እናታችን ፋናዬና ጋዜጠኛ ተመስገን በዝዋይ…
ታሪኩ ደሳለኝ
(የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወንድም)
ያቺ የስምጥ ሽለቆ ከተማ ይበልጥ መንደድ ከጀማመራት አንድ ወር አልፏታል:: በፍትህ መዛባት ስሜቱ የተጎዳ፣ በወገኖቹ ስቃይ መንፈሱ የታመመ፣ ሀገራቸውን ከስቃይ መታደግ በሚችሉበት እድሜያቸው በታሰሩ፣ በተሰደዱና በተገደሉ ወገኖቹ ልቡ ያዘነ፣ ለሀገሩና ለባንዲራው ያለው ፍቅር ጥልቅ የሆነ አንድ ወጣት ጋዜጠኛ በውስጧ ይዛለች፡፡ ዝዋይ፡፡
ከዚህች ከተማ ሦስት ኪሎ ሜትር ገደማ ወደሚርቀው የዝዋይ እስር ቤት ለመሄድ የአስፓልት ዱካ እንዳረፈበት በሚያሳብቀው ኮሮኮንቻማ መንገድ ማለፍ የግድ ይላል፡፡ ከረጅም ዓመታት በፊት ተሰርቶ ዛሬ አስታዋሽ ያጣው ይህ ጎዳና እስረኞችን የመጠየቁን ጉዞ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ከፀሐዩ ግለት ትይዩ ያለው የመሬቱ አቧራ በእግሩ ቆሞ ይሄዳል ብል አይበዛበበትም፡፡ ይህን አልፈን ግዞት ቤቱን እናገኛለን፡፡ የእስር ቤቱን መግቢያ ያለበሰው አቧራ ደግሞ ቅጥሩን በቁፋሮ የተገኘ ጥንታዊ ከተማ አስመስሎታል፡፡ የግቢው ገፅታ ለዕይታ በማይስቡ ነገሮች ቢከበብም፣ ተናፋቂውን ብዕረኛ ግን ደጋግሜ እንድጠይቀው ከወንድምነት የሚዘለው ጥንካሬው ይስበኛል፡፡
በአቧራውና በንዳዱ መካከል ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከቀድሞ ይልቅ በጠነከረ ፅናቱ ስለመኖሩ ሳስብ ደስተኛ እሆናለሁ፡፡ እናታችንስ ምን ታስብ ይሆን? የማይበርድ፣ የማይዳፈንና የማይጠፋ የሀገር ፍቅር ስሜቱ ከአቧራውና ከንዳዱ በላይ መሆኑ ለእርሷ ምን ስሜት ያጋባባታል?
እናታችንና ተሜን ሲገናኙ…
ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 20/07 ዓ.ም ነው፡፡ እናቴ አብረዋት ከኖሩ ጎረቤቶቿ ጋር በመሆን፣ ዝዋይ እስር ቤት ከከተመ አንድ ወር ያለፈውን ተመስገንን ልታየው ተሰናድታለች፡፡ ዝዋይ ከሄደ ወዲህ አይታው አታውቅም፡፡ እንደናፈቃት ግን የፊቷ ገፅታ ይመሰክራል፡፡ እንደ ልጅነቱ ፀጉሩን ባትደባብሰውም፤ እጁን ልትነካውና በዕርጅና አንደበቷ ‹እንዴት ነህ?› ልትለው ወደዚያው እያቀናች ነው፡፡ ጠዋት ወጥተው ማታ እንደሚገቡት፣ ክፍለ-ሀገር ሰንብተው እንደሚመለሱት እንደ ጓደኞቿ ልጆች ተመስገን እንደማይመለስ የተረዳችው እናታችን ልጇ ጋር እየሄደሰች ነው፡፡
ለሊት 11፡30 ከጀሞ ኮንዶሚኒየም የተነሳችው መኪና ዝዋይ የደረሰችው ከጠዋቱ 2፡20 ላይ ነበር፡፡ አስፋልት መሰል ፍርስራሽ መንገዱን ስለለመድኩት ነው መሰለኝ ዛሬ አልሰጠኝም፡፡ ፍተሻውን አልፈን እስረኛና ጠያቂ የሚገናኘበት ቦታ ላይ ደረስን፡፡ ከነበርነው ሰዎች ይልቅ እናታችን ጉጉት እንዳደረባት ለመናገር ሁኔታዋን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡
እናታችን ተመስገን በልጅነቱ ከዕኩዮቹ ጋር ተጫውቶ ሲመጣ ጠብቃዋለች፣ ትምህርት ቤት ውሎ ሲመጣ ጠብቃዋለች፣ ስራ ውሎ ሲመጣ ጠብቃዋለች፤ አንዳንዴም ሲያመሽ ደውላ ‹‹አልመሸም፤ የቀረው ለነገ ይቆይህ›› ትለዋለች፤ እርሱም ሁሌ እንደሰማት ነበር፡፡ ዛሬ ግን ልጇን የምትጠብቀው ከትምህርት ቤት አልያም ከጨዋታ ወይም ከስራ አይደለም፡፡ ከእስር ቤት ውስጥ እንጂ!
እናታችን እስረኞች ከሚወጡበት በር ላይ ከተቀመጠችበት ደቂቃ ጀምሮ አይኗን አላነሳችም፡፡ በሩ ሲከፈት የወታደር ልብስ የለበሰ ወጣት ወጣ፡፡ ከወታደሩ በኋላ ተሜ እስካርፉን እንዳደረገ ተከተለ፡፡ እናቴ ከመቀመጫዋ ተነሳች፤ ዐይኗቿ እንባ አዘሉ፡፡ በዕስረኛና በጠያቂ መሀል ያለውን አጥር ተደገፈች፡፡ ሌላ ጊዜ አጥሩን መደገፍ የሚከለክሉት ወታደሮች እናታችንን ግን ጥቂት ታገሷት፡፡ ምን ያድርጉ? እነሱም እኮ እናት አላቸው፡፡ ከተመስገን ኋላ ሌላ ወታደር አለ፡፡ በሁለት ወታደሮች መካከል ሆኖ ተሜ እናቱን አያት፤ ፈገግ አለ፡፡ እየቀረበ ሲመጣ ግን ፈገግታው ከፊቱ ላይ ጠፍቶ በሀሳብ ተተካ፡፡ እናቴን በዚህ እድሜዋ አንከራተትኳት ብሎ እንዳላሰበ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ከዚህ ይልቅ ስንትና ስንት እናቶች በየቦታው እየተንከራተቱና እየተሰቃዩ ስለመሆናቸው እያሰበ የተጨነቀ ይመስላል፡፡ እናትና ልጅ አንገት ለአንገት ተቃቅፈው ቆዩ፡፡ ምን አለ ባይለያዩ? እንዲሁ እንዳሉ ወደ ቤት ቢሄዱስ ምን ነበረበት?
ይሄ ግን አይሆንም፤ ይሄ ቦታ ተሜ ለሀገሩ የከፈለውን፣ እየከፈለ ያለውንና የሚከፍለውን መስዋዕትነት ማቅረቢያው ቦታ ነው፡፡ ተሜ ወደ ቤት አይሄድም፡፡
ተሜና እናቴ የተጫወቱት ብዙ ነው ፡፡ ሲገናኙ የነበረው ድባብ ጠፍቶ ሁለቱም ደስ ብሏቸዋል፡፡ ተሜ ትንሽ አይቷት ‹‹ከስተሻል›› ሲላት ፈገግ እንዳለች ‹‹አረ አልከሳሁም፤ አንተ ግን ጤናህ እንዴት ነው?››፤ ‹‹ደህና ነኝ››… እናቴ በየመሀሉ ጨዋታቸውን ገታ እያደረገች በስስት ታየዋለች፡፡ እናትና ልጅ የሆድ የሆዳቸውን እንዲያወሩ የፈቀዱት ወታደሮችም ሁለቱን በስስት የሚያዩ ይመስላሉ፡፡
ሳይታወቀን 6፡00 ሆነ፡፡ የመሰነባበቻ ጊዜ ደረሰ፡፡ እናቴ እየሳቀች አቀፈችው፤ ተሜም እየሳቀ ተሰናበታት፡፡ እንደ አመጣጡ በሁለቱ ወታደሮች መካከል ሲሄድ ከጀርባው ትክ ብላ አየችው፡፡ የሆነ ነገር ልትል የፈለገች ትመስላላች፡፡ ‹‹ተመስገን›› አለች፤ አልሰማትም፡፡ በሩን አልፎ ገባ፡፡ እሱ ፊት የደበቀችውን እንባ ማቆም አልቻለችም፡፡ በዝዋይ እስር ቤት ውስጥ ከፈገግታዋ ጋር አለቀሰች፡፡
እሁድ ህዳር 21/07 ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት፡፡ እናቴ ልጇ እስኪፈታ አልጋ ላይ አልተኛም ብላ መሬት መተኛት ከጀመረች 1 ወር ከ17 ቀኗ ነው፡፡ የዛሬውን ለሌት እንዳለፉት ጊዜ አንዴም ተነስታ ‹አይ ልጄ› ወይም ‹እህህ….እህህ….› ሳትል በሰላም ተኝታ በማደሯ ሳልተኛ እያየኋት አደርኩ፡፡ ልክ 12፡10 ሲል ነቃች፡፡ ስታየኝ እያየኋት ነው፡፡ ‹‹ስንት ሰዓት ሆነ?›› ነገርኳት፡፡ አላመነችም፡፡ ተሜ ከታሰረ ጀምሮ እንደ ዛሬ ተኝታ አታውቅም፡፡ ተነሳች፡፡ ‹‹እስከዚህ ሰዓት ስተኛ ዝም ትላለህ?›› አለችኝ፡፡ ‹‹እንዴት ዝም አልልም?›› አልኳት፡፡ ‹ዛሬ የዓመቷ ማሪያም ነች› አለችኝ፡፡ ፊቷ ላይ ድካም አይታይባትም፡፡ … ከደቂቃዎች በኋላ የሀገር ባህል ጥበብ ቀሚስ ለብሳ አየኋት፤ አምሮባታል፡፡ የደስታ ሲቃ ይዞኝ ‹ትላንት እንዴት ነበር?› አልኳት፡፡ በፈገግታ እያየችኝ ‹‹ልጄ ጀግና ነው፤ ጀግና›› ስትል መለሰችልኝ፡፡ እኔም በመስማማት ራሴን ነቀነኩ፡፡ እናቴ በንጋት ፀሐይ ታጅባ የሀገር ባህል ልብሷን እንደለበሰች ስትሄድ በዐይኔ ተከተልኳት፡፡ ይሄ ብርታቷ እስከመቼ እንደሚቆይ እያሰብኩ ነበር፡፡
ተሜ ለሀገሩ ሲልና ሀገሩ እንድትሆን የሚመኝላትን በመፃፉ በግዞት እስር ቤት በአቧራና በንዳድ መሀል እንዲሰነብት ተፈርዶበታል፡፡ ፍትህ የነገሰባት፣ ልጆቿ የማይገደሉባትና የማይሰደዱባት ኢትዮጵያ እንደምትመጣ በተቃጠለ ስሜት እያሰበ፣ በማለዳ የወጣችውን የንጋት ፀሐይ በፈገግታ እያያት እንደሆነ ሳስብ እኔም በደስታ ተሞላው፡፡
ሦስት የፖሊስ መኮንኖች ሰው በማፈን ወንጀል ተጠርጥረው ተከሰሱ
ታምሩ ፅጌ
-አድራሻቸው በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ የሆኑ ሦስት የፖሊስ መኮንኖች፣ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት አንድ ሰው አፍነው ወደ ጅግጅጋ በመሄድ ላይ እያሉ ተይዘው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አምስተኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎቹ ዋና ኢንስፔክተር ጐይቶም አረጋዊ ኪዳነ ማርያም፣ ረዳት ኢንስፔክተር አንተነህ አስናቀ ተፈራና ኮንስታብል ዘሪሁን ሲሳይ ሲሆኑ፣ ሁሉም በሶማሌ ክልል የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪ መሆናቸውን የክስ ቻርጁ ያስረዳል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ለሕግ ተቃራኒ በሆነ መንገድ በማስገደድና ከሕግ ውጪ የግል ተበዳይ ናቸው የተባሉትን አቶ አህመድ ኑርን ይይዟቸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከሶማሌ ክልል ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ተበዳዩን የያዟቸው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጐተራ አካባቢ መሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡
የግል ተበዳይ ናቸው የተባሉት አቶ አህመድን ከነበሩበት ተሽከርካሪ ላይ ጐትተው በማውረድ፣ በሽጉጥ በማስፈራራት፣ በቦክስ ፊታቸውንና የተለያዩ የሰውነት ክፍላቸውን በመምታት ራሳቸውን ሲስቱ፣ ተጠርጣሪዎቹ በያዙት ተሽከርካሪ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ መድኃኔዓለም አካባቢ እንደወሰዷቸውም ተገልጿል፡፡
ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ በሚገኘውና ‹‹የሶማሌ ክልል ዳያስፖራ ቢሮ›› በመባል በሚታወቀው ጊቢ በሚገኝ ሰርቪስ ቤት ውስጥ በማስገባት፣ ለሦስት ሰዓታት እንዳቆዩአቸውም ክሱ ያብራራል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከሦስት ሰዓታት በኋላ የሰሌዳ ቁጥሩ 0071 በሆነ የሶማሌ ክልል ፖሊስ ፒክአፕ ተሽከርካሪ ጭነው፣ ወደ ጅግጅጋ ያመራሉ፡፡ ልዩ ቦታው አዋሽ ድልድይ ኬላ ላይ የሚጠብቁ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል አባላት በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏቸውና ሰውን ከሕግ ውጪ ይዞ ማስቀመጥ ወንጀል መከሰሳቸውን የክስ ቻርጁ ያስረዳል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ዋስትና የጠየቁ ቢሆንም የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አምስተኛ ወንጀል ችሎት ኅዳር 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ውድቅ አድርጐ በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከራከሩ ብይን ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ
አመክሮና በቀለ ገርባ
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ምክትል ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ ስራ አስፈፃሚ የነበሩት “ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲን ሽፋን በማድረግ የአሸባሪ ቡድን የሆነው ኦነግ አባል ሆነዋል” በሚል ክስ ተመስርቶባቸው የ8 ዓመት እሥር የተበየነባቸው ሲሆን፤ ይግባኝ ጠይቀው እስሩ ወደ 3 ዓመት ከ7 ወር ዝቅ ተደርጎላቸዋል፡፡
ከ3 ዓመት ከ7 ወር የእስር ጊዜ ውስጥም 3ቱን ዓመት በመጨረሳቸው በአመክሮ ይፈቱ ዘንድ ለማረሚያ ቤቱ ያመለከቱ ሲሆን ማረሚያ ቤቱም ‹አመክሮ መስጠትም አለመስጠትም መብታችን ነው› በማለት እስከአሁን ሊፈታቸው አልቻለም፡፡ ይህም ብዙ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡
አንዳንድ ህጋዊ ሁኔታዎች ስለጉዳዩ፡
አመክሮ ምንደር ነው?
ሌላውን ትርጉም ትተን የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ‹በተወሰነ ጊዜ በአመክሮ መፈታት› በሚለው ክፍል በተለይም በአንቀፅ 202 እንደደነገገው፡
“ተቀጭው ከተወሰነበት የእስራት ጊዜ ከሶስት እጅ ሁለቱን እጅ ወይም ፍርዱ የእድሜ ልክ እስራት ሲሆን ሀያ ዓመት በፈፀመ ጊዜ አግባብ ባለው አካል ወይም በጥፋተኛው አሳሳቢነት ጥፋተኛውን ከቅጣቱ ነፃ ያወጣዋል፡፡” ይህም ማለት አመክሮ 2/3ኛውን የቅጣት ጊዜውን የጨረሰ ታራሚ ከእስር የሚፈታበት አሰራር ነው፡፡
አመክሮ ለማግኝት ምን መስፈርት ማሟላት ያስፈልጋል?
የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ከላይ በጠቀስነው አንቀፅ 202 ላይ አመክሮ ለማግኝት አንድ እስረኛ ማሟላት የሚያስፈልገውን መስፈርቶች ይዘረዝራል፡፡ ይህም፡
– ‹ታራሚው በስራ ጠባዩ የተረጋገጠ መሻሻል አሳይቶ እንደሆነ…›
– ‹ካሳ የመክፈል ግዴታ ተጥሎበት ከነበረና ካሳውን መክፈሉ የተረጋገጠ እንደሆነ…›
– ‹አመሉና ጠባዩ መልካም አኗኗር ለመኖር የሚያስችለውና በአመክሮ መፈታቱ መልካም ውጤት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ የታመነ እንደሆነ..›
ነው ብሎ ይደነግጋል፡፡
ማረሚያ ቤት ወይስ ፍርድ ቤት?
ታራሚን በአመክሮ የመልቀቅ የመጨረሻው ስልጣን የፍርድ ቤት፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን ማረሚያ ቤቱ በራሱ ተነሳሽነት ወይም በታራሚው አሳሳቢነት ለፍርድ ቤት ሲያቀርብ ነው ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሚሰጠው፡፡ እዚህ ላይ ማረሚያ ቤቱ ትልቁን ስልጣን ይዞ እናገኛለን፡፡ ማረሚያ ቤቱ ለፍርድ ቤት ማቅረብ ካልፈለገ ሊተወው የሚችልበት አግባብ አለ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ማረሚያ ቤቱ በሕግ ስር ያለ አካል እንደመሆኑ መጠን በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 202 ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን ላሟላ ታራሚ አመክሮ ሊከለክል አይችልም – የታራሚው መብት ነውና!
በቀለ ገርባስ?
አቶ በቀለ ገርባ ከተፈረደባቸው የአምስት ዓመት እስር ውስጥ 2/3ኛውን ወይም 3 ዓመት የሚሆነውን ጨርሰው የአመክሮ ጥያቄያቸው በማረሚያ ቤቱ በኩል ለፍርድ ቤት እንዲቀርብላቸው ቢጠይቁም ማረሚያ ቤቱ ‹አመክሮ መስጠትም አለመስጠትም መብታችን ነው› የሚል መልስ እንደሰጣቸው ተሰምቷል፡፡
1ኛ. አመክሮ መስጠት የማረሚያ ቤት መብት ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው፡፡ መስፈርቱን ያሟላ ታራሚ አመክሮ የማግኝት መብት ያለው መሆኑ በሌላ በኩል አመክሮ ሰጭውን አካል ላይ ግዴታ ይጥላልና፡፡
2ኛ ሌላው አቶ በቀለ ገርባ መስፈርቱን አሟልተዋል ወይስ አላሟሉም የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ 2/3ኛውን የእስር ጊዜ መጨረስ የሚለውን Objective መስፈርት እንዳሟሉ ግልፅ ሲሆን፡፡ ችግሩ የተፈጠረው Subjective መስፈርቱ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ይህም ማለት በእስር ወቅት መልካም ፀባይ አሳይተዋል ወይስ አላሳዩም የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ አንድ ታራሚ በእስር ወቅት ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ካሳየ የቅጣት ማስጠንቀቂያ ከመፃፍ እስከ ብቻውን ማሰር (Solitary Confinement) ድረስ ያሉ እርምጃዎች በማረሚያ ቤቱ ሊወሰዱበት ይችላሉ፡፡
አቶ በቀለ ገርባ ከፀባያቸው ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ቅጣት ያልተወሰደባቸው ከመሆኑም ሌላ መልካም ፀባይ እንዳሳዩ ከማረሚያ ቤቱ እንደተነገራቸው ራሳቸው ገልፀዋል፡፡ በቀለ ገርባ ምም መስፈር አሟልተዋል ማለት ነው፡፡ ታዲያ ምን ይሆን አቶ በቀለን በአመክሮ ከመፈታት ያገዳቸው?
አንዳንድ ነገሮች…
ባለው አካሄድ አብዛኛው ታራሚዎች በአመክሮ ይፈታል፡፡ ከሌባ እስከ ሙሰኛ፡፡ High Profile በሆኑ ክሶች የተከሰሱ ሰዎች ሳይቀሩ በአመክሮ ሲፈቱ እንደነበር እናስታውሳለን ለምሳሌ ቴዲ አፍሮ 24 ወራት ተፈርዶበት 16 ወራትን ጨርሶ በአመክሮ ተፈቷል፡፡ አቶ አሰፋ አብርሃ 9 ዓመት ተፈርዶባቸው ሰባት ዓመታት ታስረው ከብዙ ውዝግብ በኋላ በአመክሮ ተፈተዋል፡፡ በሌላ በኩል በቅንጅት ክስ ስር ተከሰው የነበሩት አቶ ዳንኤል በቀለና አቶ ነፃነት ደምሴ 30 ወራት የተፈረደባቸው ሲሆን 20 ወራትን በእስር አሳልፈው አመክሮ ቢጠይቁም ማረሚያ ቤቱ ‹ፍርዳችሁን ጨርሳችሁ ውጡ› በሚል ምክንያት አመክሮ ከልክሏቸው ነበር፡፡
እንግዲህ አቶ በቀለ ገርባ በሕጉ የተቀመጠውን መስፈርት አሟልተው እያለ በአመክሮ የመፈታት መብታቸው አልተከበረም ወይም ማረሚያ ቤቱ ግዴታውን ሊወጣ አልፈለገም!
ምክንያት: በጉልበተኞች የምትተዳደር ሀገር ዜጋ ስለሆኑ!
ልዩ ማስታወሻ፡-ይህ ባለፈው ጥር 16 ቀን 2006 ዓ.ም. የዞን 9 ብሎገርና የአምቦ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር ዘለዓለም ክብረት ከመታሰሩ በፊት የፃፈው ቢሆንም፤በአሁን ሰዓት እሱ ራሱ በግፍ እስር አቃቂ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ይገኛል፡፡
#FreeBekeleGerba
የሴቶች ጉዳይ ይመለከተናል የምትሉ ከወዴት ናችሁ? የእህታችን የሐና ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው!!
ብስራት ወልደሚካኤል
በቅርቡ በመዲናችን አዲስ አበባ አንዲት የ16 ዓመት ባለ ብዙ ተስፋዋ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው እህታችን ሐና ላላንጎ ለክፉ ድርጊታቸው ቃላት በማይገልፃቸው 5 ጨካኝ ወንዶች ከሰብዓዊነት በራቁ አረመኔ ወንዶች ያውም በቀን ከትምህርት ቤት ወደ መኖሪያ ቤቷ በተሳፈረችበት ታክሲ ስትሄድ ሾፌር፣ረዳትና ሌሎች ግብር አበሮቻቸው ታግታ ለቀናት በመፈራረቅ ተደፍራ ህይወቷ አልፏል፡፡ ዜናው እጅግ ዘግናኝ ከመሆኑ የተነሳ ለመግለፅ ያስቸግራል፡፡ የልጆቹን ድርጊት አንዳንዶቹ ከሌሎች የቤትና የዱር እንሰሳ ድርጊት ጋር ሊያይዙ ይሞክራሉ፡፡ እውነታው ግን የትኛውም እንሰሳ ምስያውን ያውም ተስፈኛ የስንት ታናሽ እህቱን፣ ልጁን ወይንም ወገኑን በጅምላ አግቶና አስገድዶ ደፍሮ የሚገል ፍጡር የለም፡፡
ሐና ላይ አረመኔዎች የፈፀሙት ድርጊት በምንም የሚገለፅ አይደለም፡፡ እጅግ ልብን የሚናካና አሳዛኛ ተግባር ነው፡፡ የድርጊቱ ፈፃሚዎችም የማያዳግም እርምጃ ወይም ቅጣት በአደባባይ ሊያገኙ ይገባል፡፡ ምንም እንኳ ዛሬ ያቺ ተስፈኛ ለግላጋ ወጣት በህይወት ኖራ የአረመኔዎችን ቅጣት በዓይኗ ለማየት ባትታደልም ለሌሎች አረመኔዎች ማስተማሪያ እንዲሆን እና ሌሎች እህቶቻችንም ቀና ብለው በሀገራቸው በኩራትና በነፃነት ይንቀሳቀሱ ዘንድ ለሐና ተብሎ የሚሰጠው ፍትህ የሁሉም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ በሌለበት ፍትህ መጠየቅ ህልም ቢሆንም፤ እነኚህ የድርጊቱ ፈፃሚ አረመኔዎች ግን በምንም መልኩ ተገቢውን ለሰሩት አሰናዋሪ ጭካኔ ለተሞላበት ተግባር ተገቢውን ቅጣት ሊያገኙ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡
እዚህ ላይ በጣም የገረመኝ ጥያቄ የፈጠረብኝ ነገር አለ፡፡ ይኸውም በኢትዮጵያ ያሉ የሲቪክ ተቋማት በተለይም የሰቶች ጉዳይ ቅንጅት፣ ማኀበራት፣ …የሚባሉ ተቋማት ባለፈው 2004 ዓ.ም. የበረራ አስተናጋጇ (ሆስተሷ) አበራሽ ኃይላይ ላይ በቀድሞ ባለቤቷ ተወሰደ በተባለው የበቀል እርምጃ የአካል መጉደል ደርሶባታል በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ከማድረግ በተጨማሪ በቅንጡ ሸራተን አዲስ ሆቴል ተደጋጋሚ መግለጫ እስከመስጠት ደርሰው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ለዚህም እኔው ራሴ ከዚህ ቀደም በምሰራበት ጋዜጣ ለጉዳዩ ከ2 ጊዜ ያላነሰ የዜና ሽፋን በመስጠት በመግለጫዎቹና ተቃውሞዎቹ ላይ ልክ እንደሌሎቹ የሙያ አጋሮች በተደረገ ጥሪ ተገኝቼ የታዘብኩት እውነታ ነበር፤ከሙያ በተጨማሪ በግሌም ጥቃቶችን የምቃም ነኝና፡፡ ያኔም ሆነ አሁን በካሚላት፣ በአበራሽ ላይም ሆነ በማንኛውም ሴትም ሆነ ወንድ ላይ በአጠቃላይ በማንኛውም የሰው ልጅ ላይ የሚፈፀም ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን አጥብቄ የምቃወመው ተግባር ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተማሪ ሐና ላይ በተፈፀመው አሰቃቂ ተግባር ያኔ ለነ አበራ ኃይላይ ይደረግ የነበረው እንቅስቃሴ ዛሬ የት ሄደ? ለምን?
እኔ እስከሚገባኝ ሐናም አበራሽም ሆነች ካሚላት ሁሉም ሴቶች፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሁሉም ወገኖቻችን ናቸው፡፡ ስለዚህ ሌሎች ተቋማትም ሆኑ ሴቶች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ተቋማት ከሐና ጎን ሲቆሙ አላየሁም፤ ወይም አልተገነዘብኩም፤ ለምን? ሁሉም ላይ የሚፈፀም ጥቃት እኩል ድጋፍ ሊደረግ ይገባል፤ ቢቻል ያኔ መግለጫ ለመስጠት ጋዜጠኞችን ሲጨቀጭቁ የነበሩ ይመለከተናል የሚሉ የሴቶች ማኀበራትና ተቋማት ዛሬ ከወዴት ናችሁ? ማንኛውም ሴት ላይ የሚፈፀም ጥቃት በእኩል ትኩረት በመስጠት ከጎናቸው መሆናችንን ልናሳይ የሚገባ ይመሰለኛል፡፡
በርግጥ ይህን ስል ጉዳዩ ወንዶችን አይመለከትም ማለቴ አይደለም፤ በደንብ ይመለከተናል፡፡ ምክንያቱም ሰው በመሆናችን ብቻ ሴትም ሆነ ወንድ ላይ የሚፈፀም ጥቃት የሰው ልጅ ላይ በመሆኑ ይመለከተናል፡፡ ግዴታችንም ነው፡፡ ከዛ በተጨማሪ እስኪ ማነው እናቱን የሚጠላ? ማነው እህቱ ላይ ሌላ ሰው የዚህን ዓይነት አሰቃቂ ድርጊት እንዲፈፀም የሚፈቅድ? እስኪ ማነው ልጁ ላይ እንዲህ እንዲፈፀም የሚፈቅድና ቢፈፀም ደስተኛ የሚሆን? ማንም ያለ አይመስለኛም፤ሊኖርም አይገባም፡፡ ጉዳዩ የሁላችንም ነው የምላው ለዚህ ነው፡፡
በሀገሪቱ ተመሳሳይ ድርጊት ከእንግዲህ እንዳይፈፀም ተገቢውን ፍትህ ከመስጠት በተጨማሪ ለሌሎች እህቶቻችን ቢያንስ ድርጊቱን እናወግዛለን ፣ ከጎናችሁ ነን፤ ተገቢው ፍትህ መሰጠት አለበት የሚሉ የተቃውሞ ድምፆች በጋራ በወድሞቻችን እና እህቶቻችን ሊዘጋጅ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ አለበለዚያ ድርጊቱ ነገም ሊቀጥል ይችላል፡፡ አሁንም ይሄ የሐናም ሆነ የነ ካሚላትና አበራሽ ላይ የተፈፀሙ ድርጊቶች አዲስ አበባ በመሆናቸው ለአደባባይ በቁ እንጂ…በየ ክልል ከተሞችና በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ከተጠቀሱት የሚልቅ ድርጊቶች እንደሚፈፀሙ ይታመናል፡፡ ይህ ሁሉ እንዲቀር ሴት ወንድ በሚል የፖለቲካ ፍጆታ መድረክ ከማድመቅ በዘለለ በእውነት ለሁሉም ልንደርስላቸው ይገባል፡፡
ንፁሃንን አሸባሪ እያለ በግፍ የሚያስረውና የሚያሰቃየው መንግስትስ የህፃናትና ተማሪዎችን ደህንነት ያውም በአዲስ አበባ እንዴት መታደግ አቃተው; ስንቱን የግለሰብ ምስጢር እየበረበረ የሚከታተል ደህንነትስና ፖሊስስ ንፁሃንን ከማደን ተላቆ ወንጀለኞችን በማደን እና ለፍርድ ከማቅረብ ረገደ እንዴት ነው?
ሐና…ፈጣሪ ነፍስሽን በገነት ያኖረው ዘንድ ተመኘሁ…
አሁንም…ፍትህ ለሐና ! ፍትህ ለሐና!!….ፍትህ ለሐና…!!
አቃቢ ህግ በጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ ላይ የመሰረተውን ክስ እንዲያሻሽል ታዘዘ
- ክሱ ተሻሽሎ መቅረቡን ለማየት ለህዳር 24 ቀጠሮ ተሰጥቷል
የፌደራል አቃቢ ህግ በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በጦማርያኑና በጋዜጠኞቹ ላይ የመሰረተውን የሽብር ክስ እንዲያሻሽል የልደታ ከፍተኛ ችሎት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
ፍርድ ቤቱ ዛሬ ህዳር 3/2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት ቀደም ብሎ የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ መርምሮ ብይን በመስጠት በንባብ አሰምቷል፡፡ በዚህ መሰረትም ፍርድ ቤቱ በክስ መቃወሚያው ላይ የቀረቡትን ዝርዝር ነጥቦች መርምሮ በተወሰኑ ነጥቦች ላይ አቃቢ ህግ ክሱን እንዲያሻሽል ትዕዛዝ ሲሰጥ፣ በሁለተኛነት ቀርቦ የነበረው የክስ ይዘት በአንደኛው የክስ ይዘት ላይ መጠቃለል ስለሚችል ሁለተኛውን የክስ ይዘት ፍርድ ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርጎታል፡፡
በክስ ዝርዝሩ ላይ ተከሳሾቹ ‹‹ለአመጽ ማነሳሳትና መምራት›› የሚያስችል ስልጠና ወስደዋል በሚል በተጠቀሰው ላይ ስልጠናው መቼ፣ በማን እና በምን ጉዳዮች ላይ ተሰጠ የሚለው ግልጽ ስላልሆነ አቃቢ ህግ ክሱን እንዲያሻሽል ተጠይቋል፡፡
በተጨማሪም ተከሳሾቹ አመጽ ለመምራት የስራ ክፍፍል አድርገዋል በሚል የተጠቀሰባቸው የክሱ ይዘት ‹‹ምን አይነት የስራ ክፍፍል፣ ማን ምን እንዲሰራ ክፍፍሉ ተደረገ›› የሚለውን ስለማያመለክት ይህንንም መሻሻል እንዳለበት ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡
በተጨማሪም በክሱ ዝርዝር ላይ ‹‹ቡድን›› እና ‹‹ድርጅት›› በሚል (ግንቦት 7፣ ኦነግ ወይስ ሌላ የሚለውን ስለማይገልጽ) በደፈናው የቀረቡት ነጥቦች ላይ በዝርዝር መቀመጥ ስላለባቸው አቃቢ ህግ ማሻሻያ እንዲያደርግ ታዝዟል፡፡
በሌላ በኩል የተከሳሽ ጠበቆች ‹‹በኢሳት ሬድዮና ቴሌቪዥን መረጃ በመስጠት›› በሚል ተከሳሾች ላይ የቀረበው የክስ ይዘት ሆን ተብሎ ወደ ሌላ አካል (ግንቦት 7) ጋር ለማገናኘት ነው በሚል ያቀረቡትን መቃወሚያ፣ ‹‹በኢሳትና በግንቦት 7 መካከል ያለው ግንኙነት ወደፊት በማስረጃ የሚታይ ነው በሚል ፍርድ ቤቱ መቃወሚያውን ውድቅ አድርጎታል፡፡
ከተከሳሽ ጠበቆች መካከል የሆኑት አቶ አምሃ መኮንን ከችሎቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ጠበቆች ላይ የቀረበውን የክስ መቃወሚያ ጊዜ ወስዶ መርምሮ ውሳኔ እንዳሳለፈ ጠቅሰዋል፡፡ ይሻሻላሉ የተባሉት የክሱ ይዘቶች ላይ ጥያቄ የተነሳላቸው አቶ አምሃ የውሳኔው ዝርዝር በጽሑፍ ገና እንዳልደረሳቸው ጠቅሰው፣ ‹‹አቃቢ ህግ በታዘዘው መሰረት ክሱን የማያሻሽል ከሆነ ይሻሻላሉ የተባሉት የክሱ ይዘቶች ውድቅ የሚሆኑበት አሰራር አለ›› ብለዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ክሱ ተሻሽሎ መቅረብ አለመቅረቡን ለማየት ለህዳር 24/2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ኢትዮጵያ