አባቶችና ምእመናን ‹‹ሸኚው ሸኚ ሲያጣ›› እስኪሉ ድረስ በመጣደፉ በእጅጉ ያዘኑበት የ106 ዓመት አረጋዊው የአቡነ አረጋዊ ሥርዐተ ቀብር ተፈጸመ
ዜና ሕይወቱ ወዕረፍቱ ለብፁዕ አቡነ አረጋዊ ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ አረጋዊ በ1901 ዓ.ም. በፀለምት (ሰሜን ጎንደር) ተወልደው ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ ትምህርት ቤት ገብተው ንባብና ዳዊት እንዲኹም ፀዋትወ ዜማ አጠናቅቀው ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ማዕርገ ዲቁናና ማዕርገ ቅስና ተቀብለዋል፡፡
በዋልድባ አብረንታንት ገዳም ገብተው ለዘጠኝ ዓመታት ያኽል (ከ1933 – 1942 ዓ.ም.) ሥርዓተ ገዳሙን ከአጠኑና በግብዝና ከአገለገሉ በኋላ በዚኹ ገዳም መዓርገ ምንኵስናን ተቀብለዋል፡፡ ትምህርታቸውን በመቀጠል በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በሚገኘው በደብረ ዓባይ ገዳም የደብረ ዓባይ መዝገበ ቅዳሴ ዜማ ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡
በ1943 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ፈቃድና ትእዛዝ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትን እንዲያገለግሉ ተልከው ለአራት ዓመታት ያኽል አገልግለዋል፡፡ አኹንም በቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ ወደ ግብጽ ሔደው ለ16 ዓመታት ያኽል ነገረ መለኰትን በዓረብኛ ቋንቋ አጥንተው ተመርቀዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በሓላፊነት ለማገልገል ተልከው ለስድስት ዓመታት ያኽል በአስተዳዳሪነት ሠርተዋል፡፡ በዚኹ ሓላፊነት ሳሉም በ1968 ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ኹነው በተሾሙ ጊዜ በሱዳን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው በመምጣት ለበዓሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
በ1972 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት በመኾን አገልግለዋል፡፡
በጥቅምት ወር 1983 ዓ.ም. በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ኾነው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አንብሮተ እድ ተሾመዋል፡፡
ከመጋቢት 1985 ዓ.ም. ጀምሮ የኢሉባቦርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ለአንድ ዓመት ያኽል ሠርተዋል፡፡
ከየካቲት 1986 ዓ.ም. ጀምሮ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳምና ት/ቤት የበላይ ሓላፊ ኾነው አገልግለዋል፡፡
ከሐምሌ 1968 ዓ.ም. ጀምሮ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው አገልግለዋል፡፡
ከግንቦት 1992 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ሓላፊ ኾነው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡
በመጨረሻም በዚኹ ሥራ ላይ ሳሉ ባደረባቸው ድንገተኛ ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በተወለዱ በ106 ዓመታቸው ከዚኽ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡
የቀብራቸው ሥነ ሥርዓትም በዚኹ ዕለት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ባሉበትና የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት ሥርዓተ ጸሎተ ፍትሐቱ ከተፈጸመ በኋላ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
ምንጭ፡- ሐራ ተዋህዶ
ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በህንድ ይገኛሉ – የተባበሩት መንገስታት
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ህንድ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ 2 መቶ ሺህ ለሚደርሱ ስደተኞች መጠጊያ መሆኗን አስታውቋል፡፡
በህንድ እየታየ ያለው የስደተኞች መጨመር በፈረንጆቹ 2014 በዓለማችን አለመረጋጋት ከበረከተባቸው መካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ የሚጎርፉ ስደተኞች ቁጥር መጨመር እንደምክንያት ተጠቅሷል፡፡
በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት 5.5 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡
ታዲያ በህንድ በተለያየ ምክንያቶች በመግባት በስደት ላይ ከሚገኙ ህዝቦች መካከል ኢትዮጵያዊያንም እንደሚገኙበት የተጠቀሰ ሲሆን በህንድ የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮያዊያን ቁጥር 580 ሺህ ይደርሳል ተብሏል፡፡
የሶርያ ስደተኞችም በህንድ ቁጥራቸው እጅጉን የበዛ ነው ተብሏል፡፡
የሶማሊያ ፣ የደቡብ ሱዳን ፣ የኬንያ ፣ የኮንጎ፣ ማይናማር እና ኢራቅም በህንድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ያስመዘገቡ ሀገራት ናቸው ሲል ድሬ ቲዩብ ዘግቧል፡፡
በየጊዜው ኢትዮጵያውያን ባህርና የብስ እንዲሁም አየር አቋርጠው ሀገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስደተኞች ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ እየጨመረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት ግን ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ከሚያደርጉት ስደት በተጨማሪ እስካሁን ባልተለመደ ሁኔታ ህንድን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የሩቅ ምስራቅ እስያ ሀገሮችም እየተሰደዱ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን መረጃዎች ያስረዳል፡፡
የድሆች አባት ዶ/ር በርናርድ ተለየን!
ነብዩ ሲራክ
* የኢትዮጵያ አፈር የጠራው ጠቢብ
*” ክብር ሞቱ ለሰማዕት ”
ዛሬ የምናዘክረው ሰው የኢትዮጵያ አፈር ፍቅር ጠርቶት ለጉስቁል ተገፊው ደሃ የሀገሬ ሰው ህይዎት ትንሳኤ ተግቶ ለውጥ ስላመጣ ጠቢብ ነው። ዝካሬ ታሪኩ ቢያስተምረን ፣ አርአያ ሰብዕናው ግብአት፣ ተሞክሮ ቢሆነን ፣ ህይዎት ንብረቱን በእኛው ቀዬ ስላፈሱሰ ትጉት ሀኪም ነው ! ነፍሳቸውን ይማር ብለን ለሰሩት ስራ ክብር በመስጠት እናዘክራቸዋለን! ዶክተር በርናርድ አንደርሰን ይባላሉ ! በርናርድ ዛሬ አይሰሙም ፣ አያዩንም …
የዶር በርናርድን እረፍት ያረዳችኝ መነኩሴዋ እናቴ ሀዘኑ ጎድቷት ” ልጀዋ ዋርካችን ተገረሰሰ እኮ ፣ የድሆች አባትና ጠዋሪ መድሃኒታችን አጣንኮ … ” ነበር ያለችኝ … ያልጠበቅኩት ነበርና ድንጋጤው መላ አካሌን ወረረው ። የእንባ ሳግ እየተናነቃት ሃዘኗን ያጋራችን እናቴን ከማጽናናት ባለፈ ምንም ማለት አልተቻለኝም! እናም ስለ ጠቢቡን የድሆች አባት ዶር በርናርድ አንደርሰን ላዘክር በተጎዳ ስሜት ብዕሬን ሳነሳ ጠቢቡ በሰጡት የኑዛዜ ቃል መሰረት ቀብራቸው በሚወዷት ሀገረ ኢትዮጵያ ምድር ይሆን ዘንድ በተናዘዙት መሰረት ሊፈጸም ተቃርቧል ። ውድ ባለቤታቸው የአርበኛው ደራሲ ገሪማ ታፈረ ልጅ ከሲስተር እማዋይሽ ገሪማም ከምድረ አሜሪካ የዶር በርናርድን ቃል ለመፈጸም ዛሬ እኩለ ቀን አ.አ ይገባሉ ! ጥቂት ስለድሆች አባት በርናርድ አንደርሰን ላጫውታችሁ …
ዶ/ር በርናርድን ሳውቃቸው
ከአራት አመት በፊት ጠቢቡ ወንድም አግኝቻቸዋለሁ ። ስለሚሰሩት በጎ አድታጎት በቅርብ የሚያውቋቸው ስለደግነት ቸርነታቸው አውርተው የማይጠግቡ ወገኖችን አግኝቸ ብዙ ተነግሮኛል። ከዚህም ተነስቸ ጠቡቡን ወንድም በአንድ የራዲዮ ዝግጅት ከአንጋፋው የረጅም ጊዜ የጀርመን ራዲዮ ጋዜጠኛ ከተክሌ የኋላ ጋር በመሆን በአንድ ዝግጅት ለማቅረብ ጠይቄያቸው ነበር ። ዶር በርናርድ ግን ” ምኑን ሰርቸ ታሪኬ ይነገራል ! ” በማለት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ፋና ወጊና አርአያ ተግባራቸውን ለማስተዋወቅ አልተሳካልኝም ! ያም ሆኖ ጠቢቡ በርናርድ እና ባለቤታቸው ሲስተር እማዋይሽ ገሪማን በኢትዮጵያ ባህል በተሽቆጠቆጠው ቪላቸውን ሲያስጎበኙኝ እዚህ ስላደረሳቸው መንገድ አውግተናል ። “አጴ ቴዊድሮስ በተወለዱበት እና ባቀኑት ሃገር የአህያ ግንባር የምታክል ማስታወሻና መዘከሪያ ቦታ እንዴት አይኖራቸውም? ” በሚል ለቴዎድሮስ መታሰቢያ ሙዝየም ለማስፈቀድ ሲከላተሙ ያገኘኋቸው ከእውቋ ሀገር ወዳድ ከወ/ሮ እማዋይሽ ገሪማ ጋር በመሆን የምድረ አሜሪካ የተደላደለ ኑሮ ስላፈናቀላቸው የእናት ኢትዮጵያ ፍቅር ፣ በታሪካዊዋ የጎንደር ከተማ ስላሰሩት የአዛውኖቶች መጠለያ ፣ ለህሙማን መርጃ ባቋቋመው የህክምና እርዳታ መስጫ ቦታና ያኔ ጅምር ስለነበረው የሆስፒታል ግንባታ መሰረት በሚጣልበት ማሳ ላይ ቆሜ ህልማቸውን አውገተውኛል ፣ ሃሳባቸውን ተጋርቻለሁ!
ለመሆኑ ዶ/ር በርናርድ አንደርሰን ማናቸው?
በሃገረ ጃማይካ ካትሪን ደብር ተብላ በምትታዎቅ አንዲት መንደር እ.ጎ.አ መስከረም 21 ቀን 1944 ዓም ህጻን በርናንድ አንደርሰን ከአርሶ አደር ወላጆቹ ተወለደ። የበርናንድ ህይዎት በጃማይካዋ የካትሪን ትንሽ የገጠር መንደር መጀመሩ እንጅ ከዘር ማንዘሩ ርቆ በሌላ የአለም ጫፍ ካለችው ኢትዮጵያ ጋር በፍቅር ተቆላልፎ ህይወቱን ያሳልፋል ብሎ የሚገምት አልነበረም ። ገና ከልጅነት ህይዎቱ ጀምሮ ብሩህ አዕምሮ የታደለው በርናንድ በካሪቪያን ውስጥ አንጋፋ በሆነው የዎልማር የወንዶች ት/ቤት ተግቶ በመመማር ወደ ተሻለ ደረጃ መሸጋገር ጀመረ ፣ ከዚያም ጉዞውን ቀጠለ … የተሻለ እውቀት ጥም እያንገበገበው ወደ አደገችው ምድረ አሜሪካ አቀና ፣ በትምህርቱ በመግፋት እ.ጎ. አ 1960 ዎቹ መጀመሪያ በዋንሽን ግተን ዲሲ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በህክምና ሳይንስ የመጀመሪያውን የባችለር ዲግሪ ሲቀዳጅ በከፍተኛ ማዕረግ ነበር ። ለጎልማሳው በርናንድ በከፍተኛ የህክምና ተቋማት የላቀ ውጤት ማምጣት ተራ ትምክህት ሆኖ ሳይገታው የተሻለና የላቀ ፣ ከፍ ያለ ትምህርት የመቅሰም ህልምን ሰንቆ የማታ ትምህትቱን በመከታተሉን ገፋበት ። ይህንንም ህልም በአጭር ጊዜ ታጥቆ ለስኬት አደረሰው ። እ.ጎ. አ በ1970 ዎቹ በርናንድ በከፍተኛ ማዕረግ የዶክትሬት ማዕረግ ተመረቀ፡፡
የዚያ ደርባባ ጎልማሳ ዶር ማንነት የተገነባው ከመደበ ኛው እውቀት ባለፈ አብሮት ከተቆራኘ ሰብዕና እንደነበር የሚያውቁት ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ ። ዶር በርናርድ አንደርሰን በሙያው ያጡ የነጡ፣ ጉስቁል ፣ምንዱባንን ለመርዳትና ለመደገፍ ቆርጦ ተነሳ ፣ ከምንም በላይ ደግሞ እንደ ቃል ኪዳን አድርጎ የያዘውን ተተኪ ፍለጋና ተተኪን ማፍራት ነበርና ድሎት ሳያታልለው ያደገ የተመነደገችውን ምድረ አሜሪካ ለቆ ወደሚያውቀው የድሆች ምድር አቀና ! ወደ ጃማይካ ኪንግስተን …
ጃማይካ ኪንግስተን …
ህልሙን ለማሳካት ወደ ትውልድ ሃገሩ ጃማይካ ተመልሶ በወቅቱ ታዋቂ ከነበረው የኪንግስተን የህዝብ ሆስፒታል ስራውን ጀመረ ። የቀዶ ጥገና ጥበብ ባለሙያው ጎልማሳ ሃኪም ቅድሚያ የሰጠው በድህነት የሚማቅቁ ወገኖቹን መታደግ ነበር ፣ በህክምና ድጋፉ ፣ በተጓዳኝ ጥናትና ምርምሩ አንቱ በሚያሰኘውን ተመክሮ ራሱን እያጎለበተ ጉዞ የጀመረው ሃኪም በህክምና ድጋፍ ከመስጠት ርቆ ሔዶ በመምህርነት ሙያው ተተኪ ትውልድን የማነጽ ህልሙን አሳካ ። በዚህም ጉዞው ዶር በርናርድ አንደርሰን ለሃገሩና ለወገኑ ይህ ነው የማይባል አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ቻለ !
ከጃማይካ መልስ በዋሽንግተን …
የጃማይካ ኪንግስተን ተልዕኮውን በሚገባ ከውኖ አቅፋ ደግፋ እውቀት ወደ መገበችው ሀገረ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ተመለሰ ። ዶር በርናርድ ለዚህ ላበቃው ዩኒቨርሲቲ ከእለትጉርሱ ያጠራቀመውን ከ100 ሽህ የአሜሪካ ዶላር የለገሰ ፣ ለሚሰረሰው በጎ ስረሰ ከመደሰተረ ውጭ ፣ መወደስ የማይሻ ሰብአዊም ነበር ።
ዶ/ር በርናርድ ከጃማይካ መልስ እንደ አቻ የሙያው ባልደረቦቹ ሃብት ንብረት የሚያካብትባቸው ሆስፒታሎ ች በከፍተ ኛ ገንዘብ ሊቀጥሩት ሲሻሙ አሻፈረኝ አለ። ጥቅም ፍለጋ መማሰኑን ” ወዲያልኝ ” ብሎ ፣ የጤና ከለላና ሽፋን የሌላቸው ፣ በድንገተኛ አደጋ ተጎድተው ህይዎታቸው አጣብቂኝ የገቡትን የስልጡኑ ሀገር ተገፊ ምንዱባን መታደግ ወደ ሚችልበት በዲሲ ጄኔራል ሆስፒታል በአነስተኛ ደመወዝ ተቀጥሮ መስራት ጀመረ ። በሙያው ተግቶ ፣ በሰብዕናው ጸንቶ ፣ ባሳየው ስኬትም በአጭር ጊዜ አንቱታን በማግኘቱ የሆስፒታሉ ሊቀመንበርና የቀዶ ጥገናው ክፍል ዋና ዳይሬክተር ለመሆን በቃ ! በአስተዳደር እና በሙያው ክህሎት የዲሲ ጀኔራል ሆስፒታል ከፍ ወዳለ ደረጃ ያደገው በዶር በርናርድ አንድሰን አመራር እንደነበር ዝክረ ታሪኩ ያስረዳል። ዶር በርናንድ ሆስፒታሉን ከማስተዳደር ጎን ለጎን የግል ክሊኒክ በድሆቹ መኖሪያ አቅራቢያ በዲሲ ሮድ አይላንድ መንገድ በመክፈት ፣ ለቻሉት በአነስተኛ ክፍያ ፣ ያልቻሉትን በነጻ በማከም ግልጋሎት ይሰጥም ነበር ።
የዶር በርናርድ አፍሪካና ኢትዮጵያ ትስስር …
በቀጣይ ዝካሬ ዶር በርናርድ ስነሳ እንደ አባት አቅርቤ ፣ እንደ ታላቅ ትጉህ ጠቢብ አንቱ እያልኩ መተረኬ ይገባኛል ፣ መልዕክቴ ከገባችሁ ለእኔ ያ በቂ ነው! ብቻ ያገሬ ሰው ዶር በርናርድን “የድሆች አባት ” ስላለበት አንድምታ ዘልቀን እናወጋለን …
ታህሳስ 24, 2007 ዓም ይህችን አለም የተለዩን ያልተጨበጨበላቸው ፣ ያልተነገረላቸው የኢትዮጵያ ወዳጅ ጃማይካዊ አሜሪካዊ ዶር በርናርድ የምናዘክረው በታላቅ ክብር ነው ! “ዶር በርናርድ ጉስቁል ምንዱባን ን ስትደግፍ ኖረሃልና ሞትህ የክብር ሞት ነው ! ” ክብር ሞቱ ለሰማዕት ” በሚል ትናንት እኩለ ሌሊት በዋሽንግ ተን ዲሲ በተደረገ ሰፊ የጸሎትና የዝክር ስነ ስርአት ቤተ ሰብ ፣ ወዳጅ ዘመድና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት የክብር ስንብት አድርገው በርናንድ በድናቸው እንዲያ ርፍ ወደ ፈቀዱባት ቅድስት ሀገረ ኢትዮጵያ በክብር ተሸኝተዋል ! በዚሁ ፕሮግራም ከተሰራጨው ዝክረ ህይዎት ያገኘሁትን መረጃ በቀጣይ እንደሚሆን አድርጌ የምናየው ይሆናል !
ለመላ ቤተሰብ ለወዳጆቻቸውና ለአድናቂዎቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ ! ለሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪው የድሆችን አባት ፈጣሪ በቀኙ ያሰቀምጣቸው ዘንድ የዘወትር ጸሎቴ ነው ! ነፍስ ይማር !
ታህሳስ 30 ቀን 2007 ዓ.ም
መድረክ ከኢህአዴግ ጋር በአስቸኳይ መወያየት እፈልጋለሁ አለ
በምርጫው ሂደት ላይ ቅሬታዎች አሉኝ ብሏል
የግንቦቱ ምርጫ ሂደት ላይ ቅሬታዎች እንዳሉት የገለፀው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፤ በጉዳዩ ላይ ከገዥው ፓርቲ ጋር በአስቸኳይ መወያየት እንደሚፈልግ አስታወቀ፡፡
መድረኩ ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በምርጫ ታዛቢዎችና አስፈፃሚዎች አመራረጥና በምርጫው ለሚሳተፉ ፓርቲዎች ከመንግስት በሚሰጠው የድጐማ ገንዘብ ክፍፍል ላይ ቅሬታ እንዳለው ጠቁሟል፡፡
ምርጫውን ለማስፈፀምና ለመታዘብ ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ገለልተኛ የሆኑ ሠዎች መመረጥ ያለባቸው ቢሆንም በቅርቡ የተመረጡት አስፈፃሚዎች አብዛኞቹ የገዥው ፓርቲ አባላት መሆናቸው እየታወቀ “የማንም ፓርቲ አባላት አይደለንም” እያሉ ፈርመው ወደ አስፈፃሚነቱ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል ሲል ፓርቲው ቅሬታውን ገልጿል፡፡
መንግስት ለፓርቲዎች የሚሰጠውን የገንዘብ ድጐማ በተመለከተም ገንዘቡ ለሚመለከታቸው ፓርቲዎች ብቻ በአግባቡ እንዲከፋፈል ጠይቋል፡፡ “ከመንግሰት ካዝና ወጥቶ ታማኝ ለሚባሉ ፓርቲዎች እየተከፋፈለ ያለው ገንዘብ በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን” ብሏል መድረኩ፡፡ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ያልሆነው መድረኩ፤ ጉዳዩ ከፖለቲካ ሙስና ተለይቶ አይታይም ብሏል፡፡
ቦርዱ፤ ፓርቲዎች በፓርላማና በክልል ምክር ቤት ባላቸው መቀመጫ እንዲሁም በሚያቀርባቸው እጩዎች ብዛትና የሴቶች ተሳሣትፎን መሠረት አድርጐ ገንዘቡን ለማከፋፈል መወሰኑን የተቃወመው ፓርቲው፤ በተለይ የምክር ቤት መቀመጫ የሚለው መስፈርት ኢህአዴግን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው ብሏል፡፡
“በምክር ቤት መቀመጫ ብቻ ኢህአዴግ 55 በመቶውን ድርሻ ያገኛል፤ ቀሪው 45 በመቶ 59 ፓርቲዎች የሚከፋፈሉት ይሆናል” ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ኢህአዴግ በድልድሉ የደረሰውን 10ሚ.ብር የጋራ ምክር ቤቱ አባል ለሆኑ ፓርቲዎች ማከፋፈሉ ይታወሳል፡፡
የመድረክን ተቃውሞና ቅሬታ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደምሰው በንቲ በበኩላቸው፤ የህዝብ ታዛቢዎቹ ምርጫ የተከናወነው ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ራሳቸው የፓርቲ ተወካዮች በተገኙበት፣ ተአማኒነት ባለው መልኩ በመሆኑ የቀረበው ቅሬታ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ውድቅ አድርገዋል፡፡ ከገንዘብ ክፍፍሉ ጋር ተያይዞ ከመድረክ በመግለጫ መልክ ቅሬታ መቅረቡ አግባብ አይደለም ያሉት ኃላፊው፤ ቦርዱ ክፍፍሉን በተመለከተ ፓርቲዎች ሃሳብ እንዲያቀርቡ በማሰብ እንጂ ሳያማክር በራሱ የማከፋፈል መብት አለው ብለዋል፡፡
(ምንጭ: አዲስ አድማስ ጋዜጣ)
ጎበዝ ጠንከር ነው!
ምርጫ ቦርድ ማንም ይዘዘው ማንም ወይም በግል ተነሳሽነት እያደረገ ያለው ነገር የኢትዮጵያን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ከምን ጊዜውም በለይ ወደኋላ ለመመለስ እንደሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊረዳው ይገባል፡፡ ምርጫ ቦርድ ምርጫ እንዲያሰተዳድር በተሰጠው ኃላፊነት የፓርቲዎች አስተዳደሪ ለመሆን እየቃጣው ያለ ተቋም ነው፡፡ ስናከብረው ለመከበር ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ለዚህ ተቋም መጠናክር የበኩላችንን መወጣት አለብን ብለን የተነሳን ፓርቲዎችን ጭምር እየገፉ አለቆቹን ለማስደሰት ደም ተግቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህን የሚያደርጉትን ሰዎች ደግሞ በህዝብ ፊት ለብይን እንዲቀርቡ በግልፅ ማጋለጥ ይኖርብናል፡፡
ትላንትና ዶ/ር አዲሱ በሚዲያ ቀርቦ የተናገረው በምንም መልኩ አንድነትን አይመጥንም፡፡ የተቀሩት የቦርድ አባላትም ይመጥነናል ካሉ ትዝብት ላይ ይወድቃሉ፡፡ የምርጫ ቦርድ አባላት ሳያገባቸው እንፈትፍት ሲሉ መፈተፍቱን ለእኛ ተዉልን ነው ያልናቸው፡፡ ዶ/ር አዲሱ በሚዲያ የቦርድ ውሳኔ ሊሆን ይችላል ብሎ ካቀረበ በኋላ ዛሬ ታህሳስ 28 ቀን 2007 ቦርድ ተሰብስቦ ውሳኔ ሰጥቶዋል፡፡ ይህን ውሳኔ እንገራችሁ ብለው በስልክ ከጠሩን በኋላ የአንድነት ፓርቲ የወረዳ አባላት የሆኑትንም በተመሳሳይ መልክ ጠርተው ነበር፡፡ ለነገሩ ይህ አካሄድ አንድነትን ስለማይመጥን በፅሁፍ እንዲገልፁልን ነግረናቸው ተመልሰናል፡፡ ለማንኛውም ዶ/ር አዲሱ የሰጠው መግለጫ ይህ መግለጫ እንዲሰጥ የወሰኑትን ጨምሮ ለተቀሩት የቦርድ አባላት ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ ነው፡፡ ቦርዱ ተሰብሰቦ ምንም ዓይነት ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ውሳኔውን ሚዛን የሚያሳጣ መግለጫ ለመስጠት ምን እንዳጣደፋቸው መገመት ቀላል ነው፡፡ በልባቸው የሚደግፉትን ፓርቲ ለማንገስ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው፡፡
ልክ የዛሬ አምስት ዓመት አንድነት ላይ ተመሳሳይ ግብ ግብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የዚህ ተልዕኮ ፈፃሚዎች ዛሬ ላይ ሆነው ምን እንደተጠቀሙ ሲያሰላስሉ ምን እንደሚሰማቸው ባላውቅም ዛሬ በዚህ ተግባር ላይ የተሰለፉት አባላት ደግሞ ምን እንደሚያደርጉ መጠበቅ ነው፡፡ ለመማር ያልተፈጠረን ሁሉ ምን ማድረግ ይቻላል? ማንም ተላላኪና ላኪ ሆኖ ቢያገለግልም ዛሬ የተሰማኝ ነገር አንድነት በምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን እንደዚህ ዓይነት ተቋማት በምን ያህል ደረጃ ለመዋረድ ዝግጁ እንደሆኑ ለመረዳት የሚያስችል ነው፡፡ አሁንም ትግሉ መራራ፣ የሚያስከፍለው መስዋህትነትም ውድ ሊሆን እንኳን ቢችል የአንድነት አባላት በድል እንደሚወጡት ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ እሩቅ እንደሆነ አውቀን ለጀመርነው ትግል አቋራጭ እንደማንፈልግ መግለፅ ይኖርብናል፡፡
ውድ የአንድነት አባላት ለቀጣይ አንድነት ከምርጫ ቦርድ አሻጥር ለማላቀቅ ለምናደርገው ትግል ቀበቶ ጠበቅ ነው፡፡ ከሰማይ በታች አንድነት ለመፍታት የማይችለው ፈታኝ ነገር ምርጫ ቦርድም ሆነ በውሰጥችን ያሉት ዙንቢዎች ሊያቀርቡ አይችሉም፡፡ ጎበዝ ጠንከር ነው፡፡





