Category Archives: Social and Culture

“ብሔር”ን ማን ፈጠረው?

ጌታቸው ሽፈራው

ጌታቸው ሽፈራው

የ”ብሔር”ን አፈጣጠር አስመልክቶ ሶስት ዋና ዋና አስተሳሰቦች የየራሳቸውን መልስ ይሰጣሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ተፈጥሯዊ (Primordial)፣ በማህበራዊ ሂደቶች የተፈጠረ (constructed) እና ልሂቃን ለስልጣን መሳሪያነት የፈጠሩት (instrumental) የሚባሉ ናቸው፡፡ የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ለ‹‹ብሄር›› መፈጠር የተሳታፊ ሀይሎችንና ወቅት ላይ ልዩነት ያላቸው ቢሆንም ከመጀመሪያው በተቃራኒ ‹‹ብሄር›› የሠው ልጆች የፈጠሩት እንጂ ተፈጥሯዊ አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ በመሆኑም ክርክሩ ተፈጥሯዊ እና ሰዎች የፈጠሩት በሚል ሁለት ጎራ ጠበብ ብሎ መቅረብ ይቻላል፡፡

የመጀመሪያው አስተሳሰብ ‹‹ብሄር›› ድሮ ሰው ከተፈጠረበት ወቅት ጀምሮ የኖረና ሰዎች እርስ በእርሳቸው ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ጥቅማቸውን ያስጠብቁበት የነበረ ተፈጥሯዊ (ሲወረድ ሲዋረድ የመጣ) ቡድናዊ መገለጫ ነው የሚል ነው፡፡ ሆኖም ይህ አስተሳሰብ ከጊዜ ወደጊዜ ከአንድ ‹‹ብሄር›› እየተሰነጠቁ ወይንም በሌላ ምክንያት የሚወጡ ‹‹ብሄሮች››ን ጥያቄ ሊመልስ አልቻለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአንዳንድ አገራት ጠንካራ የአገር ግንባታ ምክንያት የተለያዩ የነበሩ ህዝቦች አንድነት ስለማድረጋቸውም መለስ የለውም፡፡ ከምንም በላይ የዘመኑ ኢኮኖሚና አገራዊ ብሄርተኝነት ‹‹ብሄር›› የሚባልንም ሆነ ሌላ ማህበራዊ ስብስብን እያፈረሰ መገኘቱ ለዚህ አስተሳሰብ ድክመት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

‹‹ብሄር›› በሂደት የተፈጠረ ነው የሚለው አስተሳሰብ ‹‹ብሄር›› የተፈጠረው በተለያዩ ምክንያቶች በጊዜ ሂደት በተለይም በማህበራዊ ግንኙነት የተፈጠረ እና ትርጉሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀየረ የመጣ ነው የሚል ነው፡፡ ‹‹ብሄር›› ተፈጥሯዊ ነው ከሚሉት በተቃራኒ ‹‹ብሄር›› ማህበራዊ ፈጠራ ነው የሚለው የባህል ለውጥ፣ ድንበር፣ ታሪካዊ ወቅት፣ የግለሰቦች ሚና፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ለ‹‹ብሄር›› መፈጠር እንደ ምክንያትነት ይጠቅሳል፡፡

ሶስተኛው አስተሳሰብ ለ‹‹ብሄር›› መፈጠር ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ልሂቃንን ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ‹‹ብሄር›› የተፈጠረው ለልሂቃን መሳሪያነት (instrument) ነው ይላል፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ስር የሚገኙ ምሁራን ‹‹ብሄር››ን የፈጠሩት በ‹‹ብሄር›› ስም የሚነግዱ ልሂቃን ወይንም ‹‹የብሄር ኢንተርፕርነሮች›› (ethnic entrepreneurs) ይሏቸዋል፡፡ ይህንም የሚያደርጉት በአንድ አገር መንግስት ውስጥ ይገባናል የሚሉትን ጥቅም ለማሳደግ፣ ለዚህምና ለሌሎቹ ለሚደረጉ ትግሎች በዚህ በፈጠሩት ማንነት ስም በርከት ያሉ ምልምሎችን ለማግኘትና ይህንንም ተጠቅመው የራሳቸውን ግለሰባዊ ስልጣን ለማጠናከር ነው፡፡
ሁለተኛውና ሶስተኛም አስተሳሰቦች ከልዩነታቸው ይልቅ ተመሳሳይነታቸው የጎላ ነው፡፡ ልዩነታቸው ‹‹ብሄር›› በሂደት የመጣ ነው የሚሉት ለ‹‹ብሄር›› መፈጠር የፖለቲከኞቹን ሚና አጉልተው አለማሳየታቸው ሲሆን በአንጻሩ ‹‹ብሄር›› የልሂቃን ፈጠራ ነው የሚሉት ትልቅ ትኩረት የሚሰጡት ለልሂቃን ብቻ መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ‹‹ብሄር›› ቀስ በቀስ የተፈጠረ ነው የሚሉትም ስለልሂቃን በስፋት ባያነሱም ለ‹‹ብሄር›› መፈጠር ጠባብ ብሄርተኝነትን እንደምሳሌ ሲጠቅሱ የሚነሳው ‹‹ብሄር›› ለልሂቃን መሳሪያ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአንድ ወቅት በልሂቃን የበላይነት የተፈጠረው ብሄርተኝነት ቀስ በቀስ በህዝብ ዘንድ ሲዘወተር ለ‹‹ብሄር›› መፈጠር ድርሻቸው ከፍተኛ ስለሚሆን ሁለቱ አስተሳሰቦችን የሚመሳሰሉባቸው ነጥቦች ይበዛሉ፡፡ ሁሉቱ አስተሳሰቦች በየራሳቸው ያለባቸው መጠነኛ ክፍተትም ሁለቱን አስተሳሰቦች በጥምረት በመጠቀም ለ‹‹ብሄር›› መፈጠር ሙሉ እይታ መፍጠር እንደሚቻል ብዙዎቹ ምሁራን ያምኑበታል፡፡ ሁለቱን የጋራ የሚያደርጋቸው ደግሞ የልሂቃን ሚና ነው፡፡

ኢትዮጵያና ‹‹ብሄር››

ኢትዮጵያ የተለያየ ባህል፣ ወግ፣ ታሪክና ቋንቋ ያላቸው ህዝቦች መኖሪያ ብትሆንም ‹‹ብሄር›› በፖለቲካ ቃናው ትኩረት እየተሰጠው የመጣው ከጣሊያን ወረራ በኋላ ነው፡፡ በእርግጥ ከዚያ በፊትም ቢሆን የኢትዮጵያ የተለያዩ ገዥዎች ህዝብን በቋንቋ፣ ከባቢና በመሳሰሉት አንቀሳቅሰው ከሌሎች ጋር ያላቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልዩነት ለማጠናከር አልጣሩም ለማለት አይቻልም፡፡ በተለይ ህዝቦች በመንገድና በመሳሰሉት መሰረተ ልማት ባለመገናኘታቸው ባህል፣ቋንቋና ሌሎችም ባህላዊ እሴቶቻቸው በመለያየታቸው በሂደት ከሌሎች ለሚለዩባቸው አጋጣሚዎች ክፍተት ይፈጠራሉ፡፡ ይህን ልሂቃን በመሳሪያነት ሲጠቀሙበት ደግሞ ‹‹ብሄር›› መፈጠሩ የግድ ነው፡፡
አንድ ተመሳሳይ ቋንቋ፣ ባህልና ሌሎች ማህበራዊ እሴቶችን ይከተላል የምንለው ህዝብ በውስጡ መጠነኛ ልዩነቶች ይኖሩታል፡፡ ህዝቦች በተለያዩ ምክንያች ግንኙነታቸው ከተዳከመ እያደር እነዚህ ልዩነቶች እየተጠናከሩም በእነዚህ ህዝቦች መካከል ሰፋ ያለ ልዩነት ይፈጠራል፡፡ በተለይ እነዚህን ልዩነቶች የሚያስታርቅና የበላይ የተባለ ገዥ ማህበራዊ እሴት ከሌለ ህዝቦቹ ቀስ በቀስ ልዩነታቸው ሊሰፋ ይችላል፡፡ በየትኛውም አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ መካከል ዘየና ሌሎች ልዩነቶች በሂደት የቋንቋ መሰረታዊ ልዩነቶችን ይፈጥራሉ፡፡ ለአብነት ያህል አማርኛ እና ትግርኛ ከግዕዝ የመጡ መሆናቸው የሚነገርላቸው ቢሆንም የህዝቦች አሰፋፈር ልዩነት፣ መንገድና ሌሎችን የመሳሰሉ መሰረተ ልማት አውታሮች አለመኖር እንዲለያዩ አድርጓቸዋል፡፡ የልሂቃን ሚና ሲጨመርበት ደግሞ የአሁኑን ፖለቲካ ፈጥሯል፡፡

በአሁኑ ወቅት በትምህርት ደረጃ የሚሰጠው አማርኛ ሸዋ፣ ጎንደር፣ ጎጃምና ወሎ አካባቢ የሚነገሩ ዘየና ሌሎች የቋንቋው ልዩነቶችን ማስታረቅ ባይችል፣ በመሰረተ ልማት መገናኘት ባይችሉ እነዚህ ከጅኦግራፊያዊ አቀማመጥ ውጭ የማይለያዩ አማርኛ ተናጋሪ ህዝቦች ትግርኛ እና አማርኛ እንደተለያዩት የተለያዩ ቋንቋዎች መሆን ይችሉ እንደነበር አያጠራጥርም፡፡

ኢትዮጵያ አገውኛ ተናጋሪ ህዝቦች ይኖሩባት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩት ህዝቦች አገዎች እንደነበሩ በኢዛናና ካሌብ ዘመን የነበሩ ቅሬቶች ፍንጭ ሰጥተውል፡፡ እነዚህ ህዝቦች በአማርኛና ትግርኛ ተናጋሪው ህዝብ ተውጠው በአሁኑ ወቅት በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል በወሎና ጎጃም አገው በሚል፣ በጎንደር ቅማንት፣ በባህር ዳር አካባቢ ወይጦ እና የመሳሰሉ ስሞች ተሰጥቷቸው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ህዝቦች ትግራይና ኤርትራ ውስጥም ተበታትነው ይኖራሉ፡፡ ከከረን ጀምሮ በቋራ፣ ዳንግላ፣ ሰቆጣ፣ ጣና ዳር….ተበታትነው ከሚገኙት ውጭ ሌሎቹ በትግርኛ እና አማርኛ ተናጋሪ ሆነዋል፡፡ ይህኛው ክስተት የሚያሳየው ‹‹ብሄር›› ተፈጥሯዊ ማንነት ሳይሆን የሚዋጥ፣ የሚቀየር መሆኑን ነው፡፡ እነዚህ በአንድ ወቅት ‹‹አገው›› ተብለው የነበሩ ህዝቦች በሂደት በመጣ ማግበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ‹‹ኤርትራዊ››፣ ‹‹ትግሬ››ና ‹‹አማራ›› ተብለዋል፡፡ ልሂቃንም በተለያዩት እነዚህ ማንነቶች በአንድ ወቅት አንድ የነበሩትን ህዝቦች አንቀሳቅሰዋቸዋል፡፡ ሌላው ይቅርና ግዕዝ ከቤተክርስቲያን አልፎ በተወሰነ ህዝብ የሚነገር ቢሆኑ ኖሮ ኢህአዴግ አንድ ተጨማሪ ‹‹ብሄር›› ሊያቋቁም ነበር ማለት ነው፡፡

የአክሱም ስርወ መንግስት በተለያዩ ምክንያቶች ተዳክሞ የዛጉየ ስርወ መንግስት ሲተካ ከድልነአድ እስከ ይኩኑ አምላክ ያሉት 8 የአክሱም ስርወ መንግስት ነገስታት በሸዋ እየሸሹና ተደብቅው ኖረዋል፡፡ የአሁኑ ወቅት ልሂቅ መር የ‹‹ብሄር›› ፖለቲካ አክሱም ውስጥ የነበሩትን ነገስታት ‹‹የትግሬ ቅድመ አያቶች›› አድርገው ይወስዷቸዋል፡፡ ከአክሱም መጥተው ሸዋ ነገስትነትን የመሩትን ደግሞ ‹‹አማራ›› ይሏቸዋል፡፡ ታሪክ ደግሞ የአክሱም ስርወ መንግስት ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ይነገር የነበረው ቋንቋ አገውኛ እንደነበር ያስረዳናል፡፡

‹‹ብሄር›› ተፈጥሯዊ ቢሆን ኖሮ አገውኛ የሚናገሩት አብዛኛዎቹ ኢትዮጰያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ህዝቦች ሌሎች ቋንቋዎችን በሚናገሩ ህዝቦች ሳይዋጡ ‹‹አገው›› ሆነው በቆዩ ነበር፡፡ ትግሬ ከአክሱማውያን የመጣ ‹‹ብሄር›› ቢሆን ኖሮ መነሻቸው ከአክሱማውያን የሆኑት የሸዋ ነገስታትም እስከ አሁን ‹‹ትግሬ›› ሆነው በቀጠሉ ነበር፡፡ ይሁንና ‹‹ብሄር›› በሂደት በተለይም የልሂቃን ሚና ተጨምሮበት የሚፈጠር አዲስና የፈጠራ ማንነት በመሆኑ እነዚህ ህዝቦች የተለያዩ ማንነቶች እንዳላቸው እየተቆጠረ ነው፡፡

በአንድ ወቅት ኢህአዴግ አራት ያህል የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችን ‹‹ወጋጎዳ›› በሚል አዲስ የ‹‹ብሄር›› ማንነት ለመመስረጥ ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ ይህ አዲስ ማንነት ቢሳካ ኖሮ ሀይለማሪያም ደሳለኝ የወላይታ ሳይሆን በልሂቃን መሳሪያነት ከሌሎች ሶስት (ጋሞ፣ ጎፋና ዳዋሮ) ጋር የተለነቀጠው ‹‹ወጋጎዳ ብሄር›› ተደርገው ሊወሰዱ ነበር፡፡ ምንም እንኳ በተለያዩ ምክንያቶች ባይሳካም ‹‹የወጋጎዳ›› ፕሮጀክት ብሄርን የሚፈጥሩት ልሂቃን መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል፡፡

ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ‹‹ብሄር›› በግልጽ ተፈጥሯዊ እንደሆነ ተደርጎ ተግባራ ሊሆን ችሏል፡፡ ብሄር ተፈጥሯዊ ነው የሚለውን አስተሳሰብ የሚከተሉ አካላት አንድ ግለሰብ በ‹‹ብሄሩ›› እንጂ በግለሰባዊነቱ መቆም አይችልም የሚል አስተሳሰብ ያራምዳሉ፡፡ ይህም በእኛው ህገመንግስት ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች›› በሚል ተቀምጧል፡፡ በመሳሪያነት የሚጠቀሙ ፖለቲከኞች ‹‹ብሄር›› ተፈጥሯዊ ነው የሚሉ አካላት አስተሳሰብ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ በመሆኑም በአስተሳሰብ ደረጃ ‹‹ብሄር›› ተፈጥሯዊ ነው የሚለውን በመጠቀም ኢህአዴግ የ‹‹ብሄር ኢንተርፕርነር›› ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ‹‹ብሄር›› ተፈጥሯዊ ከሆነ የትኛውም ፖለቲከኛ ወይንም ፓርቲ ሊመሰርተው የሚችለው መንግስትም ሆነ ስርዓት ‹‹ብሄር›› ተመሳሳይ የ‹‹ብሄር›› ማንነት ላይ ያተኮረ መሆን አለበት፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ህዝቦች በአጼ ሀይለስላሴ፣ ደርግ፣ ኢህአዴግ ስር የያዙት የ‹‹ብሄር›› ማንነት በየ ስርዓቱ የተለያየና በየ ጊዜው እንደ ልሂቃኑ ጥበትና ኢትዮጵያዊ አላማ የሚወናበድ ነው፡፡

ወደ ኢህአዴግ ወረድ ብልን እንኳ በአቶ መለስና በሌሎቹ ገዥዎች ኢትዮጵያንም ሆነ በየ የኢትዮጵያን ‹‹ብሄሮች›› የሚያንቀሳቀሱበት አጋጣሚ የተለየ ነው፡፡ አንድ ህዝብ ሊከተለው የሚችለው በጊዜው በኢኮኖሚ፣ ሚዲያም ሆነ ወታደራዊ ሁኔታ ጊዜው ስልጣን የሰጠውን አካል ነው፡፡ ህወሓትና አረና የትግራይን ህዝብ የ‹‹ብሄር›› ማንነት የሚቀርጹበት ሁኔታ ተመሳሳይ አይሆንም፡፡ ብአዴንና የድሮው መአአድ፣ ኦነግና ኦህዴድ፣ የደቡብ ህብረትና ደኢህአዴን፣ ሶዴፓና ኦብነግ፣ ሻቢያና ጀብሃ እንወክለዋነን የሚሉትን ህዝብ ብሄራዊ ማንነት የሚመሩበትና የሚፈጥሩት በተለያየ መልኩ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከ20 አመት በፊት የነበሩትና አሁን ያሉት እነዚህ ፓርቲዎች ህዝብን የሚቀሰቅሱበት አጋጣሚ የተለያየ ነው፡፡ በቅርቡ ኦነግ የመገንጠል ጥያቄውን አንስቻለሁ ሲል ከ20 አመት በፊት ከነበረው የኦነግ የ‹‹ብሄር›› ማንነት መለየቱን ለመገንዘብ ይቻላል፡፡

‹‹ብሄር›› ደም

‹‹ብሄር›› ተፈጥሯዊ ካልሆነ ከደም ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም ማለት ነው፡፡ ሳይንስ በራሱ ዘር፣ ብሄርና ሌሎችን የሰው ልጅ ማህበራዊ ትስስሮች ለማመሳሰል ቢሞክርም ሊሳካለት አልቻለም፡፡ በተለይ ምዕራባዊያን ከሌሎች የተለዩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሙከራ ያደረጉ ‹‹ሳይንቲስቶች› ዘንድ የሰዎች ዘረመል የሰውን ዘርቁልጭ አድርጎ ያሳያል የሚል መላ ምት የነበራቸው ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ እስካሁን አንድ ሰው ከየትኛው አገር እንደመጣ የሚያሳይ አስተማማኝ መረጃ እንኳን ማግኘት አልተቻለም፡፡

በእነዚህ ጥናቶችን ተንተርስ ለአብነት ያህል ኢትዮጵያን እንደምሳሌ ብንወስድ የሚያሳየው የአንድ አገር ሰው በዘረመልም ሆነ በደም ከሌሎች አገራት ጋርም የሚመሳሰል ነው፡፡ እንደ ጥናቶቹ ኢትዮጵያዊያን ከቻይና፣ አብዛኛው የአረብና የኤሲያ አገራት፣ አንዳንድ የደቡብ አሜሪካና ሜክሲኮ ህዝቦች መካከል ከ10-15 የሚሆኑት በተመሳሳይ የኤ የደም ዘር ባለቤቶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን፣ አብዛኛዎቹ የአፍሪካዊያን፣ የደቡብ አሜሪካ ኤሲያ ከ5-10 እና ከ10-15 የሚሆነው ህዝባቸው ቢ የደም አይነት ያለው ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካ፣ የመንና ሳውዲ የመሳሰሉ የአረብ አገራት፣ የተወሰነ የቻይና ከፍል፣ ጥቂት የምስራቅ አውሮፓ አገራት፣ ከደቡብ አሜሪካ አገራት መካከል አንዳንድ አካባቢዎች፣ የአውስትራሊያ ጠረፋማ ክፍሎች ከሚኖሩት ህዝቦች መካከል ከ40-70 ኦ የደም አይነት ባለቤቶች ናቸው፡፡ በ‹‹ብሄሮች›› መካከል ይህን ያህል የሚመሳሰል የዘረመልና የደም አይነት ለማግኘት አልተቻለም፡፡ በዓለም ህዝቦች ሁሉ ኤ፣ ቤ፣ ኤቤና ኦ የተባሉት የደም አይነቶች የትም የሚገኙ ሲሆን ከአንድ ቤተሰብ ይልቅ በተለያዩ አገራት ያሉ ህዝቦች ለሌላኛው ደም መስጠት ይችላሉ፡፡ በመሆኑም አንድ ኦሮሞ ከብሄሩ ያላገኘውን ተመሳሳይ የደም አይነት ወይንም ልብ፣ ኩላሊትና ሌሎች ተመሳሳይ የአካል ክፍሎች ከትግሬ፣ ከአማራ፣ ከጉራጌና ከሌሎች ብሄሮች አልፎ ደቡብ አሜሪካ፣ ኤሲያ፣ አውሮፓና አውስትራሊያ ከሚገኝ ነጭ ማግኘት ይችላል፡፡

አንድ ቋንቋ የሚናገሩና በተለያየ የአየር ንብረት ከሚኖሩ ህዝቦች በተሻለ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩና በተመሳሳይ የአየር ንብረት የሚኖሩ ህዝቦች ተመሳሳይ የሰውነት ገጽታ ይኖራቸዋል፡፡ ለአብነት ያህል በመተማና ሁመራ አካባቢ የሚኖሩ ትግርኛ እና አማርኛ ተናጋሪዎች በቆላማው ሶማሊና አፋር ክልሎች ከሚኖሩት የሶማልኛና አፋርኛ ተናጋሪ ህዝቦች ተመሳሳይ የሰውነት ገጽታ፣ አለባበስና አመጋገብ ባህል አላቸው፡፡ ከምንም በላይ በአገራችን ብሄር የፈጠራ ማንነት መሆኑን የሚያሳየው ሁለት የተለያየ ማንነት አላቸው ከተባሉ ቤተሰቦች የተገኘ ልጅ የእናቱን ማንነት ትቶ የአባቱን ማንነት በግድ እንዲቀበል የመመደቡ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ግለሰብ በተለያዩ ምክንያቶች የእናቱን አሊያም ግለሰባዊ ማንነቱን መቀበል ቢፈልግ የወቅቱ የአገራችን ስርዓት በግድ የአባቱን ብሄር አባል ያደርገዋል፡፡ ሰው የፖለቲካ እንሰሳ እንደመሆኑ ‹‹ብሄር››ን ሲፈጥር እንሰሳት ከሰው የተሻለ ቁርጥ ያለ ዘር ያላቸው ማንነታውን በሂደት በሚፈጠር ማህበራዊ ማንነት አሊያም የልሂቃን ፈጠራ የሚያወናብደው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ምክንያት ባለመጠቀማቸው ብቻ ነው፡፡

ሶቭየት ወዲያ ኢትዮጵያ

በአገራችን የ‹‹ብሄር›› ማንነት የሚጣረሰው ገና ከትርጉሙ ነው፡፡ ‹‹ብሄር›› በግዕዝ አገር ማለት ቢሆንም ከ1960ው ጥራዝ ነጠቅ ትውልድ ትርጉም በኋላ አገሪቱ የተሰራችባቸው ማንነቶች ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በእነ ስታሊኑ ትርጉም እንኳ ብንሄድ ብሄር የሚለውን ‹‹ተመሳሳይ ወይንም ተቀራራቢ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣…..›› ለሚጋሩ ህዝቦች የሚሰጥ ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ህዝቦች ከሌሎች የተለዩ፣ ማንነቱ ተፈጥራዊና ከሌሎች በፍጹም የተለየ በመሆኑ መቼም ቢሆን ይህን ባህላቸውን፣ ማንነታቸውን አይቀይሩም እንደማለት ነው፡፡ ‹‹የጋራ ታሪክ ያላቸው›› ብሎ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወላይታ፣ (ቢሳካ ኖሮ ደግሞ ‹‹ወጋጎዳ)፣ ሲዳማ…ሲልም የአድዋና ማይጨውን ጨምሮ የሚጋሩት ታሪክ የላቸውም እያሉን ነው፡፡

በቭየት ህብረትና በኢትዮጵያ መካከል ከፍተኛ ልዩነት ነው ያለው፡፡ ሌኒን 15 አገራት አንድ ከማድረጉ በፊት ኢትዮጵያውያን በጋራ አገር ለመመስረት ለረዥም አመት ሰርተዋል፡፡ በአንጻሩ የሶቭየት ክፍሎች አንድ እስኪሆኑ ድረስ ያላቸው ታሪክ የተለየ ነው፡፡ የሶቭዬት ህብረት አባላት ህብረቱን ከመራችው ሩሲያም ሆነ ከሶቭየት ህብረት የተለየ የአገር ምስረታ ታሪክ አከናውነው የተቀላቀሉ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ የሩሲያ መንግስት ከመስፋፋቱ በፊት በኦቶማን ቱርክና በሌሎች ቀኝ ገዥዎች ስርም የነበሩ ናቸው፡፡

የሶቬት ህብረት ፌደራል አወቃቀር በአገራት እንጅ አገር ውስጥ ባሉ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች የተመራ አልነበረም፡፡ ኢህአዴግም የነ ስታሊንን ስርዓት ሲገለብጥ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ሀረሪ…..እያንዳንዳቸው ‹‹አገር›› ሆነው ፌደራሊዝሙን እንደተቀላቀሉ እየነገረን ነው፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያ ውስጥ በየ አካባቢው የነበሩ ነገስታት ኢትዮጵያን በራሳቸው መልክ ለመገንባት እንጅ የያዙትን አካባቢ ገንጥለው አገር ለመመስረት አልነበረም፡፡ የየራሳቸውን ግዛት ለመመስረት ነበር የሚል የፈጠራ መረጃ እንኳን ቢቀርብ ‹‹አገር›› ለመሆን የሚያስችል ቅርጽ ሳይዙ ማዕከላዊ መንግስት ውስጥ መጠቃለላቸው ከሶቬት አባላት በእጅጉ የተለዩ ያደርጋቸዋል፡፡

እንዲያው የስታሊኑን ትርጉም ብንወስድ እንኳን የእኛው የ‹‹ብሄር›› ትርጉም የተሳሳተ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ኢትዮጵያውያን ቋንቋ ሳይገድባቸው እንጀራና ጥሬ ስጋ ይመገባሉ፡፡ ጠላና ጠጅ ይጠጣሉ፡፡ ተዋልደውና በጉድፍቻ አብረው ይኖራሉ፡፡ አተራረሳቸው፣ አመራረታቸውና ምርቶቻቸው በአየር ንብረት ካልሆነ በስተቀር ልዩነቱ ጎልቶ የሚተይ አይደለም፡፡ በጋራ አላማ ቅኝ ገዥዎችን ተዋግተዋል፡፡ አገር ገንብተዋል፡፡ በመሆኑም በስታሊኑ ቋንቋ ‹‹ተመሳሳይ ወይንም ተቀራራቢ ባህል፣ ታሪክ፣ አላማ….›› መሰረት አንድ ብሄር (አገር›› ውስጥ የሚካተቱበት እንጅ የሚነጣጠሉበት አልነበረም፡፡

በነገራችን ላይ ህዝቦች የተለያዩ ናቸው ተብሎ ‹‹ብሄር›› የተለያዩ ቋንቋ ተናገሪ ህዝቦች መጠሪያ በዋለበት እንደገና ‹‹ብሄር›› ማለት አገር ማለት መሆኑን ይነገረናል፡፡ ለአብነት ያህል ብሄራዊ ቡድን ሲባል የኦሮሞ፣ የአማራ፣ ትግሬ፣ ወላይታ ተጫዋቾች ብቻ የተሰባሰቡበት ሳይሆን የአገሪቱ ቡድን መሆኑ ነው፡፡ ብሄራዊ ባንክ ሲባልም ቢሆን የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ እንጅ በሂደት ሲቀየር፣ ሲዋጥ፣ ሲያንሰራራ በኖሩት ቋንቋን መሰረት ያደረጉ ማንነቶች ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡

ከማርክሲስቱ ትርጉም ይልቅ የምዕራባዊያን ትርጓሜ ‹‹ብሄር›› የተወናበደ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡ ብሄር (አገር) በእንግሊዘኛው (በምዕራባዊያኑ አስተሳሰብም) ‹‹Nation›› በሚለው ቃል ይገለጻል፡፡ ‹‹Nationality›› የሚለው ደግሞ አንድ ግለሰብ ከአገሩ ጋር ያለው ግንኙነት የሚገለጽበት ነው፡፡ ነዋሪ፣ ተወላጅ፣ ዜጋ በሚለው ልንወክለው እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ቢሆን በፓስፖርትና በመሳሰሉት ‹‹Nationality›› ቋንቋ ሳይገድበው የሚገልጸው ዜግነትን ነው፡፡ ለፖለቲካው ዘርፍ ደግሞ ‹‹ከትልልቆቹ ብሄሮች ያነሱ›› የሚሏቸውን ማንነቶች ለመግለጽ ይውላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሄር የሚባለው ‹‹Nation›› (አገርን) ሳይሆን ‹‹ethnicity›› የሚለውን ‹‹ማንነት›› እንዲወክል ተደርጓል፡፡ ‹‹ethnicity›› ደግሞ በወጉ ይተርጎም ከተባለ ከጎሳ ያለፈ ቃል ሊገኝለት አይችልም፡፡
ይህ የሚያሳየው መሰረታቸውን ካደረጉበት የስታሊኑ ትርጉም ጋር እንኳ አብረው መሄድ አለመቻላቸውን ነው፡፡ ይህ ተቃርኖ የሚመነጨው ብሄር ከሂደቱም ይልቅ ፖለቲካ ፈጠራው ማመዘኑ ነው፡፡ በአገራችን ደግሞ ከሁለቱም ትርጉሞች ሳይሆን ጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ላይ ማተኮሩ ተቃርኖውን ውስብስብ አድርጎታል፡፡

የአድዋ ድል በዓል በሀገር ውስጭና በውጭ ባሉ ኢትዮጵያውን እየተከበረ ነው

ብስራት ወልደሚካኤል

adwa1

በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመን የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በቅኝ ለመግዛት በያዝነው የካቲት 1888ዓ.ም. ባደረገው ወረራ በኢትዮጵውያን አርበኞች በአዋድዋ ላይ ድል የተደረገበት 119ኛ ዓመት በሀገር ውስጥና በውጭ ባሉ ኢትዮጵያውን እየተከበረ ይገኛል፡፡

በዓሉ ምንም እንኳ በኢትዮጵውን የተገኘ ቢሆንም፤ በቅኝ ግዛት የነበሩ የአፍሪካ ሀገሮችና ሌሎችም ራሳቸውን ነፃ ማውጣት እንደሚችሉ ከፍተኛ መነሳሳት እንደፈጠረና በቅን የተገዙ ሀገሮች ከአውሮፓ ቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡ ዕድል እንደፈጠረላቸው በርካታ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ስለሆነም በዓሉ በተለይ ከኢትዮጵያ ባለፈ የጥቁሮች ድል ተደርጎም እየተቆጠረ ይገኛል፡፡

በወቅቱ ጣሊያኖች እጅግ ውድና ዘመን ያፈራውን የውጊያ መሳሪያ የተጠቀሙ ሲሆን፤በውጊያውም በጣሊያን በኩል በርካታ የጣሊያን ወታደሮችና ኢትዮጵውን ባንዳዎች ሲሰለፉ፤ኢትዮጵውያን ደግሞ ከተወሰኑ ጊዜ ያለፈባቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች በስተቀር ለውጊያው የተጠቀሙት ኋላ ቀርና በሀገር ውስጥ የተለመዱ መሳሪያዎችን ነበር፡፡

የጦርነቱም መንስኤ የውጫሌ ውል አንቀፅ 17 ሲሆን፤ ጣሊያን በውሉ ላይ በአማርኛውና በእንግሊዘኛው ትርጉም ሆን ብላ እንዲለያይ በማድረግ ኢትዮጵያን በቀላሉ በቅኝ ለመግዛት መነሳቷን ተክትሎ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በጦርነቱም በርካታ ኢትዮጵያውያን ምንም ተቀጥላና ልጥፍ የሌለበትን የሀገሪቱን አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ደማቅ ሰንደቅዓላማ በመያዝ ፆታ፣ዕድሜ፣ቋንቋና ኃይማኖት ሳይገድባቸው ሀገራችንን ነፃ ለማውጣት ከሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ በእግርና በፈረስ በሚደረግ ረጅም አድካሚ ጉዞ የተሳተፉ ሲሆን፤ በጦርነቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው አልፏል፡፡ ከጣሊያን ጦርም እንዲሁ በርካታ ሰዎች ሲሞት ብዙዎች ተማርከው ከድሉ በኋላ በዓለም አቀፍ ስምምነት መሰረት ከእስር ተለቀዋል፡፡

ውጊያውን በአዋጅ በማስነገር የመሩትና ወደ አድዋ የሸዋን ጦር ይዘው የዘመቱት የወቅት የኢትዮጵያው ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጼ ምኒልክና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ሲሆኑ፤እንደየ ማዕረጋቸውም ከተለያየ የሀገሪቱ አቅጣጫ ያለውን ጦር ይመሩ የነበሩ የተለያዩ የጦር አመራሮችም ንጉሱን በመከተል በአድዋው ጦርነት ላይ ተሳትፈው ሀገሪቱንና ህዝቧን ከቅኝ ግዛት ነፃ አውጥተዋል፡፡ ይህንንም ድል ሆነ ተሳታፊዎችን ማንም፣ መቼም በምንም ሊሽር በማይችል መልኩ በዓለም ታሪክ ሰፍሮ እንዲህ እየተዘከረ ይገኛል፡፡

Adwa2

በተለይ የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ራስ ጎበና፣ የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲ-ነግዴ፣ራስ አሉላ አባነጋ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ አባተ፣ራስ መንገሻ ስዩም፣ ባሻ አዋዓሎም (የጠላትን ጦር በመሰለልና መረጃ ለንጉሱ በመስጠት)፣ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ (የአጼ ኃይለስላሴ አባት፤ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማሲውን በብቃት በመወጣትና የሐረርን ጦር በመምራት፣ የወሎው አስተዳዳሪ ራስ ዓሊ፣ ደጃዝማች ባልቻ አባሳፎ (ባልቻ አባ ነፍሶ)፣ ራስ  አባተ ቧ ያለው፣…እና ሌሎችም ግንባር ቀደም የጦር አመራሮች ከነወታደሮቻቸው ከፍተኛ ተጋድሎ በመፈፀም ለዛሬው የኢትዮጵያና ለመላው ጥቁር ወርቃማ የድል ታሪክ አብቅተዋል፡፡ ይህ በኢትዮጵያውያን በተገኘው ተጋድሎ የድሉ ታሪክም በአፍሪካና በመላው ዓለም ወርቃማ የጥቁር ድል ታሪክ ሆኖ በክብር ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

ወርቃማ የህዝብ ታሪክ ዘመን ሳይሽረው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲህ እየተዘከረ ይኖራል፡፡ በትግሉ ዋጋ የከፈሉና የሰው አያቶቻችንን ነፍስ ፈጣሪ በገነት ያኑርልን፡፡

ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ፤ ክብር ለአድዋ ጀግኖች፣ ክብር ለነፃነት ላበቁን አባቶቻችን እና እናቶቻችን!!

የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ተቃጠለ

የሆሳዕከና ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ከመቃጠሉ በፊት

የሆሳዕከና ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ከመቃጠሉ በፊት

በደቡብ ክልል በከንባታ፣ሀዲያ፣ጉራጌና ስልጤ ሀገረ ስብከት፤ሆሳዕና ከተማ የሚገኘው ታሪካዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ጵጵስና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ተቃጠለ፡፡ የእሳት አደጋ ቃጠሎው የደረሰው ትናንት የካቲት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲሆን፤ የቃጠሎው መንስኤ እስካሁን አልታወቀም፡፡ በረደሰው ቃጠሎ የቤተክርስቲያኗ ህንፃ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ የጉዳቱ መጠን በአሀዝ ግን እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም፡፡ በደረሰው የቃጠሎው አደጋ በቤተክርስቲያኗ የነበሩ ታሪካዊ ቅዱሳት መፃህፍትን ጨምሮ በርካታ ንብረቶች መውደማቸው የተገለፀ ሲሆን፤ የአካባቢው ህዝብ እሳቱን ለማጥፋት ባደረገው ርብርብ ታቦታቱን ከአደጋው ማትረፍ መቻሉን ከስፍራው የመረጃው ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡

እሳቱንም ለማጥፋት በተደረገው ርብርብ ከከተማው የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታይ ምዕመናን በተጨማሪ በርካታ የአካባቢው የእስልምና እና የፕሮቴስታንት ኃይማኖት ተከታዮች በፍጥነት ደርሰው መሳተፋቸውንና በዚሀም ታሪካዊ የብራና መፅሐፍቱን እና ታቦታቱን ማዳን እንደተቻለ ከስፍራው የደረሱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ጀቤተክርስቲያኗን ጨምሮ በቤተመቅደሱ ውስጥ ያሉ ሌሎች ንብረቶች በቃጠሎው አደጋ ሙሉ ሙሉ መውደዋማቸው ታውቋል፡፡ ይሄንንም የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣የዞኑ የፀጥታ ዘርፍ ዋና ኃላፊ፣ የከተማው የሆሳዕና ከተማ ከንቲባ፣ የከተማው የእስልምና እና የፕሬቴስታንት ኃይማኖት መሪዎች በስፍራው በአካል በመገኘት ቤተክርስቲያኗ ታንፃ ወደ ቀድሞ ይዞታ እስክትመለስ ድረስ በግላቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ለቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪዎችና ሰባካ ጉባዔ ቃል መግባታቸውም ተነግሯል፡፡ ነገ ሰኞ የካቲት 23 ቀን 2007 ዓ.ም. የሀገረ ስብከቱና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀለምኒጦስ በተገኙበት  የቤተክርስቲያኗ የህንፃ አሰሪ ኮሚቴ እንደሚዋቀርና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርም ይፋ እንደሚደረግ ከሆሳዕና የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡

የሆሳዕከና ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የእሳት አደጋ በደረሰበት ወቅት

የሆሳዕከና ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የእሳት አደጋ በደረሰበት ወቅት

በሆሳዕና ከተማ በርካታ የመንግሥትና የህዝብ ተቅማት ቢኖሩም፤አሁን ከደረሰው የቤተክርስቲያን ቃጠሎ በተጨማሪ ከዚህ በፊት በደረሱ የእሳት አደጋዎች ከተለመደው የህዝብ ርብር ውጭ የከተማው መስተዳደር የእሳት አደጋ መከላከያ ዝግጅትም ሆነ መሳሪያ ባለመኖሩ በርካታ የንግድ ሱቆች ተቃጥለው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንብረቶች መውደማቸው አይዘነጋም፡፡

የካቲት 21 ቀን 2007 ዓ.ም.  በደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ቃጠሎ ምክንያት 106 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረው ታሪካዊው የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ህንፃ ሙሉ ለሙሉ መውደሙ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም በተቃጠለው ቤተክርስቲያን ምትክ አዲስ ህንፃ ቤተክርስቲያን ለማሰራት በይፋ እንቅስቃሴ በመጀመሩ፤ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ለምትፈልጉ፡-

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣

ባቴና ቅርንጫፍ፤ ሆሳዕና

ዝግ የባንክ አካውንት ቁጥር  100 011 0719 969

መርዳት እንደሚቻል በመጠቆም፤ ለምታደርጉት ድጋፍ ሁሉ በቤተክርስቲያኗ ስም ከወዲሁ ማመስገኑን የህንፃ አሰሪው ኮሜቴ አስታውቋል፡፡

ለበለጠ መረጃ 

ሀገር ውስጥ ላሉ በስልክ ቁጥር 0912- 446829 ወይም 0913-750229

ከውጭ ሀገር ከሆነ  +254 912-446829 ወይም +254 913 750229  ማነጋገር እንደሚቻል የህንፃ አሰሪው ኮሚቴ አስታውቋል፡፡

በአዋሳ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ የሟቾች ቁጥር ከ20 በላይ ነው ሲሉ የቃጠለው ሰለባ የሆኑ ሰዎች ገለፁ

የአዋሳ ከተማ ሲቲ ሴንተር አካባቢ

የአዋሳ ከተማ ሲቲ ሴንተር አካባቢ

በደቡብ ክልል ዋና ከተማ በአዋሳ የካቲት 14 ቀን 2007 ዓም በደረሰው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ የሟቾች ቁጥር በመንግስት እንደተገለጸው አንድ ሳይሆን ከ20 በላይ መሆኑን ተገጂዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

ከፍተኛ ንብረት ከወደመባቸውና እሳቱ ሲነሳ በስፍራው ከነበሩት መካከል አንዱ ለኢሳት ሲናገር፣ እርሱ የ6 ሰዎችን የተቃጠለ አስከሬን ማየቱን፣ በስፍራው የሚገኙ ጓደኞቹ ደግሞ በአጠቃላይ እስካሁን 27 አስከሬን ተፈልጎ መቀበሩን ተናገሩዋል።

አንድ ህጻነት እና አንዲት እናት ከ3 ልጆቿ ጋር ሞታ መመልከቱን፣ በማግስቱ ደግሞ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች ሞተው ማየቱን የሚናገረው ግለሰቡ፣ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች አካባቢውን ከነዋሪው በመከለል ማታ ማታ የተቃጠለ አስከሬን እየፈለጉ በመቅበር ላይ ናቸው ብሎአል። እናቶች አሁንም ድረስ ልጆቻቸውን እየጠየቁ ቢሆንም፣ በከንቲባው በኩል የሚሰጠው ምላሽ አሳዛኝ መሆኑን ግለሰቡ ገልጿል። ነዋሪዎቹ በመንግስት በኩል በቂ እርዳታ እንዳልተደረገላቸው በምሬት ተናግረዋል።

መንግስት የእሳቱን መነሻ እስካሁን ይፋ አላደረገም። ነዋሪዎች እንደሚሉት ግን መስተዳድሩ ቦታውን ለመሸጥ እሳቱን ሆን ብሎ አስነስቶታል። በጉዳዩ ዙሪያ የአዋሳን ከንቲባ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራም እንዳልተሳካ በመግለፅ ኢሳት ዘግቧል፡፡

በአዲስ አበባና በክልሎች በርካታ ኢትዮጵውያን ሙስሊሞች በመንግሥት እየታሰሩ መሆኑ ተሰማ

Ethio-muslims protest

ከጥር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ የኃይማኖት ነፃነት መብትና ህገ-መንግሥቱ እንዲከበር፤ በሰላማዊ መንገድ እየጠየቁ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሙስሊሙ ማኀበረሰብ  የመንግሥትን ህገወጥ እርምጃ ተቃውሞ መቀጠሉን ተከትሎ፤አሁንም በያዝነው የካቲት 2007 ዓ.ም. ከየቤቱና ከስራ ቦታ ጭምር የጅምላ እስሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የክልል ከተሞች የሚመጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ የመንግሥትን ያይል እርምጃ እና የኃይማኖት ነፃነት መብታቸው እንዲከበርና መንግሥትም ከኃይማኖት ጣልቃ ገብነት እንዲወጣ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ተከትሎ ሰሞኑን የጅምላ እስር እየተካሄደ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

Anuwar mosque protest

የጅምላ እስሩ እየተከናወነ የሚገኘው መንግሥት በመጪው ምርጫ 2007 ዓ.ም. ከሙስሊሙ ማኀበረሰብ ድጋፍ እንደሌለው በመረዳቱና በርካቶችም የድምፅ መስጫ በረቀት መውሰዳቸው የደረሰው መረጃ አስደንግጦት እንደሆነ ቢጠቆምም፤ ከመንግሥት በኩል ግን እየተወሰደ ስላለው የጅምላ እስር የተሰጠ  ምንም ዓይነት ማብራሪያም ሆነ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በተለይ ሰሞኑን በተወሰደውና እየተወሰደ ባለው የጅምላ እስር ተጠናክሮ መቀጠሉን ከመጠቆም ባለፈ፤እስካሁን ምን ያህል ሰዎች እንደታሰሩ ግን ለማወቅ አልተቻለም፡፡

ከዚህ ቀደም መንግሥት የኢትዮጵያ ሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ጋር ሲደራደር ቆይቶ፤ በመጨረሻም በጅምላ በማሰር የሽብር ክስ መስርቶባቸው የኮሚቴው አባላት ያለምንም ፍትህ እስካሁን በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡