የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ወደ ሳሙኤል አወቀ መኖሪያ ቤት ለቅሶ እንዳይደርሱ ታገዱ
• ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም ለሌላ ለቅሶ በመሄድ ላይ የነበሩ ዜጎች ተደብድበው ተመልሰዋል
የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ሰኔ 8/2007 ዓ.ም ደብረማርቆስ ከተማ የተገደለው የሳሙኤል አወቀ ለቅሶ እንዳይደርሱ ታገዱ፡፡ አመራሮቹና አባላቱ ዛሬ ሰኔ 13/2007 ዓ.ም በጠዋት ከአዲስ አበባ ተነስተው የሳሙኤል አወቀ ቤተሰቦች ወደሚገኙበት ምስራቅ ጎጃም ዞን ግንደወይን እያቀኑ በነበረበት ወቅት አባይ ድልድይ ላይ በፌደራል ፖሊስ ታፍነው ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ጎሃ ፂዮን ከተማ ውስጥ እስከ ምሽቱ 2 ተኩል ድረስ ታግተው ውለዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን ወደ ለቅሶ እንዳይሄዱ ያገዱት ከአዲስ አበባ የሄዱና ከቦታው ተዘጋጅተው ሲጠብቁ የነበሩ የፌደራል ፖሊሶች እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አመራሮቹና አባላቱ ለፖሊስ ቃል ሲሰጡ ከሳሙኤል አወቀ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት፣ በፓርቲው ውስጥ ያላቸውን ኃላፊነት፣ ሳሙኤልን ማን እንደገደለው የሚመለከቱ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡ ለቅሶ እንዳይደርሱ ከተከለከሉትና ታተው የዋሉት
1. ኢ/ር ይልቃል ጌትነት/ የፓርቲው ሊቀመንበር
2. ይድነቃቸው ከበደ/ የፓርቲው የህግ ጉዳይ ኃላፊ
3. ወሮታው ዋሴ /የፓርቲው የፋይናንስ ጉዳይ ኃላፊ
4. ሀብታሙ ደመቀ/ የኦዲትና ኢንስፔክሺን አባል
5. ጌታቸው ሺፈራው/ የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ
6. ጋሻው መርሻ/ የብሄራዊ ምክር ቤት አባል
7. እምላሉ ፍስሃ/ የብሄራዊ ምክር ቤት አባል
8. ሜሮን አለማየሁ/ አባል
9. ጥላሁን አበጀ/ አባል
10. ጠና ይታየው/ አባል
11. እስጢፋኖስ በኩረጽዮን /አባል
12. ኃይለማሪያም ተክለ ጊዮርጊስ/ አባል
13. ጋሻነህ ላቀ/ አባል
14. ግርማ ቢተው አባልና
15. የመኪናው ሾፌር ናቸው
ከምሽቱ 2 ሰዓት ተኩል ከአዲስ አበባ በመንገድ ትራንስፖርት ሰራተኞችና ትራፊክ ፖሊሶች ህጋዊ መሆኑ ተረጋግጦ ያለፈው እንዲሁም ለአራት ቀን ከፓርቲው ጋር ውል የያዘው መኪና እንዳይንቀሳቀስ ተከልክሎ ከፍተኛ አመራሮቹና አባላቱ ከእስር ተለቀዋል፡፡ በተጨማሪም የሰማያዊ ፓርቲ ልዑካን ይዘዋቸው የነነበሩ ቁሳቁሶች ለምርመራ በሚል በፖሊስ ተይዘዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ከአዲስ አበባ ተነስተው ምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወደ ሌላ ለቅሶ ሲሄዱ የነበሩ ዜጎች የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ከታፈኑ በኋላ ደጀን ላይ ተይዘው ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸው በግዳጅ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ ተመልሰው ወደ ለቅሶው ቢሄዱ እስከ 10 ሺህ ብር ሊቀጡ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እነዚህ ዜጎች በተያዙበት ወቅት ሰማያዊ ፓርቲ ደብረማርቆስና ባህርዳር ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያደርግ እንደሆነ እንደተገለጸላቸው፤ እነሱም የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ ላይ ትገኛላችሁ ተብለው ተጠርጥረው እንደሆነ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ከምርጫው ጋር በተያያዘ 4ኛ ሌላ የመድረክ አባል ተገደሉ
ባለፈው ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ምርጫን ተክትሎ የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ባለፈው ሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰኣት ላይ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ) አመራር አካል የነበሩት አቶ ብርሃኑ ኤረቦ መገደላቸውን መድረክ አስታውቋል፡፡ አቶ ብርሃኑ በደቡብ ክልል ሀዲያ ዞን በሚገኘው ሶሮ ወረዳ በዳና ቶራ ቀበሌ የፓርቲው የኮሚቴ አመራር አባልና በምርጫው ቅስቀሳም ላይ ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸውም ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በወቅቱ ግድያውን የፈፀሙት ብርሃኑ ደቦጭ እና ታዲዮስ ጡምቦ የተባሉ ፖሊሶች እንደሀኑ እና ከዛ በፊትም እነኚህ ፖሊሶች የመድረክ አመራሮች እና አባላቱን ሲያስፈራሩና ሲዝቱባቸው እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡ በተለይ አቶ ብርሃኑ ኤረቦ በሁለቱ ፖሊሶች መኖሪያ ቤታቸው ደጅ ተይዘው ከተደበደቡና ከተገደሉ በኋላ አስከሬናቸው ባካባቢው ባለ ወንዝ ተጥሎ እንደተገኘ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ ኤረቦ የተገደሉበት ሶሮ ወረዳ በምርጫ ዋዜማ መምህር ጌታቸው የተባሉ የመድረክ ዕጩ በኢህአዴግ በደረሰባቸው ጫና እና አስተዳደራዊ በደል በወረዳው አስተዳደር ፊት ራሳቸውን አቃጥለው ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ ወረዳው የኢህአዴግ ተወካይ እና የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሆኑት ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም የተወዳደሩበት ወረዳ መሆኑ ታውቋል፡፡
መድረክ ከግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ አቶ ብርሃኑ ኤረቦን ጨምሮ የተገደሉት የክልል አመራሮቹ ቁጥር አራት የደረሰ ሲሆን፤ እነኚህም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሚዳ ቀኝ ወረዳ አቶ ጊዲሳ ጨመዳ፣ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን ቆራ ወረዳ አቶ ገቢ ጥቤ፣ ከትግራይ ክልል ምዕራብ ትግራይ ዞን ማይካድራ ከተማ አቶ ታደሰ አብርሃ እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በምርጫው ወቅት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ የመድረክ አባላትና ደጋፊዎች በተለይም በደቡብ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ በርካታ ሰዎች እንደታሰሩ፣በጥይት ተደብድበው እንደቆሰሉ እና ቤቶቻቸው እንደተቃጠለ ከፓርቲው የተገኘ መረጃ አመልክቷል፡፡ በተመሳሳይም በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረማርቆስ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ አመራርና የህዝብ ተወካዮች ዕጩ የነበረው ወጣት ሳሙኤል አወቀም ተደብድቦ መገደሉ ይታወቃል፡፡ መድረክ እና ሰማያዊ ፓርቲ አባሎቻቸው የተገደሉት በኢህአዴግ መሆኑን እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡