Tag Archives: Gonder

በጎንደር ታላቅ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ

(አዲስ ሚዲያ) ዛሬ እሁድ ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ መዳረሻውን በጎንደር ፋሲለደስ መስቀል አደባባይ ያደረገ ታላቅ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ፡፡ የተቃውሞ ሰልፉ ዋነኛ ምክንያት ባለፈው ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. የማዕከላዊ መንግሥት የወልቃይት አማራ ማንነት መብት ጥያቄ አንሺ ኮሚቴ አባላት ከሚኖሩበት ጎንደር ከተማ በሌሊት አፍኖ ወስዶ በማሰሩ፣ ከኮሚቴ አባላት መካከልም ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እቤታቸው ሊያፍኑ የሄዱትን የፀጥታ አካላት ህጋዊ ከሆናችሁ በቀን መምጣት ትችላላችሁ፣ በሌሊት ህገወጥነት በሚል በተፈጠረ አለመግባባት የ11 የፅጥታ ኃይሎች እና 3 ሲቪሎች መገደላቸው ይታወቃል፡፡ ይህንንም ተከትሎ መንግሥት የወልቃይት አማራ ማንነት መብት ጥያቄ አቅራቢዎችን እና የፀጥታ ኃይሉ ላይ የአፀፋ ርምጃ የወሰዱትን ጨምሮ የመንግሥትን ርምጃ በማውገዝ እና ተቃውሞ ያቀረቡ የአካባቢውን ህዝብ ወንጀለኛ አድርጉ በሚዲያ በማቅረቡ የተቆጣው ህዝብ፤ ተቃውሞውን በአደባባይ ለማቅረብ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ በመደረጉ ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲወጣ እንዳደረገው ከአስተባባሪዎቹ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Gonder 1
ከጎንደር ፋሲለደስ ከተማ በተጨማሪ በደቡብ ጎንደር በእስቴ ወረዳ መካነ ኢየሱስ ከተማ፣በምዕራብ በለሳ እና ማክሰኝት ከተማ ተመሳሳይ ጥያቄ መነሻ ያደረገ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ መደረጉ ታውቋል፡፡ በተለይ በጎንደሩ ሰልፍ የተለያዩ የኃይማኖት አባቶች በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸውን የዓይን እማኞች አረጋግጠዋል፡፡

በዛሬው ተቃውሞ ሰልፍም የተለያዩ መፈክሮች የተደመጡ ሲሆን፤ በዋናነትም የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ሕገ-መንገሥታዊ መብት ነው፣ የሻዕብያ ተላላኪ ህወሃት እንጂ ወልቃይት አይደለም፣ በግፍ የታሰሩ የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በአስቸኳይ ይፈቱ፣…የሚሉትን ጨምሮ በርካታ መፈክሮች እንደተሰሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡


በተቃውሞ፤ ታሪክ ምስክር ነው ወልቃይት አማራ ነው ፣ አማራ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉአላዊነት የተዋደቀ ታላቅ አርበኛ ሕዝብ ነው ፣ ዘረኝነትን አጥብቀን እናወግዛለን ፣ የትግራይን ሕዝብ እናከብራለን፤የህወሓትን አፋኝ የአገዛዝ ፖሊሲ አጥብቀን እናወግዛለን፣አማራነት ይከበር፣ በኦሮሞ እህት ወንድሞቻችን ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል አጥብቀን እንቃወማለን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት ይፈልጋል፣ በኦሮሚያ የሚደረገው በወንድምና እህቶቻችን ላይ ግድያ ይቁም፣ ኢቢሲና ሌሎች መንግስታዊ ሚዲያዎች የጎንደርንና አካባቢውን ህዝብ ይቅርታ ይጠይቁ የሚሉ መሪ ቃሎች ተደምጠዋል፡፡

በተጨማሪም የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ እስኪመለስ ድረስ ትግሉ ይቀጥላል፣አማራነት ወንጀል አይደለም፣ የትግራይ ወሰን ተከዜ ነው፣ ወልቃይት የአማራ ነው ፣ የሐብታሙ አያሌዉ ከአገር የመዉጣት እግድ በአስቸኳይ ይነሳለት፣ ዜጎችን በፖለቲካ አመለካከታቸዉ ማሰርና ማሰቃየት ይቁም፣ በፖለቲካ አመለካከታቸዉ የታሰሩ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአስቸኳይ ይፈቱ እና የህወሓት የበላይነት ይቁም የሚሉ መፈክሮች ጎልተው ተሰምተዋል፡፡


ይህ ህዝባዊ ተቃውሞ ከሳምንት በፊት እውቅና ተጠይቆ በመንግሥት ተከልክሎ የነበረ ሲሆን፤ በድጋሚ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ቢገባም፤ መንግሥት ለህዝባዊ የተቃውሞ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና አለመስጠቱን ከማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ጋር በኢቢሲ እና ኤፍቢሲ ቢያሳውቅም ህዝቡን ለተቃውሞ ከመውጣት ማገድ አልቻለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት ህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ እውቅና መንፈጉን በስሩ ባለ መገናኛ ብዙኃን ከመግለፁ በተጨማሪ በጎንደር ከፍተኛ የመከላከያ፣ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የከተማው ሚሊሻ አባላት በበብዛት በከተማው እንዲሰፍሩ መደረጉ ታውቋል፡፡

ተቃውሞ ምንም እንኳ የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄን መነሻ ያድርግ እንጂ፤ ለዓመታት በአማራ ማኀበረሰብ ላይ በመንግሥት በተለይም በህወሓት/ኢህአዴግ አማራ ክልልን  ጨምሮ በተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል እየተፈፀመ ያለውን የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ የመብት ጥሰት ተባብሶ መቀጠሉ አንዱ የተቃውሞ አካል መሆኑን የሰልፉ ታዳሚዎች ሲያስተጋቡ ተስተውሏል፡፡

በነበረው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍም፤ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳያስከትል በሰላም መጠናቀቁን የተሳታፊዎችን ጨምሮ ዓይን እማኞች እውቅና የነፈገው የመንግሥት አካል አስታውቀዋል፡፡ በሰልፉ ላይም በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን በ25 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በብዛት ሲውለበለብ ታይቷል፡፡

በጎንደር የ17 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን መንግሥት ሲያምን፤ አንዱን የገደልኩት እኔ ነኝ ብሏል

በጎንደር ህዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በእስር ቤት ላይ በደረሰ ቃጠሎ የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተነገረ፡፡ መንግሥት ከቃጠሎው ወቅት አንድ ሰው መግደሉን ሲያምን ሌሎቹ 16 ሰዎች ህይወት የጠፋው በቃጠሎው ወቅት ከ እስር ቤቱ ለማምለጥ ሲጋፉ ነው ብሏል፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ለመንግስት ሚድያ በሰጠው መግለጫው በህዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ወህኒ ቤት ከቀኑ 7፡30 ሰዓት አካባቢ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ እስረኞች ከቃጠሎው ለመውጣት በተደረገው ግፊያ የ16 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ አንድ ሰው ሊያመልጥ ሲል ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት መገደሉን አምኗል፡፡

Gonder prison
እንደ ዓይን እማኞች ከሆነ ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች ቁጥር ከ42 በላይ እንደሚሆን እና መንግሥት ቁጥሩን ዝቅ በማድረግ በእጁ የጠፉትን ቁጥር ወደ አንድ ብቻ ማሳነሱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ እንደ ዓይን እማኞች ገለፃ ከሆነ በቃጠሎው ወቅት መንግሥት በእስረኞች ላይ ጠከታታይ ተኩስ ከፍቶ እንደነበርና የእስረኞችንም ህይወት ለማትረፍ ማንም ወደ አቅራቢያው እንዳይጠጋ የጥብቃ ኃይሎች እና ፖሊሶች ማንም የውጭ ሰው እንዳይጠጋ ሲያስፈራሩ እንደነበር ጠቁመው፤ ከሞቱት መካከል አብዛኛው በመንግሥት እጅ የተገደሉ እንጂ ከእስር ቤት ከእሳት ለማምለጥና ለመውጣት ሲጋፉ እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡
ከሞቱት በተጨማሪ በቃጠሎው በርካታ እስረኞች ጉዳት እንደደረሰባቸውና በጎንደር ሆስፒታል የህክምና እርዳታም እየተደረገላቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ የቃጠሎውን መንስኤና የተጎዱትንም ሆነ የሞቱን በተመለከተ እስካሁን በገለልተኛ አካል የተጣራ ነገር አለመኖሩ ታውቋል፡፡
በተለይ በሰሜን ጎንደር ዞን ከቃጠሎው በፊት ባሉት ቀናት የቅማንት ማኀረሰብ ባነሱት የመብት ጥያቄ ፖሊስ በወሰደው የኃይል እርምጃ እስካሁን በገለልተኛ አካልም ሆነ በመንግሥት ተጣርቶ ይፋ ባይደርግም በርካታ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውና የተወሰኑትም ምስሎቻቸውም በማኀበራዊ ሚዲያ ይፋ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

የወህኒ ቤቱ ኃላፊ በቃጠሎውም ሆነ በመንግሥት ኃይሎች እርምጃ የሞተ ሰው የለም በሚል ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ 16ቱ በቃጠሎው ወቅት በተፈጠረ መገፋፋት ሲሞቱ አንዱ ግን ሊያመልጥ ሲል በወህኒ ቤቱ ጥበቃ አባላት መገደሉን በማመን እስካሁን 17 ሰዎች መሞታቸውን አምነዋል፡፡ በተለይ በዞኑ ሰሜን ጎንደር መንግሥት በህዝቡ ላይ እየወሰደ ስላለው የኃይል እርምጃ እና በጎንደር ወህኒ ቤት በቃጠሎው እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር መደበቅና መቀነስ የተበሳጩ የጎንደር ዩኒቨርስቲ በተለይ ማራኪ እየተባለ በሚጠራው ግቢ የተማሪዎች ተቃውሞ መቀስቀሱን ተሰምቷል፡፡ በአሁን ወቅትም ተቃውሞው ወደሌሎች የዩኒቨርስቲው ግቢ እና ወደ ሌሎች የክልሉ ተቋማት ሊስፋፋ ይችላል በሚል ስጋት ዩኒቨርስቲው በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ተከቦ ጥብቅ ቁጥር እየተደረገበት መሆኑንም የአዲስ ሚዲያ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

 

%d bloggers like this: