Tag Archives: Oromia Guji zone

በጉጂ ዞን ያለው ውጥረት እስካሁንም አለመብረዱ ተገለፀ

በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል በሚገኘው ጉጂ ዞን ባለፈው መጋቢት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. በኦዶ ሻኪሶ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና ከዞኑ ከተማ መስተዳደር ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ሁለት ወጣቶች በፌደራል ፖሊስ መገደላቸውን ተከትሎ የፈጠረው ውጥረት እስካሁንም አለመብረዱ ተገለፀ፡፡ እንደምንጮች ገለፃ ከሆነ የ9ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ብስራት ኃይሌ እና በግብርና ሙያ የሚተዳደረው ወጣት ሀለቄ ሮባ በከተማው የዕለት ስራውን ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ ሳለ በፌደራል ፖሊስ በተወሰደ የጥይት ተኩስ እርምጃ ወዲያው ህይወታቸው አልፏል፡፡

በፌደራል ፖሊስ ተገደሉ ከተባሉት ተማሪዎች በተጨማሪ በከተማው ማንነቱ ባልታወቀ አካል በተተኮሰ ጥይት አንድ የፌደራል ፖሊስ ላይ ከፍተኛ አደጋ በመድረሱ ወዲያው ወደ አዲስ አበባ ለህክምና መላኩን እና በከተማውም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሌሎች ነዋሪዎች ላይ በፖሊስ በተወሰደ የኃይል እርምጃ ቆስለው በከተማው ሆስፒታል ህክምና እርዳታ ያገኙም እንዳሉበት የአዲስሚያ ምንጮች ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በጉጂ ዞን ባሉ 15 ወረዳዎች እና በሶስቱ ከተማ መስተዳደሮች ነጌሌ ቦረና፣ ክብረ መንግስትና ኦዶሻኪሶ በነዋሪውና በመንግስት ኃላፊዎች መካከልበተፈጠረ አለመግባባት እስካሁን ውጥረቱ አለመርገቡ እና ችግሩ በዞኑ ባሉ ገጠሮች ድረስ መዛመቱም ተጠቁሟል፡፡ የግጭቱ መንስኤም ተማሪዎቹ ለአስተዳዳሪዎቹ ባነሱት የመጠጥ ውሃ፣ የመብራትና ተያያዥ የመብት ጥያቄዎች መሆኑንም መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በዚህ ዙሪያ የመንግስት ኃላፊዎች እስካሁን ምንም ሰጡት ማስተባበያም ሆነ መልስ ባይኖርም፤ በወጣቶቹ መገደል በተፈጠረው ውጥረት የአካባቢው የመንግስት ሹማምንት ዛሬ እሁድ መጋቢት 7 ቀን 2006 ኣ.ም. ከጠዋቱ 3 ሰዓት በጉጂ ዞን አንድነት ፓርቲ የገንዘብና ንብረት ክፍል ኃላፊ የሆኑትን አቶ ዮሐንስ ኢብሶን ተማሪዎቹ ላነሱት ጥያቄ ምክንያት ናቸው በማለት መንግስት ማሰሩ የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡

በኦሮሚያ ሻኪሶ ሁለት ተማሪዎች በፌደራል ፖሊስ በመገደላቸው ውጥረት መንገሱ ተሰማ

 

በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል በሚገኘው ጉጂዞን ኦዶ ሻኪሶ ከተማ በተማሪዎችና በከተማው አስተዳደር መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የፌደራል ፖሊስ ጣልቃ በመግባት በወሰደው የኃይል እርምጃ አንዲት ሴት እና አንድ ወንድ በአጠቃላይ ሁለት ተማሪዎች ህይወት በማለፉ እና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በመቁሰላቸው የኦዶ ሻኪሶ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ተጠቁሟል፡፡ pic

የግጭቱ መንስኤ ተማሪዎቹ “በከተማውና አካባቢው የመጠጥ ውሃ አገልግሎት የለም፣ አንድ ባለ 25 ሊትር ጀርካን ውሃ በ 7 ብር እየተሸጠ ነው፣ በቂ የመብራት አገልግሎትም የለም፣ ከህዝቡ ሚሰበሰበው ግብር እና ከመንግስት የሚመደበው በጀት እስካሁን ምን ላይ እየዋለ ነው? ህብረተሰቡም እኛ ምበውሃጥም እየተጎዳን አስተዳደሩ እስከዛሬ ለምን ዝም አለ?” የሚሉ ጥያቄዎች በመነሳታቸው፤ የአስተዳደር አካላት ተማሪዎቹን “እናንተ ምን አገባችሁ፣ አርፋችሁ ተማሩ፤ካልሆነ እርምጃ እንወስዳለን” የሚልምላሽ በመሰጠቱ ተማሪዎችን እንዳስቆጣ የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የፌደራል ፖሊስ ድንገት ጣልቃ በመግባት ተቃውሞ በሚያሰሙ ተማሪዎች ላይ እርምጃ በመውሰዱ የከተማው ነዋሪዎችም ተቃውሞውን መቀላቀላቸው የአዲስሚዲያ ምንጮች ከስፍራው ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የከተማውና የአካባቢው ነዋሪ ከፌደራል ፖሊስ ጋር መፋጠጡን፣ ይህ እስከተዘገበበት ሰዓት ድረስም በከተማው የጦር መሳሪያ ተኩስ ሁሉ እየተሰማ መሆኑንም ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሟቾቹ ሁለቱ ተማሪዎች አስከሬን በሆስፒታል እንደሚገኝ እና ወላጆችም ወደሆሲፒታሉ እንዳይገቡ በፌደራል ፖሊስ መከልከላቸው እንዲሁም በከተማው ተወስኖ የነበረው ቁጣም ወደ ገጠሩ ነዋሪበ መስፋፋት በርካቶች በቁጣወደ ከተማው እየገቡ መሆኑንም ምንጮች አስረድተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በከተማው ከፍተኛው ጥረት መንገሱም ተጠቁሟል፡፡

እንደምንጮች ገለፃ ከሆነ ችግሩ የተፈጠረው የኦዶ ሻኪሶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው አስተዳደሩ ጥያቄያቸውን በቀጥታ ወደ ፖለቲካ በመቀየር የፌደራል ፖሊስ ተጠርቶ በቀጥታ የኃይል እርምጃ በመውሰዱ የሁለት ተማሪዎች ህይወት ወዲያው በማለፉ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ በአሁን ሰዓትም በከተማው በተለያዩ ቦታዎች የእሳት ቃጠሎ፣ የህንፃዎች መስታወት መሰባበር፣ ሌሎች ንብረቶች እየወደሙ መሆናቸውን እንዲሁም ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ እየተሰማ መሆኑንም ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ አዲስሚዲያ ይህንን ለማጣራት የኦሮሚያ ፖሊስ አዛዥ ናቸው ወደተባሉት ኮማንደር አበበ እና የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዳ ሮቤ ጋር ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረገም ለጊዜው አልተሳካም፡፡ ኦዶ ሻኪሶ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የወርቅ ማዕድን ከሚመረትባቸው አካባቢዎች ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል፡፡

%d bloggers like this: