Tag Archives: Yilkal Getnet

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በድጋሚ የሰማያዊ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ

አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ያደረገው ሰማያዊ ፓርቲ ኢ/ር ይልቃል ጌትነትን በድጋሜ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡
ትናንት ነሀሴ 16/2007 ዓ.ም ጉባኤውን የጀመረው ፓርቲው በዛሬው ሁለተኛና የማጠቃለያ ውሎው የፓርቲውን ሊቀመንበር፣ የብሄራዊ ምክር ቤት አባላት እንዲሁም የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አባላት ምርጫን አድርጓል፡፡
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በድጋሜ ለቀጣዩ ሦስት አመታት ፓርቲውን እንዲመሩ የተመረጡ ሲሆን፣ አምስት የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አባላትም በጉባኤው ተመርጠዋል፡፡ ጉባኤው የፓርቲውን የብሄራዊ ምክር ቤት አባላትንም መርጧል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ የ2007 ዓ.ም. 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ

የሰማያዊ ፓርቲ የ2007 ዓ.ም. 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ

ለፓርቲው ሊቀመንበርነት ቀደም ብለው ፓርቲውን ለሁለተኛ ዙር ለመምራት ራሳቸውን በእጩነት ያቀረቡት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ብቻ ሲሆኑ፣ ጉባኤው ተጨማሪ እጩዎችን ለመቀበል ባቀረበው ሀሳብ መሰረት ራሱን በእጩነት የሚያቀርብ ይኖራል ተብሎ ቢጠበቅም በእጩነት ራሱን ያቀረበ አልነበረም፡፡
በመሆኑም በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት ጉባኤው ተጨማሪ እጩዎችን በጥቆማ ለማወዳደር ተገድዷል፡፡ በዚህም ጉባኤው ስድስት እጩዎችን የጠቆመ ቢሆንም አምስቱ ‹‹አንወዳደርም›› በማለታቸው ከተጠቆሙት መካከል አቶ ዮናታን ተስፋዬ ብቻ ለመወዳደር ፍላጎታቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ፓርቲውን በህዝብ ግንኙነት ማገልገላቸው የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ለሊቀመንበርነት መወዳደር ችለዋል፡፡
ለሊቀመንበርነት እጩ ሆነው የቀረቡት ሁለቱ እጩዎች በጉባኤው ፊት በተመደበላቸው ጊዜ ገደብ ውስጥ ራሳቸውን ካስተዋወቁና የምረጡኝ ቅስቀሳ ካደረጉ በኋላ ወደ ድምጽ መስጠት መግባት ተችሏል፡፡ በተሰጠው ድምጽ መሰረትም ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲን ለቀጣይ ሦስት አመታት እንዲመሩ በአብላጫ ድምጽ ተመርጠዋል፤ በዚህም ኢ/ር ይልቃል ከተሰጠው ድምጽ 136 ድምጽ አግኝተው ሲያሸንፉ፣ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው 60 ድምጽ በማግኘት ፉክክር አድርገዋል፡፡

ይልቃል ጌትነት ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ

ይልቃል ጌትነት ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ

የምርጫ ውጤቱ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ንግግር ያደረጉት ተመራጩ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲ በሁለቱ ቀናት ጉባኤው ያነሳቸውን ችግሮች ለመፍታት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ውሎው ቀጣይ የፓርቲውን እንቅስቃሴ አስመልክቶም በጉባኤው አባላት አጠቃላይ ውይይት አድርጓል፡፡ በዚህም ፓርቲው ወደፊት ማደራጀት ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባው ጉባኤው አጽንኦት ሰጥቶበታል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው የብሄራዊ ምክር ቤትና የፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ያቀረቡት ሪፖርት ላይ ተወያይቶ ሪፖርቶቹ የፓርቲው ሰነድ ሆነው እንዲፀድቁ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ያካሄደውን ጉባኤ ዛሬ ነሐሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም ማጠናቀቁን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ለግንቦቱ ምርጫ 2007ዓ.ም. በዕጩነት እንዳይቀርቡ ተደረገ

  • “ምርጫ በህዝብ ፍላጎት ሳይሆን በሎተሪ ሆኗል” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
ይልቃል ጌትነት (የወቅቱ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

ይልቃል ጌትነት (የወቅቱ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

አዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 5 ለመጭው ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ሊቀርቡ የነበሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት “ከቀረቡት 17 ዕጩዎች መካከል በተጣለ ዕጣ ወድቀዋል” በመባላቸው ለመጭው ምርጫ በዕጩነት እንዳይቀርቡ መደረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል በዕጩነት በቀረቡበት ወረዳ 5 የምርጫ ጣቢያ ኢህአዴግ፣ የትግስቱ አንድነት፣ ቅንጅትን ጨምሮ ሌሎች ስድስት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ያለ ምንም ዕጣ አልፈዋል የተባለ ሲሆን “የሚያልፉት በዕጣ ነው” የተባሉት ሰማያዊን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መካከል ሰማያዊና ሌሎች አራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች “ዕጣ አልወጣላቸውም፡፡” ተብሏል፡፡

ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት “ሰማያዊ ህዝብ ውስጥ በሰፊው እየገባና እያንቀሳቀሰ ያለ ግንባር ቀደም ፓርቲ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ ያሉን ጨምሮ ዕጣ ውስጥ አይገቡም፡፡ ሰማያዊ ደግሞ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ከማያደርጉት ፓርቲዎች ጋር ዕጣ ውስጥ ገብቶ ወደቀ መባሉ ዴሞክራሲ ከጅምሩ ጀምሮ የህዝብ ድምጽ ሆኖ እያለ በእኛ አገር ሎተሪ ሆኗል ማለት ነው፡፡” ብለዋል

ሊቀመንበሩ አክለውም ‹‹ሂደቱ ምንም ይሁን ምን አንድን ፓርቲ ወይንም ተወካይን ህዝብ ነው መምረጥ ያለበት፡፡ ህዝብ የሚፈልገውና የሚመረጥ ፓርቲ ነው ለምርጫ መቅረብ ያለበት፡፡ አሁን ግን እየተባለ ያለው በአንድ በኩል ህዝብ የማይፈልገው ያለ ዕጣ ሲገባ፣ በሌላ በኩል ህዝብ የሚፈልገው ሰማያዊን የመሰለ ፓርቲ ዕጣ ውስጥ ገብቶ አላለፈም እየተባለ ነው፡፡ በአንድ በኩል ህዝብ የተማረረባቸው ያለ ቅድመ ሁኔታ ህዝብን እንደሚያንቀሳቅስ የሚታወቀው ሰማያዊ ደግሞ ህዝብ ስፈለገው አሊያም በጥንካሬው ሳይሆን በሎተሪ ወድቀሃል ተብሏል›› ሂደቱ የተሳሳተ ነው ማለታቸውን ጨምሮ ነገረ-ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

%d bloggers like this: