Tag Archives: Ethiopian Corruption

በስኳርና በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ሙስና የተጠረጠሩ ታስረው ፍርድ ቤት ቀረቡ

ታምሩ ጽጌ

በ184 ሚሊዮን ብር ሙስና የተጠረጠሩ ብርጋዴር ጄኔራል ተካተዋል
የስኳር ኮርፖሬሽን የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታሰሩ

በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የመንግሥት ኃላፊዎችን፣ ነጋዴዎችንና ባለሀብቶች በቁጥጥር ሥር ማዋል የጀመረው ፌዴራል ፖሊስ፣ ከሁለት የስኳር ፋብሪካዎችና ከአንድ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ሦስት ተጠርጣሪዎችን አስሮ ፍርድ ቤት አቀረበ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በቁጥጥር ሥር አውሎ ሐሙስ ሐምሌ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ካቀረባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ፣ በ184,008,000 ብር የተጠርጣሩት ብርጋዴር ጄኔራል ኤፍሬም ባንጌ ናቸው፡፡ ብርጋዴር ጄኔራሉ የተጠቀሰውን ገንዘብ ለግላቸው በመዋላቸው ኦሞ ኩራዝ አምስት ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በሁለት ዓመት እንዲዘገይ ማድረጋቸውንም አስረድቷል፡፡

ሌላው በቁጥጥር ሥር የዋሉት የቀድሞ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ በጋሻው ናቸው፡፡ በመንግሥት የተጣለባቸውን አደራ ወደ ጎን በመተው ኦአይኤ ለተባለ ኮንትራክተር በትውስት አርማታና ሲሚንቶ መስጠታቸውን፣ ከሰጡ በኋላም ከተከፋይ ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ ባለመቀነሱ፣ ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡

አቶ ዮሴፍ ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት ሌላም ጉዳት አድርሰዋል ያለው መርማሪ ቡድኑ፣ የአገዳ ምንጠራ ሥራ በአንድ ሔክታር 25,000 ብር ለባቱ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተሰጥቶ እያለ ሥራውን ከባቱ በመንጠቅና በአንድ ካሬ ሜትር 72,150 ብር ለየማነ ግርማይ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በመስጠት፣ በሕዝብና መንግሥት ላይ ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ሥራ አስኪያጁ በተመሳሳይ የአገዳ ምንጣሮ ላይ፣ ሥራው ሳይከናወን አሥር ሚሊዮን ብርና 20 ሚሊዮን ብር ለተለያዩ ግለሰቦች በመክፈልም ጉዳት ማድረሳቸውን፣ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ቡድን መሪ የነበሩት አቶ ካሳዬ ካቻ ደግሞ 26,771,681 ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው ታስረዋል፡፡

ተጠርጣሪው ሳትኮን ኮንስትራክሽን ለተባለ ኩባንያ ከመካኒሳ እስከ ዓለም ገና ለሚሠራ መንገድ፣ 400 በርሜል ወይም 23,456,481 ብር ግምት ያለው አስፋልት በውሰት መስጠታቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ አቶ ካሳዬ በውሰት የሰጡትን አስፋልት በሦስት ወራት ውስጥ ማስመለስ ሲገባቸው ባለማስመለሳቸው፣ በመንግሥት ላይ የ26,771,681 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

አቶ ካሳዬ በጠበቃቸው አማካይነት በሰጡት ምላሽ፣ ለሳትኮን በትውስት የተሰጠው አስፋልት በባለሥልጣን ተፈቅዶ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ድርጅቱም በወቅቱ ባለመመለሱ በፍትሐ ብሔር ክስ ተመሥርቶበት በሒደት ላይ መሆኑን በማስረዳት ሊጠየቁ እንደማይገባቸው ገልጸዋል፡፡ መጠየቅ አለባቸው ቢባል እንኳን በዋስ ሆነው በውጭ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ የጠየቁ ቢሆንም፣ መርማሪ ቡድኑ ተቃውሟል፡፡

ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ብይን የዋስትና መብት ጥያቄውን በማለፍ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ኤፍሬምና አቶ ዮሴፍ የተጠረጠሩበት ጉዳይ ቀደም ብሎ ከቀረቡ ተጠርጣሪዎች ጋር ተመሳሳይ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ ካሳዬ ላይ የተጠየቀውን 14 ቀናት በመፍቀድ፣ ለነሐሴ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ያለመከሰስ መብት ያላቸውን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታን አቶ አለማየሁ ጉጆን ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸውን በማንሳቱ በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የስኳር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ደስታ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ አቶ ኪሮስ በኮርፖሬሽኑ የቤቶችና የመስኖ ዘርፍ ልማት ዋና ዳይሬክተር እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደሪፖርተር ዘገባ ከሆነ፤ በአጠቃላይ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች ቁጥር እስከ ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት ድረስ 51 ደርሷል፡፡

ተጠየቅ ህወሓት፣ኢህአዴግ እና ብሔራዊ ባንክ፤ በትግራይ ወርቅ ጉዳይ ”በጠራራ ጸሀይ አገር ሲዘረፍ”

አቻምየለህ ታምሩ

በያዝነው የፈረንጆች ዓመት በወርሀ ጥር የወያኔ ካድሬዎችና የአገዛዙ የፕሮፓጋንዳ ተቋማት የሆኑት እነ ኤ.ቢ.ሲ.፣ ዋልታ፣ ፋና፣ ኤ.ዜ.አ. ወዘተ ትግራይ በታሪኳ ስላሉት የወርቅ ምርት መጠን በስፋት ዘግበው ነበር። የአገዛዙ ልሳን ኢ.ቢ.ሲ. እ.አ.አ. ጥር 07 ቀን 2016 ዓ.ም. ባቀረበው ርዕሰ አንቀጽ፤ ዋልታ እ.አ.አ. ጥር 09 ቀን 2016 ዓ.ም. ባስደመጠም የዜና እወጃ ፤ ኤ.ዚ.አ. ጥር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ባስነበበን ሪፖርት ትግራይ እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ 597.7 ቶን ወርቅ [በባህላዊ መንገድ] እንዳመረተችና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዳቀረበች ነግረውናል።

EBC Tigray goldFanaBC Tigray gold news

ይህንን «ልማታዊ ዜና» የሰሙ ብዙ ሰዎች «ትግራይ ከየት አምጥታ ነው ይህንን ያህል ወርቅ አምርታ ለብሔራዊ ባንክ የምታቀርበው?» በማለት ከቁጥሩ ጀርባ ያለውን የምጣኔ ሀብት ትርጉም ሳያጤኑ አጣጥለውት አልፈዋል። ሆኖም ግን ከቁጥሩ ጀርባ ወያኔ ትልቅ አገራዊ ዘረፋና ወንጀል ፈጽሟል። ወያኔ በቁጥሩ ቁማር ተጫውቶ የኢትዮጵያን የሁለት አመት ባጀት ያህል ብሔራዊ ሃብት በአንድ ግብይት ብቻ ወደ ትግራይ አሸሽቷል ወይንም አሻግሯል። ነገሩ እንዲህ ነው።

እ.ኤ.አ.ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ 597.7 ቶን ወርቅ ከትግራይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቀረበ ማለት በ42 ወር ውስጥ 597.7 ቶን ወርቅ ከትግራይ ለብሔራዊ ባንክ ቀረበ ማለት ነው። ይህ ማለት ትግራይ በአመት በአማካኝ 171 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቅርባ ነበር ማለት ነው። በኢትዮጵያ የንግድ ህግ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብቸኛው ወርቅ ገዢና አስቀሟጭ ተቋም ነው። ክልሎች በየክልሎ የተመረተውን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ሲያቀርቡ ብሔራዊ ባንክ ክልሎች ላቀረቡት የወርቅ መጠን ክፍያ ይፈጽማል። ለምሳሌ ትግራይ 597.7 ቶን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሲታቀርብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለትግራይ ክልል የ597.7 ቶን ወርቅ ክፍያ በገንዘብ ይፈጽማል። ያልቀረበ ወርቅ ሪፖርት ተደርጎ ብሔራዊ ባንክ ላልቀረበ ወርቅ እንደቀረበ ተደርጎ ክፍያ ቢፈጽም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሀብት transfter ይኖራል ማለት ነው።

Walta Tigray gold news

ወያኔ የነገረን ትግራይ ለብሔራዊ ባንክ ያቀረበችው 597.7 ቶን ወርቅ ማለት
597, 700 ኪሎ ግራም ወርቅ ማለት ነው።ይህ ማለት ደግሞ 19,216,473 ወቄት ወርቅ ማለት ነው። ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ በነበሩት አመታት ውስጥ አማካኝ የአንድ ወቄት ወርቅ ዋጋ 1,100 የአሜሪካን ዶላር ነው። ይህ ማለት ትግራይ አቀረበችው የተባለው 597.7 ቶን ወርቅ ዋጋ 21. 376 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይሆናል ማለት ነው።
ይህ ማለት [በወያኔ ዜና መሰረት] ትግራይ ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ላቀረበችው 597.7 ቶን ወርቅ ብሔራዊ ባንክ 21. 376 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍሏታል ማለት ነው። የኢትዮጵያ ያለፈው አመት ባጀት አስር ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህ ማለት ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ ትግራይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቀረበችው ለተባለው 597.7 ቶን ወርቅ የተከፈላት 21. 376 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከኢትዮጵያ የሁለት አመት በጀት በላይ ነው ማለት ነው።

ዋናውና ቁልፉ ጥያቄ እውነት ትግራይ ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 597.7 ቶን ወርቅ ወይንም ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ አቅርባለች ወይ? የሚለው ነው።
ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የአለም አገሮችን የወርቅና የሌሎች ማዕድናትን አመታዊ ምርት ማስረጃ የሚሰበስበውንና የሚያደራጀውን የUnited States Geological Survey (USGS) Minerals Resources Program አመታዊ የአለም ማዕድናት ምርት ሰንጠረዥን ማየት በቂ ነው። ይህ የአሜሪካ ተቋም በአለም ላይ ያሉ ማዕድን አምራች አገሮችን የማእድን አመታዊ ምርት አሃዝ ሰብስቦ ደረጃ ያወጣና የአለም አገሮችን በማዕድን ምርት ያወዳድራል። በዚህ መስሪያ ቤት ማስረጃ መሰረት ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ በአለም ላይ በወርቅ ምርት አንደኛ ቻይና ስትሆን አመታዊ የወርቅ ምርት መጠኗ 403 ቶን ነው።

ሁለተኛዋ የአለም ወርቅ አምራች አገር ደግሞ አውስትራሊያ ስትሆን አመታዊ የምርት መጠኗ ደግሞ 250 ቶን ወርቅ ነው። ሶስተኛ አሜሪካ [235 ቶን ወርቅ በአመት] ፤አራተኛ ሩስያ ፌድሬሽን [217.8 ቶን ወርቅ በአመት] ፤ አምስተኛ ፔሩ [161 ቶን ወርቅ በአመት] ፤ስድስተኛ ደቡብ አፍሪካ [160 ቶን ወርቅ በአመት]፤ ሰባተኛ ካናዳ [103 ቶን ወርቅ በአመት] ፤ ስምንተኛ ሜክሲኮ [96.7 ቶን ወርቅ በአመት] ፤ ዘጠነኛ ኢዝቤኪስታን [ 93 ቶን ወርቅ በአመት] እና ጋና [86.5 ቶን ወርቅ በአመት] በአለም ላይ አስሩ ከፍተኛ ወርቅ አምራች አገሮች ናቸው። የዚህ ምንጭ የሚከተለውን ትር መክፈትና መመልከት ይቻላል… http://www.indexmundi.com/minerals/…።

ወያኔ ኢትዮጵያ ትግራይ ብቻ ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቅርባለች ያለው እውነት ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ በወርቅ ምርት በአለም ደረጃ ፔሩን ቀድማ ሩስያን ተከትላ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትሆን ነበር። ልብ በሉ ከአንድ እስከ አስር የወጡ አገሮች ሁሉ ወርቅ የሚቆፍሩት በጣም ዘመናዊ በሆነ መሰርሰሪያ ማሽን ነው። ወያኔ ግን ትግራይ በየ አመቱ 171 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቅርባለች የሚለን በባህላዊ መንገድ አምርታ ነው።

ከፍ ብዬ በለጠፍሁት የUnited States Geological Survey (USGS) Minerals Resources Program አመታዊ የወርቅ ምርት እውነተኛ ደረጃ መሰረት የኢትዮጵያ አመታዊ የወርቅ አምራችነት ደረጃ 29ኛ ሲሆን አመታዊ የወርቅ ምርቷ ደግሞ 12 ቶን ብቻ ነው። ልብ በሉ ይሄ አመታዊ የኢትዮጵያ የወርቅ ምርት ዶዶላ፣ መተከል፣ ለገደንቢና ወለጋ ሜድሮክ በዘመናዊ ቴክኖሎች ታግዞ የሚያመርተውን ይጨምራል። ወያኔ ግን የትግራይን አመታዊ ምርት ብቻ 171 ቶን ይለናል።

ሜድሮክ በዶዶላ፣ በመተከል፣ በለገደንቢና በወለጋ የሚያመርታቸውን ዜሮ አድርገን ኢትዮጵያ ያመረተችውን 12ቱን ቶን ወርቅ ከትግራይ ብቻ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበ የወርቅ መጠን አድርገን ብንወስድ፤ ብሔራዊ ባንክ ከትግራይ በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ እንደቀረበለት ተደርጎ ለትግራይ በጠቅላላ ከከፈለው 21.3 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ውስጥ በያመቱ ላልቀረበ 158 ቶን ወርቅ ክፍያ ፈጽሟል። ይህ ማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከትግራይ ቀረበ ተብሎ ከፍያ ከፈጸመበት 597.7 ቶን ወርቅ ውስጥ የተረከበው ወርቅ 42 ቶብ ብቻ ነው። የተቀረው 555.7 ቶን ወርቅ ወርቁ ከትግራይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሳይቀርብ ብሄራዊ ባንክ ግን ለትግራይ ክፍያ የፈጸመበት የውሸት ቁጥር ነው። ይህ ማለት ብሔራዊ ባንክ ለትግራይ ከከፈለው 21.3 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለትግራይ የተከፈለው ላልቀረበ የውሸት ወርቅ ነው። ይህ ማለት ወያኔ ያልቀረበ ወርቅን አስታኮ 20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያገር ሀብት ወደ ትግራይ wealth transfter አድርጓል። ይህ ማለት የሁለት አመት የኢትዮጵያ የሁለት አመት አመታዊ በጀት ትግራይ ለብሔራዊ ባንክ ወርቅ ባላቀረበችው ወርቅ ተሳቦ ተከፍሏታል። ይህ ማለት የሁለት አመታት የኢትዮጵያ አመታዊ ሀብት ወደ ትግራይ እንዲሄድ ዘረፋ ተፈጽሟል። This is a huge wealth transfter. ወያኔ ከጥር ወዲህም ማራኪ ቁጥር እያቀረበ የአገር ሀብት ወደ ተስፋዋ ምድሩ እያሸጋገረ ይገኛል።

የሚገርመው ትግራይ በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቀረበች በተባለ በወሩ የቀረበው ሌላ ዜና የስርዓቱ ዜና ነው። ፋና በየካቲት 11 ቀን 2008 ዓ.ም [እ.ኢ.አ.] ያቀረበው ዜና ርዕስ እንዲህ ይላል…«ለብሄራዊ ባንክ እየቀረበ ያለው ወርቅ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ነው።» ዜናው በዚህ ብቻ አያበቃም። ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም.[እ.ኢ.አ.] በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ ትግራይ ለብሔራዊ ባንክ አቀረበች እንዳልተባለ «ብሄራዊ ባንክ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ መልኩ ተመርቶ የሚቀርበለት ወርቅ በእጅጉ ቀንሷል። በ2005 ለባንኩ የቀረበለት 8.1 ቶን ወርቅ ነበር። በ2006 ዓ.ም ደግሞ 7.4 ቶን ሆነ፤ በ2007ም በጣም አሽቆልቁሎ 5.4 ቶንድረስ ወርዷል።» አሉን። ይህ ሁሉ የሚሆነው ከትግራይ ብቻ ለብሔራዊ ባንክ በአመት 171 ቶን ወርቅ ቀረበ ተብሎ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደቀላል ወደ ትግራይ transfter እንዲሆን ባደረጉ በአንድ ወር ውስጥ ነው።
አይ አንቺ አገር! ማፍያዎች የውሸት ቁጥር እየቀቀሉ ሌላውን ጾም ደፍተፍና አራቁተው የድሆችን ሀብት ወደ መንደራቸው ያግዛሉ። በአንድ ማጭበርበር ብቻ ሀያ ቢሊዮን ዶላር የአገር ሀብት ወደ መንደራቸው አሸሹ! በቁጥር ሊሸውዱን ሲሞክሩ በትንተና እንዲህ ባጋለጥናቸው ጉዳይ ሀያ ቢሊዮን ዶላር በድብቅ ባልተወለደ አንጀታቸው ከገፈፉ ለሌላው ኢትዮጵያ ምን ያህል ያተርፉለት ይሆን?

የዓለም ባንክ በቅርቡ ለኢትዮጵያ የሰጠው 600 ሚሊዮን ዶላር የገባበት አልታወቀም

በቅርቡ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ 4ኛ ዙር የሴፍቲኔት መርሃ ግብር የሚውል 600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሰጠው ብድር እስካሁን የገባበት አለመታወቁ ተሰማ፡፡ በተለይ የዓለም ባንክ ቦርድ ዋና ዳይሬክተሩ እ.አ.አ. መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም. የባንኩ ዓለም አቀፍ የልማት ማኀበር (IDA) ለኢትዮጵያ መንግስት ብድሩን መስጠቱን እና ሀገሪቱም በተፈቀደው ብድር ተጠቃሚ መሆኗን አረጋግጧል፡፡ ባንኩ ብድሩን የሰጠው 4ኛው ዙር የሴፍቲኔት መርሃ ግብር ውጤታማ ለማድረግ በሚል ሲሆን፤ ይህም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለሚኖሩ የሴፍቲኔትን ለማዳረስ፣ድርቅን ለመቋቋም የሚደረግ ስርዓትን ለማገዝ፣ የምግብ ዋስትና ላልተረጋገጠላቸው እና የገቢ መጠናቸው አነስተኛ የሆኑ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን በመግለፅ፤ ባንኩ በቅርቡ እ.አ.አ መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በድህረ-ገፁ ላይ አስነብቧል፡፡

worldbank agreementባንኩ የሰጠውን ብድር አስመለክቶ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዧንግ ዠ ቺን ቀደም ሲል በሀገሪቱ ይተገበር የነበረው የሴፍቲ ኔት መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ዓለም አቀፉን የሚሊኒየሙን የልማት ግብ ለማገዝ ከሚደረገው ጥረት ውጭ የተራቆተ መሬትን መልሶ ማቋቋም አብሮ ተግባራዊ አለመደረጉን ገልፀዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አሁን የተሰጠው 600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር 10 ሚሊዮን የሚሆኑ የገጠር ነዋሪዎችን ተደራሽ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የተራቆተ መሬትን መልሶ ለማቋቋምም ታሳቢ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ኃይለማርም ደሳለኝ ባለፈው ግንቦት 20 ቀን 2006 ዓ.ም. የኢህአዴግን 23ኛ ዓመት የድል በዓል አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን አረጋግጣለች ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት ከ10 ሚሊዮን የማያንሱ ኢትዮጵውን የምግብ ዋስትና ችግር ስለገጠማቸው ራሱ የኢትዮጵያ መንግስት በጠየቀው መሰረት የዓለም ባንክ የምግብ ዋስትናን ችግር ለመቅረፍ እንዲያግዝ የ600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር መሰጠቱን ባንኩ ይፋ አድርጓል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት ገንዘብና ብድርን የሚመለከት ስምምነቶች በቀጥታ የሚመለከተው የገንዘብ፣ ኢኮኖሚና ልማት ሚኒስቴር የዓለም ባንክ የሰጠውን ብድር አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ ፤እንደማንኛውም ሰው ከሀገር ውስጥ ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከመስማት ባለፈ የዓለም ባንክ ስለሰጠው የ600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር መንግስት የሚያውቀው ነገር እንደሌለ መናገሩን ድሬ ቲዩብ አስነብቧል፡፡ ይህ እስከተዘገበ ድረስ ባለፈው ወር መስከረም መጨረሻ 2007 ዓ.ም. የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሰጠው 600 ሚሊዮን ዶላር ብድር እስካሁን ያለበት አልታወቅም፡፡

የሰመሃል መለስ ዜናዊ 5 ቢሊዮን ዶላር ጉዳይ

የኢትዮጵያ መንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት በሀገሪቱ እንደሚያስፈልግ የተለያዩ ተቋማት በቢሮው ግድግዳ ላይ አሊያም አንድ ለእና በሆነው ኢቴቪ በአመራሮቹ ቢደሰኮርም ከወሬ ባለፈ ሲተገብሩት ግን አይታይም፡፡ በዚህም ምክንያት በሀገሪቱ ግልፅነትና ተጠያቂነት የወሬ ቃልኪዳን እንጂ የተግባር ሲሆን ባለመታየቱ የተለያዩ አስገራሚ ክስተቶች እየተሰሙ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የገንዘብ ሙስና ዋነኛው ነው፡፡meles
ሟቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በገንዘብ በኩል ደሃ ነኝ ሲሉ ከርመው ግብዓተ መሬት ከተፈፀመላቸው በኋላ በ http://www.therichest.org/celebrity networth ዓለም አቀፍ ድህረገፅ አማካኝነት በዓለማችን ካሉ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በ 3 ቢሊዮን የአሜሪካድን ዶላር ሁለተኛ ሃብታም መሆናቸውን አነበብን፡፡ ድህረገፁ ይዋሻል እንዳይባል እስካሁን ቅሬታ ያልቀረበበት፣ተዓማኒነትና ተቀባይነት በመኖሩ የተለያዩ የበለፀጉ የዓለም ሀገሮችን ጨምሮ የተለያዩ ሀብታም ነጋዴዎችንና የሀገር መሪዎችን ሃብት መዝግቦ ይፋ ያደርጋል፡፡ በዚህም መሰረት የደሃዋ ሀገር በተለይም ከ12 ሚሊዮን በላይ ህዝቧ በቀን አንድ እንኳ የሚላስ የሚቀመስ ምግብ አጥተው ዜጎቿ በርሃብ የሚሰቃዩበትን አንዳንዶቹም እንደቅጠል በሚረግፉባት ኢትዮጵያ መሪ የነበሩት አቶ መለስ ባለፀጋ መሆናቸውን አበሰረን፡፡
ሰውዬም ሆኑ ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን በፖለቲካ ስልጣን የሀገር መሪ ከመሆናቸው ውጭ ምንም ዓይነት ሃብትም ሆነ የንግድ ስር ዘርፍ እንደሌላቸው እንዲሁም ደሃ ነን ሲሉ ለሀገሬው ህዝብ አዋጅ አዋጅ ማለታቸው በተለያየ ጊዜ በቴሌቪዥን የተናገሯቸው ቃላቶች ምስክሮች ናቸው፡፡ እኛም ያንን አምነን በገንዘብ ደሃ ናቸው ብለን ለማመን ስናገራግር ኸረ ከበርቴ ናቸው የሚል መረጃ ብቅ አለ፡፡የሳቸው ሳያንስ ሰሞኑን ደግሞ የልጃቸው ሰምሃል መለስ የ5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ቼክ እነሆ እኔም አለሁኝ አለ፡፡

የአቶ መለስ ዜና እና የወ/ሮ አዜብ መስፍን ልጅ የሆነችው ሰመሃል መለስ በአሜሪካ በአንድ ኒዮርክ በሚገኝ ባንክ የ5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የምታንቀሳቅስበት ቼክ መገኘቱ በእንግሊዝ ፓርላማ እ.አ.አ. ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. (ሐምሌ 2 ቀን 2005 ዓ.ም.)ተገለፀ፡፡ ለዚህም ሰመሃል መለስ ብሩን የምታንቀሳቅስበት ቼክ ቅጂ ነው የተባለውም ከላይ እንደምትመለከቱት በአስረጅነት አብሮ ቀርቧል፡፡ ይህንንም ያቀረቡት በእንግሊዝ አንድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ መምህር የሆኑትና የአቶ መለስን አስተዳደር በማስረጃ አስደግፈው እጅግ የሚኮንኑት ዶ/ር ወንድሙ መኮንን ናቸው፡፡semehal
በአሁን ሰዓትም ሰመሃል መለስ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በስሟ ታንቀሳቅሰዋለች ስለተባለው ጉዳይም ጉዳዩ የቀረበለት በእንግሊዝ ፓርላማ የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊ በሆኑት ሚመለከታቸው አካላት የማጣራት ስራ እየተሰራ እንደሆነም እየተገለፀ ይገኛል፡፡ በተለይ የኢህአዴግ አጋር በመሆን፣ ለመለስ አስተዳደር ጥብቅና በመቆምና ለኢትዮጵያም ከፍተኛ እርዳታ በመስጠት የምትታወቀው እንግሊዝ በሰማል መለስ ስም ተቀመጠ የተባለው ብር ትክክለኛ ሆኖ ከተገኘ የራሷን እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ይጠበቃል፡፡
አሁን አቶ መለስ ልጅ ስም ሰነድ(ቼክ) ተገኘ በተባለውም ሆነ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ቅዱስ አድርገው የሚስሏቸው አቶ መለስ አላቸው ስለተባለው 3 ቢሊዮን ዶላር የኢትዮጵያው የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽንም ሆነ እራሱ መንግስት እስካሁን የሰጠው ምላሽም ሆነ ማስተባበያ የለም፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ መንግስት አቶ መለስም ሆኑ ልጃው ሰመሃል አላቸው የተባለውን ቢሊዮን ዶላሮች አምኖ ተቀብሏል እንደማለት እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል፡፡
በተለይ የህግ ባለሙያው አቶ ዘረሰናይ እንዳሉት ከሆነ የአባትና ልጅ ቢሊዮን ዶላሮች ጉዳይ ደግሞ ሙስናን እታገላለሁ ለሚለው የአቶ ኃይለማርይም አስተዳደር እንዲሁም ለፌደራሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ጉዳይ ምላሽ ተነፍጎት የመንደር ሌቦችንና ትናንሽ የመንግስት ሌቦችን እዣለሁ መባሉ ከእንግዲህ የሚታመን እና የሚዋጥ እንደማይሆን አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡
መንግስት በበኩሉ ከእንግዲህ ሙስናን ለመዋጋት መታገስ አይገባኝም ቢልም ሰርዓቱ በራሱ የሙስና ተግባር ላይ መሰረት ያደረገ በመሆኑ መያዝ የሚገባቸውን ጨክኖ አይዝም በሚል ይታማል፡፡ ከፌደራሉ የመንግስት ሰራተኞች በተጨማሪ በክልሎች ላይ ስልጣናቸውን ተገን በማድረግ ሙስና የሚፈፅሙ የመንግስት ሰራተኞች ላይ በቅርቡም በኦሮሚያ ክልል እርምጃ መወሰድ መጀመሩን እሰየው፣ በሌሎችም በሁሉም ክልሎች ተጠናክሮ ይቀጥል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ የለም ህዝብ የሚያውቃቸው ባለስልጣናት እስካልተያዙ ድረስ በዚህ መፎከር ተገቢ አይደለም የሚሉ አልታጡም፡፡
በተለይ ሰሞኑን የአቶ መለስ ልጅ አላት በተባለው ገንዘብ ዙሪያ እሳ የየትኛውም መንግስት ሰራተኛም ሆነ ነጋዴ ስላልሆነች የገንዘቡ ትክክለኛነት ከተረጋገጠ ወላጆቿ ስልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ከህዝብ የዘረፉት ስለሚሆን ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት ምላሽ ሊቸረው እንደሚገባ እየተጠቆመ ይገኛል፡፡ ይህም የተለያዩ የማኀበራዊ ድህረ-ገፆች ላይ በስፋት መወያያ እየሆነ መገኘቱ ጉዳዩ ይበልጥ ትኩረትን ስቧል፡፡ ይህንንም ተከትሎ መንግስት በተለይ ከዳያስፖራ የአባይ ግድብን ጨምሮ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ድጋፍ ቢጠይቅ እንኳ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ለጋሾች ምንም እንኳ ሁልጊዜም ቢሆን ድጋፍ ሲያደርጉ ከሀገሮቹ ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ታሳቢ ቢያደርጉም ለኢትዮጵያ የሚሰጠው እርዳታና ብድር ለባለስልጣናቱ ኪስ ማደለቢያ ነው በሚል የራሳቸውን እርምጃ እንዲወስዱ እንዲህ ዓይነቱን መረጃ የሰሙ ዜጎቻቸው ለኢትዮጵያ የሚደረገውን ድጋፍ በመቃወም አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም፡፡

ምንጭ፡- ኢቦኒ መፅሔት

%d bloggers like this: