Category Archives: Social and Culture

ይድረስ ለአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ለኢህአዴግ አመራሮች!

ብስራት ወልደሚካኤል

afrosonb@gmail.com

 Image

በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬ በያላችሁበት ይድረሳችሁ፤ ምንም እንኳ እናንተ ብዙውን ሰላም እየነሳችሁ ብታስቸግሩም፡፡ ዛሬ ግን እስኪ በእናንተ እና በቤተሰባችሁ ላይ እንዳይፈፀም የምትፈልጉትን በሌላው ላይ ስላደረጋችሁት ከብዙው አንዲት እውነት ብቻ አንስቼ ልጠይቃችሁ ወደድሁ፡፡ የጥያቄው መልስ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለህሊናችሁ፣ እናንተ በምትመሩት አስከፊ፣ አፋኝ እና ጨቋኝ ስርዓት ሰለባ ለሆኑ እንዲሁም አሁንም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተለመደውን እኩይ ተግባር ለምትፈፅሙባቸውና ለቤተሰቦቻችሁ ይሆን ዘንድም አበክሬ እጠይቃለሁ፡፡

ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እርስዎ ተወልደው ባደጉበት የደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ቦለሶ ሶሬ ወረዳ መዲና በሆነችው አረካ ከተማን መቼም የሚረሷት አይመስለኝም፡፡ እርስዎ አሁን የደረሱበት የይምሰልም ይሁን ተግባር የጠቅላይሚኒስትርነት በትረ ስልጣን ከመጨበጦ በፊት እዛው አረካ ከተማ አካባቢ እንደ አብዛኛው የሀገራችን ህዝብ በግብርና እርሻ ሙያ ዕየተዳደሩ ነው እንበል፡፡ ታዲያ በዚህ ሙያ ሳሉ ልክ አሁን እንዳሉት ባለትዳር እና የ3 ልጆች አባት ሆነው፤ እርስዎ በሚመሩት ኢህአዴግም ይሁን 24 ሰዓት በምትኮንኑት ደርግ ስርዓት አርዓያ “ሞዴል” አርሶ አደር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተብለው የትውልደ ቀዬዎትን ወክለው በደቡብ ክልል መንግስት ቢሸለሙ ምን ይሰማዎታል? ያው ደስታ እንደሚሉኝ አልጠራጠርም፡፡

አለበለዚያም ገበሬ ሆኜ አላውቅም ካሉም፤ ያኔ አርባምንጭ የውሃ ቴክኖሎጂ ተቋም (የአሁኑ አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተመረቁበት ሲቪል ምህንድስና(Civil Engineering) አሊያም ከፊንላንድ በተመረቁበት የአካባቢ ንፅህና ምህንድስና(Sanitory Enegineering) እስተማሩና እያስተዳደሩ ሞዴል መምህር ተብለው በወቅቱ ገዥ ስርዓት ቁንጮዎች ቢሸለሙ ምን ይሰማዎታል? አሁንም ያው ደስታ ነው እንጂ ሀዘን ሊሉኝ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ማንም ሰው በሙያው ጥሮ ግሮ ላበረከተው አስተዋፅዖ እና ለሌሎች መልካም አርዓያ በመሆኑ የሚጠላ አይኖርምና፡፡ ይሄንን ምሳሌ ለራስዎ መቀበል ካልቻሉም ከቤተሰብዎ እጅግ መልካም ነው ብለው አብልጠው የሚወዱት ወንድምዎ ካሉም በእርስዎ ምትክ እርሳቸውን ተክተው እርስዎን በታዛቢነት ያስቀምጡ፤ ስሜቶንም ያሰላሱ፣ ይግለፁ፡፡

በሙያዎ  ለብዙ ዓመታት ሰርተው ለሌሎች አርዓያ ተብለው ሽልማት፣ እውቅና እና ሙገሳ ከተሽጎደጎደልዎ 3 ወር ሳይሞላ፤ ከትዳር አጋርዎ ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ እና የበኩር ልጅዎን ተማሪ ዮሐና ኃይለማርያምን ጨምረው ከሌሎች ልጆቾ ጋር አምላኬ በሰላም አሳድረኝ ብለው ተቃቅፈው ተኝተው በሸለሞት አካል አሸባሪ ተብለው ሌሊት በቤትዎና በቤተሰብዎ ላይ በ 16 “የፀረ-ሽብር” ግብረ ኃይል የጥይት እሩመታ ሲሰሙስ ምን ይሰማዎታል? አሁን ልክ እንደቅድሙ ደስታ ሊሉኝ አይችሉም፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ እርስዎን በቤተሰብዎ ፊት በሸለሞት አካል በ 16 ግብረ ኃይል ሽፍታ ነው ተብለው በክብር አርፈው ከተኙበት ቤት በሚተኮሱ የጥይት ናዳዎች በቤተሰብዎ ፊት ህይወትዎ እስከወዲያኛው ቢያልፍ እና እንደው ግማሽ ነብስ የለም እንጂ በከፊል ድርጊቱን ቢታዘቡት ምን ይላሉ; ከእርስዎ በተጨማሪ ለፍተው ጥረው ግረው ያቆሟት ቤት፣ ያፈሯቸው ላሞች ፣በጎችና በሬዎች በማያውቁት ነገር የጥይት ናዳ ሲያርፍባቸውስ;

ከላይ በተጠቀሱት ሳያበቃ ግብረ ኃይሉ አሁን የሰው ህክምና ሳይንስ የምታጠናው የበኩር ልጅዎ ተማሪ ዮሐና ሌሊቱን ገና በ8 ዓመቷ ከእቅፎ ተኝታ እርስዎ ሲገደሉ እርሷ የምትፅፍበት፣ አሊያም በትርፍ ጊዜዋ ከብቶች የምታግድበት ወይንም እንደሌሎች ህፃናት ከአቻዎቿ ጋር ለመጫወት የምትጠቀምበት የቀኝ እጇ ሙሉ ለሙሉ በጥይት ቢቆረጥስ ምን ይሰማዎታል? በዚህም ደስታ እንደማይሉኝ ግልፅ ነው፡፡ ልክ በውጊያ አውድማ እንዳለ ወታደር ከወላጆቿ እቅፍ ሳለች ቀኝ እጇ የተቆረጠችው ልጅ ስታድግስ ምን ይሰማት ይሆን? ፍርዱን ህሊና ላለው ሁሉ ልተወው፡፡

 ልክ እንደ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሌሎች የኢህአዴግ አመራሮች እና አባላት ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ቢፈፀም ምን ይሰማችኋል; እናንተም ደስታ እንደማትሉኝ አልጠራጠርም፡፡ ይህንን ሁሉ የጠቀስኩት በማንም የሰው ሰብኣዊ የሰው ልጅ ላይ እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ድርጊት እንዲፈፀም ፈልጌ አይደለም፤ ይሄንንም አቶ ኃይለማርያምም ሆኑ ሌሎች ግብር አበሮእዎ በቅን ልቦና እንድትረዱልኝ እሻለሁ፡፡

ክቡርነትዎ፤ ከላይ ብእርስዎ የጠቀስኩት ምሳሌ በሌላ ኢትዮጵያዊ ላይ በእናንተ ስርዓት አመራር የተፈፀመ እውነተኛ ድርጊት መሆኑንን ከዚህ እንደሚከተለው በአጭሩ ልነግሮት እወዳለሁ፡፡Image

ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ አረቦር ቀበሌ ልዩ ቦታው ደቀፉቀር በሚባል ስፍራ  ከሌሊቱ 12 ሰዓት ከነ መላው ቤተሰቦቻቸው አምላኬ በሰላም አሳድረኝ ብለው የተኙ፤በእነ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስርዓት ሞዴል አርሶ አድር ተብለው የተሸለሙ ታታሪ ገበሬ አቶ ማስረሻ ጥላሁን  በ 16 የፀረ ሽብር ግብረኃይል በተተኮሱ የጥይት ናዳዎች እዛው እቤታቸው ህይወታቸው አልፏል፡፡ የሚያሳዝነው ለግድያ የተላከው ግብረ ኃይል አቶ ማስረሻን ከገደሉ በኋላም በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ተከታታይ የጥይት ናዳ በማውረድ ቤታቸውን የጥይት ጌጥ ሲያደርጉት ጥረው ግረው ያፈሯቸው ከብቶችንም ከመግደል እና ከማቁሰል አልቦዘኑም ነበር፡፡ የሚገርመው እንዴት የአንድ ሰው መኖሪያ ቤት የቀድሞ የአድዋ ወይም ባድመ፣…የውጊያ ስፍራ ሊመስል እንደቻለ ግልፅ አይደለም፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ እጅግ የሚዘገንነው እና የሚያሳዝነው በተመሳሳይ ሰዓት የአቶ ማስረሻ ጥላሁን የ 8 ዓመት ልጅ ስለእናት ማስረሻ እዛው በሞት ከተነጠቀው ወላጅ አባቷ እና በፀረ ሽብር ግብረኃይል ከተሸበሩ ምስኪን ቤተሰቦቿ እቅፍ ሆና ሲነጋ ጥቅምት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ከአቻዎቿ ጋር ትምህርት ቤት ስለመሄድ እና ስለመጫወት ስታልም ብዙ ስራዎችን የምትሰራበት ቀኝ እጇ በግብረ ኃይሉ ጥይት ሙሉ ለሙሉ ተቆርጧል፡፡

አቶ ኃይለማርያም በእርስዎ እና በግብር አበርዎ የሚመራው ኢህአዴግ ሞዴል አርሶ አደር ያላችኋቸውን አቶ ማስረሻ ጥላሁንን በ 16 “የፀረ ሽብር” ግብረ ኃይል ለማስገደል በወረዳውና በዞኑ አመራሮች ሽፍታ ነው የሚል ለባለቤታቸውና በህይወት ለተረፉ ልጆቻቸው መልስ ተሰጥቶ ፍትህ እንጦርጦስ ገብቷል፤ ቀድሞም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአዴግ እስካለ ፍትህ እና ርትዕ ከማግኘት ሰማይ ቤት ደርሶ መመለስ የቀለለ ይመስል ሰው ተስፋ ቢቆርጥም፤ ለወጉም ቢሆን ፍርድ ቤት መኳተኑ አልቀረም፡፡ ነገር ግን እሮጣ ያልጠገበች፣ክፉና ደጉን የማታውቅና ቂም በቀል የሌለባት፣ ዓለማችንንም ይሁን ሀገራችንን ኸረ እንደውም አካባቢዋን በቅጡ ለይታ የማታውቅ የ 8 ዓመቷ ህፃን ስለእናት ማስረሻ ጥላሁንን ምን ብላችሁ ይን እጇ እንዲቆረጥ የተደረገው? ነው ወይስ ይህቺን ህፃንም ሽፍታ ነች ልትሉን ነው? ኸ…ረ…ረ..የፍትህ ያለህ፣…የህፃን ልጅ ያለህ፣…ቢያንስ ሰብዓዊነት እንኳ እንዴት ይሳናችኋል?

እስኪ አቶ ኃይለማርያም ስለእናት ማስረሻ ላይ የተፈፀመው በእርስዎ የበኩር ልጅ ዮሐና ኃይለማርያም ላይ ቢፈፀም ምን ይሰማዎታል; ስለ እናንተ ልጆች እንደምታስቡ ሁሉ ስለሌሎች ህፃናት ያላችሁ አስተሳሰብና አመለካከት ወይም ግንዛቤ የት ድረስ ነው? ዛሬ በዚህ ግፈኛ ስርዓት ቀኝ እጇ የተቆረጠው ስለእናት ማስረሻ ነገ እንደማንኛውም ልጅ አራሷን፣ ቤተሰቧን፣ ሀገሯን ብሎም የዓለምን ማኀበረሰብ ልታገለግል ምትችል፣ ብዙ ተስፋ የሰነቀች ነች፡፡

አሁን ግን ገና የ !ኛ ክፍል ትምህርቷን  በጀመረች አንድ ወር ከአስር ቀን የመመህሮቿን የፊደል አጣጣል ትዕዛዝ የምትቀበልበት ቀኝ እጇ ገና ከጅምሩ ተቆርጧል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰኞ ማክሰኞ እያለች ትምህርቷን መከታተል ሲገባት ፍትህ አጥታ ከምትኖርበት ዳባት ወረዳ፣ ሰሜን ጎንደር ዞን ከዚያም የአማራ ክልል ፍትህ ፅፈት ቤት እስከ ህፃናት ጉዳይ በጥይት ናዳዎች ከተረፉ ቤተሰቦቿ ጋር ፍትህን ፍለጋ እየተንከራተተች ትገኛለች፡፡

በአንፃሩ ደግሞ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ልጅ ዮሐና ኃይለማርያም በተደላደለ ሰላም፣ ጤናና እና ሁኔታ የህክምና ትምህርት ትከታተላለች፣ የብአዴኑ ሊቀመንበር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ልጆችም የተሸለ ትምህርት ቤት ከዚሁ ደህ ህዝብ በሚገኝ ገንዘብ ይማራሉ፣ የአቶ በረከት ስምዖንን ፣ የዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ የአቶ ሙክታር ከድር፣ የነ ሀሰን ሽፋ፣ የነ ጌታቸው አሰፋ ፣ የነ አያሌው ጎበዜ፣ የነ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የነ ግዛቱ አብዩ እና የሌሎች የኢህአዴግ ሹማምንት ልጆች በህዝብ ሃብት ተንደላቀው በተመቻቸ ሁኔታ ይማራሉ፡፡  የዳባት ወረዳ ነዋሪዋ ህፃን ስለ እናት ማስረሻ ደግሞ ለትምህርት ባልተመቻቸ ሁኑታ እንኳ የጀመረችውን ትምህርት እንዳትማር ቀወላጅ አባቷን በግፍ ከማጣቷ በተጨማሪ ቀኝ እጇን ተቆርጣ ፍትህን ፍለጋ ትኳትናለች፡፡

ታዲያ ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ሌሎች የኢህአዴግ ሹማምንት ሆይ፤ የምትመሩት ስርዓት በህፃናት ስም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ረብጣ ዶላሮችን እንደሚያገኝ የምትዘነጉት አይመስለኝም፡፡ ይሁን እንጂ በህፃናቱ ስም የሚመጣው እርዳታ ቢያንስ በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል ባይችል እንኳ ለምን አንዲትን ህፃን በፀረ-ሽብር ግብረኃይል በጥይት ለማስመታት ዋለ? በዚህች ህፃን ልጅ እና ወላጅ አባቷን ጨምሮ በቤተሰቦቿ ላይ የተፈፀመው ግፍ የት ድረስ ያስኬዳችኋል? ይህችን ደብዳቤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አቶ ኃለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ይህቺ ደብዳቤ ደረሳችሁ ሌሎች የኢህአዴግ አመራሮች ፤ ስለ ህፃናት ልጆቻችሁ፣ ስለ እናቶቻችሁ ፣ ስለሚስቶቻችሁ እና ስለራሳችሁ ብላችሁ የዚህቺን ህፃን እና ቤተሰቦች ጊዜ ሳትሰጡ ፍትህን ፍለጋ እየደከሙ ነውና ፍትህን ይሻሉ፡፡

እነ አቶ ኃለማርም ደሳለኝ የእውነት ከልብ አዝናችሁና እና ተሰነምቷችሁ ፍትህን መስጠት ከቻላችሁ የድርጊቱ ፈፃሚዎች  ብዙ በምታወሩበት ኢቴቪና  በሌሎች መድረኮች ሌሎች አመራሮችም ሆኑ ህዝብ እንዲማሩበት ጭምሩ ተገቢው ፍርድ በግልፅ በአደባባይ ሊሰጥ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ የሴቶች እና ህፃነት ጉዳይ ቢሮዎች፣ አቃቤ ህግ፣ ጠበቆች ፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ሌሎች የሚመለከታችሁ አካላት የድርሻችሁን ትወጡ ዘንድ ተግባሩ የት አለ? ስል መልሳችሁን በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

ታህሣሥ 2006 ዓ.ም.  ተፃፈ

አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

የድምፃዊት ሚካያ በኋሉ የቀብር ስነስርዓት ተፈፀመ

በአዲስ የሙዚቃ ስልት “ሸማመተው” በሚል የሙዚቃ አልበሟ ከህዝብ የተዋወቀችው ድምፃዊት ሚኪያ በኋሉ ባደረባት ህመም በህክምና ስትረዳ ቆይታ ትናንት ታህሳስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም. ሌሊት 36 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡ ድምፃዊቷ ወደ ሙዚቃው ኢንዱስትሪ ከመምጣቷ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ “በኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ስነ ፅሑፍ” በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቃ በስኩል ኦፍ ቱሞሮ እና በአዲስ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግላለች፡፡ Image

ድምፃዊቷ ኢትዮጵያን በመወከል በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው “ኮራ” የአፍሪካ ሙዚቃ ውድድር ላይ ደለለኝ ደለለኝ በሚል ዘፈኗ ተወዳድሯ ምርጥ ስድስት ውስጥ ገብታ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ ትናንት በሞት እስክትለይ ድረስም “በዶመስቲክ ካልቸር” ጥናት የማስተርስ ትምህርቷን የመመረቂያ ፅሑፍ እየሰራች እንደነበርም ታውቋል፡፡

የድምፃዊቷ የቀብር ስነስርዓትም ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ቤተሰቦቿ፣ ወዳጅ ዘመድ እና አድናቂዎቿ በተገኙበት በለቡ ቅዱስ ገብርኤል የቀብር ስነስርዓቷ ተፈፅሟል፡፡ ሚካያ በኃይሉ የአንዲት ሴት ልጅ እናት ነበረች፡፡ አዲስ ሚዲያም ለሚኪያ የነፍስ እረፍትን፤ለወዳጅ ቤተሰቦቿ እና አድናቂዎቿ መፅናናት ይመኛል፡፡

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የመንግስትን ማጭበርበር አጋለጡ

ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ዛሬ ጥቅምት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ከCPJ ፣ ከዶሃ ዓለም አቀፉ የሚዲያ ነፃነት ማዕከል እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ተወካዮች ጋር በአዲስ አበባ ኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተገናኝተው ተወያዩ፡፡ ጋዜጠኞቹ ለ3፡30 ሰዓት ያህል ስለኢትዮጵያ ሚዲያ አፈና፣ ስለጋዜጠኛች መከራ፣ እስርና ስቃይ እንዲሁም ስደት ከነነባራዊው ሁኔታ በዝርዝር ከነ ምክንያቱ ሰፊ ምክክር ተደርጓል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ትናንት ጥቅምት 29 ቀን 2006ዓ.ም በአፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተደረገው የአፍሪካ ሚዲያ ፎረም ላይ ነፃ ጋዜጠኞች እንዳልተጋበዙ እና የመንግስት ደጋፊዎች እንዲሳተፉ መደረጉን እንዲሁም ከነፃ ሚዲያ ከ3 ያልበለጡ በእንግሊዘኛ የሚዘጋጅ ሚዲያ አዘጋጆች በሌላ አካል እንዲሳተፉ መደረጉን፣ መንግስት ሚዲያውን ከማፈኑ በተጨማሪ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ፣ ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸውን ጨምሮ 6 ጋዜጠኖች ከጋዜጠኝነት ስራ ጋር በተያያዘ መታሰራቸው እና በተለያየ ጊዜም የተለያዩ ጋዜጠኞች እየታሰሩ እንደሚፈቱ ተጠቁሟል፡፡

በዚህም ዙሪያ በአፍሪካ ሚዲያ ፎረም ላይ ስለተጋበዙ ስለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እና ሚዲያ አፈና የተሳሳተ ዘገባ እንዳያቀርቡ እውነታውን ከ15 ያላነሱ ጋዜጠኞች አብራርተዋል፡፡ በዚህም ጋዜጠኖቹ የመንግስትን ማጭበርበር በማጋለጣቸው፤ ተወካዮቹ እውነታውን ለዓለሙ ማኀበረሰብ እነምደሚያቀርቡ እና ይህንንም በይበልጥ ለለጋስ ሀገሮች እንደሚያሳውቁ በማረጋገጥ ውይይቱ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎት የነ አቶ በቀለ ገርባን ይግባኝን እንደማያይ አስታወቀ -እነ አንዱዓለም አራጌም የፊታችን ሰኞ ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል

የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የኦፌኮ-መድረክ ምክትል ሊቀመንበር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ላይ እና የኦፌኮ ሌላው አመመራር ወጣት ኦልባና ሌሊሳ የጠየቁትን ይግባኝ ዛሬ ጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የህግ ስህተት የለውም በሚል ሰበር ሰሚ ችሎቱ ይግባኙን ውድቅ አድርጎታል፡፡ አቶ በቀለ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በፌደራሉ አቃቤ ህግ በተከሰሱበት የሽብር ወንጀል 8 ዓመት ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው ሲሆን ፤ ይህን በመቃወምፈደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቀው ነበር፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተወሰነውን የ8 ዓመት እስራት ወደ 3 ዓመት ከ7 ወር ዝቅ ማድረጉይታወቃል፡፡ አቶ ኦልባና ሌሊሳም በከፍተኛው ፍርድ ቤት 13 ዓመት ፅኑ እስራት የተፈረደባቸውን በይግባኝ ጠቅላይፍርድ ቤቱ ወደ 11 ዝቅ እንዲል አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ እነ አቶ በቀለ ገርባ የተከሰስነው በሐሰት የፈጠራወንጀል እንጂ ምንም የፈፀምነው ወንጀል ስለሌለ፤ አቃቤ ህግም በከሰሰን ወንጀል ያቀረበው ማስረጃ እርስ በርሱየሚጣረስ በመሆኑ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በነፃ ሊያሰናብተን ይገባል ሲሉ ይግባኝ ቢሉም ፤ሰበር ሰሚ ችሎቱ በዛሬውጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ውሎው የይግባኝ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

በተያያዘ ዜና የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አንዱዓለም አራጌ ፣ሌላው የፓርቲው ምክር ቤት አባል አቶ ናትናኤል መኮንን፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ እናሌሎች የአንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተወሰነባቸውንየጥፋተኝነት ውሳኔ በመቃወም ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብለዋል፡፡ በዚሁ መሰረት የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀኑ 8 ሰዓት 6 ኪሎ በሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀነ ቀጠሮ መሰጠቱንጠበቃው አቶ አበበ ጉታ አስታውቀዋል፡፡

ይህም ለነ አቶ አንዱዓለም ቀጠሮ የመጀመሪያው የሰበር ሰሚ ችሎት ቀነ ቀጠሮ መሆኑ ታውቋል፡፡ አቶ አንዱዓለምአራጌ በከፍተኛው እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕድሜ ልከል ፅኑ እስራት ሲፈረድበት ጋዜጠና እስክንድ ነጋ ደግሞ 18 ፅኑ እስራት ፍርድ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መፅናቱ ሲታወቅ የሌሎችም እንዲሁ መሆኑም አይዘነጋም፡፡

ስለ ዶክተር ኢንጂነር ቅጣው እጅጉ በጥቂቱ

የዶክተር ቅጣው እጅጉ አጭር የሕይወት ታሪክዶክተር ቅጣው እጅጉ የካቲት 16 ቀን 1940 (እ.ኢ.አ) ከአባታቸው ከአቶ እጅጉ ሃይሌ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ አስካለ በላይነህ በከፋ
ጠቅላይ ግዛት በቦንጋ ከተማ ተወለዱ። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቦንጋ፣ በዋከና በጅማ ከተማ ካጠናቀቁ በኃላበባህር ዳር በሚገኘው ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅየከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።
kitዶክተር ቅጣው ወደ ጃፓን አገር በመሄድ በኦሳካዪኒቨርስቲ በቋንቋና የጃፓን ኢኮኖሚ፣በሄሮሺማ ዩንቨርስቲ የኢንደስትሪ እናየአውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ አጥንተው ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። በኋላም አሜሪካን ሀገር ስኮላር ሺፕ አግኝተው በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ማስትሬታቸውን በመጨረሻም ለትምህርት ባላቸው ከፍተኛ ፍላጎት በኤሮ-ስፔስ ምህንድስና ዶክትሬታቸውን ተቀብለዋል።

ዶክተር ቅጣው በናሳ (NASA) በሲስተም መሃንዲስነትና በጠፈር ሳይንቲስትነት የሰሩ
ሲሆን ከሌሎች መሃንዲሶችና ሳይንትስቶች ጋር በመተባበር ለእኛ አለም (Planet Earth) እና
ለተቀሩት ፕላኔቶች የምርምር ሳይንስ (Planetary Science Research and Exploration) የሚረዱ የጠፈር መንኮራኩሮችና ሮኬቶች ፈጥረዋል።  ዶክተር ቅጣው በዚህ ከፈጣሪ በተቸሩት ታላቅ ችሎታና እውቅት ለዚህች ለምንኖርባት ዓለምና ሕዝብ ታላቅ አስተዋፅዎ አበርክትዋል። ከነዚህም ጥቂቱን ለመጥቀስ ለናሳ(NASA) ሁለት የኤሮ-ስፔስ መወርወሪያ ሜካኒዝም ለቦይንግ ኩባንያ ሲሙሌተር (Flight Dynamic Simulator) እና አድቫንስድ
ወይንም ኔክስት ጀነሬሽን (Advance or Next Generation) በመባል የሚታወቁትን
ግሎባል ፖዚሽን ሳተላይት ሲስተም(Global Positioning Satellite System)
ከፈለሰፉት ውስጥ አንደኛው ሰው እሳቸው ነበሩ ዶክተር ቅጣው Trans Tech International በመባል የሚታወቀውን ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ድርጅት በመመስረት የተለያዩ ሀገሮች የቴክኖሎጂ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ በአማካሪነት አገልገለዋል።
cabበተጨማሪም ለሀገራቸው በነበራቸው ታላቅ ፍቅር ‘የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ግንባር’ የተባለውን ድርጅት በመመስረት ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ሳይቆጥቡ ለኢትዮጵያ ሰላም ፣ ብልፅግናና አንድነት ትልቅ መስዋዕትነት የከፈሉ የትግል ሰው ነበሩ። በእውነትም ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ዓለም አንድ ትልቅ ሰው አጣች ቢባል ማጋነን አይሆንም። ዶክተር ቅጣው ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ስቴላ እጅጉ ጋር በመልካምና በደስታ ጋብቻ ተጣምረው ይኖሩ ነበር። ዶክተር ቅጣው፣ ቢንያም ያሬድ እና አቢጋኤል የተባሉ የሁለት ወንዶችና የአንድ ሴት አባት ነበሩ።

ዶክተር ቅጣው እጅጉ ወደ ኦስትን ቴክሳስ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ መጥተው ድንገት
በደርሰባቸው ሕመም ምክንያት በታማኝነትና በመሰጠት ሲያገለገሉትና ዘወትር ሊያዩት
ወደሚናፍቁት ጌታቸው እየሱስ ክርስቶስ በጃንዋሪ 12 ቀን 2006 በ58 አመታቸው ተሰብስበዋል።

kitawዶክተር ቅጣው እጅጉ በመልካም ባህሪያቸው የተወደዱ፣ በትህትናቸው የተመሰገኑ፣ በስራቸው የተደነቁ፣ በራዕያቸው ብዙ ተከታዮችን ያፈሩ፣ የብዙዎቻችን ተስፋና አርዓያ እንዲሁም የሀገር ኩራት የሆኑ ታላቅ ሰው ነበሩ። ዶክተር ቅጣውባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን አፍቃሪ፣ ዘመድ ወዳጅ አክባሪ እና ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን ፈሪ ነበሩ።