ከእስር የተለቀቁት የዞን 9 ብሎገሮች እና ጋዜጠኞች ምስጋና አቀረቡ
በድንገት ከያለንበት ተይዘን እንደታሰርነው አፈታታችንም ግራ የሚያጋባ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ክሶች ቀርበውብን እያለ ግማሾቻችን ‹ክስ ተቋርጦላችኋል› ተብለን ተፈታን፣ ግማሾቻችን ደግሞ ‹ነፃ ናችሁ› (ከሳሽ በነፃነታችን ላይ ይግባኝ መጠየቁ እንዳለ ሁኖ) ተብለን ይሄው ወጥተናል፡፡ ቀሪ ክስ ይዘን በዋስ ወጥተን እየተከራከርንም ያለን አለን፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል የሁላችንም ዕምነት ግን አንድም ቀን ሊያሳስረን የሚገባ ወንጀል አለመፈፃችን ማመናችን ነው፡፡ መፈታታችን ጥሩ ሁኖ፤ መታሰር በፍፁም የማይገባን ነበርን፡፡ መፃፋችን እና ሕግ እንዲከበር መጠየቃችን ሀገሪቱ አገራችን እንድትሻሻል እና ሁላችንም ዜጎች የተሻለ ህይወት አንዲኖራቸው ከመሻት ባለፈ ሌላ ነገር አልነበረውም/የለውም፡፡ ነገር ግን ይህን በማድረጋችን ተገርፈናል፣ ተዘልፈን-ተሰድበናል፣ ታስረናል ተሰደናልም፡፡ ይህ በፍጹም አይገባንም ነበር፡፡
የእኛ መታሰር ፖለቲካዊ ንቃት የፈጠረላቸው ሰዎች እንዳሉ ሲነግሩን ደስ ይለናል፡፡ በእኛ መታሰር ምክንያት ለመጠየቅና ለመፃፍ በጣም እንደሚፈሩ የሚነግሩን ሰዎች ስናገኝ ደግሞ እናዝናለን፡፡ የመታሰራችን ጉራማይሌ ስሜት እንደዚህ ነው፡፡ ሳይገባን በመታሰራችን የነቁ መኖራቸውን በማወቃችን የምነደሰተውን ያክል፤ ሳይገባን በመታሰራችን የተሰበሩና ከተዋስኦ መድረኩ የራቁ እንዳሉ ስናውቅ እጅግ እናዝናለን፡፡
መታሰር በደል ነው፡፡ ብዙ ነገር ያጎድላል፡፡ መታሰር መልካም ነው፡፡ ብዙ ነገር ያስተምራል፡፡ እኛ በመታሰራችን ሀገራችን የበለጠ እንድናውቃት ሁነናል፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ነፃነት አሁንም ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ተረድተናል፡፡ ሕግን መከታ አድርገው የኖሩ ‹ስም የለሽ› ዜጎች ሕጉ ሲከዳቸውና እነሱ ላይ ‹በላ› ሲያመጣባቸው ታዝበናል፡፡ ከሁሉም በላይ ፍትህ የሌለባት ሀገር ለዜጎቿ የማትመችና አገር እንደሆነች አይተናል፡፡
በእስራችን ወቅት የተለያዩ በደሎች በተቋም ደረጃ ደርሰውብናል፡፡ ግን አገር ነውና ከይቅርታ የሚያልፍ አይደለም፡፡ ለበደላችሁን አካላት እናንተ ይቅርታ ባትጠይቁንም፤ እናንተ የፈለጋችሁትን ባለማድረጋችንና ሕግን መሰረት አድርገን በመኖራችን ስላስከፋናችሁ እባካችሁ ይቅር በሉን፡፡
በዚህ ሁሉ መሃል ግን እናንተ አላችሁ፡፡ ጓደኞቻችንም ናችሁ፤ ዘመቻ አድራጊዎችም ናችሁ፤ ቤተሰቦቻችንም ናችሁ፤ ጠያቂዎቻችንም ናችሁ፤ ጠበቆቻችንም ናችሁ፣ የመንፈስ አጋሮቻችንም ናችሁ ርቀት ሳይገድባች የጮሃችሁልን አለም አቀፍ የመብት ጠያቂዎችም ናችሁ … በመታሰራችን የተረዳነው አንዱ ትልቅ ነገር የናንተን መልካምነት፣ የናንተን አጋርነት እና የናንተን የማይሰለች ድካምና ፍቅር ነው፡፡ እናንተ ባትኖሩ ‹አጭሩ› የእስር ጊዜያችን ይረዝምብን ነበር፤ ‹ቀላሏ› እስር ትከብድብን ነበር፡፡ ምስጋና ለናንተ፤ እስራችን ‹አጭር› – ፈተናችን ‹ቀላል› እንዲሆን አድርጋችሁልናልና፡፡
እናንተ ወዳጆቻችን ለሁሉም ነገር – እልፍ ምስጋና፡፡
እናመሰግናለን!
የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች
የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንደሌሉ ገለፀ
• “የስርዓቱን ሽፍትነት ያመላክታል” 3ኛ ተከሳሽ አቶ ደናሁን ቤዛ
• “የሚቀርብልን ምግብ ለእንሰሳትም መቅረብ የማይገባው ነው” 2ኛ ተከሳሽ አቶ አሸናፊ አካሉ
በዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከ2ኛ -5ኛ መዝገብ ለተከሰሱት አቶ አሸናፊ አካሉ (2ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ደናሁን ቤዛ (3ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን (4ኛ ተከሳሽ) እና አቶ አንሙት የኔዋስ (5ኛ ተከሳሽ) በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሌሉ ማረሚያ ቤቱ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛው ወንጀል ችሎት በላከው ደብዳቤ ገልፆአል፡፡ 19ኛ ወንጀል ችሎት ሀምሌ 29 ቀን 2007 ዓ.ም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ለምን እንዳላቀረበ እንዲያብራራ፣ እንዲሁም ለምስክርነት እንዲያቀርብ ለዛሬ ለጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበር ቢሆንም ማረሚያ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው ቃሊቲ እንደሌሉ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡
ተከሳሾቹ ማረሚያ ቤቱ ሲያጉላላቸው ቆይቶ አሁን የለም ማለቱ ትክክል እንዳልሆነ የገለፁ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ አቶ አሸናፊ አካሉ ማረሚያ ቤቱ ምላሽ የሰጠው በአራተኛው ትዕዛዝ መሆኑን ጠቅሶ የፍርድ ሂደታቸውን ከሚገባው በላይ እያጓተተ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ገልፆአል፡፡ ‹‹መከላከል ከጀመርን አንድ አመት ከስድስት ወር ሆነ፡፡ በግዞት ነው ያለነው፡፡ የሚቀርብልን ምግብ ለእንሰሳትም መቅረብ የማይገባው ነው›› ያለው አቶ አሸናፊ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ‹‹ፌዝ ነው›› ብሎታል፡፡
3ኛ ተከሳሽ አቶ ደናሁን ቤዛ በበኩሉ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት ሲጠቅሱ አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የሞትና የእድሜ ልክ ፍርደኛ እንደሆኑ በመጠቆም ተቃውሞ አሰምቶ እንደነበር፣ የእድሜ ልክና የሞት ፍርደኛ ቃሊቲ እንደሚታሰር ገልፆ ማረሚያ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው እንደሌሉ መግለፁ ‹‹የስርዓቱን ሽፍትነት ያመላክታል›› ብሏል፡፡ ‹‹የእድሜ ልክ ወይንም የሞት ፍርደኛ የት ነው የሚታሰረው?›› ሲልም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
3ቱ ተከሳሾች የፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉና ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ አንዳርጋቸውን እንደያዙ በቴሊቪዥን መግለፃቸውን አስታውሰው አሁንም ለሁለቱ አካላት ደብዳቤ እንደሚፅፉ ለፍርድ ቤቱ አሳውቀው የነበር ቢሆንም ከ6ኛ-9ኛ ያሉት ተከሳሾች ማረሚያ ቤቱ በፈጠረው ችግር የአቶ አንዳርጋቸውን ምስክርነት ለመስማት የፍርድ ሂደታቸው እየተጓተተባቸው በመሆኑ የአቶ አንዳርጋቸው ምስክርነት ቀርቶ ብይን እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ሆኖም ግን 4ኛ ተከሳሽ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን ‹‹ከአንዳርጋቸው ጋር ተገናኝተህ መመሪያ ተቀብለሃል ስለተባልኩ አቶ አንዳርጋቸው መጥቶ መመስከር አለበት›› ሲል አሁንም አቶ አንዳርጋቸው እንዲቀርቡለት ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱም 4ኛ ተከሳሽ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንዲቀርቡለት የሚያቀርበውን አቤቱታ ተመልክቶ ይገኙበታል ተብሎ ለታሰበው ተቋም ትዕዛዝ ለመስጠት ለጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ መሰጠቱን ነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
የሎሚ መፅሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ግዛው ታዬ የ18 ዓመት እስራትና የ100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተላለፈበት
የሎሚ መፅሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ግዛው ታዬ የ18 ዓመት እስራትና የ100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲሁም በመፅሔት አሳታሚ ድርጅቱ ላይ የ200 ሺህ ብር ቅጣት ተወስኖበታል። ጋዜጠኛ ግዛው ታዬ ከዓመት በፊት የሶስት ዓመት ከ3 ወር እስራት እንደተፈረደበት ይታወሳል።
ከ800 ሺህ ብር በላይ ታክስ በማጭበርበርና በሌሎች 14 ክሶች ጥፋተኛ የተባለው የሎሚ መጽሄት ዋና ስራ አስኪያጅ በ18 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ተወሰነ።
ውሳኔውን የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 8ኛ የወንጀል ችሎት ነው ያስተላለፈው።
ተከሳሾቹ ዳዲሞስ ኢንተርቴይንመንትና የፕሬስ ስራዎች ድርጅት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እንዲሁም የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ታዬ ግዛው ናቸው።
የፌደራል ገቢዎች እና ጉሙሩክ ባለስልጣን አቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው፥ ድርጅቱም ሆነ ስራ አስኪያጁ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ክሱ እስከተመሰረተበት ድረስ ለተከታታይ 5 ዓመታት ኦዲት አልተደረጉም።
በዚህ ሂደትም ድርጅቱም ሆነ ግለሰቡ የታክስ ማጭበርበሮችን ሲያከናውን ቆይቷል ሲል የአቃቤ ህግ ክስ ያስረዳል።
የተጨማሪ እሴት ታክስ እና የገቢ ግብር መሰወር የሚለውም በወንጀል ድርጊቱ ማስረጃዎች ጉዳይ ሲሆን፥ እንደ አቃቤ ህግ ገለጻ በዚህ ሂደት ውስጥ ድርጅቱ እና ስራ አስኪያጁ ለመንግስት መግባት የነበረበትን ከ800 ሺህ ብር በላይ አሳጥተዋል ይላል።
በዚህ የክስ መዝገብም ግለሰቡ በችሎቱ አልቀረበም።
ይህን ተከትሎም የክስ ሂደቱ በሌሉበት እንዲቀጥል በተሰጠው በይን መሰረት አቃቤ ህግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።
ጉዳዩን ሲመለክት የቆየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 8ኛ የወንጀል ችሎት በተከሳሾች ላይ የቀረበው ማስረጃ ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው የሚያረጋግጥ ነው ሲል ቅጣቱን አስተላልፏል።
የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስምንተኛ የወንጀል ችሎት ዛሬ በዋለው ችሎት ዳዲሞስ ኢንተርቴይንመንትና የፕሬስ ስራዎች ድርጅት በ200 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲሁም የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛውታዬ ላይ ደግሞ የ18 ዓመት ጽኑ እስራት እና የ100 ሺህ የገንዘብ ቅጣት አስተላልፏል።
የድርጅቱ ሎሚ መፅሔት (ዳዲሞስ ኢንተርቴይመንት) ባለቤትና ማኔጅንግ ዳይሬክተሩ አቶ ግዛው ታዬ ከዚህ በፊት “አመጽ በማስነሳት እና መሰል የሽብርተኝነት ወንጀሎች” ክስ ተመስርቶበት በ50 ሺህ ብር ዋስ ከተለቀቀ በኋላ መሰደዱ ይታወቃል፡፡ የአሁኑ ክስና ፍርድም ተከሳሹ በሌለበት ተወስኗል፡፡
ፍርድ ቤቱ ያሳለፈውን ውሳኔ በተመለከተ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን/ሬዲዮ ፋናን/ ዋቢ በማድረግ ቃልኪዳን ትዩብ ዘግቧል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ ዓለም አቀፍ ተሸላሚ ሆነ
በሽብርተኝነት ተከስሶ 18 አመት የተፈረደበትና በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ ደረጃ አንድ ሰብዓዊነት (PEN Canada’s One Humanity Award) ሽልማት ተሸላሚ መሆኑን ፔን ካናዳ ይፋ አድርጓል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በፈረንጆቹ ግንቦት 2012 የባርባር ጎልድ ስሚዝ ሽልማት እንዲሁም በሰኔ 2014 የጎልደን ፔን ሽልማት ተሸላሚ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ በካናዳ ቶሮንቶ እየተደረገ በሚገኘው 36ኛው ዓለም አቀፍ የፀሃፊዎች ፌስቲባል የፔን ካናዳ ደረጃ አንድ ሰብዓዊነት ሽልማትን ተሸልሟል፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 የአረብ አብዮትን ተከትሎ መንግስት ለውጥ የማያደርግ ከሆነ ተመሳሳይ ህዝባዊ ንቅናቄ በኢትዮጵያም ሊከሰት ይችላል የሚል አስተያየቱን ማንጸባረቁን ተከትሎ ለእስር የተዳረገውና በፀረ ሽብር ህጉ ተከስሶ 18 አመት የተፈረደበት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ በበርካታ የሰብአዊ መብት ተቋማት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ዓለማቀፍ መብቱን መጠቀሙን በማስታወስ እስክንድር የህሊና እስረኛ እንደሆነ በመግለፅ ከእስር እንዲለቀቅ መጠየቃቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ከእስር እንዲለቅ ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በእስር ቤቱ ከሚደረግበት ከፍተኛ ቁጥጥርና ጫና ባሻገር ከቤተሰብ ውጭ እንዳይጠየቅ ተከልክሎ ይገኛል፡፡
ምንጭ፡ ነገረ ኢትዮጵያ
በፍቃዱ ሀይሉ በ20 ሺህ ብር ዋስ ከእስር ተለቀቀ
ባለፈው ጥቅምት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. አራቱ የዞን ዘጠኝ አባላት መካከል ናትናኤል ፈለቀ፣ አቤል ዋበላ፣ አጥናፍ ብርሃኔ እና በሌለችበት ክስ የተመሰረተባት ሶሊያና ሽመልስ) በነፃ እንዲለቀቁ ሲወሰን፤ ዛሬ ጥቅምት 10 ቀን 2088 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በወንጀለኛ መቅጫ ህግ 257/ሀ እንዲከላከል ተብይኖበት የነበረው በፍቃዱ ኃይሉ በ20 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲለቀቅ ተወሰነ፡፡
ብሎገርና ጋዜጠኛ በፍቃዱ ሀይሉ ጥቅምት 5 ቀን 2008 ዓ.ም ለልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ጠይቆ በነበረው መሰረት ለዛሬ ጥቅምት 10/2008 ዓ.ም የዋስትናውን ጉዳይ ለማየት ቀጠሮ የሰጠው የልደታ ፍርድ ቤት በ20 ሺህ ብር ዋስ ወጥቶ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል ወስኗል፡፡
አራቱ የዞን ዘጠኝ አባላት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ በተወሰነበት ወቅት ክሱ ከሽብርተኝነት ወጥቶ በማስረጃነት የቀረቡበት ፅሁፎች አመፅ ቀስቃሽ ናቸው በሚል በወንጀለኛ መቅጫ ህግ 257/ሀ እንዲከላከል የተወሰነበት በፍቃዱ ሀይሉ መከላከያ ምስክሮቹን እንዲያሰማ ለህዳር 27 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡




