ለቀድሞው የአንድነት አመራር “ እናርድሃለን፣…ራስህን በጥይት እንበትነዋለን….” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው
የመንግሥት ደህንነቶች ለቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት ተክሌ በቀለ የመጨረሻያሉትን እናርድሃለን፣…ራስህን በጥይት እንበትነዋለን..የሚል ማሰጠንቀቂ መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ማስጠንቀቂያውና ማስፈራሪው በሌሎቹም የቀድሞው የፓርቲ አመራሮች ላይም የቀጠለ ሲሆን፣በዛው ዕለት የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባልና የማኀበራዊ ጉዳይ ኃላፊ የነበረው አቶ አለነ ማፀንቱ መታሰሩ ታውቋል፡፡በተለይ የአቶ ተክሌ በቀለ ሁኔታን በተመለከተ ራሳቸው በአጭሩ እንደሚከተለው አስቀምጠውታል፡፡
ለሆነ ጎዳይ ከእንድ ጓደኛየ ጋር ዛሬ ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡30 ላይ ከቦሌ ተነስተን ኮተቤ(02) አካባቤ ሄድን፡፡ የቤት ታርጋ የለጠፈች ነጭ መኪና 4 ጎሮምሶችን ይዛ ትከተን ነበር፡፡ ቦታ ስተን ኑሮ የሆነ መታጠፊያ ላይ ወደ ኋላ ስንዞር ተገጣጠምን፡፡ ባንድ መስመር ስዞር ቦታ የዘጋሁባቸዉ መስሎኝ ይቅርታ ስጠይቃቸዉ የሚነዳው ወንድም መኪናዉን አቁሞ ሳይወርድ የስድብ መዓት አወረደብኝ፡፡ ያ ያገሬ ልጅ! ከዚያም ሄዱ፡፡እነማን እንደ ሆኑም ገባኝ፡፡ ጓደኛየ ወደ ቢሮዉ ገብቶ ጉዳዩን ጨርሶ እስኪወጣ ወርጄ ስጠብቀዉ በመኪኗ ተመልሰዉ መጡ፡፡ በማዶ ላይ የቀን ሰራተኞች ምሳ በልተዉ ሰዓቱ እስኪደርስ ጥላ ላይ ያረፉ ነበሩ፡፡ሁኔታዉን ይከታተሉ ኖሮ ትተዉኝ ሲሄዱ መጥተዉ ጠየቁኝ፡፡የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባል እንደነበርኩና አሁን እንደሌለሁበት፤የስርኣቱ ደህንነት ነን ባዮች ሲሆኑ እያስፈራሩኝ መሆኑንም ስነግራቸዉ በጣም ተናደዱ፡፡ለምን ግርግር አትፈጥርም ነበር አንለቃቸዉም ነበር…..ክብር ለዜጎች! ውድ ህይወት ተከፍሎበት በነበረ ስርዓት ውስጥ፤ህግ አክባሪና ሃይማኖተኛ በሆነ ማህበረሰብ ዉስጥ ተወልዶ ያደገ፤ከድሃ ግብር ደሞዝ የሚበላ የደህንነት ሰራተኛ ነኝ ባይ “እናርዳሃለን….መንግስት ነን፣ ራስህን በጥይት እንበትነዋለን…የምትሰራዉን ሁሉ እናዉቃለን…እድሉን ተጠቀምበት የመጨረሻህ ነዉ….” የሚሉ ቃላት እንዲናገሩ ሰልጥነዉ ሲላኩ በእዉነት ያሳፍራል፡፡ ዱላ ቀረሽ ስድብ አዝንበዉብኝ መኪናቸዉን አስነስተዉ እብስ አሉ፡፡ የመጀመሪያየ ባይሆንም የከዚህ ቀደሞቹ ግን ጨዋዎች ነበሩ! ግን፤ አርፈንም እንድናርፍ አይፈቀድልንም እንዴ? እኛ እንሰራው የነበረው ፖለቲካ ፍጽም ሰላማዊና ህገ መንግስታዊ ነበር፡፡ አሁንም መብታችን ነዉ፡፡ የነአሞራዉ ደም የፈሰሰዉ ለዚህም እንደነበር እንረዳለን፡፡ተሸብራችሁ ከሆነ በስራችሁ እንጂ በኛ አይደልም፡፡ እኛ ግን ለግዜው ከጨዋታው ውጪ ስላደረጋችሁን በጨዋታው ሜዳ የለንበትም፡፡ ለማስጠንቀቂያውም ለመረጃውም ስርዓት አለው፡፡ የመንግስት አካል የሆነ ተቋም በፈለገዉ መንገድ ህጋዊ ሆኖ ማናገር ይችላል፡፡ መንግስትነት ትልቅ ሃላፊነትና ተቋም መሆኑን ልንነግራችሁ አቅም የለንም፡፡ የተበተነን የቀድሞ የፓርቲ አመራር ማስፈራራትና ማሰር ተራ ብቀላ ይመስላል፡፡ ተራ ህይወት እየመራንም፤አርፈን ተቀምጠንም ልትተዉን ካልቻላችሁ በግፉ መንገድ ግፉበት፡፡ እኛ ከማን እንበልጣለንና ነው!!!
የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ላይ የኢህአዴግ እስር እና ማስፈራሪያ ተጠናክሮ ቀጥሏል
በኢትዮጵያ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት የነበረውና በመላ ሀገሪቱ ፅህፈት ቤቶች ከፍቶ ሲንቀሳቀስ የነበረው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ላይ የኢህአዴግ እስር እና ማስፈራሪያ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለፀ፡፡ በተለይ ምርጫ ቦርድ ባለፈው የካቲት 2007 ዓ.ም. ፓርቲው የፊታችን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ ዋነኛ የኢህአዴግ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ መወሰኑን እና ለዚህም ይፋ የምርጫ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን በማፍረሱ የቀድሞው የአንድነት አመራሮች እና አባላት ከፖለቲካው እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡
ይሁን እንጂ የተወሰኑ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች እና አባላት ፓርቲያቸው በኢህአዴግ እና በምርጫ ቦርድ በይፋ ተነጥቆ እንዲፈርስ በመደረጉ የተወሰኑ አመራሮች እና አባላት ሰማያዊ ፓርቲን በይፋ ተቀላቅለው የፖለቲካ ትግሉን ቢጀምሩም አሁንም ከኢህአዴግ እስርና ማስፈራሪያ መዳን አልቻሉመ፡፡ በዚህም በርካታ የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ወጣት አመራሮች እና አባላት ሰማያዊ ፓርቲን ከተቀላቀሉ በኋላ እነ ስንታየሁ ቸኮል በእስር ላይ ይገኛሉ፡:
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፓርቲያቸው በምርጫ ቦርድ ፈርሶ፤ ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ለእኔ ለሚታዘዙልኝ በሚል ራሱ ቦርዱ ለመረጣቸው አካላት ቢያስተላልፍም በርካታ የቀድሞ የአንድነት አመራሮች ከፖለቲካ ድርጅት ትግል እንዲታቀቡ ቢደረግም፤ ማስፈራሪያና እስሩ ግን አሁንም ቀጥሏል፡፡ በዚህም ትናንት ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባልና የማኀበራዊ ጉዳይ ኃላፊ የነበረው አለነ ማፀንቱ ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከመኖሪያ ቤቱ በደህንነት እና በፖሊስ ኃይል ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ ከፍተኛ ድብደባ በመፈፀም የኢሜይል አካውንቱን የይለፍ ቃል በግድ በደህንነቶች ከተወሰደ በኋላ በአዲስ አበባ ጉለሌ ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፓርቲው ፕሬዘዳንት የነበረው አቶ በላይ ፈቃዱ እና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት የነበረው አቶ ተክሌ በቀለም በተመሳሳይ ዕለት በደህንነት ኃይሎች ከፍተኛ ማስፈራሪ እና ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፓርቲው በምርጫ ቦርድ ከፈረሰ በኋላ የስራ አስፈፃሚ አባል የነበረው አቶ ዳዊትአስራደን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች እስማኤል ዳውድ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ መሳይ ትኩዕ፣ ፋንቱ ዳኜ በደህንነት እና ፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸውና መደብደባቸው ይታወቃል፡፡ ቀደም ሲል የፓርቲው ወጣት ከፍተኛ አመራሮች የነበሩት አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ዳንኤል ሺበሺ እና ሀብታሙ አያሌው በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ አንድነት የፊታችን እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ450 በላይ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ማቅረቡን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በቀጠለው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴ ምክንያት የካቲት 2007 ዓ.ም. ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን አፍርሶ “ለእኔ ለሚታዘዙልኝ…” በሚል ጋዜጣዊ መግለጫ ራሱ ቦርዱ ለመረጠው አመራር የፓርቲውን ስም መስጠቱን ይፋ ማድረጉ አያዘነጋም፡፡
ወጣት ስንታየሁ ቸኮል 6 ወር ሲፈረድበት፤ ፋንቱ ዳኜ ከመኖሪያ ቤቱ ተወስዶ መታሰሩ ተሰማ
ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ ወጣቶች አመራር የነበረውና በአሁን ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ አባል ወጣት ስንታየሁ ቸኮል 6 ወር እስራት ተፈረደበት፡፡ ወጣት ስንታየሁ ቄራ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ሲቪል በለበሱ ደህንነቶች ተወስዶ ከታሰረ በኋላ የፌደራሉ ፍርድ ቤት ቄራ ምድብ ችሎት ቀርቦ የአካባቢው የኢህአዴግ ካድሬዎች ከመሰከሩበት በኋላ እንደተፈረደበት ታውቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ለቀረበበት ክስ መከላከያ ምስክር አሊያም የቅጣት ማቅለያ እንዲያቀርብ ቢጠይቀውም፤ ወጣት ስንታየሁ “ከሳሼም፣መስካሪየም፣ፈራጁም ኢህአዴግ ስለሆነ የመከላከያ ምስክር ብዬ ሰዎችን አላንገላታም፣የቅጣት ማቅለያም አላቀርም፤የፈለጋችሁትን ፍረዱ” ሲል ችሎት ላይ መናገሩ ትውቋል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ በችሎት የተናገርውና የቀረበበት ክስ ከዓመት በላይ የሚያስቀጣ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቱ በ6 ወር እስራት እንዲቀጣ መፍረዱ ታውቋል፡፡
ስንታየሁ ቸኮል ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ከቀድሞው አንድነት ፓርቲ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ የፀጥና ደህንነት ኃይሎች ተደጋጋሚ ሲታሰርና ሲደበደብ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ በተደረጉ በተለያዩ የስርዓቱ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ የስርዓቱን ድርጊት የሚያመለክቱ ልዩ መፈክሮችን ይዞ በመውጣትም ይታወቃል፡፡
በተያያዘ ዜና ሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ፀሐፊ የነበረው ፋንቱ ዳኜ ሳሪስ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች ተይዞ መታሰሩ ታውቋል፡፡ አቶ ፋንቱ በወቅቱ ሳሪስ ፖሊስ ጣቢያ ቢወሰድም እስካሁን ለምን እንደተያዘ እና እንደታሰረ የተገለፀ ነገር እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ወጣት ፋንቱ ከቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ጠንካራ ወጣት አመራሮች መካከል አንዱ እንደነበር ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች አባላቱ እየታሰሩና እየተደበደቡ መሆናቸው ገለፀ
በጋሞጎፋ ዞን በርካታ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች እየታደኑ እየታሰሩ መሆኑን የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪዎች ገልጸዋል፡፡ ከትናንት ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ጋሞ ጎፋ ዞን ጎፋ ወረዳ ሳውላ ከተማው ውስጥ በርካታ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች መታሰራቸውን የጋሞ ጎፋ ዞን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ በትናንትናው ዕለት በጋሞጎፋ ዞን ዳራማሎ ወረዳ ቅስቀሳ ላይ የነበሩ 17 የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ታስረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጋሞጎፋ ዞን ቦንኬ ወረዳ ለፖሊስ “ለሰማያዊ ፓርቲ የሚቀሰቅስ ማንኛውም አካል ላይ እርምጃ ውሰዱ” የሚል ትዕዛዝ መተላለፉን የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪዎች ገልፀዋል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሮ ወረዳ ጎራና ቀበሌ የሰማያዊ ፓርቲ የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ የሆነው አቶ ዮናታን ሰይድ በካድሬዎች ድብደባ እንደተፈፀመበት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡ አቶ ዮናታን ዛሬ ከዋቱ 3፡20 አካባቢ ጊራና ከተማ ላይ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረገ በነበረበት ወቅት የብአዴን/ኢህአዴግ ካድሬዎች ‹‹ለምን ትቀሰቅሷላችሁ? ደፍራችሁናል!›› በማለት ድብደባ እንደፈፀሙበት ገልጾአል፡፡ ሆስፒታል ሆኖ በስልክ ያነጋገረን አቶ ዮናታን በተለይ እግሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ገልጾአል፡፡
መንግስት ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም አይ ኤስ አይ ኤስን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ሰበብ እየታደኑ እየታሰሩ መሆኑን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡ ሀሙስ ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም ብሌን መስፍንና ተዋቸው ዳምጤ ከመስሪያ ቤት ተይዘው የታሰሩ ሲሆን ሚያዝያ 24 ቀን 2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበው ‹‹ሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተደረገውን አመጽ መርታችኋል፡፡›› በሚል ፖሊስ ክስ እንዳቀረበባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ ዛሬ ሚያዝያ 26 ቀን 2007 ዓ.ም ማቲያስ መኩሪያ ቤቱ ውስጥ እያለ በፖሊስ ተይዞ ታስሯል፡፡ ማቲያስ፣ ብሌንና ተዋቸው ወረዳ 10 (ላዛሪስት ፖሊስ ጣቢያ) ታስረው ይገኛሉ፡፡ ይህንን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ የሚደረገው እስርም “መንግስት በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የጀመረውን የሀሰት ክስ እውነት ለማስመሰል የታቀደ ነው፡፡ ፖሊስ ምርመራ ሳይጨርስ በሀሰት 20 አባላትንና 6 አመራሮችን አስረናል ብለው ነበር፡፡ እነሱ የፈለጉት ይህን ሚዲያ ላይ ወጥተው በሀሰት የፈፀሙትን ውንጀላ ማሰመሰል ነው፡፡” ሲል አቶ ዮናታን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
በሌላ ዜና በየ ክፍለ ሀገሩ የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ ደህንነትና ፖሊስ የሚፈፅመው ድብደባ አሁንም መቀጠሉ ተገልጾአል፡፡ የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪና የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነችው የሀሳብ ጌታቸው “ለሰማያዊ ፓርቲ ወረቀት በትነሻል” በሚል ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀሙባት ተገልጾአል፡፡
ፖሊስ በ”በሁከትና ብጥብጥ” ተጠርጣሪዎች ላይ ሦስት መዝገብ አደራጅቻለሁ አለ
•እነ ወይንሸት ለሁለተኛ ጊዜ 6 ቀን ተቀጥሮባቸዋል
•”ወይንሸት ከአሁን በፊትም ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ስታሸብር ነበር” ፖሊስ
ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስ ሊቢያ በሚገኙ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ የሽብር ድርጊት ለማውገዝ ጠርቶት በነበረው ሰልፍ ላይ “ሁከትና ብጥብጥ አስነስታችኋል፤ ተካፍላችኋልም” በሚል ፖሊስ ባሰራቸው ሰዎች ላይ ሦስት የተለያዩ መዝገቦች ማደራጀቱን አስታውቋል፡፡
ሚያዝያ 22 ቀን 2007ዓ.ም በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቀረቡ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ሌሎች በዕለቱ የተያዙ ሰዎችን በተመለከተ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ እንደገለጸው፣ ፖሊስ የራሱን ቡድን በማዋቀር ተጠርጣሪዎችን በሦስት መዝገቦች ስር እንደየተሳትፏቸው አደራጅቻለሁ ብሏል፡፡ በዚህ መሰረት በሶስተኛው መዝገብ ላይ ያካተታቸውን በርካታ ታሳሪዎች አጣርቶ መልቀቁን የገለጸው ፖሊስ፣ በሁለተኛውና በአንደኛው መዝገብ ላይ ባሉት ተጠርጣሪዎች ግን ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጹዋል፡፡
አንደኛው መዝገብ ላይ በእነ ወይንሸት ሞላ መዝገብ 5 ሰዎች የተካተቱ ሲሆን አራቱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቸው፤ አንደኛዋ ተጠርጣሪ ደግሞ ፖሊስ የፓርቲው አባል እንደሆነች የሚገልጸው፣ እሷ ግን አባል አለመሆኗን የገለጸች መሆኗን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስለሆነም በዚህ መዝገብ የተካተቱት ወይንሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ጸጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ማስተዋል እና የፓርቲው አባል ያልሆነችው ቤተልሄም ይገኙበታል፡፡ ማስተዋል በዛሬው ዕለት ቀደም ብሎ የተሰጠው የቀጠሮ ቀን ስላልደረሰ ፍርድ ቤት አልቀረበም፡፡ ቤተልሄም ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሳልሆን አባል ነሽ እየተባልኩ ምርመራ ይደረግብኛል፤ ሌሊት እየተጠራሁ እመኝ እየተባልኩ ነው›› ስትል ለፍርድ ቤቱ ገልጻለች፡፡
በሁለተኛው መዝገብ ላይ ደግሞ 15 ተጠርጣሪዎች ተካትተዋል፡፡ ፖሊስ በዚህ መዝገብ በተካተቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ክሱን ሲያሰማ እንዲህ ብሏል፤ “ተጠርጣሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ሲያደርጉ ‹ጠንካራ መሪ እንጂ ጠንጋራ መሪ አንፈልግም›፣ ‹ወያኔ አሳረደን›፣ ‹ፍትህ የለም! በማለት ሁከት እንዲነሳ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡”
የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በምርመራ ወቅት የገጠማቸውን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ ያሰሙ ሲሆን፣ በተለይ የሚደረግባቸው ምርመራ ከፓርቲው ጋር የተያያዘ እንጂ ከተጠረጠርንበት ጉዳይ ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ምርመራው ከጉዳዩ ጋር የሚገናኝ አይደለም፤ ሌሊት ሌሊት እየተጠራሁ ምርመራ ይደረግብኛል፡፡ የፓርቲ አባል መሆን ወንጀል እስኪመስለኝ በፓርቲ አባልነቴ ጫና ይደረግብኛል፡፡ በዚያ ላይ የጤና እከል ገጥሞኛል፤ ህክምና ያስፈልገኛል” ስትል ለፍርድ ቤቱ ያስረዳችው ወይንሸት ሞላ፣ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት እንዲሰጣት ጠይቃለች፡፡
በሁለቱም መዝገብ የተካተቱት ሁሉም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፖሊስ በበኩሉ በመጀመሪያው መዝገብ ላይ ያሉት እነ ወይንሸት ላይ የምርመራ ስራውን እንዳልጨረሰ በመግለጽ 14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ በተለይ ወይንሸት ሞላ ላይ ፖሊስ፣ “ከአሁን በፊትም ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር ተመሳስላ በመልበስ ስታሸብር ነበር” በማለት ዋስትና እንዳይሰጥና የጠየቀው የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ በሁለተኛው መዝገብ ላሉት ደግሞ 7 ቀን ፖሊስ ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ በሁለቱም መዝገብ ላይ በተመሳሳይ የ6 ቀን ጊዜ በመስጠት ለሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
መንግስት በጠራው ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች እስር አሁንም እንደቀጠለ የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ በትናንትናው ዕለትም ሦስት የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አባላት (አንደኛው አሁን ላይ የሰማያዊ አባል) መታሰራቸው ይታወሳል፡፡
በተያያዘ ዜና ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስ ሊቢያ በሚገኙ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ የሽብር ድርጊት ለማውገዝ ጠርቶት በነበረው ሰልፍ ሳይጀመርና ከሰልፉ በኋላ ተይዘው የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ቤት ተበረበረ፡፡ ካሳንቺስ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ትናንት ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ቀርበው የ6 ቀን ቀጠሮ ከተሰጠባቸው በኋላ ምሽት ላይ ቤታቸው መበርበሩንና ንብረቶቻቸው መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በብርበራው ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በሰላማዊ ሰልፍና በሌሎች አጋጣሚዎች የሚለብሱት የሰማያዊ ፓርቲ አርማ ያለበት ቲሸርት፣ የምርጫና ሌሎች ቅስቀሳ ወረቀቶችም ለ‹ምርመራ› ተወስደዋል፡፡
ቤታቸው ለሰዓታት የተበረበረባቸው ወይንሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ጸጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬና ማስተዋል ፍቃዱ ሲሆኑ ወይንሸት ሞላ የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ ወረቀቶች፣ የሰማያዊ ፓርቲ አርማ ያለበት ቲሸርት፣ ሲዲዎች፣ አርማ የሌለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ (በተናጠል አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የሆነ)፣መጽሐፎች እና ሌሎችም ህጋዊ ሰነዶች እንደተወሰዱባት ገልጻለች፡፡ ዳንኤል ተስፋዬ የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አርማ ያለበት ቲሸርት፣ በአንድ ላይ ያስጠረዛቸው የፋክትና የአዲስ ጉዳይ እትሞች፣ ሲዲዎችና ካሴቶች ተወስደውበታል፡፡ በተመሳሳይ ኤርሚያስ ጸጋዬ ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተር፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሰነዶች፣ ሲዲዎች፣ ማስታወሻ ደብተሮችና ሌሎችም ህጋዊ ሰነዶች ተወስደውብኛል ብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በመሻር ዋስትና የከለከላቸውን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እየወሰደ እየመረመረ ነው፡፡ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ የታሰሩ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም ጠዋት በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርበው የ6000 ብር የሰው ዋስትና እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበር ቢሆንም ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በመሻር በእስር አቆይቷቸዋል፡፡
ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ጥሶ በአሁኑ ወቅት ካሳንቺስ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ አስሯቸው የሚገኙትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ማዕከላዊ እየወሰደ እየመረመረ ይገኛል፡፡ በዛሬው ዕለት ዳንኤል ተስፋዬ ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት ተወስዶ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ውስጥ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ምንጮች ከስፍራው አስታውቀዋል፡፡









