Tag Archives: Ethiopian Justice

በዶ/ር መረራ ላይ ሁለት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ተሰሙ

ጌታቸው ሺፈራው

የፌደራል አቃቤ ህግ በኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ ዛሬ ጥቅምት 24/2010 ዓም ሁለት ምስክሮች አሰምቷል። ሁለቱም ምስክሮች ታህሳስ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ዶ/ር መረራ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ከኮምፒውተር የወጣን ፅሁፍ የእራሴ ነው ብለው ሲፈርሙ ተገኝተን ታዝበናል ያሉ የደረጃ ምስክሮች ናቸው። ስማቸው ደራራ እና ጌታቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤት ያስመዘገቡት ምስክሮች በአንድ ቀን የታዘቡ እና የሚተዋወቁ ጓደኛሞች እንደሆኑ ገልፀዋል።

Dr.Merera Gudina
ዶ/ር መረራ ጉዲና

ደራራ (አንደኛ ምስክር) ወደ ማዕከላዊ የሄደበትን ምክንያት ሲጠየቅ ቶሎሳ የሚባል ዘመዱን ሊጠይቅ መሄዱን፣ ብቻዬን ከምሄድ በሚል ሁለተኛ ምስክር (ጌታቸው) አብሮት እንዲሄድ ጠይቆት ከሚሰሩበት መስርያቤት አስፈቅደው አብረው እንደሄዱ እና ፖሊስ ታዛቢ እንዲሆኑት ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ጠይቋቸው እንደተስማሙ ገልፆአል።

በሌላ በኩል ሁለተኛ ምስክር (ጌታቸው) አንደኛ ምስክር (ደራራ) ጋር አንድ ክፍለ ከተማ እንጅ አንድ መስርያ ቤት እንደማይሰሩ፣ ብቻውን በመስርያ ቤት ትዕዛዝ ለመርማሪዎች ሰነድ ለመስጠት እንደሄደ፣ ስራውን ጨርሶ ከመርማሪው ቢሮ ሲወጣ ኮማንደር አሰፋ በተባለ የምርመራ ክፍል ሀላፊ እማኝ እንዲሆን መጠየቁን፣ እሱ ስራዉን ጨርሶ ከወጣ እና እማኝ ለመሆን ፈቃደኛ ከሆነ በኋላ ደራራን እንዳገኘው እንዲሁም አንደኛ ምስክር (ደራራ) ወደ ማዕከላዊ የመጣበትን ጉዳይ የነገረው እማኝ ከሆነ በኋላ እንደሆነ አንደኛ ምስክር ከመሰከረው የተለየ ቃሉን ለፍርድ ቤቱ ሰጥቷል።

በተጨማሪም አንደኛ ምስክር በወቅቱ ዶ/ር መረራ ሹራብ ለብሰው ነበር ሲል ሁለተኛ ምስክር ጅንስ ሱሪና ጅንስ ሸሚዝ ለብሰው ነበር ብሏል። አንደኛ ምስክር (ደራራ) ዶ/ር መረራ በኮማንደር አሰፋ ብቻ ታጅበው ምስክሮቹ ወደነበሩበት ምርመራ ቢሮ እንደገቡ ሲመሰክር፣ ሁለተኛ ምስክር (ጌታቸው) ከኮማንደር አሰፋ በተጨማሪ ሁለት ፖሊሶች ነበሩ ብሏል።

አንደኛ ምስክር ዶ/ር መረራ ወደ ምርመራ ቢሮ እስኪመጡ በግምት ለአንድ ሰዓት ያህል መጠበቃቸውን ሲገልፅ፣ ሁለተኛ ምስክር ( ጌታቸው) በግምት ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ያህል ብቻ እንደጠበቁ ገልፆአል። አንደኛ ምስክር የዶ/ር መረራ ነው ከተባለ ኮምፒውተር ፕሪንት ተደርገው የወጡ ፅሁፎችን በከፊል እንዳነበበ ሲመሰክር ሁለተኛ ምስክር የፅሁፎችን ይዘት ብቻ ሳይሆን ርዕሶችንም አለማንበባቸውን፣ ዶ/ር መረራ አንብበው ሲፈርሙ ታዝበው መፈረማቸውን ገልፀዋል።

በዶ/ር መረራ ላይ ይቀርባሉ ተብለው የነበሩት ሌሎች ሁለት ምስክሮችን ፖሊስ በአድራሻቸው ፈልጎ እንዳላገኛቸው የገለፀ ሲሆን ሁለቱን ቀሪ ምስክሮች ለመስማት ለህዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

የአቶ ዮናታን ተስፋዬ ይግባኝ ክርክር ተሰማ

ጌታቸው ሺፈራው

በማነሳሳት የ”ሽብር” ክስ ተመስርቶበት 6 አመት ከ6 ወር የተፈረደበት አቶ ዮናታን ተስፋዬ የይግባኝ ክርክር ዛሬ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተሰምቷል። አቶ ዮናታን ተስፋዬ የተፈረደበት ፌስ ቡክ ላይ በፃፈው ፅሁፍ ሲሆን ጠበቃው አቶ ሽብሩ በለጠ አቶ ዮናታን ተስፋዬ የተከሰሰውና የተፈረደበት ሀሳቡን በነፃነት በመግለፁ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አብራርተዋል። ከዚህም ባሻገር አቶ ዮናታን የተከሰሰበትና የተፈረደበት አንቀፅ በህትመት ለወጣ ፅሁፍ የተደነገገ እንጅ በማህበራዊ ሚዲያ ለወጣ (ላልታተመ ፅሁፍ) እንዳልሆነ በመግለፅ አቶ ዮናታን በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 6 ሊከሰስ እና ሊቀጣ አይገባም ነበር ብለው ተከራክረዋል።

ጠበቃው አቶ ዮናታን ህገ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ ሀሳቡን በነፃነት ገለፀ እንጅ ሽብርተኝነትን የማበረታት ተግባር አለመፈፀሙን፣ ሆኖም የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ህግና ማስረጃን መሰረት ያላደረገ፣ ስህተትና ያልተገባ ነው ብለዋል። በመሆኑም ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በመሻር ይግባኝ ባይን እንዲያሰናብት ጠይቀዋል። ይህ ከታለፈ እንኳን እስካሁን የታሰረው ጊዜ በቂ ተብሎ ከእስር እንዲለቀቅ አመልክተዋል። ፍርድ ቤቱ አቶ ዮናታን በበቂ እንዲለቀቅ የቀረበውን ጥያቄ ካለፈውም ፣ ለስር ፍርድ ቤቱ 6 በመረጃ የተረጋገጡ ማቅለያዎች ቀርበው ፣ በእነዚህ ማቅለያዎች መሰረት ስድስት እርከን ዝቅ ብሎ መወሰን ሲገባ ሶስት እርከን ብቻ በመቀነስ ውሳኔ ስለተሰጠ ማቅለያዎቹ ተይዘው የቅጣት ውሳኔው ተሻሽሎ እንዲወሰን የይግባኝ ክርክር አቅርበዋል።

በሌላ በኩል አቃቤ ህግ አቶ መኩርያ አለሙ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በፅሁፉ በኦነግ አላማ ሲያነሳሳ እንደነበር እና የተፈረደበትም በዝቅተኛ ደረጃ በመሆኑ ፍርዱን ሊቀንስለት አይገባም ብሎ ተከራክሯል። አቶ ዮናታን በበኩሉ አቃቤ ህግ ከኦነግ ጋር ግንኙነት አለው ብሎ ክስ ማቅረቡንና በዚህም እንደተፈረደበት በማስታወስ፣ ሆኖም በቀረበው ክስ ላይ ከኦነግ ጋር አለው ስለተባለው ግንኙነት ማስረጃ እንዳልቀረበ፣ ፍርዱም ትክክል እንዳልሆነ ተከራክሯል።

አቶ ዮናታን ተስፋዬ የተከሰሰውና የተፈረደበት ከ”ማስተር ፕላን” ጋር በተያያዘ ኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ በነበረው የህዝብ ንቅናቄ ሰበብ ሲሆን አቶ ኃይለማይያም ደሳለኝ በመንግስት ሚዲያዎች ቀርበው ኦሮሚያ ውስጥ የተፈጠረው ችግር የመልካም አስተዳደር ችግር እንጅ የሽብር ባህሪ የለውም ብለው መግለጫ ሰጥተው እንደነበር ጠበቃ ሽብሩ በለጠ አስታውሰዋል። የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ ለመበየን ለህዳር 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ተቀጥሯል።

የፍርድ ቤት ችሎት ትዝብት

ማህሌት ፋንታሁን

የጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ትዝብት። ብዙ መዝገቦች በቀጠሯቸው መሰረት ሳይሰሩ ተለዋጭ ቀጠሮዎች እየተሰጠባቸው ነው። የሚሰጠው ምክንያት ‘ለችሎቱ አዲስ ዳኞች በመሆናችን’ የሚል ነው። ተከሳሾችም በጉዳያቸው አላግባብ መራዘም እና በማረሚያ ቤት በሚደርስባቸው በደል ተማረው አቤቱታቸውን እያሰሙ ነው።
የዛሬዎቹን አቤቱታዎች በስሱ እነሆ!

� አቤቱታ አንድ። በእነ ክንዱ ዱቤ መዝገብ 2ኛ ተከሳሽ ዘመነ ጌቴ ፤ “ማእከላዊ እያለሁ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ግፍ እና በደል ደርሶብኛል። በድቅድቅ ጨለማ ለ6ወር ተቀምጫለሁ። በድብደባ ብዛት የግራ አይኔ ማየት አይችልም። ዘሬን እንዳልተካ የዘር ፍሬዬን መተውኛል። አማራነታችን እየተጠቀሰ ይሰድቡናል። እኛ ስንወለድ አማራ ሆነን ወይም ኦሮሞ ሆነን መወለድ ፈልገን አይደለም። የተፈጥሮ ነገር ሆኖ ነው። አማራ አህያ ነው። አማራ ጅብ ነው። አህያውን በጅቡ እናስበላዋለን ይሉናል። በማእከላዊ የነበረው ስቃይም ተከትሎኝ ቂሊንጦ መጥቷል። የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች እየጠሩ ይደበድቡኛል። ምንም አይነት የመኖር ህልውና የለንም።” ዘመነ ጌቴ ይህን እያለ ዳኞቹ እንዲያበቃ/እንዲያቆም ሲነግሩት አብዛኞቹ እስረኞች ‘ይናገር! የሆነውን ነው ሚያወራው’ በማለት መናገሩን እንዲቀጥል ጠይቀዋል። ዘመነ ጌቴ ይህን ብሎ አቤቱታውን አጠቃሏል። “ስቃዬን እየተናገርኩ ነው። ስነልቦናዊ እና አካላዊ ጉዳት ደርሶብኛል፤ እየደረሰብኝም ነው። ፍርድ ቤቱ መፍትሄ ይሰጥልኝ ዘንድ ነው የምናገረው።”

�አቤቱታ ሁለት። በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል መዝገብ አባ ገ/እየሱስ ፤ “ማእከላዊ የደረሰብንን ግፍ ከዚ ቀደም ተናግረናል። ቂሊንጦ ከገባሁ በኋላ ችግር እየተከሰተብኝ ነው። ከወንድሞቼ ጋር እንዳልገናኝ እና አብሬ እንዳልበላ ይከለክሉኛል። ኦፊሰር ካሱ የሚባለው የዞን 3 ሃላፊ ነው የሚከለክለኝ። እኔ አዲስ አበባ ዘመድ ስላለኝ በሰሃን ተቋጥራ የምትመጣልኝን ምግብ ከሌሎች ጋር ተካፍዬ እንዳልበላ ተደርጌአለሁ። ማውራትም መጫወትም አልቻልኩም። ተፅእኖ እየተደረገብኝ ነው። ይሄን ክረምት የከረምኩት ክራሞት እ/ር የቁጠረው።”

�አቤቱታ ሶስት። 5ኛ ተከሳሽ አባ ” እሳቸው[አባ ገ/እየሱስ] የተናገሩት በደልና ግፍ በኔ ላይም ደርሷል። እኔ ወገን የለኝም። በልጅነቴ ነው ወገኔን ትቼ ገዳም የገባሁት። በገዳሙ[ዋልድባ] የነበሩትን አፅመ ቅዱሳን አፈራርሰው ዛፎቹን ቆርጠው ክሰል እያወጡበት ነው። ይህን ተቃውመን ብንናገር አሸባሪ ተባልን።” አባ ይህን ሲናገሩ ዳኞቹ በፊት ስለተከሰተ ነገር ሳይሆን በማረሚያ ቤት ስለሚደርስባቸው በደል ብቻ መናገር ገልፀውላቸዋል። ሆኖም አባ “ስለበፊቱም ስለአሁኑም መናገር እችላለሁ” ብለው የነበረ ቢሆንም ዳኛው ስነስረአቱ እንደማይፈቅድላቸው ከገለፁላቸው በኋላ አባ በማረሚያ ቤቱ ስለሚደርስባቸው በደል ማሰማት ቀጥለዋል። ” በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 3ቴ እና 4ቴ ቢሮ እየጠሩ ያንገራግሩናል (ያስፈራሩናል ፤ ይዝቱብናል)። ፀሎት እንድንፀልይ አይፈቀድልንም። መንግስት ነው እንዴ ይቺን ሃገር የሚጠብቃት?! እ/ር ነው የሚጠብቃት! አበበ የሚባል ፖሊስ እና ካሱ የሚባል ኦፊሰር ‘አመፅ እያነሳሳችሁ ነው ጨለማ ቤት እናስገባችኋለን’ እያሉ ያስፈራሩናል። ከ2004 ጀምሮ እየተሰቃየን ነው። ገዳም እንዳንቀመጥ ተከለከልን። እናንተስ ለምንድነው እውነት ማትፈርዱልን? ለምን ፀሎት እንዳንፀልይ ተከለከልን?”

�አቤቱታ አራት። በእነ ተሰኢድ ኑርሁሴን ኑሩ ” የታሰርኩት አማራ ስለሆንኩ ነው። ጎንደሬ ስለሆንኩ ነው። ማእከላዊ ጥፍሬን ነቅለውኛል። ማእከላዊ የዘር ፍሬ ሚኮላሽበት የሶት ልጅ ጡት አስረው የሚጎትቱበት የስቃይ ቦታ ነው። እዚህ ያለነው ሁላችንም በማእከላዊ ስቃይ አሳልፈናል። በአደባባይ መናገር የቻልነው እና የደፈርነው ብቻ እንናገር ብለን ነው። እኔ የኪነጥበብ ሰው ነኝ። የዜማ እና የግጥም ደራሲ ነኝ። ያሰሩኝ ‘ላባ’ የተሰኘ ባለ መቶ ገፅ የግጥም መድብሌን ለማሳተም እየሄድኩ ሳለ ነው። እና የግጥም መድብሉ አልተመለሰልኝም። የጣሱት የሰብአዊ መብት እንኳን ሊመለስልኝ የሚቻል አይደለም። የግጥም መድብሌን ይመልሱልኝ። ከክሱ ጋር ግንኙነት የለውም። በማስረጃነትም አልተያያዘም። እያዝናና የሚያስተምር የስነፅሁፍ ስራ ነው። በተጨማሪም ፀሎት እንዳላደርግ ተከልክያለው። እኔ ሙስሊም ነኝ። እንዳልሰግድ ይከለክሉኛል። ክርስቲያኖችም እንዳይፀልዩ ተከልክለዋል። ከዚህ የመጣችሁ ቤተሰቦች ይህን በደላችንን ለሚዲያዎች ሁሉ ንገሩልን። ” ዳኞች የሰይድን አቤቱታ ከሰሙ በኋላ በማእከላዊ መርማሪዎች ተወሰደብኝ ያለውን የግጥም መድብል በተመለከተ ለማጣራት ከማእከላዊ የመጣ ፖሊስ መምጣቱን ጠይቀው ሲቪል የለበሱ እና ከአቃቤ ህግ ጎን ቁጭ ብለው ከነበሩ 3ት የማእከላዊ ፖሊሶች አንዱ በመቆም ከማእከላዊ መምጣቱን ለዳኞቹ መልስ ሰጥቷል። ፖሊሱ ስለጉዳዩ ሲጠየቅ የሚያቀው ነገር እንደሌለ የገለፀ ሲሆን ዳኞች በቀጣይ ቀጠሮ አጣርቶ ምላሽ ይዞ እንዲመጣ ካዘዙት በኋላ ስሙን ሲጠይቁት በችሎት ስሙን ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ዳኞች ከመታወቂያው ላይ ስሙን እንዲገለብጡም መታወቂያውን በማውጣትም በችሎት አስተባባሪ በኩል ለዳኞቹ ልኳል።

�አቤቱታ አምስት። በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል መዝገብ 28ኛ ተከሳሽ አራጋው፤ ” በማእከላዊ ድብደባ ያደረሱብን መርማሪዎች እዚሁ ቁጭ ብለዋል። ግፍና በደል ያደረሱብን እነሱ ናቸው። ያልሆነ ነገር ፤ ያላልነውን ፤ ያላደረግነውን ፅፈው በግዳጅ ያስፈረሙን እነሱ ናቸው። መርማሪው ስሙን ሲጠየቅ በግልፅ ያልተናገረበት ምክንያት ይታወቃል። የሰራውን ስለሚያውቅ ነው። ህግ ካለ በህግ እንዳኝ። እነዚህ [ወደ ማእከላዊ መርማሪ ፖሊሶች እየጠቆመ] መርማሪዎች ናቸው፤ ደብዳቢዎች ናቸው እንደገና እዚህ መጥተው ደግሞ ይከታተሉናል። ምስክርም የሚሆኑት እነሱ ናቸው። ብዙ ነገር ሆነው ነው የሚሰሩት። ” ዳኞች የአራጋውን አቤቱታ ሰምተው ከማእከላዊ የሚመጡ ፖሊሶች እንደማንኛውም ሰው መጥተው ችለቱን መከታተል እንደሚችሉ እና የመከልከል ስልጣን እንደሌላቸው ተናግረዋል።

�አቤቱታ ስድስት። በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል መዝገብ ተከሳሽ ሙላቱ ተሰማ ፤ ” ማእከላዊ በነበርኩ ጊዜ አሁን ልገልፀው በማልችለው አካሌ ላይ ድብደባ ደርሶብኛል። ከተፈቀደልኝ ልብሴን አውልቄ አሳያለሁ። እኔ የአንድነት የፍትህ እና ዲሞክራሲ ፓርቲ አባል ነኝ እንጂ አሸባሪ አይደለሁም። ካሸባሪም ጋር የምገናኝ አይደለሁም። ቂሊንጦ ጠባብ ክፍል ውስጥ አርባ እና ሃምሳ ሆነን ነው የምንኖረው። በ90ሳሜ ፍራሽ ላይ ለሁለት ነው ምንተኛው የሚቀርብልን ምግብ ተመጣጣኝ አይደለም። ቤተሰቡ ቅርብ ያለ የሚቋጥርለትን ይበላል። እኛ ሚጠይቀን የሌለ በቂ ምግብ አናገኝም። የክልላችን ፍርድ ቤት ስልጣን ስላለው ክሳችን ወደ ክልላችን ይዙርልን።”

�አቤቱታ ሰባት። በነተሻገር ወ/ሚካኤል መዝገብ ተከሳሽ ተስፋሁን ማኔ ፤ ” ማእከላዊ እያለሁ መርማሪው ተምረሃል ወይ ብሎ ጠየቀኝ። አዎ ስለው ፤ ስንት ጊዜ ወደቅክ አለኝ። አልወደቅኩም ስለው፤ አማራ ደደብ አይደለ እንዴ እንዴት አልወደቅክም? አለኝ። በቂሊንጦም ግንባታ እያስፋፉ ነው። ለግንባታው የሚሆን ድንጋይ በግዳጅ እንድሸከም እየተደረኩ ነው። ጀርባዬ ተላልጧል። ጉዳያችን በክልላችን ይታይልን።”

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባል የ”ሽብር” ክስ ቀረበበት

በጌታቸው ሺፈራው

አዴኃን የአርበኞች ግንቦት 7 ክንፍ ነው ሲል አቃቤ ህግ ክስ አቀረበ
• የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባል የ”ሽብር” ክስ ቀርቦበታል

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አዴኃን) የአርበኞች ግንቦት 7 ክንፍ ነው ሲል ክስ አቅርቧል። ዛሬ ጥቅምት 6/2010 ዓ•ም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል አባል በነበረ ግለሰብ ላይ በቀረበው የ”ሽብር” ክስ አዴኃን የአርበኞች ግንቦት 7 ክንፍ ነው በሚል ተጠቅሷል። አቃቤ ህግ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባል የነበረው ኮንስታብል ብርሃን በላይ ቸኮል ላይ ባቃረበው ክስ አዴኃንን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ክንፍ ከማለቱም ባሻገር የ”ሽብር ቡድን” ሲል በ”ሽብር” ፈርጆታል።

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ በተነበበው ክስ ኮንስታብል ብርሃን አማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢጠና ወረዳ አውንት ጎንቻ ጫካ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት ቄስ ደመቀ ዓለሜ፣ አበባው መኮንን፣ አበራ ምናሉ፣ ልቅናው ምህረት፣ ምትኩ ፀጋዬ፣ ዮናስ ጋሻው እና ደሳለኝ የተባሉ የአዴኃን ታጣቂዎች ጋር አብሮ እንዲሰራ ተልዕኮ ተሰጥቶት ተስማምቷል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

በተጨማሪም ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ ያሉና የከዱ ጠንካራ አባላትን ለመመልመል ተስማምቷል፣ አባላትን መልምሎ ወደ ኤርትራ ልኳል፣ ባህርዳር አካባቢ ሆኖ ለአዴኃን ለመስራት ተስማምቷል፣ ስለ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና አመራሮቹ ጠቃሚ መረጃ ለአዴኃን ሰጥቷል የሚል ዝርዝር ክስ ቀርቦበታል።

አቃቤ ህግ “በኢፌዲሪ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ አባል ሆኖ ሲሰራ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅ የገባውን ቃል ኪዳን በማፍረስ እራሱን የአርበኞች ግንቦት 7 በማለት በሚጠራው የሽብር ቡድን ክንፍ በሆነው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ በማለት በሚጠራው የሽብር ቡድን” አባል ነው በሚል ባቀረበው ክስ ኮንስታብል ብርሃንን የአርበኞች ግንቦት 7፣ እንዲሁም የአርበኞች ግንቦት 7 ክንፍ የሆነው አዴኃን አባል ነው የሚል ክስ አቅርቦበታል። አባላትን በመመልመል፣ በማደራጀት፣ ለአዴኃን አባላትና አመራሮች መረጃ በማቀበል ” በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ አባል መሆን በማንኛውም መልኩ በመሳተፍ ወንጀል” ክስ የቀረበበት ኮንስታብል ብርሃን የክስ መቃወሚያ ለማቅረብ ለጥቅምት 29/2010 ቀጠሮ ተሰጥቶታል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ በፀረ ሽብር አዋጁ ከተፈረጁት የፖለቲካ ቡድኖች ውስጥ እንዳልሆነ የሚታወቅ ሲሆን በፀረ ሽብር አዋጁ ባልተፈረጁት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አዴኃን)፣ የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ( ጋህነን)፣ የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን)፣ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን)፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) አባልነት በ”ሽብር”የተከሰሱና የተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይታወቃል።

በአዋጁ በ”ሽብርተኝነት” ያልተፈረጁ ድርጅቶች ከአርበኞች ግንቦት 7 እና ኦነግ ጋር ግንባር ፈጥረዋል፣ አብረው ስራ እየሰሩ ነው እንዲሁም በ”ሽብር” የተፈረጁት ድርጅቶች ክንፍ ናቸው በሚል በድርጅቶቹ ስም ክስ የሚቀርብባቸው ተከሳሾች አቀቤ ህግ የሚያቀርብባቸውን ክስ በሀሰት እና ሆን ተብሎ ለማጥቃት የቀረበ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

የአርበኞች ግንቦት 7 አባል ናችሁ ተብለው ክስ የተመሰረተባቸው በአርባምንጭ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ፍርድ ቤት ቀረቡ

የአርበኞች ግንቦት 7 አባል ናችሁ ተብለው ክስ የተመሰረተባቸው በአርባምንጭ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እነ ሉሉ መሰለ ዛሬ ጥቅምት 9፣ 2010 ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ችሎት ቀርበው ነበር።
★በመዝገቡ ክስ የተመሰረተባቸው 13 ሰዎች ሲሆኑ በብይን አንዱ ነፃ ሲወጣ (መሃመድ ዳና) 12ቱ እንዲከላከሉ ተበይኖ ነበር።

★ እንዲከላከሉ ከተባሉት ውስጥ 5ቱ (አለም ክንፈ፣ በረከት ተገኔ፣ ደረጄ አደመ፣ ሲሳይ አምባው እና አጥናፉ አበራ) አንከላከልም በማለታቸው መጋቢት 29 ቀን 2009 አራት አመት ከአምስት ወር ተፈርዶባቸዋል።

★እንከላከላለን ያሉት የተቀሩት ሰባቱ (ሉሉ መሰለ፣ አየለች አበበ፣ በጋሻው ዱንጋ፣ ዘኪዎስ ዘሪሁን፣ ጌታሁን ቃፃ፣ መርዶኪዮስ ሽብሩ እና ያረጋል ሙሉአለም) በግንቦት ወር 2009 ውስጥ መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰምተው አጨርሰዋል።

★በባለፈው አመት በተደጋጋሚ ለፍርድ ተቀጥረው የነበረ ቢሆንም የምስክሮች ቃል አልተገለበጠም እየተባለ ተለዋጭ ቀጠሮ ሲሰጣቸው የነበረ ሲሆን የዛሬውም ቀጠሮ ፍርዱን ለማሳወቅ ነበር።

★ሆኖም ዳኞች ፍርዱን ሰርተው እንዳልጨረሱ በመግለፅ “ለጥቅምት 28 ለማድረስ እንሞክራለን” ብለዋል።
★ በተደጋጋሚ በሚሰጠው ቀጠሮ የተማረሩት ተከሳሾቹን በመወከል 1ኛ ተከሳሽ ሉሉ መሰለ ይህን ብለዋል። “2008 የተከፈተ መዝገብ ነው። ባለፈው አመት ግንቦት ላይ ነው መከለከያ ምስክር አሰምተን የጨረስነው። ከኛ በኋላ መከላከያ ምስክር ያሰሙ ፍርድ ተሰርቶላቸዋል። የኛ በምን ምክንያት እንደዘገየ አላቅም። ቤተሰቦቻችን ከ500 ኪሜ ርቀት ነው ሚጠይቁን። እየተንገላቱ ነው። ጠያቂም የለንም።”
★እነ ሉሉ መሰለ በጥቅምት ወር 2008 በፖሊስ ተይዘው ማእከላዊ 4ት ወር ቆይተው የካቲት ወር 2008 ላይ ነው ክስ የተመሰረተባቸው።

ምንጭ፦ የፍርድ ቤት ውሎዎች