Category Archives: News

አትሌት ገንዘቤ ዲባባ አዲስ የዓለም ከብረ-ወሰን በማስመዝገብ አሸነፈች

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በስዊድን ስቶኮሎም የ2015 ዓለም አቀፍ የ5,000 ሜትር የቤት ውስጥ ዓለም አቀፍ ውድድር አሸነፈች፡፡ አትሌት ገንዘቤ ውድድሩን ያሸነፈችው ከዚህ ቀደም ተመዝግቦ የነበረውን ክብረ-ወሰን በማሻሻል ነው፡፡

አትሌት ገንዘቤ ዲባባ

አትሌት ገንዘቤ ዲባባ

ገንዘቤ ውድድሩን ያሸነፈችው 14 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ ከ86 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ነው፡፡ በውድድሩ ከዚህ ቀደም የነበረው የዓለም ክብረወሰን 14 ደቂቃ ከ24 ሰከንድ ከ37 ማይክሮ ሰከንድ ሲሆን፤ ይህም በኢትዮጵያዊቷ አትሌት መሰረት ደፋር ተይዞ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አትሌት ገነዝቤ ዲባባ የአትሌት ጥሩነሽ እና የአትሌት እጅጋየሁ ዲባባ ታናሽ እህት ስትሆን፤ በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ አዳዲስ የዓለም ክብረወሰን እያስመዘገበች ማሸነፏ ይታወቃል፡፡

ምርጫ ቦርድ ከ200 በላይ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችን ሰረዘ

  • “ምርጫ ቦርድ ሰማያዊ በምርጫ ሂደቱ እንዲቆይ አይፈልግም” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት

ELEC

ሰማያዊ ፓርቲ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከ200 በላይ ዕጩዎቹ በምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ እንደተሰረዙበት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በመላ አገሪቱ በተለይም በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በወላይታ፣ በቤንች ማጅ፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በሲዳማ፣ በከምባታ፣ በጋሞጎፋ፣ አዲስ አበባ፣ በደቡብ ጎንደርና ጉጅን ጨምሮ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ከ200 በላይ ዕጩዎቹ አንድን ዕጩ ለመሰረዝ የሚያበቃ ምንም አይነት ህጋዊ ምክንያት ሳይኖር “ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ታዘናል” በማለት ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤትና ለክልል ምክር ቤቶች ያስመዘገብናቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎቹን በመሰረዝ ከምርጫው ውድድር ውጪ እንዲሆኑ እየተደረገ እንደሆነ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት አስረድተዋል፡፡

በየክፍለ ሀገሩ የተሰረዙት ዕጩዎች “ፓርቲው ትብብር የሚባል ህገ ወጥ አደረጃጀት መስርቷል፣ የሌሎች ፓርቲዎች አባላት ናችሁ” የመሳሰሉ ምክንያቶችና ደብዳቤ የተሰጣቸው ሲሆን በአንጻሩ በአዲስ አበባ የተሰረዙት ዕጩዎች ከምርጫ አስፈጻሚዎች ምንም አይነት ምክንያትና ደብዳቤ እንዳልተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዕጩዎቹ “የተሰረዝንበትን ምክንያት ንገሩን፣ ደብዳቤ ልትሰጡን ይገባል” ቢሉም የምርጫ አስፈጻሚዎቹ “እኛ እናንተን ለመመዝገብ ችግር የለብንም፡፡ ግን ከበላይ አካል እንዳንመዘግብ ተነግሮናል፡፡ ደብዳቤም ልንሰጣችሁ አንችልም፡፡” የሚል መልስ እንደሰጧቸው ገልፀዋል፡፡

Semayawi-Party

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች መሰረዛቸውን ተከትሎ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የቦርዱን ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃናን ለማግኘት ቢጥሩም “ከከተማ ውጭ ናቸው፡፡ አሁን አታገኟቸውም” የተባሉ ሲሆን ፕ/ር መርጋ የህወሓትን 40ኛ አመት ለማክበር መቀሌ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በትናንትናው ዕለት በጉዳዩ ላይ ከቦርዱ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፌሳ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን አቶ ነጋ “ማመልከቻ አስገቡ” ከማለት ውጭ ዕጩዎቹ ለመሰረዛቸው ተጨባጭ ምክንያት መስጠት እንዳልቻሉ  ኢ/ር ይልቃል ገልጸውልናል፡፡

“የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችን ያለ አግባብ የሚሰርዙት ሰማያዊ በምርጫ ሂደቱ ጫና መፍጠር ስለሚችል በሂደቱ እንዲቆ ስለማይፈልጉ ነው” ያሉት ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት፤ ሆኖም ይህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ለነጻነት የሚያደርጉትን ትግል ትክክለኛ እንደሆነ እንዳስረገጠላቸው፣ ይህን የነፃነት ትግልም አጠናክረው እንደሚቀጥሉና የካቲት 22 ፓርቲያቸው ከትብብሩ ፓርቲዎች ጋር በ15 ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜ በ15 ከተሞች የሚያደርገው ሰልፍ የዚሁ የነጻነት ትግል አካል እንደሆነ መግለፃቸውን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያን ሴቶች የወሊድ መከላከያ እንዲወስዱ ተገደዋል መባሉን እስራኤል አመነች

ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ቤተ እስራኤላውያን ሴቶች ለረዥም ጊዜ የሚያገለግለውን ዴፖ ፕሮቬራ የተባለ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት ለመወጋት ካልተስማሙ ወደ እስራኤል ሊገቡ እንደማይችሉ ይነገራቸው እንደነበር ይታወቃል።

ክሊኒኩን ያስተድድር የነበረው “Joint Distribution Committee” እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውንጀላውን ማስተባበላቸው የሚታወስ ቢሆንም ዛሬ በወጣው ሪፓርት የእስራኤል መንግስት ውንጀላውን አምኗል።

ethio-jewish

በርካታ ሴቶች፣ በኢትዮጵያ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ሳሉ በክትባት መልክ የሚሰጠውን የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒት እንዲወስዱ እንዴት ያግባቧቸውና ያስፈራሯቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ቤተ-እስራኤላውያኑ ሲገልፁ “የማትወስዱ ከሆነ ወደ እስራኤል አትሄዱም፤ እርዳታና ህክምናም አታገኙ ተባልን፡፡ ይሄኔ ፈራን፤ ምንም ምርጫ አልነበረንም፡፡ ያለ እነሱ እርዳታ መውጣት አንችልም ነበር፡፡ ስለዚህ ክትባቱን ለመወጋት ተስማማን፡፡” ሲሉ ቤተ-እስራኤላውያን መናገራቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በመጥቀስ ዎርልድ ቡሌቲን ዘግቧል፡፡ ቤተ-እስራኤላውያኑ ከዚህ ቀደም በእስራኤል መንግሥትና ቀድመው እስራኤል በገቡ ዜጎች ከተለያዩ ማኀበራዊ የመንግሥት አገልግሎቶች ጭምር ይገለሉ እንደነበር መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር በ15 ከተሞች የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጠራ

“ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” በሚልመርህ የሚካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ የካቲት 22 ቀን 2007 ዓም በ15 ከተሞች እንደሚካሄድ ትብብሩ አስታውቋል።

ከግራ ወደ ቀኝ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከ(ሰማያዊ) እና አቶ ግርማ በቀለ ከ(ኦህዴህ)

ከግራ ወደ ቀኝ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከ(ሰማያዊ) እና አቶ ግርማ በቀለ ከ(ኦህዴህ)

“የሙስሊም ማህበረሰቡ ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓም በኑር መስጂድ ፣ የካቲት 6 ቀን 2007 ዓም ደግሞ በአንዋር መስኪድ ያደረገው ተቃውሞ እንዲሁም የባህርዳር ከተማ ህዝብ ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓም ያሳየው ህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል በሃይል ሊዳፈን ቢችልም እንደማይጠፋ ትምህርት ሰጥቷል” ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ትብብሩ፣ ገዢው ፓርቲ እያደረሰ ያለው የመብት ረገጣ፣ የሙስና መስፋፋትና የመልካም አስተዳደር እጦት የህዝቡን የለውጥ ፍላጎትና የትግል ተነሳሽነት እንዳሳደገው ገልጿል።

ትብብሩ ገዢው ፓርቲ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ከቃላት ያለፈ እምነትም ሆነ ቁርጠኝነት እንደሌለው በመግለጽ፣ ምርጫ ቦርድን በቁጥጥር ስር በማዋል ጠንካራ ፓርቲዎችን ከመጪው ምርጫ ለማግለል እየሰራ መሆኑን የአንድነትና መኢአድን ጉዳይ በመግለፅ አብራርተዋል።

ከሰሞኑ ኢቢሲ ያቀረበው የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የመኖር ትርጉም ዋጋ የሚያሳጣው ‹‹መንግስትንና የመንግስት አስፈጻሚዎችን ከተቻችሁ፣ ካላከበራችሁ ወይም ጸጥ ለጥ ብላችሁ የምርጫ አጃቢ ካልሆናችሁ እስከ 15 ዓመት ትታሰራላችሁ›› የሚል አንድምታ ያለው በ ‹‹ባለሙያዎች ትንታኔ ›› ሥም የተላከው የማስፈራሪያ መልዕክትና የሌሉ የፈጠራ ክሶችን ለመፈብረክ በአባል ፓርቲዎቻችን ላይ ‹‹የሞተ ጉዳይን ከመቃብር በመቀስቀስ›› እና በአዲስ መልክ የተጀመረው የሚዲያ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በግልጽ ያስተላለፈው ገዢው ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ስርአት እንዳይኖር መፈለጉን ነው ሲል አክሏል።

የእኛ፣ የአገራችንና ዜጓቿ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በሁለት አማራጮች ላይ የተንጠለጠለ ነው የሚለው ትብብሩ አንድም ያለውን አምባገነናዊ ሥርዓት ተቀብለን፣የአገራችን ሉዓላዊነት በጥያቄ ውስጥ ባለበት፣ የጭቆና ቀንበር ተሸክመን በከፋ ውርደት ሥር ሰጥ ለጥ ብሎ መገዛት፤ አሊያም አምባገነንነትና ጭቆናን “በቃ” በማለት በሕዝባዊ የተቀናጀ ሰላማዊ ትግል ለአገራችን ሉዓላዊነትና የዜግነት ክብራችንን ለማስመለስ በህገ መንግስታዊ መብታችን ተጠቅመን ትግላችንን እስከማይቀረው ለውጥ/ ድል ደጃፍ ድረስ በቆራጥነት መቀጠል፣ ናቸው ብሏል፡፡

ሁሉን አቀፍ የነፃነትና ክብርን የማስመለስ ሰላማዊ ትግል ለ9ኙ ፓርቲዎች ብቸኛ አማራጭ መሆኑም ትብብሩ አስምሮበታል፡፡

ፓርቲዎቹ በመጨረሻም በሚደረገው አገራዊ፣ ሰላማዊና ሕዝባዊ ትግል በማይቀረው የሥርዓት ለውጥ ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በአንድነትና በቆራጥነት ህዝቡ እንዲነሳና በየካቲት 22 የተቃውሞ ሰልፍ ላይ እንዲገኝ በመግለጫቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የዞን 9 ብሎገሮችና 3ቱ ጋዜጠኞች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

∙ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል

z9

በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው 6ቱ የዞን 9 ብሎገሮችና 3ቱ ጋዜጠኞች ዛሬ የካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ለ20ኛ ጊዜ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ሲሆን፣ በዚህ መሰረትም ተከሳሾች ከችሎት እንዲነሱ አቤቱታ ያቀረቡባቸው ሰብሳቢ ዳኛ ሳይቀየሩ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርገዋል፡፡ በመሆኑም ከሁለተኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ ጀምሮ እያንዳንዳቸው ‹‹በክሱ ላይ የተጠቀሰውን ወንጀል ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም?›› የሚል ጥያቄ እየቀረበላቸው ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

በዚህ መሰረት ሁሉም ተከሳሾች የቀረበባቸውን የሽብር ክስ እንዳልፈጸሙ ለችሎቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉን ጨምሮ ተከሳሾቹ ክሱን በተደጋጋሚ ቢያነቡትም ግልጽ ሊሆንላቸው እንዳልቻለ ቢገልጹም የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠት እንዳለባቸው ተገልጾ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ የተጠቀሰውን ክስ እንዳልፈጸመ በመግለጽ “ህግ የተከበረበት ሀገር ቢሆን ኖሮ በእኔ ቦታ ከሳሾቼ ነበሩ መቆም ያለባቸው” ብሏል፡፡ ሌሎችም እንዲሁ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን አስረድተዋል፡፡ 10ኛ ተከሳሽ ተስፋለም ወልደየስ በበኩሉ፣ “እኔ ጋዜጠኛ ነኝ፤ ጋዜጠኝነት ወንጀልም ሽብርም አይደለም፡፡ ጥፋተኛ አይደለሁም” ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ አቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያሰማ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ከመጋቢት 21-23  ቀን 2007 ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት ቀጠሮ መስጠቱን የነገረ-ኢትዮጵ ዘገባ አመልክቷል፡፡