ፖሊስ በ”በሁከትና ብጥብጥ” ተጠርጣሪዎች ላይ ሦስት መዝገብ አደራጅቻለሁ አለ
•እነ ወይንሸት ለሁለተኛ ጊዜ 6 ቀን ተቀጥሮባቸዋል
•”ወይንሸት ከአሁን በፊትም ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ስታሸብር ነበር” ፖሊስ
ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስ ሊቢያ በሚገኙ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ የሽብር ድርጊት ለማውገዝ ጠርቶት በነበረው ሰልፍ ላይ “ሁከትና ብጥብጥ አስነስታችኋል፤ ተካፍላችኋልም” በሚል ፖሊስ ባሰራቸው ሰዎች ላይ ሦስት የተለያዩ መዝገቦች ማደራጀቱን አስታውቋል፡፡
ሚያዝያ 22 ቀን 2007ዓ.ም በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቀረቡ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ሌሎች በዕለቱ የተያዙ ሰዎችን በተመለከተ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ እንደገለጸው፣ ፖሊስ የራሱን ቡድን በማዋቀር ተጠርጣሪዎችን በሦስት መዝገቦች ስር እንደየተሳትፏቸው አደራጅቻለሁ ብሏል፡፡ በዚህ መሰረት በሶስተኛው መዝገብ ላይ ያካተታቸውን በርካታ ታሳሪዎች አጣርቶ መልቀቁን የገለጸው ፖሊስ፣ በሁለተኛውና በአንደኛው መዝገብ ላይ ባሉት ተጠርጣሪዎች ግን ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጹዋል፡፡
አንደኛው መዝገብ ላይ በእነ ወይንሸት ሞላ መዝገብ 5 ሰዎች የተካተቱ ሲሆን አራቱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቸው፤ አንደኛዋ ተጠርጣሪ ደግሞ ፖሊስ የፓርቲው አባል እንደሆነች የሚገልጸው፣ እሷ ግን አባል አለመሆኗን የገለጸች መሆኗን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስለሆነም በዚህ መዝገብ የተካተቱት ወይንሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ጸጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ማስተዋል እና የፓርቲው አባል ያልሆነችው ቤተልሄም ይገኙበታል፡፡ ማስተዋል በዛሬው ዕለት ቀደም ብሎ የተሰጠው የቀጠሮ ቀን ስላልደረሰ ፍርድ ቤት አልቀረበም፡፡ ቤተልሄም ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሳልሆን አባል ነሽ እየተባልኩ ምርመራ ይደረግብኛል፤ ሌሊት እየተጠራሁ እመኝ እየተባልኩ ነው›› ስትል ለፍርድ ቤቱ ገልጻለች፡፡
በሁለተኛው መዝገብ ላይ ደግሞ 15 ተጠርጣሪዎች ተካትተዋል፡፡ ፖሊስ በዚህ መዝገብ በተካተቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ክሱን ሲያሰማ እንዲህ ብሏል፤ “ተጠርጣሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ሲያደርጉ ‹ጠንካራ መሪ እንጂ ጠንጋራ መሪ አንፈልግም›፣ ‹ወያኔ አሳረደን›፣ ‹ፍትህ የለም! በማለት ሁከት እንዲነሳ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡”
የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በምርመራ ወቅት የገጠማቸውን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ ያሰሙ ሲሆን፣ በተለይ የሚደረግባቸው ምርመራ ከፓርቲው ጋር የተያያዘ እንጂ ከተጠረጠርንበት ጉዳይ ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ምርመራው ከጉዳዩ ጋር የሚገናኝ አይደለም፤ ሌሊት ሌሊት እየተጠራሁ ምርመራ ይደረግብኛል፡፡ የፓርቲ አባል መሆን ወንጀል እስኪመስለኝ በፓርቲ አባልነቴ ጫና ይደረግብኛል፡፡ በዚያ ላይ የጤና እከል ገጥሞኛል፤ ህክምና ያስፈልገኛል” ስትል ለፍርድ ቤቱ ያስረዳችው ወይንሸት ሞላ፣ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት እንዲሰጣት ጠይቃለች፡፡
በሁለቱም መዝገብ የተካተቱት ሁሉም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፖሊስ በበኩሉ በመጀመሪያው መዝገብ ላይ ያሉት እነ ወይንሸት ላይ የምርመራ ስራውን እንዳልጨረሰ በመግለጽ 14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ በተለይ ወይንሸት ሞላ ላይ ፖሊስ፣ “ከአሁን በፊትም ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ተመሳስላ በመልበስ ስታሸብር ነበር” በማለት ዋስትና እንዳይሰጥና የጠየቀው የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ በሁለተኛው መዝገብ ላሉት ደግሞ 7 ቀን ፖሊስ ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ በሁለቱም መዝገብ ላይ በተመሳሳይ የ6 ቀን ጊዜ በመስጠት ለሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
መንግስት በጠራው ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች እስር አሁንም እንደቀጠለ የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ በትናንትናው ዕለትም ሦስት የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አባላት (አንደኛው አሁን ላይ የሰማያዊ አባል) መታሰራቸው ይታወሳል፡፡
በተያያዘ ዜና ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስ ሊቢያ በሚገኙ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ የሽብር ድርጊት ለማውገዝ ጠርቶት በነበረው ሰልፍ ሳይጀመርና ከሰልፉ በኋላ ተይዘው የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ቤት ተበረበረ፡፡ ካሳንቺስ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ትናንት ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ቀርበው የ6 ቀን ቀጠሮ ከተሰጠባቸው በኋላ ምሽት ላይ ቤታቸው መበርበሩንና ንብረቶቻቸው መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በብርበራው ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በሰላማዊ ሰልፍና በሌሎች አጋጣሚዎች የሚለብሱት የሰማያዊ ፓርቲ አርማ ያለበት ቲሸርት፣ የምርጫና ሌሎች ቅስቀሳ ወረቀቶችም ለ‹ምርመራ› ተወስደዋል፡፡
ቤታቸው ለሰዓታት የተበረበረባቸው ወይንሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ጸጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬና ማስተዋል ፍቃዱ ሲሆኑ ወይንሸት ሞላ የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ ወረቀቶች፣ የሰማያዊ ፓርቲ አርማ ያለበት ቲሸርት፣ ሲዲዎች፣ አርማ የሌለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ (በተናጠል አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የሆነ)፣መጽሐፎች እና ሌሎችም ህጋዊ ሰነዶች እንደተወሰዱባት ገልጻለች፡፡ ዳንኤል ተስፋዬ የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አርማ ያለበት ቲሸርት፣ በአንድ ላይ ያስጠረዛቸው የፋክትና የአዲስ ጉዳይ እትሞች፣ ሲዲዎችና ካሴቶች ተወስደውበታል፡፡ በተመሳሳይ ኤርሚያስ ጸጋዬ ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተር፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሰነዶች፣ ሲዲዎች፣ ማስታወሻ ደብተሮችና ሌሎችም ህጋዊ ሰነዶች ተወስደውብኛል ብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በመሻር ዋስትና የከለከላቸውን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እየወሰደ እየመረመረ ነው፡፡ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ የታሰሩ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም ጠዋት በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርበው የ6000 ብር የሰው ዋስትና እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበር ቢሆንም ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በመሻር በእስር አቆይቷቸዋል፡፡
ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ጥሶ በአሁኑ ወቅት ካሳንቺስ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ አስሯቸው የሚገኙትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ማዕከላዊ እየወሰደ እየመረመረ ይገኛል፡፡ በዛሬው ዕለት ዳንኤል ተስፋዬ ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት ተወስዶ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ውስጥ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ምንጮች ከስፍራው አስታውቀዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ህዝቡ በከፍተኛ ደረጃ ለተቃዋሚዎች ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ተከትሎ ገዥው ፓርቲ ኦህዴድ/ኢህአዴግ ምርጫውን ከወዲሁ ማስጀመሩ ተገለፀ
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ገዥው ፓርቲ ምርጫውን ከአሁኑ እንደጀመረው ምንጮች ገለፁ፡፡ በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች የገዥው ኢህአዴግ ካድሬዎች መራጮችን በጋንታ፣ በሴልና በኔትወርክ እያደራጁ “ኦህዴድ/ኢህአዴግን መርጫለሁ” በሚል እያስፈረሙና ፎርም እያስሞሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጋንታ፣ በሴልና በኔትወርክ ተደራጅተው ‹‹ኦህዴድን መርጠናል›› ብለው እንዲፈርሙ የተደረጉ ዜጎች ፎርሙን ከሞሉበት ቀን ጀምሮ የምርጫ ካርዳቸውን ለጋንታ፣ ሴልና ኔትወርክ መሪዎቻቸው እንደሚሰጡ ታውቋል፡፡ የጋንታ፣ የሴልና የኔትወርክ መሪዎችም ኢህአዴግን ከአሁኑ መርጠዋል ተብለው የተደራጁ ዜጎችን ስምና የምርጫ ካርድም ለኦህዴድ/ኢህአዴግ ከፍተኛ ካድሬዎች እንደሚሰጡ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
የኦህዴድ/ኢህአዴግ ካድሬዎች ግንቦት 16 ቀን በፊት የምርጫ ካርዳቸውን ለጋንታ፣ ለሴልና ለኔትወርክ መሪዎች የሚሰጡትን ዜጎች ቤት ለቤት እየዞሩ እያስፈረሙ እንደሚገኙ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ በጋንታ፣ ሴልና ኔትወርክ ተደራጅተው ኦህዴድ/ኢህአዴግን ከአሁኑ እንደመረጡ በፊርማቸው አረጋግጠዋል የተባሉት ዜጎች ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም በሚደረገው ምርጫ እንደማይሳተፉ የታወቀ ሲሆን አብዛኛዎቹ በግዳጅና በማስፈራሪያ እየሞሉ እንደሚገኙ ተገልጾአል፡፡
የጋንታ፣ የሴልና የኔትወርክ እንዲሁም የመራጮች ስምና ፊርማቸው እየሰፈረበት ከግንቦት 16 በፊት እንደመረጡ ተደርጎ ዜጎች እንዲሞሉት የሚደረገውና ከስር የሚታየው ቅጽ ካድሬዎች በአርሲ ዞን በቆጅ ወረዳ ቤት ለቤት ሲያስሞሉ መገኘቱ ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይም በምዕራብ ኢትዮጵያ እዚሁ ኦሮሚያ ክልል ተመሳሳይ ድርጊት እየተፈፀመ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ በተለይ በዶ/ር መረራ ጉዲና የሚመራው ቡድን በአካባቢው የተጠናከረ የምርጫ ቅስቀሳ በማድረጋቸውና ኦፌኮ/መድረክ በአካባቢው ህዝብ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ የኦህዴድ/ኢህአዴግ ካድሬዎች ከአካባቢው የፀጥታ ኃይል ጋር በመሆን የተቃዋሚ ደጋፊዎችና የአካባቢው እጮዎች ጭምር ድብደባና እስራት እየፈፀመባቸው መሆኑን ምንጮችን ጠቅሶ ነገረ-ኢትዮጵያ ዘግቧል ፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ መንግስት የከፈተበትን የጥላቻ ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳሰበ
መንግስት ሊቢያ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ላይ አሰቃቂ እርምጃ የወሰደውን አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም ራሱ በጠራው ሰልፍ ላይ ከህዝብ የገጠመውን ተቃውሞ ተከትሎ ሰማያዊ ላይ የጥላቻ ዘመቻ እንደከፈተበትና ይህንን የጥላቻ ዘመቻውን እንዲያቆም ሰማያዊ ፓርቲ በሰጠው መግለጫ አሳስቧል፡፡
መንግስት የጠራውን ሰልፍ ከማንም ተቃዋሚ ፓርቲ ቀድሞ የደገፈው ሰማያዊ እንደሆነ የገለጸው መግለጫው “የዜጎችን ስቃይ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል የፈለገው ህወሓት/ኢህአዴግ ሰማያዊ ፓርቲ በወገኖቻችን ላይ ለሚደርሰው በደል መፍትሄ እንዲሰጥ መወትወቱ፣ የፖለቲካ ልዩነታችንን ወደ ጎን አድርገን በሰልፉ ላይ መገኘታችን እንዳላስደሰተው ከሰልፉ ቀን ጀምሮ በፓርቲያችን ላይ የተከፈተው ዘመቻ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡” ብሏል፡፡
ከሰልፉ ማብቃት ጀምሮም ጉዳዩን ገና ፖሊስ ሳይመረምረው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን ሰማያዊ ፓርቲ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት እየጣረ ነው በሚል መወንጀላቸውን፣ የመንግስት ሚዲያዎች ሰማያዊ ፓርቲ ሁከትና ብጥብጥ ሊያስነሳ ነው ብለው ሚዛናዊ ያልሆነ መረጃ ማሰራጨታቸውንና አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም ተብለው በተጠሩ ሰልፎችም ሁሉ መንግስት ሰማያዊ ፓርቲ ለመቃወም እየተጠቀመባቸው መሆኑን መግለጫው አትቷል፡፡
በተጨማሪም በሰልፉ ዕለት የሰማያዊ አባላት ገና ሰልፉ ሳይጀመርና መስቀል አደባባይ ሳይደርሱ እንዲሁም ሰልፉ ካበቃ በኋላ እየታደኑ ሲታሰሩ መስቀል አደባባይ ላይ የተያዙት የኢህአዴግ አባላት ከቀበሌ ደብዳቤ እያመጡ መፈታታቸው መንግስት ሰማያዊን በሀሰት ለመወንጀል መነሳቱን ያሳያል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል 6 ያህል የሰማያዊ አባላት በታሰሩበት ሁኔታ መንግስት 7 አመራሮችና 20 ያህል አባላት ታስረዋል ማለቱ ትክክል አለመሆኑንና ከመጀመሪያውም 6 አባላቱ የታሰሩበት መንገድና አሁንም በሰማያዊ ላይ የሚቀርበው ክስ መሰረተ ቢስ ነው ብሎታል፡፡
“ይህ በህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት አማካኝነት እየቀረበ ያለው ክስ እና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ህወሓት/ኢህአዴግ ለዜጎች ህይወት የማይጨነቅ እና በዜጎች ሞት የራሱን የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ እና ጠንካራ ተቃዋሚ የሆነውን ሰማያዊ ፓርቲን ለማጥቃት እየተጠቀመበት መሆኑን በተጨባጭ የሚያሳይ ነው፡፡” ሲልም የመንግስትን ተግባር ተቃውሟል፡፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተሰጠበትን ጉዳይ ተጠርጣሪ ከማለት ይልቅ ወንጀለኞች ናቸው በማለት በህገወጥ ስራ እንደተሰማራ ያሳያል ሲልም ወቅሷል፡፡
“መንግስት እና የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ከዚህ አኩይ ተግባራቸው የማይታቀቡ ከሆነ፣ የሰማያዊን ስም በሀሰት በማጠልሸት ስራ ላይ የተሰማሩ የመንግስት ተቋማትን እና ግለሰቦችን በህግ ፊት ለማቆም ይገደዳል” ያለው መግለጫው ሌሎች ተከታታይነት ያላቸውን እርምጃዎችም እንደሚወስድና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሰማያዊ ፓርቲ ለሚያደርጋቸው ህዝባዊ ጥሪዎች በንቃት ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በሀዲያ ዞን በምርጫ 2007 ዓ.ም. ቅስቀሳ ምክንያት የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ
በደቡብ ክልል በሀድያ ዞን ሶሮ ወረዳ ጊምቢቹ ከተማ በህዝብና በራሱ ላይ በሚፈፀመው አስተዳደራዊ በደል የተማረረውና በተደጋጋሚ በሚፈፀሙት አስተዳደራዊ በደሎች ላይ ቅሬታ አቅርቦ መፍትሄ ያላገኘው የአካባቢው የ2007 ዓ.ም. ምርጫ የመድረክ ዕጩ የነበረው መምህር ጌታቸው አብርሃም ሚያዝያ 17 ቀን 2007ዓ.ም በጊምቢቹ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ግቢ ውስጥ ራሱን ያቃጠለ ሲሆን በሆሳዕና ሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት ቢቆይም ህይወቱ እንዳለፈች ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ቡሬ ለንጌ ትምህርትር ቤት የሲቪክስ መምህር የነበረው መምህር ጌታቸው በአካባቢው ባለው የከፋፍለህ ግዛና የጎሳ ፖለቲካ ተጠቂ ከመሆኑም ባሻገር በህዝብና በእሱ ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም መፍትሄ እንዲሰጥ ለባለስልጣናት ሲያሳውቅ መቆየቱን፣ ሆኖም ህዝቡ እና በራሱ ላይ የሚፈፀምበት በደል በመባባሱና መፍትሄ ማግኘት ባለመቻሉ አስተዳደሩ ግቢ ውስጥ ራሱን ማቃጠሉ ታውቋል፡፡
መምህር ጌታቸው ራሱና ህዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም በከተማው አስተዳደር ምክር ቤት ግቢ ውስጥ ራሱ ላይ ጋዝ በማርከፍከፍ ራሱን ባቃጠለበት ወቅት ግቢው ውስጥ የነበሩት ሰዎች ደርሰው እሳቱን በማጥፋታቸው ህይወቱን ለማዳን ጥረት አድርገው የነበር ቢሆንም የደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር ህይወቱ አልፏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛው በሀድያ ዞን አምቡላንሶች ለምርጫ ቅስቀሳ እየዋሉ በመሆኑ ህመምተኞች በተለይም ነፍሰ ጡር እናቶች ህክምና ሳያገኙ ለሞት እንደሚዳረጉ ነዋሪዎቹ ገለፁ፡፡ ሚያዝያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም አንዲት ምጥ የተያዙ እናት በአቅራቢያቸው በሚገኝ የጎምበራ የጤና ጣቢያ በሄዱበት ወቅት ‹‹ከአቅማችን በላይ ነው!›› ተብለው ወደ ሆሳዕና ሪፈራል ሆስፒታል ሄደው እንዲታከሙ ሪፈር ቢፃፍላቸውም በትራንስፖርት ችግር ነፍሳቸው አልፋለች፡፡
ለጤና ጣቢያው የተመደበችው አምቡላንስ በጎምበራ ወረዳ ኦሌ ቀበሌ ለገዥው ደኢህዴን/ኢህአዴግ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ በመውጣቷ ቤተሰብ ነፍሰጡሯን ከጎምበራ ክሊኒክ ወደ ሆሳዕና ሪፈራል ሆስፒታል በቃሬዛ ለመውሰድ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ሆሳዕና ሆስፒታል በቶሎ መድረስ ባለመቻላቸው የነፍሰ ጡሯ ህይወት መንገድ ላይ ሊያልፍ ችሏል፡፡
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት ከሆነ አምቡላንሶች ለምርጫ ቅስቀሳ በመዋላቸው ምክንያት በርካታ ህመምተኞች በተለይም እናቶችና ህፃናት በቶሎ ወደ ሆስፒታል መድረስ ባለመቻላቸው ተመሳሳይ ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በምርጫ 2002 ዓ.ም ወቅትም በተመሳሳይ መልኩ በዚሁ በሀዲያ ዞን አምቡላንሶች ለኢህአዴግ ምርጫ ቅስቀሳ ወጥተው ነፍሰ ጡር እናቶች ህይወታቸው ማለፉ አይዘነጋም፡፡
በሜዴትራኒያን ባህር ላይ በደረሰ የጀልባ አደጋ ከ16 በላይ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው አለፈ
ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሜዴትራኒያን ባህር ከሊቢያ ወደ አውሮፓ በስደት ሲጓዙ ከነበሩ 700 ሰዎች መካከል በርካቶች መሞታቸውንና የ28 ሰው ህይወት ብቻ በጣሊያን ባህር ኃይሎች ማትረፍ ቢቻልም፤ የአብዛኛው ተጓዥ ሕይወት ማለፉ ታውቋል፡፡ ህይወታቸው ካለፉት ውስጥ በርካታ ኤርትራውያን እንዳሉበት ቀደም ሲል የተገለፀ ቢሆንም፤ አሁን እየወጡ ባሉ መረጃዎች በተለይም ከሞት በተረፉ ኢትዮጵያውያን እንደተገለፀ ከሆነ ከ16 በላይ ኢትዮጵያውውን መሞተታቸው ታውቋል፡፡ በጉዞ ጀልባዋ ላይ በደረሰ የመስጠም አደጋ ህይወታቸው ካለፉት መካከል 8 ወጣቶች ከአዲስ አበባ መርካቶ ልዩ ስሙ አባኮራን በሚባል አካባቢ፣ 8 ወጣቶች ከባሌ እንዲሁም የድሬዳዋ ልጆች ህይወታቸው ማለፉን ቢቢኤን እና ፍትህ ሬዲዮን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ከሀገር ቤት ቤሰቦቻቸውን ዋቢ በማድረግ ያሰራጩት ዘገባ አመልክቷል፡፡
በተለይ ከአዲስ አበባ መርካቶ አባኮራን አካባቢ በጋራ ከተጓዙ 10 ወጣቶች መካከል 9ኙ በአደጋው ህይወታቸው ማለፉን እና አንዱ ከአደጋው የተረፈው ኢትዮጵያዊ ወጣት ጣሊያን እንደገባ ሀገር ቤት ደውሎ ማርዳቱ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም መሰረት የ8ቱ ቤተሰቦች ሀዘን ሲቀመጡ የአንዱ ወጣት ወላጆች ግን እስካሁን የልጃቸው ህይወት አልፏል መባሉን እንዳላመኑ እና እንዳልተቀበሉም የአካባቢው ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ በሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊቢያ ሜዲትራኒያን ባህር በደረሰው አደጋ ህይወታቸው ካለፈ የአዲስ አበባ አባኮራን ሰፈር ወጣቶች መካከል አብዱ ጅላል ወጉ (ሙራድ)፣የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረው ኑሩ መሐመድ፣አብዱልከሪም ዘይኒ፣ ሰይድ ይመር፣ አሊ መሐመድ፣ ነጃ ሳቢር አወል እና የኢንፎኔት ኮሌጅ ተመራቂ የነበረው ኢድሪስ አደም እና ወጣት ሸበቴ ህይወታቸው በማለፉ ቤተሰቦቻቸው ተረድተው ሀዘን መቀመጣቸው ተጠቁሟል፡፡ በሰጠመችው ጀልባ ከባሌ አካባቢ ህይወታቸው ካለፉት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መካከል አብዱረዛቅ አቡበክር፣ በሪሲና አብዱልወሃብ፣ ሰይፈዲን አሊዪ፣ ሬድዋን ሙሃመድ፣ አሊይ ረሻድ፣ ኢሳ አማን፣ ኑእማን ሁሴን እና ሲራጅ ሙሃመድ እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡ በዚህ አደጋ ከድሬዳዋ አካባቢም ህይወታቸው ያለፈ ወጣቶች እንደሚገኙበትና ቤተሰብም ተረድቶ ሀዘን መቀመጣቸውን የቢቢኤን ዘገባ አመልክቷል፡፡
በዚህ አደጋ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ከ350 ያላነሱ ኤርትራውያንን ጨምሮ በርካታ የሶማሊያ እና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገር ዜጎች ህይወታቸው ማለፉን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ባለፈውበደደቡብ አፍሪካ፣ በየመን እንዲሁም በሊቢያ በረሃ በዓለም አቀፉ አሸባሪው አይ ኤስ አይ ኤል 28 ኢትዮጵያውያን መገደላቸው ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ ያለው የሀዘን ድባብ ሳያባራ አሁን ደግሞ በሊቢያ ሜዴትራኒያን ባህር ሰጥመው መሞታቸው ህዝቡን የበለጠ ሀዘን ውስጥ መክተቱ ታውቋል፡፡
ባለፈው ሚያዝያ መጨረሻ 2007 ዓ.ም. በሊቢያ ታስረው የነበሩ 27 ኢትዮጵያውያን በግብፅ መንግሥት ጥረት እንዲለቀቁ ተደርገው ወደ ካይሮ ሲገቡ የግብፁ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ ኤል ሲሲ በአውሮፕላን ማረፊያው ድረስ በመሄድ አቀባበል ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡





