ሰማያዊ ፓርቲ መንግስት የከፈተበትን የጥላቻ ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳሰበ
መንግስት ሊቢያ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ላይ አሰቃቂ እርምጃ የወሰደውን አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም ራሱ በጠራው ሰልፍ ላይ ከህዝብ የገጠመውን ተቃውሞ ተከትሎ ሰማያዊ ላይ የጥላቻ ዘመቻ እንደከፈተበትና ይህንን የጥላቻ ዘመቻውን እንዲያቆም ሰማያዊ ፓርቲ በሰጠው መግለጫ አሳስቧል፡፡
መንግስት የጠራውን ሰልፍ ከማንም ተቃዋሚ ፓርቲ ቀድሞ የደገፈው ሰማያዊ እንደሆነ የገለጸው መግለጫው “የዜጎችን ስቃይ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል የፈለገው ህወሓት/ኢህአዴግ ሰማያዊ ፓርቲ በወገኖቻችን ላይ ለሚደርሰው በደል መፍትሄ እንዲሰጥ መወትወቱ፣ የፖለቲካ ልዩነታችንን ወደ ጎን አድርገን በሰልፉ ላይ መገኘታችን እንዳላስደሰተው ከሰልፉ ቀን ጀምሮ በፓርቲያችን ላይ የተከፈተው ዘመቻ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡” ብሏል፡፡
ከሰልፉ ማብቃት ጀምሮም ጉዳዩን ገና ፖሊስ ሳይመረምረው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን ሰማያዊ ፓርቲ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት እየጣረ ነው በሚል መወንጀላቸውን፣ የመንግስት ሚዲያዎች ሰማያዊ ፓርቲ ሁከትና ብጥብጥ ሊያስነሳ ነው ብለው ሚዛናዊ ያልሆነ መረጃ ማሰራጨታቸውንና አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም ተብለው በተጠሩ ሰልፎችም ሁሉ መንግስት ሰማያዊ ፓርቲ ለመቃወም እየተጠቀመባቸው መሆኑን መግለጫው አትቷል፡፡
በተጨማሪም በሰልፉ ዕለት የሰማያዊ አባላት ገና ሰልፉ ሳይጀመርና መስቀል አደባባይ ሳይደርሱ እንዲሁም ሰልፉ ካበቃ በኋላ እየታደኑ ሲታሰሩ መስቀል አደባባይ ላይ የተያዙት የኢህአዴግ አባላት ከቀበሌ ደብዳቤ እያመጡ መፈታታቸው መንግስት ሰማያዊን በሀሰት ለመወንጀል መነሳቱን ያሳያል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል 6 ያህል የሰማያዊ አባላት በታሰሩበት ሁኔታ መንግስት 7 አመራሮችና 20 ያህል አባላት ታስረዋል ማለቱ ትክክል አለመሆኑንና ከመጀመሪያውም 6 አባላቱ የታሰሩበት መንገድና አሁንም በሰማያዊ ላይ የሚቀርበው ክስ መሰረተ ቢስ ነው ብሎታል፡፡
“ይህ በህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት አማካኝነት እየቀረበ ያለው ክስ እና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ህወሓት/ኢህአዴግ ለዜጎች ህይወት የማይጨነቅ እና በዜጎች ሞት የራሱን የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ እና ጠንካራ ተቃዋሚ የሆነውን ሰማያዊ ፓርቲን ለማጥቃት እየተጠቀመበት መሆኑን በተጨባጭ የሚያሳይ ነው፡፡” ሲልም የመንግስትን ተግባር ተቃውሟል፡፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተሰጠበትን ጉዳይ ተጠርጣሪ ከማለት ይልቅ ወንጀለኞች ናቸው በማለት በህገወጥ ስራ እንደተሰማራ ያሳያል ሲልም ወቅሷል፡፡
“መንግስት እና የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ከዚህ አኩይ ተግባራቸው የማይታቀቡ ከሆነ፣ የሰማያዊን ስም በሀሰት በማጠልሸት ስራ ላይ የተሰማሩ የመንግስት ተቋማትን እና ግለሰቦችን በህግ ፊት ለማቆም ይገደዳል” ያለው መግለጫው ሌሎች ተከታታይነት ያላቸውን እርምጃዎችም እንደሚወስድና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሰማያዊ ፓርቲ ለሚያደርጋቸው ህዝባዊ ጥሪዎች በንቃት ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በሀዲያ ዞን በምርጫ 2007 ዓ.ም. ቅስቀሳ ምክንያት የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ
በደቡብ ክልል በሀድያ ዞን ሶሮ ወረዳ ጊምቢቹ ከተማ በህዝብና በራሱ ላይ በሚፈፀመው አስተዳደራዊ በደል የተማረረውና በተደጋጋሚ በሚፈፀሙት አስተዳደራዊ በደሎች ላይ ቅሬታ አቅርቦ መፍትሄ ያላገኘው የአካባቢው የ2007 ዓ.ም. ምርጫ የመድረክ ዕጩ የነበረው መምህር ጌታቸው አብርሃም ሚያዝያ 17 ቀን 2007ዓ.ም በጊምቢቹ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ግቢ ውስጥ ራሱን ያቃጠለ ሲሆን በሆሳዕና ሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት ቢቆይም ህይወቱ እንዳለፈች ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ቡሬ ለንጌ ትምህርትር ቤት የሲቪክስ መምህር የነበረው መምህር ጌታቸው በአካባቢው ባለው የከፋፍለህ ግዛና የጎሳ ፖለቲካ ተጠቂ ከመሆኑም ባሻገር በህዝብና በእሱ ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም መፍትሄ እንዲሰጥ ለባለስልጣናት ሲያሳውቅ መቆየቱን፣ ሆኖም ህዝቡ እና በራሱ ላይ የሚፈፀምበት በደል በመባባሱና መፍትሄ ማግኘት ባለመቻሉ አስተዳደሩ ግቢ ውስጥ ራሱን ማቃጠሉ ታውቋል፡፡
መምህር ጌታቸው ራሱና ህዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም በከተማው አስተዳደር ምክር ቤት ግቢ ውስጥ ራሱ ላይ ጋዝ በማርከፍከፍ ራሱን ባቃጠለበት ወቅት ግቢው ውስጥ የነበሩት ሰዎች ደርሰው እሳቱን በማጥፋታቸው ህይወቱን ለማዳን ጥረት አድርገው የነበር ቢሆንም የደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር ህይወቱ አልፏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛው በሀድያ ዞን አምቡላንሶች ለምርጫ ቅስቀሳ እየዋሉ በመሆኑ ህመምተኞች በተለይም ነፍሰ ጡር እናቶች ህክምና ሳያገኙ ለሞት እንደሚዳረጉ ነዋሪዎቹ ገለፁ፡፡ ሚያዝያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም አንዲት ምጥ የተያዙ እናት በአቅራቢያቸው በሚገኝ የጎምበራ የጤና ጣቢያ በሄዱበት ወቅት ‹‹ከአቅማችን በላይ ነው!›› ተብለው ወደ ሆሳዕና ሪፈራል ሆስፒታል ሄደው እንዲታከሙ ሪፈር ቢፃፍላቸውም በትራንስፖርት ችግር ነፍሳቸው አልፋለች፡፡
ለጤና ጣቢያው የተመደበችው አምቡላንስ በጎምበራ ወረዳ ኦሌ ቀበሌ ለገዥው ደኢህዴን/ኢህአዴግ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ በመውጣቷ ቤተሰብ ነፍሰጡሯን ከጎምበራ ክሊኒክ ወደ ሆሳዕና ሪፈራል ሆስፒታል በቃሬዛ ለመውሰድ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ሆሳዕና ሆስፒታል በቶሎ መድረስ ባለመቻላቸው የነፍሰ ጡሯ ህይወት መንገድ ላይ ሊያልፍ ችሏል፡፡
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት ከሆነ አምቡላንሶች ለምርጫ ቅስቀሳ በመዋላቸው ምክንያት በርካታ ህመምተኞች በተለይም እናቶችና ህፃናት በቶሎ ወደ ሆስፒታል መድረስ ባለመቻላቸው ተመሳሳይ ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በምርጫ 2002 ዓ.ም ወቅትም በተመሳሳይ መልኩ በዚሁ በሀዲያ ዞን አምቡላንሶች ለኢህአዴግ ምርጫ ቅስቀሳ ወጥተው ነፍሰ ጡር እናቶች ህይወታቸው ማለፉ አይዘነጋም፡፡
በሜዴትራኒያን ባህር ላይ በደረሰ የጀልባ አደጋ ከ16 በላይ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው አለፈ
ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሜዴትራኒያን ባህር ከሊቢያ ወደ አውሮፓ በስደት ሲጓዙ ከነበሩ 700 ሰዎች መካከል በርካቶች መሞታቸውንና የ28 ሰው ህይወት ብቻ በጣሊያን ባህር ኃይሎች ማትረፍ ቢቻልም፤ የአብዛኛው ተጓዥ ሕይወት ማለፉ ታውቋል፡፡ ህይወታቸው ካለፉት ውስጥ በርካታ ኤርትራውያን እንዳሉበት ቀደም ሲል የተገለፀ ቢሆንም፤ አሁን እየወጡ ባሉ መረጃዎች በተለይም ከሞት በተረፉ ኢትዮጵያውያን እንደተገለፀ ከሆነ ከ16 በላይ ኢትዮጵያውውን መሞተታቸው ታውቋል፡፡ በጉዞ ጀልባዋ ላይ በደረሰ የመስጠም አደጋ ህይወታቸው ካለፉት መካከል 8 ወጣቶች ከአዲስ አበባ መርካቶ ልዩ ስሙ አባኮራን በሚባል አካባቢ፣ 8 ወጣቶች ከባሌ እንዲሁም የድሬዳዋ ልጆች ህይወታቸው ማለፉን ቢቢኤን እና ፍትህ ሬዲዮን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ከሀገር ቤት ቤሰቦቻቸውን ዋቢ በማድረግ ያሰራጩት ዘገባ አመልክቷል፡፡
በተለይ ከአዲስ አበባ መርካቶ አባኮራን አካባቢ በጋራ ከተጓዙ 10 ወጣቶች መካከል 9ኙ በአደጋው ህይወታቸው ማለፉን እና አንዱ ከአደጋው የተረፈው ኢትዮጵያዊ ወጣት ጣሊያን እንደገባ ሀገር ቤት ደውሎ ማርዳቱ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም መሰረት የ8ቱ ቤተሰቦች ሀዘን ሲቀመጡ የአንዱ ወጣት ወላጆች ግን እስካሁን የልጃቸው ህይወት አልፏል መባሉን እንዳላመኑ እና እንዳልተቀበሉም የአካባቢው ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ በሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊቢያ ሜዲትራኒያን ባህር በደረሰው አደጋ ህይወታቸው ካለፈ የአዲስ አበባ አባኮራን ሰፈር ወጣቶች መካከል አብዱ ጅላል ወጉ (ሙራድ)፣የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረው ኑሩ መሐመድ፣አብዱልከሪም ዘይኒ፣ ሰይድ ይመር፣ አሊ መሐመድ፣ ነጃ ሳቢር አወል እና የኢንፎኔት ኮሌጅ ተመራቂ የነበረው ኢድሪስ አደም እና ወጣት ሸበቴ ህይወታቸው በማለፉ ቤተሰቦቻቸው ተረድተው ሀዘን መቀመጣቸው ተጠቁሟል፡፡ በሰጠመችው ጀልባ ከባሌ አካባቢ ህይወታቸው ካለፉት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መካከል አብዱረዛቅ አቡበክር፣ በሪሲና አብዱልወሃብ፣ ሰይፈዲን አሊዪ፣ ሬድዋን ሙሃመድ፣ አሊይ ረሻድ፣ ኢሳ አማን፣ ኑእማን ሁሴን እና ሲራጅ ሙሃመድ እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡ በዚህ አደጋ ከድሬዳዋ አካባቢም ህይወታቸው ያለፈ ወጣቶች እንደሚገኙበትና ቤተሰብም ተረድቶ ሀዘን መቀመጣቸውን የቢቢኤን ዘገባ አመልክቷል፡፡
በዚህ አደጋ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ከ350 ያላነሱ ኤርትራውያንን ጨምሮ በርካታ የሶማሊያ እና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገር ዜጎች ህይወታቸው ማለፉን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ባለፈውበደደቡብ አፍሪካ፣ በየመን እንዲሁም በሊቢያ በረሃ በዓለም አቀፉ አሸባሪው አይ ኤስ አይ ኤል 28 ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ ያለው የሀዘን ድባብ ሳያባራ አሁን ደግሞ በሊቢያ ሜዴትራኒያን ባህር ሰጥመው መሞታቸው ህዝቡን የበለጠ ሀዘን ውስጥ መክተቱ ታውቋል፡፡
ባለፈው ሚያዝያ መጨረሻ 2007 ዓ.ም. በሊቢያ ታስረው የነበሩ 27 ኢትዮጵያውያን በግብፅ መንግሥት ጥረት እንዲለቀቁ ተደርገው ወደ ካይሮ ሲገቡ የግብፁ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ ኤል ሲሲ በአውሮፕላን ማረፊያው ድረስ በመሄድ አቀባበል ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
መንግሥት ራሱ በጠራው ሰልፍ በርካታ ሰዎችን ሲደበድብ፤ ከመቶ በላይ ሰዎች ታስረዋል
ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት በሊቢያ፣በደቡብ አፍሪካና በየመን ኢትዮጵያውያን በግፍ መገደላቸውን በተመለከተ በአዲስ አበባ ድርጊቱን ለማውገዝና ለመቃም ሰልፍ ጠርቶ የነበረ ቢሆንም፤ በሰልፍ የተገኙ በርካታ ሰዎች በፖሊስ ተደብድበው ወደ አካባቢው ሆስፒታሎች የተወሰዱ ሲሆን፤ ከ100 በላይ ሰዎች መታሰራቸውንም አልጀዚራን ጨምሮ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከስፍራው በቀጥታ ዘግበዋል፡፡ በተለይ በአሸባሪው በ አይ ኤስ አይ ኤል (ISIL) ቢያንስ 28 ኢትዮጵያውያን በጭካኔ መገደላቸውና መንግሥትም ለዚህ ያሳየው ቸልተንነት ህዝቡን የበለጠ በማስቆጣቱ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ያለማንም ቀስቃሽ የአዲስ አበባ ነዋሪ ለተቃውሞ ሰልፍ ቢወጣም መንግሥት ፈቃድ አልሰጠሁም በሚል በርካቶች ከደበደበ በኋላ ለሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ራሱ ድርጊቱን በመቃወም ሰልፍ ቢጠራም መጨረሻው በፖሊስ ከፍተኛ ድብደባና እስር ተጠናቋል፡፡ ሰልፉ ከመጀመሩ በፊት የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች ወደሰልፉ ሲሄዱ የታሰሩ ሲሆን፤ ከሰልፉ በኋላ የመንግሥት ባለሰልጣናት መስቀል አደባባይ ንግግር ሲያደርጊ ህዝቡ በልቅሶ ተቃውሞ ካሰማ በኋላ የአዲስ አበባ እና የፌደራል ፖሊስ እዛው ሰልፉ ቦታ ሲደበድብ ታይቷል፡፡ ይሄንንም የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በቀጥታ አሰራጭተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ አሸባሪው ቡድን ISIL በሊቢያ የገደልኩት ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ቢልም፤ በአዲስ አበባው ተቃውሞ የእስልምና እና የክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች በጋራ ድርጊቱን ሲያወግዙ ተስተውሏል፡፡ በዕለቱም በርካታ መፈክሮች የተሰሙ ሲሆን፤
ታርዷል ወገኔ፣ ታርዷል ወገኔ…(በኡኡታና ልቅሶ)
ሽብርን እንቃወማለን፣እናወግዛለን
መንግሥት ኃላፊነቱን አልተወጣም
ሞት ለወያኔ፤ ያረደንም ያሳረደንም ወያኔ ነው
ይለያል ዘንድሮ የዌኔ ኑሮ
ውሸት ሰለቸን፤ የወንድሞቻችን ደም ይመለስ
የሀገር ውስጥ ISIL ወያኔ ነው፤…በቃን
ISIL እስልምናን አይወክልም፤ እኛ የኢትዮጵያውያ ሙስሊሞች ወንድሞቻችን ክርስቲያኖች በአሸባሪ ቡድኑ መገደላቸውን አጥብቀን እናወግዛለን፤ ድርግቱም ሽብር እንጂ እስልምናን አይወክልም (በተለይ በሰልፉ የተገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች)
መንግሠት የሌለው እዚህ ብቻ ነው
የኢትዮጵ አምላክ ይፍረድ (በተለይ የሟቾቹ ቤተሰቦች)
ና ና መንጌ ና ና (የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምን)
የቤት አንበሳ የውጭ እሬሳ (መንግሥትን) የሚሉ መፈክሮች ይገኙበታል፡፡
በመጨረሻም በመንግሥት ላይ የህዝቡ ተቃውሞ ተጠናክሮ ሲቀጥል የመንግሥት ባለስልጣናት ንግግር በቅጡ ሳይሰማ የተቋረጠ ሲሆን፤ ፖሊስም ወዲያውኑ ያገኘውን ሁሉ እያሳደደ ሲደበድብ ለማየት ተችሏል፡፡ በቂርቆስ ሰፈር ልቅሶ ቤት አካባቢ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ መነሻ በስፍራው እጅግ በርካታ ፖሊሶች በስፍራው የነመበሩ ሲሆን፤ በኋላም ከፍተኛ የመሳሪያ ተኩስ ተሰምቷል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ በተተኮሰው ጥይት በሰው ህይወትና አካል ላይ ጉዳት ስለማደረሱ የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም መስቀል አደባባይ በነበረው የፖሊስ ድብደባ ራሳቸውን ስተው የወደቁ ሴቶች፣እናቶችና ወጣቶች የታዩ ሲሆን፤ ብዙ ወጣቶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በአምቡላንስ እና በሰው እግዛ ወደ ህክምና ጣቢያ ሲሄዱና የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ታይቷል፡፡
መንግሥትም በተመሳሳይ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የሽብር ድርጊቱን በመቃወም በመዋቅሩ ሰልፍ ማዘጋጀቱና ለዚህም የኢህአዴግ ሊግና ፎረነም አባላት ከየቀበሌው በነበረው መዋቅር ወደሰልፍ እንዲወጡ፣ ሌላ ወደተቃውሞው ሰልፍ የሚመጣ ካለ በደንብ ከበው እንዲከታተሉት፣ መፈክሮችም በኢህአዴግ ብቻ እንዲዘጋጅ ከዛ ውጭ ያለ መፈክር ይዞ የሚመጣ ማንኛውም አካል ካለ ወደሰልፉ መሐል ከመቀላቀሉ በፊት ጥብቅ ምርመራ መደረግ እንዳለበት ትዕዛዝ መሰጠቱንም ምንጮች ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡
በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ቀደም ሲል የሽብር ድርጊቱን በማውገዝ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ በፌስ ቡክ ግድግዳቸው ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢናገሩም፤ በመጨረሻም አሸባሪው ድርጅት ላይ በመንግሥት እርምጃ ይወሰዳል ተብሎ ሲጠበቅ፤ በአዲስ አበባ ሰልፈኛ ላይ እርምጃ ሲወስድ ታይቷል፡፡ መንግሥት በበኩሉ እርምጃ የተወሰደው ፖሊሶች ላይ ድንጋይ ስለተወረወረ ነው የሚል ምክንያት ሰጥቷል፡፡
በተለይ በሊቢያ የሟቾች ማንነት እየተለየ ሲሆን፤ ስማቸውም ኢያሱ ይኮኖአምላክ፣ ባልቻ በለጠ፣ ብሩክ ካሳ፣ በቀለ ታጠቅ እና ኤልያስ ተጫኔ ከአዲስ አበባ ቂርቆስ ሰፈር፤ መንግሥቱ ጋሼ እና አወቀ ገመቹ ከወለጋ ነቀምት፣ በቀለ አርሰማ ከጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ካራቻ አካባቢ፣ የጅማ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ የነበረው ዳንኤል ሓዱሽ፣ አለም ተስፋይ እና ዳዊት ሀድጉ ከትግራይ መቀሌ አካባቢ፣ ክርስቲያን ወንድሞቼን ለይታችሁ አትገድሉም፤ በእስልምና የሰውን ህይወት ማጥፋት ኃጥትም ወንጀልም ነው፣ እኔ ከእነሱ አልለይም በማለት ሲከራከር የነበረው ኢትዮጵዊው ሙስሊም ጀማል ረህማንም አብሮ መገደሉ ታውቋል፡፡ በአሸባሪው ቡድን ከተገደሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ተስፋይ ኪዳኔን ጨምሮ ሶስት ኤርትራውያንም እንደሚገኙበት የታወቀ ሲሆን፤ በተለይ ተስፋይ ከዚህ በፊት በእስራኤል ጥገኝነት ጠይቆ በመከልከሉ በሊቢያ ወደ አውሮፓ ለመሄድ ሲሞክር በአሸባሪ ቡድኑ እጅ መግባቱ ተጠቁሟል፡፡
በአዲስ አበባ የተቃውሞና የሀዘን ሰልፍ በመንግሥት ተበተነ፤በሊቢያ አሁንም በርካታ ኢትዮጵያውን የአድኑን ጥሪ እያሰሙ ነው
ዛሬ ሚያዚያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ባለፈው እሁድ በበኣለም አቀፉ አሸባሪው አይ ኤስ አይ ኤል በተባለው ቡድን በሊቢያ በጥቂቱ 28 ኢትዮጵያውያን በመገደላቸው በመላው ኢትዮጵያውያን ሀዘኑ የበረታ ቢሆንም፤ በአዲስ አበባ ግን ህዝቡ በራሱ አነሳሽነት የተቃውሞና የቁጣ ሰልፍ ወጥቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ህዝቡ ከተገደሉት መካከል የአዲስ አበባ ቂርቆስ ሰፈር ቀበሌ 25 ነዋሪ የነበሩት ጓደኛሞች ኢያሱ ይኮኖአምላክ እና ባልቻ በለጠ ቤተሰብ ልቅሶ ከደረሱ በኋላ በርካታ ሰዎች “አንመካም በጉልበታችን …” መዝሙር፣”ወያኔ ሌባ…ኢቴቪ ሌባ…መንግሥት የሌለው እዚህ ብቻ ነው፣ ታርዷል ወገኔ…” የሚሉ መፈክሮች፣ ልቅሶና ተቃውሞ እያሰሙ ወደ ቤተመንግሥት ለማቅናት ሲሞክሩ በተደጋጋሚ በአዲስ አበባና በፌደራል ፖሊስ ሲከለከሉ ታይቷል፡፡
ህዝቡ የመጀመሪያ መነሻውን ከልቅሶ ቤት ያደረገ ሲሆን በሌላ በኩል ከቄራ ቡልጋሪያ ሰፈርና ከሳሪስ ጎተራ ሪቼ መሷለኪያ ባለው መንገድ እንዲሁም ከሜክሲኮ መስመር ወደመስቀል አደባባይ ሲመጡ አብዛኞቹ በፖሊስ ድብደባና ክልከላ እንዲበተኑ መደረጉን ታውቋል፡፡ በመጨረሻም በተደጋጋሚ በፖሊስ አገታና የተደረገበት የሪቼው፤የሟቾቹ ቤተሰቦች ያሉበት ከቂርቆስ ሪቼ መስቀል አደባባይ የነበረው ሰልፍ እስጢፋኖስን አልፎ ወደ ውጭበ ጉዳይ ሚኒስቴር አካባቢ ሲደር ሙሉ ለሙሉ በፖሊስ ከታገተ ቧላ መንግሥት ለነገ ሐሙስ ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰልፍ መጥራቱን አስታውቋል፡፡
ዛሬ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ድርጊቱን በማውገዝ ከነገ ጀምሮ የ3 ቀናት ብሔራዊ ሀዘን ያወጀ ሲሆን፤ የሀገሪቱ ሰንደቅዓላማም በመላ ሀገሪቱ እና የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንስላ ጽህፈት ቤት በሚገኙበት ሁሉ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተወስኗል፡፡ በተለይ በፓርላማ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የተሰማቸውን ሀዘን ከገለፁ በኋላ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ ቢናገሩም ምን ዓይነት እርምጃ በመንግሥት እንደሚወሰድ ግን እስካሁን በዝርዝር አልገለፁም፡፡
በኢትዮጵያውን ላይ በአሸባሪ ቡድኑ የተፈፀመውን ጥቃት ኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ የአሜሪካ መንግሥት፣ በእንግሊዝ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ፣ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና በውጭ የሚገኘው የኢትዮጵያው ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን በትናንትናው ዕለት ድርጊቱን ወዲያው አውግዘዋል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት፣ መድረክ፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኢዴፓ፣ ድምፃችን ይሰማ ድርጊቱን በመቃወም አውግዘው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በተለይ ከህዝቡ ቁጣን የቀሰቀሰው የኢትዮጵ መንግሥት አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያውን ክርስቲያኖችን መግደሉን ቢያሳውቅም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እና በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስ ድርጊቱ ቢያወግዙም ዜግነታቸው ኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው አላጣራንም ካሉ በሁለተኛው ቀን አምነው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ መንግሥትም ሆነ ቤተክርስቲያኗ ከማመናቸው በፊት ከተገደሉት ኢትዮጵያውን መካከል የኢያሱ እና ባልቻ ቤተሰቦች ቀድመው በማወቅ ልቅሶ መቀመጣቸው ታውቋል፡፡ ይህም በህዝቡ ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ ዛሬ ዘግይቶ በተገኘው መረጃ መሰረት ከተገደሉት መካከል ቀደም ሲል ኢያሱና ባልቻ የታወቁ ሲሆን፤አሁን ደግሞ ከመቀሌ አካባቢ የጅማ ዩኒቨረስቲ ምሩቅ የነበረው ዳንኤል ሓድሽ እና አለም ተስፋይ እንዲሁም አንድ ኤርትራዊ እንደነበሩበት መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በአሁን ሰዓትም በርካታ ኢትዮጵውያን ከሊቢያ ትሪፖሊ ባልታወቁ ሰዎች ታፍሰው መወሰዳቸውን እና በስከተማው እና በሊቢያ ባህር ዳርቻ አካባቢ ከአሸባሪ ቡድኑ ጥቃት የተደበቁ በርካታ ኢትዮጵያውያን የአድኑን ጥሪ በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡













