የመድረክ እጩ ተወዳዳሪ በትግራይ ተምቤን በፖሊስ ተደበደበ
የወርቃ ኣምባ ምርጫ ክልል መድረክን ወክሎ ለክልል ምክርቤት በእጩነት የቀረበው ወጣት ዜናዊ ኣስመላሽ በፖሊስ ተደብድቦ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶታል።
ወጣት ዜናዊ ኣስመላሽ ትናንት ቅዳሜ የካቲት 7 ቀን 2007ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት የወርቃ ኣምባ ከተማ ኣስተዳዳሪ ተስፋይ ሃይሉ “..ይዛቹ ኣምጡት ብሎናል..” በማለት ሃፍተ ኪሮስ የተባለ ፖሊስና ገብረተኽለ ወለቸኣልና ገብረጀወርግስ ሙሉ የተባሉ ሚሊሻዎች ወደ ፖሊስ ኮሚኒቲ እየደበደቡ ወስደውታል። በወቅቱ በርካታ ህዝብ እየተመለከተ የነበረ ሲሆን ድብደባው በህዝቡ እርዳታ እንዲቆምና ወደ ዋና ፖሊስ ጣብያ ወስደው እንዲያስሩትና ድብደባው እንዲያቋርጡት ተቃውሞው በማሰማቱ ድብደባው ተቋርጧል።
ተደባዳቢው ፖሊስና ሚልሻዎቹ ለምን እንደደበደቡት ሲጠየቁ “..ወደ ፖሊስ ጣብያ ስንወስደው ቀስ እያለ ሲሄድ ፈጠን በል ስንለው ቀስ እያለ በመሄዱ ነው..” ሲሉ መልሰዋል።
ፖሊስ ኣዛዡ ያለ ምንም ምክንያት እንደተደበደበ ካረጋገጠ በሗላ “..ፖሊሱ ሰካራም መሆኑና ቅር ሊለው እንደማይገባው..” ነግሮ ማታ ሰዎስት ሰዓት ከእስር ቤቱ ኣስፈትቶታል።
ወጣት ዜናዊ ኣስመላሽ ከእስር ከተለቀቀ በሗላ በጤና ኬላ የህግምና እርዳታ ተደርጎለታል።
ማታ 5 ሰዓት ኣከባቢ ፖሊስ ሃፍተ ኪሮስ ከ3 ሚልሻዎች በመሆን ወዳረፈበት ቤት በመሄድ ለባለ ቤቱ ማስፈራራት ኣድርሰዋል።
የህወሓት መንግስት በሑመራና ሽረ የሚገኙ ኣባሎቻችንም ተመሳሳይ ድብደባ ኣድርሰዋል ሲል በመቀሌ የመድረክ አመራር አባል ገልፀዋል፡፡
በከተማ ባቡር መስመር ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ተዘጋጀ
ታምሩ ጽጌ
– ሰሞኑን ሁለት ተሽከርካሪዎች በመስመሩ ላይ ጉዳት አድርሰዋል
በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ በሚገኘው የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ረቂቅ ሕግ መዘጋጀቱ ተጠቆመ፡፡
የቀላል የባቡር ፕሮጀክቱ የመጨረሻ ምዕራፍ የሙከራ አገልግሎት የተጀመረ ቢሆንም፣ ሰሞኑን በመስመሩ ላይ የተከሰቱ ሁለት አደጋዎች ፕሮጀክቱን በማከናወን ላይ ያሉትን ቻይናውያን ሳይቀር ሥጋት ላይ ጥለዋል፡፡
በመሆኑም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተሽከርካሪዎችና እግረኞች በምን ሁኔታ እንደሚስተናገዱ፣ በተለይ ተሽከርካሪዎች ለሚያደርሱት ጉዳት ተጠያቂ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ መረቀቁንና ለውይይት ለሕዝብ ሊቀርብ መሆኑን፣ የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ አስረድተዋል፡፡
የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ሌሊቱን አንድ የግል ንብረት የሆነ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ከነጭነቱ ሳሪስ ኦይል ሊቢያ ዲፖ ፊት ለፊት ያለውን የባቡር ሐዲድ አጥር ጥሶ ገብቷል፡፡ ተሽከርካሪው ምንም እንኳን በሰው ሕይወት ላይ አደጋ ባያስከትልም፣ እስካሁን በውል ያልታወቀ ኪሳራ ማድረሱ ታውቋል፡፡ አደጋ የደረሰበት የመስመሩ አጥር መልሶ ከተገጣጠመ በኋላ፣ ባቡር እንዲያልፍበት ተደርጎ ጥንካሬው ሲፈተሽ ችግር እንደሌለው መረጋገጡን አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡ ወጪውን በሚመለከት የኢንሹራንስ ግምት እየተጠበቀ መሆኑንም አክለዋል፡፡
በተለይ ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ተናግረው፣ ወደፊት ባቡሩ ሙሉ በሙሉ ሥራ በሚጀምርበት ወቅት ምን ያህል የከፋ ነገር ሊገጥም እንደሚችል ጠቋሚ በመሆኑ ሕግ መውጣቱ ተገቢ መሆኑን፣ በፍጥነት ፀድቆ ወደ ተግባር መሄድ እንደሚገባ መናገራቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
ኣሸጎዳ የንፋስ መብራት ማመንጫ ሃይል ዲናሞ በመቃጠሉ ምክንያት ከጥቅም ውጭ ሆነ
በመቀሌ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኝ የኣሸጎዳ በንፋስ የሚሰራ ኤለክትሪክ ማመንጫ ሃይል በዲናሞ መቃጠል ምክንያት ከስራ ውጭ መሆኑ ታውቋል። የተቃጠለው ዲናሞ 150 ሜጋዋት የማመንጨት ኣቅም የነበረው ሲሆን ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት በመቃጠሉ ሃይል የማመንጨት ኣቅሙ ሙሉ በሙሉ ማቆሙ ታውቋል።
የተቃጠለው ዲናሞ ቅያሪ በሃገር ውስጥ እንደሌለና ከፈረንሳይ ሃገር እንደሚመጣ ታውቋል። የህወሓት የ40 ዓመት የልደት በዓል እንደ ታላቅ ውጤትና ማጣፈጫ ተደርጎ ሊወሰደ ታስቦ የነበረ ሲሆን ባልታወቀ ምክንያት መቃጠሉ በክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከፍተኛ ቁጣና ድንጋጤ መፍጠሩ ታውቋል።
የትግራይ ባለስልጣናት እንደ ግዝያዊ መፍትሄ ኣድርገው የወሰዱት የየካቲት በዓል እስኪያልፍ ከፈርንሳይ በክራይ እንዲመጣና ብልሸት እንዳልደረሰው ኣስመስሎ በማሳለፍ በዓሉ ከተጠናቀቀ በሗላ ዲናሞው ወደ ፈረንስይ እንዲመለስ የሚል ትእዛዝ ኣስተላልፈዋል።
የህወሓት ባለስልጣናት የየካቲት በዓል ታዳሚዎች ኣሳፋሪ በሆነ ድራማ ኣጭበርብረው ለመመልስ ከፈረንሳይ ዲናሞ ተከራይተው ካሳዩሗቹ በሗላ ተመልሰው ወደ መጣበት ይመልሱታል። ህወሓት የዲናሞው መቃጠል ለየካቲት በዓል ማክበርያ ካወጣችው 1 ቢልዮን ብር ወጪ የምታወጣው ተጨማሪ ግዙፍ ብር ይሆናል።
ሰማያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤቱን እንዲለቅ ክስ ቀረበበት
• በወር 40 ሺህ ብር ኪራይና 250,000 ብር ለ‹‹ኪሳራ›› እንዲከፍል ተጠይቋል
ሰማያዊ ፓርቲ የካ ክ/ከተማ በቀድሞው መጠሪያው ቀበሌ 15 እንዲሁም በአዲሱ መጠሪያው ወረዳ 6 የቤት ቁጥር 460 የሆነውን ጽ/ቤቱን 25000 ሺህ ብር ቅጣት ከፍሎ እንዲለቅ በአከራዮቹ በኩል ክስ ቀረበበት፡፡ በከሳሽ እነ አቶ ሚስጥረ ሽበሽ የተመሰረተው ክስ ‹‹ቤቱን ለቀው ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው …በወር ብር 40,000 (አርባ ሺህ ብር) ሒሳብ ከጥር 16 ቀን 2007 ጀምሮ ቤቱን ለቀው እስከሚያስረክቡ ድረስ ባልተነጣጠለ ኃላፊነት እንዲከፍሉን›› ያሉ ሲሆን ‹‹ከሳሽ ቤቱን ለማደስ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በገባነው ውል መሰረት የደረሰብንን 250 ሺህ ብር ኪሳራ እንዲተኩልን›› ሲሉ ከሰዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሚፈልግባቸው ጊዜያት የቀበሌ ካድሬዎች አከራዮቹና ደላሎቹ ለፓርቲው እንዳያከራዩ ሲያስጠነቅቁ የቆዩ ሲሆን በተለይ በጥር ወር 2007 ዓ.ም ይህ ጽ/ቤት እንዳይከራይ ግፊት የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ድብደባ ከተፈጸመባቸው ሁለት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የአንደኛው ሕይወቱ አለፈ
ታምሩ ጽጌ
–ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ ናቸው
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አካባቢ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ፣ ሁለት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የጥበቃ ሠራተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው አንደኛው ሕይወቱ ማለፉ ተረጋገጠ፡፡
ጥር 23 ቀን 2007 ዓ.ም. የግማሽ ዓመት ፈተናቸውን ካጠናቀቁት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል፣ ሙሉቀን ከበደና ታምራት አባተ የተባሉ ተማሪዎች በዕለቱ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ታውቋል፡፡ ተማሪዎቹ ፈተናቸውን እንዳጠናቀቁ ከግቢ ወጥተው ሲዝናኑ ካመሹ በኋላ ወደ ማደሪያ ክፍላቸው ሲመለሱ፣ ፀደቀ አድማሱ ከሚባለው ተጠርጣሪ የጥበቃ ሠራተኛ ጋር መጋጨታቸውን ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ሊገቡ ሲሉ ተጠርጣሪው እንዲቆሙ ሲያደርጋቸው ተማሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጡበትን መታወቂያ ቢያሳዩም፣ ከተጠርጣሪው ጋር ሊግባቡ ባለመቻላቸው ድብድቡ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ተጠርጣሪው በወቅቱ ይዞት በነበረው የእንጨት ዱላ ደጋግሞ ሲደበድባቸው የተመለከተ ሾፌር፣ ሌሎች የተኙ ጥበቃዎችን በማስነሳቱ የተፈጠረው ድብድብ የቆመ ቢሆንም፣ ተማሪዎቹ በደረሰባቸው ድብደባ ተጎድተው ስለነበር በአቅራቢያቸው በሚገኘው ጥሩነሽ ቤጂንግ ጠቅላላ ሆስፒታል መወሰዳቸውም ተጠቁሟል፡፡
ታምራት አባተ የተባለው ተማሪ በጥሩነሽ ቤጂንግ ጠቅላላ ሆስፒታል በተደረገለት ሕክምና የተረፈ ቢሆንም፣ የደረሰበት ድብደባ ከባድ በመሆኑ ለተጨማሪ ሕክምና ሪፈር የተደረገው ተማሪ ሙሉቀን፣ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሕክምና ላይ እያለ ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ሕይወቱ ማለፉ ታውቋል፡፡ ፖሊስ በድብደባው ተሳትፈዋል በማለት በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ተጠርጣሪ የዩኒቨርሲቲውን የጥበቃ ሠራተኞችን ፍርድ ቤት አቅርቦ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመጠየቅ በምርምራ ላይ መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡





