ጀዊ ስደተኞች ካምፕ የሚኖሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች፣ 21 ሰዎች ገድለው ሰባት ሰዎች ማቁሰላቸውን ሪፖርተር ከሥፍራው የደረሰው መረጃ አመልክቷል፡፡
የግድያው ምክንያት ሐሙስ ረፋድ ላይ በጋምቤላ ከተማ ከሚገኙ ስድስት ካምፖች አንዱ በሆነው ጀዊ ስደተኞች ካምፕ ውኃ የሚያመላልስ ቦቴ ተሽከርካሪ፣ ብስክሌት ይጫወቱ የነበሩ ሁለት ሕፃናት ስደተኞች ላይ አደጋ ማድረሱ ነው፡፡ በድንገተኛው የተሽከርካሪ አደጋ የሕፃናቱ ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ስደተኞቹ ይህ አደጋ ሆን ተብሎ የደረሰ ነው በማለት ወዲያውኑ በኢትዮጵያውያን ላይ አደጋ ማድረስ ጀመሩ፡፡
በአደጋው እስካለፈው ዓርብ ድረስ የ21 ሰዎች አስከሬን ተሰብስቦ ወደ ጋምቤላ ሆስፒታል የተጓጓዘ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል የጋምቤላ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ስደተኞቹ ደቡብ ሱዳናውያን ድንጋይ፣ ገጀራና ጦር በመጠቀም በሥፍራው በአሸዋ ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ መፈጸማቸው ተነግሯል፡፡ ጭፍጨፋው የተካሄደበት ቦታ ጫካማ በመሆኑ ራሳቸውን ለማዳን ወደ ጫካ የሸሹ ሰዎች በመኖራቸው፣ በወቅቱም ያልተገኙ ሰዎች ስለነበሩ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የቆሰሉ ሰዎች ጋምቤላ ክልል ውስጥ በምትገኘው ቦንጋ ከተማ ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህ ጭፍጨፋ የተሽከርካሪ አደጋን ምክንያት ያድርግ እንጂ፣ የክልሉ ነዋሪዎች መሰንበቻውን በክልሉ የተከሰቱት ጭፍጨፋዎች ከዚህ ቀደም ታይተው በማይታወቁ መንገዶች የተፈጸሙ በመሆናቸው ከፍተኛ ሥጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡
ጋምቤላ ሚያዝያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት በደረሰው ጭፍጨፋ የ182 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ ከዚህ ቀደም ባሉት ቀናት ከነበረው ግድያ ጋር በድምሩ የ208 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ታውቋል፡፡ 72 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ይታወቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ 36 ሕፃናት በዕለቱ ታፍነው ሲወሰዱ ቀደም ባሉት ቀናት ከተወሰዱት ጋር የታፈኑት ሕፃናት ቁጥር 108 ደርሷል፡፡ ከ2,000 በላይ ከብቶች ተነድተዋል፡፡ ይህ ዘግናኝ ክስተት መላ ኢትዮጵያውያን ለከፍተኛ ሐዘን ዳርጎ ባለበት ወቅት፣ በድጋሚ በሳምንቱ ተመሳሳይ ጭፍጨፋ መከሰቱ ብዙዎችን አስቆጥቷል፡፡
ለሚያዝያ 7 ቀን ጥቃት መንግሥት አፀፋዊ ዕርምጃ በመውሰድና ሕፃናቱን ለማስለቀቅ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ዓርብ ሚያዝያ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ ታፍነው የተወሰዱ ሕፃናት ያሉበት ቦታ ተለይቷል፡፡ አቶ ተወልደ ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰው ጥቃት ከጀርባው የፖለቲካ አጀንዳ መኖር አለመኖሩ፣ ጥቃቱን ያደረሰው አካል ማንነት እየተመረመረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት ይህንን ግድያ በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ሕዝቡን ለማረጋጋት በተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ ላይ እንዳሉ ገልጸው፣ በሁለተኛው ግድያ ዙሪያ ሙሉ የተሟላ መረጃ እንደሌላቸውም ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ችግሩ የተከሰተው በተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት ለበቀል በተነሱ ስደተኞች መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ 272,648,300 የተለያዩ አገሮች ስደተኞችን ታስተናግዳለች፡፡ ከዚህ ውስጥ በጋምቤላ ክልል የሚገኘውና ይህ ጭፍጨፋ የተፈጸመበት ጀዊ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ 48,648 ስደተኞች ይገኛሉ እንደሚገኙ እና ስደተኞችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ስደተኞችና ስደት ተመላሾች ባለሥልጣን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ በሪፖርተር የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን በመጠቆም ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
በተለይ የትናንት በስቲያውን ግድያ ተከትሎ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ተቃውሞ በማሰማት የ21 ኢትዮጵያውያንን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደሚገኙበት ጀዊ ሲያቀኑ ከመከላከያ ሰራዊትና ከፖሊስ ግጭት በመፈጠሩ በኢትዮጵያውያኑ ግድያ ተቃውሞ ሲያሰሙ ከነበሩት መካከል ቢያንስ 2 ሰዎች በፀጥታ ኃይሉ በተወሰደ ርምጃ እንደተገደሉ የኢሳ ዘገባ አመልክቷል፡፡ አካባቢው ይህ እስከተዘገበበት ድረስ አለመረጋጋት እንደሚታይበት የአከባቢው ነዋሪዎች ይናራሉ፡፡
ምንጭ፡-ሪፖርተር ጋዜጣ እና ኢሳት