“ክርስትና ዘውድ ሰጣቸው፥ ክርስትና ነጠቃቸው” ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
ያሬድ ሹመቴ
በምስጋናው ታደሰ የተደረሰውን “ሚካኤል ንጉሰ ወሎ ወትግሬ” የተሰኘውን አዲስ መጽሐፍ ለመመረቅ ጥቅምት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በደሴ አይጠየፍ አዳራሽ የተገኙ ምሁራን ማራኪ ሀሳቦቻቸውን በመድረኩ አቅርበዋል። ከአቅራቢዎቹ መሀል ለዛሬ የዶክተር ዳኛቸውን ውብ ገለፃ ለንባብ እንዲመች አድርጌ በማቀናበር እነሆ በዝርዝር አቅርቤላችኋለሁ።(ያሬድ ሹመቴ)
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ “እንግዲህ ንግግሬን የምጀምረው እንደ ጥሩ “ወሎዬ” በግጥም ነው። ገጣሚ ስላልሆኩ የኔን ሀሳብ የሚገልጸውን የቀኝ አዝማች ምስጋናው አዱኛን የተወሰነ ስንኝ ተውሼ ልጀምር።
‘በጣሙን ጨነቀኝ ልቤ ተበትኖ፥
እንጀራዬ ሸዋ ቤቴ ጎንደር ሁኖ።’
የዚህ ስንኝ መንፈስ የኔን አመለካከት ይገልጽልኛል ብዬ ስለማምን የሳቸውን ትከሻ ተንተርሼ እጀምራለሁ።
‘በጣሙን ጨነቀኝ ልቤ ተበትኖ፥
ውሎዬ ሸዋ ላይ ልቤ ወሎ ሁኖ።’
ብዬ እጀምራለሁ።
አልፎ አልፎ ከምስጋናው ጋር ስለዚህ መጽሐፍ በስልክ ስናወራ እኔ “ራስ ማይክ” ብዬ ስጠራው እሱ ደግሞ “የሰገሌው” ብሎ ይጠራኛል። ሁለቱም ምክንያት አላቸው። እሱ ስለ ራስ (የኃላው) ንጉስ ሚካኤል ስለጻፈ፥ ራስ ገብረየስ የተባሉ የኔ ቅድመ አያት ከዚች ቦታ [አይጠየፍ] ተነስተው ከራስ ሚካኤል ጋር አብረው ሰገሌ ዘምተው [በኃላ በራስ ካሳ ስር እስረኛ ሁነው ቢመለሱም] ወሎየነቴ ሰገሌን ያልፋል ለማለት ነው እንጂ እንዲያው በዚህ ሳልፍ እግረ መንገዴን ወሎዬ ነኝ አላልኩም ለማለት ነው።
ወሎዬ ነኝ ስል፥ አደራችሁን፥ ሰሜን ወሎ ነኝ አላልኩም። ደቡብ ወሎ አላልኩም። አርጎባም አላልኩም። ከሚሴ ነኝም አላልኩም። ሚሌም ነኝ አላልኩም። በደፈናው ወሎዬ ነኝ ነው ያልኩት።
እንግዲህ እንጀምር፡-
ትልቁ የጀርመን ፈላስፋ ሄግል አንድ ቦታ ላይ ስለ ታሪክ እንዲህ ይላል። ‘አፍሪካ በደፈናው ታሪክ የላትም። ይህንንም ስል ምክንያቴ ስለማትጽፍ ነው’ ይላል። በሱ አነጋገር ‘እንዲያውም ትንሽ ታሪክ ላይ የደረሱት አረቦቹ ናቸው። እነሱ ይጽፋሉና’ ይላል። እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደምንጽፍ ሄግል አያውቅም። የምስጋናው መጽሐፍ ለዚህ መልሱ ነው። የንጉስ ሚካኤልና የወሎ ታሪክ ባይፃፍ ኖሮ ተረት ተረት ሆኖ ነበር የሚቀረው።
ሁላችንም ቤት ውስጥ [ይህ ታሪክ] የአፍ ብቻ ታሪክ ሆኖ ተቀምጦ ኖሯል። “ካልተጻፈ ታሪክ የለም።” መጻፍ መዘገብ ካልቻለ በአፍ ያለው ጠፍቶ ተረት ተረት ሆኖ ይቀራል። ታሪክ ከጽሁፍ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ መፃፍ አለበት። ለዚህ ደግሞ ምስጋናው ተገቢ መልስ በመስጠቱ ባለውለታችን ነው የሚል እምነት አለኝ።
ሌላው ከክርስቶስ ልደት 600 ዓመት በፊት የነበረው ታላቁ ግሪካዊው የታሪክ ቀመር መስራች ሱሲዲየስ ምን ይላል? ‘ታሪክን ለመፃፍ የሚነሳ ሰው ቢያንስ ቢያንስ አርባ አመት ቢሞላው ይመረጣል’ ይላል። ‘ፀሀፊው እድሜው የጠና ካልሆነ እንዲሁ የሆነውን ያልሆነውን እየጻፈ ህዝብ ያበጣብጣል።’ ሲል ያክላል።
በአንድ በኩል እውነቱን ነው። ባለፉት ከ25 እስከ 30 ዓመታት ውስጥ የወጡትን “የታሪክ ድርሳናት” ስንመለከት መርዶ አቅራቢዎች ናቸው። ‘በእንዲህ ያለ ጊዜ እንዲህ እና እንዲያ ተደርገሀል፥ በእንዲህ ያለ ቦታ እንዲህ ተደርጎብሀል’ እየተባለ ይፃፋል። ታሪክ የተወሳሰበ ዲሲፕሊን ነው። ከመርዶ ነገራ በእጥፉ ይለያል።
በተጨማሪም ታሪክ ከመርዶ ነገራ አልፎ የርዕዮተ ዓለም እና የፖለቲካ አሽከር በሚሆንበት ጊዜ ብዙ ጣጣ ይመጣል። ርዕዮተ አለሙ ይቀድምና ታሪክ የበታችነትን ቦታ ትይዛለች። ይሄን ልጅ (ምስጋናው) ከዚህ አንፃር ስናየው 40 ዓመት ገና አልሞላውም። እንዲያውም አንድ ሰው ለአንድ ጓደኛዬ ’40 አመት ያልሞላው ሰው ታሪክ መፃፍ የለበትም ብሏል ዳኛቸው። እድሜው ያልደረሰውን ምስጋናው የፃፈውን መጽሀፍ ለመመረቅ ለምን ሄደ?’ ብሎ ጠይቋል። ስለ ታሪክ አረዳድ፥ ስለታሪክ ምርምር እና ስለ ታሪክ ትንተና እስከ ከፍተኛ ትምህርት ደርሶ የተማረው ምስጋናው፥ ትምህርቱ ባበረከተለት እውቀት የእድሜውን ማነስ ተሻግሮታል ብዬ አምናለው። እውቀት የእድሜን ክፍተት ይሞላልና።
የዚህ መጽሀፍ ንባብ ሲጀመር ገና ከጠዋቱ ጥያቄዎች ተጀምረዋል። አንዱ ‘የኔን አያት በደንብ አልፃፋቸውም’ ሲል ሌላው ደግሞ ‘የኔ ቅድም አያት ሊቀ መኳስ እከሌን አሳንሶ ጽፏቸዋል’ [እንዲህ እንዲያ] ወዘተርፈ ይላል። ለዚህ ደግሞ አጭሩ መልስ፥ የታሪክ ጸሀፊ ሊዘግበው በተነሳው ርዕስ ዙሪያ ሁሉንም ምንም ሳይተው አጠቃላይ ዘገባ ማቅረብ በፍፁም አይቻለውም። በመሆኑም የታሪክ ዘገባ የሚከናወነው ወሳኝ የሚላቸውን ጉዳዮች በመምረጥ እንጂ ሁሉንም በማካተት ሊፃፍ አይችልም።
[ሌላው ጉዳይ] ታሪክን ከአንድ ከማይላወስ እና ከማይነቃነቅ መድረክ ላይ ሆነን የምንረዳው እውነታ አይደለም። ታሪክ ምን ግዜም ተለዋዋጭ እና ፈሳሽ መሆኑን ማጤን ተገቢ ነው። ለምሳሌ የመንግስቱ ነዋይን ግርግር ደርግ ከመምጣቱ በፊት ያጠና ሰው የወታደር መፈንቅለ መንግስትን የሚያይበት አተያይ አለው። ከነመንግስቱ ነዋይ በኋላ የወታደር መንግስት 17 ዓመት በስልጣንከቆየ በኋል የመንግስቱ ነዋይን ታሪክ የሚያጠና ሰው አተያዩ በጭራሽ እንደ መጀመሪያው አይሆንም። ስለዚህ ታሪክን ከተለዋዋጭነቱ ሁኔታ አንጻር ማየት የግድ ይላል።
በሌላ መልኩ ደግሞ ዋናው የቀደመ ታሪክን ለመረዳት፥ የጀርመን ፈላስፋዎች እንደሚሉት አሁን ባለንበት በኛ ዘመን እና ባለፈው ዘመን መካከል የአተያይ አድማሳት ዑደትን ማግኘት ተገቢ ነው። (fusion of horizon)በመሆኑም 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን 19ኛውን ክፍለ ዘመን ለመረዳት ሀሳባችንን መንፈስና ቀልባችንን ወደ ዘመኑ መላክ ተገቢ ነው። ያለፈውን እሴት ወግ እና መቼት በሚገባ ካላጠናን፥ የኛን ዘመን የአመለካከት ዘይቤ ብቻ ይዘን ያንኛውን ዘመን ልንረዳው አንችልም። በመንፈስ ልናጠናው ወደ ፈለግነው ዘመን እስካልተጠጋን ድረስ ያ ዘመን ለኛ ምን ግዜም ባይተዋር ሆኖ ይቀጥላል።
ከዚህ አኳያ ስንመለከት የምስጋናው ታደሰ መጽሐፍ ከመቶ አመታት በፊት የተካሄደውን የታሪክ ሂደት ከውጭ ሆኖ ሳይሆን በጊዜው እንዴት ያስቡ እንደ ነበርና የአመለካከት አድማሳቸውን በተገቢ አውድ በማስቀመጥ አቅርቦታል።
ወደ ሌላ ነጥብ ስናልፍ፥ ስለ መሪዎቻችን በምናወሳበት ጊዜ በአንድ ወጥ ትረካ መሪዎቹን አናገኛቸውም። እንደ ምሳሌም መምህር አለማየሁ ሞገስ ‘መልክዓ ኢትዮጵያ’ ላይ ከሰበሰቧቸው ስነ ቃሎች መሀል አፄ ቴውድሮስ ሲሞቱ የተገጠመላቸውን ሙሾ ላንሳላችሁ።
“ከመላክ ከሰይጣን እግዜር የሰራው…
….ቆንጥረው ቆንጥረው ሁሉን ያካበቱ
የመጨረሻው ቀን ግስላ ሆኑና ታነቁና ሞቱ’
‘ቆንጥረው ቆንጥረው ሁሉን ያካበቱ’ የሚለውን ያዙልኝ።
ሁሉም መሪዎቻችን ቆንጥረው ቆንጥረው ሁሉን ያካበቱ ናቸውና። በአንድ ቁንጠራ አንፍረዳቸው። ሚካኤል ስንል የዓድዋውን ሚካኤል ማስታወስ ሊኖርብን ይገባል። ሚካኤል ስንል ይህንን ወሎ የተባለውን ሀገር ያቆሙልንን ልናወሳ ይገባል። ሚካኤል ስንል ደግሞም ከአፄ ዮሀንስ ጋር ሆነው በኃይማኖት ጉዳይ ችግር የፈጠሩትን ልናነሳ እንችላለን። ይሄንን መቀበል ይኖርብናል። አንዷን ብቻ ይዘን ሚካኤል ይሄ ነው ለማለት በጣም አስቸጋሪ ይሆንብናል።
አፄ ቴውድሮስ ቆንጥረው ቆንጥረው ሁሉን ያካበቱ እንደተባሉት ማለት ነው። እዚህ መሀል ጎንደሬዎች ካላችሁ እንዳትቀየሙ። ስለሳቸው ከጀግንነት ውጪ ያወራ ሰው ሊሰዋ ይችላል ተብሏል አሉ። (ከፍተኛ ሳቅ)
ወደ ሌላ ወሳኝ ጉዳይ ስናመራ፥ ከወሎ ባህል ያፈነገጠውን ሙስሊሞችን ክርስቲያን የማድረግ ዘመቻ – የአፄ ዮሐንስ ፖሊሲን እናገኛለን። ምስጋናው በመጽሀፉ ምንም የደበቀው ነገር የለም። እንዲያውም ‘አራት እና አምስት አመታት ለወሎ ሙስሊሞች የጭንቅ አመታት ነበሩ’ ይላል። ትልልቅ ሸሆች ተጋድለው መስዋዕትነት መክፈላቸውንም ይተነትናል።
እኔ ንጉስ ሚካኤል ከአፄ ዮሐንስ ጋር አብረው ስህተት ሰርተዋል ነው የምለው። በወሎ ሙስሊሞች ላይ ትልቅ ጫና እና ሰቆቃ ደርሶባቸዋል። ከፊሉ ለስደት ሲዳረግ ከፊሉ ተቃውሞ ጀሀድ አውጆ ለሀይማኖቱ ተጋድሎ ተሰውቷል። ቀሪው ደግሞ ክርስትናን የተቀበለ መስሎ ህይወቱን አትርፏል። ምንም የሚያስደብቅ ነገር የለም። መሪዎች በሁሉ ነገር ልክ ናቸው ማለት አንችልም።
በምስጋናው መጽሐፍ ውስጥ ሙስሊሞቹ በጉልበት እንዲጠመቁና የክርስቲያን ስጋ እንዲመገቡ ሲገደዱ ቅሬታቸውን በሚያንፀባርቅ ስነ ቃል ስሜታቸውን ገልፀዋል እንዲህ ሲሉ ገልፀዋል።
“ታላቅ ታናሽ በላን ከርካ አደባባይ
አለ ልብ ስጋ ይጣፍጣል ወይ”
እንደዚሁም ሸህ ሁሴን ጅብሪል፡-
“ለጥቂት ቀን ብዬ አልበላም ነጃሳ
ወንዝ ለወንዝ ሄጄ እበላለሁ አሳ″
በሌላ በኩል ደግሞ ‘ሰው ያላመነበትን እንዲቀበል ማስገደል ልክ አይደልም’ ሲሉ ሊቁ ክርስቲያን መምህር አካለ ወልድ ይህን ዘመቻ አለመውደዳቸውን ገልፀዋል።
ይህ ሁሉ መዓት ከወሎ ህዝብ ከራሱ የመጣ አለመሆኑንም ማረጋገጥ ከፈለግን፥ አፄ ዮሐንስ አልፈው አፄ ምኒልክ ሲነግሱ፥ የክርስትና ሀይማኖትን በኃይል የመጫን ፖሊሲ ሲያበቃ፥ በወሎ ሙስሊም እና ክርስቲያን መሀል የነበረው የቀደመ ፍቅር መልሶ ቀጥሏል።
ንጉስ ሚካኤልን በኃይማኖት ጉዳይ የነበራቸውን ክፉ ጥላ ትንሽ ይቅር ለማለት የምንችለው የአፄ ዮሐንስ ስርዓት ሲያከትም ይኸው ተግባርም በዚያው በማክተሙ ነው። እንዲያውም ልጃቸው አቤቶ እያሱ ኢትዮጵያን የማስተዳደር ስልጣን ሲያገኙ፥ “ሙስሊምና ክርስቲያኑ እኩል ሊታይ ይገባል” ባሉ ጊዜ ንጉስ ሚካኤል አልተቃወሟቸውም ። ይሄ እሳቸውን ትንሽ ይቅር ለማለት ያስችለናል።
ከማመዶቹ ስርዐት ጋር ተፋልመው ከአፄ ዮሐንስ እና አፄ ምኒልክ ዘመን ጋር ተፋልመው ወሎ የፖለቲካ ወሳኝ ማዕከልነትን ቦታ እንድትይዝ ሲያደርጓት ደግሞ ታያላችሁ። አፄ ምኒልክ እንዳረፉ የአቤቶ እያሱን አልጋ ወራሽነት ፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ሲያውጁ ‘ሸዋ ተስማምቷል፥ ወሎ ተስማምቷል’ ብለው ነው የሚጀምሩት። ይህ አዋጅ ከአጀማመሩ የወሎን የፖለቲካ ማዕከላዊነት ያሳያል። በነገራችን ላይ አሁን በያዝነው ዘመን ሸዋ ተስማማ ወሎ ተስማማ ምንም ለውጥ ያለው አይመስለኝም። (ከፍተኛ ሳቅ) ነገሮች ተለዋውጠዋል።
ሌላው የኔ ልብ የሚመታው ሰገሌ ላይ ነው። ሰገሌን የሚመለከት ያለኝ ምክረ ሐሳብ (thesis) ፥ ንጉስ ሚካኤልን “ክርስትና ዘውድ ጫነላቸው በአንፃሩ ደግሞ የክርስትና እምነታቸው ዘውዳቸውን ነጠቃቸው” ነው እኔ የምለው። ክርስቲያን ባይሆኑ ኖሮ አይነግሱም ነበር። ደግሞ ደንበኛ አማኝ ክርስቲያን ባይሆኑ ኖሮ ሰገሌ ላይ አይሸነፉም ነበር። “የፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ደብዳቤ አታለላቸው” የሚለው የልጆች ተረት ተረት ነው ለኔ። መስቀል ተልኮ ትልልቅ ቀሳውስት አባቶች ካህናት ተልከው እንዴት እምቢ ይበሉ? አማኝ ናቸዋ።
እዚህ ላይ የኒኮሎ ማኪያቬሊን አስተምህሮት ማስታወስ ጠቃሚ ይሆናል። ለማኪያቬሊ ሁለት አይነት የሞራል አድማስ አለ። አንደኛው “የክርስቲያን ሀይማኖታዊ ‘ሞራሊቲ′ (ግብረ ገብ)” ይለዋል። ሁለተኛውን “ማህበረሰባዊ የፖለቲካ ሞራሊቲ″ ይለዋል። በመሆኑም ፖለቲካል አለም ውስጥ መጠቀም ያለብን የማህበረሰባዊ የፖለቲካ ሞራሊቲን እንጂ የክርስቲያን ሀይማኖታዊ ሞራሊቲ አይደለም” ይላል።
ለመሆኑ በሁለቱ የሞራሊቲ መርሆች መካከል ልዩነቱ ምንድን ነው?
ለማኪያቬሊ የክርስቲያን ስነ ምግባራት እንደ ርህራሄ፥ ለቃል መታመን፥ መሀላ፥ መማለድ እና ወዘተርፈ ሲሆኑ። በአንፃሩ የፖለቲካ ሞራሊቲ ማለት የወጠንከው ግቡ ላይ ለመድረስ ማናቸውንም አማራጮች የሞራል መስፈርት ጥሶ ያለ ገደብ መጠቀም ማለት ነው። ለምሳሌ፡- ሀይማኖትን እንደ መሸምገኛ መጠቀም፥ የማያከብሩትን ቃል መግባት፥ በውሸት መማል፥ ወዳጅነትን እንደ ማዘናጊያ ማቅረብ እና ወዘተርፈ።
ወደ ሰገሌ ስንመጣ ሸዋ የፖለቲካ ሞራሊቲ ይዞ መጣ። ወሎ የክርስቲያን ሞራሊቲ ይዞ ቀረበ። የምስጋናው መጽሐፍ እንደሚያስተምረን፥ ንጉስ ሚካኤል፥ ከሸዋ ቀድሞ የመጣውን የራስ ልዑል ሰገድን ጦር ቶራ መስክ ላይ ከደመሰሱ በኋላ ገስግሰው ወደ አዲስ አበባ ሳይገቡ ለምን እንደ ቀሩ እና የሸዋው ኃይል ከየጠቅላይ ግዛቱ ጦሩን እስኪያሰባስብ ድረስ ለምን ሰገሌ ላይ እንደቆዩ ብዙ ጊዜ የሚሰጠው መልስ የሚከተለው ነው።
“ፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ በተለመደው ብልሀታቸው ከንጉስ ሚካኤል ጋራ እንደሆኑ እና አቤቶ እያሱን እንዳልከዱ በመግለጽ ለጊዜው አሉበት ቦታ ሆነው እንዲቆዩላቸው መልዕክት ልከው ስላታለሏቸው ነው።” ይባላል። ይሔ ለኔ ተረት ተረት ነው።
የአሸናፊዎቹ ተረት ተረት የሆነው ደብዳቤ ተጽፏል ወይ? አዎ ተጽፏል። ግን ከልባቸው አምነው የተታለሉት ለመስቀሉ ነበር። የክርስትናን እውነታ ፀንተው ስለያዙ ተታለሉ። ‘ክርስቲያ አይዋሽም። ክርስቲያን ቃሉን ይጠብቃል’ ከሚል እምነታቸው ተነስተው ዘውድ የሰጣቸው ክርስትና በእምነታቸው ምክንያት ዘውዱን መልሶ ነጠቃቸው።
ንጉስ ሚካኤል በእመነታቸው ፀኑ። ሀብቴ አባ መላ ግን “መስቀልም አውጥተን ታቦትም አውጥተን ይሄን ሰው ማሸነፍ አለብን” አሉ። ይሄ ማለት ከላይ ለማሳየት እንደሞከርነው ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ የማኪያቬሊን የፖለቲካ ሞራሊቲ ይዘው ሲመጡ፥ እኚህ ደግሞ የክርስቲያን ሞራሊቲ ይዘው ስለቀረቡ ለኃብተ ጊዮርጊስ “ክርስቲያናዊ” ጥሪ ታምነው የፖለቲካዊ ሞራሊቲ ሰለባ ሆኑ።
ዕምነቱን እንደ መሰሪያ የተጠቀሙት ፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ብልህ ብልጥ ሲባሉ፥ በሀይማኖታቸው መርህ የፀኑት ንጉስ ሚካኤል ግን ገራገር ተባሉ። ይኸው እስካሁን ወሎ ገራገሩ እየተባለ ይዘፈናል። (ሳቅ) ወይ ሀብቴ አባ መላ… ይሄ መቼስ የሚገርም ነው። (ሳቅ)
በመጨረሻም፡-
አደራ እምለው፥ ከወሎ ባህል ያፈነገጠና አስከፊ የሆነው የእምነት ጫና እና ግፊት ህዝቡ ተሻግሮ እንዳለፈው ሁሉ፥ የወሎን ህብረ ብሔራዊነት ተፃፈ ከተባለው ህገ መንግስት እና ፌዴሬሽን በፊት በወሎ የኖረውን የሀይማኖት መደጋገፍ እና ተቻችሎ በፍቅር የመኖርን ባህል አንግሶ መቀጠል ይገባናል ስል ንግግሬን እጨርሳለሁ። አመሰግናለሁ።” (ታላቅ ጭብጨባ)
ዶክተር ዳኛቸው ጋር የቀረቡ ሌሎች ጥናቶችን በሌላ ጽሁፍ እመለስባቸዋለሁ። በእለቱ ከተሳታፊዎች ጥያቄዋች እና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
አንድ መንፈሳዊ አባት በንግግራቸው ንጉስ ሚካኤል በእምነታቸው ጥልቀት አማካኝነት መሸነፋቸው የሀይማኖት ሰማዕት እንዳደረጋቸው በመግለጽ ዘውትር ስመ ክርስትናቸውን በቤተ ክርስቲያን እየተነሳ ፀሎተ ፍትሀት ይደረግላቸዋል” ሲሉ የምሁሩን ሀሳብ አጠናክረዋል።
በተሳታፊዎች “ታሪክን ወደ ኋላ ሂዶ መዘገብ ስለምን በመንግስት በኩል አስፈሪ ሊሆን ቻለ?” የሚል እና የንጉስ ሚካኤልን ሀውልት ማቆም የተመለከቱ ጥያቄዋች ቀርቦ፥ ዶክተር ዳኛቸው ሲመልሱ “የንጉስ ሚካኤልን ሀውልት በሚመለከት፥ ሲታሰብ የሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ለሀይማኖታቸው ሲሉ የወደቁ ኢማሞች አሉና ለነሱም ሀውልት ሊቆም ይገባል። ምን አልባት በእስልምና ሀይማኖት ሀውልት የማይፈቀድ ከሆነ በስማቸው የጥናት ማዕከላት ሊገነቡ ይችላል። የራሳችን ታሪክ አካል ስለሆነ ተቻችለን ተሳስበን መዘከር ይገባናል።
ታሪኩ ለምን አልወረደም ላልሽው፥ እኔ እምልሽ ታሪክ በጣም ከባድ ነገር ነው። አንድ አንድ ጊዜ ታሪክ የፖለቲካ አሽከር የምትሆንበት ጊዜ አለ። የፖለቲካ ሀይሉ ጠምዝዞ ይመራዋል። በአፄ ኃይለ ስላሴ ጊዜ ስለ ልጅ እያሱ መፃፍ በጣም አስቸጋሪ ነበር። በደርግ ጊዜ ስለ አፄ ኃይለ ስላሴ መፃፍ አስቸጋሪ ነበር። አሁን ደግሞ አንድ አንድ ሁኔታዎች መፃፍ አስቸጋሪ ነው። ከዚህ አልተላቀቅንም።
እንዲያውም “ሀቅ ሀቁን ለህፃናት” የሚል የፕሮፖጋንዳ መጽሀፍ ተለቋል አሁን። እሚገርም ነው መቼም። አስቸጋሪ ነው። አረ ተመስገን ነው። አይጠየፍ ሁነን እንዲህ ያለ ውይይት ማድረጋችንም ተመስገን ነው። (በከፍተኛ ሳቅ እና ጭንጨባ ተቋጨ)
ምንጭ፡- ቋጠሮ ድረ-ገፅ
የኢትዮጵያ ድርቅና ርሃብ ትናንት እና ዛሬ
ብስራት ወልደሚካኤል
በርግጥ ድርቅ በተፈጥሮ ሊከሰት የሚችል የአየር መዛባት አደጋ ውጤት ነው፡፡ ድርቅ ባለፀጋም ሆነ እንደኛ ባሉ ደሃ ሀገራት ሊከሰት ይችላል፡፡ የድርቁ መንስኤም ተፈጥሯዊ አሊያም ሰው ሰራሽ ሊሆን ይችላል፡፡
ርሃብ በምግብ እጥረት የሚከሰት ሲሆን፤ መንስዔውም የምርት አቅርቦት ማነስ አሊያም የምግብ ፍላጎት ከምርት አቅርቦት ጋር አለመጣጣም ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ፍላጎት እና አቅርቦትን አሊያም የሀገር ምርት ለማሳደግ ሀገሪቱ የምትከተለው ፖሊሲ ትግበራ ውጤት ነው፡፡ በኢትዮጵያም በተለያዩ መንግሥታትም ሆነ ዘመን ድርግቅን ተከትሎም ይሁን ያለድርቅ ለተከሰቱት እና እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች ዋነኛ መንስዔው ፖለቲካዊ የፖሊሲ ትግበራ ውጤት ነው፡፡
ርሃብ በተፈጥሮ የሚከሰት ሳይሆን የሀገሪቱ መንግሥት ስርዓት በሚከተለው የፖሊሲ ንድፍና ትግበራ ውጤት ነው፡፡ ደካማ ወይም ተፈጥሮንና የሀገሪቱን ህዝብ አቅምና ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ፖሊሲ ትግበራ ባለበት ሀገር ድርቅ ከተከሰተ ምንጊዜም ርሃብ አለ፡፡ ርሃቡ ምንም እንኳ ድርቅን ተከትሎ የመጣ ቢሆንም ዋነኛ ምክንያቱ ግን የፖሊሲ ንድፍና ትግበራ ውጤት ነው፡፡
በሀገራችን በተከታታይ የተከሰተውም ርሃብ ዋነኛ ምክንያት ድርቁ ሳይሆን የደካማ ፖሊሲ ውጤት ነው፡፡ ምክንያቱም ድርቅ የተከሰተባቸው ሀገሮች ሁሉ ርሃብ አይከሰትም፡፡ ደካማ ፖሊሲ ያለባቸው ሀገሮች ግን ድርቅ ካለ ምንም ጊዜም ርሃብ አለና፡፡
በዘመናዊ ኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ጎልቶ መታወቅ የጀመረው በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመን ቢሆንም እስከዛሬም ይህን ችግር የሚቀርፍ የመንግሥት ፖሊሲና ተግባር አልታየም፡፡ አሳዛኙ ነገር በዘመነ ዳግማዊ ምኒልክ የነበረውን ርሃብ ለዓለም ማኀበረሰብ አሳውቆ ተገቢውን ርዳታ ይቆ ለተጎጂዎች በማድረስ ህይወት ለማትረፍ ቴክኖሎጂው ችግር ነበረብን፡፡ ቢሆንም ግን ይህን ክፍተት ንጉሱን ጨምሮ ባለሟሎቹ (አመራሮቹ) የተፈጠረውን ርሃብ በድርቅ ላይ ሳያመሃኙ ወዲያው ለህዝቡ በማሳወቅ ወገን ለወገን በሚችለው አቅም እንዲረዳዳ እና የመንግሥት ካዝና (ለችግር ጊዜ የተቀመጠ የእህል ጎተራ) ሳይቀር በይፋ ተከፍቶ ለተጎጂዎች ወዲያው እንዲደርስ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ይህ በጎ አስተሳሰብ ቢሆንም ከነበረው የእህል ክምችት አናሳነት እና የትራንስፖርት ችግር አኳያ ለሁሉም ተጎጂ እኩል ማድረስ ባይቻልም መንግሥት ችግሩን አምኖ የህዝቡን ድጋፍ ጤቆ ተገቢውን ምላሽ አግኝቶ ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ብዙ ወገኖቻችንን በርሃቡ አጥተናል፡፡
በዘመነ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የነበረው በ1965/66 ዓ.ም. ርሃብ ግን ንጉሱም ህዝቡም እንዳያውቁ መኳንንቱ ለመሸፋፈን ሞክረዋል፡፡ በዚህም መኳንንቱ ጠግበው እየበሉ በርካታ ወገኖቻችን በወቅቱ በተከሰተው ርሃብ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ይሄ በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍለክ እጅግ የከፋ የታሪክ ጠባስም ጥሎልን አልፏል፡፡
በዘመነ ደርግ በተለይ በ1977 ዓ.ም. የተከሰተውን ልብ ይሏል፡ የተከሰተውን ርሃብ የሀገሪቱ መራሄ መንግሥት መንግሥቱ ኃይለማርያምና ሁሉም ሹማምንት ቢያውቁም ከሀገሪቱ ህዝብ (ርሃብ ካልነካቸውን) እና ከዓለሙ ማኀበረሰብ ለመደበቅ ተሞክሯል፡፡ በዚህም ብዙ ወገኖቻችን በጊዜ ማዳን ሲቻል በሞት ተነጥቀናል፤የበለጠ ክብራችንም እንዲዋረድ በር ከፍቷል፡፡
በዘመነ ኢህአዴግ ከአንዴም ሶሰት ጊዜ፤በተለይ በ1985ዓ.ም.፣ 1986/87 ዓ.ም. እና የአሁኑን የ 2007/08 ዓ.ም. ርሃብ መንግሥት ከሀገሬው ህዝብና ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ለመደበቅ ሞክሯል፤ባይችልም፡፡ በቅርቡ በተለይም ባለፈው ክረምት በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የተጀመረው ርሃብ ወደ ሰሜኑ እና መካከለኛው የሀገራችን ክፍል በፍጥነት ቢዛመትም መንግሥት በምግብ ራሳችንን ችለናል፣ ርሃብ አልተከሰተብ፣ …ወዘተ የሚለው ፈሊጥ አንድ ወር እንኳ አልሞላውም፡፡ ርሃቡ ልክ እንደሰደድ እሳት እና አውሎ ነፋስ ማዕበል ምስራቁን፣ ሰሜኑን እና ከፊል መሐከለኛ የሀገራችን አካባቢ በፍጥነት ተዛመተ፡፡ ርሃብ የለም፣ በምግብ ራሳችንን ችለኛል፣…የክፉዎች ወሬ ነው ሲባል የነበረው ርሃብ፤ አሁን መንግሥት በህዝብ ላይ እና በእንሰሳቶቻቸው ላይ ከፍተኛ እልቂ ከደረሰ በኋላ “ኢሊኖ በሚባለው ድርቅን ተከትሎ በነሳው ርሃብ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር 5 ሚሊዮን አካባቢ ደርሷል፣ ከዓለም አቀፉ ለጋሽ ድርጅቶች እና ሀገራት አፋጣኝ እና በቂ ድጋፍ አላገኘንም,…” የሚል ይፋ ልመናዊ መግለጫ ተሰጠ፡፡ የተራቡ ወገኖቻንን ቁጥር መገመትና መናገር ቢከብድም አስቸኳይ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ግን ከ 10 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡
በጣም የሚያሳዝነው ሁሉም ስርዓቶች በተፈጥሮ ሃብትና በግብርና ላይ ያላቸው ፖሊሲ የአንዳቸው ከአንዳቸው የማይሻል፣ ያልተለየ ቢሆንም በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ግን ርሃብ ለመደበቅ አልተሞከረም፤ ይልቁንም ከመንግሥት ካዝና በተጨማሪ ህዝቡ እንዲረዳዳ የጠማፅኞ ጥሪ ተደረገ እንጂ፡፡ በኃይለስላሴ ዘመንም ቢሆን ሹማምንቱ ከንጉሱ እና ርሃብ ካልደረሰበት ህዝብ ለመደበቅ ቢሞከርም መደበቁ አልቻሉም፡፡ የደርግና ኢህአዴግ ስርዓት ክፋት ግን ከበታች ሹም እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ድረስ ርሃቡን እያወቁ ለመደበቅ መሞከራቸው የፖሊሲ ችግራቸውን ለመደበቅ ከመሞከራቸው ይልቅ በሰብዓዊ ፍጡር ህይወት ላይ ያላቸውን ጭካኔ ያሳያል፡፡ ምክንያቱም ርሃብ ቀን አይሰጥምና፡፡ ርሃብ የሰውንም ሆነ የእንሰሳትን ህይወት ሲቀጥፍ ዳግም አናገኛቸውምና፡፡
አሁን ርሃቡ በዋነኛነት የተከሰተው ውሃ ቅዳ ውሃ መለስ የሆነው የመንግሥት ስርዓትና በመሪዎች ቸልተኝነት፤ የተፈጥሮ ሃብት፣ የመሬት፣ ስነ ህዝብ፣የምግብ እና የመረጃ ጥንቅር ፖሊሲ ችግር ነው፡፡ ባለፈው ከነበረው ችግር ለነገው አለመማራችን እና ለመማር አለመዘጋጀታችን ውጤትም ነው፡፡ ስለዚህ ርሃብን እና የተራበውን ህዝብ ቁጥር በመደበቅና በማዛበት ርሃብን ማቆም እንደማይቻል ልናውቅ ይገባል፡፡ ስለዚህ በርሃብ የተጎዱ ወገኖቻችንን በተመለከተ የውጭ መንዛሪ እጠረት ለመሸፈን ባለመ የውጭ ለጋሽ ሀገሮችን ተማፅኞ ብቻ ሳይሆን ዜጎች ወገኖቻችንን እንዲረዳዳ ዕድሉ ሊሰጥና በይፋ የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ማሰባሰብ ስራ በማድረግ የወገኖቻችንን ህይወት መታደግ ይቻላል፡፡ ለዚህም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፤ ርሃብ ጊዜ አይሰጥምና፡፡
ከፖሊሲ ችግር አንዱ ከዝናብ ጥገኝነት ለመውጣት የሚያስችል መስኖ አለማስፋፋት፣ የመሬት ባለቤትነት፣ የሜትሪዮሎጂ ተቋም ብቃት ባላቸው የአየር ትንበያ ባለሙያዎች አለመዋቀር እና አለመጠናከር፣ መስኖ በሌለባቸውና ዓመታዊ የዝናብ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ቆላማ አካባቢዎች የተለየ ትኩረትና ጥንቃቄ እንዲሁም በቂ የእንሰሳትና የሰው ህክምና እና የምግብ ቅድመ ዝግጅት ክምችት አለማድረግን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ከአስቸኳይ ርስበርስ የመረዳዳት እና ዓለም አቀፍ ድጋፍ ጥየቃ እንቅስቃሴው እንዳለ ሆኖ፤ ለ24 ዓመታት ተሰርቶበት ለውጥ ያላመጣውን ፖሊሲም ማሻሻል አሊያም መቀየር ዋነኛው ቁልፍ ተግባር መሆን አለበት፡፡ አለበሊያ በኢህአዴግ ዘመን ለ4ኛ እና 5ኛ ጊዜ መከሰቱ እንደማይቀር የአሁኑን ጨምሮ ያለፉት ጊዜያት ከበቂ በላይ አስተማሪዎች ናቸውና ከፖለቲካ ጋጋታ ትርፍ ይልቅ ሕይወት የማዳኑ ተግባር ሊፈጥን ይገባዋል፡፡
አዳማ የኤድስ ተጠቂዎች ማደርያን ወደ መቅዲ ባርና ሬስቶራንት ቀየረች?!
የትነበርክ ታደለ
ይህ የምስራች እንዳይመስላችሁ! እጅግ ዘግናኝ አሳፋሪና አሳዛኝ የሀገራችን እውነታ ነው። ከአመታት በፊት ሀገር በኤች አይቪ የደረሰባትን የጭለማ ድባብ አንረሳውም! እርግጥ አሁንም ገና ከሀዘኑ ሙሉ በሙሉ አልተላቀቅንም። በዝያ የጭለማ ዘመን፣ መፍትሄ ከሀገር ውስጥም ከውጭም ሲፈለግ፣ ወጣቱ በየቦታው ሲረግፍ፣ ቤተሰብ ሲበተን አዳማ ውስጥ አንድ ሰው ተገኘ።
ይህ ሰው መስፍን ፈይሳ ይባላል። መስፍን ራሱም የቫይረሱ ተጠቂ መሆኑን ይፋ አውጥቶ በመናገር የሱ ቢጤ ወገኖቹን ለመርዳት ቆርጦ ተነሳ። እሱ እንደሚናገረው ማዳበርያ ከረጢት አንገቱ ላይ አስሮ በየደጃፉ እየዞረ ምግብ እየለመነ የሰበሰባቸውን ወገኖቹን መመገብ ያዘ።
እየቆየ ጥረቱ ፍሬ አፍርቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጠውና ከ5000 ሰዎች በላይ የተረዱበት “መስፍን ፈይሳ ኢኒሼቲቭ በጎ አድራጎት” ተቋቋመ።
ይህ ተቋም አሁን “መቅዲ ባርና ሬስሮራንት ተብሎ ወጣቶች ቀንና ለሊት የሚጨፍሩበት፣ በሺሻ ጢስ የሚታጠኑበትና ህልማቸውን የሚነጠቁበት ቦታ ሆኗል።
ከሰአታት በፊት ግለሰቡ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ በለቀቀው ቪዲዮ እንዳስታወቀው በጉልበት ከሀገር እንድወጣ ካደረጉኝ በኋላ ተቋሙን አፈራርሰው አራት ሚሊየን የሚገመት ንብረት ዘርፈው ጉዳተኞቹን በትነው ህንጻውን ከኤች አይቪ መከላከያነት ወደ ማሳራጫነት አዙረውታል ብሏል።
እጅግ የሚደንቀው ደግሞ ይህ ተቋም (አሁን መቅዲ ባር) የሚገኘው ከአዳማ ዩኒቨርስቲ አጠገብ መሆኑ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ አለማቀፍ ሚዲያዎች እንደሚዘግቡት ሀገራችን ውስጥ ዝሙት በርካሽ የሚሸጥባቸው ስፍራዎች ዩኒቨርስቲዎች ባሉበት አካባቢ ነው።
በተለይ ደግሞ አዳማ ናዝሬት በዚህ ግምባር ቀደም ተጠቃሿ ናት። አንድ የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው አዳማ 230.000 ነዋሪዎች ያላት ስትሆን ከዚህም ውስጥ ካሉት ሴቶች 5000 ዝሙት አዳሪዎች ናቸው። ይህም ማለት ከመቶ አምስት ፐርሰንቱ በዚሁ ስራ የሚተዳደሩ ናቸው። ልብ በሉ ይህ ቁጥር የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን አይጨምርም።
እንግዲህ ይህንን አይነት ጉድ የተሸከመች ከተማ እንዴት ባለ አስተዳደር እጅ ብትወድቅ ነው የህዝብን ሁለንተናዊ ጤንነት ከመጠበቅ ሀላፊነቱ እየሸሸ በግለሰብ የተቋቋመ ተቋም ለማፈረስ የተደፈረው?
እጅግ በጣም የሚገርመው ደግሞ ይህ ተቋም ሲጀመር የመሰረት ድንጋይ የጣሉት በአሁን ሰአት የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት ኦቦ ሙክታር ከድር መሆናቸው ነው። (አቡነ ጳውሎስም በቦታው ነበሩ)
እና ምነው? ኦቦ ሙክታር አዳማ ውስጥ ምን እየተካሄደ ማወቅ አይችሉም ማለት ነው? ለአንድ ትልቅ አላማ ራሳቸው በቦታው ድረስ ሄደው መሰረት የጣሉለት ተቋም እጅግ በሚያሳፍርና በሚያዋርድ ሁኔታ ተሽቆልቁሎ ሲጠፋ ምንም አልሰሙም ማለት ነው? አዳማ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ነች! ይህንን ሳይስሙና ሳያዩ ወለጋ ጫፍ ወይም አርሲ ቦረና ስላለው እንዴት ሊሰሙ ይችላሉ? ነው ወይስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሳቸው ይሁንታ አለበት? እውነት ለመናገር መልስ ሊሰጡበት የሚገባ ጥያቄ ነው።
የአዳማ ህዝብስ ቢሆን በራሱ ጉዳይ ላይ ከሱ የተሻለ ማን ሊጠይቅለት ይችላል? ግለሰቡ እንደተናገሩት ወደዚህ ባርና ሬስቶራንት ልጆቻችሁ እየሄዱ እያያችሁ ዝም ብትሉ በልጆቻችሁ ህይወት ላይ ፈርዳችኋል።
መንግስትም ቢሆን እነ መቄዶኒያን የመሳሰሉ ወገንን ከጎዳና የሚሰበስቡ ተቋማት ነገ በተመሳሳይ መንገድ እንደማይፈርሱና ወደ ሺሻ ቤትነት እንደማይቀየሩ ምን ማስተማመኛ ይሰጠናል? ትውልድ እየጠፋ ነው! ህግ እየተጣሰ ነው! የምንፈልገውን እያጣን የማንፈልገው እየተጫነብን በዚህ ላይ ለጩሀታችን ዝምታ እየተመለሰልን ነው! ነገ አጣብቂኙ ለሀገር ነውና መቅዲ ባር በአስቸኳይ ወገኖቻችን ወደ ሚረዱበት ተቋምነት ይመለስልን! ወገን በጭፈራ ቤት አይታከምም!
እነ ዘመነ ምህረት የእምነት ክህደት ቃላቸው ሰጡ
• “ሽብር ተፈፅሞብኛል እንጅ አሸባሪ አይደለሁም”
• “ፍትህ ቢኖር ኖሮ እኔ ሳልሆን ወያኔና ግብረ አበሮቹ ነበሩ እዚህ መቆም የነበረባቸው” አቶ ጌትነት ደርሶ
• “የተከሰስኩት ድርቡሽ እንኳ ያልደፈረውን የጎንደር ጥምቀት ላይ ፈንጅ ልታፈነዳ ነበር ተብዬ ነው፡፡ ምርመራ ላይ ግን ለምን የመኢአድ አባል ሆንክ ይሉኛል” አቶ ዘመነ ምህረት
ዘመነ ምህረት የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት የተከሰሱት የቀድሞው መኢአድ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ዘመነ ምህረትና ሌላኛው የመኢአድ አባል የሆነው አቶ ጌትነት ደርሶ ዛሬ ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ የልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ለዛሬ ቀጠሮ የሰጠው አቶ ዘመነ ምህረት ማረሚያ ቤቱ ውስጥ በደል እየደረሰበት መሆኑን ባመለከተው መሰረት ማረሚያ ቤቱ ጉዳዩን አጣርቶ እንዲያቀርብ፣ እንዲሁም በዚሁ መዝገብ 3ኛ ተከሳሽ የነበረው የመኢአድ አባል መለሰ መንገሻ ክስ የተለየ ይዘት ስላለው ክሱ ተለጥሎ እንዲታይና የቀሪዎቹን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን የእምነት ክህደት ቃል እንዲሁ እየሰማሁ እመዘግባለሁ ብሎ የነበር ቢሆንም አቶ ዘመነ ምህረት ‹‹በድምፅ እንዲቀዳልኝ እፈልጋለሁ›› በማለቱ የሁለቱም ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃል በድምፅ እንዲቀረፅ ተደርጓል፡፡1ኛ ተከሳሽ አቶ ዘመነ ምህረት የጎንደር ጥምቅት ላይ ፈንጅ ሊያፈነዳ እንደነበር መከሰሱን ሲገልፅ ‹‹ሰው አይደለም እንሰሳት እንኳን የማይደፍሩትን፣ ድርቡሽ እንኳን ያልደፈረውን ጥምቀት እኔ በክስትና ሀይማኖትና ባህል ተኮትኩቼ ያደኩትን ሰው ፈንጅ ልታፈነዳበት ነበር መባሌ ያሳዝናል›› ብሏል፡፡ በሌላ በኩል ግን በምርመራ ወቅት ‹‹ለምን የመኢአድ አባል ሆንክ? ለምን የኢህአዴግ አባል አልሆንክም?›› እንደተባለ የገለፀው አቶ ዘመነ ይህም ‹‹ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ዥግራ ነሽ ይሏታል ነው›› ሲል እሱን ለማሰር የተቀነባበረ ሴራ መሆኑን ገልፆል፡፡ አቶ ዘመነ ምህረት አክሎም የታሰረው ኤርትራ እንዳትገነጠል ሲታገሉ የኖሩትን፣ እንዲሁም የሰላማዊ ትግሉ ፈር ቀዳጅ የሆኑት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ያስጀመሩትን ትግልን የመኢአድ አመራር ሆኖ እያስቀጠለ በመሆኑ እንደሆነ ገልፆል፡፡ በመሆኑም ወንጀሉን እንዳልፈፀመው የገለፀ ሲሆን ‹‹ከተጠቀሰው መካከል ግን የማምነው አለኝ፡፡ ኢህአዴግን ዛሬም ነገም እታገለዋለሁ›› ብሏል፡፡
2ኛ ተከሳሽ የሆነው አቶ ጌትነት ደርሶ በበኩሉ ‹‹ሽብር ተፈፅሞብኛል እንጅ እኔ አሸባሪ አይደለሁም›› ብሏል፡፡ አቶ ጌትነት አክሎም ‹‹ፍትህ ቢኖር ኖሮ እዚህ መቆም የነበረኝ እኔ ሳልሆን ወያኔና ግብረ አበሮቹ ነበሩ ነበሩ፡፡ እዚህ መቆም የነበረበት መሳሪያን ተገን አድሮጎ ለ3 ወር ጨለማ ቤት ዘግቶ ጭካኔ የፈፀመብኝ ወያኔ ነበር›› ሲል ወንጀሉን እንዳልፈፀመው ክዶ ተከራክሯል፡፡
ምንም እንኳ ፍርድ ቤቱ ባለፈው ቀጠሮ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አቶ ዘመነ ምህረት ተፈፀመብኝ ያለውን በደል አጣርቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበር ቢሆንም የማረሚያ ቤቱ ተወካይ ‹‹የደረሰኝ መረጃ የለም›› ብለዋል፡፡ ዛሬም በድጋሜ አቤቱታውን ያቀረበው አቶ ዘመነ ምህረት ‹‹እኛ እየራበን ነው፡፡ ምግቡን እንሰሳት እንኳን ሊበሉት አይችሉም፡፡ ቤተሰቦቼ እንዳይጠይቁኝ ተደርጓል፡፡›› በማለት ከተያዙበት ጥር 10 ቀን 2007 ጀምሮ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ የዘር መድሎ እየደረሰባቸው እንደሆነ እና ሽንት ቤት ጥግ እንዲተኙ መደረጋቸውንም ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡ ዛሬ ለፍርድ ቤቱ ቅሬታ በማቅረቡም ከማረሚያ ቤቱ ስቃይ ሊገጥመው እንደሚችል ስጋቱን የገለፀው አቶ ዘመነ ጉዳያቸው በተዘዋዋሪ ችሎት እንዲታይ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የ3ኛ ተከሳሽ ክስ ከእነ ዘመነ ምህረት ክስ ተነጥሎ በሌላ ችሎት እንዲታይ ብይን የሰጠ ሲሆን አንደኛ ተከሳሽ በማረሚያ ቤቱ ላይ ያሰማቸው አቤቱታዎችን ማረሚያ ቤቱ አጣርቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በሁለቱ ተከሳሾች ላይ የሰው ምስክር ለማቅረብም ለህዳር 3 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ-ኢትዮጵያ
ከእስር የተለቀቁት የዞን 9 ብሎገሮች እና ጋዜጠኞች ምስጋና አቀረቡ
በድንገት ከያለንበት ተይዘን እንደታሰርነው አፈታታችንም ግራ የሚያጋባ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ክሶች ቀርበውብን እያለ ግማሾቻችን ‹ክስ ተቋርጦላችኋል› ተብለን ተፈታን፣ ግማሾቻችን ደግሞ ‹ነፃ ናችሁ› (ከሳሽ በነፃነታችን ላይ ይግባኝ መጠየቁ እንዳለ ሁኖ) ተብለን ይሄው ወጥተናል፡፡ ቀሪ ክስ ይዘን በዋስ ወጥተን እየተከራከርንም ያለን አለን፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል የሁላችንም ዕምነት ግን አንድም ቀን ሊያሳስረን የሚገባ ወንጀል አለመፈፃችን ማመናችን ነው፡፡ መፈታታችን ጥሩ ሁኖ፤ መታሰር በፍፁም የማይገባን ነበርን፡፡ መፃፋችን እና ሕግ እንዲከበር መጠየቃችን ሀገሪቱ አገራችን እንድትሻሻል እና ሁላችንም ዜጎች የተሻለ ህይወት አንዲኖራቸው ከመሻት ባለፈ ሌላ ነገር አልነበረውም/የለውም፡፡ ነገር ግን ይህን በማድረጋችን ተገርፈናል፣ ተዘልፈን-ተሰድበናል፣ ታስረናል ተሰደናልም፡፡ ይህ በፍጹም አይገባንም ነበር፡፡
የእኛ መታሰር ፖለቲካዊ ንቃት የፈጠረላቸው ሰዎች እንዳሉ ሲነግሩን ደስ ይለናል፡፡ በእኛ መታሰር ምክንያት ለመጠየቅና ለመፃፍ በጣም እንደሚፈሩ የሚነግሩን ሰዎች ስናገኝ ደግሞ እናዝናለን፡፡ የመታሰራችን ጉራማይሌ ስሜት እንደዚህ ነው፡፡ ሳይገባን በመታሰራችን የነቁ መኖራቸውን በማወቃችን የምነደሰተውን ያክል፤ ሳይገባን በመታሰራችን የተሰበሩና ከተዋስኦ መድረኩ የራቁ እንዳሉ ስናውቅ እጅግ እናዝናለን፡፡
መታሰር በደል ነው፡፡ ብዙ ነገር ያጎድላል፡፡ መታሰር መልካም ነው፡፡ ብዙ ነገር ያስተምራል፡፡ እኛ በመታሰራችን ሀገራችን የበለጠ እንድናውቃት ሁነናል፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ነፃነት አሁንም ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ተረድተናል፡፡ ሕግን መከታ አድርገው የኖሩ ‹ስም የለሽ› ዜጎች ሕጉ ሲከዳቸውና እነሱ ላይ ‹በላ› ሲያመጣባቸው ታዝበናል፡፡ ከሁሉም በላይ ፍትህ የሌለባት ሀገር ለዜጎቿ የማትመችና አገር እንደሆነች አይተናል፡፡
በእስራችን ወቅት የተለያዩ በደሎች በተቋም ደረጃ ደርሰውብናል፡፡ ግን አገር ነውና ከይቅርታ የሚያልፍ አይደለም፡፡ ለበደላችሁን አካላት እናንተ ይቅርታ ባትጠይቁንም፤ እናንተ የፈለጋችሁትን ባለማድረጋችንና ሕግን መሰረት አድርገን በመኖራችን ስላስከፋናችሁ እባካችሁ ይቅር በሉን፡፡
በዚህ ሁሉ መሃል ግን እናንተ አላችሁ፡፡ ጓደኞቻችንም ናችሁ፤ ዘመቻ አድራጊዎችም ናችሁ፤ ቤተሰቦቻችንም ናችሁ፤ ጠያቂዎቻችንም ናችሁ፤ ጠበቆቻችንም ናችሁ፣ የመንፈስ አጋሮቻችንም ናችሁ ርቀት ሳይገድባች የጮሃችሁልን አለም አቀፍ የመብት ጠያቂዎችም ናችሁ … በመታሰራችን የተረዳነው አንዱ ትልቅ ነገር የናንተን መልካምነት፣ የናንተን አጋርነት እና የናንተን የማይሰለች ድካምና ፍቅር ነው፡፡ እናንተ ባትኖሩ ‹አጭሩ› የእስር ጊዜያችን ይረዝምብን ነበር፤ ‹ቀላሏ› እስር ትከብድብን ነበር፡፡ ምስጋና ለናንተ፤ እስራችን ‹አጭር› – ፈተናችን ‹ቀላል› እንዲሆን አድርጋችሁልናልና፡፡
እናንተ ወዳጆቻችን ለሁሉም ነገር – እልፍ ምስጋና፡፡
እናመሰግናለን!
የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች






