Tag Archives: Ethiopian press freedom

ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ የአንድ ዓመት እስር እና 1,500 ብር ቅጣት ተፈረደበት

ኢትዮ ምህዳር ጋዜጣም 10ሺህ ብር ቅጣት ተፈረደበት

getachew-worku

(አዲስ ሚዲያ) ዛሬ ህዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም.  የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 6ኛ ወንጀል በዋለው ችሎት የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ መስራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ አንድ ዓመት እስራትና 1,500 ብር ቅጣት ተፈረደበት፡፡ ከጋዜጠኛው በተጨማሪ ድርጅቱ ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣም የ10 ሺህ ብር ቅጣት ተፈርዶበታል፡፡

ጋዜጠኛው እና ጋዜጣው ላይ የዛሬ ፍርድ ውሳኔ የተላለፈው አዲስ አበባ መንበረ ጵጵስና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ ተፈፀመ የተባለውን ሙስና የሚያጋልጥ ዜና በጋዜጣው መሰራጨቱን ተከትሎ፤ የደብሩ እና የቤተክህነቱ ኃላፊዎች ”በጋዜጣው ስማችን ጠፍቷል” በሚል በመሰረቱት ክስለ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከፍርድ ቤቱ ቅጣት ውሳኔ በኋላም ጋዜጠኛው በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ አዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ በሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት የእስር ቅጣቱ ተፈፃሚ እንዲሆን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ መታሰሩ ታውቋል፡፡ በችሎቱ ላይ ከወዳጆቹ እና ጋዜጠኞች በተጨማሪ ከሳሾቹ ካህናት እና የደብሩ ኃላፊዎች ተገኝተው እንደነበር የተጠቆመ ሲሆን፤ ጋዜጠኛውም በመጨረሻ ”እውነት ትመነምናለች እንጂ አትጠፋም፤እውነቱ አንድ ቀን ይወጣል፡፡ ይህ ፍርድ የተፈረደብኝ ጋዜጣውን ለመዝጋት ታቅዶ ነው፡፡” ማለቱ ተሰምቷል፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ቀደም ሲል ሐዋሳ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ላይ የተፈፀሙ የሙስና መረጃዎችን በጋዜጣው ለህዝብ በማድረሱ ተከሶ ከፍተኛ መጉላላት፣ እስርና እንግልት እንዲሁም በባልደረባው ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው በአዲስ አበባ መንበረ ጵጵስና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈፀመ ሙስና የሚያጋልጥ ዜና በቂ መረጃ እንዳለው ለፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ ቢያሳውቅም፤ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ጋዜጠኛው ለቀጣይ አንድ ዓመት በእስር ቅጣት እንዲያሳልፍ በመወሰኑ ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ለንባብ ይበቃ የነበረው ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ህትመትም እንደማይቀጥል መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ከኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት በተጨማሪ በመንግሥት እውቅና የተነፈገውና በ2004 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መብትና ጥቅም እንዲሁም በፕሬስ ነፃነት ዙሪያ ለመስራት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ እንደነበርም ይታወቃል፡፡

ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ በድጋሚ ታሰረ

“ኮማንድ ፖስቱ ሊያናግርህ ይፈልጋል”

befekadu-hailu

ከተለያዩ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ከዞን፱ ጦማሪያን ስብስብ ጋር በመሆን ሽልማቶችን ያገኘው ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ህዳር 02 ቀን 2009ዓ.ም ጠዋት ከቤቱ በፀጥታ ኃይሎች ወደ ፖሊስ ጣብያ ተወስዷል።

ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፈቃዱ ሚያዝያ 17 ቀን በ2006ዓ.ም ከሌሎች የዞን፱ ጦማሪያን እና ሶስት ጋዜጠኖች ጋር በመሆን በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሲሆን ከአንድ አመት ከስድስት ወር የእስር ቆይታ በኋላ የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የተከሰሰበትን የሽብር ወንጀል ወደ አመፅ ማነሳሳት ቀይሮ በ20ሺ ብር ዋስ እንዲወጣ ፈቅዶለት ነበር። በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያልተደሰተው አቃቤ ህግ በበፍቃዱ ላይና ሌሎች ፍርድ በቤቱ ነፃ የለቀቃቸው የዞን፱ ጦማሪያን (ሶልያና ሽመልስ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አጥናፉ ብርሃኔና አቤል ዋበላ) ላይ ይግባኝ የጠየቀ ሲሆን የፊታችን ማክሰኞ ህዳር 06 ቀን 2009 ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ በጠየቀው ይጋባኝ ላይ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በፈቃዱ ኃይሉ ከእስር ከተፈታ አንድ አመት በኋላ ዛሬ ጠዋት ላይ በመኖሪያ ቤቱ እያለ “ኮማንድ ፖስቱ ሊያናግርህ ይፈልጋል” በሚል በፀጥታ ሀይሎች ሊወሰድ ችሏል።

ጋዜጠኛ እና ጦማሪ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች በፍቃዱ ኃይሉ ከእስር ከተፈታ በኋላ በአጭር ጊዜ ተወዳጅ በሆነችውና ከ10 እትም በኋላ ከገበያ በወጣችው ውይይት መፅሄት ላይ በዋና አዘጋጅነት ይሰራ እንደነበር ይታወቃል።
ምንጭ፡- EHRP.

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ለ3ኛ ጊዜ ለብይን ተቀጠረ

‹ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ግንቦት ሰባት ከተባለው አሸባሪ ቡድን አመራሮች ጋር ግንኙነት አድርገሃል› በሚል የሽብር ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ለ3ኛ ጊዜ ለብይን ቀጠሮ ተሰጥቶበታል፡፡

Getachew Shiferaw

ጥቅምት 21 ቀን 2009 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች ጉዳዩን በጽህፈት ቤት የተመለከቱት ሲሆን፣ ዳኞቹ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ ለህዳር 28 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡

በሌሎች መዝገቦች ከዛሬ ቀደም ቀጠሮ የነበራቸውን ተከሳሾች ሳያቀርብ የቆየው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጋዜጠኛ ጌታቸውን ጨምሮ ሌሎች በዕለቱ ቀጠሮ ያላቸውን ተከሳሾች ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡

ተከሳሹ ጌታቸው ሺፈራው ጉዳዩ ሲታይ የቆየው 14ኛ ወንጀል ችሎት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ላይ ጉዳዩን የሚያየው ችሎት 4ኛ ወንጀል ችሎት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም ቀደም ሲል በነበረው ችሎት በአንድ ዳኛ ይታይ የነበረው የክስ ጉዳዩ በአሁኑ ችሎት በሦስት ዳኞች የሚታይ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው የቀረበበትን ክስ መከላከል ይገባዋል ወይስ መከላከል ሳያስፈልገው በነጻ ይሰናበት የሚለውን ብይን ለመስማት ፍርድ ቤት ቀጠሮ ሲሰጥ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው፡፡ ተከሳሹ ላይ አቃቤ ህግ ከሰነድ ማስረጃዎች ሌላ የሰው ምስክር አላቀረበበትም፡፡

ጌታቸው ታህሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ለእስር ከተዳረገበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ጉዳዩን በእስር ቤት ሆኖ እየተከታተለ ይገኛል፡፡
ምንጭ፡- EHRP.

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል

*ጌታቸው ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደርጓል

Getachew Shiferaw

ከሽብር ቡድን አመራሮች ጋር በፌስቡክና በስልክ ግንኙነት በመፍጠር መረጃዎችን አስተላልፏል በሚል የሽብር ክስ የቀረበበት የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የእምነት ክህደት ቃሉን ለፍርድ ቤት ሰጥቷል፡፡

አርብ ሐምሌ 8 ቀን 2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው ጋዜጠኛ ጌታቸው ቀደም ሲል ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ውድቅ መሆኑን ተከትሎ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ በችሎቱ ተጠይቆ ‹‹የቀረበብኝን የወንጀል ድርጊት አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛም አይደለሁም›› ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡

መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ተከሳሹ ቀደም ሲል ያቀረበው የክስ መቃወሚያን መርምሮ ብይን ለመስጠት ሲሆን፣ ጉዳዩን የሚያየው 14ኛ ወንጀል ችሎት የተከሳሹን መቃወሚያ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ችሎቱ የመቃወሚያ ብይኑን በንባብ ከማሰማት ይልቅ በጥቅሉ “የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ አድርገነዋል” ሲል ለተከሳሹ ገልጹዋል፡፡

”በአጭሩ የክስ አቀራረቡ ከተጠቀሰው የወንጀሉ ክፍል አለመጣጣምን በተመለከተ የቀረበው መቃወሚያ አልተቀበልነውም፤ ዝርዘሩን ማስረጃ ስንመዝን እናየዋለን፡፡ የቀረበው ክስ ግልጽ አይደለም የተባለውን በተመለከተም፣ ክሱን ስንመለከተው በተብራራ መልኩ የቀረበ መሆኑን ስለተገነዘብን ውድቅ አድርገነዋል” በማለት የመቃወሚያው ውድቅ መሆንን ችሎቱ በቃል ለተከሳሹ አስረድቷል፡፡

ችሎቱ ተከሳሹ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲሰጥ ወንጀሉን አልፈጸምኩም፣ ጥፋተኛም አይደለሁም ማለቱን ተከትሎ የአቃቤ ህግን አስተያየት የጠየቀ ሲሆን፣ አቃቤ ህጉ በበኩሉ ከክስ ማመልከቻ ጋር ያያያዘው የሰነድ ማስረጃ ተመርምሮ ብይን እንዲሰጥለት አመልክቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም የሰነድ ማስረጃውን መርምሮ ብይን ለማሰማት ለሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ ከሳሽ ያቀረበበት የሰው ማስረጃ እንደሌለ በችሎቱ ተገልጹዋል፡፡

ምንጭ፡- EHRP

በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ የቀረበው የሽብር ክስ በንባብ ተሰምቷል

*ተከሳሹ ጥቁር ልብስ ለብሰሃል በሚል በቀጠሮው ሰዓት አለመቅረቡ ታውቋል

Getachew Shiferaw

የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በሆነው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ የፌደራል አቃቤ ህግ ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. የመሰረተው የሽብር ክስ ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት በንባብ ተሰምቷል፡፡

ተከሳሹ ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርቦ ክሱ ሊነበብለት የነበር ቢሆንም ከጠበቃው ጋር ሳይመካከር ክሱ እንዲነበብለት እንደማይፈልግ በመግለጹ በቀጠሮ ሰንብቶ ዛሬ ተነቦለታል፡፡ ከክስ ዝርዝሩ መረዳት እንደተቻለው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ላይ የቀረበው ክስ የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) ላይ የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት መተላለፍ የሚል ሆኗል፡፡

አቃቤ ህግ በክሱ ላይ እንዳመለከተው ተከሳሹ ከ24/05/2006 ዓ.ም እስከ 13/04/2008 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት ግንቦት ሰባት ከተባለ የሽብር ድርጅት አመራሮች ጋር በማህበራዊ ድረ ገጽ በተለይም ፌስቡክ እና ስልክ ግንኙነት በመፍጠር ለሽብር ቡድኑ ተልዕኮ የተለያዩ መረጃዎች በማስተላለፍና በሽብር ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል ፈጽሟል ሲል ጠቅሷል፡፡

ተከሳሹ ‹‹…በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር እየተገናኘ መረጃ በመሰብሰብ በውጭ ሀገር ለሚገኙ የሽብር ቡድኑ አመራሮች መረጃ በማስተላለፍ….›› በሽብር ድርጅት ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል፡፡

ችሎቱ ክሱን በንባብ አሰምቶ ሲያጠናቅቅ በተከሳሹ ላይ የተጠቀሱ የአቃቤ ህግ የማስረጃ ዝርዝሮችን በተመለከተ እንደገለጸው፣ ተከሳሹ የተጠቀሰበት ማስረጃ የሰነድ ማስረጃ ብቻ መሆኑ ተገልጹዋል፡፡
ተከሳሹ ከግንቦት 11 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኝ ሲሆን፣ በዛሬው የችሎት ቀጠሮ በጠዋት እንዲቀርብ የሚል ቢሆንም የእስር ቤቱ አስተዳደር ‹‹ጥቁር ልብስ ለብሰህ ፍርድ ቤት መሄድ አትችልም›› በሚል ጠዋት ሳያቀርቡት ከቆዩ በኋላ ከሰዓት ሊያቀርቡት ችለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ የክስ መቃወሚያን ለመቀበል ለሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡- EHRP