Tag Archives: TPLF Democracy

የኢህአዴግ መንግስት በሰሜን ጎንደር የአንድነት ፓርቲ አመራሮችን ማሰሩ ተገለፀ

gon1በዛሬው ዕለት ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ከለሊቱ 11:00 ሰዓት ላይ በሰሜን ጎንደር ዞን በምዕራብ አምርማጭሆ አብርሃ ጅራ ከተማ የአንድነት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አንጋው ተገኝ እና የወረዳው ሌላ አመራር አባላት አቶ አባይ ዘውዱ እና አቶ እንግዳው ዋኘው የፌደራል ፖሊሶች የቤታቸውን በር ገንጥለው በመግባት እየደበደቡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸው ተጠቁሟል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪም ወደ ሌላ ቦታ እንዳይወስዷቸው ፖሊስ ጣቢያውን ከቦ እየጠበቀ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በተያያዘ ዜና በዛው ሰሜን ጎንደር ዞን በመተማ ከተማ የአንድነት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ በላይነህ ሲሳይ በፖሊሶች በዛሬው ዕለት ከለሊቱ 11:00 ሰዓት በፖሊሶች ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።

ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ መልኩ በወላይታ ዞን የአንድነት አመራሮችም ከፍተኛ ድብደባና ወከባ እንደደረሰባቸው በፍኖተ ነፃነት የተዘገበ ሲሆን፤ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ በተለይም የአንድነት አመራሮች ላይ በኢህአዴግ የሚፈጠረው ጫና እንደቀጠለ መሆኑን የፓርቲው ልሳን ዘገባ ያመለክታል፡፡

gon2ከዚህ ቀደምም አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ የሺዋስ ይሁንዓለሙ፣ ሻምበል ዮሐንስ ተረፈ፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው ፤በቅርቡ ደግሞ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው ከአረና እና ሰማያዊ
ፓርቲ አመራር ከሆኑት አቶ አብርሃ ደስታና አቶ የሺዋስ አሰፋ ጋር መታሰራቸው አይዘነጋም፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በተመሰረተበት ክስ 3 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት

የቀድሞ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና መስራች፣ የአዲስ ታየምስ መፅሔት፣ የልዕልና ጋዜጣ በመጨረሻም የፋክት መፅሔት ባልደረባና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በተመሰረተበትና ጥፋተኛ በተባለበት 3 ክሶች መካከል በአንዱ ክስ ብቻ የ3 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት፡፡ጋዜጠኛው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ በመሰረተበት ክስ ጥፋተኛ የሚል ብይን ከሰጠ በኋላ ቅጣት የተጣለበት በ2004 ዓ.ም. በፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበረበት ወቅት በፃፋቸው ፅሑፎችን መሰረት አድርጎ መሆኑ ታውቋል፡፡

temesegen dጋዜጠኛው የተፈረበት፤ዛሬ ጥቅምት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋለው ችሎትም ጋዜጠኛው ጥፋተኛ ከተባለበት 3 ክሶች መካከል በአንዱ ክስ ብቻ የ3 ዓመት ፅኑ እስራት ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ በዚህም መሰረት ጋዜጠኛ ተመስገን በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንደሆነ፤ወደ አቃቂ ቂሊንጦ ወደሚገኘው ወህኒ ቤት ተወስዷል፡፡

የጋዜጠኛው ተከላካይ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን ቅጣቱን እና ፍርዱን በሚመለከት ይግባኝ እንደሚጠይቁ የተገለፀ ሲሆን፤ በቅጣት ፍርዱ አቃቤ ህጉም ሆኑ ተከላካይ ጠበቃው የቅጣት ማክበጃም ሆነ ማቅለያ አለመጠየቃቸው ተጠቅሟል፡፡ በኢትዮጵያ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ የታሰሩት ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች ቁጥር 18 መድረሱ ታውቋል፡፡

ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት በፃፉት ፅሑፍ የተከሰሱ፣የታሰሩም ሆነ የተፈረደባቸው ጋዜጠኞችም የሉም የሚል ተደጋጋሚ ማስተባበያ ቢሰጥም፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጨምሮ ከታሰሩት 18 ጋዜጠኞችና ብሎገሮች መካከል 15ቱ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችና ብሎገሮች የቀረበባቸው ክስናም ሆነ ፍርድ ከስራቸው ጋር በተያያዘ በፃፉትና በተናገሩት መሆኑ የተመሰረተባቸው ክስ ያመለክታል፡፡