Daily Archives: March 24th, 2013

በማረሚያ ቤቱ አሰራር የፍትህ ሚኒስቴርም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደማያገባቸው ተገለፀ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) አመራር አባል የሆኑትና በፌደራሉ አቃቤ ህግ በ”ሽብርተኝነት” በሚል ተከሰው በቃሊቲ ቂሊንጦ ልዩ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ወህኒ ቤት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ናትናኤል መኮንን ከሐሙስ መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ምክንያቱ ባልተገለፀበት ሁኔታ ከወዳጅ ቤተሰብ እንዳይገናኝ ተከልክሏል፡፡ ይህንንም የአዲስ ሚዲያና የፍኖተ ነፃነት ዝግጅት ክፍል ከባለቤቱ ወይዘሮ ፍቅርተ ጋር በመሆን ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2005ዓ.ም. እዛው ቃሊቲ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በአካል በመሄድ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

አቶ ናትኤል መኮንን በምን የህግ አግባብ ለአንድ ወር ከወዳጅ ቤተሰቦቹ በተለይም ዘወትር ከሚጠይቁትና ስንቅ ከሚያመላልሱለት ባለቤቱና ልጁ እንዳይገናኝ እንደተደረገ የፍትህ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑትን አቶ ደሳለኝ ታረቀኝን የጠየቅናቸው ሲሆን እሳቸውም “ታራሚዎች ከቤተሰቦቻቸው እንዳይገናኙ የሚያዝ ህግ የለም በይበልጥ የማረሚያ ቤቱን ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው መኮንን መልስ ይስጠዋችሁ “ መርተውናል፡፡ ኮማንደር አስቻለው በበኩላቸው “በርግጥ እስረኞች የማረሚያ ቤቱን ስነምግባር ከጣሰ በማረሚያ ቤቱ አሰራር መሰረት ቅጣት ይኖራል፤ ነገር ግን የሚፈፀመው የማረሚያ ቤት ቅጣት ምክንያቱን ቤተሰቡና ታራሚው እንዲያውቁ ስለሚደረግ ማነጋገር ትችላላችሁ” የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

የወህኒ ቤቱ ጥበቃዎችና በዕለቱ ያሉ ኃላፊዎች ግን ስንቅ ይዘው ሊጠይቁ የሄዱትን ቤተሰብ መገናኘት እንደማይችሉና የያዙትን ምግብ ይዘው እንዲመለሱ ከማዘዝ ውጭ የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ “ማረሚያ ቤቱ የራሱ አሰራር ስላለው አይደለም የፍትህ ሚኒስቴርና ኮማንደር አስቻለው ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢመጡ አያገባቸውም” ሲሉ በወቅቱ ስማቸውን ማወቅ ያልተቻለ የዕለቱ የጥበቃ ኃለፊና ሁለት የጥበቃ አባላት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አፋር ክልል በተከሰተ ርሃብ ሰዎች እየሞቱ ነው

በአፋር ክልል ዞን አንድ “ኤሊዳኣልና ቢሩ “ በሚባሉ ወረዳዎች ከፍተኛ የሆነ ርሃብ መከሰቱ ተጠቆመ፡፡ በተለይ በሁለቱ ወረዳዎች ከመጋቢት 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ የረሃቡ ሁኔታ እጅግ ከመክፋቱ የተነሳ በአካባቢው ምግብና ውሃ በመጥፋቱ ለከብቶች መኖ  “አብዳ” የሚባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የሰጠውን ፉርሽካ ነዋሪዎች ጋግረው መብላት መጀመራቸውን ምንጮቻችን ከስፍራው ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ነዋሪዎች ባለ25 ሊትር ውሃ እስከ 200 ብር እየገዛ ከመሆኑም በተጨማሪ በተከሰተው ርሃብ እስካሁን 7 ሰዎች መሞታቸውንም ከስፍራው የዓይን እማኞች ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በስፍራው ቢገኝም ባልታወቀ ምክንያት እስካሁን ምንም ዓይነት የዕርዳታ ድጋፍ ባለማድረጉ ባካባቢው ነዋሪዎች ቅርሬታ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ አለመስጠቱ ተነግሯል፡፡ የፌደራሉ አደጋ መካላከል ዝግጁነት አስተባባሪ መስሪያ ቤትም እስካሁን ምላሽ አለመስጠቱ ተጠቁሟል፡፡

የዝግጅት ክፍሉም የአፋር ክልላዊ መንግስት በተጠቀሱ ወረዳዎች የተከሰተው ርሃብ ያደረሰውን ጉዳትና መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ጠይቀን የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መሐመድ “የደረሰውን ጉዳት ገና እያጣራን ነው፣ ልዑካንን ወደ አካባቢው ልከናል፤ አደጋ መከላከል መረጃውን ስላልሰጠን ባልተጣራ ጉዳይ ላይ መረጃ ልሰጥ አልችልም “ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

%d bloggers like this: